Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ዓለም የደረሰበትን የሕክምና መሣሪያ በማስገባት ሕሙማንን ከስቃይ ማስታገስ አለብን››

አቶ መክብብ ነጋሽ፣ የደብሊው ኤም ጂ ሥራ አስኪያጅ

ደብሊው ኤምጂ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ከአሥር ዓመት በፊት የተመሠረተው፣ በጤና ዘርፍ በተለይም በሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦትም ሆነ ከገቡ በኋላ ለሚገጥሙ ብልሽቶች መፍትሔ ለመስጠት ነው፡፡ ከውጭ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎችን ለማስመጣትና ለተበላሹ ጥገና ለመስጠት የተቋቋመው ድርጅቱ፣ የካንሰር ሕክምናን ከእንጭጩ ለማወቅና ለማከም የሚያስችል መሣሪያ ለማስገባትም በቻይና መንግሥት የሚተዳደረው አይስቶፕ ኮርፐሬሽንና የግል ኩባንያው ኒዮሶፍት ከጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር የመግባቢያ ሰነድ እንዲፈራረሙ አመቻችቷል፡፡ አቶ መክብብ ነጋሽ የደብሊው ኤም ጂ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በድርጅቱ ሥራ ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ለግል ባለሀብት የሕክምና መሣሪያዎችን ማስገባት በተለይ እናንተ በጀመራችሁበት ጊዜ ከባድ ነበር፡፡ ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግም ይህንንም ያህል ትኩረት አልነበረውም፡፡ በዚህ ውስጥ እንዴት መሥራት ቻላችሁ?

አቶ መክብብ፡- የባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ በመንግሥት ትኩረት ያገኘውና በትምህርት ፖሊሲው ትኩረት የተሰጠው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሜካኒካል ኤሌክትሪካል ኢንጂነሮችችና ከኮምፒውተር ሳይንስ የወጡ ባለሙያዎች ነበር በተደራቢ የሚሠሩት፡፡ መንግሥት የተማረውን የሰው ኃይል ከገበያው ጋር ለማቀናጀት በጀመረው ሥራ ዘርፎች በመለየታቸው፤ ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ፣ ባዮሎጂንና ሜዲካል ሳይንስን፣ ሜካኒካል ኢንጂነሪንግንና ኤሌክትሮኒክስን አካቶ የባዮሜዲካል ኢንጂነሪነግ ዘርፍ በመጀመርያና በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ነው፡፡ አዲስ አበባ፣ ጎንደርና ጅማ ዩኒቨርሲቲዎችም ትምህርቱን እየሰጡና ባለሙያዎች እያስመረቁ ነው፡፡ ተግባረዕድ ደግሞ ቴክኒሻኖችን እያፈራ ነው፡፡ ዘርፉ ከዚህ ቀደም የተረሳ ነበር፡፡ በድርብ ነበር የሚሠራው፡፡ የአገሪቱ ሕክምና ሣይንስ ከዕለት ዕለት እያደገ ሲመጣ፣ ሙያው ገፍቶ ያወጣው እንጂ በጥናት ተደግፎ የወጣም አይደለም፡፡ ምክንያቱም አገልግሎቱ ሊቀጥል አልቻለም፡፡ የሕክምና መሣሪያዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሲቆሙ በአብዛኛው የሚጠገኑት ከውጭ በሚመጡ ባለሙያዎች ነው፡፡ ይህ በብዙ ምክንያቶች የሚያስኬድ አልነበረም፡፡ ይህንን ለመቅረፍ ሲባል ነው ጤና ሚኒስቴርና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወያይተው ዘርፍ እንዲከፈት የተደረገው፡፡

ሪፖርተር፡- የባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ዘርፍ ከተከፈተ በኋላ መሻሻል አለ?

