Tuesday, May 28, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ዕውን የዘር ፖለቲካ በዘመን ኢሕአዴግ ነበር?

በታዲዮስ ጥበቡ

አገራችን ያሳለፈቻቸው የፖለቲካ ሥርዓቶች ለብዙኃኑ ሕዝብ ጠብ ያደረገው ነገር ኖሮ አያውቅም፡፡ በመቼም ጊዜ ቢሆን አድሎአዊነትና የሕግ የበታችነት ተንሰራፍቶ ብዙ ዘመናትን እየተሻገሩ አሁን ካለንበት የኦሕዴድ/ኦዴፓ መራሽ የሽግግር ፖለቲካ ሥርዓት ላይ ደርሰናል፡፡ በዚህ ሰዓት ‹ሽግግር› እያልን እየጠራነው ያለው የፖለቲካ ሥርዓት አሻግሮ የት እንደሚያደርሰን ለመገመት ይከብዳል፡፡

ከኦሕዴድ የተቀጣጠለው የለውጥ ነዲድ በአቶ ለማ መገርሳ መሪነት ‹‹ቲም ለማ›› ተብሎ ሲቀጣጠል በሙስናና ከፋፍለህ ግዛው መርህ የሕወሓት መራሹ አመራር ከግንቦት 1983 ጀምሮ ሕዝቡን በከፋ የጭቆና አገዛዝ አገሪቱን እንደ አገር ሰላም ያጣች እንድትሆን ያደረገ ስለነበር ቲም ለማ በኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ሰፊ ድጋፍ፣ እንዲሁም በአማርኛ ሕዝብም ይሁን መሪዎች እንዲሁ ከፍተኛ ድጋፍ በማግኘት የሕወሓት የበላይነትን ዝቅ በማድረግ የለውጥ የፖለቲካ መርህ እንዲስተጋባ ተደረገ፡፡

በዚሁ የለውጥ ሒደት ይበልጥ እንዲፋፋም ያደረገው በሕወሓት ሿሚ ሻሪነት ላለፉት 27 ዓመታት ትመራ የነበረችው አገራችን የመጨረሻ የሕወሓት ሹመኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከኢሕአዴግ ሊቀመንበርነታቸውና ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው በገዛ ፈቃደቸው ከሥልጣን ሲለቁ ኦሕዴድ ይህን ሥልጣን ለመረከብ መልካም አጋጣሚ ሆነ፡፡ የኢንጂነር ኃይለ ማርያም በፈቃድ መልቀቅ የሕወሓት የበላይነትን ዝቅ ለማድረግ የራሱ የሆነ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ የሥልጣን ጊዜያቸውን እስከሚያጠናቅቁ ቢቆዩ ኖሮ የትግሉ አቅጣጫም ይሁን የአገሪቱ የፖለቲካና ፀጥታ ሁኔታ ምን ይሆን ነበር? ቢባል ለመግለጽ ይከብዳል፡፡

ኦሕዴድ የሚለው ስያሜም ይሁን እንደ ፖለቲካ ድርጅትም እንዲመሠረት ሕወሓት ትልቅ ባለውለታ ነበር፡፡ መቼም በፖለቲካ ውስጥ ውለታ ቦታ የለውም እንጂ ሕወሓትንም ለመንግሥት ሥልጣን እንዲበቃ ያደረገው ሻቢያ ሲሆን በ1992 ዓ.ም. የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የውለታ ቢስነት ማረጋገጫ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ሕወሓትን ከነበረው የ27 ዓመታት የበላይነት ሥልጣን ዝቅ ብሎ በትግራይ ብቻ እንዲናኝ የኦሕዴድ ወጣት ለውጥ ፈላጊ ትግል አቀጣጣይና የቲም ለማ አመራር ብቻ ነበር ማለት ግን ስህተት ነው፡፡ የብአዴን አመራሮች እነ ደመቀ መኮንንና ገዱ አንዳርጋቸው እንዲሁም ወጣት ለውጥ ፈላጊው አማራ ትኩሳትና የተቀናጀ ትግል ተደምሮ ሕወሓትን ከነበረበት ከፍታ ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡ ይህ የአማራው ድጋፍ ባይታከልበት የቲም ለማ አመራርና የኦሮምኛ ተናጋሪው ለውጥ ፈላጊ ወጣት ትግል መክኖ ሊቀር እንደሚችል መገመት አያዳግትም ነበር፡፡ እዚህ ላይ በዚህ የትግል ሒደት የአማርኛና ኦሮምኛ ተናጋሪዎች የጎላ ድርሻ ነበራቸው ለማለት እንጂ የሌሎች ብሔረሰቦች የድጋፍ ትግል አልነበረም ብሎ ለመካድ አይደለም፡፡ ከኦሕዴድ ዶ/ር ዓብይ አህመድ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርነት ሲታጩ እንዲመረጡ ድጋፍ የሰጡት የደኢሕዴን አባላት ባይታከሉበት ኖሮ ሕወሓት የበላይነቱን ይዞ እንደሚቀጥል አያጠራጥርም ነበር፡፡ የጉራጌው፣ የኮንሶው፣ የወላይታው፣ የጋሞው፣ ወዘተ ይነስም ይብዛም በትግሉ ወቅት ተሳታፊ በመሆን የድርሻቸውን አበርክተዋል፡፡

