በኢትዮጵያ ኅብረተሰቡ የሚያዘወትረው የተለያየ ስፖርት ቢኖርም ጠንካራ መዋቅራዊ መሠረት ስለሌለው ውጤታማ ሲሆን አይታይም፡፡ በዚህ ጉዳይ የቀረቡ የተለያዩ የምርምርና የጥናታዊ ውጤቶች እንደሚያመላክቱት ከሆነ፣ ተቋማቱ ሲመሠረቱ ይዘውት የሚነሱት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ስትራቴጂዎች መነሻና መድረሻቸው የማይታወቅ መርሕ አልባ መሆኑ ነው፡፡ ችግሩ በታሪክ አጋጣሚ አገሪቱን የማስተዳደር ዕድል ከነበራቸው መንግሥታዊ መዋቅሮች እንደሚጀምር፣ ስፖርቱ የሚመራበትን ሥርዓት ማለትም ተጠያቂነትና ግልጽነት ያለበት ወጥ የሆነ መዋቅር ክፍተት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል ተብሎም ይታመናል፡፡ ሐሳቡን ከሚጋሩት መካከል የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ሆነው አቶ አድማሱ ሳጂ ይጠቀሳሉ፡፡
ምሁሩ በስፖርት ሳይንስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ የሠሩ ከመሆኑም በላይ ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በአትሌቲክስ አሠልጣኝነት ፈቃድ እንዲሁም በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) ኢትዮጵያ ለምትገኝበት ቀጣና የእንግሊዝኛ ተናጋሪ አገሮች የአሠልጣኞች አሠልጣኝ (ኢንስትራክተር) እውቅና አግኝተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከ2001 ዓ.ም እስከ ሪዮ ኦሊምፒክ የመካከለኛና የረዥም ርቀት ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሆነው ከማገልገላቸው ባሻገር በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ ከስፖርት መዋቅራዊ ይዘት ጋር ተያይዞ በተለይ በፖሊሲ ደረጃ ካስቀመጣቸው አቅጣጫዎች በመነሳት ክፍተት ነው ብለው የሚያምኑት፣ የአንድ አገር ስፖርት የሚመራበት የራሱ አካሄድ እንዳለውና ኢትዮጵያም ይህንኑ ተከትላ ተቋማቱን ለመመሥረት ዕቅድ ነድፋ ስትንቀሳቀስ መቆየቷን ይናገራሉ፡፡
አንዳንዶቹ የስፖርት ተቋማት ምሥረታ ከ1950ዎቹ እንደሚጀምር፣ ይሁንና ተቋማቱ የተቋቋሙለትን ዕቅድ ከማሳካት አኳያ ከአዎንታዊ ይልቅ አሉታዊ ጎናቸው እያመዘነ ስፖርቱ ውጤታማ ሊሆን እንዳልቻለ ያምናሉ፡፡ ምክንያቱም አንድ ተቋም ሲመራ የራሱ የሆነ አደረጃጀትና የራሱ የሆነ የሥራ ዝርዝር እንዲሁም ፈጻሚና አስፈጻሚ አካላት ይኖሩታል፣ በዚህ መነሻነት የኢትዮጵያ ስፖርት መዋቅራዊ ይዘት ከመነሻው አሁን እስካለንበት ጉልህ ክፍተቶች በተጨባጭ የሚስተዋሉበት መሆኑ አቶ አድማሱ ሳጂ ይናገራሉ፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡– በኢትዮጵያ ከስፖርቱ አደረጃጀት ጋር ተያይዞ መሠረታዊ ሆነው ከሚነሱ ተግዳሮቶች፣ መዋቅራዊ ይዘታቸው አንዱና ዋናው እንደሆነ ይነገራል፡፡ እንደ ስፖርት ሳይንስ ምሁርነትዎ የአገሪቱን የስፖርት መዋቅርና አደረጃጀቱን ጭምር እንዴት ይገልጹታል?
