በውብሸት ሙላት
በቅርቡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስለፊስካል ፌዴራሊዝም ውይይት አድርጓል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትንሽ ጠንከር ያለ ውይይት ከሚያደርግባቸው ጉዳዮች አንዱ ይኼው ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ድጎማና የጋራ ገቢ ክፍፍልን በሚመለከት፡፡ የጋራ ገቢ ክፍፍልን በሚመለከት ከተደረጉት ውሳኔዎች ይልቅ ስለድጎማ በርከት ያሉ ተለዋዋጭ ውሳኔዎች ተላልፈዋል፡፡ እንደዚያም ሆኖ፣ በተለይም ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ በመነሳት፣ ጠንካራ ክርክር ነበር ማለት አይቻልም፡፡ በየክልሎቹ እየተስተዋለ የመጣው የመካረር አዝማሚያ ያለው ብሔርተኝነት በጨመረ ቁጥር ወጥና ተቀባይነት ያለው አሠራር ካልተዘረጋለት ወደፊት የጭቅጭቅ መነሻ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ይህ ጽሑፍ አትኩሮቱም በፊስካል ፌዴራሊዝምና የተወሰኑ ጭብጦችን በመለየት የሚኖረውን አንድምታ መጠቋቆም ነው፡፡
የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን የተለያዩ ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚያስፈልጋቸውን ገቢ ከነምንጮቹ በመዘርዘር ሁሉም የየራሱን ድርሻ እንዲወጣ፣ ከዚህ የተረፈውን ደግሞ ከፌዴራል ወደ ክልሎች በጀት በማስተላለፍ ሊሸፈን እንደሚችል ከሕገ መንግሥቱ የተለያዩ አንቀጾች መረዳት ይቻላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የክልሎችን ሥልጣናቸውን፣ ተግባራቸውንና ኃላፊነታቸውን ዘርዝሯል የፌዴራሉንም ጭምር፡፡ ፌዴራል መንግሥቱም ይሁን ክልሎች የድርሻቸው የሆኑትን ኃላፊነቶች ለመወጣት ገንዘብ የግድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እንደየሥራቸው መጠን ተመጣጣኝ በማድረግ በሕገ መንግሥቱ ማከፋፈል አስፈላጊ ነው፡፡ የእኛም ሕገ መንግሥት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ለየብቻቸውና በጋራ የሚሰበስቧቸውና የሚጠቀሙባቸው የገቢ ምንጮችን ለይቶ አስቀምጧል፡፡ አሁን ላይ ያልተገለጸ ወይም ያልታወቀ ግብር ካለ ለክልል፣ ወይም ለፌዴራል ወይም ለጋራ የሚሆንበትን አሠራር በአንቀጽ 99 ላይ ደንብ አብጅቶለታል፡፡
የፌዴራላዊ አወቃቀር አንዱ በጎነቱ በሀብት ከተሻለው ክልል ቆንጥሮ ለሌላው መስጠት የሚያስችል የታወቀ ሥርዓት መጠቀም መቻሉ ነው፡፡ በየትም አገር ቢሆን ሁሉም ክልሎችም ይሁኑ አስተዳደራዊ መዋቅሮች እኩል ሀብት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ በዕድገትም አቻ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ በሕዝብ ብዛትና በቆዳ ስፋትም እንዲሁ፡፡ የተሻለ የተፈጥሮም ይሁን ሌላ ሀብት ኖሮት፣ የሕዝብ ቁጥሩ ዝቅተኛ የሆነ፣ ብዙ የመሠረተ ልማት ግንባታ ከሌለበት ወጪው ዝቅተኛ ሊሆን ስለሚችል