ማንም ሰው ሕግ የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ ጋዜጠኛም ጭምር፡፡ ሕግ አስከባሪውም በተሻለ ደረጃ ላይ ሆኖ ሕግ የማክበር ኃላፊነትና ግዴታ አለበት፡፡ ሕግ ለማክበርም ሆነ ለማስከበር የሚያስፈልገው፣ በሕግ የበላይነት ሥር መሆን ነው፡፡ በዚህ ቁመና ላይ ሳይገኙ ሕግ ማክበርም ሆነ ማስከበር ቀልድ ይሆናል፡፡ ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን ያልተቀበለ ግለሰብም ሆነ ቡድን፣ ለሕግ ያለው አረዳድ የንቀት ይሆናል፡፡ በዚህ ዓይነት ነውጠኛ ስሜት የተሞሉ ጉልበተኞች በሕግ ስም ከንቱ ተግባራት እየፈጸሙ ብዙ ጥፋት አድርሰዋል፡፡ የአገርን መልካም ገጽታ አበላሽተው ንፁኃንን አሰቃይተዋል፡፡ ከዚያ ማጥ ውስጥ ለመውጣት ጥረት ሲደረግ የዚያኑ ዓይነት ችግር የሚያጋጥም ከሆነ፣ አሁንም ፈውስ ያልተገኘለት ደዌ ተፀናውቶናል ማለት ነው፡፡ ሐኪም፣ መምህር፣ ነጋዴ፣ መሐንዲስ፣ አርሶ አደር፣ ጋዜጠኛ ወይም በሌሎች ሙያዎች ተሰማርቶ መሥራት የተለየ አስተያየት ወይም አድልኦ ሳይኖር፣ በሕግ ፊት እኩል ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ሲያጠፉም የሚጠየቁት በሕግ አግባብ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ፍርድ ቤት ሲቀርቡም ሆነ ለምርመራ ሲፈለጉ ሕጉ በሚያዘው መንገድ ብቻ ነው ሒደቱ መከናወን ያለበት፡፡ ሕግ ለማስከበር ሲባል ሕግ መጣስ የለበትምና፡፡
ሰሞኑን ታስሮ የተፈታው የአሀዱ ሚዲያ ጋዜጠኛ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ለቀናት መቆየቱ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ጋዜጠኛው በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ከሚሠራበት ሥፍራ መወሰዱ ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ጋዜጠኛ ሲያጠፋ እንደ ማንኛውም ሰው መጠየቅ እንዳለበት ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ፖሊስ ወይም ዓቃቤ ሕግ ጠርቶት ቃሉን ሊቀበለው ይችላል፡፡ ፍርድ ቤት እስከሚቀርብ ድረስ ግን ሊታሰር አይገባም፡፡ የፍርድ ቤት መጥሪያ የያዘ ፖሊስም መጥሪያውን ሰጥቶት ይሄዳል እንጂ፣ በቁጥጥር ሥር ማዋል የለበትም፡፡ ፖሊስ ቃሉን እቀበላለሁ ቢል እንኳ በመታወቂያ ዋስ መልቀቅ ግዴታው ነው፡፡ ጋዜጠኛው ፍርድ ቤት ቀርቦ ተሟግቶ ከተረታ በኋላ የፍርድ ቤት ውሳኔ እንደ ማንም ሰው ተፈጻሚ ይሆንበታል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ይህንን ዓይነቱን ሥርዓት ሊፈጽም ባለመቻሉ ነው አገሪቱ የጋዜጠኞች እስር ቤት የሆነችው፡፡ አሁንም ያንን ዓይነት አሳዛኝ ድርጊት ሲፈጸምና ችግር ሲያጋጥም ፈር ማስያዝ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ጋዜጠኛው የፈለገውን ያህል ተሳስቷል ቢባል እንኳን የሚዳኘው በሕግ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ማዋከብ መብት መጋፋትና የበፊቱን ሰቆቃ በሌላ ገጽታ ማስቀጠል ነው የሚሆነው፡፡ ይህ ደግሞ ለማንም አልጠቀመም፡፡
ኢትዮጵያ ፀረ ሚዲያ ከሆኑ አፋኝ አገሮች ተርታ በግንባር ቀደምትነት ተሠልፋ፣ ለበርካታ ዓመታት ስሟ ጥቀርሻ ለብሶ ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ፣ ይህ የጎደፈ ስም እየታደሰ ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም አገሪቱ ደረጃዋን በ40 ነጥብ አሻሽላ በጎ ስሟ ሲወሳ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ እዚህ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን የተከበረው፣ የኢትዮጵያ ገጽታ ከፍተኛ ማሻሻል ስለተደረገበት እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ይህንን በጎና ተስፋ ሰጪ ጉዳይ እንደ ተራ ነገር ወደ ጎን በመወርወር ገጽታ ለማበላሸት መማሰን ያሳዝናል፡፡ አሁንም ደግመን ደጋግመን የምንለው በጋዜጠኝነት ጭምብል ወንጀል መሠራት የለበትም ነው፡፡ ተጠያቂነት መኖር አለበት፡፡ ነገር ግን በአግባቡ የተቀመጠ ሕጋዊ ሥርዓት እያለ ወከባ መፍጠር፣ ገጽታ ከማበላሸት አልፎ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ተስፋ በተጣለበት አገር ውስጥ አፋኝ አሠራሮችን ተግባራዊ እያደረጉ መውረግረግ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ያስገምታል እንጂ ለማንም አይጠቅምም፡፡
ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ የታሰሩና የተሰደዱ ጋዜጠኞች በብዛት ወደ ሥራ እየገቡ ነው፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙ፣ የሙያና የሥነ ምግባር እሴቶችን ይዞ እንዲሠራ ማገዝ ተገቢ ነው፡፡ ስህተት ሲፈጠርም በሕጉ መሠረት እንዲስተካከል ማድረግ ይገባል፡፡ ሙያው ከሌሎች ሙያዎች በበለጠ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚያገናኝና ለስህተት የተጋለጠ በመሆኑ፣ በተቻለ መጠን ሚዛናዊ ሥራዎች እንዲቀርቡ የበኩልን ድርሻ መወጣት የግድ ይሆናል፡፡ ጋዜጠኝነት የጎደለው እየተሟላና የተጣመመው እየተቃና የሚሠራበት በመሆኑ፣ እስከ ምን ድረስ ስህተት ሊኖር እንደሚችል መገንዘብ ይገባል፡፡ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭና ዜጎችም ድምፃቸውን በነፃነት የሚያሰሙበት እንዲሆን መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ እንዲያው በደፈናው ‹‹ጋዜጠኛ ለምን አይጠየቅም?›› ከማለት በፊት፣ ጋዜጠኞች የሚሠሩበት ምኅዳር የተመቻቸ እንዲሆን ማገዝ ተገቢ ነው፡፡ መረጃ ሲጠየቁ እንቢ የሚሉ የመንግሥት ተሿሚዎች በበዙበት አገር ውስጥ ‹‹አገኘሁህ!›› ዓይነት ውክቢያም መወገዝ አለበት፡፡ ጋዜጠኞችም ከአክቲቪስትነትና ከጥሬ አስተያየት ሰጪነት በመላቀቅ፣ ሙያው የሚፈልገውን ኃላፊነት በከፍተኛ ደረጃ የመወጣት ግዴታ አለባቸው፡፡ ሕግ ማክበር ማለት ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት ማለት ነው፡፡ ኃላፊነትን ሳይወጡ መብትን መጠየቅ እንደማይቻል ሁሉ፣ ለሚዲያ ነፃነት በሚመጥን ቁመና ላይ ለመገኘት ጥረት ማድረግ የግድ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ለመገኘት የሚለፉ ሚዲያዎችን ማገዝ ደግሞ የመንግሥትም የኅብረተሰቡም ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡
መንግሥት በሥሩ ያሉ ተቋማት ሕግ በማስከበር ስም ሕግ ሲጥሱ ከማንም በፊት የማስቆም ኃላፊነት አለበት፡፡ ሕግ አስከባሪ ተቋማትም ኃላፊነታቸውን መወጣት ያለባቸው ሕጉን በሚገባ ተረድተው ነው፡፡ በሕግ የሚጠየቅ ሰው ክብሩና መብቱ ተጠብቆ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት ሲሆን፣ የፍርድ ሒደቱ እስከሚያልቅ ድረስ እንደ ንፁህ ይቆጠራል የሚለው ሕጉ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ሰዎችን ሲይዙ ማዋከብና አካባቢውን በፖሊስ ኃይል ማስወረር፣ ከዚህ በፊት የተለመደ የተጠላ ተግባር ስለሆነ የባሰ ጥላቻ ነው የሚፈጥረው፡፡ በጋዜጠኝነት ደግሞ የተፈጠረ ስህተት ካለ ስህተቱ እንዲታረም ይደረጋል እንጂ፣ እየነዱ ወስዶ እስር ቤት ማጎር ከሕጉ ጋር ይጣረሳል፡፡ ስህተት የሥራው አካል እንደሆነ ሊታመን ይገባል፡፡ በወንጀል የተከሰሰን ጋዜጠኛ እንኳን ፖሊስ ሊያስረው ይቅርና ራሱ ፍርድ ቤት ነው በውጭ ሆኖ እንዲከራከር የሚፈቅድለት፡፡ ይህም በመገናኛ ብዙኃን ነፃነት አዋጅ ላይ የሠፈረ ድንጋጌ ነው፡፡ ሕግ አስከባሪ ተቋማት በዚህ መሠረት ሥራቸውን ሲያከናውኑ ሕጉ በሁሉም ወገኖች ይከበራል፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ድርጊት ቀደም ባሉት ዓመታት ኢትዮጵያን አንገት ያስደፋ፣ ልጆቿን ለመከራ የዳረገና መንግሥትን በሕገወጥነት ያስፈረጀ ነው፡፡ በቂም በቀል የተሞሉ ሰዎች የሚፈጽሙት እኩይ ድርጊት ነው፡፡ አሁንም ጋዜጠኛም ሆነ ማንኛውም ዜጋ በሕግ አግባብ ይስተናገድ፡፡ የሕግ የበላይነትን ማስከበር ተገቢ እንደሆነ ሁሉ፣ በዚህ ከለላ ሕገወጥ ድርጊት ሲፈጸም በፍጥነት መቆም አለበት፡፡ ቃሉን ሰጥቶ በመታወቂያ ዋስትና የሚለቀቅን ሰው በአሳቻ ሰዓት አስሮ አቧራ ማስነሳት የአገር ገጽታ ከማበላሸቱም በላይ፣ ለለውጥ የሚተጉትን ጭምር አንገት ያስደፋል፡፡ ሕግ ለማስከበር ሕግ አይጣስ!