Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ለግል ባንኮች የፈቀደውን 100 ሚሊዮን ዶላር ድልድል አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፈቀደውን 100 ሚሊዮን ዶላር ዝግጁ ማድረጉንና እያንዳንዱ ባንክ የሚደርሰውን የውጭ ምንዛሪ እንዳስታወቃቸው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ያስታወቀው ረዕቡ ግንቦት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ለሁሉም የግል ባንኮች በላከው ደብዳቤ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ብሔራዊ ባንክ 100 ሚሊዮን ዶላሩን ቀደም ብሎ ባስቀመጠው መሥፈርት መሠረት እያንዳንዱ የግል ባንክ በሚደርሰው የውጭ ምንዛሪ ተቀናሽ የሚደረግበትን ሒሳብ በማሳወቅ፣ የተፈቀደላቸውን የውጭ ምንዛሪ እንዲወስዱ ነግሯቸዋል፡፡

በተለያዩ ባንኮች ተመዝግበው የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች፣ ከብሔራዊ ባንክ መጠባበቂያ ላይ ወጪ የማረጋጋት ሥራ እንዲከናወን ከተመደበው ዶላር ውስጥ፣ የተመደበላቸውን መጠን ጠቅሶ አስታውቋቸዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የተመደበውን የውጭ ምንዛሪ ባንኮቹ ለደንበኞቻቸው የሚያደርጉትን ድልድል በተመለከተ በመመርያ ቁጥር FXD/57/2018 አንቀጽ 6.1.1 መሠረት በምዝገባ ወረፋ ቅደም ተከተል ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎች ብቻ እንዲሆን፣ ድልድሉ ለየባንኮቹ ከተፈቀደው ጠቅላላ የውጭ ምንዛሪ ውስጥ ለአንድ ፕሮፎርማ ከአምስት በመቶ ያልበለጠ መሆን ያለበት መሆኑን፣ እንዲሁም ለአንድ ደንበኛ ከሁለት ፕሮፎርማ በላይ የማይፈቀድ እንደሆነ ለባንኮቹ አስታውቋል፡፡

‹‹ስለሆነም የውጭ ምንዛሪውን የምናስተላልፍበትንና ተመጣጣኝ ብር ተቀናሽ የምናደርግበት ሒሳብ ስታስታውቁን፣ የውጭ ምንዛሪውን የምናስተላልፍ መሆኑን እንገልጻለን፤›› ያለው ብሔራዊ ባንክ፣ ከዚህ በተጨማሪ ሁሉም ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ድልድል ያደረጉበትን ዝርዝር ሪፖርት ለብሔራዊ ባንክ እንዲያቀርቡም አሳስቧቸዋል፡፡

በብሔራዊ ባንክ የተፈቀደውን የውጭ ምንዛሪ ባንኮቹ የምዝገባ ቅደም ተከተል ጠብቀው፣ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ዘርፎች እንዲሰጡ አሳስቧቸዋል፡፡

ከምንጮች መረዳት እንደተቻለው ከ12 እስከ 15 ሚሊዮን ዶላር ከደረሳቸው ባንኮች መካከል ዳሸን ባንክና ብርሃን ባንክ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሌሎቹ ባንኮች በአብዛኛው ከአምስት እስከ ሰባት ሚሊዮን ዶላር እንደደረሳቸው፣ አንድ ባንክ ደግሞ 1.6 ሚሊዮን ዶላር ማግኝቱን ከምንጮች የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች