Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየግዕዝ መጻሕፍት ምንጭ በአገራዊ ቋንቋ

የግዕዝ መጻሕፍት ምንጭ በአገራዊ ቋንቋ

ቀን:

‹‹ስለ ኢትዮጵያ ጥናት የሚያደርጉ ተመራማሪዎች በአብዛኛው የሚጽፉት በእንግሊዝኛና በሌሎች የአውሮፓ ቋንቋዎች እንጂ አገሬው በሚረዳው ቋንቋ ስላልሆነ ባለጉዳዩ ሕዝብ በኢትዮጵያ ጥናት ጉዳይ ባይተዋር ሆኖ ይታያል፡፡ ከአሁን በፊት በጣም ጥቂት ሥራዎች በአማርኛ ቀርበዋል፣ ሆኖም ይዘዋቸውም ትኩረታቸውም የተለያየ ሲሆን ያካተቷቸው ጉዳዮችም ውሱንነት ይታይባቸዋል፡፡ የዚህ መጽሐፍ አንደኛው ዓላማ የኢትዮጵያ ጥናት መስክን በአማርኛ ለመረዳትና ምርምር ለማድረግ እንዲያግዝ በማለት ነው፡፡››

ይህ አንቀጽ መሰንበቻውን የኅትመት ብርሃን ባየው ‹‹ነቅዐ መጻሕፍት ከ600 በላይ በግዕዝ የተጻፉ ኢትዮጵያ መጻሕፍት ዝርዝር ከማብራሪያ ጋር›› የሚለውን መጽሐፋቸውን ለመጻፍ ያነሳሳቸውን ምክንያት አዘጋጁ ቀሲስ አምሳሉ ተፈራ (ዶ/ር) የገለጹበት ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥንታውያን ጽሑፎች ጥናት (ፊሎሎጂ) ረዳት ፕሮፌሰር ሆነው በማስተማርና በምርምር ላይ የሚገኙት ቀሲስ አምሳሉ፣ በትምህርት በቆዩባቸው በጣልያንና በጀርመን፣ እንዲሁም ጥናትና ምርምር ባደረጉባቸው ዩናይትድ ኪንግደምና የተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ከሚኖሩ ምዕመናን ስለ ግዕዝ ሥነ ጽሑፍ ይቀርብላቸው የነበሩ ተደጋጋሚ ጥያቄዎችም ለመጽሐፉ መዘጋጀት ሌላኛው መንስኤ ናቸው፡፡ ከጥያቄዎቹ ዋና ዋናዎቹ ‹‹ስለመጽሐፈ ሔኖክና ኩፋሌ እንዲሁም ስለ ግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ማወቅ እንችላለን?››፣ ‹‹ከኢትዮጵያ የተዘረፉ ቅርሶችና የብርና መጻሕፍት የት የት ይገኛሉ?››፣ ‹‹የኢትዮጵያ ትርጓሜና የአንድምታ ታሪክ››፣ ‹‹ምን ያህል ገድላት በግዕዝ ይገኛሉ?››፣ ‹‹የግዕዝ ገድላትንና ድርሳናት ታሪክ እንዴት ማወቅ እንችላለን?›› ወዘተ . . . ለሚሉት ቁልፍ ጥያቄዎች መጽሐፉ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአምስት ዐበይት ምዕራፎች የተደራጀው ነቅዐ መጻሕፍት (የመጻሕፍት ምንጭ) ይዞታ የኢትዮጵያን የጽሑፍና መጻሕፍት ታሪክ፣ የአንድምታ ትርጓሜ፣ የገድል መጻሕፍት ዝርዝርና ማብራሪያ ድርሳናትና ሌሎች የትምህርት መጻሕፍትን ከመግለጹ ባሻገር የተብራሩ መጻሕፍትም ይገኙበታል፡፡ ከነዚህም መካከል ስለ ቅዱስ ያሬድ መጻሕፍት የሚሉት፣ በ”ራእየ ማርያም” የ1961 ዓ.ም. የአማርኛ ትርጉም ውስጥ አሉ የተባሉት ብሔር ተኮር ቃላት ከግዕዙ እና ከሌሎች የአማርኛ ትርጉሞች ጋር በማስተያየት ያነሷቸው ነጥቦች ይገኙባቸዋል፡፡ እንዲሁም ከውጭ ደራስያን ከኤፍሬም ሶርያዊ ሥራዎች በጥቂቱ ሲጠቀሱ፣ የመወድስ ቅኔ በጥንት አማርኛ ምንነቱና ይዘቱም ተብራርቷል፡፡

በትርጓሜያት ክፍሉ የግዕዝ መጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሒደት፣ ክፍሎቹና ልዩ ልዩ ኅትመቶች፣ የግዕዝ በግዕዝ ትርጓሜ፣ እንዲሁም የአንድምታ ትርጓሜ የተዘጋጀላቸው መጻሕፍት፣ ስለ ሰማንያ አንዱ ቅዱሳት መጻሕፍት መግለጫና ማብራሪያ ቀርቦበታል፡፡

ገድል ከተጻፈላቸው መካከል በቅድስናቸው የሚታወቁት ነገሥታት አብርሃአጽብሐ፣  ካሌብ፣ ላሊበላ፣ ነአኩቶ ለአብ፣ መስቀል ክብራ (የላሊበላ ባለቤት) ገላውዴዎስ፣ ታላቁ ኢያሱ አድያም ሰገድ ይጠቀሳሉ፡፡ ከሊቃውንትም ገድል የተጻፈላቸው ቅዱስ ያሬድና አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንደሚገኙበት መጽሐፉ ያሳያል።