የሕወሓትን የበላይ አገዛዝ ሕዝቡ ለምን ጠላው? የውድቀቱስ መንስዔ ምንድን ነበር? የሚሉትን ለመዳሰስ ቢፈልግ ብዙ ሰው ዘረኝነቱና በሙስና የተጨማለቀ መሆኑ በዋናነት የሚጠቀሱ ሲሆን በኢኮኖሚውም የበላይነቱን ለማጎልበት ለከት የሌለው የኢኮኖሚ አሻጥር በመፈጸም ሀብትን ከሕወሓት ደረጃ አንድ ተጠቃሚ አባላት ጀምሮ ኢንደውመንት በሚል ሽፋን እስከ ፖለቲካ ድርጅቱ ማግበስበስ የማያባራና የዕርካታ ገደብ የሌለው ስግብግብነት ውስጥ ተዘፈቀ፡፡ ይህንኑ የሀብት ማግበስበስ መንገድ የሚያመቻቹም ይሁኑ ከለላ የሚሰጥ የስም ፖለቲከኛ የግብር የሥልጣን የገንዘብ ጥመኞችን በስመ ኢሕአዴግ ጥላ ሥር በማሰባሰብ አገዛዙን የከፋ አደረገው፡፡ የሕወሓትን የአገዛዝ ዘመን ለማራዘም ተግተው የሚሠሩ ጀሌ ካድሬዎች ታማኝነታቸውን ማረጋገጫ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ሕወሓት የሚዘርፈውን ሀብት ከሚያንጠባጥበው ትርፍራፊ አንጋጠው የሚቀበሉ ሙሰኛ መሆን የግድ ይላል፡፡ በአጭሩ የፖለቲካ ታማኝነት በሕወሓት የሚለካው በሙሰኝነት ሆነ፡፡ ሀቅና እውነትን ይዞ የሚሮጥ የኢሕአዴግ ካድሬም ቢሆን በሙስናው ካልተቀባ ምናልባት ዝቅ ያለ ሹመት ይሰጠው ካልሆነ በስተቀር ከፍ ወዳለው ድርሻ እንዲል አይፈቀድለትም፡፡ ዝቅ ያለውንም ቢሆን የሚሰጠው የመጠቃቀሚያ መሥመሮቹን/ኔትወርኩን የማይዘጋ ከሆነና እውነትንም ይሁን ሀቅን የማያራግብ ከሆነ ነው፡፡ ስለ እውነትና ሀቅ ማውራት ይችላል፡፡ ወሬው ለማስመሰያ ስለሚፈልግ፡፡ ለእውነትና ሀቅን ይዞ ‹‹ፓርቲው ለምን ሙሰኞችን ያበረታታል?›› የሚል ጠያቂ ካድሬ ቢኖር ተጠያቂው የትኛውም የበላይ አመራር ምላሹ ‹‹ትክክል ነህ ፓርቲያችን ሙሰኞችን መታገል ነው ያለበት፡፡ አንተም ታገል፤›› ይባላል፡፡ ‹‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ›› እንደሚባለው፡፡ እንዲህ እንደምላሹ እውነት መስሎት ከእውነትና ለሀቅ ሽንጡን ገትሮ ተሟጋች ከሆነ በሾኬ ተመቶ ሥልጣን ወደሚባለው አካባቢ ይቅርና ሽታው ወዳለበት ቦታ እንኳን እንዳይደርስ ይደረጋል፡፡

በጣም በተወሰነ አስተሳሰብ በልዩ ሁኔታ በሚያመነጩት በሳል የፖለቲካ ፍልስፍና ይጠቅማሉ የሚሏቸውን ካድሬዎች ጥቅም በሚያስገኝላቸው ጉዳዮች ወይም የጥቅም መዝረፊያውን መሥመር የማይዘጉ፣ አይተው እንዳላዩና ሰምተው እንዳልሰሙ የሚሆኑ ካሉ ከፍ ወዳለ ሥልጣን ያወጧቸው፡፡ የበሳል የፖለቲካ አስተሳሰብ ሐሳብ  አቅራቢዎች እንጂ ውሳኔ ሰጪዎች እንዳይሆኑም ልዩ ጥንቃቄ ይደረግባቸዋል፡፡ ይህን በመሰለ መልኩ ሙስና ለግለሰቦችና ለፓርቲው ሕወሓት የሀብት ማካበቻ ዓይነተኛ መንገድ ተደርጎ ሲወሰድ እንደ ፖለቲካ ደግሞ አገዛዙን ማራዘሚያ መሣሪያ ተደርጎ ነበር ላለፉት ሕወሓት መራሽ የአገዛዝ ዘመን የቆመው፡፡ ፓርቲውን ከሕዝብ አመጽ መጠበቂያ ዓይነተኛ መሣሪያ ተደርጎ ተወስዶ ነበር፡፡ በሙሰኛ ካድሬዎች አፉን የታፈነው ሕዝብ በታጣቂ ከማፈን ብቸኛ የወቅቱ ረቂቅ የፖለቲካ ሥልት በመሆኑ ሥልታዊ የመጨቆኛ መሣሪያ አድርገውት ነበር፡፡ ሙስና የሕዝብን ሀብት ለጥቂቶች በመስጠት የሕዝብን ኑሮ ቀውስ ውስጥ የሚከት እንዲሁም ሥራ አጥነትን የሚያበዛ ነው፡፡ የጥቂቶችን ሥነ ልቦና ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሲሆን የብዙኃኑን ሕዝብ ሥነ ልቦና የሚያሸማቅቅና የበታችነት ስያሜን የሚያላብስ ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ የአገዛዝ ፍልስፍናም ግቡ ይኸው ነው፡፡ የጥቂት ጨካኝና ጨቋኝ ገዥዎችን በቡዝኃን ተጨቋኝ ጫንቃ ላይ መጫን ነው፡፡ ሕዝቡ አንድ እንዳይሆን ይበትኑታል፣ ለሕዝብ ጥቅም የሚታገሉትንና ጭቆናውን በማውገዝ የሕዝብ አፍ በመሆን ከፊት ለፊት በመጋፈጣቸው ሕዝብ የሚወዳቸውና የሚደግፋቸው ከሆነ ‹ፖፒሊስት› የሚል ቅጥያ ስም በመስጠት የሕዝብን ድምፅ ለማዳፈን ይሯሯጣሉ፡፡ ዕድርና በጋራ ተሰብስቦ ቡና በመጠጣት እንኳን ሳይቀር ከስለላ መረብ ውስጥ ይገባል፡፡ በዓይነ ቁራኛ ይጠበቃል፡፡ ማነው ዳኛው? ማነው ቡና ጠሪው? ማነው በሕዝብ ተወዳጁ? ማነው ሰብሳቢው? ብሔሩስ? ወዘተ እየተባለ ክትትል ይደረግበታል፡፡