አቶ አድማሱ፡– ስፖርቱን በሚመለከት አገሪቱ የምትመራበት ሥርዓት ለመኖሩ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም አገር ተቋም ሲመሠረት ተቋሙ የሚመራበት የራሱ የሆነ አደረጃጀትና ዝርዝር ፈጻሚና አስፈጻሚ አካላት ይኖሩታል፡፡ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያን ስፖርት አሁን ላይ ሆነን ስንመለከተው በተለይ ከአደረጃጀት ጋር ያለው ክፍተት በጉልህ የሚታይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከመነሻው የተረጋጋ የስፖርት መዋቅር የለንም፣ መዋቅሩና አደረጃጀቱ አንዳንድ ጊዜ ከባህል ሌላ ጊዜ ደግሞ ከቱሪዝምና ሲያሻው ስፖርት ኮሚሽን ሲመላለስ የኖረ ዘርፍ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሥር እንዲሆን ተደርጎ፣ አስፈጻሚውን ስንመለከት ደግሞ ሚኒስቴር ዴኤታ፣ ኮሚሽነርና ምክትል ኮሚሽነር በሚል እንዲዋቀር ተደርጓል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ከየትኛውም አገር ተሞክሮ እንመልከት ብንል እንኳን ስፖርት ራሱን ችሎ ትልቅ ተቋም ሆኗል፡፡ በብዙ አገሮች ያለው ተሞክሮ የሚሳየው ስፖርቱ ሲዋቀር፣ የሚያሳትፈው የማኅበረሰብ አባላትና የሚያስገኘው ጠቀሜታ ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውጤታማ ነው ብለን የምንወስደውን አትሌቲክስን ብንመለከት፣ ምን ያህል የውጪ ምንዛሪ እያስገኘ ነው? እግር ኳሳችንና ሌሎች ስፖርቶቻችን ተቋማዊ አደረጃጀታቸው ተፈትሾ ውጤታማ ቢሆኑ የሚለውን ብንወስድ ያለውን ጠቀሜታ ለመገመት አያዳግትም፡፡ ስለሆነም መሆን ካለበት ስፖርቱ በሚኒስቴር ደረጃ እንኳን ባይሆን ስያሜውን ሳይለቅ ከሚቀርበው ተቋም ጋር መዋቀር ይኖርበታል፡፡ ስፖርቱ በአሁኑ ወቅት በባህልና ቱሪዝም ሥር እንዲሆን ነው የተደረገው፡፡ ይህ እንደ ትልቅ ክፍተት ተወስዶ መስተካከል ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱም ስፖርቱ የአገሪቱ ተረካቢ ተብሎ የሚወሰደውን አምራች ኃይል ያቀፈ ነው፣ ቀደም ሲል የሚያሳትፈው የማኅበረሰብ ክፍል የሚለውን ማሳያ የተጠቀምኩት ይህን ከግምት በማስገባት ነው፡፡ በአገሪቱ 45 በመቶ በላይ ወጣት ነው፣ ታዲያ እንዴት ነው ይህን እውነታ ወደ ጎን አድርገን የምንመለከተው? ከዚህም በላይ በአገሪቱ ከሚገኙት 45 ዩኒቨርሲቲዎች ወደ 27 የሚጠጉት በስፖርት ሳይንስ ሙያተኞችን ሁለተኛ ዲግሪና ዶክትሬት ጭምር በማስተማር ላይ ናቸው፡፡ ባለሙያዎች የዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ ከሆኑ ወርደው ማኅበረሰቡን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለያየ የስፖርት ዘርፍ በርካታ ባለሙያዎች እየወጡ ነው፣ ከዚህም በላይ ስፖርቱ ራሱ ከጤና አኳያ ከሕክምና ተቋማት ባልተናነሰ ተመራጭ እየሆነ ነው፡፡ የዚህን ዘርፍ መለያ ስያሜውን ከላይ ማጥፋት ፋይዳው አይታየኝም፡፡
ሪፖርተር፡– ከላይ ስያሜውን ማጣቱ ከውጤታማነቱ ጋር የሚያገናኘው ምንድነው? ከዚህ ቀደም ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ተብሎ ምን የተለየ ነገር ነበረው?
አቶ አድማሱ፡– ብዙ ልዩነት አለው፣ ከብዙ በጥቂቱ በአስፈጻሚ አካላት ምደባ ላይ ራሱን የቻለ ልዩነት አለው፡፡ ወጥ የሆነ ስያሜና ተለዋዋጭ ስያሜ ሲሆን ኅብረተሰቡ ውስጥ የሚኖረው ተቀባይነት በራሱ ሠፊ ልዩነት ይፈጥራል፡፡ በአደረጃጀት ደረጃ ወስደን ስንመለከተው፣ አደረጃጀት ሥራን፣ አቅጣጫንና ግብረ መልሱን ጭምር የሚያሳይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– የአስፈጻሚ አካላት ጉዳይን በተመለከተ፣ በኢትዮጵያ ስፖርት አደረጃጀት በዋናነት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ካልሆነ፣ የሙያ ብቃትና ክህሎት ብዙም ትኩረት እንደማይሰጠው ይነገራል፡፡ በአንዳንድ ወገኖች የችግሩ ቁልፍ ከዚህ እንደሚጀምር ሲናገሩ ይደመጣል፣ እንዴት ያዩታል?
