Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርግንቦት ሃያና አሰልቺው የሞኝ ዘፈን

ግንቦት ሃያና አሰልቺው የሞኝ ዘፈን

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

ከጣና ሐይቅ ፈርጧ ከባህር ዳር ከተማ የመኖሪያ አካባቢዎች አንዱና በቆዳ ስፋቱም ሆነ በያዘው የሕዝብ ብዛት ትልቁ የሆነው ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ክፍለ ከተማ ይባላል፡፡ አካባቢን በቁጥር መጥራት ከተለመደበት አሠራር ጋር በተያያዘ ይበልጡኑ ቀበሌ 14 እየተባለ ጭምር ሲጠራ የቆየው ይኸው የመኖሪያ አካባቢ፣ አዲሱን ስያሜውን የተቀበለው በመካሄድ ላይ ያለውን ለውጥ ተከትሎ ነው፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት ሕጋዊ መጠሪያው በመጀመርያ ግንቦት 20 ቀበሌ አስተዳደር፣ በኋላ ደግሞ ክፍለ ከተማ ሲባል ነበር የዘለቀው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች ክፍለ ከተማቸው ለምን በዚህ ባዕድ ስም ሲጠራ እንደኖረ፣ ከተራ ግምት በዘለለ ዝርዝር ዕውቀት የላቸውም፡፡ በስም አወጣጡ ወቅትም ያማከራቸው አካል አልነበረም፡፡ ብቻ ኢሕአዴግ መንግሥታዊ መንበረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ ልዩ ክብርና ሞገስ ያገኘ ያህል ግንቦት 20 ተብሎ መጠራቱን፣ ስለጉዳዩ የጠየቅኋቸው አንዳንድ ወገኖች በቁጭት ያስታውሱታል፡፡

- Advertisement -

አሁን ማን ይሙት ግንቦት 20 በማደግ ላይ ለምትገኘው የባህር ዳር ከተማ ምኗ ነው? ለተጠቀሰው ክፍለ ከተማዋስ ምን ትሩፋት ቢኖረው ነው የአካባቢው መጠሪያ ስም እስከ መሆን የደረሰው? ለነገሩ ውቢቱ ባህር ዳር በዚህ ረገድ ከሌሎች እህት የኢትዮጵያ ከተሞችም የላቀ የተመራጭነት ዕድል ሳታገኝ አልቀረችም ብል፣ ከምፀት እንዳይቆጠርብኝ አስቀድሜ እማፀናለሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ የከተማይቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ እኮ እስከ ዛሬም ድረስ በግንቦት 20 ስም ነው የሚታወቀው፡፡

የጎንደሩና የመቀሌው አቻዎቹ በአፄ ቴዎድሮስና በአሉላ አባ ነጋ ስሞች በኩራት እንደተሰየሙት ሁሉ፣ በደጃዝማች በላይ ዘለቀ ስም መሆን አለበት እንጂ የምትሉ ወገኖች ብትኖሩ በእጅጉ ከስራችኋል፡፡ በእርግጥ አሁን አሁን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጆች ለመንገደኞቻቸው የአየር ላይ መረጃ ሲሰጡ፣ ‹‹ከባህር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ተነስተናል›› ወይም ‹‹ባህር ዳር አርፈናል›› በማለት፣ ‹ግንቦት 20› የሚለውን ያልተገባ ቅጥያ በራሳቸው ሥልጣን ለማንሳት እየተዳፈሩ መምጣታቸውን ታዝቤያለሁ፡፡ ትግል በየፈርጁ ይሏችኋል እንግዲህ ይኼ ነው፡፡ አንጋፋው የሬዲዮ ጋዜጠኛ ንጉሤ አክሊሉ አድማጮቹን ከአንድ ዓብይ ቁም ነገር ወደ ሌላው አዋዝቶ በቀላሉ ለመሸጋገር ሲፈልግ፣ ‹‹ነገርን ነገር ያመጣዋል›› ማለት ያዘወትራል፡፡ እኔም ይህንኑ የመሸጋገሪያ ብልኃት ከብልሁ ጋዜጠኛ ልዋስና ይህችን ሙጫ መጣጥፍ ወደ ወጠንኩበት ዓብይ ርዕሰ ጉዳይ አዋዝቼ ልረማመድ መሰለኝ፡፡