ሕወሓት ፖለቲካው በዘር ላይ የተመሠረተ ነው? የአገሪቱንም የአስተዳደር ወሰን ዘርን መሠረት ያደረገ ነው? ሕገ መንግሥቱስ ዘረኝነት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው? ዘርስ ምንድነው? ቋንቋስ ምንድነው? የሕወሓት መራሽ መንግሥት ፖለቲካው የዘር ነው? ወይንስ የቋንቋ? እኔ ዘርንና ቋንቋን ትርጓሜያቸውን ለመስጠት ሌሎች ሰዎች ወደተረጎሙበት ሐሳብ አልሄድኩም፡፡ ትርጉሙን ለመስጠት የምችል ነኝ ብዬ ስለማስብ፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ የሌላ ሰውን ካልጠቀስን በተለይ ደግሞ የነጭን ሐሳብ ካልጠቀስን የራሳችንን ሐሳብ ስንናገር እንደ ውሸት ይቆጠራል፡፡ እውነተኝነት ከሌሎች መጥቀስ ነው፡፡ በተለይ ከፈረንጅ፣ ሌሎች ወይም ፈረንጅ ዋሽቶ የተናገረው ይሁን አይሁን መጨነቅ አያስፈልግም፣ በሥነ ልቦና ለፈረንጅ ሐሳብ የበላይነት ቦታ የሰጠን ራሳችንን የበታች ያደረግን መሆናችንን ያወቅን ይሁን ያላወቅን ሆነን ነው? የዚህ ምላሽ ለመስጠት አልተቸገረም፡፡ አበው እንዳሉት ጨው ለራስህ ብለህ ጣፍጥ አለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሀል እንዳንሆን ስለሆነም ዘርንና ቋንቋን ትርጓሜያቸውን ለማስቀመጥ የተወሳስቦም ባለመሆኑ ትርጓሜያቸውን በራሴ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ፡፡

ዘር በሥነ ሕይወታዊ ትስስር መቀራረብን አመላካች ነው፡፡ የሰው ዘር ሁሉ ሰው ነው፡፡ ሰው በመሆን ሥነ ሕይወታዊ ውስጥ ቅርርቡ እስከ ወላጅ አባት፣ እናትና ልጅ ድረስ ይደርሳል፡፡ ይህ በአንድ የሥነ ሕይወት ትስስር ውስጥ በሚኖር ቅርበትና ርቀት በዚህ ዘመን መለኪያው ጅን/ዘረመል እንዲሆን ሳንሳዊ መግባባት የተደረሰበት ነው፡፡ ሰውን ከሌላ ሥነ ሕይወት የሚለየው ዘረመል አለ፡፡ እንዲሁም በሰው ዘር በራሱ የአነድንቱን ርቀትና ቅርበት የሚለካበትም ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህ መለኪያ እውነት ነው? አይደለም? የሚለውን አነጋጋሪነት ትተነው ዓለም በአብዛኛው የተቀበለው የሳይንስ ግንት መሆኑን አምነን በመቀበል አንዱ ሰው ከሌላው ሰው የሚኖረውን የዘር ርቀትና ቅርበት መለኪያ መሆን ይችላል ብለን እንውሰድ፡፡ አሁን ላይ ባለ ቅቡል የሳይንስ ጥበብ አባትነትን፣ እናትነትንና ሌሎች የዝምድና አንድነትን የምናረጋግጥበትና የሚነገረን ውጤትም አሜን ብለን የምንቀበለው፡፡ አሜን እንላለን እንጂ ለምን ብለን አንጠቀቅም፡፡

ከእነዚህ መጠነኛ ማብራሪያ መነሻነት ዘር የደም፣ የሥጋ፣ የአጥንትና ቆዳ አንድነትን በተወሰነ ደረጃ መገለጫ ነው፡፡ በተወሰነ ያልኩበት ምክንያት ፍፁምነት አይኖርም በሚል እሳቤ ነው፡፡ ከላይ በቀረበው መሠረትም ዘር በጅን የሚገለጽ ነው፡፡ ከአካላችን በሚወሰድ ቅንጣተመል (ድኤንኤ) የዘር ቅርርባችንን በሌላ መልኩ ዝምድናችንን የምንገልጽ ይሆናል፡፡ እንግዲህ ዘር ማለት በቤተ ሙከራ የሚረጋገጥ የሰው ዘርን ዝምድና ቅርበትና ርቀት ተለክቶ የሚገልጽበት ሳይንሳዊ መንገድ ነው፡፡

