በቁምላቸው አበበ ይማም
‹‹አራተኛው መንግሥት›› (The Fourth Estate) የሚለው ስያሜ ሐረግ ለመጀመርያ ጊዜ ሥራ ላይ የዋለው የዛሬ 232 ዓመት በእንግሊዝ ነው፡፡ አንዳንድ የታሪክ መዛግብት ደግሞ ከዚህ ግማሽ ክፍለ ዘመን ቀድሞ እንደነበረም ያወሳሉ፡፡ በዚያ ጊዜ ሦስቱ መንግሥታት በመባል ይታወቁ የነበሩት ቤተ ክርስቲያኗ፣ መሳፍንቱና ተራው ሕዝብ ሲሆኑ፣ ጋዜጠኞችና መገናኛ ብዙኃን ነበሩ፡፡ አራተኛው መንግሥት የሚለውን አባባል ለመጀመርያ ጊዜ የተጠቀሙት የታላቋ ብሪታኒያ የፓርላማ አባል ኤድሞንድ ቡርክ ሲሆኑ፣ ዓመቱም እ.ኤ.አ. በ1787 እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ከትበው አቆይተውናል፡፡ ከዚህ ቀደም ባሉት ዓመታት ንግሥቷ የሕግ ባለሙያዎች (Lawyers) እና ዝቅተኛው መደብ ላብ አደሩ (Proletariat) እንደ አራተኛ መንግሥት ይቆጠሩ ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ስያሜው ወደ ጋዜጠኞችና ሚዲያ ቋሚ መጠሪያነት ተሸጋግሯል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በሒደት ሦስቱ መንግሥታት ቀደም ሲል ከነበራቸው ስያሜ ወደ ሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ መለወጣቸውን እነዚሁ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ እነዚህ የመንግሥት አካላት መንግሥታቸውን የመቆጣጠሪያ ሚዛንና መመዘኛ (Check and Balance) መድበው በመሆን ያገለግላሉ፡፡ ሚዲያው አራተኛው መንግሥት መባሉ በአንድ አገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳይ ምን ያህል ከፍ ያለ ቦታ ሚና እንዳለው ያሳያል፡፡ በምዕራባውያን በተለይ በእንግሊዝና በአሜሪካ ሚዲያው ከሦስቱ የመንግሥት አካላት ተርታ መሠለፍ ችሏል፡፡ በአኅጉራችን በደቡብ አፍሪካ፣ በጋና፣ በናይጄሪያ. . . በተወሰነ ደረጃ በኬንያ፣ በኮትዲቯርና በሌሎች አገሮች ሚዲያው የአራተኛው የመንግሥት አካልነት ሚናቸውን ኃላፊነታቸውን ከእነ ውስንነታቸው እየተወጡ ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ አገራችን የጎለበተ ጥንታዊ የአገረ መንግሥት ልምምድ ቢኖራትም፣ ሚዲያችን ግን አራተኛው የመንግሥት አካል ለመባል ገና ብዙ ብዙ ይቀረዋል፡፡
ስለሆነም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የመንበሩን አለመያዝ ተረድተው ይመስላል በአንድ መድረክ በአገራችን የገነነውን ሙስና አራተኛው መንግሥት በማለት እንደገለጹት ሁሉ፣ እኔም በአገራችን አሉታዊ ተፅዕኖው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ የመጣውን በጊዜ ሃይ ካልተባለ ለአገራችን ህልውና አደጋ እየደቀነ ያለውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከጉሊት እስከ ጅምላ ንግድ በአጠቃላይ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሕይወታችንን እየናጠ ያለውን አደገኛ እየሆነ የመጣውን በሰዓት የተጠመደ ቦምብ (Time Bomb) ይገልጽልኛል ብዬ ስላመንኩ ‹‹ድለላን›› ሳልወድ አምባሻ ሳልቆርስ ‹‹አራተኛው መንግሥት!