Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርበፈጣን የክፍያ መንገድ ያልተከሰሱ ወንጀለኞች

በፈጣን የክፍያ መንገድ ያልተከሰሱ ወንጀለኞች

ቀን:

በዳዊት ንጉሡ

አገራችን ኢትዮጵያ በፈጣን ዕድገት ላይ ያለች በርካታ አጓጊ መስዕቦች ያሏት፣ በርካታዎች የእኛ ባደረጋት ብለው እጅግ የሚጓጉላት የዜጎቿ ገፀ በረከት መሆኗን ሁላችንም እናውቃለን ብል ማጋነን አይመስለኝም፡፡ ታዲያ ይህች ባለብዙ ፈርጥ የሆነችው ውድ አገራችን ከእኛ አልፎ በርካታ የውጭ ዜጎች ያላትን ምቹ የኢኮኖሚ ምንጭነት ለመጠቀም፣ ከተለያዩ አገሮች በርካታ በቱሪስትነትም ሆነ በሥራ ወደዚች ውድ አገር በመገስገስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በአገር ቤትም ሠርተው፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አመንጭተው፣ መኪናም ሸምተው አገሪቱ በሠራቻቸው የተለያዩ መንገዶች የሚፈሱም አገር በቀሎችም ቁጥር ስፍር የላቸውም፡፡

ታዲያ ውድ አንባቢያን ይህችን አነስተኛ መግቢያ ይዤ ወደዚህ የተንደረደርኩት ወድጄ አይደለም፡፡ እንዲሁ ያለ ምንም መግቢያን ዘው ብሎ ሐሳብን መጀመር ባህላችንም አለመሆኑ አስጨንቆኝ እንጂ፡፡ ውድ አንባቢያን ልብ እንዲሉኝ የምፈልገው ዋና ጉዳይ ቢኖር እኔ ይህንን የጻፍኩት ለበርካታ ጊዜ የፈጣን መንገዱ ተመላላሽ በመሆኔ፣ ያየሁትንና የታዘብኩትን ብቻ መሆኑን እንዲረዱልኝ እፈልጋለሁ፡፡

- Advertisement -

ከአዲስ አበባ አዳማ ወይም ከአዲስ አበባ ቢሾፍቱ የሚያስኬደውን ፈጣን መንገድ  እጠቀማለሁ፡፡ መንገዱ እጅግ ምቹ፣ የትራፊክ መጨናነቅ ፈፅሞ የማይታይበት፣ እንዲሁም ደግሞ በተፈለገውና በተፈቀደው ፍጥነት አሽከርካሪ ቢጓዝበት መልካም መሆኑን መንገር ለቀባሪ እንደማርዳት ይቆጠራል፡፡ ታዲያ ይህ መንገድ ምን ምቹ ቢሆን በድንገት አደጋ እንዲከሰት የሚያደርጉ ሳንካዎችና በርካታ የሕይወትም ሆነ የንብረት ውድመትን የሚያስከትሉ ችግሮች እየተስተዋሉበት እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ፡፡ መንገዱ ቀን የሚመቸውን ያህል ምሽት ላይም በጣም ይመቻል፣ ከነፋሻ አየሩ ጋር፡፡ ነገር ግን በዚህ ጽሑፌ ያልተከሰሱ ወንጀለኞች ያልኳቸው በዋናነት ከየት መጡ ሳይባል በፈጣን የክፍያ መንገዱ ዘው ብለው ራሳቸውን ለሕልፈተ ሕይወት፣ የሚገጫቸውን ደግሞ ለሕይወትና ለንብረት አደጋ የሚያጋልጡትን ጅቦች ነው፡፡ እንደው ለአብነት ያህል በቅርቡ ያጋጠመኝን ልንገራችሁ፡፡ አሰላ ጉዳይ ነበረኝና ቅዳሜ ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት አሰላ ለመድረስ፣ ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ከቢሾፍቱ ተነስቼ ወደ አሰላ እየነዳሁ ነው፡፡ በእኔ መኪናና ከፊት ለፊት በጅቦቹ ምክንያት ችግር ባጋጠመው መኪና መሀል ያለው የጊዜ ልዩነት ሦስት ደቂቃም አይሞላም፡፡

ታዲያ ምን ሆነ መሰላችሁ? ከእኔ ፊት የነበረው መኪና ቶዮታ ፒክ አፕ D4D የ2008/9 ዓ.ም. ሞዴል ይመስለኛል፡፡ ከመኪናው ኋላ  አንድ ትልቅ ጅብ ወድቋል፡፡ ገና ሕይወቱ ልታልፍ እያጣጣረ ነው፡፡ ከወደ አፉ ጠቆር ያለ ደም አስፋልቱ ላይ እየፈሰሰ  ሕልፈተ ሕይወቱን እያጣደፈው ይገኛል፡፡ የመኪናው ሾፌርና አብረውት የነበሩት ሦስት ተሳፋሪዎች ከመኪናው ወርደው እየሆነ ያለውን በግርምትና በድንጋጤ እየተመለከቱ ነበር፡፡

እኔም ዶልፊን መኪና ነበር እየነዳሁ የነበረውና መኪናዬን ይኼ አግኝቷት ቢሆን ኖሮ ምን ትሆን ነበር በሚል አግራሞት ከመኪናዬ ወርጄ፣ በድንጋጤና በግርምት የሆነውን ሾፌሩን ጠየቅኩት፡፡ እሱም መለሰልኝ እንዲህ በማለት፣ ‹‹እኔ እየነዳሁ አዳማ ፈጣን መንገዱን ለመጨረስ ጥቂት ኪሎ ሜትር የቀረው ይመስለኛል፡፡ ሁለት ጅቦች ተከታትለው ወደ አዲስ አበባ የሚያስኬደውን መንገድ ዘለው ከፊት ለፊቴ ከግራ በኩል ካለው አስፋልት ተሻግረው እኔ የምነዳበትን አስፋልት አቋርጠው ሲያልፉ፣ እነሱን በትዝብት እየተከታተልኩ ሦስተኛው ጅብ ሳላየው ዘሎ ገባብኝ፡፡ እኔም ገጨሁት፡፡ ፍጥነቴን ቀንሼ እየነዳሁ ባይሆን ኖሮ መኪናዬም እኔም አንተርፍም ነበር፤›› ብሎ በግርምት ነበር ያወጋኝ፡፡

አደጋው የተከሰተበት ሰዓት ጠዋት ለአንድ አሥር ጉዳይ ነበር፡፡ እንግዲህ ጅብ ጠዋትም አለ ማለት ነው፡፡ ምን መሰላችሁ? በዕለቱ ጅቡ የመኪናውን የፊት ለፊት የግራ መብራት በኩል ያለውን ፈረፋንጎ ብረት እንዳለ ከጥቅም ውጪ አድርጎት እስከ ወዲያኛው አሸልቧል፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ችግር ሲከሰት ጥፋተኛው ማን ነው? ማነው ተጠያቂው? ሾፌሩ ነው ወይስ ጅቡ? ወይስ የክፍያ መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት? እንዲያው የፈጣን መንገድ ክፍያ እንደ መኪኖቹ ዓይነትና ክብደት ክፍያ መጨመሩ ይታወሳል፡፡

የሥራዬ ፀባይ ሆኖ አመሻለሁ፡፡ ግን ስነዳ ከአሁን አሁን እነ አጅሬ አይከሰሱ ገቡ ወይስ አልገቡም በማለት በጣም እሳቀቃለሁ፡፡ በምሽት እንደ እኔ እየተሳቀቁ የሚነዱትን እኔ ማወቅ አልችልም፡፡ ነገር ግን በርካቶች እንደሚሆኑ ለመገመት አልቸገርም፡፡ ጉዳዩ አሳሳቢ የመሆኑን ያህል አፋጣኝ መፍትሔ ያሻዋል ብል ማጋነን እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ምነው የአገራችን ትራፊክ ፖሊስ ፈጣን መንገድ መግቢያው ላይ በመሆን በርካታ ሾፌሮችን በጥፋተኝነት ሲቀጡ ይውላሉ፣ ያመሻሉ፡፡ ቅጣቱስ ባልከፋ ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ትራፊክ ፖሊስ የመንገዱን አደገኛነት፣ ሊከሰሱና በደንብ መተላለፍ ምክንያት ሊቀጡ የማይችሉ ጅቦችን ችግር ለበላይ ኃላፊዎቻቸው ሳይታክቱ ምን ያህል አመልክተው የውሳኔ ሐሳብስ አሰጥተዋል የሚለውን ለእነሱ እተወዋለሁ፡፡ መንገዱ ከክፍያ መንገድ መግቢያ እስከ መውጫ ድረስ እንኳን ሁለት ተቀባባሪና አብሮ ነዋሪ ጎረቤታሞችን የለየ እንደመሆኑ መጠን፣ ሁለቱ ግራና ቀኝ ያሉ ተጎራባች የነባር ቀዬዎቹ ባለቤቶች እንደ ልብ መንገዱን ተሻግረው ቡና ባይጠጡ እንኳን ለችግር መደራረስና መጠያየቅ የሚችሉ አይመስለኝም፡፡ ችግሩ እንግዲህ ቀደም ብሎ የተከሰተ ቢመስለኝም ጅቦቹ እየገቡ ያሉት ምናልባት መንደርተኞቹ በቀደዱት አጥር፣ ወይም መጠገን ሲገባው ትኩረት ባልተሰጠውና ባልተጠገነው አጥር ዘለው ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡

መንገዱን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የክፍያ መንገዶች ባለሥልጣን፣  በመንገዱ የውጭ ግራና ቀኝ በኩል ያለውን የሽቦ አጥር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶት ቢያስጠግን የመፍትሔ አካል ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ቀደም ሲል ፈጣን የክፍያ መንገዱ ሲሠራ በመንገዱ ግራና ቀኝ በኩል የሚገኙ ነዋሪዎችን እንደ ልብ የማያጠያይቅና የአካባቢው ማኅበረሰብ ችግር ፈቺ አለመሆኑ በጥናት ከተረጋገጠ፣ ቢቻል በተወሰነ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከአዲስ አበባ መውጫው ላይ ቃሊቲ አካባቢና ሌሎችም መንገዶች ላይ እየተሠሩ እንዳሉት ድልድዮች ቢሠሩ የመፍትሔ አካል ነው እላለሁ፡፡

አሁን አሁን ደግሞ ቀን በቀን በፈጣን መንገዱ ላይ ጋሪዎች፣ ፈረሶች፣ አህያዎችና የተለያዩ የቁም ከብቶችን ማየት እየተለመደ መጥቷል፡፡ እነዚህ እንስሳት በፍጥነት መንገዱ የቀን ተቀን እንቅስቃሴ ላይ እክል ፈጣሪዎች በመሆናቸው፣ የእነዚህ እንስሳትና ተሽከርካሪ ባለቤትና የክፍያ መንገዶች ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት በጋራ ሆነው ወይም በተናጠል ድርሻቸውን ቢወጡ፣ እንደ ቀልድ የሚጠፋውን ሕይወትና ንብረት መታደግ ይችላሉ በማለት ጽሑፌን እዚሁ ላይ ገታሁ፡፡ በሌላ ጊዜ በሌላ ማኅበራዊ ጉዳይ እንገናኝ፡፡ ደህና እንሰንብት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...