በእኛ አባቶች ዘር በትውፊታዊ የዘር ግንድ ወደ ላይና ወደታች በሚደረግ ቆጠራ እስከተወሰነ የዘር ደረጃ ድረስ ተሂዶ የሚቆምበት ነው፡፡ በሳይንሱ ከአካላችን የሚወሰደው ቅንጣተ መል የዝምድና ማረጋገጫ መንገድ ይሁን እንጂ ከቅርቡ ወላጆች ጀምሮ እስከ ሩቁ የት ድረስ ማረጋገጥ ይቻላል? የሚለውን ለመመለስ በዚህ ደረጃ አልችልም፡፡ ሄዶ ሄዶ ግን ዘር የዝምድና ትስስርን በቅርቡም ይሁን ለሩቅ መግለጫ ነው፡፡ እንደ አባቶቻችን ትውፊት ዝምድና እስከ ሰባት ትውልድ የሚዘልቅ መሆኑን ይነገራል፡፡ ከዚህም እንደሚያልፍ በተምሳሌትም ይነገራል፡፡ ይህን በሳል ተምሳሌት በእንዲህ ያቀርቡታል፡፡ ‹‹አንድ ገንቦ ማር አዘጋጅ ከጋን ውስጥ ጨምረው ጋኑን ሰባት ገንቦ ውኃ ጨምሮበትና ከበጠበጥከው በኋላ ቅመሰው ጥፍጥናው አለ፤ ሌላ ሰባት ገንቦ ውኃ ጨምርበት ጥፍጥናው የደከመ ይሆናል፤ ስለዚህ ዝምድና የሚከስመው ከሁለት ሰባት ቤት በኋላ ነው›› ይላሉ፡፡ መቼም ሰባት ቁጥር ብዙ ሥነ መለኮታዊ ዳራ አላት፡፡ ከሁለት ሰባት ቤት በኋላ ዘመድ ከሚለው ይልቅ ወገን ከዚያም የሰው ዘር የሚባለው ይጠቀሳል፡፡ በሳይንሱ ቅንጣተ መል እስከ ስንት ትውልድ ማረጋገጫ እንደሚሰጥ ሁላችንም ራሳችንን እንጠይቅ፡፡

ስለዚህ ይህችን ታክል ከነካካን ቋንቋስ ምንድነው? ቋንቋ ከዘር ጋር ትስስር አለው? የሚለውን ለማየት ትንሽ ቢውተረተር፡፡ ዘር ህያውነትን የሚያስገኝ ነው ህያውነትንም የምናጣበት ነው፡፡ ሥነ ሕይወታዊ ነው የምንለውም ለዚህ ነው ይህ ማለት ደግሞ ቁሳዊ መሆኑንም ያመለክታል፡፡ የዘር ፍሬ መነሻነት ቁስ አካል ሆነን ከተገኘን በኋላ ነው፡፡ ይህም የተለያዩ ሥነ ሕይወታዊ ሒደቶችን ካለፍን በኋላ ማለት ነው፡፡ ሳይንሱ እንደሚለው ንጥረ መል (ሴል) የዘር ፍሬ መነሻነት ቁስ አካል ሆነን ያለንን የሰውነት አካል ይዘን እንድንገኝ ያደርገናል፡፡ ቁስ አካል ሆነን ከተገኘን በኋላ በተለያዩ ሒደቶች ቁስ አካል ሆነን እንኖራለን ማለት ነው፡፡ ቁስ አካል ከአንድ ቁስ ወደ ሌላ ቁስ እየተሸጋገረ ይኖራል እንጂ አይጠፋም አይፈጠርም የሚለው የቁስ አካላውያን ትርክት ያለ ቢሆንም ትንሿን ንጥረ መል ያስገኘው ሌላው ቁስ አካል በመሆኑ እንደ አዲስ አልተፈጠረም ለማለት ይሆናል፡፡ ሰው በሕይወት እያለ ሰው ነው ሲሞት ደግሞ አፈር ይሆናል አፈር ሌላ ቁስ ነው፡፡ በሥነ መለኮታዊው ሰውን ‹‹ከአፈር ነውና የወጣኸው ወደ አፈርም ትመለሳለህ›› ይላል፡፡ ዙሩ ይቀጥል አይቀጥል ባናውቅም እንደ ቁሳውያኖች ቁስ ዘላለማዊ ነው ይላሉ፡፡ ቋንቋ ግን ህያውነትን አያስገኝም ቋንቋ ቁሳዊነትንም አያስገኝም ቁሳዊ ባለመሆኑ ዘላለማዊም ሊሆን አይችልም ዘርና ቋንቋ ምንም የሚያገናኛቸው የለም፡፡

