Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበፈተና ውስጥ ያለውን የዴሞክራሲ ጉዞ መታደግ የግድ ነው!

በፈተና ውስጥ ያለውን የዴሞክራሲ ጉዞ መታደግ የግድ ነው!

ቀን:

በንጉሥ ወዳጅነው

ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ አገራችን ከለየለት ወታደራዊ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ፣ ከእርስ በርስ ጦርነትና ከአስከፊ ድህነት መውጣት ጀማምራ ነበር፡፡ ለብሔር ብሔረሰቦች ዕውቅና መስጠትና የዜጎች መብት መከበር፣ የልማትና ዕድገት ጅማሮ ጉዞም ላይ ቢሆን ሥርዓቱ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከእነ ችግሩም ቢሆን የሚናቅ አልነበረም፡፡

ያም ሆኖ በተለይ ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ ክፉኛ የዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና የገዥው ፓርቲ ጠቅላይነት ጎልቶ ታይቷል፡፡ ልማቱም ቢሆን በአንድ በኩል የፍትሐዊነት ችግር ሲጠልፈው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሙስናና የኑሮ ውድነት ተብትበውት የሕዝብን እርካታ ከማረጋገጥ ይልቅ ቅሬታና መከፋትን አስከትሏል፡፡ ከሁሉም በላይ የመልካም አስተዳዳር ዕጦትና አንድነትን ማጠናከር የተሳነው የጎሳ ፌዴራሊዝም ያፈላቀቀው ትውልድ፣ ወደ ጥላቻና መገፋፋት እንዲያማትር ማድረጉ ነገሮችን አባብሷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህም ምክንያት ሥርዓቱ ‹‹በአብላጫ ድምፅ አገሪቱን የመምራት የሕዝብ ድጋፍ አገኘሁ›› ባለ አንድ ዓመት እንኳን ሳይሞላው፣ በየአካባቢው የሕዝቡ በተለይም የወጣቱ ቅሬታ ተቀስቅሷል፡፡ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተቀጣጥሎ በኋላ በተለያዩ አካባቢዎችም የተዳረሰው የሕዝብ እንቢተኝነት ከዴሞክራሲ በሮች መዘጋት፣ ከማንነት ጥያቄዎች መነሳት፣ ከድህነትና ‹‹ተዘረፍን›› ባይነት ጋር ተዳምሮ በመንግሥት ላይ አለመረጋጋትን ፈጥሯል፡፡ ነገሩ ወደ ሕዝብ ለሕዝብ እየደረሰም ግጭት፣ መፈናቀልና የልማት አውታሮችን የመጉዳት መዘዝ ማስከተሉ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡ አሁንም ችግሩ ይታያል፡፡

በአገሪቱ ለተከሰተው የተደማመረ የሕዝብ ቅሬታ የመንግሥትና የገዥው ፓርቲ ጉድለቶች ጎልተው ቢታዩም ሕዝቡ፣ ምሁራንና ፖለቲከኞችም የየራሳቸውን ድክመት  እንደነበረባቸው የታወቀ ነበር፡፡ በእርግጥ ሥርዓቱ ሕዝብን ከማዳመጥ ይልቅ የአብዛኛውን ካድሬና አመራር (ልማታዊ ጋዜጠኛ ተብዬዎቹን ጨምሮ) የውሸት ሪፖርት ብቻ ሲያዳምጥ እየዋለ እያደረ ወደ መጨረሻ ላይ የመላውን ሕዝብ ጥያቄዎች ሙሉ ለሙሉ መመለስ ወደማይችልበትና ዓመኔታን ያሳጣበት ቀውስ ውስጥ ለመውደቅ ተገድዷል፡፡

በዚህ ምክንያት ሕዝቡ ከዳር እስከ ዳር ቅሬታ ውስጥ ቢገባም፣ ሥርዓቱ በጊዜያዊነትም ቢሆን የፀጥታ መዋቅሩንና የደኅንነት ኃይሉን በሕዝብ ላይ ለማዝመት አልቦዘነም ነበር፡፡ ነገር ግን ችግሩ እየተባባሰ ሄዶ አገር ያፈርስ እንደሆን እንጂ፣ በተለይ ወጣቱ ደረቱን ለጥይት ሰጥቶ ከመታገል የሚመለስ አልሆነም ነበር፡፡ ይህን ተከትሎ ነው እንግዲህ በራሱ በመዋቅሩም ውስጥ መጪው ጊዜ ያሰፈራቸው የለውጥ ኃይሎች ተነስተው ወደ ገደል የሚደረገውን አገራዊ የውድቀት ጥድፊያ ለመቀልበስ የለውጥ ጥረት የጀመሩት፡፡

በእርግጥ ‹‹ለውጥም›› ይባል ‹‹ተሃድሶ›› ግንባሩ አሁን የታዩትንና ሌሎችን ጠንካራ ማሻሻያዎችን ባያደርግ፣ በሌላው ዓለም እንደሚታየው በሕዝባዊ እንቢተኝነት በከፋ ደረጃ መፈራረሱ አይቀርም ነበር የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ሥርዓቱ ከሥር ነቀል ለውጥ በመለስ በውስን ኪሳራ፣ እንደዚህ ያለውን ሽግግር ማምጣቱ ለገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፣ ለአገርና ለሕዝብም ጠቃሚ እንደሆነ ጥርጥር አልነበረውም፡፡ ክፋቱ ግን ‹‹የገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶችና አመራሮች ብሎም የበታች ካድሬዎች ሁሉ በተሟላ መንገድ የተስማሙበት ለውጥ ነው የተካሄደው፤›› ለማለት አሁንም አዳጋች መሆኑ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ (ምንም እንኳን ተፈናቃዮችን የመመለስ ጥረት ቢጀመርም)  በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች አሉ፡፡ የሕዝቦች መፈናቀልና የሰላም መደፍረስ እየተከሰተ መሆኑም አንድ ማሳያ ነው፡፡ ልማትና ዕድገቱም ቢሆን ወደ ጤናማ ጉዞው እንዳይመለስ የሚያደርጉ መደነቃቀፎች እየተስተዋሉ በመገኘታቸው ነው፡፡

በእርግጥ ለእነዚህ ቀውሶች መባባስ በአንድ በኩል የተገኘውን ነፃነት በወጉ ማጣጣም ያልቻሉ የአንዳንድ አካባቢዎች ወጣቶች ስሜታዊነት፣ በሌላ በኩል በይቅርታም ይባል በምሕረት ወደ አገር የገቡ አንዳንድ የታጠቁ ኃይሎች በስሜታዊ ፖለቲካ መመራታቸው በር ከፍቷል፡፡ ከሁሉ በላይ ሥርዓቱ ለዓመታት በሕዝቡ ውስጥ የፈጠረው አክራሪ ብሔርተኝነትና የጥላቻ ፖለቲካ መደማመጥን በመግፈፍ የእኔ፣ የእኔ ‹‹ባይነትን›› ማንገሡ የችግሩ ሁሉ ሰንኮፍ ሆኖ ይስተዋላል፡፡

ራሱ መንግሥት (በሥራ አስፈጻሚ ስብሰባም ሆነ በፓርላማ ውይይት) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዳረጋገጠው ደግሞ፣ በየአካባቢው ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው፣ እንዲሁም ስግብግብ ግለሰቦችና ቡድኖች ችግር ከመፍጠር አልተቆጠቡም፡፡ አንዳንዶቹ እነዚህ አመራሮች ደግሞ በየጥልቅ ተሃድሶው መድረክና በየመገናኛ ብዙኃኑ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተው፣ ቢያንስ እስከ መጪው ምርጫ ሕዝቡም ይቅርታ ያደረገላቸው ናቸው፡፡

ይሁንና በለውጡ ባቡር ተሳፍሮ አገረ መንግሥቱን ከማጠናከር ይልቅ ወደ ሌላኛው ዙር ግጭትና ያደገ የእርስ በርስ መጠላላትና ጥፋት ለመግባት መንደርደር መታረም ያለበት ብቻ ሳይሆን፣ አሳፋሪና መወገዝ የሚገባው ነው፡፡ ሕዝቡም አምርሮና ጨክኖ ሊታገለው ይገባል፡፡

