Monday, October 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ‹‹ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባልነት ተጠቋሚዎችን አጣርቶ ለማቅረብ የታሰበው ፓርላማው በሰኔ መጨረሻ ከመበተኑ በፊት ነው›› ሸዋረጋ መሸሻ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ መልማይ ኮሚቴ ሰብሳቢ

  የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድን ለመቋቋም በወጣው በአዋጅ ቁጥር 1133/2011 መሠረት፣ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድን በሥራ አመራር ቦርድ አባልነት የሚያገለግሉ ሰዎችን ለመሾም ለተቋቋመው መልማይ ኮሚቴ አባላት በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መሰየማቸው ይታወሳል፡፡ ይህንን መልማይ ኮሚቴ በሰብሳቢነት እንዲመሩ የተመደቡት ደግሞ መሸሻ ሸዋረጋ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እንድሪስ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሰብሳቢ፣ አቶ ካሳሁን ፎሎ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት፣ አቶ ዘገየ አስፋው ከአገር ሽማግሌዎች/ሲቪክ ማኅበራት፣ አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና ወ/ሮ ዘነበ ወርቅ ታደሰ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ በአባልነት ተካተዋል፡፡ በመሸሻ ሸዋረጋ (ዶ/ር) የሚመራው ይህ ኮሚቴ ዋነኛ ተግባሩ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በሥራ አመራር ቦርድ አባልነት ይመራሉ የተባሉ አምስት ሰዎችን ለመሾም የሚያስችለውን ጥቆማ ከሕዝብ በማሰባሰብ፣ ብቁ ናቸው የሚባሉትን አሥር ሰዎች በመለየት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረብ ነው፡፡ በአዋጁ መሠረት አምስቱ የመጨረሻ ዕጩዎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተለይተው ሹመታቸው በፓርላማ ይፀድቃል፡፡ በዋናነት ከሕዝቡ ጥቆማ የመቀበልና በአዋጁ በግልጽ በተቀመጡት መሥፈርቶች መሠረት ተጠቋሚዎችን የማጣራት ሥራ የተሰጠው ይህ መልማይ ኮሚቴ፣ በይፋ ሥራ መጀመሩን ማክሰኞ ግንቦት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡ የምርጫ ቦርድ አባላትን ለመሰየም እንደ መነሻ የሚታየውን ምልመላ የሚያከናውነው ይህ ኮሚቴ፣ አዲሱን አሠራር እንዴት ለማከናወን እንደተዘጋጀና አጠቃላይ የሥራ ሒደቱን በተመለከተ ዳዊት ታዬ የመልማይ ኮሚቴ ሰብሳቢውን መሸሻ ሸዋረጋን (ዶ/ር) አነጋግሯል፡፡ መሸሻ (ዶ/ር) የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት አግኝተዋል፡፡ ከኦስትሪያ ዩኒቨርሲቲ በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስና ፐብሊክ ሴክተር፣ እንዲሁም በኢኮኖሚክስ የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ወስደዋል፡፡ በሥራው ዓለም ለረዥም ዓመታት በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ደግሞ በክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅት (CRDA) በዋና ኃላፊነት ሠርተዋል፡፡ አርጋናይዜሸን ኦፍ ሶሻል ሳይንስ ለምሥራቅና ለደቡብ አፍሪካ በሚባል ተቋም በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና ጸሐፊ በመሆን እያገለገሉ ናቸው፡፡ ቃለ ምልልሱ እንዲህ ተጠናቅሯል፡፡

  ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በአባልነት የሚመሩ ግለሰቦችን ለመሰየም ዕጩዎችን በቅድሚያ የመመልመል ኃላፊነት የተሰጠው የመልማይ ኮሚቴ አባላት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ መሰየማቸው ይታወሳል፡፡ እርስዎ ደግሞ የዚህ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን እንዲሠሩ ተመድበዋል፡፡ እርስዎና ሌሎች በኮሚቴው አባልነት እንድታገለግሉ የተመረጣችሁት እንዴት ነው?

