በምግባሩ ታዬ
ታሪክ የኋሊት እንደሚያሳየን ኢትዮጵያ በጂኦግራፊ ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት ስትሰፋና ስትጠብ ነው፡፡ በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል በዓድዋ የተደረገው ጦርነት ውጤቱ፣ በሰሜን በኩል የኢትዮጵያ ዳር ድንበር በስምምነት የተመለከተበት እንደነበርና ኤርትራ በጣሊያን ቅኝ ተገዥነት የቀጠለች መሆኑን ያረጋገጠ ነበር፡፡ ከዓመታት በኋላ ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ንግንኙነት ሲቀጥልም፣ ከኢትዮጵያ ጋር መዋሀድዋን ተከትሎ በኤርትራ ተቋዋሚ ድርጅቶችና በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት መካከል የተደረገ ረዥም ዓመታትን የፈጀ ጦርነት ተካሄደ፡፡ ለመግለጽ የሚከብዱ ብዙ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳቶች አስከትሎም አለፈ፡፡
ኤርትራ እንደ አገር ዕውቅና አግኝታ ህልውናዋን ያረጋገጠችው፣ የደርግ የመንግሥት አስተዳደር ከሥልጣን በተወገደ ማግሥት በሕዝበ ውሳኔ ነበር፡፡ እነዚህ ዋና ዋና አንኳር ክስተቶች ለዚህ ጽሑፍ ዓላማ እንደ መንደርደሪያ ይረዳሉ በሚል ለትውስታ የቀረበ ነው፡፡
ኤርትራ እንደ አገር ዕውቅና እንዳገኘች ከአሥር ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ‹‹በድንበር›› ምክንያት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተካሄደው ጦርነት፣ በሁለቱም ወገን በአሥር ሺዎች የሚገመት አምራች የሰው ኃይል ያጡበት፣ ከዚሁ ቁጥር በላይ አካል ጉዳተኛ የሆነበት ደም አፋሳሽና ከፍተኛ ቁሳዊ ሀብት የወደመበት፣ ዓለምን በእጅጉ ያስገረመና ያሳዘነ ጦርነት አካሄዱ፡፡
የጦርነቱ መንስዔና ምክንያት ከተለያዩ መላምቶች ከሚነገር በስተቀር፣ አሁንም አወዛጋቢና በውል የማይታወቅ በመሆኑ ለታሪክ ጸሐፍት ሳይቀር ግልጽ የሆነ መረጃ ካለመኖሩም አልፎ፣ የሁለቱም አገሮች ሕዝቦች ምክንያቱን አውቀው ተጠያቂ የሚያደርጉት አካል ለጊዜው ባለመኖሩ ጉዳዩ በእንጥልጥል የሚገኝ ነው፡፡ ስለዚህ በደረሰው ጉዳት ልንማርበት ዳግም ወደዚህ ዓይነት አስከፊ ጦርነት እንዳንገባ ሊረዳን ከሚችል በስተቀር፣ በሁለቱም አገሮች የጦርነቱ ተዋናዮች ጉዳዩ ተከድኖ ይብሰል በሚል እስካሁኗ ሰዓት ምንም ትንፍሽ የተባለ ነገር የለም፡፡
ጦርነቱን ለማስቆም የተደረገውን ጥረትና ሒደት በአጭሩ እዚህ ላይ ማንሳቱ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ የአልጄርስ ስምምነት በመባል በሚታወቀው ሌሎች የዓለም አገሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የተሳተፉበት፣ ሁለቱም አገሮች በሦስተኛ አካል አደራዳሪነት የካሳና የድንበር ኮሚሽኖች ተቋቁመው የድንበር ውዝግቡ ‹‹አሳሪና የመጨረሻ ውሳኔ›› ተብሎ በድንበር ኮሚሽን ተሰጥቶ፣ ድንበሩ በካርታ ደረጃ (Virtual Demarcation) ተመላክቶ ሲጠናቀቅ፣ የካሳ ኮሚሽንም በሁለቱም አገሮች ለተጎዱ ወገኖች አገሮቹ ካሳ እንዲከፍሉ ውሳኔ በመስጠት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ አተገባበሩ ግን ለሁለት አሥርት ዓመታት ፍፃሜ ሳያገኝ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት፣ በሁለቱም አገሮች መካከል የነበረው ግንኙነት ‹‹ሰላምም ጦርነትም ሳይኖር›› በድንበሮቻቸው ግዙፍ ሠራዊትና የጦር መሣሪያ አከማችተው ወታደሮቻቸው ተፋጠው መቆየታቸው ነው፡፡ ለሕዝቦቻቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሁለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት ማነቆ ሆኖ እንደቆየባቸውም እማኝነት የሚስፈልገው ጉዳይ አይደለም፡፡ አገሮቹ ድህነት ተኮርና በሕግ የበላይነት የሚመሩ የመንግሥት አስተዳደር በመቅረፅ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ገድቧቸው እንደቆየ፣ በሕዝቦቻቸው በደረሰውና እየደረሰ ያለው በተለያየ መንገድ የሚገለጽ ጉዳት ማስተናገዳቸው በገሀድ የሚታወቅ ነው፡፡ በድህነት አረንቋ ውስጥ መግባት፣ ስደትና ሞት ለአብነት የሚገለጹ ናቸው፡፡
