እነሆ መንገድ። ከመካኒሳ ወደ ጀሞ ልንጓዝ ነው። ቀና ሲሉት እየጎበጠ ታጠፈ ሲሉት እየረዘመ መንገድ ጠመዝማዛው ዛሬም ያሸናል። ለአፍታ ባወጋንበት በዚህ ጎዳና ለዘመን በተወዳጀንበት በዚህ መንገድ ከስሜታችን የታለበ ማስረጊያ ዜማ ‘መለያየት ሞት ነው’ የሚለው ብቻ ነው። አሁን አሁን እየተካው ቅድም በትዝታ ወዲያ ወደ ኋላ እየጋለበ፣ ነገ የሥጋት ጦሩን ሰብቆ እያስጨነቀ ጊዜ ሲያልፍ ጊዜ ይተካል። መንገድ ሲያልቅ መንገድ ይጀመራል። ‹‹አንተ እባክህ መስኮቱን ዝጋው፤›› ትነጫነጫለች የወያላው መከዳ ላይ አንገቷን ያንተራሰች ተሳፋሪ። ‹‹ዕውን መስኮቱ ነው እንዲህ የሚያስጮህሽ? ነገር ነው እንጂ፤›› እያለ ወያላው መስኮቱን ይዘጋል። ‹‹ብርድ ብመታ ታሳክመኛለህ?›› ሙግት ጀመረች። ‹‹ብርድ የሚባል ነገር የለም። ምላስ እንጂ ንፋስ ጥሎን አያውቅም ማነሽ?›› ይላል ግንባሩን ቅጭም አድርጎ ሚስጥር አዘል ሥዕል እንደሚያጠና ሆኖ አጠገቧ የተቀመጠ ጎልማሳ። ‹‹ኧረ ሰማይ የሚባልም የለም። ዕድሜ ለህዋ ሳይንስ. . .›› ይላል መሀል መቀመጫ አጠገቤ የተቀመጠ ወጣት፣ የደወለላቸውን ደንበኛ ከአገልግሎት መስጫ ክልል የሉም ተብሎ የሚያደርገው ጠፍቶት።
‹‹ሳይንስ አልከው? ምናለበት የምናምነውን እያስጨበጡ ያመነውን ቢያስጥሉን?›› ይጠይቃል ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጠ ወጣት። ቆያይቶ ደግሞ፣ ‹‹ለነገሩ እነሱ ምን አደረጉ? የአምላክን ሥራ ገለጡ እንጂ ምን አደረጉ? አለን እንጂ መሬት ክብ መሆኗን የሰማን ዕለት እምነትን ያህል ትልቅ ነገር እንደ ኳስ ልንጫወትበት የሚያምረን?›› ቢል፣ ‹‹እንኳን በክብነት አመንን እንጂ ግዴለም ዞረን ዞረን ከመሬት ነን፤›› ትለዋለች አጠገቡ የተመቀጠች ወይዘሮ። ‹‹ምኑን ተመለስነው ወደ ሮቦት ዘመን እየገባን?›› ሲላት ክንብንቡን እያስተካከለ፣ ‹‹እህ እሱማ እንግዲህ ከአቅም በላይ ነው። መቼም በዚህ ጉዳይ ተመልካች እንጂ ውሳኔ ሰጪ እንድንሆን አልታደልን?›› ብላው ቅብጥብጥ የሚለውን ወያላ አተኩራ አየችው። የሮቦት ወያላ ታያት ይሆን እንዴ? ምን ይታወቃል እኛም በዓይናችን እናይ ይሆናል እኮ!