  ዶ/ር መሸሻ፡- በኮሚቴው ውስጥ በሰብሳቢነትና በአባልነት እንድናገለግል የተሰየምነው አዲሱን የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅን ተንተርሶ ነው፡፡ መልማይ ኮሚቴውን በሚመለከት በአዋጁ አንቀጽ አምስት ላይ፣ የኮሚቴው አባላት ከየት እንደመወከሉና ኮሚቴውም እንዴት እንደሚዋቀር ይጠቅሳል፡፡ በአዋጁ የዕጩ መልማይ ኮሚቴው ከእምነት ተቋማት፣ ከሲቪል ማኅበራትና ከሽማግሌዎች፣ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ይወከላሉ ይላል፡፡ ስለዚህ ይኼ እኔ የምመራውና በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰየመው ኮሚቴ ሊዋቀር የቻለው፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1133/2011 ተብሎ ከአንድ ወር በፊት በወጣው አዋጅ ውስጥ በተቀመጠው መሠረት ነው፡፡   

  ሪፖርተር፡- ጥያቄውን ግልጽ ለማድረግ በአዲሱ አዋጅ መሠረት የዕጩ መልማይ ኮሚቴው ምን ይሠራል? አጠቃላይ ተግባራችሁ እንዴት ይገለጻል? እስካሁንስ ምን እየሠራችሁ ነው?

  ዶ/ር መሸሻ፡- እስካሁን ስንሠራ የነበረው የመጀመርያው ይህንን ኃላፊነት እንዴት ነው የምንወጣው? እንዴት ነው የምንሠራው? እንዴት ነው ጥቆማ የምንቀበለው? አጠቃላይ ሥራችንን እንዴት ነው የምናካሂደው? መቼ ነው የምንገናኘው? የት ነው የምንገናኘው? የሚሉትን ነገሮች የሚመለከት አንድ ዝርዝር የሥራ መመርያ ማዘጋጀት ነው፡፡ ይህንን ያዘጋጀነውን መመርያ ካፀደቅን በኋላ ወደ ሥራ ገባን፡፡ ሁለተኛ ሥራዎችን መቼና እንዴት እንደምንሠራ የሚመለከት የድርጊት መርሐ ግብር አዘጋጅተናል፡፡ ሦስተኛ የሠራነው ነገር ጠቋሚዎችን በተለያየ መንገድ ለመድረስ እንድንችል የሕዝብ ማስታወቂያ ማዘጋጀት ነበርና እሱንም አዘጋጅተናል፡፡ በይፋ ሥራ በመጀመራችን ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪል ማኅበረሰቡ ተቋማት ጥቆማዎቻቸውን ማቅረብ እንዲችሉ ይፋዊ የሆነ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት ስለነበረብን ይህንንም አድርገናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ጥቆማዎች እየተቀበልን ነው፡፡ ሥራውን በሚመለከት አዋጁ ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ አንዱ የምንሠራው ጥቆማዎችን መቀበል ነው፡፡ ሁለተኛ በአዋጁ ተጠቋሚዎችን የምንለይባቸው ግልጽ መሥፈርቶች የተቀመጡ በመሆናቸው፣ እነሱን መሠረት በማድረግ አወዳዳሪ በሆነ መንገድ ዕጩዎቹን መለየትና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እንዲቀርቡ ማድረግ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የሚቀመጠው የታጩት ሰዎች ለሕዝብ ግልጽ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ በመጨረሻ የተለዩት እነማን እንደሆኑ እንዲታወቁ ለማድረግ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረብ ነው፡፡ እነዚህ ዋና ዋና ሥራዎቻችን ናቸው፡፡

  ሪፖርተር፡- ዕጩዎችን እንዴት ነው የምትቀበሉት? ጥቆማዎችን ለመቀበል የሚያስችላችሁ ቅድመ ዝግጅት ምን ያህል የተደራጀ ነው? ጥቆማው የሚቀርብበት ቢሮስ አላችሁ? ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ለመድረስ የሚያስችል አሠራር ዘርግተናል ብላችሁ ታምናላችሁ?