›› ብየዋለሁ፡፡ አዎ! ከላይ ስለሐረጉ ሥረወ ቃል (Etymology) ሳትት ጽንሰ ሐሳቡ በቀደመው ዘመን ንግሥቷን፣ የሕግ ባለሙያንና ሠራተኛውን ለመግለጽ ይውል እንደነበረው ሁሉ፣ እኔም ዛሬ ድለላ በአገራችን ከደቀነው ወቅታዊና ከቡድን ተፅዕኖ አኳያ አራተኛው የመንግሥት አካል ብለው ያንስበት ይሆን እንደሆነ እንጂ አይበዛበትም፡፡
እንዲያውም ከሕግ አውጭው፣ ከአስፈጻሚውና ከተርጓሚው፣ እንዲሁም ከሚዲያው በላይ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን፣ ጓዳ ጎድጓዳችንን አንዳንድ ጊዜም አልጋ ተጋሪያችንን፣ አንሶላ ተጋፋፊያችንን እስከ መወሰን ከፍ ሲልም ውኃ አጣጫችንን እስከ መምረጥ. . . ስለተሸጋገረው ‹‹ድለላ!?›› አንደኛው የመንግሥት አካል ቢባል ያንሰው ይሆናል እንጂ አይበዛበትም፡፡ አዎ! ደላላ ስንበላ የሚበላ፣ ስንጠጣ የሚጠጣ፣ ስንለብስ የሚለብስ፣ ስንገዛ የሚገዛ፣ ስንሸጥ የሚሸጥ፣ ስንከራይ የሚከራይ፣ ምን አለፋችሁ ስንሠራ ካለመሥራቱ፣ ስንራብ ካለመራቡ፣ ስንታረዝ ካለመታረዙ፣ በችጋር ስንገረፍ ካለመገረፉ፣ በኑሮ ወድነት ስንሰቃይ ካለመሰቃየቱ፣ በዋጋ ግሽበት ኪሳችን፣ ቦርሳችን ሲገለበጥ ካለመገልበጡ በስተቀር የማይገባበት የሕይወታችን ቅንጣትና የማያንኳኳው በር የለም፡፡ ታዲያ አይደለም አራተኛው አንደኛው መንግሥት ቢሆን ይበዛበታል?
በእያንዳንዳችን ሕይወት አዛዥ ናዛዥ የሆነው ‹‹ድለላ!›› የቃሉ ትርጉም ምን ማለት ይሆን? ምንም እንኳ በሥነ ልሳን Lingustic አስተምህሮ በስያሜውና በተሰያሚው መካከል የባህሪ ግንኙነት እንደሌለ ቢበየንም፣ የቃሉ ምግባርና ግብር ስለተምታታብንና ስለተጣረሰብን ትርጉሙን እንመልከት፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በ1993 ዓ.ም. ያዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ‹‹ደላላ››ን ‹ገንዘብ እየተከፈለው ተፈላላጊዎችን (ሻጭና ገዥን፣ አከራይና ተከራይን. . . ) አገናኝና አስማሚ› በማለት ይተረጉመዋል፡፡ በመደለል ሥራ ላይ የተሰማራ ሰው አታላይና በውሸት አግባብቶ ለማሳመን የሚሞክር፣ ‹ድላል›ን ደግሞ ለደላላ የሚከፈል ገንዘብ በማለት ይተረጉማል፡፡ የደስታ ተክለ ወልድ ዘሀገረ ወግዳ በ1970 ዓ.ም. የአማርኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ ደለለ አሞኘ፣ አታለለ፣ ሸነገለና የማያደርገውን አደርጋለሁ አለ
ደላላ አመልካች፣ ጠቋሚ ድላል ለጠቋሚና ላስማማ የሚሰጥ ገንዘብ ሲል ይተረጉመዋል፡፡
ይኼኛው ትርጉም ከቀደመው ይልቅ የአገራችንን ደላላ ቁልጭ አድርጎ ይገልጸዋል፡፡ የእንግሊዝኛውን ትርጉም ‹‹Broker›› ሥረወ ቃል ስንመለከት ‹‹Brocour›› ከሚለው የፈረሣይኛ ቃል የመጣ ሲሆን፣ ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የቋንቋው አካል መሆኑን ሜሪያም ዌቢስተር የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ያወሳና ትርጉሙም፣
‹‹Bro·ker: a Person who Helps Other People to Reach Agreements, to Make Deals, or to Buy and Sell Property (Such as Stocks or Houses)›› ነው ይለናል፡፡ የአማርኛውም ሆነ የእንግሊዝኛው መሠረታዊ ትርጉም ተቀራራቢ ቢሆንም፣ ‹‹ድለላ›› ሲነሳ አብሮ ማታለል፣ መሸንገል፣ ማሞኘትና በውሸት አግባብቶ ማሳመን የሚሉ አሉታዊ አንድምታዎች ግዘፍ ከመንሳት አልፈው ‹‹ድለላ›› በተነሳ ቁጥር ቀድመው ወደ አዕምሯችን የሚመጡት እነዚህ አሉታዊ ብያኔዎች ናቸው፡፡ በአገራችን ያለውን አብዛኛውን ደላላም ይገልጹታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ሆኖም እጅግ እጅግ ያነሱ በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም ታማኝ፣ ሀቀኛና መልካም ሥነ ምግባር ያላቸው ደላሎች መኖራቸው ግን ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ድለላን ከመንግሥት አካላት ተርታ ከማሠለፍ አልፌ እንደ አንደኛው መንግሥት የቆጠርኩበትን ዓበይት መፍትሔዎችንና መገለጫዎችን ሳነሳሳ ኢኮኖሚያችን ከሌሎች አገሮች ለየት ያደርገዋል ብዬ ከማምንባቸው ግርምቶች ቀዳሚው በአዳም ስሚዝ የኢኮኖሚክስ ሀ ሁ. . . ዝቅተኛ መሥፈርት በሆኑት ፍላጎት (Demand) እና አቅርቦት (Supply) አለመዘወሩ ነው፡፡
ከጉልት እስከ ጅምላ ንግድ፣ ከጎጥ እስከ ፌዴራል፣ ከሽንኩርት ማሳ እስከ አትክልት ተራ፣ ከሚዛን ተራ እስከ እህል በረንዳ፣ ከአንድ ክፍል ጭቃ ቤት እስከ ተንጣለለ ቪላና ፎቅ፣ ከአንድ ጥማድ መሬት እስከ ጋሻ መሬትና ከአራጣ ብድር እስከ ባንክ ብድር፣ ከታች እስከ ላይ በተሰገሰጉ ህልቆ መሳፍርት ደላሎች ሳምባ የሚተነፍስ ኢኮኖሚ መሆኑ ነው፡፡ አንድ ወዳጄ በዚያ ሰሞን እንዳጫወተኝ ከሆነ የደላላ እጅ ሃይ ባይ በማጣቱ ረዝሞ ረዝሞ፣ በአንድ ወቅት አገራችን በምትፈርማቸው ብድርና ዕርዳታ ሳይቀር ፈርቅ እስከ መያዝ ደርሶ ነበር፡፡ እግራችን እስኪቀጥን ብንዞር የደላላ እጅ ያልገባበት የኢኮኖሚ ዘርፍ የለም፡፡
ከላይ ከትርጉሙ እንደተመለከትነው የድለላ ሥራ ሻጭና ገዥን ማገናኘት፣ ለዚህም ድላል (የአገልግሎት ክፍያ) መቀበል ቢሆንም፣ የአገራችን ደላላ ግን በዓለም ታይቶም፣ ተሰምቶም በማያውቅ ሁኔታ ዋጋ ቆራጭ፣ ታማኝ ገበያ መሪ እስከ መሆን ደርሷል፡፡ አሁን ያለው የእህል፣ የአትክልት፣ የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ፣ የመኪና የንግድም ሆነ የኪራይ ቤት ክፍያ፣ የመሬት ዋጋ፣ ወዘተ. የተቆረጠውና የተተመነው በገበያ ሳይሆን በደላላ ነው፡፡ በዚህም ገበያ አመጣሽ ሳይሆን ደላላ ዘራሽ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት አስከትሏል፡፡ በዚህ የተነሳ ዜጋው በኑሮ ውድነት ፍዳውን እያየ ነው፡፡ የሸቀጡ የምርቱ፣ የአገልግሎቱ አምራች፣ አቅራቢም የሚገባውን ጥቅም እያገኘ አይደለም፡፡ ከሸማቹም፣ ከሻጩም በሁለት ቢላዋ እየበላ ያለው ሕገወጥ ደላላው ነው፡፡ ዛሬ በመላው አገራችን ያሉ አርሶ አደሮችም ሆኑ አርብቶ አደሮች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ጥያቄ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውና ለምርታቸው፣ ለገበያ ከሚቀርቡ እንስሳትም ሆነ ተዋጽኦ ተገቢውን የድካማቸውን ዋጋ እንዲያገኙ ሲወተውቱና ሲማፀኑ በየሚዲያው ብንሰማምና ብንመለከትም፣ መፍትሔ ባለማግኘታቸው ዋጋ የሚቆርጥላቸው ደላላው ነው፡፡ በምርቱ ተጠቃሚዎች እነሱ ሳይሆን ደላላው ነው፡፡
አርሶ አደሩም ሆነ አርብቶ አደሩ የድካሙና የላቡ ተጠቃሚ ካለመሆኑ ባሻገር ደላላ አመጣሽ የሆነው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት ኢኮኖሚውን ወደ ለየለት ቀውስ እያንደረደረው ነው፡፡ ሕገወጥ ደላላው ያለ አዛዥ ናዛዥ ገበያውን በብቸኝነት በመቆጣጠሩ፣ መንግሥት በነፃ ኢኮኖሚ ስም የመነሻ ዋጋ ተመንና የትርፍ ህዳግን (Profit Margin ) አለመወሰኑ ከሕገወጥ ደላላው ጋር እሳትና ጭድ ሆኑ፡፡ የኑሮ ወድነቱን እያቀጣጠለ በዜጋው ላይ ብሶትን፣ ምሬትን ተስፋ መቁረጥን እያዳረሰ ይገኛል፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ወደ ለየለት ፓለቲካዊ ቀውስ የማያመራበት ምክንያት የለም፡፡ በዓለማችን የነፃ ገበያ አባት የምንላቸው ምዕራባውያን ሳይቀሩ የትርፍ ህዳግንም ሆነ የመነሻ ዋጋ ደረጃን እያወሱ ገበያውን እየተቆጣጠሩ ባለበት፣ እኛ ለዚያውም ያልሠለጠነውን ኢኮኖሚ ስድ መልቀቃችን ዛሬ ለምንገኝበት ምሬትና እሮሮ ዳርጎናል፡፡
ማኅበራዊ
ባለፉት ዓመታት ምሳሌ አርዓያ የሚሆን ቤተሰብ፣ ተቋምና መሪ በየደረጃው አለመፈጠሩ የግብረ ገብ ትምህርት አለመሰጠቱና ፈሪኃ እግዚአብሔር (ፈጣሪ) ያለው ትውልድ አለመታነፁ፣ ዛሬ ለምንገኝበት የማኅበራዊ ቀውስ አፋፍ አድርሶናል፡፡ ውሸት፣ ሌብነት፣ ዘረፋ፣ ማጭበርበር፣ መካድና ጥሎ ማለፍ ነውር መሆናቸው ቀርቶ የሚያሸልሙበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ የዚህ ትውልድ ማኅበራዊ ቀውስ ውጤት የሆነው አብዛኛው ደላላም መዋሸትን፣ ማታለልንና በአቋራጭ መክበርን ሙያ እስከ ማድረግ ተግቷል፡፡ ገንዘብ እስካገኘ ድረስ ለዜጋው ለወገኑ ደንታ ቢስ ሆነ፡፡ እህት ወንድሞቹን በማይጨበጥ ተስፋ እየደለለ ለስደታና ለመከራ ዳረገ፡፡ በበረሃና በባህር አለቁ፡፡ በአረመኔዎች እጅ ወድቀው የአካላቸውን ክፍል አጡ፡፡ ሕገወጥ ድለላው በዚህ የሚያበቃ አይደለም፡፡