‹‹እኔ ምለው ግን?›› ይላል ጎልማሳው ወደ ወይዘሮዋና ዲያቆኑ ዘወር ብሎ። ‹‹በተበከለ አየር ልቀት አየር ንብረቱን እንዲህ መፐዋወዛቸው ሳያንስ የሮቦት ማኅበረሰብ ሰው ልጆች መሀል ማቀናጀት ሲያስቡ ዝም ብለን ልናይ ነው?›› ከማለቱ አንዱ የሰሞኑ ብርድ በጥርስ ቁርጥማት አላመጠኝ ባይ፣ ‹‹አስበውማ ጨርሰዋል። ይልቅ በጊዜ ደህና ጥሩር ለብሰን መጠበቅ ነው። እንኳን ከሮቦት ጋር ከታክሲ ተጋፍተን እርስ በርሳችንም ወላልቀን አልቀናል፤›› ብላ መጨረሻ ወንበር የተቀመጠች የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የጨዋታው አባሪ ሆና ብቅ አለች። ‹‹እኔ እኮ. . . ወይ ሐበሻ! . . . አሁን እስኪ የሮቦት ነው የማጣት ታሪካችን ነው የሚቀድመው? በቃ ያልበላንን ዝም ብለን መፎከት?›› አለ በንዴት ከተማሪዋ አጠገብ የተቀመጠ ቸልተኛ መሳይ ወጣት። ‹‹ይቅርታ ‘መፎከት’ ምን ማለት ነው?›› ብላ ሳይሏት ተማሪዋ መጠየቅ።
ልጁም ነገር ያማረው ቢጤ ነው፣ ‹‹ይቅርታ በእንግሊዝኛ የማብራራት አቅም ስለሌለኝ ለቀቅ አድርጊኝ። የዘንድሮ ምሩቃን እንደሆናችሁ የባጥ የቆጡን በጉራማይሌ እየቀየጣችሁ የምታደናብሩን ሳያንስ በገዛ ቋንቋችን ‘ሼም’ ልታሲይዙን እንዲህ ያለ ጥያቄ ትጠይቃላችሁ?›› ብሎ መዳፉን አማታ። ‹‹ኧረ ተረጋጋ። እንዲያውም እሷ እግዜር ይስጣትና አለማወቋን አውቃ ጠይቃለች። ካልክስ አሉልህ በየሚዲያው አገር፣ ወገን፣ ዕድገትና ልማት እያሉ ሲያበቁ በመልካም ቋንቋ አጠቃቀም ችግር የመልካም አስተዳደር ችግራችንን የሚያባብሱት፤›› ብሎ አጠገቤ የተቀመጠው ብሶቱን ሲናገር፣ ‹‹ኧረ እባካችሁ እንዳመጣልን አናውራ? እንዴ! አሁን እስኪ ላትጨርሱ ሳይንስን አንስታችሁ ሮቦቶችን አምታችሁ ስለቋንቋ ያነሳችሁት ምኑ ከምኑ ቢያያዝ ነው?›› ብላ የንፋስ ‹ፎቢያ› ያለባት ወጣት ዘው አለች። ይኼኔ ከጎኗ ‹‹በቃ! ግራ የገባው እኮ ከዚህም በላይ ይቃብዛል። ለማኗኗርም አኗኗር ሲጠፋን ጨዋታስ ላይጠፋን ነው? እንዴት ነው ነገሩ?›› ብሎ ገላመጣትና አረፈው። የአየር ንብረቱ ብቻ ሳይሆን የንግግርና የወግ ሚዛናችን ጭምር ሳይዛባ አልቀረም መሰል ዘንድሮ! ኑሮ ከባድ ሚዛን ሆኖ!
ሾፌሩ ሙዚቃ ሊከፍት ቴፕ ይጎረጉራል። ወያላው፣ ‹‹እስኪ ቅድም ያስጫንኳቸውን ዘፈኖች ክፈታቸው፤›› ብሎ ‘ፍላሽ’ ያቀብለዋል። ‹‹ካልክስ እስኪ የጥላሁንን ጋብዘንማ ሾፌር፤›› ብሎ ጎልማሳው አንገቱን እየወዘወዘ ከንፈሩን መምጠጥ ያዘ። አፍታ ሳይቆይ ደግሞ፣ ‹‹ምን ጥልቅ አድርጎኝ በሰዎች ነገር ምንስ አግብቶኝ በሰዎች ነገር’ አለ አፈር ልብላለትና . . .›› እያለ ሊቀጥል ሲል፣ ‹‹አያገባንም ብለንማ ይኼው አገር ስትፈርስ ይኼው ቆመን እያየን ነው፤›› ብላ ወይዘሮዋ ጉድ አፈላች። ‹‹በሕግ አምላክ! መንግሥት ባለበት አገር አገር ፈረሰ ብሎ ማውራት ወንጀል ነው የእኔ እመቤት፤›› አላት ጎልማሳው ቆጣ ብሎ። ‹‹እህ ታዲያ ዋሸሁ? ዓይተን እንዳላየን ሰምተን እንዳልሰማን መሆናችን መሰለኝ ያለ ሙያው፣ ያለ አቅሙና ያለ ችሎታው ትንሽ ትልቁ አናታችን ላይ ቁብ እያለ የተበጠበጥነው። አይደለም እንዴ? በሉ እንጂ አርሙኝ?›› ብላ ተሳፋሪዎችን ቃኘች።
‹‹ነው። ግን ደግሞ ያገባኛል ይመለከተኛል ባይ ተቆርቋሪም ከመደቆስና ከመዳፈን ሌላ በለስ ሲቀናው አላየንም። ስለዚህ አርፈን ልጆቻችንን ለማሳደግ የጥላሁንን ዓይነት ዜማ ሳንወድ በግድ እንደግፋለን። አይሞት ታዲያ? የሞተ ተጎዳ!›› ብሎ መጨረሻ ወንበር አካባቢ ሰላሳን ያለፈ ወጣት ፀጉሩን እየፈተለ አስተያየት ሰጠን። ‹‹ልክ ነው። ዕድሜ ለሆደ ሰፊው መንግሥታችን መሀል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይመታል ብለን አንሥጋ። ደግሞ. . . ህም. . . ከዝም ጭጭ በቀር ሌላ ዕድሜ ማራዘሚያ ዘዴ አለ እንዴ ጎበዝ? ስለዚህ ምን ጥልቅ አድርጎን?›› ብላ ሳትጨርስ ጋቢና የተቀመጠች ጠይም ቆንጆ፣ ‹‹እኮ ሰው በሰው ላይ ሲሠለጥን፣ ሲያሴር፣ ሲገል፣ ሲሰርቅ፣ ሲያቄም፣ ሲያታልል ዝም? በቃ ይኼ ሆኖ ቀረ አትንኩኝ ባይነት?›› ብለው ከጎኗ ተቀምጠው የነበሩ አዛውንት በትዝብት አዩዋት። ኧረ አንዳንዱንስ እንኳን የትዝብት የአጥፍቶ ጠፊ ዓይንም አላስደነግጠው ብሏል። ምን እንደሚሻል እኮ እንጃ እናንተ?
ከወደ ጋቢና ደግሞ እነሆ ሌላ ጫዋታ ይደመጣል። ከዚህ ቀደም በደንብ የሚተዋወቁ ወዳጅ ቢጤ ናቸው። አንደኛው መምህር ሳይሆን አይቀርም። ‹‹ለመሆኑ አሁንም የምታስተምረው እዚያው ነው ወይስ ቀየሩህ?›› ይጠይቃል የወዲያኛው። ‹‹ተቀይሬ ሌላ ትምህርት ቤት ተመድቤያለሁ። ምን ቦታ መቀያየር መሠረታዊ ለውጥ ያስከትል ይመስል ባለበት የሚረጋ እኮ ጠፍቷል፤›› ይመልሳል መምህሩ። ‹‹ለዚያ ይሆን ሽግሽጉና ዝውውሩ የበዛው?›› ይላል ከወደ ኋላ መቀመጫ አንድ ወጣት። ‹‹በጣም! ምን እንደሚሻለን ግራ ገብቶናል፤›› ከጋቢና ጠያቂው ተናገረ። ‹‹እህል ቢያላምጡት ካልዋጡት ጥቅም የለውም። ሀቁን ተረድተው ካልሠሩበትና ሌሎች እንዲረከቡ ካልታገሉ እውነተኛ ለውጥ ማምጣት እንዴት ይቻላል?›› አለ መምህሩ፡፡ መቼም መምህር ዘንድ ምሳሌ አይጠፋምና በምሳሌ እያብራራ።
