Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትየዘንድሮው ግንቦት ሃያ ደግሞ ሲበዛ ሌላ ነው!

የዘንድሮው ግንቦት ሃያ ደግሞ ሲበዛ ሌላ ነው!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የደርግም፣ የኢሕአዴግም ፖለቲከኞችና ካድሬዎች ፈርዶባቸው አንድ የሚያደርጋቸው፣ በአንዴ አንድም ብዙም የሆነ ነገር አለ፡፡ የሁለቱም ቡድን ካድሬዎች ለምዶባቸውና እንደዚህ ልማዳቸው የሕዝብን ዝምታ ውስጥ የተመሸገ ብስለት ለማጤን ያልቻለ፣ በ‹‹ጨዋ›› ስሙ አለማወቃቸውን በትክክለኛ መጠሪያው ደግሞ ድድብናቸውንና ድንቁርናቸውን ማጋለጥ አንዱ መለያቸው ነው፡፡ የሁለቱም ካድሬዎች አደራ የተሰጣቸው አንድ ግንዛቤ በአንዱ ቁጭታ ሕዝብ ላይ መሙላትና መጫን፣ ወይም ሕዝብ ቢጥመውም ባይጥመውም የታዘዙትን ብሎና አስብሎ አቋም ማስያዝ የጋራ ፀባያቸው ነው፡፡ ሁለቱም የተለያየ አጋጣሚን ምክንያት ያደርጉና ወይም ይንተራሱና እኛ (ሕዝባቸው/ሕዝቦቻቸው) እንድናስበውና እንዲሰማን የሚፈለግ ሐሳብና ስሜት የምሁራን ትንታኔ ሆኖ፣ በራሳቸው በደጋፊዎቻቸውና አባላት የሚነገር ከሞላ ጎደል ይዘቱ ተመሳሳይ የሆነ ‹‹የሕዝብ አስተያየት›› ያቀርብልናል፣ ያሰፍርልናል፡፡

ደርግም፣ ኢሕአዴግም (የእስከ 2010ሩ ኢሕአዴግ) ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አቋቁመናል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃና ያልተጭበረበረ ምርጫ አካሄዶ የፈቃዱ ውጤት የሆነ መንግሥት ዓይቶ አያውቅም እንጂ፡፡ አገራችን ውስጥ የምርጫ ድምፅና ደጋፊ ገና ተግባብተው አያውቁም እንጂ፡፡ ሌላ አመለካከት እንዳይወሰድብኝ፣ ችግር እንዳይገጥመኝ፣ እንዳልበደልና እንዳልንጓለል ተብሎ ለምርጫ መመዝገብ፣ ወደ ምርጫ መሄድ፣ ያልወደዱትንም መምረጥ አዲስ አበባም ውስጥ ሞልቶ ኖሯልና የ‹‹በአገር እኖር ብዬ፣ ልጅ አሳድግ ብዬ፣ ከብት አረባ ብዬ፣ ለባሻ ዳርኩለት ሚስቴን እቴ (እህቴ) ብዬ›› ዓይነት ‹‹ግፍ›› ነው፡፡

- Advertisement -

ደርግና ኢሕአዴግ ሁለቱም (አዲሱን ኢሕአዴግ ገና ‹‹አየነው/ለየነው›› አላልንም እንጂ) ከበዓል በዓል ይለያሉ፡፡ የዘንድሮን በዓል ‹‹ልዩ›› የሚያደርገው ማለት ግልብ ነገር፣ ትርጉም የሌለው ‹‹ዜማ›› ያባዛሉ፡፡ ይህ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የነበረው ተመሳሳይነታቸው ነው፡፡

በሊቀመንበር ዓብይ አህመድ የሚመራው ኢሕአዴግ ያለቀላቸውን ክስረቶቹን ከተቀበለ፣ ከራሱ ውጪ ሌሎች ወገኖችን የማድመጥ ለውጥ ካደረገ፣ የኢትዮጵያን ዕድገት ከራሱ መስመርና ዕቅድ ጋር አንድ አድርጎ ከማየት ጉድጓድ ካወጣ (ወይም ይህን ሁሉ አደረገ ማለትም ክስረቶቻችን ተቀበለ፣ ለውጥ አደረገ፣ ከጉድጓዱ ወጣ ከተባለ) በኋላ ግንቦት 20 ሲከበር የዘንድሮ ሁለተኛው ነው፡፡