ጥቂቶች ከዚህ ቀደምም የተሳጣቸውን የሕዝብ ሥልጣን ተጠቅመው ያደረሱት ጉዳት (በተለይ በዘረፋና በሰብዓዊ መበት ጥሰት)፣ በሕዝቡ ውስጥ የማይሽር ቁስል የጣለ ነበር፡፡ አንዳንዶች በየደረጃው በማናለብኝነት የፓርቲና የመንግሥት ሥራን በመቀላቀል ሕገወጥ ተግባራት መፈጸማቸው ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲውን መግደላቸው፣ በኔትወርክ በመቧደን ሕዝብን ወደ ቀውስ መክተታቸውም ሊያስጠይቃቸው የሚገባ ነበር፡፡ ይህን ጉዳይ መንግሥትና የለውጥ ኃይሉ ቸል በማለታቸው (በሆደ ሰፊነት በመታለፉ) ነው፣ ጭራሽ ለውጡን ለመቀልበስ እስከ ሞመከር የሚደፍሩ የውስጥ ቦርቧሪዎች እየተነሱ ያሉት የሚለውን የብዙዎች ሒስ መፈተሽ ይገባል፡፡

በሌላ በኩል አሁንም የገዥው ፓርቲ መዋቅርና አስፈጻሚ ሙሉ በሙሉ ባለመቀየሩ፣ ጥገኝነቱና ሕዝብ የሚያማርር ጥልፍልፉ እንዳይቀየር ተብትቦት ነው የሚገኘው፡፡ በየደረጃው (በተለይ በክልሎች) የተሾሙና የተቀጠሩ አንዳንድ ጥገኞች  በየመሥሪያ ቤቱ መብታቸውን ለማስከበርና አገልግሎት ለማግኘት የሚንቀሳቀሱ ዜጎችን ማንገላታታቸውና በጉቦ መማረራቸው፣ ብሎም በማንነት መዘዝ መድልኦና ማፈናቀልን እንደ አማራጭ መከተላቸው ጋብ ቢልም፣ አሁንም የማገርሸት ምልክት እየታየበት መሆኑም ሊፈተሽ የሚገባው ነው፡፡

እዚህ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በሕዝቡ መሀል ትርምስ ለመፍጠር እንደተሞከረው፣ አኩራፊው ሁሉ አማካሪና የኃላፊ ረዳት እየተባለ ተሰግስጎ ዳግም መንግሥትን ከሕዝብ እንዳያጋጭ ፈጣን ዕርምት ሊደረግበትም ግድ ይላል የሚሉ በጎ አሳቢዎችን ማዳመጥ ያስፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲውን ከፈተና ለማውጣት ይህን ዓይነቱን ሳንካ ለይቶ ማረም ይገባል፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ ከዓመታት በፊት ጀምሮ ‹‹መንግሥት ሕዝብን የማዳመጥ ችግር ደግሞ ደጋግሞ እያሳየ ነው›› የሚለውን ወቀሳ ባለመቀበሉ ነበር ችግሮች የተባባሱት፡፡ በዚያ የተዛባ አካሄድም በተደጋጋሚ የቀረቡ አቤቱታዎች ሰሚ ስላላገኙ አሁንም መፍትሔ አይመጣም የሚል ሕዝባዊ ድምዳሜ እንዲነግሥ አድርጎ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ ይህን ክፍተት አሁንም ነቃ ብሎ ማረምና ብዙኃኑን ሕዝብ ማዳመጥ ካልተቻለ ደግሞ፣ ቅሬታው እየተጠራቀመ ሕዝብ በአክራሪ ፖለቲከኛውና ‹‹አክቲቪስት ነኝ›› ባዩ እንዲናጥ ይገፋዋል፡፡ ዴሞክራሲውም ሌላ ፈተና ላይ ይወድቃል፡፡ ስለዚህ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ማረም ለነገ ሊባል አይገባም፡፡

ከሁሉ በላይ ሕዝቡ በድህነትም ቢሆን በአገሩ በነፃነት ተንቀሳቅሶና ባሻው አካባቢ እንዲኖር የፈቀደለትን ሕግ እየጣሰ ያለው፣ አኩራፊውና የለውጥ አደናቃፊው  ኃይል እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የከፋም ወንጀል ነው፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ ሕዝብና መንግሥትን ሆድና ጀርባ የሚያደርጉ የፖለቲካ አመራሮችና ካድሬዎች ከመጠየቅ ሊድኑ አይችሉም፣ አይገባምም፡፡ እርግጥ ጠባብ ብሔርተኞችና የጥላቻ አስተምህሮዎችም እያገዟቸው እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡

እሱ ብቻ ሳይሆን የሕዝቦችን አንድነትና የአገረ መንግሥትን ጥንካሬ የሚያረጋግጡ የፖለቲካ ውሳኔዎች በመጥፋታቸውና በመዘግየታቸውም የበርካቶች ሕይወት እየተቀጠፈ፣ አካል እየጎደለ፣ ብሎም የጅምላ ስደትና መፈናቀል እየተከሰተ  እንደሆነ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባ ነው፡፡ ስለዚህ ዴሞክራሲውን እየተደቀኑበት ካሉ አስቸጋሪ ፈተናዎች ለመታደግም ሆነ፣ አገርን ከውድቀት ለማዳን ከዚህ አዙሪት መውጣት ያስፈልገናል፡፡

ከዚህ አንፃር አሁንም ብዙዎችን እያስማማ የመጣው መንግሥትን ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎችና ያገባኛል ባዮች ባሳተፈ መንገድ መፍትሔ የማፈላለጉ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ከሕገ መንግሥት ማሻሻያ አንስቶ፣ የዜግነት ፖለቲካን ፈር ለማስያዝና የአገር አንድነትንና ሰላምን ለማረጋጋጥ መንቀሳቀስና ብሔራዊ ምክክር ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር ሊሆን ይገባዋል፡፡

በመሠረቱ ካለፈው ስህተት እንደወጣና ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እየገነባሁ ነው›› እንደሚል፣ ከመንግሥት የሚጠበቀውም ይህንን መድረክ በቅንነትና በቁርጠኝነት መፍጠር ወይም ማመቻቸት ነው፡፡ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታም እንዲስተካከልና ወደ አብሮነትና ብልፅግና እንድንጓዝ ማድረግም ይገባል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው ሚናቸው የማይናቅና ምናልባትም ከገዥው ፓርቲ  እንደሚስተካከል ከማያጠያይቁት ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ማኅበራትና ከዴሞክራሲ ተቋማት ጋር መደራደርን (አሁን በተያዘው አሸናፊው ቀድሞ በታወቀበት የፖለቲካ ጨዋታ ሳይሆን፣ በተሻለ አሳታፊነትና ሰጥቶ መቀበል መርህ መሠረት) ቅድሚያ መስጠት ይገባል፡፡ የሕዝብ ጥያቄን በአግባቡ መመለስ የሚቻለውም በዚሁ ዴሞክራሲያዊነት ብቻ ነውና፡፡

እርግጥ አሁን ከተጀመረው ለውጥና አጭር ጊዜ አኳያ ሁሉም ችግሮች በአንድ ጊዜ መፍትሔ ያገኛሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በአንድ አፍታ ሁሉም ጥያቄዎች ምላሽ ሊገኝላቸውም አይችልም፡፡ ነገር ግን በጣም መሠረታዊ የሚባሉ ጥያቄዎች (የሕዝቦችን አብሮነት የሚያጠናክሩ ውሳኔዎች፣ የወሰንና የሰላም ኮሚሽን በጥናት ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎች፣ ተፈናቃዮችን የመመለስና የማቋቋም፣ በየአካባቢው ሰላምና መረጋጋትን መመለስ፣ በሒደት ወጣቱን ወደ ሥራ ማስገባት፣ የጥላቻ ንግግርና ግጭት አስነሺ አመለካከትና ተግባራትን መከልከል ወዘተ…) ግን መተግበር አለባቸው፡፡

ለዚህም መንግሥትና ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም እንደ ተቆርቋሪ ዜጋ  ዕፎይ ብለን የምንቀመጥበት ጊዜ ላይ እንዳልደረስን ተገንዝበን የየድርሻችንን ልንወጣ ይገባል። ሁልጊዜም ቢሆን ዴሞክራሲ ሥርዓት ሆኖ እንዲቀጥል ኃላፊነቱ የመንግሥት ወይም የገዥው ፓርቲ ብቻ እንዳልሆነ ሕዝቡ መገንዘብ አለበት፡፡ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎችም ከተደበላላቀ ስሜት በመውጣት፣ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድና ለሕግ የበላይነት ዘብ በመቆም ለውጡ ከዳር እንዲደርስ መሥራት የጠበቅባቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ተደጋግሞ በብዙዎች እንደሚነገረው ፖለቲካችን ከዘውጌ አስተሳሳብና ከተናጠል ደፋ ቀና እንዲላቀቅ መትጋትም የመፍትሔው አካል ነው፡፡ ባለፉት ጊዜያት በሚያስተዛዝብ ደረጃ እንደታየው የፖለቲካ ፓርቲ እንደ ሱቅ በደረቴ ‹‹መሥርቶ አለሁ›› በማለት የተበታተነ ትግል ከመምራት ይልቅ፣ በርዕዮተ ዓለምና በዓላማ እንግባባለን የሚሉ ሁሉ ተደማምጠውና ተሰባስበው ጠንካራ ድርጅት (ግንባር) ጥምረት ወይም ሌላ መፍጠር ይገባቸው ዘንዳ ሕዝብ ይወክለኛል በሚለው ላይ ሁሉ ግፊት ማድረግ ይገባዋል፡፡ እዚህ ላይ ከሰሞኑ ሰባት ፓርቲዎች ወደ አንድ ውህድ ፓርቲ መምጣታቸውና ስያሜና አመራር መምረጣቸው በመልካም ጅምር ይጠቀሳል፡፡

መንግሥትም ከይሉኝታ ወጥቶ ሊያደፋፍረው የሚገባው ወሳኝና ታሪካዊ ጉዳይ ይኼ ነው፡፡ በእርግጥ ራሱ ገዥው ፓርቲ ለውህደት የጀመረው ጥረት ቢሳካለት በጎ ተፅዕኖ ከመፍጠር ባሻገር፣ ሕዝቡንም ይበልጥ ሊያወህደው የሚችል ነው፡፡ ንግግርን ከተግባር ጋር አዛምዶ የመከወን ፈተና ይከብዳል እንጂ የለውጥ ኃይሉም ፍላጎት እንዳለው አመላካች ነገሮች አሉ፡፡

እንደሚታወቀው በኢሕአዴግ የለውጥ ኃይሎች የተመራውን ተሃድሶ ሕዝቡ ገና በለጋነቱ ከዳር ዳር በሙሉ ልብ የደገፈው ለዴሞክራሲና ልማት ከሰጠው ትኩረት በላይ፣ ለሕዝቦች አብሮነትና ለአገር አንድነት ቀናዒ የሚመስሉ የመሪዎቹ ሐሳቦች በመንፀባረቃቸው ነበር፡፡ ስለዚህ ተወደደም ተጠላም ዜጎች በነፃነትና በአንድነት የሚኖሩባትን ኢትዮጵያ ለመገንባት የሚረዱ ስትራቴጂዎችን መተግባር አማራጭ ያለው ጉዳይ አይደለም፡፡ 

በተለይ ቀደም ሲል ጀምሮ ገዥው ፓርቲ የጎሳ ፌዴራሊዝምን ማራመዱ ያለውን አደጋ መመርመር ተገቢ ይሆናል፡፡ የተጠመደልንና ለወደፊቱም የምንባላባትን የቤት ሥራ ቀድሞ ማክሸፍም አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም አሁን ያለው የለውጥ ኃይል ጉዳዩን  ቢሸሸው እንኳን ሕዝቡና የዴሞክራሲ ኃይሎች ሁሉ የሕዝቦች ዕርቅና ሰላም፣ ብሎም ፍቅርና ኢትዮጵዊ ብሔርተኝነት ከወደቀበት እንዲነሳ መረባረብ አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ኃይሎች የተደራጀና የተሰባሰበ ትግል ወሳኝ ነው፡፡

በመሠረቱ በዚህ አገር የብሔር ጥያቄ አንገብጋቢ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ነገሮች የተቀያየሩበት የታሪክ ምዕራፍ ድረስ፣ የዘውጌ ፖለቲከኞች የጋራ ሰሚ የላቸውም፡፡ ሕዝቡም ቢሆን ከዚህ በኋላ በብሔርም ይሁን በጥቂት ግለሰቦች አደረጃጀት ውስጥ ሆነው በምርጫ ጊዜ ብቻ ከያሉበት እየተጠራሩ በመንጠራወዝ፣  ‹‹ምረጡን›› የሚሉትን  በቃችሁ ሊላቸው ይገባል። ተወዳዳሪዎችን በጠራ ፖሊሲ፣ ማኒፌስቶም ይባል ፕሮግራም እየመዘነ ከግለሰቦች ሰብዕና ይልቅ ለብዙኃኑ ሕዝብ ጥቅምና ለአገር አንድነትና ደኅንነት ያላቸውን አስተዋጽኦ እየፈተሸ ዕውቅና ሊሰጥ ግድ ይለዋል፣ ይገባልም፡፡