አቶ አድማሱ፡– ቀደም ሲል የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ሙያተኞችን እያፈሩ ነው ስል አንዱና ዋናው መነሻዬ ይህ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የስፖርት ተቋማት አስፈጻሚዎች የሚመደቡት ባላቸው የፖለቲካ ቁርጠኝነት ነው፡፡ በዚህ ዘመን የስፖርት አመራር ራሱን የቻለ ክህሎትና እሳቤ እንዲሁም ባህሪ እንዲኖረው ሆኗል፡፡ በዚህ ሒደት ሰዎች ሳይንሱን ደረጃውን በጠበቀ አኳኋን ሊማሩትና ሊታጠቁት የሚገባ ክህሎት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ከላይ እስከታች የተቀመጡት አካላት ሌሎች ተቋማትን የመምራት አቅም ሊኖራቸው ይችል ይሆናል በስፖርቱ ግን አይመስለኝም፡፡ ቀደም ሲል ለመናገር እንደሞከርኩት ዩኒቨርሲቲዎች በፒኤችዲ ደረጃ ሙያተኞችን እያወጡ ነው፣ ሙያተኞቹ በፖለቲካው ያላቸው ቁርጠኝነትም ቢሆን ያን ያህል ሩቅ ያልሆኑ ናቸው፡፡ በመሆኑም ለእነዚህ ሰዎች ተርጓሚና አስተርጓሚ ሳያስፈልግ ሥራውን አውርደው እንዲሠሩና እንዲያሠሩ ኃላፊነት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡– ችግሩ በዋናነት መንግሥት ለስፖርቱ በጀት ከመመደብ ባለፈ የሚሰጠው ትኩረት ያነሰ እንደሆነና በዚህ ረገድ አማካሪዎች እንደሌሉት ጭምር የሚናገሩ አሉ፣ በእርሶ አስተያየቱ እንዴት ይገለጻል?
አቶ አድማሱ፡– ችላ ብሎታል ከሚለው የተሻለው በዘርፉ መንግሥትን የሚያማክሩ ትክክለኛ ሰዎች የሉትም። በተለይ አማካሪ በሚለው እስማማለሁ፡፡ ምክንያቱም ባለው የመንግሥት መዋቅር ከላይ እስከታች ሁሉንም ሙያና ሴክተር ሙሉ እውቀት ባላቸው ሰዎች እየተመራ ነው የሚል እምነት የለኝም፡፡ እነዚህ ክፍተቶች የሚሞሉበት አካሄድ የሚመስለኝ አማካሪዎች በየተቋማቱ እንዲኖሩ ነው የሚደረገው፡፡ ተጨባጭ ማስረጃ ማቅረብ ባልችልም ስፖርቱ ላይ መንግሥትን የሚያማክር ትክክለኛ ሙያተኛ አለው ብዬ ለመናገር ይከብደኛል፡፡ የመዋቅር ክፍተቱም የሚጀምረው ከዚህ እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ ከመዋቅር አኳያ ይህ ዘርፍ ደምቆና ጎልቶ እንዳይታይ የሆነው ለዚህ ነው ብሎ መውሰድ የሚቻል ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡– መንግሥት ከሌሎች የልማት ዘርፎች በተለየም ባይሆን ከፍተኛ በጀት ስፖርቱ ላይ እንደሚያውል ይታመናል፡፡ እርሶን የመሳሰሉ የስፖርት ምሁራን ለመንግሥት ሙያዊ ምክር መስጠት የሙያ ግዴታ ብቻም ሳይሆን የዜግነት ግዴታም ነው ብሎ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ምን ይላሉ?