አቶ መክብብ፡- ይህ ሣይንስ ከተከፈተ በኋላ የሕክምና መሣሪያዎች ጥገና አገልግሎት የተሻለ ደረጃ ላይ ነው፡፡ ትልቁ ችግር የሕክምና መሣሪያዎች በበቂ ደረጃ አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸው ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ አገር ውስጥ የሚሰጡ ሥልጠናዎች ንድፈ ሐሳብ ላይ ከማተኮር ባለፈ ተማሪዎችን ወደ ውጭ ልኮ ማስተማሩ ላይ ትኩረት ስለሌለ ነው፡፡ በግል ዘርፍ በኩል ሲታይ አቅራቢ እንደመሆናችን በሸጥነው ማሽን ላይ ለባለሙያዎች ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ የማሽኖች ብልሽት ከሠልጣኞች አቅም በላይ ሲሆን ሻጩ ኩባንያ በገባው የዋስትና መሠረት ይሠራል፡፡ በመሆኑም በእኛ በኩል የተገዙ የሕክምና ማሽኖች በባለሙያ እጥረት ምክንያት ችግር የሚገጥማቸው አይደሉም፡፡ ትልቁ ችግር የሆነብን አገሪቱ ለጤና ቅድሚያ ሰጥታ የውጭ ምንዛሪ ብታቀርብም፣ ገንዘቡ ያተኮረው መድኃኒት ላይ መሆኑ ነው፡፡ መድኃኒት ላይ ማተኮር ብቻውን ውጤታማ አያደርግም፡፡ ሰው መድኃኒት መጠቀም የሚችለውም ተመርምሮ በሽታው ሲታወቅ ነው፡፡ ለምርመራው የሕክምና መሣሪያዎች ኖረው ሐኪሙ መርዳት ሲችል ብቻ ነው ታማሚ መድኃኒት ሊወስድ የሚችለው፡፡ ይህ እየተፈጸመ ግን አይደለም፡፡ ለምሳሌ ድርጅታችን የሕክምና ቁሳቁስ መለዋወጫ ለማስመጣት የውጭ ምንዛሪ ችግር አለበት፡፡ መንግሥት በፖሊስ ደረጃ ለጤናው ዘርፍ ቅድሚያ ቢልም፣ ለሕክምና መሣሪያዎች ትኩረት አልተሰጠም፡፡ የሕክምና መሣሪያዎች አስመጪ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ለዶላር ይሠለፋል፡፡ ሆኖም የሕክምና መሣሪያዎች እንደ መድኃኒት ተቆጥረው ቅድሚያ ሊሰጣቸውና ሊደገፉ ይገባል፡፡ ሥልጠናን በተመለከተ በአገር ውስጥ ከሚሰጠው ሥልጠና በተጨማሪ ድርጅታችን ውጭ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ትላልቅ የሕክምና ማሽኖች የሚገዙ ሲመጡ፣ የገዛው አካል ባለሙያዎች ውጭ ሄደው የሚሠለጥኑበትን እያመቻቸን እየሠራን ነው፡፡ በቅርቡ ኢትዮጵያ ለማስገባት ላቀድነው ፔት ሲቲ ማሽን (የካንሰር ሕክምና መስጫ) የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የራዲዮሎጂ ባለሙያዎች ቻይና ሄደው እንዲሠለጥኑ አድርገናል፡፡ የፔት ሲት ማሽን ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢገባ በተለይ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል ሕክምና ማግኘት ይችላል፡፡ ሕክምናው በአገር ውስጥ የሌለና በውጭውም ዓለም ውድ በመሆኑ ብዙዎች የቴክኖሎጂው ቱሩፋት አልደረሳቸውም፡፡ አንድ የካንሰር ታማሚ በፔት ሲቲ ማሽን ታይቶ ለመታከም በትንሹ ስምንት ሺሕ ዶላር መክፈል አለበት፡፡ ይህ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚሆን አይደለም፡፡ በመሆኑም ማሽኑ ኢትዮጵያ ቢገባ ምንም እንኳን ማሽኑ ኑክሌር ቴክኖሎጂ የሚጠቀምና ውድ ቢሆንም፣ በአገር ውስጥ ውጭ ካለው ዋጋ ከግማሽ ባነሰ አገልግሎቱን መስጠት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ፔት ማሽኑን ከማስመጣት ቀድሞ ማሽኑ ለሚያክምበትን መድኃኒት ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ ማሽኑ በሌለበት መድኃኒቱ ሊሠራ አይችልም፡፡ በመሆኑም እዚህ ላይ ግንዛቤ እየፈጠርን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፔት ሲቲ ማሽንን ወደ ኢትዮጵያ የማስገባቱ ሒደት ምን ደረጃ ደርሷል?

አቶ መክብብ፡- ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረምም አንድ እመርታ ነው፡፡ የቻይና መንግሥት አይሶቶፕ ኤንድ ራዲየሽን ኮርፖሬሽን ኃላፊዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመሥራት ፈቃደኝነታቸውን በመግለጽ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር ተፈራርመዋል፡፡ ሆስፒታሉ የካንሰር ሕክምና ማዕከል ቢኖረውም፣ ዕድገቱ ዓለም የደረሰበት አይደለም፡፡ ድርጅታችን የቻይና መንግሥት የጤናው ዘርፍና ጤና ሚኒስቴር አብረው እንዲሠሩ እየሠራ ነው፡፡ ኅብረተሰቡም በሚቻለው ወይም ጥቂት ተጎድቶ ከፍሎ የሚታከምበትን እያመቻቸን ነው፡፡ ኅብረተሰቡም ይጠቀማል፣ የጤናው ዘርፍ ያድጋል እኛም እንጠቀማለን፡፡

ሪፖርተር፡- ፔት ሲቲ ማሽንን ኢትዮጵያ ለማስገባት ያለው ፍላጎት ምን ይመስላል?

አቶ መክብብ፡- በፔት ሲት ማሽን የሚደረግ ሕክምናን አገር ውስጥ ማስገባት ከውጭ ሲታይ ከባድና የማይቻል ይመስላል፡፡ በአፍሪካ ግብፅ አላት፡፡ ኬንያ በሒደት ላይ ስትሆን አሜሪካ ከአራት ሺሕ በላይ አላት፡፡ በአምራቿ ቻይናና ባደጉ አገሮች ማሽኑ አለ፡፡ በአገራችን ባይኖርም መንግሥት በብዛት ለማምጣት ሐሳቡ አለው፡፡ በተለይ ማሽኑ የሚያክምበትን መድኃኒት የማምረት ሥራው መንግሥት በሰፊው ጀምሮታል፡፡ ትልቅ ሣይንስ የሚፈልግም ነው፡፡ ፔት ማሽን ከሌሎቹ የሚለየው በሽታው እንደጀመረ ማወቅ ስለሚያስችል ነው፡፡ በሽታው ስለመኖሩ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ያለበትን ቦታ ይለያል፣ እዛው የማከም አቅምም አለው፡፡ የእኛ ጥያቄ እንዲህ አቅም ያለው መሣሪያ አገር ውስጥ ይግባ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ደብሊው ኤምጂ በሕክምናው ዘርፍ ያለው አስተዋጽኦ ምን ይመስላል?

አቶ መክብብ፡- የባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ በተሻለ መጠን እያደገ እንዲሄድ እየሠራን ነው፡፡ በፔት ማሽን ብቻ ሳይሆን ከካንሰር ባለፈም ለሌሎች ሕክምናዎች የሚያገለግሉና ዓለም የደረሰባቸው የሕክምና መሣሪያዎች እንዲገቡ እየሠራን ነው፡፡ ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር አብሮ በመሥራት ሕክምና ዘርፍ እንዲያድግ እንሠራለን፡፡ የድርጅቱ ባለቤት አቶ ምኒልክ አጋ ባዮሜዲካል ኢንጂነሪንግ ላይ ስፔሻላይዝ ያደረጉ ስለሆኑና ብዙ ዓመትም በዘርፉ ስለሠሩ ያለውን ክፍተት ያውቁታል፡፡ ስለሆነም በሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦትና ጥገና ላይ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የባዮሜዲካል ኢንጂነሮች እጥረት በአገሪቱ አለ፡፡ ድርጅታችሁ የሕክምና መሣሪያዎችን ከማስመጣት ባለፈ እዚህ ላይ ምን ይሠራል?

አቶ መክብብ፡- የሆስፒታል ዕቃዎችን እናስመጣለን፡፡ በማሽኖቹ ላይ ሥልጠና ብሎም የጥገና አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ ከምናስመጣቸው ዕቃዎች ውስጥ በባለሙያ እጥረት ምክንያት ከአገልግሎት የተስተጓጎለ የለም፡፡ ትልቁ ክፍተትና መንግሥት ማሰብ ያለበት የሆስፒታል ዕቃዎች ጥገናን ሌሎች እንዲሠሩት ወይም አቅራቢዎቹ እንዲጠግኑ ማድረግ ላይ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ መንግሥት ብቻውን የአገሪቱን ጤና ሽፋን ሊደርስ አይችልም፡፡ ኤክስሬይ ማሽን በመንግሥት ሆስፒታል ከተበላሸ ሕሙማን ውጪ ተነስተው እንዲያመጡ ይጠይቃሉ፡፡ ነው የሚባለው፡፡ ሆኖም መንግሥት ማሽኑን ከገዛበት አካል ጋር የጥገና ስምምነት ውል ቢገባ ችግሩን መቅረፍ ይቻላል፡፡ በእርግጥ መንግሥት እዚህ ላይ አቅጣጫ ይዟል፡፡ እኛም የምንደግፈው ነው፡፡ የጤናውን ዘርፍ ለማዘመን መንግሥት ከሚገዛቸው ማሽኖች ጎን ለጎን አገልግሎቱ ሳይቆራረጥ ለማስቀጠል የፖሊሲ አቅጣጫ ሊያስቀምጥ፣ ያስቀመጠውን ፖሊሲ መሬት አውርዶ ሊተገብር ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ የሕክምና መሣሪያዎች ማጉረፍ ብቻውን ትክክል አይመስለኝም፡፡ በመንግሥት የተገዙ የሕክምና መሣሪያዎች የት ናቸው? አገልግሎት እየሰጡ ነው ወይ? ምን ያህሉ ተበላሽተዋል፣ መጠገን የሚችሉትና የማይችሉት ተለይተዋል ወይ? ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች መሣሪያ ተሟልቶ ነው ወይ የተከፈቱት፣ የሚሉት መታየት አለባቸው፡፡ መንግሥት ታች ወርዶ ማየት አለበት፡፡ የጤናው ዘርፍ በግልም ተያዘ፣ በመንግሥት ማኅበራዊ አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ በመሆኑም ንግድ ሆኖ ሰው እንዳይበዘበዝ ሕክምናም ሆነ የሕክምና መሣሪያዎች እንደታለመላቸው እየሄዱ መሆኑን መቆጣጠር ግድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በድርጅቱ በኩል አቅርቦቱን ለማስፋት ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ መክብብ፡- ብዙ ገዥዎች አሉን፡፡ ሥራችንን ክልል ድረስ እያሰፋን ነው፡፡ ድሬዳዋ ላይ አንድ ሆስፒታል በጋራ ለመሥራትና ሥራችንን ለማስፋት ዕቅድ አለን፡፡ የራሳችን ዳያግኖስቲክ ሴንተር እንዲኖረን እየሠራን ነው፡፡ ሞዴል ሆስፒታሎች ለመሥራት አቅደን ድሬዳዋ ላይ ኸርት ሆስፒታል የሚል በጋራ እየገነባን ነው፡፡ በእኛ በኩል ኢሜጂንግ ዳያግኖስቲክ ማዕከሎች እንዲያድግ እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- የሕክምና መሣሪያዎች በተለይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመለየትም ሆነ ለማከም የሚያስችሉ ማሽኖች ትልቅ የኤሌክትሪክ አቅም የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በኃይል አቅርቦት እጥረት ምክንያት የሕክምና መሣሪያዎች አገልግሎት ሲያቋርጡ ይስተዋላል፡፡ የሕክምና መሣሪያዎችን ስታቀርቡ ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት እንደሚያስፈልግ ታሳውቃላችሁ?