የተሻለ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ ከላይ ያሉት ሲገለበጡ ደግሞ ችግሩ ይበረክታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በክልሎች መካከል የገቢ አለመጣጣምን ያስከትላል፡፡ የገቢ አለመጣጣም በፌዴራልና በክልሎችም መካከል ሊከሰት ይችላል፡፡ የፌዴራሉ መንግሥት ብዙ የገቢ ምንጭ ኖሮት ክልሎች ግን ብዙ ሥራ ሲኖራቸው፣ ወይም የመከሰት ዕድሉ ጠባብ ቢሆንም ክልሎች ብዙ ገቢ፣ ፌዴራሉ ደግሞ ብዙ ሥራ ሲኖረው ሊመጣ ይችላል፡፡
ከላይ በተገለጹት ሁለት ሁኔታዎች አማካይነት የገቢ አለመጣጣም ሲኖር የገንዘብ ማዟዟር አስፈላጊ ነው፡፡ ገንዘብ ከሚዟዟርባቸው ሥልቶች አንዱ ድጎማ ነው፡፡ በድጎማ ሥርዓት ተቀባዮቹ ቢደሰቱም ሀብታም የሆኑት ክልሎች ገቢያቸው ስለሚቀንስባቸው መከፋታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ስለሆነም ድጎማው ሲያንስ ያነሰባቸው ክልሎች ከፌዴሬሽኑ ተጠቃሚ አልሆንም በማለት ሊያኮርፉ ይችላሉ፡፡ ድጎማ አድራጊዎቹም ባንደጉምና ባይቀነስብን የተሻለ ልማትና ብልፅግና ማምጣት እንችል ነበር ማለታቸው ስለማይቀር እነሱም በተራቸው ሊቀየሙ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም አነስተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸውም ይሁኑ የተሻለ፣ ቅያሜያቸው ሲበዛና እየቀጠለ የሚሄድ ከሆነ የመገንጠልና ነፃ አገር የመመሥረት አማራጭ ሊወስዱ ይችላሉ፡፡
ሌላው ዋና ዋና የገቢ ምንጮችን ለፌዴራል መንግሥት መስጠቱ አንዱ የቅሬታ ምንጭ ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥቱ ከሰበሰበው ውስጥ የፈለገውን መጠን ያህል ለክልሎች ይደጉማል፡፡ የፈለገውን መጠን የሚባለውም፣ የፌዴራሉ መንግሥት ለራሱ ተለይተው በተሰጡት የገቢ ምንጮች አማካይነት ከሰበሰበው ውስጥ ምን ያህል ፐርሰንቱን ለክልሎች በድጎማ መልክ መስጠት እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ ላይም ይሁን በሌሎች ሕጎች ስላልተደነገገ ነው፡፡
የፌደሬሽን ምክር ቤትም ቢሆን ድጎማው እንዴት መከፋፈል እንዳለበት ከመወሰን ባለፈ ይኼንን የመወሰን ሥልጣን አለው ማለት አይቻልም፡፡ የፌዴራሉና የክልሎች የጋራ የሆኑትን ገቢዎች በተመለከተ የፌዴራሉ ድርሻ ምን ያህል ይሁን የሚለውን የመወሰን ሥልጣን አለው፡፡ አንዱ የቅሬታ መነሻ ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ ጣጣው የሚበዛው በፌዴራልና በክልሎች የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢያሸንፉና የፌዴራሉ መንግሥት ለድጎማ የሚሆን የይስሙላ ገንዘብ ቢመድብ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያገኛትን ብቻ ከማከፋፈል ውጭ ሥልጣን ከሌለው ክልሎችን አደጋ ላይ መጣሉ አይቀርም፡፡ ስለድጎማ ካነሳን አይቀር ጥቂት ነጥቦችን እንጨምር፡፡ የድጎማ ቀመር ሲዘጋጅ መነሻ ከሚደረጉ መርሆች የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡፡
የመጀመርያው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በመንግሥት ገንዘብ ከሚካሄዱት ማኅበራዊ አገልግሎቶች እኩል የመጠቀም መብት ነው፡፡ የመርሁ ምንጭ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 41(3) ላይ የተገለጸው ነው፡፡ ሌላው መንግሥት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው እንዲሻሻልና እኩል ዕድል እንዲኖረው ሀብትን በፍትሐዊነት የማከፋፈል ግዴታ እንዳለበት በአንቀጽ 89(2) የተቀመጠው መንግሥታዊ ግዴታ ነው፡፡ ሦስተኛው መርህ፣ በዚሁ አንቀጽ ላይ የተገለጸው በዕድገት ወደ ኋላ ለቀሩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩ ድጋፍ የማድረግ የፌዴራል መንግሥት ግዴታ ነው፡፡ አራተኛው ደግሞ የፌዴራል መንግሥትም የራሱን፣ ክልልም የራሱን ወጪ የመሸፈን መርህ ሲሆን፣ ምንጩም አንቀጽ 94(1) ነው፡፡ የመጨረሻው፣ የተመጣጠነ ዕድገትን በማያፋልስ ሁኔታ ለክልሎች ድጋፍ የማድረግ መርህ የሚለው በአንቀጽ 94(2) ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ነው፡፡ ከላይ የተገለጹት ሕገ መንግሥታዊ መርሆችን ለማጣጣም ከፍተኛ ብልኃት ይጠይቃል፡፡ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ፣ የትም ክልል ይኑር የት፣ ብሔሩ ምንም ይሁን ምን፣ ከመንግሥታዊ አገልግሎት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ፍትሐዊ ነው፡፡ በአንድነት እስከኖርን ድረስ ያለንን በጋራ መቋደስ ተገቢ ነው፡፡ ይህንን ከጋብቻ ጋር ማነፃፀር ይቻላል፡፡ ባልና ሚስት ከጋብቻ በፊትም ይሁን ከጋብቻ በኋላ ያፈሯቸውንም የሚያፈሯቸውንም በትዳር ውስጥ እስካሉ ድረስ በጋራ መጠቀማቸው አይቀርም፡፡ እንበልና ከጋብቻ በፊት ባል ወይም ሚስት ንብረት ነበራቸው፡፡ መቼም ቢሆን በትዳር አብረው እያሉ ባልም የብቻው ሚስትም የብቻቸው ይጠቀሙበታል ተብሎ አይታሰብም፤ ሚስት እየበላች ባል ጾም እደር፣ ባል እየበላ ሚስት ጾም እደሪ አይባልም፡፡ እንደዚሁ ሁሉ አብረን በአንድ አገር እየኖርን አንዱ ብሔር ወይም አካባቢ መንገዱ ተስፋፍቶ፣ መብራት፣ ውኃ፣ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታልና ስልክ ወዘተ. እያለ ሌላውን ባዶ ማስቀረት ድረስ ፍትሐዊ አይመስልም፡፡
በተቃራኒው እንመልከተው፡፡ በሀብት የተሻለው ለሌለው ማካፈሉ ከሞራል ኃላፊነት ውጭ ሌላ ግዴታ የለበትም፡፡ በተለይ ደግሞ የራሱ መሠረታዊ ፍላጎት ሳይሟላ ለሌላው አካፍል ማለት ተጠየቃዊ አይደለም፡፡ ‹‹የራሷ አሮባት የሰው ታማስል!›› ነው ነገሩ፡፡ በዕድገት የተሻሉት በዕድገት ወደ ኋላ ለቀሩት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከሀብታቸው ተቀንሶ እንዲሰጥ፣ ዜጎችን እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ ሲባል የሚወሰኑ ውሳኔዎች አጣብቂኝ ውስጥ መክተታቸውና የመገንጠል ፍላጎትን ሊያጭሩ እንደሚችሉ መረዳት አለብን፡፡
