ከሥራ አጥነት እስከ ሰብል ምግብ እጥረት ፈታኝ ችግሮች ተንሰራፍተዋል
ከማዳበሪያ ፋብሪካዎች እስከ መስኖ እርሻ ጅምሮች ተስፋ ተደርገዋል
የግብርናው ዘርፍ በዕቅድ የተቀመጠለትን ሳያሳካ ያውም በዝቅተኛ ደረጃ እንዲያሳካው የሚጠበቀውን ውጤት ሳያስገኝ የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዓመታትን ሊያገደባድድ ዓመት ፈሪ ሆኗል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ውጤት የተገኘባቸውና ተስፋም የሰጡ ክንውኖች የመኖራቸውን ያህል፣ አደጋ እየደቀኑ የመጡ ሥጋቶችም ተበራክተዋል፡፡
ከሥጋቶቹ መካከል ሚዛን የሚደፋው ደግሞ የግብርናው ዘርፍ በቂ ምርት ማምረት ተስኖት መገኘቱ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 20 ሚሊዮን ያህል ሕዝብ በምግብ ዕጦት ችግር ውስጥ እንዲገሚገኝ ሲገለጽ፣ የአገሪቱ አምራች አካባቢዎችም በአዳዲስና መጤ የእንሳስትና የሰብል በሽታዎች የአደጋ ቀለበት ውስጥ መውደቋን መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡ የአየር ሁኔታ ትንበያዎችም በመጪው ክረምት መደበኛና ከመደበኛ በታች የዝናብ መጠን በአብዛኛው የክረምት አብቃይ አካባቢዎች እንደሚጠበቅ የአየር ሁኔታ ትንበያዎች እንደሚሳዩ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ይፋ አድርጓል፡፡
ምንም እንኳ በአገሪቱ የሰብል ምርቶች መጠን በየጊዜው እየጨመረ እንደሚገኝ ቢጠቀስም፣ አሁንም ድረስ ከ20 ሚሊዮን ያላነሰ ሕዝብ ለምግብ ዕጦት መዳረጉን፣ ከአገሪቱ ሕዝብ 38 በመቶ ሕፃናት ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተዳረጉባት ኢትዮጵያና የግብርና መስኳ አሳሳቢም አስፈሪም ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ባለሥልጣናት የገለጹበት መድረክ በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ተሰናድቶ ነበር፡፡
ከቀበሌ፣ ከወረዳና ከዞኖች ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የግብርናው ዘርፍ አመራሮች ብሎም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ምክትላቸው አቶ ደመቀ መኮንን እንዲሁም የየሚኒስቴሩ ሹማምንት በአዳማ ከተማ ግንቦት 17 እና 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ተሰብስበው ስለግብርናው ዘርፍ መክረዋል፡፡ ከ1,500 በላይ አመራሮች የታደሙበት ይህ መድረክ ‹‹ለግብርና ትራንስፎሜሽን የአመራሩ ሚና›› በሚል ርዕስ በተካሄደው ስብሰባ ወቅት የአደጋ ሥጋቶች መኖራቸው በሰፊው ሲጠቀስ ነበር፡፡
ቅዳሜ ግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ተጀምሮ እሑድ በተጠናቀቀው የሁለት ቀናት ስብሰባ፣ መነሻውን በግብርና መስክ የአመራሩ ሚናና የዘርፉ ችግሮችና ተስፋዎች ላይ ያጠነጠነ አጀንዳ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የመሩት ይህ ስብሰባ፣ የግብርና ሚኒስቴር ኃላፊዎችም የክልል አመራሮችም ሥጋታቸውንና ተስፋቸውን ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
‹‹የልማት አክቲቪዝም››