ጥበብ ከደረሰበት የአሁን ላይ ደረጃ ድረስ ቋንቋ ለሰው ዘር የተሰጠው የመግባቢያ መንገድ (ሚዲያ) ነው፡፡ ሌሎች ህያዋን ፍጥረታት አይግባቡም እንዴ? ድምፅ ይሰማሉ ምልክትም ያሳያሉ፣ ከዚያም መልዕክት ያስተላልፋሉ፣ ሠልጥነው ብዙ ትርዒቶችንም ያሳያሉ ታዲያ ይህን ሁሉ ከውነው ለምን ቋንቋ አላልነውም? አዎ አላልነውም ሌሎች ያንን አሜን ብለን ስለተቀበልን ላም ጥጃዋን ማጥባት ስትፈልግ ትጮሀለች የፍየል ግልገል ከእናቷ ጋር መገናኘት ስትፈልግ ስትፈልግ ትጮሀለች ውሻ ሲርበው ይጮሀል፣ ጅብ የሚበላው ሲያገኝ ይጮሀል ወዘተ. እንደየቢጤያቸው ሁሉም ይግባቡበታል፡፡ ግን ቋንቋ አንለውም ብለን ሰዎች ተስማምተን አቋም ይዘናል፡፡ ቋንቋ ላለመባልም ጉድለቶች ያልናቸውን በሰውኛ አንደበትም እንዘረዝራለን፡፡

ዘርን በተፈጥሮ እንጂ በተለምዶ የምናገኘው አይደለም፡፡ አጭር የሆነ ሰው ዕድሜውን ሙሉ ከረዣዥሞች ጋር ቢኖር አይረዝምም፡፡ ነጩ ሰው ከጥቁሮች ጋር በመኖሩ ብቻ ጥቁር አይሆንም፣ ረዥሙ ሰው ድንክዬ መሆን ቢመኝ አይችልም፡፡ ዘር የሚቀይረው በተፈጥሯዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ረዥምና አጭር ሌላ ዘርን ለመተካት ሲያገኙ ሌላ አቋም ለው ህያዊ ፍጡር ይገኛል፡፡ ነጭ ከጥቁር ጋርም እንዲሁ ቋንቋን ግን በተለምዶ የምናገኘው ነው፡፡ ነጩ ከነጭ ዘር ህያው የሆነ ቢሆንም በጥቁሮች መሀል በሕፃንነቱ ቢቀላቀል ያደገበትን ቋንቋ ለምዶ እሱኑ ተናጋሪ ይሆናል፡፡ ጥቁሩም እንዲሁ ስለዚህ ቋንቋ የምንማረው እንጂ በዘር የምናገኘውና በዘር የምንወስደው አይደለም፡፡ ቋንቋ በዘር የማይተላለፍ ይሁን እንጂ ማኅበራዊ ተፅዕኖ የሚገራው ነው፡፡ ተወልደን ያደግንበት ወይም አፋችንን ከምንፈታበት ጊዜ ጀምሮ የምናድግበት ኅብረተሰብ የሚሰጠን የመግባቢያ መንገድ ነው፡፡ ምክንያቱም ለአጭር ጊዜም ይሁን ለረዥም ጊዜ በኅብረተሰቡ ውስጥ ስንኖር ማኅበራዊ ትስስሩ ስለሚያስገድደን ከማኅበረሰቡ ጋር ለመኖር ስንል ቋንቋውንም እንለምደዋለን፡፡ ታዲያ ተፅዕኖ የፈጠረው ዘሩ ሳይሆን ኅብረተሰቡ ነው ማለት ነው፡፡ ኅብረተሰቡም አስገድዶት አይደለም፡፡ እንደ አንድ የኅብረተሰብ አባል አብሮ ለመኖር ምርጫው ላደረገው ኅብረተሰብ ውስጥ የሚያዋህደውን መስተጋብር ውስጥ ተዋህዶ ለመኖር ወዶና ፈቅዶ የሚቀበለው ነው እንጂ የውዴታ ግዴታ መሆኑ ነው ማንም በኃይል አስገድዶ ሳይጭንበት በፍቃዱ በውዴታ የሚቀበለው ነው፡፡ ኃይል ደግሞ አካላዊ ጥቃት ብቻ ሳይሆን ሥነ ልቦናዊ ማሽማቀቅንም ይጨምራል፡፡ ይህን ካልፈጸምክ ይህ ችግር ይደርስብሃል የሚለውን ሥነ ልቦናዊ ጫና ያካትታል፡፡ ታዲያ ወዶንና ፈቅዶን ወይም ውስጡ ስለኖርንበት የተቀበልነውን ቋንቋ ተፅዕኖ የፈጠረው ዘሩ ሳይሆን ኅብረተሰቡ ነው ማለት ነው፡፡ ቋንቋ የዘር ሳይሆን የምርጫ ጉዳይ ነው ምርጫውም አብሮ ከሚኖረው ኅብረተሰቡ ጋር የሚጣመር ነው፡፡ ከእንግሊዞች ጋር ተዋህዶ ለመኖር የፈለገ ኦሮሞ፣ ሐሪሪ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ከንባታ፣ ሀዲያ፣ ሱማሌ፣ አፋር ወዘተ. እንግሊዝኛን ምርጫው አድርጎ ለንደን ኑሮውን ያደርጋል እንጂ ኦሮምኛን፣ አደርኛን፣ ጉራግኛን፣ አማርኛን፣ ትግርኛን፣ ከንባትኛን፣ ሀድያን፣ ሱማሌኛን፣ ሐረሪኛ፣ ወዘተ. በመናገር አይደለም ከሌላው የእንግሊዝ ኅብረተሰብ ተግባብቶና ተዋህዶ የሚኖረው በዋናነት እንግሊዝኛን በመናገር እንጂ የለንደን ነዋሪ እንግሊዛዊ አስገድዶ እንግሊዝኛ ካልተናገርክ ለንደን አትኖርም ወይም ከለንደን ትባረራለህ ወይም ትገደላለህ ወይም መሥራት አትችልም ወይም ያፈራኸውን ሀብት ትቀማለህ ወዘተ. ብሎ አስገድዶት አይደለም፡፡ የአገሪቷን ሕግ ጠብቆና አክብሮ እስከ ኖረ ድረስ መኖር ይችላል፡፡ ሩዚያ መኖር የፈለገ ኢትዮጵያዊ ሩዚያኛ መናገር የግድ ይለዋል ጃፓንም መኖር የፈለገ እንዲሁ፡፡