በኢትዮጵያ ከላይ የተገለጹትንና ሌሎች ተጨማሪ መሥፈርቶችን ከግምት ያስገባ ለአምስት ዓመት የሚያገለግል ቀመር ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ቀደም ብለው ሌሎች ቀመሮችም ነበሩ፡፡ ለክልሎች የሚያስፈልጋቸው ወጪና መሰብሰብ የሚችሉት የገቢ አቅም ልዩነቱ ተጠንቶ፣ እሱን ለመድፈን ሲባል የተዘጋጀ ነው፡፡ ቀመሩ ከአዲስ አበባ ውጭ ላሉት ክልሎች ድሬዳዋን ጨምሮ ያገለግላል፡፡ አዲስ አበባ ከድጎማ ተላቃ ራሷን ችላለች፡፡ በመሆኑም የፌዴራል መንግሥቱ ለድጎማ ከሚነይተው (ከሚሰጠው) በጀት ላይ የሚከተለውን ያህል ድርሻ አላቸው፡፡ የሕዝባቸው ብዛት ከአጠቃላይ ሕዝቡ በመቶኛና ድርሻቸውን በመቶኛ እንይ፡፡ ይህ ድርሻ ከ2005 የበጀት ዓመት ጀምሮ እስከዚህ ዓመት በሥራ ላይ ያለውን ብቻ የሚያመለክት ነው፡፡ ከዚህ በታች የቀረበው መረጃ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራል በጀት ድጎማ አሰረጫጨት ከ2012/13-2016/17 (እ.ኤ.አ.) እንዲያገለግል ከተዘጋጀው ቀመርና የ1999 ዓ.ም. የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት መሠረት በማድረግ የተቀነባበረ ነው፡፡
የትግራይ ክልል አጠቃላይ ከአገሪቱ በቆዳ ስፋት የሚሸፍነው 5.53 በመቶ፣ የሕዝቡ ብዛት 5.8 በመቶ ሲሆን የድጎማ ድርሻው 7.18 በመቶ ነው፡፡ የአፋር ክልል አጠቃላይ ከአገሪቱ በቆዳ ስፋት የሚሸፍነው 2.03 በመቶ፣ የሕዝቡ ብዛት 1.9 በመቶ ሲሆን የድጎማ ድርሻው 3.15 በመቶ ነው፡፡ የአማራ ክልል አጠቃላይ ከአገሪቱ በቆዳ ስፋት የሚሸፍነው 17.34 በመቶ፣ የሕዝቡ ብዛት 23.3 በመቶ ሲሆን የድጎማ ድርሻው 23.17 በመቶ ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል አጠቃላይ ከአገሪቱ በቆዳ ስፋት የሚሸፍነው 33.05 በመቶ፣ የሕዝቡ ብዛት 36.7 በመቶ ሲሆን የድጎማ ድርሻው 32.5 በመቶ ነው፡፡
የሶማሌ ክልል አጠቃላይ ከአገሪቱ በቆዳ ስፋት የሚሸፍነው 19.82 በመቶ፣ የሕዝቡ ብዛት 6.0 በመቶ ሲሆን የድጎማ ድርሻው 8.14 በመቶ ነው፡፡ የደቡብ ክልል አጠቃላይ ከአገሪቱ በቆዳ ስፋት የሚሸፍነው 10.28 በመቶ፣ የሕዝቡ ብዛት 20.4 በመቶ ሲሆን የድጎማ ድርሻው 20.1 በመቶ ነው፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አጠቃላይ ከአገሪቱ በቆዳ ስፋት የሚሸፍነው 4.3 በመቶ፣ የሕዝቡ ብዛት 0.9 በመቶ ሲሆን የድጎማ ድርሻው 2.1 በመቶ ነው፡፡ የጋምቤላ ክልል አጠቃላይ ከአገሪቱ በቆዳ ስፋት የሚሸፍነው 2.4 በመቶ፣ የሕዝቡ ብዛት 0.4 በመቶ ሲሆን የድጎማ ድርሻው 1.5 በመቶ ነው፡፡ የሐረር ክልል አጠቃላይ ከአገሪቱ በቆዳ ስፋት የሚሸፍነው 0.03 በመቶ፣ የሕዝቡ ብዛት 0.2 በመቶ ሲሆን የድጎማ ድርሻው 1 በመቶ ነው፡፡ የድሬዳዋ ክልል አጠቃላይ ከአገሪቱ በቆዳ ስፋት የሚሸፍነው 0.15 በመቶ፣ የሕዝቡ ብዛት 0.5 በመቶ ሲሆን የድጎማ ድርሻው 1.16 በመቶ ነው፡፡ አዲስ አበባ፣ በ2011 የበጀት ዓመት ድጎማ ቢደርሳትም ከዚያ በፊት የተዘለለችበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡
ከላይ ከቀረበው መረጃ ብዙ ቁም ነገሮችን ማስተዋል ይቻላል፡፡ የመጀመርያው ድጎማው በሕዝብ ብዛት መሠረት አለመሆኑን ነው፡፡ እንደ ሕዝብ ብዛታቸው ብቻ ቀመሩ ቢዘጋጅ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ እንዲሁም በአንፃራዊነት የሶማሌና የትግራይ ክልሎች ከፍተኛ ችግር ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ በመሆኑም አካባቢው ሞቃታማ መሆኑ፣ የመሠረተ ልማት ሥርጭቱ አነስተኛ መሆኑ፣ ለግብርና ታክስ መሠረት የሚሆን ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በእነዚህ አካባቢ አለመኖር፣ አንፃራዊ የሆነ የፀጥታ ችግር መኖሩ ወዘተ. ሲደማመሩ እንደ ሕዝባቸው ድጎማ ይደረግ ማለት ፍትሐዊ ላይሆን ይችላል፡፡
እርግጥ ነው እኩል ደረጃ ላይ ያልሆኑ ክልሎችን እኩል ማየት ተገቢ አይሆንም፡፡ ነገር ግን የሐረር፣ የድሬዳዋና የትግራይ ምናልባት ጥያቄ ሊያጭር ይችላል፡፡ የድሬዳዋና የሐረር ከተማነት፣ የትግራይ ደግሞ ከሌሎቹ በበለጠ ከመደበኛ በጀት ውጭ ከፍተኛ የሆነ ለክልሉ የሚውል የገንዝብ ምንጭ መኖሩ ፍትሐዊነቱን የተጓደለ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ቀመሩ ሲዘጋጅም እንዲህ ዓይነት የገቢ ምንጮችን ታሳቢ አላደረገም፡፡ እንዲህ ዓይነት ምንጮች በተወሰነ መልኩ በአማራ፣ አነስ ባለ ሁኔታ ደግሞ በኦሮሚያና በደቡብ ያሉ ቢሆንም በሌሎቹ ክልሎች ብዙም ጠንካራ ካልሆኑት ከልማት ማኅበሮች ውጪ ሌሎች የሉም፡፡ ሌላው የምንታዘበው በተለይ ኦሮሚያ ከሕዝቡ አንፃር ዝቅተኛ ድጎማ ማግኘቱን ነው፡፡ የደቡብም ቢሆን ከሕዝብ ቁጥሩ በታች ነው፡፡ በአንፃራዊነት እንደ ሕዝቡ መጠን ድጎማ የሚያገኘው የአማራ ክልል ነው፡፡ ስለሆነም ኦሮሚያ የመጀመርያው ደጓሚ ሲሆን፣ ቀጥሎ ደቡብ ከዚያ አማራ መሆናቸው ነው፡፡
ፍትሐዊ ስለመሆኑ ወይም አለመሆኑ ከዶክተር ሰሎሞን ንጉሥ ስለፊስካል ፌዴራሊዝም ሰፊ ትንታኔ ከሰጡበት መጽሐፋቸው የሚከተለውን መረጃ በመውሰድ አንድ ብቻ ማሳያ እንመልከት፡፡ ጋምቤላንና ቤንች ማጂ ዞንን እንውሰድ፡፡ በአንድ ወቅት ቤንች ማጂ ዞን (ከ650 ሺሕ በላይ) የጋምቤላን (305 ሺሕ አካባቢ) ወደ እጥፍ የሚጠጋ ሕዝብ እያለውና ተመጣጣኝ የዕድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ቢታወቅም፣ ለጋምቤላ 143 ሚሊዮን ብር ድጎማ ሲያገኝ ቤንች ማጂ ዞን ግን 33 ሚሊዮን ብቻ ነው የደረሰው፡፡ እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ክልል መመሥረት አዋጭም አትራፊም ይመስላል፡፡ የተለያዩ ብሔሮችም ወዲዚሁ ሊያመሩ ይችላሉ፡፡
የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ የሐረርና አፋር ክልሎች ሕዝብ ተደምሮ የአርሲ ዞን ሕዝብን አይበልጥም፡፡ ወይም ከደቡብ ወሎ ዞን የሚጠጋጋ ነው፡፡ ለእነዚህ ዞኖች ከፌዴራሉ መንግሥት በክልል በኩል አልፎ የሚደርሳቸውን ድጎማ ከእነዚህ ክልሎች አንፃር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ፍትሐዊነቱም ያጠያይቃል፡፡ ድጎማው ሲደረግ ደግሞ የብሔሮችን ብቻም ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 89(2) መሠረትም የዜጎችም እኩል ተጠቃሚነት ሊታሰብበት ይገባል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሻለ ክርክር ያደርጋል ከሚባልባቸው ጉዳዮች አንዱ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች የሚሰጠውን የበጀት ድጎማ የተመለከተ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለድጎማው ማከፋፈያ የሚሆነው ቀመርም ሆነ ዝርዝር ጥናቱን የሚከናውነው በየጊዜው የሚቋቋሙት አማካሪዎች ናቸው፡፡ የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ከፌዴራል ወደ ክልል የሚተላለፍ በጀትን በሚመለከት ሙያዊ የሆኑ ጉዳዮችን ማስጠናት እንዳለበት ይጠበቃል፡፡ የበጀት ጉዳይ ቋሚ ኮሜቴም ቢሆን እንዲሁ! ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ የሚጠቀሙት አማካሪዎችን ስለሆነና ሊቀያየሩ ስለሚችሉ የጥናት ውጤታቸው በየጊዜው ይቀያየራል፡፡ ወጥና ቀጣይነት አይኖረውም፡፡ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን የሚወስኑት ሰዎችም እንዲሁ በየጊዜው መቀያየራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ባለሙያዎቹም ፖለቲከኞቹም ስለሚቀያየሩ ለውሳኔ መነሻ የሚሆነውም ውሳኔውም ቶሎ ቶሎ መቀያየሩ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የሚካፈሉት የገቢ ድርሻም ላይ ሆነ ድጎማውን ክልሎች የሚከፋፈሉበት መጠን ላይ ተፅዕኖው ቀላል አይሆንም፡፡ በተለይ የሁለተኛው ነጥብ በርካታ ጊዜ የተቀያየረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለተወሰኑ የበጀት ዓመታት ድጎማውን ለማከፋፈል ከግምት የገቡትንና የተሰጡትን ነጥቦች ብቻ እንመልከት፡፡ ለ1987 የሒሳብ ዓመት በመቶኛ የሚታሰብ የሚከተሉትን መሥፈርቶች ሥራ ላይ ውለው ነበር፡፡ የክልሎቹ ለሕዝብ ብዛት 30፣ ከማዕከል ለሚኖር ርቀት 25፣ ገቢ ለማመንጨት አቅም 20፣ ከዓመት በፊት ለልማት ለተመደበው የበጀት ዓመት 15 እና ለክልሉ የቆዳ ስፋት አሥር ነጥቦች ተሰጥተውት ነበር፡፡
በ1988 የሒሳብ ዓመት ደግሞ ከላይ የነበሩት መነሻዎች ቀርተው ሦስት ነገሮችን በመውሰድ እኩል 33.3 ከመቶ ነጥብ ተሰጣቸው፡፡ እነዚህም የሕዝብ ብዛት፣ ክልሉ ያለበት የዕድገት ደረጃና በ1987 የበጀት ዓመት የሰበሰቡት የገቢ መጠን ናቸው፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ሌላ መሥፈርት መጣ፡፡ መሥፈርቶቹ አሁንም ሦስት ሲሆኑ ለሕዝብ ብዛት 60 ከመቶ፣ በልማት ላሉበት ደረጃ 25 ከመቶ እንዲሁም ላላቸው ገቢ የማመንጭት አቅም 15 