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግብርናው ቢያድግም፣ ለኢኮኖሚው የድርሻውን ቢያበረክትም በበርካታ ማነቆዎች ተተብትቦ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ግብርና ሊሰጠን የሚችለው በሰጠነው ልክ ነው፡፡ ዝናብ እየተጠበቀ የሚሠራው ሥራ እዚህ አድርሶናል፡፡ ጊዜና ወቅትን ጠብቆ በሚደርስ የግብርና ውጤት የትም መድረስ አይቻልም፤›› በማለት፣ በየመጠለያው የሚገኙ ዜጎችን፣ የዕለት ደራሽ የምግብ ዕርዳታ የሚጠባበቁትን ከምግብ ዕጦት አዙሪት ለማውጣት ግብርናውን መለወጥ ያሻል ያሉት አቶ ደመቀ፣ ግብርናው በበልግ ዝናብ መቅረት የምርት ዕድል እንዳጣ አስታውሰዋል፡፡
‹‹ግብርና ከምርት በላይ ነው›› ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የመስኖ ሥራ ለምግብ ሰብል ምርት መጨመር አንዱ መፍትሔ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ የአነስተኛና መካከለኛ መስኖ እርሻን ማስፋፋት ይገባል በማለት ‹‹የልማት አክቲቪዝም›› ወይም የልማት አራማጅነት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የልማት አራማጅነት እንዲተገበርባቸው ከተጠየቁት መካከል አገሪቱ ለምትገኝበት ከፍተኛ የሥራ አጥነት ችግር የግብርና ልማት ሥራ እንደሆነ፣ በዚህም አብዛኛው ሥራ ያጡ የገበሬው ልጆች በመሆናቸው፣ በቤተሰብ እርሻና በግብርናው መስክ አነቃናቂ መሪዎች እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ መከናወን አለበት ብልዋል፡፡
ምንም እንኳ የግብርና ልማት አራማጅነትና የወጣቶች የግብርናው ዘርፍ ተዋናይነት መምጣት አለበት ይበሉ እንጂ፣ አብዛኛው የወረዳና የዞን አመራር ብሎም የፌዴራል ግብርና ሹማምንት ግን በዘርፉ የሚታየው ችግር እንደውም ከዘርፉ ለመውጣት ያለው ከፍተኛ ፍላጎት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ ከ70 በመቶ ያላነሱ የዘርፉ ሠራተኞችና ባለሙያዎች በአነስተኛ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ከባድ የሥራ ጫና ባለበት ዘርፍ ውስጥ መቆየት እንደማይፈልጉ ግብርና ሚኒስቴር ማጥናቱን ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሑሴን ይፋ አድርገዋል፡፡ እንደውም በ80 ቀናት ውስጥ በተከናወነ ጥናት አብዛኛው ተሳታፊ ካነሳቸው በላይ በርካታ ችግሮች መታወቃቸውን አስታውሰዋል፡፡
ጽሑፍ አቅራቢዎቹ ሚኒስትሮች
የግብርናው መድረክ በአንድ ጊዜ ከላይ እስከ ታች ያሉ ኃላፊዎችን በአንድ መድረክ ሲያገናኝ የመጀመሪያው ነው ተብሎለታል፡፡ ተሳታፊዎችም በዚህ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ የመድረኩ አጋፋሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲም ይህ መድረክ፣ እንደሌላው ጊዜ በባለሙያዎች ሳይሆን በሚኒስትሮች ጽሑፍ የቀረበበት በመሆኑ የለውጥ ጅምርነቱን አጣቅሰዋል፡፡
በመሆኑም የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን ስለሚመሩት ዘርፍ ሥጋቶችና ተስፋዎች ብሎም ስለሚገኝበት ወቅታዊ ሁኔታዎች አቅርበዋል፡፡ የግብርናው ዘርፍ ዕድገት እያስመዘገበ እንደመጣ አስታውሰው፣ ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ሊደረስበት ከሚገባው በታች እያደገ እንደሚገኝ አሳይተዋል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን፣ በዝቅተኛው የዕድገት መሰላል በየዓመቱ እንዲያድግ የታቀደው በስምንት በመቶ ነበር፡፡ ይሁንና ያደገው ግን በ5.7 በመቶ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ካለፉት ሁለት ዓመታት አኳያ የተሻለ ይባል እንጂ ከሦስት በመቶ በታች ያደገበት ወቅትም ነበር፡፡ ይህ ሊሆን የሚችልበት ቅድመ ትንበያ አመላካቾች እንደታዩና፣ ዕድገቱ ወደ 2.8 በመቶ ዝቅ ሊል የሚችልባቸው ሁኔታዎች ስለታዩ፣ አመራሩ ‹‹የአደጋ ጊዜ ጥሪ›› ማስተጋባት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በወጪ ምርቶች ረገድም መስክ በተለይ በቅባት እህሎችና በጥራጥሬ ምርት ላይ ሊከሰት እንደሚችል የተተነበየው የምርት ቅናሽ አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡ በቅባት እህሎች የአሥር በመቶ፣ በጥራጥሬ የ5.2 በመቶ የምርት ቅናሽ ሊኖር እንደሚችል አመላክተዋል፡፡
ምንም እንኳ በምርት መመዘኛዎች ሲታይ ከምሥራቅ አፍሪካ የተሻለ ቢመስልም የኢትዮጵያ ግብርና የተራራ ያህል የከበዱ ሥጋቶች ተደቅነውበታል፡፡ ከኢትዮጵያ ጠቅላላ ኢኮኖሚ (ከአገር ውስጥ ምርት አንፃር) የ34 በመቶ ድርሻ የያዘው ግብርና፣ የአገሪቱን አንድ አራተኛ ሕዝብ ማለትም 18 ሚሊዮኖችን መመገብ ያልቻለ፣ በድርቅ አደጋ ብቻ ከ5.7 ሚሊዮኖች በላይ ለዕለት ደራሽ ዕርዳታ የተዳረጉባትንና ከሦስት ሚሊዮን በላይ የእርስ በርስ ግጭት ሰለባዎችን መታደግ ያልቻለ ሆኖ ይገኛል፡፡
ዘርፉ በዝናብ ላይ ጥገኛ ከመሆኑ ባሻገር በግብዓት አቅርቦት ችግሮች የታጠረ፣ ዘመናዊ ዘዴዎችና የመስኖ እርሻ እምብዛም የማያውቁት ሆኖ ከርሟል፡፡ አገሪቱ ያላት የእንስሳት ሀብትም ይህ ነው በሚባል ደረጃ ጥቅም ላይ ያልዋለ፣ እንደውም ሚኒስትር ኡመር እንደጠቀሱት የመንግሥት ዓይኖች እያዩ እንስሳቱ ድንበር ተሻግረው ለጎረቤት አገሮች ሲሳይ የሆኑበት ደካማ መስክ ነው፡፡ ‹‹አመራሩም ባለሙያውም ዓይኑ እያየ እንስሳት ተነድተው እየወጡ ነው፡፡ ግመልና ፍየል የሚወጣባቸው ድንበሮች ይታወቃሉ፡፡ በሶማሌ በኩል፣ በሑመራ በኩል እየተነዳ ነው፤›› ያሉት አቶ ኡመር፣ በተለይ የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ሙስጠፋ አህመድ ድንበሩ ላይ ቁጥጥር በማድረግ ካገዙ ለውጥ ይኖራል ብለዋል፡፡ ‹‹ዘንድሮ ግብርናው አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን እያየን ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ በእንስሳት መኖ እጥረት፣ በማዳበሪያና በምርጥ ዘር ችግር ገበሬው እየተናጠ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
ከተሳታፊዎቹ በተደመጠው መሠረትም ከዚህ በፊት ገበሬው ሳይፈልግ ማዳበሪያ በግድም ጭምር እንዲጠቀም እንዲለምድ ተደርጓል፡፡ አሁን በተራው ገበሬው ሲለምደው፣ ስጡኝ አምጡልኝ ማለት ሲጀምር ግን የአቅርቦት ችግር መፈጠሩን እንደውም ‹‹ገበሬውን ለስብሰባ ስንጠራው ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ካላመጣችሁ አትጥሩን፤›› ይለናል በማለት ከወረዳና ከዞን የተገኙ የግብርና ኃላፊዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ስለምርጥ ዘር እጥረቱም ሆነ ስለማዳበሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት ሚኒስትሩ፣ የማዳበሪያ አቅርቦት ላይ የታዩ መንጠባጠቦች ቢኖሩም፣ በዚህ ዓመት የ25 መርከቦች የማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ እስካሁንም 18 መርከቦች ወደብ ደርሰው፣ ማዳበሪያውም ወደ አገር ውስጥ መግባቱን አስታውቀዋል፡፡ በአማካይ ከ35 እስከ 40 በመቶ ሥርጭት መካሄዱንም ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ለማካሄድ ከውጭ ኩባንያ ጋር የሽርክና ስምምነት መፈረሙን አቶ ኡመር ገጸዋል፡፡ በስብሰባው ማጠቃለያ ዕለት የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በበኩላቸው፣ በቅርቡ ይፋ የሚደረገው የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት፣ ከውጭ ፎስፌት ብቻ በማስመጣት እንደ ተፈጥሮ ጋዝና ፖታሽ ያሉ ግብዓቶች በአገር ውስጥ ስለሚገኙ በቶሎ ፋብሪካውን ዕውን ለማድረግ የሚቻልባቸው ዕድሎች አሉ ብለዋል፡፡
በምርጥ ዘር በኩል በተለይ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ማሽላና ጤፍ ትኩረት እንደተሰጣቸው ሲገለጽ፣ በመስኖ እርሻ መስክም አገሪቱ የምትመራበት የወደፊት የግብርናው መንገድ ተደርጓል፡፡ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ለአነስተኛና መካከለኛ መስኖ ሥራዎች መንግሥት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት እንደሚመድም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ አቶ ኡመር በበኩላቸው በአፋር ክልል በ3000 ሔክታር መሬት ላይ በመስኖ የለማ ስንዴ ጥሬ በሙከራው ውጤት ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡ በአነስተኛ መስኖ እርሻ ከ471 ሺሕ ሔክታር በላይ ለማልማት መታቀዱም ታውቋል፡፡
እንዲህ ያሉ የተስፋ ጅምሮች የተንጸባረቁበት የኢትዮጵያ ግብርና፣ በዚህ ዓመት ካስገኘው ከ300 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት፣ በመጪው ዓመት ወደ 406 ሚሊዮን ኩንታል እንዲያስገኝ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
በሌላ በኩል በመላ አገሪቱ በክረምቱ ወራት ሕፃናት ተማሪዎች ሳይቀሩ ከሰኔ 30 በፊት የሚሳተፉበት አገር አቀፍ የዛፍ ችግኝ ተከላ ፕሮግራም እንደሚካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በአዳማ ገልማ አባገዳ አዳራሽ አቅራቢያ ችግኝ በመትከል መርሐ ግብሩን አስጀምረዋል፡፡ አራት ቢሊዮን ችግኞች እስከ ነሐሴ መጨረሻ እንደሚተከሉም ታስቧል፡፡
‹‹ውሎ አዳሩና ቡና መጠጫው ወሬ ሁሉ ፖለቲካ ከሆነበት አጉል አዙሪት በመውጣት፣ ወደ ልማት መዞር አለብን፤›› ያሉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ተቋም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም፣ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን የልማት አክቲቪዝምን ሐሳብ በማጠናከር፣ ስለአገሪቱ ወቅታዊ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ብሎም በአጣዳፊነት መሠራት ስላለባቸው የግብርና ልማት ሥራዎች አብራርተዋል፡፡