የዘንድሮውን ሃያ ስምንተኛውን የግንቦት 20 በዓል ‹‹ልዩ የሚያደርገው›› በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ የተፈጠረው መገለባበጥ፣ ከዓምናው በበለጠ ጎልቶ የወጣበት መሆኑ ነው፡፡ ይህን በግንባሩ ውስጥ የታየውን መገለባበጥ ራሱን አፍ ሞልቶ ሳይሆን፣ አፍ አውጥቶ ለመናገር ገና አየሩም መንገዱም የጠራ ‹‹ፈቃጅ››ም አይደለም፡፡ ያስፈራል፣ ያስፈራራል፡፡ በኢሕአዴግ ግንባር ውስጥ የደረሰው መገለባበጥ የአንዱን የግንባር አባል ድርጅት የበላይነትና አቅጣጫ ነዳፊነት አናግቷል፣ የሌላውን አባል ድርጅት ወደ ላይ አንስቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ብዙ ለውጥና ‹‹ለውጥ›› ታይቷል፡፡

ለውጡ ግን የመጣው አገር ሳይፈርስ፣ መንግሥት ሳይገረሰስ ቢሆንም፣ ዛሬ በፓርቲዎች መካከል ያለው ግንኙነት እንደሚያሳየው በ‹‹ስምምነት››ና ያላንዳች አደጋ አልነበረም፡፡ የአንዱ አባል ድርጅት ምሪት ሰጪነትና አቅጣጫ ነዳፊነት በሌላው የተተካው ሲጀመር እንዲህ ያለ ነገር ስለነበርና አሁን ደግሞ በስምምነት የእንቶኔ ተራ ነው ተብሎ አይደለም፡፡ እውነቱን ለመናገር የሕወሓት የበላይነትና አቅጣጫ ነዳፊነት ተናግቶ፣ የእሱ ሲም ካርድነትና ምሪት ሰጪነት ቀርቶ፣ ሕዴድ (ሁሉንም የምጠራቸው በድሮው ስማቸው ነው) ብአዴንንና ደኢሕዴንንም ይዞ ወደ ላይ የተነሳበት ለውጥ ሲታይ ከጅምሩ፣ ሳይቀደሙ የመቅደምና የተቀናቃኝን ሥውርና ግልጽ የጥቃት ወጥመዶች የማምለጥ ፈጣን ሩጫ የተከናወነበት ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የመጀመርያው ንግግር ህሊናን ከታከተው፣ አገርንና ዕይታን በብጥስጣሽ ብሔርተኝነት ካነካከተው ታሪክ፣ ትረካና ልፍላፎ ወጥቶ የኢትዮጵያ ግንባታና ታሪካዊ አዘላለቅ የሁሉም ሕዝቦች ደምና አጥንት ውጤት መሆኑንና የመተባበርን ጥንካሬነት ያሳዩበት ንግግር የፈጣኑ ሩጫ መክፈቻ ነበር፡፡

የሩጫውም የመጀመርያ መክፈቻ ፈጣን ውጤት አሳየ፡፡ የአፈና ሰለባ የሆኑ እስረኞች ፍቺ በላይ በላይ ተከታተለ፡፡ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመሄድ በማራኪ ንግግሮችና ውይይቶች ከሕዝብ ጋር ተገናኘ፡፡ ወደ ጎረቤት አገሮችም ሄዶ እስረኛ አስፈታ፡፡ የሞቀ መግባባት የታየባቸው የዲፕሎማሲ ስኬቶችን አሳየ፡፡ መከፋፈልና መሸካከር የቦረቦራቸውን የእስልምናና የኦርቶዶክስ ቤተ እምነቶችን ወደ ዕርቅ እንዲያመሩ አገዘ፡፡ በውስጥና በውጭ ያሉ ኩርርፎችን ሰብሮ በእርስ በርስ መፃረር ውስጥ የኖሩ ቡድናዊ ሠፈሮችን ቢያንስ ቢያንስ በዓብይ የለውጥ መንግሥት ደጋፊነት ላይ እንዲገናኙ አደረገ፡፡ ከፓርቲ ታማኝነት የተላቀቁ አድርጎ መንግሥታዊና መብት ነክ ተቋማትን የማነፅ ቁርጠኝነት አሳየ፡፡ እምነትም አሳድሮ በተቃውሞ የተሠለፉ ቡድኖች ወደ አገራቸው እንዲገቡና በሰላም እንዲሠሩ ለውጡንም እንዲያግዙ ጠራ፡፡ ቀጣናዊ ትቅቅፍን በማቀንቀን ሳይወሰን የሁለቱን ሕዝቦች ስሜት የፈነቀለ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት ፈጠረ፣ ወዘተ፣ ወዘተ፡፡ እነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎችና ክንዋኔዎች ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ አገር ብሔረሰብና ጎራ ያልለየ የኢትጵያውያንንና የኢትዮጵያ ተወላጆችን ድጋፍ አሳፍሷል፡፡ በጎረቤትና በታላላቆቹ ወዳጅ አገሮችም ዘንድ አድናቆትን አስገኝቷል፡፡