  ዶ/ር መሸሻ፡- ለዚህ ተብሎ የተደራጀ ቢሮ አለ፡፡ በተቻለ አቅም ለጥቆማ አቅራቢዎች አመቺ አሠራር አቅርበናል፡፡ ለምሳሌ ኢሜይል አንዱ ነው፡፡ ቴክኖሎጂውን መጠቀም ለሚችሉ ሰዎች ተብሎ የተደረገ ነው፡፡ በስልክ መጠቆም ይቻላል፡፡ ሦስት የስልክ መስመሮች ተዘጋጅተዋል፡፡ በእነዚህ ስልኮች መጠቆም፣ አስተያየት መስጠትና ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች እንዲብራሩ መጠየቅ ይቻላል፡፡ ጠቋሚዎች ይህንን ማድረግ የሚችሉበትንም መንገድ ፈጥረናል፡፡ ሌላው የፖስታ ሳጥን ቁጥር ነው፡፡ ስለተጠቋሚዎቹ አጭር መግለጫና ለመሳሰሉት በፖስታ መላክ ይቻላል፡፡  ሌላው ፋክስ ነው፡፡ ፋክስ መጠቀም ለሚችሉ ሰዎች አዘጋጅተናል፡፡ በአካል የሚመጣውን ሁሉ ማስተናገድ በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ፣ አማራጭ የመጠቆሚያ ዘዴዎችን አዘጋጅተናል፡፡ ለምሳሌ ከኢሉአባቦር ወይም ከወለጋ እዚህ ድረስ መጥቶ ለመጠቆም አይቻልም፡፡ ደግሞም ሁሉም ሰው እንዲሳተፍበት ተብሎ የተፈጠረ ዕድል እንደ መሆኑ መጠን፣ በዚህ ጉዳይ መሳተፍ የሚፈልጉ ሰዎች ሳይከለከሉና ሳይገደቡ መሳተፍ እንዲችሉ ሲባልና በአካል ተደራሽ ለማድረግ አንድ ቢሮ አዘጋጅተናል፡፡ ሳጥን ስለተዘጋጀ ወደዚህ በመምጣት በአካል ጥቆማውን በተዘጋጀው ሳጥን ውስጥ ማስገባት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ማድረግ የምንችለውን ሁሉ አድርገናል፡፡

  ሪፖርተር፡- ጥቆማውን ለመቀበል የሚያስችላችሁን ማመቻቸታችሁን ነግረውናል፡፡ በተሰጣችሁ ኃላፊነት መሠረት ምን ያህል ተጠቃሚዎችን ተቀብላችሁ ልታስተናግዱ ትችላላችሁ? ዕጩዎችን ከተቀበላችሁ በኋላ በምን መሥፈርት ለይታችሁ ነው የመጨረሻዎቹን ሰዎች የምታቀርቡት?

