ግንቦት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ንፋስ ስልክ አካባቢ ወደ ሚገኘው መኖሪያዬ አመሻሹን ደረስኩ፡፡ በሠፈሩ መብራት አልነበረም፡፡ ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥም መብራት ጠፍቶ ስለነበር ለተጨማሪ ሦስተኛ ቀን መብራት ይጠፋል ብዬ አልገመትኩም፡፡ ሰዓቱ ከምሽቱ 2፡40 ሰዓት ነበርና ምናልባት በአዲሱ የፈረቃ ዕደላ መሠረት ሊመጣ ይችላል በማለት ጠበኩ፡፡ ድራሹ የለም፡፡
ከምችለው በላይ ስለጠበቅሁ፣ አማራጬ በስምንት ብር የገዛሁትን ሻማ በመለኮስ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ያለ ፈረቃዬ መብራት ያሳጣኝኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እያስታወስሁ ትዝብቴን እየገልጽኩ ይቺን ጽሑፍ በሻማዋ ጭላንጭል እንደምንም አገባደድሁ፡፡
ለሦስት ተከታታይ ቀናት መብራት ሳላይ በመንጋቱ በእኔና በሠፈሬ ነዋሪዎች ስም አቤት ብል ይገባኛል፡፡ አገልግሎት ሰጪው ተቋም የኃይል ሥርጭቱን በፈረቃ ለማድረግ ሲወስን፣ ችግሩ የአገር ነው ብለን እንደመቀበላችን የኃይል ሥርጭቱን ግን ባወጣው ፕሮግራም መሠረት በአግባቡ ሊያቀርብልን ይገባው ነበር፡፡ ይሁንና አገልግሎቱን በማስተጓጎል እኔንና እኔን መሰሎች መክፈል የሌለብንን ዋጋ እያስከፈለን ይገኛል፡፡ የፈረቃ ሥርጭቱን አተገባበር ይፋ ባደረገበት ወቅት፣ ዕደላው በአግባቡ እንደሚካሄድ በመንግሥት ሹማምንት ተነግሮን ነበር፡፡ በቀን ሦስት ጊዜ የሚቀያየረው ወደ ሁለት ዝቅ እንዲል ተደርጎ፣ ምሽቱ ላይ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበት አሠራር እንደተዘረጋ ተገለጸለን፡፡ ነገር ግን ከጅምሩ ጉራማይሌ አሠራሮችን እየታዘብን ነው፡፡
የፈረቃ ሥርጭቱ ከተነገረው የዕደላ ፕሮግራም ጋር ሊጣጣምልኝ አልቻለም፡፡ እንደተጠቀሰው ከ5 እስከ 11 ሰዓት እንዲሁም ከ6 እስከ 10 ሰዓት ይሆናል ቢባልም፣ ዕደላው ግን ሰዓቱን ጠብቆ አልመጣም፡፡ ይህ ቢሆንም እኔና መሰሎቼ በተከታታይ ባልተቀጣንና በጨለማ ባልከረምን ነበር፡፡ እንደ አገር የገጠመንን ችግር በመረዳትና ወደፊት ይጠፋብን ይሆን ብለን ሳንሠጋ ብርሃን የምናገኝበት ቀን እንደሚመጣ በማሰብ ፈረቃውን እንዳመጣብን ብንቀበልም፣ የተመለከትነው ግን የፈረቃ ፕሮግራሙ በአግባቡ እንደማይተገበር ነው፡፡
የኃይል ሥርጭቱ በየት አካባቢ በምን ሰዓት በምን ያህል ጊዜ እንደሚለቀቅና እንደሚጠፋ የሚያሳይ በጽሑፍ የተደገፈ ፕሮግራም ለደንበኞች መድረስ ይኖርበት ነበር፡፡ ሁሉም ያችን ፕሮግራም እያየ በዚያች መረጃ መሠረት ተዘጋጅቶ ኃይል በሚያገኝባቸው ቀናት መሠራት የሚገባውን እንዲሠራ ይረዳዋል፡፡ ደንበኞች በፕሮግራም እንዲንቀሳቀሱ ያስችላል፡፡
የወጣው ፕሮግራም በአንዳንድ ቦታዎች ሲዛባ ለምን ተብሎ የሚጠየቅበትና ያለፕሮግራም የኃይል መቋረጥ ሲፈጠር የሚስተካከልበት መንገድ ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡ እርግጥ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጥቆማ መስመር በመዘርጋት ተገልጋዩ ያልተገባ መቋረጥ ሲያጋጥመው እንዲያስውቅና እንዲጠይቅ ሲገልጽ አድምጠናል፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ ተጠቃሚዎች ኃይል መቼ እንደሚቋረጥበትና እንደሚለቀቅለት በቂ መረጃ የላቸውም፡፡ ቢኖረውም ሲጠብቅ ይውላል አያገኝም፡፡ ከሰሞኑ እንደታዘብነው ለሰዓታት ብቻ ጠፍቶ ይቆያል የተባለው ኃይል ቀንና ሌሊት እልም የማለቱ ነገር ያበሳጫል፡፡
በፕሮግራሙ መሠረት ለምን አልተፈጸመም ብሎ መጠየቅና ዕርምት መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ ተቋሙ በየአካባቢው ባወጣው ፕሮግራም መሠረት ኃይል እየቀረበ ስለመሆኑ የመስክ ክትትል ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ የግድ ተጠቃሚው ስልክ እስኪደውል መጠበቅ የለበትም፡፡ እየዞረ ማየቱና መፈተሹ ባለማየት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችንም ሊያስቀርለት ይችላል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና ባለኢንዱስትሪዎች ከኃይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥም ችግርን ለመፍታት ስምምነት ማድረጋቸውን እናስታውሳለን፡፡ ይህ ስምምነት የኃይል አቅርቦቱ ሲስተጓጎል ተጠያቂውን ማን እንደሆነ በግልጽ ለማወቅ ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን ስምምነትና አሠራር ማምጣቱ በበጎ ጅምሩ የሚታይ ነው፡፡ በተግባር ምን ያህል ተፈጽሟል የሚለው ጉዳይ ግን ያጠያይቃል፡፡ በአገልግሎት ሰጪና ተቀባይ መካከል ያለው ግንኙነት ተጠያቂነትንም ያካተተ መሆን አለበት፡፡
ገና ከጅምሩ የኃይል ሥርጭቱ እንዲህ ያሉ ክፍተቶች ከታዩበት፣ በመጩዎቹ 40 እና 50 ቀናት ውስጥ ደንበኞች ችግር ውስጥ የሚገቡና በፕሮግራም እንዳይመሩ የሚያስገድድ ቀውስ ያመጣልና የኃይል ሥርጭቱ እንደተባለው በፕሮግራሙ መሠረት ይፈጸም ዘንድ እንለምናለን፡፡ እንዲህ ያለ የኃይል ሥርጭት ላይ ማተኮር ያለበት ሌላው ጉዳይ ለዚህ አገልግሎት የተመደቡ ሠራተኞች ሥራቸውን በአግባቡ እየሠሩ መሆን አለመሆኑን ጭምር በአግባቡ መቆጣጠርን የሚጠይቅ መሆኑ ነው፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች መታዘብ እንደሚችለው ደግሞ በወጣው ፕሮግራም መሠረት ኃይል ያለማግኘቱ ሳያንስ በመከራ ኃይል ሳይለቀቅ ደግሞ ያልተመጠነ የኃይል አለቃቀቅ ይዟል፡፡ አንዳንዴ በዝቶ ጉዳት ሳያስከትል ኃይሉ ተለቆም ኃይሉ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ መሣሪያዎችን የማያንቀሳቅስ ሆኖ ይገኛል፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ማለት ይህ ነው፡፡ ስለዚህ ያለውንም ኃይል በአግባቡ ለማሠራጨትና ለማደል ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ መሠራት ይኖርበታል፡፡
የዕለት ተዕለት ፕሮግራም ከማዛባት ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ጫናውም ቢሆን በቀላል አይታይም፡፡ በዚህች ጥቂት ቀናት መታዘብ እንዲቻል ነው፡፡ በፕሮግራሙ መሠረት ኃይል አለመካሄዱ ሸመታ ላይ ራሱ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡
ለወትሮውም በርካታ ስንክሳሮች የበዙት የግብይት ሥርዓትና የኑሮ ውድነቱ ጣሪያ እየነካ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የኃይል አቅርቦት መቆራረጡ የዕለት ጉርስ ላይ ከፍተኛ ጫና እያመጣ ነው፡፡ ሌላውን ትተን እንጀራና ዳቦ መብራት የለም በሚል ሰበብ ብቻ በጭማሪ ዋጋ እንደሚሸጡ ታዝበናል፡፡
ከሰሞኑ በኃይል እጥረት ሰበብ በእንጀራ ላይ አንድ ብር ዋጋ ሲጨምር ከመብራት ፈረቃው እወጃ ቀደም ብሎ ነዳጅ ጨመረና የጤፍ ዋጋ ተወደደ በሚል ሰበብ የአንድ ብር ጭማሪ ታክሏል፡፡ ስለዚህ ዛሬ በአማካይ አምስት ብር ይሸጥ የነበረ እንጀራ ስድስትና ሰባት ብር ሆኗል፡፡ ሌሎች ምርቶችም ዋጋቸው እጨመረ ሸማቾች በዋጋ ንረትና በኑሮ ውድነት እየፈተኑ ነው፡፡
ይህ በመብራት ጠፋ ሰበብ የተፈጠረው እጥረት ያስከተለው የዋጋ ዕድገት ደግሞ ነገ የኃይል አቅርቦቱ ቢስተካከል እንኳን ለመመለስ አስቸጋሪ ስለሚሆን ጉዳቱ የበዛ ይሆናል፡፡ ቅጥ ያጣው የዋጋ ግሽበት ከኃይል እጥረቱ ጋር ተደማምሮ ሸማቾችን የመፍትሔ ያለ እያሉ ነውና በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣውን የዋጋ ግሽበት በመቆጣጠሩ ረገድ ሊታሰብበት ይገባል፡፡