የለውጥ ጉዞው ግን ሲጀመርም፣ አሁንም ከአንድ ዓመት በኋላ ከመደነቃቀፍና ከሥጋት ቀውስም ለማምለጥ አልቻለም፡፡ ያ የሩጫው የመጀመርያ መክፈቻ ፈጣን ውጤት ካሳየ በኋላ ቅልበሳን ሳይሞከር ለማንርጰርጰር የሚያስችል፣ ቢሞከርም አዝረጥርጦ ለመሰለቃቀጥ የማይመለስ የምልዓተ ሕዝብ ድጋፍን በገፍ የመታጠቅ ክንዋኔ በላይ በላዩ ያጎረፈው ሁኔታ ግን ብዙ ነገሮች ሸርሽረውታል፡፡

የሕዝብ ድጋፍን ጭምር የሸረሸሩትና የለውጥ ጉዞውን ውጣ ውረድ ያበዙበት ነገሮች ግን ከላይ ከላይ እንደሚታየው ‹‹ትሻልን›› ትቶ ‹‹ትብስን›› የመምረጥ ጉዳይ አይደለም፡፡ እውነት ነው በለውጡ ውስጥ ከምንጊዜውም በላይ ብዙዎቹ ተፈናቅለዋል፡፡ በቅርቡ በሪፖርተር (ቁጥር 1986 ግንቦት 4 ቀን 2011 ዓ.ም.) ስለ ‹‹የአገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታና ቀጣይ ዕርምጃዎች›› የጻፉት ሦስት ጄኔራል መኮንኖች እንኳን ኢትዮጵያ ‹‹ፖለቲካ ቀውስ›› ውስጥ አለች ብለው እንደሚያምኑ፣ ቢያንስ ቢያንስ አምስት ጊዜ ያህል ጠቅሰዋል፡፡ አገሪቷን የፎረሹ አገሮች ምድብ ውስጥ ያስገቡም አገር በቀል ተመራማሪም አልጠፉም፡፡ በውስጥም በውጭም በመንግሥት ውስጥም ጭምር መንግሥትን ‹‹የሕግ የበላይነትን›› ባለማስከበር ፋይል ስም ከመደዴ እስከ ልሂቅና ምሁር የሚዥጎደጎድ ክስ አለ፡፡ የዚህ ሁሉ ክስ ትርጉም ሕግ የማስከበር ሥራ አልሠራህም፣ ሕግ ተላላፊነትን ዝም ብለሃል፣ እንደ መንግሥት ኃላፊነትን አልተወጣህም፣ ግፋ ቢል የሕግ ጥበቃን አጓድለሃል ነው፡፡

እውነት ነው የአገሪቱን ፀጥታና ሰላም የማስከበርን ጉዳይ ፈተና የገጠመው አዲሱ የለውጥ መንግሥት በማያውቅበት ገብቶ ይይዘው ይጨብጠው አጥቶ፣ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ሆኖበት ወይም ‹‹አይ መሬት ላይ ያለ ሰው›› ዓይነት መተረቻ ሆኖ አይደለም፡፡ መጀመርያ ነገር ለሕግ ተላላፊነት ምላሽ መስጠትን፣ ሕግን፣ ፀጥታንና ሰላም የማስከበር ጉዳይን አዲስና አስፈላጊ ያደረጉ ችግሮች የተቀፈቀፉትና የተወለዱት ካለፉት 27/28 ዓመታት ኢሕአዴግ ሠራሽ ማኅፀን ውስጥ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የኢትዮጵያ ዋነኛ መሠረታዊ ጥያቄ የብሔረሰብ ጥያቄ ነው ብሎ ያመጣው መፍትሔ የፈጠረው ችግር ነው፡፡ ይህንን ወደ ኋላ በዝርዝር እመለስበታሁ፡፡  

