Saturday, July 13, 2024

የመንግሥት ዕርምጃዎች በመርህ ላይ ካልተመሠረቱ ቀውስ ይፈጥራሉ!

በፌዴራልም ሆነ በክልል ብሔራዊ መንግሥታት የሚወሰዱ ማናቸውም ዕርምጃዎች፣ በመርህ ላይ የተመሠረቱና የሕዝብን ፍላጎት ያማከሉ መሆን አለባቸው፡፡ መርህ በምክንያታዊነት መመራትን፣ ትክክለኛና ስህተትን መለየትን፣ ግልጽነትን፣ ሀቀኝነትን፣ ብስለትን፣ ፍትሐዊነትን፣ ሥነ ምግባርንና የመሳሰሉትን እሴቶች መላበስ ነው፡፡ መንግሥት አገር ሲያስተዳድር በተቻለ መጠን ውሳኔዎቹ በመርህ ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ የሕዝብን ጤና፣ ሰላም፣ ደኅንነትና ህልውና የሚጎዱ ማናቸውንም ዓይነት ድርጊቶች የመከላከል ኃላፊነት አለበት፡፡ ሕዝብም መንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ማገዝ ሲኖርበት፣ ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን ማጋለጥ ይጠበቅበታል፡፡ ሕገወጥ ከሚባሉ ድርጊቶች መካከል ሌብነት፣ የአደንዛዥ ዕፆች ዝውውር፣ ኮንትሮባንድ፣ የመሬት ወረራ፣ ንብረት ማውደም፣ ሰላም ማደፍረስ፣ የጦር መሣሪያ ዝውውርና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ሕገወጥነት በሕጋዊነት ላይ የበላይነት እንዳይዝ መንግሥትና ሕዝብ በአንድነት መቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡ መንግሥት በተለመደው አዝጋሚ አፈጻጸሙ ድንገት እየባነነ ቁረጠው ፍለጠው ዓይነት ዘመቻ ውስጥ ሲገባ፣ ሕዝብ ደግሞ ይህ ዓይነቱ አካሄድ በነበረበት እንዳይቀጥል መግታት ይኖርበታል፡፡ በተለይ በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ምሁራንና ልሂቃን በዚህ በኩል ጠንከር ያለ አቋም መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ግራና ቀኙን የማያማትሩ የመንግሥት መርህ አልባ ዕርምጃዎች የሚያስከትሉት ጦስ አገር ይጎዳልና፡፡

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሕገወጥ ቤቶችን ለማፍረስ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ ሕገወጥ ግንባታዎች በስፋት ይገኙባቸዋል የተባሉት ቦሌ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ጉለሌና የካ ክፍላተ ከተሞች መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ገንቢዎቹ በሁለት ሳምንታት ውስጥ አፍርሰው ንብረታቸውን እንዲያነሱ፣ በተባለው ጊዜ ውስጥ ተፈጻሚ ካልሆነ ደግሞ የከተማው አስተዳደር ከፀጥታ አካላት ጋር ሆኖ ዕርምጃ እንደሚወስድ ምክትል ከንቲባው አስጠንቅቀዋል፡፡ የመንግሥት አካላት በሕገወጥ ግንባታዎች ተሳታፊ ከሆኑም ንብረታቸው ከመፍረሱ በተጨማሪ፣ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑም አስታውቀዋል፡፡ የመንግሥት ተሿሚዎች ጉዳይ ሲነሳ የገነቡት ብቻ ሳይሆኑ፣ ግንባታ ሲካሄድ ዓይተው እንዳላዩ የሆኑም ኃላፊነትን ባለመወጣት በሕግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ እነሱ በሚያዙበት አካባቢ ሕገወጥነት ሲስፋፋ ዝም ያሉትን ማለፍ ልክ አይሆንም፡፡ የሹማምንቱ ዝምታ የዝርፊያ ጥቅም ተጋሪነት ተሳትፎ ስላለበት ጭምር፣ ጠንከር ያለ ቆፍጣና ሕጋዊ ዕርምጃ የግድ ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል በሕገወጥ ቤቶቹ ውስጥ በኑሮ ውድነት ምክንያት በአነስተኛ ኪራይ የሚኖሩ ምስኪኖች በብዛት ስለሚገኙ፣ ክረምት እየገባ ማፍረስ ሲጀመር የሚፈጠረው ጩኸትና ሰቆቃ ታስቦበታል ወይ? ይህንን አጋጣሚ አሰፍስፈው የሚጠብቁ ያደፈጡ ኃይሎች ጉዳይስ? ለማኅበረሰቡ በቂ ግንዛቤ ሳያስጨብጡና ሁኔታውን በተመለከተ ግልጽና የተብራራ መግለጫ ሳይኖር ወጥመድ የሚመስል ነገር ውስጥ ዘው ብሎ መግባት፣ እንደተለመደው ለብሔር ቁማርተኞች አመቺ ሁኔታ ፈጥሮ ያልታሰበ ትርምስና ግጭት ውስጥ ይገባል፡፡ በመሀል ደግሞ በርካታ ነገሮች ይበላሻሉ፡፡ በተለይ ክረምት እየገባ ስለሆነ ብርቱ ጥንቃቄ ያሻል፡፡

ምክትል ከንቲባው ከማኅበረሰቡ ጋር ንግግሩ መጀመሩንና ውይይቱም እንደሚቀጥል ቢናገሩም፣ አሁንም ከመንግሥት የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ደካማነትና በፍጥነት መረጃዎችን ለመልቀቅ የሚያስችል ቁመና ላይ ካለመገኘት አንፃር ውጤታማነቱ አጠራጣሪ ይመስላል፡፡ መሬት በሕገወጦች በወረራ ተይዞ በርካታ ሕገወጥ ቤቶች የተሠሩባቸውን አካባቢዎች በተመለከተ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ለመስጠት የተከናወነ አመርቂ ሥራ በሌለበት፣ ኅብረተሰቡም የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ተረድቶ ለአፀፋ ፕሮፓጋንዳ የማይጋለጥበት ሥልት ሳይዘረጋ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች አክሳሪ መሆናቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በሕገወጥ ግንባታዎቹ የተሳተፉ አካላት የጥንካሬያቸው መጠን ምን ያህል እንደሆነ ይታወቃል? በአጭር ጊዜ ውስጥስ አምስት ክፍላተ ከተሞችን ያለ ከልካይ እንዴት ሊወሩ ቻሉ? ባለሀብቶች፣ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት፣ ደላሎችና የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ኃይሎች ጭምር ተሳትፎ እንዳላቸው በግልጽ በከተማ አስተዳደሩ እየተነገረ ስለሆነ፣ የእነዚህን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚኖረው ጥንካሬ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? እነዚህ የተደራጁ ኃይሎች የሚነዙትን ፕሮፓጋንዳ ለማክሸፍ የተደረገው ዝግጅትስ ምን ያህል አሳማኝ ነው? ለእነዚህና ለሌሎች መሰል ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ሳይቻል ወደ ዕርምጃ ከተገባ፣ ሊፈጠር የሚችለውን ችግር ለመተንበይ ነቢይ መሆን አያስፈልግም፡፡ ግልጽ ነውና፡፡

