Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ እያላት በዝናብ እጥረት ኃይል የሚቋረጥበት አገር መሆን የለባትም

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጋዝ እያላት በዝናብ እጥረት ኃይል የሚቋረጥበት አገር መሆን የለባትም

ቀን:

በጌታቸው ተስፋዬ

ከብዙ ሳምንታት የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር በኋላ የውኃ፣ የመስኖና የኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ትልቁ የጊቤ ሦስት ግድብ በቂ ውኃ ባለመያዙ፣ አገሪቱ የ426 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ እጥረት እንዳጋጠማትና በዚህ የተነሳ በመላው አገሪቱ የፈረቃ ፕሮግራም እንደተጀመረ ተናግረዋል፡፡ አገሪቱ የምትፈልገው 2,500 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ቢሆንም፣ አሁን ባለችበት ሁኔታ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር መግጠሙ የሚያስገርም አይደለም፡፡ ምክንያቱም ላለፉት በርካታ ዓመታት በአገሪቱ የኢነርጂ ፖሊሲ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ከተፈጥሮ ጋዝ ይመረታል የሚል ዓረፍተ ነገር አልነበረበትም፡፡

የዓረብ ባህረ ሰላጤ አገሮች፣ ምዕራብ እስያና ሰሜን አፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኙት ከተፈጥሮ ጋዝ ነው፡፡ እንደ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ሩሲያ፣ ቻይናን የመሳሰሉት አገሮች ከኑክሌርና ከከሰል በተጨማሪ የተፈጥሮ ጋዝን ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ይጠቀማሉ፡፡ ስለተፈጥሮ ጋዝ አጠቃቀም ያሉት የቅርብ ዘመን መረጃዎች የሚያሳዩት በዓለማችን ውስጥ የተፈጥሮ ጋዝ እስከ 40 በመቶ የሚውለው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጭት ነው፡፡ የተቀረው ለቤት ውስጥ ማብሰያ፣ ለማሞቂያ፣ ለማዳበሪያ ግብዓት፣ ለፕላስቲክና ለሴንቴቲክ ምርቶች ይውላል፡፡

ኢትዮጵያ በሶማሌ ክልል የነዳጅ ዘይትን ጋዝ ፍለጋ ስታካሂድ ወደ 60 ዓመታትን አሳልፋለች፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ. በ1973  ወደ 2.7 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ፊት የሚደርስ የጋዝ ክምችትን በካሉብና በሂላላ አካባቢ ያገኘው ቴኔኮ የተባለው የአሜሪካ ኩባንያ ሥራውን ለቆ እንዲሄድ የደርግ ኮሙዩኒስታዊ አገዛዝ ካስገደደው በኋላ የሩሲያ፣ የማሌዥያ፣ የካናዳና የእንግሊዝ ኩባንያዎች ፍለጋ ሲያካሂዱ እንደነበርና በቅርቡም ፖሊ ጂሲኤል የተባል የቻይና ኩባንያ ተጨማሪ የጋዝ ክምችት እንዳገኘና ጠቅላላ ክምችቱ ወደ ስድስት ትሪሊዮን ኪዩቢክ ፊት እንደሚደርስ፣ የማዕድን ፔትሮሊየምና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴርን ጠቅሶ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቦ ነበር::

የሶማሌ ክልል የተፈጥሮ ጋዝ ከሁለት እስከ ሦስት ሺሕ ሜትር ጥልቀት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህ ጋዝ ያለ ምንም ጥቅም ላለፉት 46 ዓመታት በከርሰ ምድር ውስጥ ተቀምጦ አሳልፏል፡፡ ይሁን እንጂ በዘመነ ኢሕአዴግ የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር ጋዙ እንዲለማ በርካታ ሙከራዎችን አድርጓል፡፡ እንደ ሲኮር፣ ሳንታ ፌ፣ ሳይቴክ፣ ጂዲሲ፣ ኮምፕላንት የመሳሰሉት ኩባንያዎች ጋዙን ለማልማጥ የአዋጭነት ጥናት አካሂደዋል፡፡ በርካታዎቹ ከጥናታቸው የደረሱበት ጉዳይ የኤሌክትሪክ ኃይልን ማመንጨት ለአገሪቱም፣ ለኩባንያዎቹም አዋጭና ጠቃሚነቱን ነበር፡፡ ሆኖም የአገሪቱ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ውኃ ላይ ብቻ ተኮር ስለነበሩ ጉዳዩ ተቀባይነት ስላላገኘ ልማቱ እንደ ቀረ በቂ መረጃዎች አሉ፡፡

ዓለማችን ዛሬ በከፍተኛና የሙቀት መጠን እየተመታች መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ የአየር ንብረቱ በአስከፊ ሁኔታ በመለዋወጡ የተነሳ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በድርቅ እየተመታች ያለችበት ሁኔታ እንደ አዙሪት ይቆጠራል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ዕድል ፈንታ በዚህ ረገድ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ አይቀርም፡፡ የዝናብ መጠን በቀነሰ ቁጥር የግድቦች ውኃ ሲቀንስ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የሚስተጓጎል ከሆነ፣ የአገሪቱ የዕድገት ዕቅዶች እንደማይሳኩ ዕሙን ነው፡፡ ከመግለጫው እንደምንረዳው በርካታ የኢኮኖሚው ዘርፎች በኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ እንደሚጎዱ ገሃድ ነው፡፡ አነስተኛና ጥቃቅን አምራቾችን ሳንጨምር ማለት ነው፡፡ ሆኖም ከብዙ ዘመናት ፍለጋና ከፍተኛ ወጪ በኋላ የተገኘን የተፈጥሮ ጋዝ በተጨማሪ የመጠቀምን ሐሳብ በፖሊሲ የታገደ በመሆኑ፣ አገሪቱን ያለ ተጨማሪ አማራጭ በማስቀረቱ አገራችን በዕውቀት እንዳልተመራች አመላካች ነው፡፡ ስለሆነም በአስቸኳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

የተፈጥሮ ጋዝ ክምችታችን በአየር ንብረት ለውጥ እንደ ግድቦች ውኃ የሚቀንስ አይደለም፡፡ እርሻችንን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ ዕቅድ ቢኖረንም፣ አሁንም በቂ የውኃ ክምችት ማስፈለጉ የግድ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ የተፈጥሮ ጋዝ ኅብረታችንን ለብሔራዊ ዕድገታችንና ጥቅማችን ለመጠቀም የወቅቱ ሁኔታዎች ያስገድዱናል፡፡ በእርግጠኛነት ይህንን ጋዝ በመጠቀም የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት መንግሥት ቢወስንና ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪዎች ጨረታ ቢያወጣ፣ ገንዘባቸውንና ቴክኖሎጂያቸውን ይዘው ለመምጣት በርካታ ኩባንያዎች እንደሚወዳደሩ ያለፉት ዘመናት የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተሞክሮዎች ምስክር ናቸው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...