በዚህም ምክንያት ከኢሕአዴግ እኔ ብቻ ልክ፣ ድኅረ 83 አዲሲቷ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ፕሮፓጋንዳ ሥር ሲንተከተኩ የቆዩ፣ ታፍነው ሰሚ አጥተው ያደሩና ሕዝብን ከሕዝብና ሕዝብን ከመንግሥት ሲያነካኩና ሲያነታርኩም የነበሩ ጥያቄዎችና ውዝግቦች ለውጡን አምጠው ከመገላገላቸው በተጨማሪ፣ ለውጡ በፈጠረው አዲስ ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ውስጥ እዚህም እዚያም ደጅ እየወጡና እየተቅበጠበጡ በቀላሉ ወደ ሁከት መንሸራተታቸው በጭራሽ የማይጠበቅ አልነበረም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ አለመታደል ሆኖ የዓብይን የለውጥ ቡድን ከኢሕአዴግ ከራሱ ከውስጡ ያወጣው ቁጣና ውድመት ጭምር ስለነበር፣ ያ የመንግሥትን ጆሮ ማግኛ የሆነበት ልምድም ለብሶተኞች ያንኑ ሥልት ለጥያቄ ፈጣን ምላሽ ማግኛ፣ ወይም ተቃውሞን መግለጫ ወይም መልዕክት ማስተላለፊያ አድርገው እንዲጠቀሙበት ማስተማሩ አልቀረም፡፡ ለውጡን በትርምስ ማጎሳቆል፣ ማሳጣት፣ ከተቻለም መቅጨት ለፈለጉም ያልተቃለለ ብሶትና ቅሬታ፣ ኢሕአዴግ ራሱ የፈጠረው ችግር ጥሩ ሽፋን ሆኖ አገልግሏቸዋል፡፡ በዚህ ላይ የሐሳብ ውድድሮችን የማስተናገድ ልምምድ ያልነበረውና ጨርሶ የማያውቀው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር፣ በለውጡ ግብዣ ወደ አገር ውስጥ የገቡ የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖችን ማስተናገድ አቅቶት ምን ያህል አገርን ለውጪ ነፍስ ግቢ ነፍስ አደጋ እንደዳረጋት የ2010 ዓ.ም. መሰናበቻና የ2011 ዓ.ም. መባቻ ወራት ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የአገሪቱን ፀጥታና ሰላም የማስከበር አዲሱ ወቅታዊ ፈተና ደግሞ፣ የፀጥታ ኃይሎችን ከፖለቲካ ወገናዊነት ከማፅዳት ሥራ ጋር ደርቦ የማካሄድ ተግባር ውስጥም የግድ እንድንገባ አድርጎናል፡፡ ይህ በራሱ ዴሞክራሲያዊነትን ቆንጠጥና ጠበብ አድርጎ መራመድን የሚያስገድድ ቢሆንም፣ ዛሬ የሚታየውና የሚሰነዘረው ክስም ከዚህ የመነጨ አይደለም፡፡ ግጭትና ማፈናቀልን በኃይል በመደፍጠጥ አይደለም የለውጡ መንግሥት የሚከሰሰው፡፡ ክሱም የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡

ዛሬ በየቦታው እየተቅበጠበጡ መጣሁ ቀረሁ የሚሉት፣ አንዳንድ ቦታም እየተዘረገፉ የመላውን አገር ትርምስ ለመፍጠር የሚፈነዱት ጥያቄዎች መነሻና የሥር የመሠረት ምንጭ (በስሙ ይጠራ ከተባለ) ብሔርተኝነት ነው፡፡ ብሔርተኝነት የትኛውም በጎ በጎ ቅጽል ተሰጠው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትም ቢባል ብሔረሰብ መብትን አስከብሮ ከመኗኗር ያለፈና የወጣ ፖለቲካ ነው፡፡ ክፍልፋይ ወገንተኛነት፣ ጎጆኛነትና ብጥስጣሽነት፣ እንዲሁም አፈናቃይነት ለብሔረሰብ/ለብሔር ጥያቄ መልስ እሰጣለሁ ብሎ ከተነሳው ከሕወሓት/ኢሕአዴግ (ከቀድሞ ኢሕአዴግ) የፖለቲካ ተግባር የተወለደ ችግር ነው፡፡

ከዚህ የኢሕአዴግ የፖለቲካ ተግባር ውስጥ የተወለዱትን ችግሮች ምንና ምን ናቸው ብሎ መጠየቅ ነገሩን ያብራራዋል፡፡ ችግሮቹ በአጭሩ በጎጆኛነት የእኔ የሆነና ያልሆነ ሕዝብ ብሎ ከሰው ሰው መለየት፣ ከዚሁ ጋር የእኔ ብሔረሰብ የሚሉትን መሬት በመተሳሰብ ውስጥ መጠመድ፣ የእኔ/የእኛ የተባለ ሕዝብና መሬት ለይቶ ገዥነትንና በሊታነትን መቆጣጠር፣ በዚህም አማካይነት ጎጆኛ አዕምሮን ማስፋፋትና ማዛመት (ማለትም ከውጥንቅጥ ከተሜ አደግነትና በተለይም ከአማራነት ጋር የተዛመደ ኢትዮጵያዊነት ላይ ያተኮረን ዕይታ፣ በብሔር ማንነት በማፈርና ሌላውን በመዋጥ ትምክህታዊነትን እየቀጠቀጡ ወደ ጎጆኛነት መበጣጠስ)፣ የአካባቢን ኅብረተሰብ በቤተኛነትና በባይተዋርነት ማንጓለል፣ ሲከፋም ማፈናቀል፣ ብሔረሰብ ወይም አካባቢ የለዩ የንግድ ተቋማትን ፈጥሮ አካባቢ አለፍ የሀብት ሽሚያ ውስጥ መግባት፣ ምድሬ በሚሉት ሥፍራ ውስጥ ግን በባይተዋርነትና በበዝባዥነት በፈረጁት ላይ አትነግድብን የሚል ተቃውሞና ውድመት ማድረስ ተብለው የሚጠቃለሉ ናቸው ችግሮቹ፡፡

እነዚህ ችግሮችና ጣጣዎች የተፈጠሩት ተደጋግሞ እንደተገለጸው ከኢሕአዴግ የብሔር ጥያቄ የብሔረሰብ መብት ምላሽ ነው፡፡ ባለፉት 28 ዓመታት የመጡ ችግሮች ናቸው፡፡ ኢሕአዴግም ቢሆን ችግሮቹ የእሱ ዘመን መሆናቸውን ክዶ አያውቅም፡፡ የሚክደው ‹‹ሥርዓቱ›› ያመጣቸው አይደሉም፣ የአፈጻጸምና የአያያዝ ችግሮች ናቸው ብሎ ነው፡፡ ሥርዓቱ ማለትና ሕገ መንግሥቱ ወይም ፌዴራሊዝም ማለትን ሳናምታታ ጉዳዩን ማብራራት ልቀጥል፡፡

ብሔርተኝነት አንድ ብሎ የሚጀምረው ሕዝቤ፣ ብሔሬ/ብሔረሰቤ ብሎ ነው፡፡ እንዲህ ብሎ ሲነሳ ሌላውን የእኔ ያልሆነ፣ ሌላ ሕዝብ፣ የእነሱ ሕዝብ ብሎ ይለያል፡፡ በብሔረሰብ መብት ውስጥ መኖር፣ በብሔረሰብ ማንነት ከማፈር የመብት ረገጣ መላቀቅና መብትን አስከብሮ ከሌላው ጋር መኖር ከብሔርተኝነት ጋር በጣም የተለያየ ነገር ነው፡፡ ብሔርተኝነት ብሔረሰባዊ መብትን አስከብሮ ከመኗኗር ያለፈና ፕሮግራምን ነድፎ የያዘ ፖለቲካ ነው፡፡ ሻዕቢያም ኦነግም ሆነ ሕወሓት ሕዝቤ መሬቴ ማለት የጀመሩት ገና በጎረቤት አገር ውስጥም ሆነ በበረሃ ውስጥ ሲላወሱ/ሲንቀሳቀሱ ነው፡፡ የይዞታ ካርታ የሠሩትም ለሥልጣን ከመብቃታቸው በፊት ነው፡፡ ሻዕቢያ በ1983 ዓ.ም. ድል መታሁ ሲል ከያዘው ውጪ ቀረኝ የሚለውን መሬት በመቆጣጠር እንቅስቃሴ ውስጥ ተጠምዶ ነበር፡፡ የኦነግ ዋና ሩጫም በአካልም በርዕዮተ ዓለምም የኦሮሞ ያለውን መሬት መቆጣጠር ነበር፡፡ በመጨረሻም ወታደራዊው መንግሥት (በኋላ ኢሕድሪ የተባለው) ሲገረሰስ የሽግግሩ መንግሥት ተቋቋመ፡፡ በሽግግሩ መንግሥት ውስጥ ያሉት ብሔርተኛ ቡድኖች ብሔሬ/ብሔረሰቤ በሚሉት ሕዝብ ላይ መቀመጥ ተቀዳሚ ፍላጎታቸው ሆነ፡፡ ኋላም በሽግግሩ መንግሥት ውስጥ መቀመጫ ያገኙት የ‹‹ሁሉም›› ቡድኖች የጋራ መገናኛ ሊሆን የሚችል፣ ምናልባትም ማናቸውም መሠረታዊ ልዩነት የማያነሱበት፣ እንዲያውም ወያኔ/ኢሕአዴግና ኦነግ በሚስጥር የተስማሙበት እየተባለ ሲታሙበት የነበረ፣ የቋንቋን ሥርጭት ዋነኛ መሥፈርት ያደረገ የካርታ ቅድመ ዝግጅት ላይ ብሔራዊ ክልሎች ተሸነሸኑ፡፡ ሕዝቦች አገናዝበው፣ አብላልተውና መክረው የፀና ሕገ መንግሥታዊ ትስስር ከመገንባት ጋር ሊወስኑበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የአሁኑን የክልሎች ክፍፍል ለመወሰን የወጣው የጥር 5 ቀን 1984 ዓ.ም. አዋጅ ቁጥር 7/1984 ነው፡፡

በቤተኝነትና በመጤነት መጥመድና ማፈናቀል የተጀመረው ግን ገና በጠዋቱ ከ1983 ዓ.ም. ማክተሚያ ጀምሮ አማራን በነፍጠኛነት ከማዋከብ ጋር ነው፡፡ ቀስ እያለ ባለቤትና ባይተዋር መባባል በመብት ማንጓለልና ማፈናቀል ለሁሉም ተዳረሰ፡፡ በአማራ የተጀመረው መጤ እየተባለ እስከ መፈናቀል የሄደ መገፋትም በስተኋላ ለትግራዩ፣ ለኦሮሞው፣ ለጉራጌው፣ ለወላይታው፣ ለሶማሌው፣ ለኑዌሩ፣ ለአኝዋኩ፣ ወዘተ ሁሉ የሚደርሰውና ሁሉም አካባቢ የሚፈጽመው ለመሆን በቃ፡፡ የችግሮች የበላይና የዴሞክራሲ ሁለመና የብሔሮች ጥያቄ ሆኖ ሲያርፍ፣ የብሔር/ብሔረሰብ ትንሽ ፓርቲዎች ሲረቡ፣ የብሔር/ብሔረሰብ ውክልና ገና ከመናሻው በሕዝብ ድጋፍ የማይወሰን የራስ በራስ ሹመት ሲሆን፣ የአማራ ሕዝብ ጥቅምና ውክልና የኢሕዲን/ብአዴን/አዴፓ፣ የትግራይ የሕወሓት፣ የኦሮሞ የኦሕዴድ/ኦዴፓ፣ የደቡብ የደኢሕዴን፣ ወዘተ እያለ ሲዘልቅ፣ እንዲሁም ትክክለኛ የሚባለው አተያይና አቦዳደን ሁሉ ከፖለቲካ እስከ ትዳር ብሔረሰባዊ ሲሆን፣ ብሔርተኞች የየራሳቸው መሬት ለባለ ካርታ ይሁኑ ሲባል፣ ኢትዮጵያን ለአደጋ ለፍጅት ያዘጋጃት አዲስ በሽታ በሠራ አካላቷ ገባ፡፡ የዛሬው ድኅረ መጋቢት 2010 ዓ.ም. ውድመት፣ ጥፋትና መፈናቀል የዚህ ውጤት እንጂ አዲስ ነገር አይለደም፡፡