ሕወሓትና ሰሞነኛው የፃዕረ ሞት መግለጫው

ከሰው ልጅ ፅኑ የስሜት ሕመሞች ሁሉ የፍፁም ቀቢፀ ተስፋን ያህል አደገኛና ለመከራ የሚዳርግ በሽታ የለም፡፡ እንዲህ ያለው ኩነት በጤንነት የማሰብንና ነገሮችን በሚታዩበት ልክ ተረድቶ በትክክል የመመዘንን ተፈጥሯዊ ችሎታ ክፉኛ ይገዳደራል፡፡ ከዚህም የተነሳ ከገቡበት ማጥ እንኳ በደመ ነፍሳዊ ዳበሳም ሆነ፣ በአርቆ አስተዋይነት ለመውጣት የሚኖርን ጭላንጭል ዕድል አስቀድሞ ይዘጋል፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያ ከለውጡ ማግሥት የድርጅታዊ መግለጫዎች ባለዋጋነት አብዝቶ ባሽቆለቆለበት በአሁኑ ወቅት፣ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ትን ባለው ቁጥር ድንገት ተነስቶ በሚያሠራጨው የአቋም መግለጫ ላይ ሐተታዎችን በተከታታይ እየጻፉ ታዳሚያንን ማሰልቸት ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ በውል እረዳለሁ፡፡ ግን ደግሞ አንዳንዶቹ ለከት ያጡ ሆነው እንደ መታየታቸው መጠን ለትችትና ለአስተያየት እንደማይበቁ ተቆጥረው በዝምታ ይታለፉ ቢባል፣ የሰውን ልጅ የመማርና አካባቢን የመገንዘብ አቅም ለመፈታተን የቻሉ ያህል ያላግባብ መተርጎማቸው አይቀርም፡፡

ግንቦት 20ን አስመልክቶ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሰሞኑን ያወጣውና ለሕዝብ ያሠራጨው ድርጅታዊ መግለጫ፣ ከሁሉም በላይ ሕገ መንግሥቱ በብሔር ፖለቲካ አሰባስቦ ያዋቀራት ፌዴራላዊትና ዴሞክራሲያዊት አገራችን በፀረ ሰላም ኃይሎችና በግዛት አንድነት ናፋቂዎች የተጣመረና የተቀነባበረ ህቡዕ ሴራ ከናካቴው ወደ መበታተን ጠርዝ እየተገፋች የመምጣቷን አስከፊ መርዶ አሰምቶናል፡፡ ሕወሓት በዚህ የተለመደ ሟርቱ ከሌሎች የግንባሩ ተጣማሪ ድርጅቶች ተለይቶ ወይም ቢያንስ እነሱን በጊዜ ቀድሞ በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረና አገራችንም እየፈረሰች ስለሆነ፣ ከዛሬው ይልቅ የትናንቱ ይሻለናል በማለት በዴሞክራሲያዊ ሸምቀቆ እንዳይለያዩ አድርጌ አስተሳሰርኳቸው የሚላቸው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በሥርዓቱ ላይ የተደቀነውን የመቀልበስ አደጋ እንደገና ተጠራርተውና  አዲስ የትብብር ግንባር ፈጥረው እንዲታገሉ የቀቢፀ ተስፋ ተማፅኖውን አስተጋብቷል፡፡

በዚህ ጸሐፊ ትዝብት ጀንበር ሲያዘቀዝቅ የተሰማው ይህ ዓይነቱ ዋይታ የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊው ክንፍ የቆሞ ቀርነት ማሳያ ነው ከሚባል በስተቀር፣ ሰሚውን የሚማርክ አንዳች ቃና የለውም፡፡ ቀዳሚ ባለገንዘቦቹ የነበሩት የትናንቷ ሶቪየት ኅብረትና በአምሳሏ የቀረፀቻቸው የቀድሞዎቹ የምሥራቅ አውሮፓ አጫፋሪዎቿ ዓይተውና መርምረው በመጨረሻ ያንገዋለሉት የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ዝቃጭ የሆነው አሮጌው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግብዓተ መሬቱ ከተፈጸመ ከአንድ ሩብ ክፍለ ዘመን በኋላ፣ ዛሬም ነፍስ እንዲዘራበትና አገራዊ የዕድገት መመርያ ሆኖ እንዲያገለግል መመኘቱ የእማሆይ ትርፌን የዘወትር መረግረጊያ ያስታውሰኛል፡፡ ሴትዮዋ፣ ‹‹የባለጌ ሃይማኖት ከጅማት ይጠነክራል፤›› ይሉ ነበር፡፡