  ዶ/ር መሸሻ፡- የምናቀርባቸው ሰዎች በአዋጁ በግልጽ እንደተቀመጠው የመመዘኛ መሥፈርቶች አሉ፡፡ በመጨረሻ የቦርድ አባላት ሆነው የሚሾሙት አምስት ቢሆኑም፣ በእኛ በኩል ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚቀርቡት አሥር ናቸው፡፡ ከእነዚህ አምስቱን ወስደው ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ተነጋግረው የታመነባቸውን ሰዎች ፓርላማ ቀርበው የሚሾሙ መሆኑን ነው አዋጁ የሚያስቀምጠው፡፡ እኛ የምናቀርበው አሥር ዕጩዎችን ነው፡፡ ከምናወዳድርባቸው መሥፈርቶች አንዱ ዜግነት ነው፡፡ ሁለተኛ የፖለቲካ ገለልተኝነት ነው፡፡ በዚህ ቦርድ ውስጥ በአባልነት የሚካተት ሰው የፖለቲካ ድርጅት አባል መሆን አይችልም፣ አይፈቀድለትም፡፡ ሌላው መመዘኛ የሙያ ብቃት ነው፡፡ የሙያ ብቃትን በተመለከተ ከምርጫ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ቦታዎች ላይ ብቃት ያላቸው ሰዎች እንዲመጡ ነው የምንፈልገው፡፡ ከሙያ ብቃት አንፃር በሕግ፣ በፖለቲካ ሳንይስ፣ በሕዝብ አስተዳደር፣ በስታትስቲክስ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በመሳሰሉት በተለይ ከምርጫ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ትምህርት ያላቸው ሰዎች ናቸው የሚፈለጉት፡፡ ሌላው የምናየው ነገር መልካም ሰብዕናና ሥነ ምግባር ነው፡፡ በአብዛኛው በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን እሴቶች የሚጠብቁ ሰዎች እንዲሆኑና ለዚህም የተመሰከረ ልምድ ያላቸው ሰዎች እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡ ሌላው ኃላፊነት የመሸከም ብቃት ነው፡፡ ከዚህ በፊት በነበረ የሥራ ልምዳቸው ትልልቅ ኃላፊነትን የመሸከም ልምድ አላቸው ወይ የሚለውንም እናያለን፡፡ ከዚህ በፊት ትልልቅ ኃላፊነቶች ተሰጥተዋቸው ሥነ ምግባርን በጠበቀ ሁኔታ ሙያዊ ክህሎት የሚጠይቀውን ነገር ማድረግ የቻሉ ሰዎች ናቸው ወይ የሚለውንም እናያለን፡፡ ፈቃደኝነትም አንዱ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- በፈቃደኝነት ላይ ተመሥርቶ ሊሠራ የሚፈልግን ዕጩ ማድረግ የሚችልበት ዕድል አለ ማለት ነው?

  ዶ/ር መሸሻ፡- ፈቃደኝነት ስንል ጠቋሚው መጀመርያ ማድረግ ያለበት ተጠቋሚው ከመጠቆሙ በፊት ፈቃደኛ ነው ወይ? በቦርድ አባልነት ቢሾም ይቀበላል ወይ? በፈቃደኝነት የቦርድ አባል እሆናለሁ ብሎ የሚቀበል ነው ወይ? ምክንያቱም በግዴታ አንድን ሰው እንዲህ ያለውን ኃላፊነት ውሰድ ማለት ይከብዳል፡፡ አስቸጋሪ ኃላፊነት እንደሆነ ይጠበቃል፡፡ የሚጠየቀው ጥንቃቄና ዝግጁነት በጣም ከፍ ያለ ነው፡፡ ስለዚህ እኔ ይህ አለኝ፣ ይህንን ኃላፊነት በሙሉ ፈቃደኝነት እቀበላለሁ ማለት አለበት፡፡ ሌላው ተዓማኒነት ነው፡፡ የሚናገረውን የሚያደርግ ነው ወይ? ላመነበት መርህ ተገዥ ነው ወይ? ይኼም አንዱ የሚታይ ነው፡፡ እነዚህ መሥፈርቶች በአዋጁ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ምናልባት ተጨማሪ አድርገን የምናየው ከሌሎች ጋር አብሮ የመሥራት ብቃትን ነው፡፡ ይኼ ከሌሎች ጋር የመሥራት ነገር (Team Sprit) ማለት ነው፡፡ የማስተባበር ብቃት፣ ከሌሎች ጋር ተደማምጦ የመሥራት ብቃት ያለው ሰው ነው ወይ? የሚለውንም እናያለን፡፡ እንዲህ ዓይነት ክህሎቶች የሚገለጹበት ሰው ነው ወይ? ይህንን እናያለን፡፡ በመጨረሻ የምንለያቸውን አሥሩን ሰዎች ለቃለ መጠይቅ እንጠራቸዋለን፡፡ ገጽ ለገጽ እናገኛቸዋለን፡፡ ምክንያቱም ወረቀት ላይ ያለው አንድ ነገር ሆኖ ፈቃደኝነታቸውን እንደገና ማረጋገጥ አለብን፡፡ የፖለቲካ ድርጅት አባል አለመሆናቸውን ማረጋገጥ አለብን፡፡ እንደገና ደግሞ በፊት ለፊት ግንኙነቱ ወቅት በወረቀት ላይ ያለው ነገራቸው በእነሱ ላይ መታየቱን እንመለከታለን፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ ካጣራን በኋላ ነው ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሥሩን ሰዎች የምናቀርበው፡፡