ቋንቋ ከዚህ ጋር ቁርኝት የነበረው ቢሆን ኖሮ የራሳቸው ቋንቋ ያላቸው የሁለት ጥቁሮች ልጅ ነጮች አገር ቢወለድ ወይም በአፍ መፍቻው ጊዜ ጀምሮ ቢያድግ እናትና አባቱ ከሚናገሩት የራሳቸው ቋንቋ ይልቅ እሱ የሚኖርበትን ማኅበረሰብ ቋንቋ ተናጋሪ ይሆናል፡፡ የዘሩን ቋንቋ መናገር የግድ ቢለው ኖሮ የእናትና አባቱን ቋንቋ ብቻ ይናገር ነበር፡፡ ነገር ግን የተናገረው ወይም የሚናገረው ተዋህዶ የሚኖርበትን ኅብረተሰብ ቋንቋ ነው፡፡ የመረተው የማኅበረሰቡ መግባቢያ ቋንቋ የበላይ ሆኖም አይደለም፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር መጣመር፣ መዋሃድና መግባባት ስለሚያስፈልገው እንጂ ሊተወውም ይችላል፡፡ መብቱ ነው፡፡ ማኅበረሰቡም ለምን ተውከው ብሎ አይከሰውም ወይም አያስገድደውም፡፡ ምርጫው የተናጋሪው በመሆኑ ነገር ግን ከዚያ ኅብረተሰብ ወጥቶ በሚመረጠው ሌላ ኅብረተሰብ በመቀላቀል የመረጠውን ኅብረተሰብ ቋንቋ መናገር የግድ ይለዋል፡፡ ሰው ማኅበራዊ እንስሳ በመሆኑ ሳይናገርና ሳይግባባ ብቸኛ ሆኖ መኖር አይቻልምና ከዚህም የበዙ ማስረጃዎች ስለ ቋንቋ ተለምዷዊነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ ማንዛዛት ካልሆነ  በስተቀር ለመረዳት ይኼው በቂ መሆን ይችላል፡፡ ብዥታ እየፈጠረብን ያለው ኦሮምኛ ከሚናገሩ ወላጆች ተወልደን እዚያው ኦሮምኛ ከሚናገር ኅብረተሰብ ጋር ስላደግን፣ ትግርኛ ከሚናገሩ እናትና አባት ተወልደን እዚያው ትግርኛ ከሚናገር ማኅበረሰብ ውስጥ ስላደግን፣ አማርኛ ከሚናገሩ እናትና አባት ተወልደን እዚያው አማርኛ ከሚናገር ማኅበረሰብ ውስጥ ስላደግን፣ ሲዳሞኛ ከሚናገሩ እናትና አባት ተወልደን እዚያው ሲዳምኛ ከሚናገር ማኅበረሰብ ውስጥ ስላደግን ወዘተ. ቋንቋውንና ዘራችንን እናቀላቅለዋለን፡፡ ይህ ግን ስህተት ነው፡፡ ከኒዊር ተናጋሪ  አባትና አማርኛ ተናጋሪ እናት ኑዌር ተናጋሪ ኅብረተሰብ ውስጥ ተወልዶ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ኑዌር ቢሆን አማርኛ ተናጋሪ እናቱ ዘሩ አይደለችም? ከትግርኛ ተናጋሪ አባትና ኦሮምኛ ተናጋሪ እናት ኦሮምኛ ተናጋሪ ኅብረተሰብ ውስጥ የተወለደ ልጅ ኦሮምኛ ብቻ ቢናገር አባቱ ዘሩ አይደለም? አማርኛ ከሚናገር አባትና ትግርኛ ከምትናገር እናት ትግርኛ ከሚነገርበት ማኅበረሰብ ቢወለድና ትግርኛ ብቻ ቢናገር አማርኛ ተናጋሪ አባቱ ዘሩ አይደለም? ሶማልኛ ከምትናገር እናትና ሀድያ ከሚናገር አባት ሶማልኛ ከሚናገር ኅብረተሰብ ውስጥ በመወለዱ ሶማልኛ የአፍ መፍቻዋ ቋንቋ ቢሆን ሀድያ ተናጋሪው አባቷ ዘሯ አይደለም? አፋርኛ ተናጋሪው አባትና ከአንዲት ወሎዬ እናት የተወለደች  ሴት አፋርኛ በሚነገርበት ማኅበረሰብ ብትወለድና አፋርኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋዋ ቢሆን ወሎዬዋ እናቷ ዘሯ አይደለችም? አገውኛ ከሚናገር አባትና አኙዋኛ ከምትናገር እናት የተወለደች ልጅ አኙዋኛ ተናጋሪ ኅብረተሰብ ውስጥ ብትወለድና አኙዋኛ ብቻ ብትናገር አገውኛ ተናጋሪ አባቷ ዘሯ አይደለም? ጉራግኛ ከምትናገር እናትና ሐረሪኛ ከሚናገር አባት ጉራግኛ ከሚነገርበት ማኅበረሰብ የተወለደና ያደገ ልጅ ጉራግኛ ቢናገር አደሬ አባቱ ዘሩ አይደለም? ወዘተ ብዙ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል ስድስት ቋንቋ ከሚናገሩ ዘሮች የተገኘ ልጅ ሰባተኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ የእናቱ እናት አንድ ቋንቋ፣ የእናቱ አባት ሌላ ቋንቋ፣ የአባቱ እናት ሌላ ቋንቋ፣ የአባቱ አባት ሌላ ቋንቋ፣ አባቱ ሌላ ቋንቋ፣ እናቱ ሌላ ቋንቋ፣ ልጅ ሌላ ቋንቋ በድምሩ ሰባት ቋንቋ የሚነገርበት የዘር ትስስር እንጂ የቋንቋ ትስስር ነው የሚያይለው? ለምሳሌነቱም ብቻ ሳይሆን እውነታውም ይኸው ነው፡፡ የእናት የአባቱንም ቋንቋ ሳይሆን ሌላ ቋንቋ ቢናገር እናትና አባቱ ለልጁ ዘሩ አይደለም? በተገላቢጢሹም እንዲሁ፡፡

እንግዲህ የዘርን ትርጓሜ ማንም ሰው በሚመስለው ትርጉም ሌላ ዕይታ ለማመላከት ይችል ይሆናል፡፡ ዘርን ከቀለም ጋር ያያይዙታል ዘርን ከቋንቋ ጋር ያያይዙታል ዘርን ከአገር ጋር ያያይዙታል ወዘተ መሠረታዊ አንድነቱንና ልዩነቱን በጥልቀት ልንረዳው ይገባል፡፡ ሰዎችን ስንፈርጅ ወይም በተለያዩ ቡድኖች ልንከፋፍል ግን ስንፈልግ በምን መልኩ እናድናቸው? በምን መልኩ እንፈርጃቸው? በምን እንከፋፍላቸው? የሚለውን የመለያያ ሥልት ከመሆን ያለፈ አይደለም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles