[ለክቡር ሚኒስትሩ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ይደውሉላቸዋል]
- እንኳን አደረስዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ለምኑ?
- ለድል በዓል ነዋ፡፡
- አለፈ አይደል እንዴ?
- መቼ ነው ያለፈው?
- ባለፈው አይደል እንዴ የዓድዋን የድል በዓል ያከበርነው?
- እኔ ለዚህኛው የድል በዓል ነው እንኳን አደረስዎት ያልኩዎት፡፡
- ለየትኛው የድል በዓል?
- እየቀለዱ ነው ወይስ የምርዎን ነው?
- ኧረ የምሬን ነው፡፡
- እየቀለዱ ነው እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምን ቀልድ ነው?
- እንደዚያ ስንት መስዋዕትነት የተከፈለበትን የድል በዓል እንዴት አያስታውሱትም?
- የምን መስዋዕትነት ነው የተከፈለው?
- በሉ እዚህ ጋ ያቁሙ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑን ነው የማቆመው?
- ቀልዱን ነዋ፡፡
- የምን ቀልድ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር ለዚህ የድል በዓል ሕዝብ ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሷል፡፡
- ትንሽ አታፍርም?
- ምኑ ነው የሚያሳፍረኝ?
- የድል በዓል ስትል ነዋ?
- እና የምን በዓል ነው?
- ያልገባኝ ነገር ምኑ ነው ድሉ?
- እ. . .
- ወንድም ወንድሙን ገድሎ የምን ድል አለ?
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር?
- ስማ ወንድም የራሱን ወንድም ገድሎ ምንም ዓይነት ድል ሊኖር አይችልም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በግንቦት 20 እንዲህ ሊቀልዱ አይችሉም፡፡
- ከገባህ የሚሰማኝን ነግሬሃለሁ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ጨቋኝና አሸባሪውን የደርግ ሥርዓት የገረሰስንበት በዓል እኮ ነው፡፡
- ጥያቄው እሱ አይደለማ፡፡
- ምንድነው ጥያቄው?
- በምትኩ ምን ዓይነት ሥርዓት ገነባችሁ የሚለው ነው?
- ዴሞክራሲያዊና አገሪቱን በልማት ጎዳና ያስኬደ ሥርዓት ነዋ፡፡
- ለዚያ ነው አሁን አገሪቱ እንደዚህ እየተተራመሰች ያለችው?
- እ. . .
- አገሪቱ እኮ በግጭት ከመተራመሷ ባሻገር ደሃ ከሚባሉት አገሮች መካከል ናት፡፡
- ከሥልጣን አባረራችሁና ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እ. . .
- ሕዝቡን ስላስመረራችሁት እኮ ነው ያበረራችሁ፡፡
- እሱማ በሴራ ነው የተባረርነው፡፡
- ሴራውንም ቢሆን ከእናንተ በላይ የሚያውቀው ማን አለ?
- ሴረኞች ናችሁ እያሉን ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ጥያቄ አለው?
- ጊዜ ጥሎን ነው ግዴለም፡፡
- የጣላችሁ ጊዜ ሳይሆን ሥራችሁ ነው፡፡
- ለማንኛውንም አሁን እንዴት ነው የሚከበረው?
- ምኑ?
- ግንቦት 20 ነዋ፡፡
- አታስቀኝ እስኪ፡፡
- ምኑ ነው የሚያስቀው ክቡር ሚኒስትር?
- እንዲያውም ምን ልናደርግ እንደሆነ ታውቃለህ?
- ምን ልታደርጉ ነው?
- ልንሰርዘው፡፡
- ምኑን?
- ግንቦት 20!
[ለክቡር ሚኒስትሩ ሌላ የቀድሞ ሚኒስትር ስልክ ደወሉላቸው]
- በጣም ያሳዝናል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ ነው የሚያሳዝነው?