‹‹የሞኝ ዘፈን ሁል ጊዜ አበባዬ›› ካልሆነ በስተቀር እውነትም ብልሆቹ መንግሥታት ለረዥም ጊዜ ሲለማመዱት ከቆዩ በኋላ እንዳላዋጣቸው በመረዳት፣ አሽቀንጥረው የጣሉትን አደንቋሪና ቀያጅ ርዕዮት የዚህ ዘመን የሥልጣኔ ትሩፋት ተቋዳሽ መሆን የሚጠበቅበት አፍሪካዊ ቡድን፣ ለምን የሙጥኝ ሊለው እንደሚገባ ለመገንዘብ ከባድ ነው፡፡ ሕወሓት በ11ኛው ሰዓት ላይ ባወጣው በዚህኛው ድርጅታዊ መግለጫ አንድ ሌላ አስገራሚ ነገር ጭሮ ለማለፍ የተመኘ ይመስላል፡፡ እንደ መግለጫው ከሆነ አገሪቱን የገጠማት እንጦርጦስ የመውረድ አደጋ ከመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. የጀመረ ነው፡፡ ይህ ወቅት ደግሞ ሕወሓት ራሱ የታቀፈበት ኢሕአዴግ በጥልቀት ታድሻለሁ በማለት እሱ በፈቀደበት መንገድም ባይሆን፣ የአመራር ለውጥ ያካሄደበትና የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ ወጥ ፓርላማው አማካይነት በይፋ የሰየመበት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ክስተት ነውና ሁላችንም እናስታውሰዋለን፡፡

እንዲህ ያለውን የተንሸዋረረ የሕወሓት አቋም የታዘበ ማንኛውም ሰው ቡድኑ በእርግጥ የኢሕአዴግ አባል ሆኖ ስለመቀጠሉ አብዝቶ ቢጠራጠር ሊገርም ከቶ አይችል ይሆናል፡፡ ለነገሩ ቡድኑ ደጋግሞ በሚዋዥቀው አመለካከቱ ሳቢያ ያን ያህል እምነት ስለማይጣልበት ነው እንጂ፣ በሐሳቡም ሆነ በግብሩ ከግንባሩ ማኅበርተኝነት ከተለየና የጥምረቱ አባል ድርጅቶች ከሚገዙባቸው መርሆችና እሴቶች ማፈንገጥ ከጀመረ እኮ ትንሽ ከራርሟል ቢባል መሳሳት አይሆንም፡፡

ለመሆኑ ግንቦት 20ን ማክበር ያለበት ማነው?

እንደዚህ ጸሐፊ የግል አስተያየት ከሆነ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. የጡት አባቱ በነበረው በሻዕቢያ ታንኮችና ከባድ መሣሪያዎች እየታገዘ ሕወሓት በፊታውራሪነት የመራው ጀግናው የኢሕአዴግ ሠራዊት ወደ መሀል አገር የገባበት፣ የደርግ መንግሥት ሲጠቀምበት የነበረውን የአዲስ አበባ ራዲዮ ‹ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም› ሊያውለው በማሰብ የተቆጣጠረበት ቀን በመሆኑ፣ ቡድኑ ይህንን ዕለት በተለየ ሁኔታ ዓመት እየጠበቀ ቢያከብረው ሊገርመን አይገባም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓል ነው ለማለት ግን በጣሙን ይቸግራል፡፡ እንዲያውም ወታደራዊው ደርግ ዘውዳዊውን ሥርዓት በመፈንቅለ መንግሥት ገልብጦ መንበረ ሥልጣኑን በኃይል ከተቆናጠጠበት ከመስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. በምን እንደሚለይ ለመረዳት ያዳግታል፡፡

ያ ዕለት አፋኙና ጨፍጫፊው የደርግ አገዛዝ የተወገደበት መሆኑ ባይካድም፣ ተተኪው ሥርዓት እምብዛም ከእሱ የተሻለ ሆኖ አለመገኘቱ ግን መላ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያትን ከልብ አሳዝኗል፡፡ ከሦስት አሥርት ዓመታት በፊት በቀጣናው ከቀይ ባህር ኃያላን አንደኛዋ የነበረችው አገራችን ኢትዮጵያ በግንቦት 20 አማካይነት የበኩር ልጇ የነበረችውን ኤርትራን በክፍለ ሀገርነት ማጣቷ ብቻ ሳይሆን፣ ከታሪካዊ የባህር በሮቿ መካከል አንዱንስ እንኳ እንድታስቀር ስላልተፈቀደላት ለዘለዓለሙ በየብስ ተዘግቶባት እንድትኖር በገዛ ልጆቿ ተፈርዶባታል፡፡

መቼም በተጋነነ ወጪ የባህር በር ተከራይቶ ገቢና ወጪ ዕቃዎችን ለማስተናገድ የትንሿ ጅቡቲ ተለማማጭና ጥገኛ ሆኖ ለመዝለቅ ስለዳረገን፣ ግንቦት 20ን በፍቅርና በድምቀት እንድናከብረውም ሆነ እንድናስበው አይጠበቅብንም፡፡ እነሆ ደሃዋ አገራችን እርጥቦችን አስረክባ በደረቅ ወደቦች ግንባታና አስተዳደር ፍዳዋን የምታየው በግንቦት 20 ምክንያት መሆኑን ፈጽሞ መዘንጋት አይቻለንም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ግንቦት 20 በጊዜው አንግቦት የመጣውና በብሔር ላይ የተመሠረተው የፖለቲካ ሥርዓት፣ አሁን ለምንገኝበት የእርስ በርስ መናቆር የዳረገን መሆኑ ሊስተባበል የሚችል አይደለም፡፡ እንደ ደርግ መንግሥት  በይፋ ሳይሆን በህዕቡ በተደራጁ የማሰቃያ እስር ቤቶች በወንጀል ምርመራ ስም በገፍ ስንጋዝና ወደር የሌለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ ሲፈጸምብን የቆየውም በግንቦት 20 ስም መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ይህ ሲታሰብማ ዕለቱ ከብሔራዊው የቀን መቁጠሪያ ቢሰረዝ እንኳ የሚከፋው ወገን ብዙ የሚሆን አይመስለኝም፡፡

ለወትሮው አምባገነኑ የደርግ አገዛዝ የወደቀበት የግንቦት 20 በዓል አከባበር ሕወሓት ብቻ የሚጨነቅበት አጀንዳ አልነበረም፡፡ አበው ‹እምነ መምህሩ ይሄይስ ደቀ መዝሙሩ› ሲሉ እንደሚያስተምሩን፣ በዓሉን የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋሮቻቸው ሳይቀሩ ከሁለት አሥርተ ዓመታት ለበለጠ ጊዜ በታማኝ ጋሻ ጃግሬነት ሲያከብሩትና በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኘውን መገናኛ ብዙኃን ተጠቅመው የአንድ ሠፈር ተጋዳላዮችን ያለመታከት ሲያጀግኑበትና ያለ ይሉኝታ ሲያሞግሱበት ኖረዋል፡፡

እነሆ ‹በድሮ በሬ ያረሰ የለም›ና ካለፈው ዓመት ወዲህ ይህ ዓይነቱ መረን የለቀቀ ጉራ ለበስ ዳንኪራ፣ በእርግጥ ቀስ በቀስ እየቀነሰና እየቀረም የመጣ ይመስላል፡፡ ከዚህ አንፃር ለውጡን እንደ ከሃዲነት የሚቆጥረው ሕወሓት ግን ክፉኛ ቢበሳጭና አዱ ገነትን ከርቀት አሻግሮ እየተመለከተ በቁጭት ቢንገበገብና ቢወራጭ ሊያስደንቀን አይገባም፡፡ ለመፃኢው ዕድላችን የሚበጀው ግን እንደ ቡድኑ አመለካከት ታስረንበት በቆየነው የበረታ እግረ ሙቅ እንደ ተቸነከሩ መዝለቅ ሳይሆን፣ ‹‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል›› ነውና በፅኑ የተቃውሞ ጓጉንቸር እስከ ወዲያኛው ክርችም ብሎ የተቆለፈ የሚመስለውን አዕምሯችንን በአገራችን ለተነቃቃው ለውጥ ክፍት በማድረግ፣ አቃፊ የልማትና የዕድገት አማራጮችን ለመመርመርና ለመቀበል መዘጋጀት ብቻ ይሆናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋከልቲ ያገኙ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...