 ለአገር ሰላምና ለሕዝብ ደኅንነት ሲባል ከሚወሰዱ ዕርምጃዎች በፊት፣ የዝግጀቱን ጥንካሬና በሕዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ሕገወጥ ድርጊቶችን በሕግ አደብ ማስገዛት ተገቢ ሲሆን፣ በገዛ ጉያ ውስጥ ያሉ ሕገወጦችን ታቅፎ ለመንቀሳቀስ መሞከር ትርፉ የእነሱ ሰለባ መሆን ነው፡፡ ከዚህም አልፎ የፖለቲካ ነጥብ በነፃ ለማስቆጠር ለሚባዝኑ ያልታሰበ ሲሳይ ማስገኘት ነው፡፡ ‹‹ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል›› እንደሚባለው፣ በቂ ዝግጅት ያልተደረገበትና ሕዝብን ከጎን ማሠለፍ ያልቻለ ዕርምጃ በኋላ ለቁጭት ይዳርጋል፡፡ ይህንን ጉዳይ አፅንኦት ሰጥተን የምናነሳው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ብዙ ጊዜ የመንግሥት ሹማምንት በቅንነት የሚነገሯቸውን ጠቃሚ ምክሮች አይሰሙም፡፡ የአድርባዮችና የአስመሳዮች መቀለጃ ስለሆኑ በተደጋጋሚ ለስህተቶች ይዳረጋሉ፡፡ የእነሱ ተደጋጋሚ ስህተቶች አገርን ለመከራ፣ ሕዝብን ደግሞ ለሰቆቃ እየዳረጉ ብዙዎች ተንገሽግሸዋል፡፡ የመንግሥት መዋቅሮች ከታች እስከ ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት ስለሌባቸው፣ የዘራፊዎችና የአቀባባዮች መቀለጃ ናቸው፡፡ ይህም በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ይህንንም ማጤን ተገቢ ይሆናል፡፡ መርህ አልባ መሆን ውጤቱ ጥፋት ነውና፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሚታወቅባቸው ባህሪያት መካከል ጨዋነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ከመልካም ሥነ ምግባር ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶችን መፀየፍ፣ ሕግ አክባሪነትና ሰላም ወዳድነት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይህንን የመሰለ የአኩሪ እሴቶች ባለቤት የሆነ ሕዝብ ይዞ የሕገወጦች መቀለጃ መሆን አይገባም፡፡ ሕገወጦች እንዳሻቸው እንዲፈነጩ ሜዳውን ካመቻቹ በኋላ፣ ሰዶ የማሳደድ ድርጊት ውስጥ እየተገባ ነው የሕዝባችን የሞራልና የሥነ ምግባር እሴቶች የሚናዱት፡፡ ይህንን ታላቅና አስተዋይ ሕዝብ የሚመራ መንግሥት መጀመርያ ከሕገወጦች፣ ከአድርባዮችና ከአስመሳዮች፣ እንዲሁም እንዳሻን እንፈንጭ ከሚሉ ዋልጌዎች ራሱን ማፅዳት አለበት፡፡ በመቀጠል ደግሞ በየትኛውም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ማስፈን የግድ ይሆናል፡፡ የሕዝብ ድጋፍና አመኔታ የሚገኘው በዚህ ቁመና ላይ መገኘት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ በሕገወጦች ላይ የበላይነት መያዝ የሚቻለው ነገሮች ከተበላሹና ዋጋ ካስከፈሉ በኋላ ሳይሆን ቀደም ብሎ ተቋማትን በማጠናከር፣ እንዲሁም ብቃታቸውና ሥነ ምግባራቸው ለተመሰከረላቸው ብርቱዎች ኃላፊነት በመስጠት ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ሳይቻል ሲቀር ግን ውጤቱ ቀውስ ነው፡፡ ዕርምጃው የሚወሰደው በክረምት ወቅት መሆኑ ደግሞ ጩኸቱን እያባባሰና የፕሮፓጋንዳ ዙር እያከረረ ቀውሱን ያባብሰዋል፡፡ በሕገወጥነት ላይ የበላይ መሆን የሚቻለው በመርህ መመራት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው የመንግሥት ዕርምጃዎች በመርህ ላይ ካልተመሠረቱ ቀውስ ይፈጠራል የሚባለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...

የታመቀ ስሜት!

የዛሬ ጉዞ ከመርካቶ በዮሐንስ ወደ አዲሱ ገበያ ነው፡፡ ታክሲ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ተፃራሪ ላለመሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ድብልቅልቅ ስሜት የሚፈጥሩ በርካታ ሁነቶች ማጋጠማቸው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ በዚህ ወቅት ከተለያዩ ፍላጎቶችና ዓላማዎች ጋር የተሸራረቡ ሥጋት ፈጣሪ ችግሮች በብዛት እየተስተዋሉ ነው፡፡...

መንግሥት ቃሉና ተግባሩ ይመጣጠን!

‹‹ሁሉንም ሰው በአንዴ ለማስደሰት ከፈለግህ አይስክሬም ነጋዴ ሁን›› የሚል የተለምዶ አባባል ይታወቃል፡፡ በፖለቲካው መስክ በተለይ ሥልጣነ መንበሩን የጨበጠ ኃይል ለሚያስተዳድረው ሕዝብ ባለበት ኃላፊነት፣ በተቻለ...

ልዩነትን ይዞ ለዘለቄታዊ ሰላምና ጥቅም መተባበር አያቅትም!

መሰንበቻውን በአውሮፓ ታላላቅ ቡድኖች ተጫውተው ያለፉ ዝነኛ የአፍሪካ እግር ኳስ ከዋክብት በኢትዮጵያ ቆይታ አድርገው ነበር፡፡ ዝነኞቹ ንዋንኮ ካኑ፣ ዳንኤል አሞካቺ፣ ታሪቡ ዌስት፣ ካማራና መሰሎቻቸው...