- ያሉትን ሰምቼ በጣም አዝኛለሁ፡፡
- ምን አልኩ?
- የድል በዓል ይሰረዛል እያሉ ነው አሉ?
- እናንተ ሰዎች ምን ሆናችኋል?
- ምን ሆንን?
- ይህ በዓል በምንም መለኪያ የድል በዓል ሊባል አይችልም፡፡
- ለምንድነው የማይባለው?
- በጦርነት ድል ሊባል የሚችለው ልክ እንደ ዓድዋ ወራሪ ኃይልን ድል ስንነሳ ነው፡፡
- ድሮም ለእናንተ ከዓድዋ በላይ መቼ የድል በዓል አለ?
- ወንድም ወንድሙን ገድሎ ድል ሊኖር አይችልም፡፡
- በግንቦት 20 በርካታ ድሎች ተገኝተዋል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እስኪ ጥቀስልኝ?
- አፋኙና ጨቋኙ የደርግ ሥርዓት ተገርስሷል፡፡
- እሺ?
- አገሪቱ ከድህነት አረንቋ ወጥታለች፡፡
- ሌላስ?
- ሕዝቡ ከባርነት ቀንበር ተላቆ በነፃነት መኖር ጀምሯል፡፡
- ኪኪኪ. . .
- ምን ያስቃል?
- ሌላ ነፃ ያወጣችሁት አገር ነበር እንዴ?
- ምን ማለት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- ስለየትኛዋ አገር ነው የምታወራው ብዬ ነው?
- ስለኢትዮጵያ ነዋ፡፡
- በእርግጥ አፋኙና ጨቋኙ ደርግ ተገርስሷል፡፡
- እሱን እኮ ነው የምልዎት፡፡
- ግን በምትኩ ሌላ አፋኝና ጨቋኝ ሥርዓት ነው የተተካው፡፡
- እ. . .
- አገሪቱም ከድህነት ወደ ድህነት ነው የተሸጋገረችው፡፡
- እንዳይሳሳቱ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሕዝቡም ቢሆን ከባርነት ወደ ሌላ ባርነት ነው የተሸጋገረው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎ የድሮ ሥርዓት ናፋቂ እንደሆኑ አውቃለሁ፡፡
- እናንተ ናችሁ እንጂ የድሮ ሥርዓት ናፋቂዎች፡፡
- ለማንኛውም ይህ የድል በዓል በደመቀ መንገድ እንዲከበር እንፈልጋለን፡፡
- እሱ ድሮ ቀረ፡፡
- እንግዲህ እንተያያለን፡፡
- ምኑን ነው የምንተያየው?
- በዓሉ እንዴት እንደሚከበር ነዋ፡፡
- ምን ልታደርጉ?
- የድል በዓሉን ወደ ቀድሞ ክብሩ ለመመለስ ሁሉን ነገር እናደርጋለን፡፡
- እኮ ምን?
- ካስፈለገም እንገባለን፡፡
- የት?
- ጫካ!
[ደላላው ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ይመጣል]
- ለምን መጣህ?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- እዚህ ቢሮ እንዳትመጣ ብዬህ አልነበር?
- አይቆጡ እንጂ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የምነግርህን ለምን አትሰማም?
- በስልክ የማይወራ ጉዳይ ይዤ ነዋ፡፡
- ታዲያ ውጪ ለምን አትቀጥረኝም?
- መቼ ጊዜ አለዎት ክቡር ሚኒስትር?
- ለመሆኑ የምን ጉዳይ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር ሕይወታችንን የሚቀይር ጉዳይ ነው፡፡
- መቼም ደላላዎች ስትባሉ ሲኦል ራሱ ገነት ነው ብላችሁ ነው የምታወሩት፡፡
- የእውነቴን ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኮ ምንድነው?
- በአጭር ጊዜ ሚሊየነሮች የሚያደርገን ሥራ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ንገረኛ?
- ግን ትንሽ ያስፈራል፡፡
- ምኑ ነው የሚያስፈራው?
- ሕገወጥ ነዋ፡፡
- አንተ መቼ ሕጋዊ ሥራ ሠርተህ ታውቃለህ?
- እርሱስ እውነትዎን ነው፡፡
- እኮ ንገረኛ?
- የኦርጋን ሽያጭ ነው፡፡
- የምን ኦርጋን?
- የሰው ነዋ፡፡
- ምን?
- በቃ የሰዎች የሰውነት ክፍሎችን መሸጥ፡፡
- እ. . .
- ክቡር ሚኒስትር የሚገርም ቢዝነስ ነው፡፡
- የሞቱ ነው በሕይወት ያሉ ሰዎች የሰውነት ክፍል የሚሸጠው?
- የሁለቱም፡፡
- እ. . . እንዴት?
- የሰውነት ክፍሎቹ ከሞቱ ሰዎች ላይም በሕይወት ካሉትም ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡
- በሕይወት ካሉት እንዴት ነው የሚወሰደው?
- ሰዎቹ ይጠለፉና ማደንዘዣ ተወግተው የሰውነት ክፍላቸው ይወሰዳል፡፡
- እ. . .
- ሥራውን በሚገባ የሚያውቁት ባለሙያዎች ስላሉ ስለሱ አይጨነቁ፡፡
- የሰውነት ክፍል መሸጥ ሕገወጥ እኮ ነው?
- ሕጋዊ ሥራማ እንደማልሠራ ያውቃሉ?
- ወይ ጣጣ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ሁለታችንም በአንዴ ነበር ሚሊየነሮች የምንሆነው፡፡
- ስማ ይኼን ቆሻሻ ገንዘብ ከየት አመጣሁ እላለሁ?
- ለእርሱ አይጨነቁ፡፡
- ለምን አልጨነቅ?
- መፍትሔ አለን፡፡
- ምን ዓይነት?
- ገንዘቡ. . .
- እ. . .
- ይታጠባል!
[ለክቡር ሚኒስትሩ ሌላ የመሬት ደላላ ስልክ ይደውልላቸዋል]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት ነህ?
- አሁን በቃ ቀን መጣልን፡፡
- እንዴት?
- ሁሉን ነገር አመቻችቼያለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምን አመቻቸህ?
- በርካታ መሬት ፈላጊዎች አግኝቻለሁ፡፡
- እሺ?
- የሚፈለጉ ቦታዎችንም የሚያቀርቡልኝ ሰዎች አግኝቻለሁ፡፡
- በጣም ጥሩ፡፡
- ለቦታዎቹ ሕጋዊ ዶክመንቶችን የሚያዘጋጁልን ተገኝተዋል፡፡
- ሥራ በዝቶብህ ነበራ?
- የመሬት ወረራው ሲደረግ አፋጣኝ ግንባታ የሚያከናውንልን ድርጅትም ተገኝቷል፡፡
- ስለዚህ ሁሉም ዝግጁ ነው እያልከኝ ነው?
- ክቡር ሚኒስትር የሚጠበቀው የእርስዎ ይሁንታ ብቻ ነው፡፡
- እ. . .
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ያው ሕገወጥ ነገር ያስፈራል እኮ?
- ክቡር ሚኒስትር እኛ ምን ቸገረን የድርሻችንን ይዘን ዞር ማለት ነው፡፡
- ያው ከፍተኛ የመሬት ወረራ ለመፈጸም ስላቀድን ትንሽ ፈራሁ፡፡
- ምንም አያስቡ ሁሉን ነገር እኮ ሕጋዊ ሽፋን ሰጥተን ነው የምናንቀሳቅሰው፡፡
- ለመሆኑ ያ ሁሉ መሬት ሲታጠር ምን ልንል ነው?
- ከተማ እየገነባን ነዋ፡፡
- ምን ዓይነት ከተማ?
- ሕገወጥ ከተማ!