  ሪፖርተር፡- መቼም የምርጫ ቦርድን ለመምራት የሚችሉ ሰዎችን ለይቶ ለማቅረብ የምታካሂዱት ሥራ ቀላል አይሆንም፡፡ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ አሁን በገለጹልኝ መንገድ የሚደርሳችሁን ጥቆማ መሠረት አድርጋችሁ በተቀመጡ መሥፈርቶች፣ የምታካሂዱት ማጣራት ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ ደግሞም አሥር ሰዎችን በዕጩነት ለማቅረብ 300 እና 400 ጥቆማዎች ሊደርሷችሁ ቢችሉ፣ እያንዳንዱን ተጠቋሚ በተባሉት መሥፈርቶች መሠረት ለመመዘንና የመጨረሻዎቹን ዕጩዎች መርጦ ለማቅረብ ያላችሁ ጊዜ በቂ ነው ብላችሁ ታምናላችሁ? የእናንተ ስብስብስ ይኼንን የማድረግ አቅሙ ምን ያህል ነው? የሌሎች አካላት ዕገዛስ አያስፈልግም? ለምሳሌ ስለተጠቋሚው በቂ መረጃ ለማግኘት የምትሄዱት ርቀት ምን ያህል ውጤታማ ያደርገናል ብላችሁ ታስባላችሁ? በአጠቃላይ አቅሙ አለን ብላችሁ ታምናላችሁ?

  ዶ/ር መሸሻ፡- እንግዲህ በርካታ ሰዎች ከመጡ አሁን አንተ ያልከው ነገር እርግጥ ነው ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ቅድም ያስቀመጥናቸው መሥፈርቶች አሉ፡፡ በእነዚህ መሥፈርቶች መሠረት ለምሳሌ ዜግነት አንዱ ማግለያ ነው፡፡ ሁለተኛው የፖለቲካ ገለልተኝነት ነው፡፡ ሦስተኛ የሙያ ብቃት ነው፡፡ ቀደም ብዬ በጠቀስኩልህ ዘርፎች ያልተማረ ሰው በመጀመርያው ዙር ላይ ይወጣል፡፡ መልካም ሥነ ምግባሩ በደንብ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ይህንን በሚመለከት የሚጠየቅበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ ሌላው ኃላፊነት የመሸከም ሁኔታንም እንዲሁ እናያለን፡፡ ከዚህ ቀደም ኃላፊነትን በመሸከም ረገድ ያለውን ልምድ እናያለን፡፡ በተለይ ዜግነት፣ የፖለቲካ ገለልተኝነትና የሙያ ብቃት አብዛኛዎቹን ተጠቋሚዎች የሚያጣሩ ናቸው፡፡ አንድ ተጠቋሚ በትምህርት ቆይታው ምንድነው የተማረው ለሚለው ከምርጫ ጋር የማይገናኝ ከሆነ በመጀመርያው ዙር እንዲወጣ እናደርጋለን፡፡

  ሪፖርተር፡- በዚህ በእናንተ ሥራ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚገመተው የአንድን ተጠቋሚ የፖለቲካ ገለልተኛነት ማጣራት ነው፡፡ ከፖለቲካ ገለልተኛ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ ሊከብድ ይችላል፡፡ ፖለቲካ ውስጥ የነበረ፣ ከፖለቲካ ጋር የተሳሰረና ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት ሊሠራ የሚችል ነገር ግን ራሱን የደበቀ ከሆነ፣ እሱን የምትለዩት እንዴት ነው? ሳይታወቅ ሊያመልጥ ቢችል ውዝግብ ሊያስነሳ ይችላልና የእናንተ ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ወሳኝ ስለሆነ፣ እንዲህ ያለው ነገር እንዳይፈጠር የእናንተ ዝግጅት ምን ያህል ነው?

