Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምየተሬሳ ሜይ አወዳደቅ

የተሬሳ ሜይ አወዳደቅ

ቀን:

የብሪታንያ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በፈቃዳቸው ሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ፣ ለእንግሊዝ ሁለተኛዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ተሬሳ ሜይ፣ ሥልጣናቸውን ግንቦት 30 ቀን 2011 ዓ.ም. እንደሚያስረክቡ ያስታወቁት ባለፈው ዓርብ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 እንግሊዛውያኑ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት የደረሱትን ድምፀ ውሳኔ ለማስፈጸም፣ የብሪታንያ ከኅብረቱ መውጣት በስምምነት የታጠረ መሆን አለበት በሚል ኅብረቱ ባስቀመጠው ስምምነት ላይ ከኅብረቱ ጋር ድርድር ሲያደርጉና ፓርላማቸውን ሲወተውቱ የከረሙት ሜይ፣ ከፓርላማው ተቀባይነትን ባለማግኘታቸው ከፓርቲያቸው ኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ ለመልቀቃቸው ምክንያት ነው፡፡

እንግሊዛውያኑ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት ድምፀ ውሳኔ ባሳለፉ በወሩ ወደ ሥልጣን የመጡት ሜይ፣ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ያሳለፉት ብሪኤግዚት አጀንዳ ላይ ተጠምደው ነው፡፡

- Advertisement -

ሜይ እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት ስትወጣ ስምምነቶች መቀመጥ አለባቸው ካሉት ከአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት ጋር በተደጋጋሚ መክረውና ስምምነት ደርሰው በፓላርማቸው ለማፀደቅ የሄዱት ጉዞ ፍሬ አላፈራም፡፡ ቢቢሲ እንደሚለውም፣ ሐሳቡን ሦስት ጊዜ ያህል ፓርላማ አቅርበው ውድቅ ተደርጎባቸዋል፡፡

ብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት በስምምነት መታጠሯን የፓርቲያቸው አባላት ወግ አጥባቂዎቹ ብቻ ሳይሆኑ፣ የአውሮፓ ኅብረት የቀኝ እጅ የሆኑ ተቃዋሚዎችም አጣጥለውባቸዋል፡፡ ስምምነቱ ብሪታንያን ከአውሮፓ ኅብረት በቅርብ ያስተሳስራል ሲሉም ተችተዋል፡፡

የተሬሳ ሜይ አወዳደቅ

 

ሜይ በስንብት ንግግራቸው፣ ከአውሮፓ ኅብረት ጋር ሲደራደሩ የከረሙት ከጎረቤት አገሮች ጋር አዲስና መልካም ግንኙነት ለመፍጠር፤ የሥራን፣ የደኅንነትንና አብሮ የመኖርን ምኅዳር ለማስፋት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

‹‹የፓርላማ አባላትን በስምምነቶቹ ላይ ለማሳመን ለፍቻለሁ፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ግን አልተሳካልኝም፤›› ያሉት ሜይ፣ አገሪቷን በቀጣይ የሚመራት ጠቅላይ ሚኒስትር የአገሪቱን ፍላጎት ጠብቆ የተጀመረውን ጥረት ያስቀጥላል ብለዋል፡፡

ሜይ በኅብረቱ ባስቀመጨው የፍቺ መደራደሪያ አጀንዳዎች ላይ መክረው ስምምነቱ ይፈጸም ማለታቸው፤ ያለምንም ስምምነት ፍቺው መፈጸም አለበት ከሚሉት ጋር ተወዳድሮ በፓርላማቸው ውድቅ ቢደረግም፣ የንግዱ ማኅበረሰብና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ሥጋት ገብቷቸዋል፡፡ ብሪታኒያ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ትገባለች ሲሉም ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ብሪኤግዚትን ከመነሻው ሲቃወሙ የከረሙት የስኮትላንድ ተቀዳሚ ሚኒስትር ኒኮላ ስቱርጀን፣ ‹‹የሜይ ከሥልጣን መሸሽ የብሪኤግዚትን ዝብርቅርቅ አያስተካክለውም፡፡ ይልቁንም የበለጠ ጠንካራ ችግር ይገጥማል፡፡ ያለምንም ስምምነት ከአውሮፓ ኅብረት መውጣትም በጣም የሚያሳስብ ነው፤›› ሲሉ በትዊታቸው ማስፈራቸውን ቢቢሲ አክሏል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት የሜይን ስንብት አክብረው የብሪኤግዚት ስምምነት ላይ ዳግም ለድርድር እንደማይቀመጡ አሳውቀዋል፡፡ ‹‹ብሪታኒያ ከአውሮፓ ኀብረት በምትወጣበት ስምምነት ላይ አቋማችንን አስቀምጠናል፤›› ሲሉም የአውሮፓ ኅብረት ቃል አቀባይ ሚና አንድሪቫ ተናግረዋል፡፡

አንድሪቫ፣ ኅብረቱ ለሜይ ክብር እንዳለው አክለው ከሚመጣው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር የሚያሠራ ድባብ ለመፍጠር እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡

የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ መርከል ከብሪታንያ ጋር መልካም ግንኙነት ፈጥረው በትብብር እንደሚሠሩ ሲያሳውቁ፣ ከዚህ ቀደም ከሜይ በተቃራኒ የቆሙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ‹‹አዝኛለሁ›› ብለዋል፡፡

ሜይና የአውሮፓ ኅብረት ተደራድረው የደረሱት ስምምነት

 ሜይ ሥልጣን ከያዙ ማግሥት ጀምሮ ከአውሮፓ ኅብረት መሪዎች ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ የተቀመጡት ኅብረቱና ብሪታንያ ከፍቺው በኋላ እንዴት አብረው ሊሠሩ ይችላሉ በሚሉት ላይ ከስምምነት ለመድረስ ነበር፡፡

በዚህም ከሦስት ሚሊዮን የሚበልጡ የአወሮፓ ኅብረት ዜጎች በብሪታንያ እንዲሠሩ የሚፈቅድ ስምምነት ተደርሶ ነበር፡፡ በብሪታንያ ሥራ በመሥራት ላይ የሚገኙ የኅብረቱ አባል አገሮች ዜጎች መብት ተጠብቆ እዚያው የሚኖሩበት ሁኔታ መፍጠርም የስምምነቱ አካል ነው፡፡

ስምምነቱ በብሪታንያ የማይኖሩ ቤተሰቦች በብሪታንያ ካሉት ዘመዶቻቸው መልሰው የሚገናኙበትን ከማካተቱ በተጨማሪ፣ የአውሮፓ ኮርት ኦፍ ጀስቲስ (ኢሲጄ) በእንግሊዝ የሚኖሩ የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ዜጎችን ብሪታንያ ከኅብረቱ ከወጣች እስከ ስምንት ዓመት ድረስ መዳኘት እንደሚችል ይገኝበታል፡፡

ብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት ብትወጣም ለኅብረቱ የምትከፍለው የአባልነት ክፍያ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ማብቂያ እንዲቀጥል፣ ከኅብረቱ ስትወጣም 50 ቢሊዮን ፓውንድ መክፈል እንዳለባት ስምምነቱ ያትታል፡፡ ሌላ ቀድሞ ስምምነት ካልተደረሰ በስተቀር በብሪታንያና በአየርላንድ ድንበር አጠቃቀም ላይ የተደረሰውን ስምምነት ሙሉ ለሙሉ መተግበር ይጠበቅባታል የሚሉና ሌሎችም ከፍቺው ጋር ተያይዘው ተፈጸሚ መሆን ያለባቸው ስምምነቶች ላይ ነበር ሜይ ከኅብረቱ ተደራድረው ይዘው የቀረቡት የእንግሊዝ ፓርላማ ግን የሜይን ጥረት ውድቅ አድርጓል፡፡

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ ብሪታንያ ያለምንም ስምምነት ከአውሮፓ ኅብረት መውጣቷ የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ኪሳራ ያደርስባታል፡፡ ሜይ ሲታገሉ የቆዩትም የእንግሊዝ ዜጎች ጉልህ የሚባል ችግር ሳይገጥማቸው ከመነጣጠል በኋላም ከአውሮፓ አገሮች ጋር በሰላም የሚኖሩበትን ለማመቻቸት ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ጥረታቸው አለመሳካቱ ከሥልጣን ለመውረዳቸው ምክንያት ሆኗል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...