ድሬዳዋ ፈርዶበት ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ የመጀመርያው የክልሎች አሸናሸን ሕግም ሆነ (የጥር 1984 አዋጅ) ሕገ መንግሥቱ ድሬዳዋ የሚባል ‹‹ክልል››ም ሆነ ሥፍራ አያውቅም፡፡ ዛሬ ሕገ መንግሥት ተጣሰ፣ ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት አደጋ ላይ ነው፣ ፌዴራሊዝም እየተናደ ነው ብለው በሕግ አምላክ የሚሉትን ስለ‹‹ሕግ የበላይነት›› ነጋ ጠባ የሚሰብኩትን ይገባቸው፣ ይደንቃቸው፣ ያነዝራቸው ከሆነ ‹‹የድሬዳዋ ከተማ የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች ወደ የክልላቸው ይዞታ እንዲካለል በወቅቱ አንስተውት የነበረው ጥያቄ በሕግ መሠረት የመጨረሻ ውሳኔ እስኪያገኝ፣ በመንግሥት በተወሰነው መሠረት ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ ሆኖ ሲተዳደር የቆየ ከተማ፤›› ነው፡፡ ይኼም የተባለው በአዋጅ (በአዋጅ ቁጥር 416/96) በ1996 ዓ.ም. ከ12 ዓመታት ዝምታና ማድበስበስ በኋላ፣ ‹‹ዘላቂ የሆነ ሕጋዊ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ›› ተብሎ ድሬዳዋ ባለ ቻርተር ከተማ እንድትሆን ሲደረግ ነው፡፡ የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች የእኔ ነው፣ የእኔ ነው፣ ብለው የተጣሉበት ጉዳይ ‹‹በሕግ መሠረት የመጨረሻ ውሳኔ›› ማግኘት ያለበት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48(2) መሠረት በሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡ ግንቦት 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲከበር ድሬዳዋም ኢትዮጵያ የ28 ዓመታት የተወዘፈ ጉዷን ‹‹ያከብራሉ››፡፡

የክልሎች ወሰን ቢካለልም ባይካለልም፣ ወሰኑ ለአስተዳደርና ለልማት እንዲመች ሊለውጥ የሚችል እርጥብ ወሰን መሆኑ ቀርቶ አገርን ያህል ደም የሚያፋስስ ማብቂያ የሌለው የትንቅንቅ ‹‹ድንበር›› የሆነው፣ አገር በብሔርተኝነትና በቁርጥራጭነት በመቀኘቱ ነው፡፡ ድርሻዬ ወደ ሌላ አለፈ ብሎ መብከንከንና ሒሳብ ማወራረድ ሌላው መናቆሪያ ነው፡፡  

እርግጥ ነው ግንቦት 20 ወታደራዊ አምባገነንነት እንዳይሆን የፈረሰበት፣ ፈላጭ ቆራጮች እምቧጮ የሆኑበት፣ ወታደራዊ ኃይላቸውና የፀጥታ መረባቸው የተበጣጠሰበት ነው፡፡ ግንቦት 20 የተጠናቀቀው የትጥቅ ትግል ራሱ 17 ዓመታት መፍጀቱ እንደ ድል መቆጠር ያለበት ጉዳይ ነው ወይ? ወዘተ የሚለውን ትተን ዛሬ የሚያንገላታን ቀውስ ምንጭ ለችግራችን መፍትሔ ነው ብለን ድኅረ 1983 ዓ.ም. የወሰድነው ፖሊሲና አቋም ነው፡፡

በዚያ ምክንያት ከላይ የዘረዘርናቸው ጣጣዎችና በሽታዎች መጡ፡፡ በብሔርተኝት የተሟሹ ማኅበራዊ አዕምሮዎች ብቻ ደሩ፡፡ ቡድኖች የእኔ የብቻዬ የሚሉት የየርስታቸው ትናንሽ መንግሥታት ሆኑ፡፡ ኅብረ ብሔራዊ የጋራ ትግል ተመታ፡፡ ዴሞክራሲ የይስሙላና የውሸት ሆነ፡፡ እንዲህ ያለ አገር ውስጥ እንኳን ሥልጣን ግለሰባዊ ፀቦች ሳይቀሩ በብሔረሰብ ዓይን እየታዩ፣ የጅምላ አምባጓሮና የሰፋ ግጭት መክፈቻ ሆነው አገር አተራመሱ፡፡ ብሔር፣ ጎሳ፣ ጎጥ እየለየ ተማሪ ከተማሪ፣ እግር ኳስ ደጋፊ ከእግር ኳስ ደጋፊ መፋለጥ መጣ፡፡ ማረም፣ ማስቀረትና ማከም ያብን ይህንን ነው፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...