በአገራችን እየተስፋፋ በመጣው የወሲብ ንግድም ግንባር ቀደም ተዋናይ ነው፡፡ ለአቅመ ሔዋን ያልደረሱ ልጃገረድ ሕፃናትን ሳይቀር ለሕገወጥ የወሲብ ንግድ እስከ ማቅረብ፣ የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችን ለዚህ ሕገወጥ ተግባር እየመለመለ የፎቶ አልበም አዘጋጅቶ የሚያቀርብ አረመኔ ደላላ፣ በየዩኒቨርሲቲዎቻችን በሮች ማግኘት እየተለመደ መምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ደግሞ አዲስ የድለላ ዘርፍ ማለትም ስለየማህፀን ኪራይ (Surrogacy) ደላሎች መስማት ከጀመርን ውለን አደርን፡፡ ልጅህን ለልጄ ማለት እየቀረ ተጋቢዎች ራሳቸው ወስነው ትዳር መመሥረት እየተለመደ ቢመጣም፣ አሁን ሦስት ጉልቻ በደላላም ተጀምሯል፡፡ ምን አለፋችሁ ድለላ ያልገባበት የሕይወታችን ቅንጣት የለም፡፡ በእንቅርት ላይ እንዲሉ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች እየተሸረሸረ በመጣው ማኅበራዊ ተራክቦ ላይ፣ ሥነ ምግባር የሌለው ሕገወጥ ደላላ በአናቱ ተጨምሮበት ቀውሱን እያባባሰው ነው፡፡
ፖለቲካዊ
ሕገወጥ ደላላው በኢኮኖሚው የሚስተዋሉ መዋቅራዊና ተቋማዊ ችግሮችን በማባባስ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ፈታኝ እያደረገው ይገኛል፡፡ በዓል በመጣ ቁጥር የሚስተዋሉ እጅግ የተጋነኑ የዋጋ ጭማሪዎችን እዚህ ላይ በአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡ በቋሚነት የኑሮ ወድነቱንና የዋጋ ግሽበቱን በማባባስ ዜጋውን ለብሶትና ለምሬት እየዳረገ ነው፡፡ እዚህም እዚያም ለሚስተዋሉ ግጭቶች በአንድም በሌላ በኩል የዋጋ ግሽበቱና የኑሮ ውድነቱ የፈጠረው ተስፋ መቁረጥ፣ እንደ ክብሪት ሆኖ በማገልገል ላይ መሆኑን የተለያዩ አካላት እያነሱ መሆኑ የሕገወጥ ደላላ እጅ ከኢኮኖሚው አልፎ በማኅበራዊ መዋቅራችን ከፍ ሲልም ከሌሎች መንስዔዎች ጋር ተዳብሎ አገራዊ ቀውስ በመለፈፍ፣ በመጥራት ላይ መሆኑን ተገንዝቦ ከዚህ በላይ ሳይረፍድ፣ ሳይቃጠል በቅጠል ሊባል ይገባል፡፡
እንደ መውጫ