አቶ መክብብ፡- አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ኃይል የመቆጠብ፣ ብክለት የመቀነስ፣ ሁኔታ አላቸው፡፡ የኃይል አቅርቦትን በተመለከተ አንዳንድ ሆስፒታሎች ትልልቅ የሕክምና መሣሪያዎችን መሸከም የሚችል የኃይል አቅርቦት የላቸውም፡፡ መሣሪያ ልንገጥም ሄደን ስሪ ፊዝ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የሌለው ሆስፒታል አጋጥሞናል፡፡ ሆስፒታል ሲገነባ ጀምሮ መንግሥት ለኃይል አቅርቦት ትኩረት መስጠት አለበት፡፡ አንዳንዱ ታች ፈጻሚው ጋር ያለ ችግር ሲሆን፣ ከመሠረተ ልማት መጓደል ጋር የተያያዘም አለ፡፡ ሆፒታሎች የሚገነቡበት ቦታ የኃይል አቅርቦቱን ለማድረስ ከፍተኛ ወጪ የጠይቅ ሊሆንም ይችላል፡፡ ስለዚህ ከአዋጪነት ጥናት ጀምሮ የሆስፒታል ቦታዎችን መምረጥም ሆነ ስለሚሰጠው አገልግሎትና መሟላት ስላለበት ቀድሞ መለየት አለበት፡፡ ለሕክምና ቅድሚ ይሰጣል ቢባልም፣ ሲፈጸም አይታይም፡፡ የጤናን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ያለው ጤና ሚኒስቴር ብቻውን መሆኑም ሌላ ችግር ነው፡፡ ሌሎች ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች የጤናውን ዘርፍ ሥራዬ ብለው ከሥራቸው ጋር ማቀናጀት አለባቸው፡፡ በየትኛውም ዘርፍ ምርታማነት በቀጥታ የሚገናኘው ከጤናማ ማኅበረሰብ ጋር ነው፡፡ በፖሊሲና በአቅጣጫ ደረጃ ችግር ባይኖርም፣ ተቀናጅቶ መሥራት ላይ ችግር አለ፡፡ ወደ ኃይል አቅርቦቱ ስንመጣ መንግሥት ስለጤና ተቋማት ሲያቅድ ቀድሞ የኃይል አቅርቦቱ ላይ መፍትሔ ማበጀት አለበት፡፡ እኛም የምንመክረው ከግንባታ ጀምሮ የሕክምና መሣሪያዎችን ሊሸከሙ የሚችሉ አሠራሮች እንዲዘረጉ ነው፡፡ ትልልቅ ሆስፒታል ላይ የኃይል አቅርቦት ችግር አለ ብሎ መናገሩ በራሱ እንደ መንግሥት የሚሳፍር ነው፡፡ ሆስፒታሎችን በተመለከተ ውሳኔ መስጠት ግድ ነው፡፡ የሰው ሕይወት ለማዳን እስከሆነ ድረስ ጄኔሬተር ያስፈልጋል ብሎ መወሰንም አማራጭ ነው፡፡ ተጠያቂነት በመሸሽ ችግሮችን ሳይፈቱ መቆየቱ አግባብ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙዎቹ የሕክምና ማሽኖች ጨረር አመንጪ በመሆናቸው ግንባታዎችን በተመለከተ ግንዛቤ ትፈጥራላችሁ?

አቶ መክብብ፡- የጨረር ባለሥልጣንን ጨረር አመንጪ መሣሪያዎች ከመግባታቸው በፊት ጀምሮ መረጃው አለው፡፡ ማሽኑ የተከለከለ ይሁን አይሁን አይቶ ፈቃድ የሚሰጠውም ባለሥልጣኑ ነው፡፡ የምንሸጣቸውን ማሽኖች አስመልክቶ ከመሸጣችን በፊት ገዥው ከባለሥልጣኑ ፈቃድ ያለው መሆኑን አረጋግጠን ነው፡፡ ዝቅተኛ ወይም ከፍተኛ ጨረር የሚያመነጩ አሉ፡፡ እንደ ፔት ማሽን የመሳሰሉ የካንሰር ሕክምና መስጫዎች የግድግዳቸው መጠን አንድ ሜትር ከ50 ውፍረት ባለው ክፍል ውስጥ የሚቀመጡና በጣም ጥንቃቄ የሚፈልጉ ቴክኖሎጂዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ማሽኖች ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልጉና፣ በሳይንሳዊ መንገድ ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው፡፡ እኛ ማሽኖች ስናመጣም ሆነ ስንተክል ሳይንሱ ባስቀመጣቸው መሥፈርቶች መሠረት ነው፡፡ ዕቃውን ከመግጠማችን በፊትም ገዥው ለሕክምና ማሽኑ የሚመጥንና መሥፈርቱንና ደረጃውን የሚያሟላ ክፍል እንዲዘጋጁ እናደርጋለን፡፡ እንደ ፔት ያሉ አዳዲስ ማሽኖች ሲሆኑ ደግሞ ዓለም አቀፍ መሥፈርት ተከትልን ቅድመ ሁኔታ እንዲመቻች ለጠየቁን የመንግሥት አካላት ግንዛቤ እንፈጥራልን፡፡ ጨረር ባለሥልጣንም በደረጃው መሠረት አይቶ ነው ፈቃድ የሚሰጠው፡፡ የባለሥልጣኑ ዕውቅና በሌለበት የሕክምና መሣሪያ አንተክልም፡፡      

ሪፖርተር፡- የሕክምና መሣሪያዎችን አገር ውስጥ በማስገባት በኩል ከዕውቀት ክፍተት ጋር ተያይዞ ችግሮች ነበሩ፡፡ መሣሪያው ጉምሩክ ተይዞ ወራትን የሚያስቆጥርበት ጊዜም ነበር፡፡ እናንተ ይህ ችግር ገጥሟችኋል? እንዴት ፈታችሁት?

አቶ መክብብ፡- የምናመጣቸው ዕቃዎች የተመዘገቡ ናቸው፡፡ ተቆጣጣሪው ኤፌማካ መልሶ እየተዋቀረ ነው፡፡ ይህ የሕክምና መሣሪያ ለማስገባት የነበረውን የጊዜ መጓተት ይቀንሰዋል ብለን እናምናለን፡፡ አሁንም ቢሆን ከዚህ ቀደም እስከ ስድስት ወር የሚወስድን አሠራር ወደ 15 ቀን አውርዷል፡፡ አንድ ሁለት ጉዳዮች አጋጥሞንም ችግሩን ፈትተናል፡፡ በሁለት ቀን የሚጨርሱበት ጊዜም አለ፡፡ የሥራ መጓተቱ እየቀነሰ ነው፡፡ ኤፌማካ ላይ የነበረው ክፍተት እየቀነሰ ነው፡፡ በእኛ በኩል በሚገቡ ማሽኖች ላይ የግንዛቤ ክፍተት ካለ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚከብድ አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ ግንዛቤ ለመፍጠርስ ምን ትሠራላችሁ?

አቶ መክብብ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከማናቸውም ጊዜ በበለጠ አደገኛ እየሆኑ ነው፡፡ እንደሌላው ሕክምና በቀላሉ ሊድኑ የሚችሉም  አይደሉም፡፡ በደብሊው ኤምጂ በኩል ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን ለመወጣት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስመልክቶ በተለያዩ መድረኮች ግንዛቤ ለመፍጠር እንጥራለን፡፡ መንግሥትም ሆነ የግል ኩባንያዎች ይህንን አስመልክተው ዝግጅት ሲያደርጉ ስፖንሰር እናደርጋለን፡፡ ሕክምናው ለግለሰብም ሆነ ለአገር የሚያስወጣው ውድ ዋጋ እንደ አገርም እንደ ግል ካምፓኒም ይመለከተናል፡፡ በሽታውን መቆጣጠር አለብን፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ዓለም የደረሰበትን የሕክምና መሣሪያ በማስገባት ሕሙማንን መርዳት፣ ከስቃያቸው ማስታገስ አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- የቻይና ዕቃ ሲባል ያለው ግንዛቤ ጥራቱ የወደቀ ዓይነት ነው፡፡ የሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦት ላይ ይህ እክል አልፈጠረም?

አቶ መክብብ፡- የእኛ አቅራቢዎች የአሜሪካና የአውሮፓ ደረጃ ሠርተፊኬት ያላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ፔትሲቲ ማሽን ከቻይና እናስመጣለን፡፡ በፔት ሲቲ ማሽን ቻይናዎች የታወቁና ለአሜሪካና ለአውሮፓም የሚያቀርቡ ናቸው፡፡ ኤክስሬይ ከጃፓን፣ ኢንኩቤተር ከብራዚል እናመጣለን፡፡ አገሮች በሠለጠኑበት ቴክኖሎጂ አይተን ነው የምናመጣው፡፡ ቻይናዎች በፔት ቴክኖሎጂ የመጠቁና በዓለም የታወቁ ናቸው፡፡ የምንገዛው የሕክምና መሣሪያም በሠለጠኑት አገሮች ደረጃና መስፈርት ዕውቅና ካላቸው ነው፡፡ እስካሁንም ከቻይና የሕክምና መሣሪያ አምጥተን ተበላሽተው የቆሙ አልገጠሙንም፡፡ እንደ ማንኛውም ማሽን ጥገና እየተደረገላቸውም ይሠራሉ፡፡ የሕክምና መሣሪያ ጨርቅ አይደለም፡፡ የሰው ሕይወት ላይ የሚፈርድ ነው፡፡ በመሆኑም ደረጃውን የጠበቀውን መርጠን ወደ አገር እናስገባለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የምንዛሪ ገበያ እንዳይኖር ሊመክሩ ነው

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን...

ባንኮች ከሚያበድሩት 20 በመቶውን የግምጃ ቤት ሰነድ እንዲገዙበት የሚያስገድድ መመርያ ፀደቀ

ሁሉም የንግድ ባንኮች ከሚለቁት ብድር ውስጥ 20 በመቶውን በየወሩ...