በተመስገን ተጋፋው
ሃያ ዘጠኝ የኩላሊት ሕመምተኞች ንቅለ ተከላ እስኪያደርጉ ድረስ በቋሚነት ነፃ የኩላሊት እጥበት አገልግሎት በዘውዲቱ ሆስፒታል እንዲያገኙ መደረጉን የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሳሙኤል ይርጋ ገለጹ፡፡ የነፃ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ከተመረጡት መካከል ዘጠኙ የሕክምና ወጪያቸውን ለመሸፈን በየጎዳናው የሚለምኑ እንደሆኑ ታውቋል፡፡
ነፃ ሕክምና እንዲያገኙ የተመረጡት ሕሙማን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከጤና ቢሮ፣ እንዲሁም ኩላሊት ላይ የሚሠሩ ሐኪሞችና ድርጅቶች ይሁንታ የሰጡባቸው እንደሆነ ሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
‹‹ከራስ ቆርሶ ለራስ ማዋጣት›› በሚል መሪ ቃል ታዋቂ ግለሰቦች፣ አርቲስቶችና ከመንገድ ልመና ላይ የተነሱ ሕሙማኖች ባሉበት ግንቦት 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለጸው፣ በግል የሕክምና ተቋማት አንድ ዲያሊስስ (የኩላሊት እጥበት) ለማድረግ 4,500 ብር ይፍጅ የነበረው ከግል ክሊኒኮች ጋር በመነጋገር በአማካይ ወደ 1,350 ብር እንዲወርድ ማድረግ ተችሏል፡፡
በመንግሥት ሆስፒታሎች ላይም አንድ ዲያሊስስ እስከ 500 መቶ ብር እንደሚሰጥም ተነግሯል፡፡
የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ከ17 ባንኮችና ሌሎች አገር በቀል ድርጅቶች ጋር እየሠራ መሆኑም ታውቋል፡፡
‹‹ለሁሉም ባንኮች ደብዳቤ በመጻፍ የዲያሊስስ አካውንት ከፍተውልን ይኼን ዲያሊስስ አካውንት በየቅርንጫፋቸው እንዲያስተዋውቁልን አድርገናል›› የሚሉት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰሎሞን አሰፋ ናቸው፡፡ ከጤና ጥበቃ ጋር በመነጋገር የዲያሊስስ ታማሚዎች ሕክምናው እዚህ አገር እንዲሰጥ ያደረገው የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡
ከሁሉም ባንኮች ዘንድ ገንዘብ ቢገባም ገንዘቡን የሚለግሱት የባንኩ ሠራተኞች ይሁኑ ተጠቃሚዎች የሚለውን ያሳወቁ አምስት ባንኮች ብቻ እንደሆኑ፣ ሌሎች ባንኮች ግን ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳልሰጡ አቶ ሰሎሞን ተናግረዋል፡፡
ባንኮቹ 4,193 ሺሕ ቅርንጫፎች ያላቸው ሲሆን፣ በአጠቃላይ 100 ሺሕ የሆኑ ሠራተኞች ይገኛሉ፡፡ እያንዳንዱ ሠራተኛ በየወሩ 20 ብር ቢያስቆርጥ በወር ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ብር እንድናገኝ ያስችለናል በማለት ገልጸዋል፡፡
ከሞተ ሰው ኩላሊት መውሰድና ለሕሙማን መስጠት የሚያስችለውን የሕግ ማዕቀፍ ወጥቶ ብዙ የኩላሊት በሽተኞች የሚረዱበት ዕድል መፍጠር እንዲቻል በድርጅቱ ስም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