ከኋላ መቀመጫ የጋቢናው ጭውውት አንድ ሰበዝ ተመዞ ሌላ መልክ ይዟል። ‹‹ዛሬ የማይቀየር ተጫዋች ቀይረው መስሎን ጉድ የሠሩን? እንዲያው ይኼ መቀያየርና መተካካት ምናለበት በሰዓትና በጊዜው በአግባቡ ተፈጻሚነት ቢኖረው?›› ሲል አንደኛው ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ሰው ሆኖ የማይሳሳት እንጨት ሆኖ የማይጨስ የለም እኮ?›› ይላል፡፡ ‹‹ሰው ሲሠራ ነው የሚሳሳተው። አንዳንዴ ፋታ መስጠት ዕድል አለመንፈግ ቢለምድብን እንዴት ጥሩ ነበር?›› ትላለች ከሴቶች ወገን። ቅያሪውና መተካካቱ በዝቷል። የአቅጣጫና የቦታ እንጂ የአስተሳሰብ መሆንና አለመሆኑን አጣርቶ ማን እንደሚነግረን ግን ግራ ገብቶናል። የጠያቂው ብዛት መጥኔ ያሰኛል!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። አንድ አዛውንቱ ስልክ እየደዋወሉ ከዘመን ጓኞቻቸው ጋር ለመገናኘት ይወተውታሉ። የአንዱን ዘግተው ወደ አንዱ ሲሞክሩ፣ ‹‹በስተርጅና እስኪ አሁን ‘ቢዚ’ ነን ሲሉ አያፍሩም? ምን መዓት ነው የመጣብኝ ልጄ? ዕድሜያችንን በቀልድ አሳልፈን ስናበቃ በማረፊያችን ሰዓት ተሰብስበን የጥንት የጠዋቱን በማውጊያችን እንዲህ ለእንጀራ ተጠምደን እንረፈው?›› እያሉ አንዴ ሾፌሩን አንዴ ወጣቷን ያያሉ። ያ ከሾፌሩ ጀርባ ፊቱ የማይፈታው፣ ‹‹ያኔማ ምን አለ አባት? ቫት የለ ታክስ የለ፣ በየወሩ የቤት ኪራይ አይጨምር፣ የእህል ዋጋ ሰማይ አልነካ። ሁሉ ያለውን ተካፍሎ ይኖራል፤›› ብሎ ተግ ሲል፣ “አሁንስ?” አሉት። የማያውቁትን እንደሚነግራቸው ሁሉ በምፀት እያጤኑት። ‹‹አሁንማ እንኳን የምናካፍለው የምንጎርሰውም በቅጡ አይገኝ። ያዩት የለም እንዴ? ትንሽ መንታፊው ይሻል እንደሆነ እንጂ ሠርቶ አዳሪውስ አልሆነለትም፤›› ብሎ ያንን ፊቱን ይባስ ከሰከሰው።
‹‹እንዴ! ግፉስ እናንተ? የድሮ ሰው እኮ ነው ይኼን ሁሉ ፍዳ ያመጣብን፤›› ሲል ከጎኔ ያለው መዓት እንደመጣብኝ ተሸማቅቄ አየሁት። “የምን ግፍ?” አለው ጎልማሳው። ‹‹የእህል የውኃው. . .›› ሳይጨርስ ጎልማሳው አቋርጦ፣ ‹‹ጡር’ አትልም ታዲያ? በተለያዩ ጉዳዮች ተሸናሽነን በዓይነ ቁራኛ የምንተያየው አንሶ ደግሞ በዕድሜ ልትለያየን ነው? ስንቱን እንገስጽ እናንተ?›› እያለ ያዙኝ ልቀቁኝ አለ። ‹‹ዝም አትለውም? ቋንጣ በጠጅ ተወራረደ፣ በፍሪዳ ደም በጮማ ስብ ታሪክ ተጻፈ ብሎ አባቶቻችንን ከሚወቅስ ፈጣኑ የኢኮኖሚ ዕድገታችን አምሮታችንን ገደበብን ብሎ አይገላገልም? ማንን ፈርቶ ነው? ዘመኑ እኮ የዴሞክራሲ ነው። አህያውን ፈርቶ ዳውላውን? ሆሆ?›› ባዩዋ ወይዘሮዋ ናት። ዕውን ከዓባይ መገደብ የአምሮታችን መገደብ የሚያብከነክነን ብዙ እንሆን እንዴ? ግን በቀኝ ሲሉት በግራ እያለ ዳኝነትን እንዲህ ያከበደው ምን ይሆን ጎበዝ? ፍርድ እንደ ራስ ነው ብለን እንውረድ? ወይስ አጥንት ድረስ ዘልቆ በሚሰማው ቅዝቃዜ እናስብ? ‹እትትት. . .›› ያለው ማን ነበር? ‹እንኳን ተነክተን እንዲሁም ቁጡ ነን› ተብሎ ነበር በአንድ ወቅት፡፡ መልካም ጉዞ