በአገራችን ዘመናዊ ታሪክ  እንደምናውቃቸውም ሆነ ባሳለፍናቸው አምስት የሚደርሱ አገር አቀፍ ምርጫዎች ላይ ያየናቸውና የሚበዙት የተቃውሞው ፖለቲካ ስብስቦች ችግሮቻቸው ትንሽ አልነበሩም፡፡ የአንዳንዶቹ የፖለቲካ ባህላቸው ኋላቀር፣ ከሥልጣኔ ጋር የማይተዋወቅ፣ ለሰጥቶ መቀበል መርህ ቦታ የማይሰጥ፣ በጭፍን ጥላቻ የተዋጠ፣ ከውይይትና ከድርድር ይልቅ እልህና ጉልበት የሚበረታበት፣ በሸፍጥና በሴራ የተተበተበና ቡድንተኝነት የሚያጠቃው እንደነበር ሊካድ አይችልም። ይህን ኋላ ቀር አስተሳሳብና የስግብግብነት መንገድ ግን በዚህ ለውጥ ውስጥ ማስቀጠል የሚታሰብ ሊሆን አይገባም፣ መቆም ይኖርበታል፡፡

ተደጋግሞ እንደታየው በችኮላና በስሜታዊነት ከሚካሄድ መጣመር የአገርን ጥቅም ማስቀደም ይገባል፡፡ እስካሁን ከጊዜያዊ ኅብረት ምሥረታ እስከ ግንባርና ውህደት ድረስ በታዩ ውጣ ውረዶች የተከፈለው ዋጋ ከግምት ውስጥ ሊገባ ይገባዋል፡፡ እንደ ፖለቲከኛ ማንም ቢሆን በሰጥቶ መቀበል መርህ የጋራ አጀንዳ እየነደፈ፣ ልዩነትን አስታርቆ መሥራት እንጂ ‹‹ሥልጣን ወይም ሞት!!›› እያሉ መስገብገብ የሚያከስረው በዋናነት አገርና ሕዝብን እንደሆነ ማጤን ይገባል፡፡

በመሠረቱ ዴሞክራሲ ሐሳቦች በነፃነት የሚንሸራሸሩበት፣ የማያስማሙ ጉዳዮችን እያቻቻሉ በሚያስማሙ ጉዳዮች ላይ የሚግባቡበት መድረክ ነው፡፡ ከኃይል ይልቅ ውይይትን የሚያስቀድሙበትና ለሕዝብ ፍላጎት ተገዥ የሚሆኑበት ምኅዳር ነው እንጂ፣ ጉልበተኞችንና በስሜት የሚጎርፉ ተከታዮችን ማስፈራሪያ በማድረግ የሚፈነጩበትና አላዋቂዎች የሚቀልዱበት መድረክ አይደለም፣ ሊሆን አይገባም፡፡

በተለይ ደግሞ ምርጫ  ሕዝብ ያለ ምንም መሸማቀቅና ፍራቻ ተወካዮቹን በነፃነት የሚመርጥበት ሥርዓት እንደመሆኑ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩል ሜዳ ላይ በነፃነት ሊወዳደሩ ዝግጁ መሆናቸው የሚረጋገጠው ለእንዲህ ዓይነት የውይይት መድረኮች ባላቸው ቀናዒነትና ሥልጡንነት መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ሕዝቡም ይህን እውነታ ማዕከል ያደረገ ትግል ይጠብቀዋል፡፡

በአጠቃላይ ዴሞክራሲ በሕግ የበላይነት ሥር የሚመራ ሥርዓት  እንደመሆኑ፣  በራሱ በገዥው ፓርቲም ውስጥ ሆነ በሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች መካካል የሚደረግ ንግግር፣ ይህንኑ ዓለም አቀፍ መርህ ማስቀደም አለበት፡፡ ውይይትም ሆነ ድርድር ለማድረግ የሚዘጋጁ ኃይሎችም፣ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ለአገርና ለሕዝብ የማይጠቅሙትን ያለፉትን ቂምና ቁርሾዎች ወደ ጎን ከማድረግ መነሳት አለባቸው፡፡

አዲሱን ጉዞ በሠለጠነ መንገድ ላይ በመጓዝ ማጠናከር እንጂ ሕዝብን ያላማከሉ ጩኸቶችን በማሰማት፣ ለትርምስና ውዝግብ በር መክፈት ለማንም ቢሆን ሊፈቀድም አይገባም፡፡ በእነዚህና መሰል እሴቶች ነው በፈተና ውስጥ ያለውን የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዞ መታደግ የሚቻለው የሚል እምነት አለኝ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...