Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሥነ ልኬቱን ዓለም በመሠረታዊነት የለወጠው አዲስ ግኝት   

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዓለም የሥነ ልክ ቀን ሐሙስ ግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሲዘከር፣ የሥነ ልክን ሳይንስና ሥርዓት የቀረ አዲስ ግኝት ተዋውቋል፡፡

የዘንድሮው የዓለም የሥነ ልክ ቀን ‹‹የዓለም አቀፉ የልኬት አሐዶች ሥርዓት በመሠረታዊነት የተሻለ›› በሚል መሪ ቃል በዓለም ለ144ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ለ12ኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1875 የተፈረመውን የሜትር ወይም የልኬት ስምምነት ለመዘከር በየዓመቱ ግንቦት 12 ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሥነ ልክ ቀን ሆኖ ይከበራል፡፡ ኢትዮጵያም እ.ኤ.አ. በ1962 ስምምነቱን ተቀብላ ከኦገስት 31 ቀን 1963 ጀምሮ በአዋጅ ደንግጋ ሥራ ላይ አውላለች፡፡

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የልኬት ቀን እ.ኤ.እ. በኖቬምበር 16 ቀን 2018 በክብደትና ልኬት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ጠቅላላ ጉባዔ ሲካሄድ፣ በልኬት ላይ መሠረታዊ ለውጦች ለማድረግ ስምምነት በመደረሱ ለዓለም እንዲተዋወቅና ወደ ሥራ እንዲገባ የተመረጠበት ቀን ሆኗል፡፡

በልኬት ዘርፍ በመሠረታዊነት የተለወጠ የአለካክ መስኮች ሲኖሩ የዘንድሮው የልኬት ቀንም እ.ኤ.አ. ከ1869 ጀምሮ በሥራ ላይ የዋሉትን ክብደትን ይወስኑ የነበሩ የኪሎ ግራም ልኬት፣ የብረት ሲሊንደሮች ፕላንክ ኮንስታንት በመባል በሚታወቀው የኳንተም ብዛት መተካታቸውን አብስሯል፡፡

የልኬት ዓለም ብረቶችን ተጠቅሞ ክብደት ሲለካ በብረት ሲሊንደሩ ላይ በሚደረሰው መጫጫርና ሌሎችም እክሎች ሳቢያ ትክክለኛ ልኬት እንዳይመጣ የሚያደርጉ ፈታኝ ሁኔታዎች ሆነው ቆይተዋል፡፡ በልኬት ወይም በሚዛን የሚደረግ ማጭበርበር፣ በተለይም በተለምዶ ኪሎ ተብለው በየመደብሩ አገልግሎት የሚሰጡ የብረት ሚዛኖችም ‹‹ሰላቢ›› እየተባሉ ሸማች ያማርራሉ፡፡ ይህንን የሚለውጥ ሥርዓት ለዓለም ተዋውቋል፡፡ በኳንተም ብዛት የሚደረገው ልኬት ሆን ተብሎም ሆነ በአጋጣሚ በሚፈጸም ንክኪና ጭረት የሚፈጠረውን የልኬት ጉድለት ያስቀራል፡፡

ይህን የልኬት ለውጥ ባፀደቀው 26ተኛው የክብደትና ልኬቶች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የሙቀት፣ የኤሌክትሪክ ንዘረትና፣ የቁሶች መጠን መለኪያ የሆኑት ‹‹ኬልቪን››፣ ‹‹አምፒር›› እና ‹‹ሞል›› በተሰኙት ዓለም አቀፍ የክብደትና የመጠን መመዘኛዎች ዳግመኛ ልኬት እንዲሠራላቸው ተወስኗል፡፡

‹‹የሥነ ልክ መስፋፋትና ማደግ መንግሥት በታለመው የልማት አቅጣጫ መሠረት ሳይንስና ቴክኖሎጂ በአገራችን እንዲያድግና እንዲስፋፋ፣ ከገጠሯ ትንሽ መንደር እስከ ከተማው ያለው ኅብረተሰብ ዘመናዊ ልኬትን እንዲያስፋፋ፣ ኋላቀር የመለኪያ መሣሪያዎችን በአዳዲሶቹ እንዲተካ፣ ዘመናዊ ያመራረትና የግብይት ሥርዓት እንዲኖር ያደርጋል፤›› ሲሉ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ጥራትና ራጉላቶሪ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው በመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት ገልጸዋል፡፡

‹‹የአገራችን የጥራት መሠረት ልማት ለማስፋፋት የሥነ ልክ ኢንስቲትዩትም በተሻለ ሁኔታ እንዲደራጅ ተደርጓል፤›› ሲሉም አቶ እሸቴ አክለዋል፡፡

የዓለም የሥነ ልክ ቀንን ምክንያት በማድረግ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሥር ያሉ ተቋማትና ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ የፊዚክስ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሲሆኑ፣ ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበዋል፡፡

ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ካቀረቡት መካከል ፍራንዝ ሔንስበርገር (ዶ/ር) የብሔራዊ የሥነ ልክ ኢንስቲትዩት አማካሪ ሲሆኑ፣ አዲስ ስለተለወጡ የዓለም አቀፍ የልኬት አሐዶች እንዲሁም የዓለም አቀፍ የልኬት አሐዶች ታሪክ በሰፊው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሔንስበርገር (ዶ/ር) ማብራሪያቸውን የጀመሩት ከልኬት ታሪካዊ አመጣጥ ሲሆን፣ ድሮ ድሮ ርዝመት የሚለካው የሰውን አካል በመጠቀም እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይህ ልኬት የማያስቸግር ቢሆንም የሚስማማ ግን አልነበረም፡፡ ስለዚህ እንደ መፍትሔ የተወሰደው የንጉሡን ወይም የፈርኦኑን የሰውነት አካል በመጠቀም እንደ መለኪያ መውሰድ ነበር፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ እ.ኤ.አ. በ1983 የርዝመት ልኬትን ማለትም ሜትርን በ1/299,792,458 ሰከንድ ጊዜ ውስጥ በባዶ አየር ወይም ‹‹ቫክዩም›› አማካይነት የሚሄድ የብርሃን ርዝመት ነው በማለት ትርጉም እንደሰጡት አውስተዋል፡፡

ይህ የሜትር ትርጓሜ የረቀቀ መሆኑን አስረድተው፣ ለኪሎ ግራም ይኸው እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1793 ኪሎ ግራም ማለት የአንድ ሊትር ውኃ ክብደት እንደነበር ገልጸው፣ ይህ ግን አስቸጋሪ ነበር ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ግን ኪሎ ግራም የብረት ስብስብ ክብደት በማለት ልኬቱን ሰጥተውታል፡፡ ነገር ግን ይህም ትልቅ ችግር ነበረበት፣ ምክንያቱም ኪሎ ግራም የተገለጸው በቅርፅ ነበር፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር በዘላቂነት ይፈታል በተባለው ፕላንክ ኮንስታንት በመባል በሚታወቀው የኳንተም ብዛት ተተክቷል በማለት አብራርተዋል፡፡

በጥራት መሠረት ልማት መዋቅር ዓለም አቀፍ፣ አኅጉራዊና አገራዊ ደረጃ የሥነ ልክ ሚና በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት ደግሞ የብሔራዊ ሥነ ልክ ኢንስቲትዩት የጥራት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ፍቅረአብ ማርቆስ ናቸው፡፡

አቶ ፍቅረአብ ብሔራዊ የመሠረተ ልማት መዋቅር ጥራት በኢትዮጵያ እንዳያድግ ተፅዕኖ ያሳደረው ምንድነው እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ2017 የብሔራዊ የመሠረተ ልማት መዋቅር ምን ይመስል ነበር የሚለው ላይ ትኩረት አድርገው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ተፅዕኖ ያሳደረው ብቁ የሆነ የሰው ኃይል አለመኖር፣ ግልጽ ያልሆነ የመንግሥት ድጋፍ እንዲሁም የተገደበ የሰርቪስ ሽፋን ከተጠቀሱት መሀል ናቸው፡፡

ብሔራዊ የሥነ ልክ ኢንስቲትዩት በየካቲት 2003 ዓ.ም. ጀምሮ የተቋቋመ አገልግሎት ሰጪ መንግሥታዊ ተቋም ሲሆን፣ በወቅቱ ተጠሪነቱ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ቢሆንም ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሆኗል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች