በዚህ አርዕስት ስር አንባቢያንን ሊያስደንቁና ሊስቡ ይችላሉ ተብለው የተመረጡ ዝርዝር ነገሮች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡ እነዚህ ዝርዝር ነገሮች የተለያዩ የአዕዋፍ ዝርያዎችን የተለያዩ ባህርያትንና ተፈጥሮአቸውን የሚዳስሱ ናቸው፡፡
የዶሮ ጥርስ?
ዶሮች ብቻ ሳይሆኑ በአጠቃላይ የወፍ ዝርያዎች ጥርስ-አልባ ናቸው፡፡ ጥርስ አልባ መሆናቸው ግን ችግር አልፈጠረባቸውም፡፡ ስለዚህ ያለምንም ችግር ምግባቸውን ሲውጡ ይታያል፡፡ ለዚህም ጭንጭራ (Gizzard) የተባለው የጨጓራቸው ክፍል ይረዳቸዋል፡፡ አንዳንዴም አነስ ያሉ ድንጋዮችን በመዋጥ ከጭንጭራ ጋር በአንድነት ምግብን (እንደ ፍሬና ጥራጥሬ ያሉትን) ለማድቀቅ ይጠቀሙበታል፡፡
ከረጢት የመሰለ ቋተ-መኖ፡- የኦሶፋገስ (Oesophagus) ክፍል ያላቸው ሲሆን፤ ምግብን ለማጠራቀም ይረዳል፡፡ ይህ ክፍል ብዙ ምግቦች ሳይፈጩ በፊት ያለምንም ችግር እንዲቀመጡበት ይሆናል፡፡ እንደ ርግብ ያሉ ጥቂት ወፎች ደግሞ ወተታማ ነገረ ቋተ-መኖው ውስጥ ያመነጫሉ፡፡ ይህንንም ለጫጩቶቻቸው በማስመለስ ይመግቧቸዋል፡፡
ወፎች ከቀጭኔ ይበልጣሉ?
ከቀጭኔ የአንገት አጥንት ይልቅ ማናቸውም የወፍ ዝርያዎች በቁጥር የበለጠ አጥንት አላቸው፡፡ የአጥንቱ ቁጥር እንደየወፉ ዓይነት ይለያያል፡፡ ረጅም አንገት ያላቸው የበለጠ የአንገት አጥንት አላቸው፡፡ የእንግሊዝ ስፓሮው (English Sparrow) -14፣ ዳክዬ -16 እና ስዋን (Swan) -23 ሲኖራቸው ቀጭኔ ግን እንደ ማንኛዎቹም አጥቢዎች 7 ብቻ ነው ያለው፡፡
በሽታ ተሸካሚዎቹ
ከወፍ ወደ ሰው ጥቂት በሽታዎች ይተላለፋሉ፡፡ ከሁሉም ግን የበቀቀን ትኩሳት (Parrot Fever) አደገኛ ነው፡፡ በሽታው በብዛት የእንስሳት መሸጫ ውስጥ የሚሠሩትን ያጠቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወፎች የተባዮችና ሌሎች ጥገኞች አስተናጋጅ ሆነው ይገኛሉ፡፡ በዚህም በሽታን ወደ ሰውና እንስሳ ያስተላልፋሉ፡፡
ከጥቅም አንፃር ሲታይ ደግሞ ወፎች ብዙ ተባዮችን ለመቆጣጠር ይረዳሉ፡፡ አንዳንድ ዝርያዎች ሦስት አፅቄዎችን (Insects)፣ ወባንና በንክሻ በሽታ የሚያስተላልፉ ሦስት አፅቄዎች (Insects) በመብላት ይታወቃሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ሺስቶሶማ (Schistosoma) የሚያስተላልፈው ቀንድ አውጣ በብዛት በውኃ ውስጥ ወፎችና ጋጋኖን በመሳሰሉ ይበላል፡፡
9,900 ከሚገመቱት የወፎች ዝርያ ግማሾቹ ሦስት አፅቄዎች ይመገባሉ፡፡ ብዙዎቹ በዋነኝነት ሦስት አፅቄዎችን ለምግብነት ይመርጣሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙዎቹን ጎጂ ሦስት አፅቄዎችንም በመቆጣጠር ያገለግላሉ፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎችም በሦስት አፅቄዎቹ ሊመጣ ከሚችል አደጋ ይከላከላሉ፡፡ በተለይም ሰብሎችን ከጥፋት በመታደግ፡፡
ጠላቶቻቸው
የወፎች ጠላቶች ከሦስት አፅቄዎች እስከ ሰዎች ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ የወፍ ዝርያዎችም ለሌሎች የወፍ ዝርያዎች ጠላት ናቸው፡፡ አንዳንድ ጉንዳኖች ዕንቁላሎችን በመውሰድና መሬት ላይ ያሉ የወፍ ጉጆዎችን በማውደም ይታወቃሉ፡፡
ቀበሮ፣ ዊዝል (Weasel)፣ ስከንክ (Skunk)፣ አርማዲሎ (Armadillo)፣ እንሽላሊት፣ እባብ እንዲሁም ሌሎች እንስሳት የወፎችን ዕንቁላል ከጎጆ አውጥተው ይመገባሉ፡፡ በዚህ ደረጃ ቁራ (Crow)፣ ማግፒ (Magpi) እና ሰማያዊ ጃይ (Blue Jay) በጣም አደገኛ አጥቂዎች ተብለው ይመደባሉ፡፡ ታዳጊ ወፎች ደግሚ ከኤሊ እስከ ጭልፊት ድረስ ጠላት ይኖራቸዋል፡፡ ሙቀት፣ መብረቅ እና በሽታም ጉዳት ያደርስባቸዋል፡፡ ሰው ደግሞ ብዙዎችን አጥፍቷል፤ አለያም የተፈጥሮ መገኛቸውን አጥብቧል፡፡ የቤት ውስጥ ድመቶችና ሌሎች እንስሶችም ለመጥፋታቸው እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡
ለሰው ጠቃሚዎቹ
አንድ አንድ ወፎች ለምግብነት ያገለግላሉ፤ ላባቸውም በዋነኝነት የሴቶችን ባርኔጣ ለማስዋብና ትራስ ለመሥራት ስለሚያገለግል በጣም ተፈላጊነት አለው፡፡ እነዚህም ማስዋቢያዎች የሚገኙት ከእዝዝ ወፎች፣ ሳቢሳዎች (Egrets) ፣ ሸመላዎች (Herons)፣ የገነት ወፎች (Birds of paradise)፣ ተርን (Terns)፣ ስዋን (Swan)፣ ኮንዶር (Condor) እና አልባትሮስ (Albatross) ነው፡፡ ይህም ተፈላጊነታቸው የወፎቹን ቁጥር ሲያመነምን ይታያል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚበሉ የአዕዋፍ ዝርያዎች ረጅም ርቀት መብረር የማይችሉት ናቸው፡፡ እነዚህም ጅግራ (Guineafowl)፣ ቆቅ (Partridge)፣ ቤት ዶሮዎች (Domesticfowl)ናቸው፡፡ ሰጎን በረሃ ነዋሪ በመሆኗ በኢትዮጵያውያን ከመበላት ተርፋለች፡፡
- ማንይንገረው ሸንቁጥ ‹‹ባለ አከርካሪዎች›› (2004)