ከመቶ ነጥብ ተሰጠ፡፡ እንዲህ እያለ መቀያየሩ ይቀጥላል፡፡ በእርግጥ በየዓመቱ መቀያየሩ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ከፌዴራል ለክልሎች የሚሰጥ ድጎማ በቀዳሚነት በፌዴራሉና በክልሎች መካከል ያለውን የገቢና ወጪ አለመመጣጠን ለማጥበብ ይደረጋል፡፡ በክልሎች መካከል ያለውን የዕድገት ልዩነት ለማቀራረብ ይረዳል፡፡ ይሁን እንጂ የፌዴራል መንግሥት ለክልል ያስተላለፈውን ድጎማ ለማከፋፈል የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በመሆኑ በክልሎች መካከል በሚኖረው ሰላማዊ ግንኙነት ላይ በእጅጉ የሚንጠለጠል ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም ከምክር ቤቱ አባላት ግማሽ አካባቢ የሚሆኑት ከአንድ ክልል ብቻ የሚመጡ መሆናቸውን ስናስብ ወይም ደግሞ አናሳ የተወካይ ቁጥር ያላቸው ክልሎች ሊጎዱ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ በመሆኑም፣ በመካከላቸው የሚኖረውን የዕድገት ልዩነት ማጥበብ ሊሳናቸው ይችላል፡፡ ለዚያም ይመስላል ለሕዝብ ብዛት ከፍተኛ ነጥብ መስጠትን የመረጡት፡፡
ለክልሎች የሚሰጥ ድጎማ ሁልጊዜም በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ላይ መዋሉን የፌዴራል መንግሥቱ ኦዲት በማድረግ ማረጋገጥ አለበት፡፡ ወደ ክልል የሚላክ የድጎማ ገንዘብ አንዳንድ ክልሎችን የበለጠ እንደሚጠቅም ቢታሰብም ውጤታማ የሆነ አጠቃቀምና አያያዝ አሁንም የጎደለው መሆኑን ሌሎች ክልሎችን የሚጎዳ ነው፡፡ ሌሎች ክልሎች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ በመጥፎ ትምህርትነትም እኩል ተጠያቂነት እንዳይኖር ከማድረግ አንፃርም አድልኦ ስለሚሆን ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ካልሆነ፣ የሚሰጠው ድጎማ ላይ ሌሎች ክልሎች በተቃራኒው ድምፅ ቢሰጡ ችግሩ የባሰ ሊሆን ይችላል፡፡ ድጎማ ጋር ተቀራራቢ የሆነው የፌዴራልና የክልሎች የጋራ ገቢዎችን የሚጋሩት አሠራር ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን አሁን ይህንን የጋራ ገቢ ሊያናጉ የሚችሉ አዝማሚያዎች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ለአብነት ሰፋፊ የማዕድን ሥራዎችን ላይ የተሰማሩ አልሚዎችን በመንጠቅ በየክልሉ ለሚገኙ ወጣቶች የሥራ ዕድል የመፍጠር ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ከከፍተኛ የማዕድን ማውጣት የሚገኘው ገቢ የፌዴራልና የክልል ሲሆን በአነስተኛ አልሚዎች የሚገኘው ግን የክልሎች ብቻ ነው፡፡
ሌላው በአንድ ሰው የሚቋቋም ኩባንያን እንውሰድ፡፡ የንግድ ሕጉ ተሻሽሎ ሥራ ላይ ሲውል አንድ ሰው ብቻውን ኩባንያ ሊያቋቁም ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በርካታ ነጋዴዎች የኩባንያ ባለቤት እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ ከኩባንያ የሚገኝ ግብር ደግሞ የፌዴራልና የክልል የጋራ ገቢ ነው፡፡ ከነጋዴዎች የሚገኘው ደግሞ የክልሎች፡፡ ይህ ሁኔታ የክልሎችን የግብር አቅም በመቀነስ የፌዴራሉን ይጨምራል ማለት ነው፡፡ በመሆኑም፣ የማዕድን ሥራውም ይሁን የኩባንያው ጉዳዮች የገቢ ሁኔታው ላይ ተፅዕኖ ያመጣሉ፡፡ ሌላው የፊስካል ፌዴራሊዝም አንዱ ግብ የተመጠጣነ ዕድገትና እኩልነት እንዲኖር ማድረግ እንደሆነ ሕገ መንግሥቱ ላይ የተገለጸ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ከዚህ አንፃር፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያስታዋልናቸው ካሉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱን እንጥቀስ፡፡ የኢንዱስትሪ ዞኖች ምሥረታ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ዞኖች መመሥረት ምክንያት በአካባቢው ከክልል በተጨማሪና በራሱ በጀት የፌዴራል መንግሥት ተጨማሪ የልማት ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ በርካታ የክልሉ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጠርላቸዋል፡፡ በኩባንያ መልክ ፋብሪካና ሌሎች ድርጅቶችን ተቋቁመው በግብር ከሚገኘው ገቢም ከሌላው ክልል በተሻለ ሁኔታ (50 ከመቶ) ገቢ ያገኛሉ፡፡ ስለሆነም፣ የኢንዱስትሪ ዞኖች የተገነባባቸው ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች ገቢያቸው ይጨምራል፡፡ በአጠቃላይ ዕድገቱም ላይ ለውጥ ይኖረዋል፡፡ ለግንባታቸው ብቻ እንኳን በቢሊዮን የሚገመት ብር የሚወጣባቸው እነዚህ የኢንዱስትሪ ዞኖች እስካሁን እንደታዘብነው በሶማሌ፣ በሐረር፣ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አንድም እንኳን አልተገነባም፡፡ በአፋር የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል፡፡
እንዲህ ዓይነት ከፍተኛ የክልል ልማትን የሚደግፉ ነገር ግን ጭራሹንም እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ የሌለባቸውን ከላይ የገለጽናቸውን አራት ክልሎች ስናስብ የተመጣጠነ ዕድገት በክልሎች መካከል መኖር የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት እንዲኖር የሚጠይቀውን የሕገ መንግሥት መርህ የሚቃረኑ አካሄዶች መሆናቸውን ለመረዳት የሚከብድ አይደለም፡፡ ስለዚህ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በብሔሮችም ይሁን በክልሎች መካከል እኩልነትን ለመፍጠር ሊጠቀምበት ከሚችልባቸው መንገዶች አንዱ ገቢን ከፌዴራል ወደ ክልሎች በማስተላለፍ ስለሆነ በተቻለ መጠን በቋሚነት ሥራቸው ይኼው የሆነ ባለሙያዎች በማቋቋምና ሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎችንም ጭምር ከግምት ማስገባት ለፌዴራል ሥርዓቱ ጤናማነት ሊጠቅም ይችላል፡፡
አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