በሁለቱም አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያለ ነበር፣ ኢትዮጵያን በማስተዳደር ላይ በሚገኘው በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጥ በተፈጠረው የአመራር ለውጥ ወደፊት ከመጡት ዶ/ር ዓብይ አማካይነት፣ በሁለቱም አገሮች ሻክሮ እንዲቆይ ምክንያት ስለሆነው ‹‹የድንበር›› ውዝግብ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የአልጄርስ ስምምነትን አገራቸው እንደምትቀበል ጥሪ የቀረበው፡፡ የሰላም ጥሪው በኤርትራ መንግሥት ተቀባይነት አግኝቶ ፍሬ በማፍራቱ ደረጃ በደረጃ የተወሰዱ አንዳንድ ዕርምጃዎች ለመጥቀስ ያህል፣ የሁለቱም አገር መሪዎች ተራ በተራ በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራና በአዲስ አበባ በመገኘት ጉብኝት ማድረጋቸው፣ ነፃ የበረራ የአየር ክልል መፍቀዳቸው፣ በአስመራና በአዲስ አበባ ቀጥታ የአውሮፕላን በረራ መጀመር፣ በሁለቱም አገሮች የየብስ ድንበሮች በመክፈት ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲጀምር መደረጉ፣ የኤርትራ መሪ አቶ ኢሳያስና የሰላም ልዑካቸው በኢትዮጵያ አንዳንድ ክልሎች (ደቡብ ክልል ሐዋሳ፣ አማራ ክልል ጎንደርና ባህር ዳር፣ ኦሮሚያ ክልል ጂማ፣ አዳማ) ጉብኝትና የባህል ልውውጥ ማድረጋቸው ተጠቃሾች ናቸው፡፡
እንዲሁም በሁለቱም መንግሥታት ፀብ ጫሪነትን የሚከለክልና በሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች በአስመራ፣ በአዲስ አበባ፣ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች አደራዳሪነት የተደረጉ ስምምነቶች፣ ስምምነቶቹ ለሕዝብ ግልጽ አይደሉም ተብሎ አከራካሪነታቸው መቀጠሉ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በሁለቱም አገሮች መፃኢ መልካም ግንኙነትና መተማመን በመፍጠር በኩል ግን የሚጫወቱት ገንቢ ሚና እንዳለ ዕሙን ነው፡፡
ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረው የዶ/ር ዓብይ የሰላም ጥሪ ከተበሰረ ጀምሮ በሁለቱም አገሮች መልካም የሚባሉ ፍፃሜዎች እንዳሉ ሆኖ፣ ግንኙነቱ እንደ አጀማመሩ ፍጥነት አለማሳየቱ በአንዳንድ ጉዳዮችም ወደ ኋላ የመመለስ አዝማሚያ መታየቱ፣ በአንዳንድ ወገኖች ጥርጣሬ እየፈጠረ በመምጣቱ በጉዳዩ ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተለያዩ ሚዲያዎች፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ ትኩረት እያገኘ የመጣ ነው፡፡
በግልጽ ወጥቶ ሌላ ምክንያት እስካልተሰጠው ድረስ የሁለቱም አገር ሕዝቦች፣ የፀቡ ምክንያት መጀመርያና መጨረሻ የድንበር ጉዳይ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ታዲያ ይህን ችግር እስከ ወዲያኛው ለመዝጋት እስካሁን ድረስ በሁለቱም መንግሥታት (በተለይ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ) ጉዳዩን በቀጥታ መፍትሔ የሚሰጡ ምን ዓይነት የሚታዩና የሚዳሰሱ ተጨባጭ ዕርምጃዎች ተወሰዱ? በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ከድንበር ማካለልም ሆነ ከሌሎች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በፊት የሁለቱም ሕዝቦች ግንኙነት በማስቀደም፣ ማኅበራዊ ግንኙነቱን ማጠናከር በቅድሚያ መምረጡንና በተግባርም ለዚህ ዓላማ ሲባል መንቀሳቀሱን ይገልጻል፡፡
ይሁን እንጂ ይኼንን ዓላማ በሚጎዳ ሁኔታ ሕዝብ ለሕዝብ ለማገናኘት በመሪዎች ደረጃ የተከፈቱት የየብስ ድንበሮች ሁሉ ተራ በተራ መዘጋታቸው፣ ከዚህም አልፎ የመዘጋታቸው ምክንያት በሁለቱም አገሮች ኦፊሴላዊ መግለጫ አለመሰጠቱን ተከትሎ ሌላ ዓይነት አማራጭ ወይም የማስተካከያ ዕርምጃ እስካሁን ድረስ አለመወሰዱ፣ በሁለቱም አገር መንግሥታት መካከል የተፈጠረው ግንኙነት በጠንካራ መሠረት ላይ እንዳልተገነባ ሥጋታቸውን የሚገልጹ ወገኖች አሉ፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ የነበረውን የድንበር ውዝግብ በሕጋዊ መንገድና በፍጥነት መልስ አለማግኘቱ ተጠቃሚው ማነው ተጎጂውስ? ስለውይይት መቅረብ ያለበት ጉዳይ አይደለም ትላላችሁ?
በግልጽ እንነጋገር ከተባለ ከኤርትራ ጋር ያለው የድንበር ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደ በፊቱ (ከዓመት በፊት እንደነበረው) በሚፈለገው መንገድ መወያያ እየሆነ አይደለም፡፡ እንዲያውም የተወገዘ የማይነሳ ጉዳይ እስከ መሆን ደርሷል ለማለት እደፍራለሁ፡፡ ካለፈው ታሪካችን መማር ያልቻልነው ነገር ቢኖር በይደር ወይም በቸልታ በመተው ደጋግመን ለሌላ ችግር መዳረጋችን ነው፡፡
በበኩሌ ሕጋዊነትን የተከተለ ለሁለቱም አገር ሕዝቦች ግልጽ በሆነና ተሳትፎአቸውን በተለያየ መንገድ ባረጋገጠ አኳኋን የድንበር ውዝግቡ መቋጫ ቢደረግለት፣ የሁለቱም አገር ሕዝቦች እኩል ተጠቃሚ ይሆናሉ ብቻ ሳይሆን በቀጣይ በሚያደርጉት ግንኙነትና ዝምድና መሠረት የሚጥልና መተማመኛ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡ የሁለቱም አገር መንግሥታት ቀጣናዊ ውህደት ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት መልካም ሆኖ እያለ፣ በጠንካራ መሠረት ላይ የተገነባ ካልሆነ አመርቂ ውጤት ስለማምጣቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ቀጣናዊ የአገሮች ውህደት ለማምጣት በቅድሚያ በአገሮቻቸው ያለውን ፀጥታ፣ ሰላም፣ የሕዝቦቻቸው የመቻቻልና የአንድነት ስሜት በተግባር መፍጠር እስካልቻለ ድረስ፣ አይደለም ቀጣናዊ ከአንድ ጎረቤት አገር ጋር እንኳን ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር ከቶም አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የውስጥ ችግር ለጎረቤት አገርም ስለሚተርፍ ነው፡፡
በተለይ ደግሞ በኢትዮጵያና በኤርትራ መሀል በተደረገው አስከፊ ጦርነት (አላስፈላጊ ጦርነት ይሉታል አንዳንድ ጸሐፍት) ምክንያት፣ በሁለቱም አገር ሕዝቦች ለሁለት አሥርት ዓመታት ለፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ሲባል የተለያዩ የጥላቻና የቂም በቀል ትርክቶች ሲዘሩ ቆይተዋል፡፡ ግንኙነቱ እንዲሁ በቀላሉ ሊለወጥ የሚችል ባለመሆኑ ይህንን ያልተስተካከለ ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ ብዙ ጥረትና ትዕግሥት የሚጠይቅ ነው፡፡ በአገሮቹ መንግሥታት በኩል ምን ያህል ፍላጎት ቢኖር በዚህ ጉዳይ አቋራጭ መንገድ ያለ ስለማይመስል ሁኔታዎችን በችኮላ ለመፈጸም ከመጣር ይልቅ፣ መከናወን ያለባቸውን ደረጃ በደረጃ እያከናወኑ ውጤቱንም እየገመገሙ መጓዝ ለሁለንተናዊና ዘላቂ ጥቅም ዋስትና የሚሰጥ ይሆናል እላለሁ፡፡ ሰላምና ፍቅር ለአገራችን!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