ኢትዮጵያ በዘመናት የዳበረ የጽሑፍ ባለቤት መሆኗን የሚያስረዱት ረዳት ፕሮፌሰር አምሳሉ (ዶ/ር)፣ አንዳንድ የውጭ አገር ጸሐፊዎች የኢትዮጵያ ጽሑፎች በሙሉ ከውጭ የተመለሱ ትርጉሞች ናቸው እንጂ ብሔራዊ ሥራ የላቸውም የሚለውን አስተሳሰብ የተዛባና ከእውነት የራቀ ነው በማለት በማስረጃ ይሞግታሉ፡፡

ለዚህም ማሳያ እንዲሆን ከስድስተኛው እስከ 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዝናቸው የጎላውን ዋና ዋና ኢትዮጵያውያን ጸሐፊዎችን ከነሥራዎቻቸው እንዲህ ዘርዝረዋል፡፡ እነርሱም ቅዱስ ያሬድ ማኅሌታዊ፣ ርቱዕ ሃይማኖት፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ፣ አርከ ሥሉስ፣ አባ ባሕርይ፣ እጨጌ ዕንባቆም፣ አዛዥ ጌራና አዛዥ ራጉኤል፣ ስብሐት ለአብ ዘጎንደር፣ አፄ ናዖድ፣ ዐፄ በእደ ማርያም፣ ዐፄ ልብነ ድንግል፣ እንዲሁም የዜና መዋዕልና የታሪከ ነገሥት ጸሓፊዎችም ተጠቅሰዋል፡፡    

የብራና መጻሕፍት ከአገር ውጪ የሚገኙባቸው አገሮች ከነቁጥራቸው በመጽሐፋቸው እንዲህ ገልጸዋቸዋል፡፡ በፈረንሳይ 1050፣ በእንግሊዝ 618፣ በጀርመን ከ931 በላይ፣ በጣሊያን ከ1292 በላይ፣ በኢየሩሳሌም 871፣ በአሜሪካ 1080፣ በስዊድን ከ134 በላይ፣ በኦስትሪያ 50፣ በቤልጂየም 41፣ በዴንማርክ 5፣ በካናዳ 14፣ በግብፅ 30፣ በፊንላንድ 6፣ በሩሲያ 118፣ በአየርላንድ 76፣ በኖርዌ 50፣ በኔዘርላንድስ 220፣ በፖላንድ 25፣ ኒውዚላንድ ከ3 በላይ፣ እና በስፔን 3 ይገኛሉ።

ስለ ቀሲስ አምሳሉ (ዶ/ር) ነቅዐ መጻሕፍት ታላቅነት ምስክርነት የሰጡት ሥነ ጽሑፍ ሊቅነታቸው የሚታወቁት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ናቸው፡፡ በጻፉት ቀዳሚ ቃል እንደገለጹት፡- ኢትዮጵያ ታሪክ መምህራንና ተመራማሪዎች ኢትዮጵያ ጥንታዊት አገር ናት ሲሉ በዋና ማስረጃነት የሚሰጡት አገሪቱ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የጽሕፈት በትውፊት እንደነበራትና የጥንቶቹ ጽሑፎቹ በድንጋይ ተቀርፀው፣  በብራና ላይ ተጽፎ መገኘታቸው መሆኑን የዶ/ር ቀሲስ አምሳሉ ተፈራ ነቅዐ መጻሕፍት ያስተምራል፡፡

 ፕሮፌሰር ኤኖ ሊትማን የዛሬ መቶ ዓመት ግድም፣ የግዕዝን ሥነ ጽሑፍ ታሪክ መሠረት ሲጥል፣ ጽሑፉን የጀመረው፣ ‹‹በግዕዝ መጻሕፍት ላይ የሚደረገው ምርምር ገና ብዙ ርቆ ስላልሄደ፣ በአሁኑ ሰዓት አስተማማኝ የሆነ የግዕዝን ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ለማጻፍ አይቻልም›› ብሎ እንደ ነበር ያስታወሱት፡፡

ከሊትማን ድርሰት በኋላ የተደረገው ምርምር የተሟላ ባይሆንም፣ የዶ/ር ቀሲስ አምሳሉ ተፈራ የዛሬው አስተዋጽኦው እንደሚመሰክረው፣ በተጨባጭ ልዩነት አምጥቷል፡፡ አምሳሉ ምርምሮቹን መርምሯቸዋል፡፡ የምርምር መሠረት የሆኑትንና ገና ያልተመረመሩትን መጻሕፍት ያውቃቸዋል፡፡ በአካልና በምስል የተከማቹትን ነቅዐ መጻሕፍት ውስጥ በጥንቃቄና በዝርዝር አቅርቧቸዋል፡፡ የት እንደሚገኙም አድራሻቸውን ነግሮናል፡፡ አንዳንዶቹንም ካሉበት ቦታ ድረስ ሄዶ ለምርመራ የሚያስፈልገውን ያህል አብሯቸው ቆይቷል፡፡ በእንግሊዝ፣ በፈረንሣይ፣ በኢጣልያ፣ በጀርመን ያሉትን መጻሕፍት በእጁ አገላብጧቸው፣ ልናውቃቸው ይገባል ያላቸውን ቦጭቆላቸዋል፡፡ ሰው አገር ምን እግር እንደጣላቸው (ተፈንግለው፣ ተጠልፈው፣ ተዘርፈው፣ ተገዝተው)፣ ታሪካቸውን ለመከታተል በሚያጓጓ አጻጻፍ መዝግቦልናል፤›› ሲሉ ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...