  ዶ/ር መሸሻ፡- ይህንን በተመለከተ በኋላ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ውይይት እንደሚደረግ መዘንጋት የለበትም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፉ አድርገናል፡፡

  ሪፖርተር፡- እንዴት?

  ዶ/ር መሸሻ፡- ማለትም የፖለቲካ ፓርቲዎች በመጠቆሙ ረገድ በምርጫ ቦርድ በኩል መልዕክት እንዲደርሳቸው፣ እንደገናም የተለያዩ የዜና ዕወጃዎችንና የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ተደራሽነትን አስፍተናል፡፡ ሕዝቡ እንዲሳተፍ ዕድሉ አለ፡፡ እንግዲህ እንዳልከው አደጋ የሚሆነው ሰዎች ሰብዕናቸውን ደብቀው፣ የነበራቸውን የፖለቲካ ተሳትፎ ደብቀው፣ ከፖለቲካ ፓርቲ ነፃ ነኝ ብለው መጨረሻ በአንዱ ወይም በሌላው መንገድ ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጋር ወግነው፣ ወይም መደበኛ በሆነ መንገድ በአባልነት ተመዝግበው ከተገኙ ይኼ አውቶማቲክ ዕርምጃ የሚያስወስድ ነው የሚሆነው፡፡ በእኛ በኩል ግን ማረጋገጫ እናስፈርማቸዋለን፡፡ የፖለቲካ ድርጅት አባል ወይም ደጋፊ አለመሆናቸውን እናስፈርማቸዋለን፡፡ አንዱ መሥፈርት እሱ ነው፡፡ በመጨረሻ የምንወስዳቸው ሰዎች የግዴታ ይፈርማሉ፡፡ ‹እኔ የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም፣ ሆኜ ብገኝ ሕጋዊ ዕርምጃ ይወሰድብኝ ዘንድ ተስማምቻለሁ› ብለው  እንዲፈርሙ እናደርጋቸዋለን፡፡ በዚህ ዓይነት መንገድ በተቻለ አቅም እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳይከሰት  ለማድረግ በኮሚቴው በኩል ዝግጅት አድርገናል፡፡

  ሪፖርተር፡- ብዙ ሥራ የሚጠበቅችሁ ቢሆንም የዕጩዎችን ጥቆማ ተቀብላችሁ፣ የማጣራቱን ሥራ አጠናቃችሁ የመጨረሻዎቹን ዕጩዎች የመለየት ሥራ መቼ ታጠናቅቃላችሁ?

  ዶ/ር መሸሻ፡- እንግዲህ ሁኔታዎች በዚህ ዓይነት መንገድ የሚቀጥሉ ከሆነ በተያዘው የጊዜ ገደብ እናጠናቅቃለን፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ ሰዎች ጥቆማ እየሰጡ ነው፡፡ በኢሜይልም እያደረሱ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ እስከ ግንቦት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ጥቆማውን እንቀበላለን፡፡ ከግንቦት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በኋላ የማጣራት ሥራዎችን እንጀምራለን፡፡ የመጀመርያው ቅድም ባልኳቸው መሥፈርቶች መሠረት ማጣራትና መቀነስ፣ ቀጥሎ ለፍፃሜ የሚደርሱትን መለየት ነው፡፡ ይህንንም እስከ ሰኔ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ እንጨርሳለን፡፡ እንደሚታወቀው ፓርላማው ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ይዘጋል፡፡ ስለዚህ ይኼ ሥራ ከዚያ በፊት ተጠናቆ መድረስ አለበት፡፡ አጣዳፊ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- ስለዚህ እናንተ መጨረሻ የምትመርጧቸውን ሰዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርባችሁ፣ እሳቸው ደግሞ አምስቱን በመምረጥ ለፓርላማ ማቅረብና ለማፀደቅ የታሰበው የ2011 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን ከመዘጋቱ በፊት ነው ማለት ነው?