አቶ አድማሱ፡– ሙሉ በሙሉ የምቀበለው ብቻ ሳይሆን የማምንበትም ነው፡፡ መንግሥት ስፖርቱን ጨምሮ ከአገሪቱ የኅብረተሰብ ክፍል በተለያየ አግባብ የሚያገኘውን ሀብት እንደሚመድብ አውቃለሁ፡፡ ሀብቱ እንዴትና ለምን አገልግሎት ዋለ የሚለውን የማያውቅ ከሆነና የሀብት አጠቃቀሙን የሚያመላክት ሥርዓት ካልፈጠረ በጀት መመደብ ብቻውን የጎንዮሽ ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ክለቦች የሀብት አጠቃቀም ብንመለከት በቂ ነው፡፡ ክለቦቻችን ለአንድ ተጨዋች የሚከፍሉት ወርሃዊ ክፍያ ከገቢያቸው አንፃር ሲታይ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ይህ ሀብት ከላይ ከመንግሥት ጀምሮ በስፖርቱ የመዋቅርና የአደረጃጀት ክፍተት እንዳለ በግልጽ የሚያመላክት ይመስለኛል፡፡ ለዚህ የሌሎች አገሮች አደረጃጀት መመልከት ይኖርብናል ከተባለ በእግር ኳሱም ሆነ በሌሎች ስፖርቶች ውጤታማ የሆነችው እንግሊዝ የስፖርቱ መዋቅር ወጥ ሆኖ፣ አሰያየሙም ስፖርትና ቅርስ ሚኒስቴር ነው፡፡ ሚኒስትሩ ምን ያህል እየሠራ ለመሆኑ ሁሉም ስፖርት ከፖለቲካዊና ማኅበራዊ ፋይዳው በላይ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አይቶ መናገር ይቻላል፡፡ በዓለም አሉ የሚባሉ ባለሀብቶችን ቀልብ ገዝቶ ጭስ አልባ አንዱስትሪ ብቻ ሳይሆን የሀብት ምንጭ እየሆነ ይገኛል፡፡ እኛ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አውርደን በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሥር እንዲሆን ስንወስን ጥናት ተደርጎ ነወይ? የሚለው በራሱ አነጋጋሪ ይመስለኛል፡፡ አማካሪዎች ካሉ ለዚህ ማብራሪያ ያስፈልገዋል፡፡ ከአፍሪካ ጎረቤት ኬንያን ስፖርትና ወጣቶች ሚኒስቴር ተብሎ ይጠራል፣ ናይጄሪያ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ነው፣ ወደ ደቡብ አፍሪካ ስንሄድ የስፖርትና ትምህርት ሚኒስቴር ነው፣ ከዚህ አኳያ ወደ አገራችን ተሞክሮ ስንመጣ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው የምንመለከተው፡፡ መንግሥት በሚከተለው አቅጣጫ ቅራኔ ባይኖረኝም ስፖርቱ ላይ ግን አካሄዱ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም የአገሪቱ ብዙውን ዜጋ የሚያሳትፍ ቢኖር ስፖርት ሆኖ ሳለ ዘርፉ ለምን ችላ እየተባለ ግልጽ አልሆነልኝም፡፡
ሪፖርተር፡– መንግሥት በስፖርቱ የፖሊሲ ክለሳ እንዲያደርግ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ይታወቃል፣ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አልተጠየቁም?
አቶ አድማሱ፡– እኔ ከምሠራበት ተቋም ጭምር የተውጣጡ ምሁራን በስፖርት አደረጃጀትና ፖሊሲዎች ላይ ጥናት የሚያደርጉ እንዳሉ አውቃለሁ፣ የጥናት ቡድኑ አባል ግን አይደለሁም፡፡ ወደፊት የምጋበዝ ከሆነ ድርሻዬው ለመወጣት አላቅማማም፡፡ ምክንያቱም ለአገሪቱ የስፖርት ዕድገት ውዴታ ሳይሆን ግዴታችንም ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡– የስፖርት ሳይንስ ባለሙያ ከመሆንዎ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ነዎት፣ በአሠልጣኝነትም የረዥም ዓመታት ልምድ ካላቸው ሙያተኞች አንዱ መሆንዎ ይታወቃል፡፡ አትሌቲክሱን በሚመለከት ያለዎት አስተያየት ምንድነው?
አቶ አድማሱ፡– ብዙ ተሳታፊዎችን በማሳተፍ ደረጃ እግር ኳስ የበለጠ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ እያስመዘገበ ካለው ውጤት እንዲሁም ከሚያበረክተው የአገር ገጽታ ግንባታና የውጪ ሀብት በማስገባት አኳያ አትሌቲክሱ ውጤታማ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በዚህ የተነሳ ኅብረተሰባችን ለአትሌቲክሱ ትልቅ ትኩረት መስጠት መጀመሩ ውጤቱ ሲቀንስ የዛኑ ያህል ወቀሳና ትችቶች ይኖራሉ፣ ተገቢም ነው ብዬ እወስዳለሁ፡፡ በርካታ ታዳጊ ወጣቶች ከምንጊዜውም በላይ እየመጡ ነው፣ ይሁንና አንዳንድ ጊዜ የውጤት መውጣትና መውረድ ስለሚኖርና ባህሪውም በመሆኑ ስፖርቱ ካለው አገራዊ ፋይዳና ጠቀሜታ አኳያ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሁን ካለው በተሻለ መሥራት እንደሚጠበቅበት አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም አትሌቲክስ ለኢትዮጵያ ቁልፍ ስፖርት ነውና፣ እንደ ስፖርት ባለሙያ ሌሎችም ስፖርቶች የአትሌቲክሱን ፈለግ እንዲከተሉ ሥርዓቶችን ማበጀትና ለተግባራዊነቱም መትጋት ያስፈልጋል የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