ራሳቸውን ሕጋዊ ብለው የሚጠሩትም ሆነ ሕገወጥ ደላላዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ በዜጎች፣ በአገሪቱ ላይ እያሳደሩት ያለውን አሉታዊ ዘርፈ ብዙ ተፅዕኖ ለማስወገድ መንግሥት የዘነጋውንና ችላ ያለውን ኃላፊነቱን ዛሬ ነገ ሳይል መወጣት ሊጀምር ይገባል፡፡ በድለላ የሚዘወረው ኢኮኖሚ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የሆነው ሸማች፣ ሕዝብም ኢኮኖሚውን ከድለላ ምርኮ ነፃ ለማውጣት የድርሻውን ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን መጠየቅ፣ ከጥልቅ እንቅልፋቸው መቀስቀስ ይጠበቅበታል፡፡ የዘርፉ ልሂቃንም የአደጋውን ስፋት በጥናት ተንትነው ሊያስረዱ ይገባል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን መንግሥት በየደረጃው ከጎጥ እስከ ፌዴራል፣ ከሽንኩርትና ከቲማቲም እስከ ጅምላ ንግድ ገበያውን የንግድ ሥርዓቱን በኔትወርክ ተደራጅቶ እያተራመሰ ያለውን ሕገወጥ የድለላ ኃይል ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በቃህ ሊለው ይገባል፡፡ መንግሥት በአጭር ጊዜ መሠረታዊ ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ ከደላላ ነፃ በማድረግ፣ ሸማቹና ሻጩ ያለ ደላላ በገበያ ሥርዓት በቀጥታ እንዲገበያዩ መደላደሉን ሊፈጥር ይገባል፡፡ ከዚህ በመቀጠል የገበያ ሰንሰለቱን ከሕገወጥ ደላላ መዳፍ ፈልቅቆ ነፃ አውጥቶ ሕግን ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡ በመቀጠል ሕጋዊ ደላላው የሚገዛበት ሕገ ደንብና እንደ አስፈላጊነቱ የሥነ ምግባር መመርያ ሊዘጋጅ ይገባል፡፡ የደላላ ክፍያና ድለላ የሚፈቀድባቸውና የሚከለከልባቸው ምርቶችና አገልግሎቶች በሕግ በማያሻማ ሁኔታ መለየት፣ ይህንን በሚተላለፉ ደላሎችም ሆነ ሻጭና ሸማቾች ላይ ሕጋዊ ተጠያቂነትን ማስፈን አለበት፡፡
በመጨረሻም መንግሥት በማንኛውም የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አገሮች እንደሚደረገው ኢኮኖሚውን ባማከለ ሁኔታ የሸቀጦችንና የአገልግሎቶችን መነሻ የገበያ ዋጋ ተመንና የትርፍ ህዳግ በሕግ መወሰን ይጠበቅበታል፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆኑትና ስዊድናዊው የሂዩማን ብሪጅ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አዳሙ አንለይ በሚኖሩባት ስዊድንም ሆነ በሌሎች ምዕራባውያን አገሮች፣ በማንኛውም ሸቀጥና አገልግሎት ላይ እንደ ገበያ ባህሪው የዋጋ ተመንና የትርፍ ህዳግ እንደሚቀመጥ ገልጸውልኛል፡፡ ከኩባንያ ኩባንያ የዋጋ ልዩነት ቢኖር እንኳ ከተመኑና ከትርፍ ህዳጉ ብዙ ልዩነት እንደሌለው አረጋግጠውልኛል፡፡ ስለሆነም ያለ ልጓም በ‹‹ነፃ ገበያ›› ስም ቼቼ እያለ እየደነበረ ያለው ሕገወጥ ደላላና ገበያ ልጓም ሊበጅለት ይገባል፡፡ ደላላውም መንግሥት በፈቀደለት ዘርፍ ብቻ ሻጭና ገዥን፣ አከራይና ተከራይ ከማገናኘት የዘለለ ተግባር እንዳይኖረው በሕግ ገደብ ሊጣልበት ያሻል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