  ዶ/ር መሸሻ፡- አዎ፡፡ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተጠቋሚዎችን አጣርቶ ለማቅረብ የታሰበው ፓርላማው በሰኔ መጨረሻ ከመበተኑ በፊት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ያመንባቸውንና የመረጥናቸውን ሰዎች ለሕዝቡና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ ሰኔ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. ለማቅረብ ነው ያቀድነው፡፡

  ሪፖርተር፡- እንዲያው የግልዎን አስተያየት እንዲሰጡ ፈልጌ ነው፡፡ የምርጫ ቦርድን  በሥራ አመራር ቦርድ አባልነት ለማገልገል የሚሾሙ ሰዎች የሚጠቆሙበት መንገድ በተለየ ሁኔታ እንዲካሄድ ሊደረግ ነው፡፡ ይህ የአሰያየም ዘዴ ከበፊቱ ጋር እንዴት ሊነፃፀር ይችላል? እርስዎስ በግልዎ ልዩነቱን እንዴት ያዩታል?

  ዶ/ር መሸሻ፡- በዚህ ላይ አስተያየት መስጠት አልፈልግም፡፡ እንዴት እንደነበር እኔ አሠራሩን አላውቅም፡፡ ተዓማኒነቱ ላይ የሚነሳ ጥያቄ እንዳለ እሰማለሁ፡፡ ከዚያ ውጪ ግን  ሰዎች እንዴት ሲሰየሙ እንደነበር፣ በምን መሥፈርት ይመረጡ እንደነበር፣ ምን ዓይነት ሒደት እንደነበር እውነቱን ለመናገር ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡

  ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ኮሚቴ በሰብሳቢነት እንዲመሩ ደብዳቤ ሲደርስዎ ምን ተሰማዎት? የተሰጣችሁ ኃላፊነት ከባድና አዲስ ዓይነት ነውና አካሄዱን እንዴት ተመለከታችሁት?

  ዶ/ር መሸሻ፡- ስሜቴ ሁለት ነው፡፡ በአዋጁ ላይ ገለልተኝነታቸው የተረጋገጠ ነው የሚለው፡፡ ብቃታችንና ገለልተኝነታችን በምን መንገድ እንደታየ እኔ መግለጽ አልችልም፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ የነበረን ልምድና ታሪክ ታይቶ፣ ያውም ደግሞ እኔ በሰብሳቢነት መሰየሜ በአንድ በኩል የመንፈስ እርካታ ይሰጣል፡፡ በዚህ ደረጃ ገለልተኛ ነው፣ ብቃትም አለው ተብሎ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ካየነው አብሮት የሚመጣው ኃላፊነት በጣም ከባድ ነው፡፡ ቀላል ነገር አይለደም፡፡ እንዳልከው በርካታ ሰዎች የሚጠቁሙ ከሆነ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ የእኛ ሚና አጣርተን ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረብ ነው፡፡ እሳቸው ናቸው የመጨረሻውን የሚወስኑት፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ ለብቻቸው አይችሉም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማሳተፍ እንዳለባቸው አዋጁ ይደነግጋል፡፡ ይህ አዲስ ዓይነት አካሄድ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ወደ ፓርላማ የሚሄደው፡፡ ስለዚህ የሥራው ከባድነት፣ በአጭር ጊዜ ይህንን ሥራ ሠርቶ ማቅረብ፣ እንደገና ደግሞ ከዚህ በፊት ያልተሞከረና የሁሉም ዓይን ያለበት በመሆኑ የሚፈጥረው ጭንቀት ቀላል  አይደለም፡፡ ከባድ ኃላፊነት እንደተሸከምን አድርገን ነው የምናየው፡፡ ይኼ የእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የሌሎቹም በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ስሜት ይህንን ነው የሚያሳየው፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች