ሰላም! ሰላም! ‘እንደገና ፍቅር እንደገና፣ እንደገና አይገኝምና’ ይሉት ዘፈን እንደ እውነቱ ለፍቅር ቢሠራም ለእኔና ለእናንተ ግን አልሠራም። እንዴት ሰነበታችሁ? ቀኑን እየገፋነው ይሁን ወይ እየገፋን ይኼው በሰንበት አንተጣጣም። በዛም ተባለ በዚህ ዘመኑ የገፊና የተገፊ ነዋ! የአፈናቃይና የተፈናቃይ ማለቴ ነው፡፡ ምን ይደረግ? ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ጋሽ መሐሙድ አህመድ ይህችን የእንደገና ዜማ ርዕሰ ጉዳይ እየለዋወጠ ደጋግሞ ቢጫወታት እንዴት ሸጋ ነበር? አንበርብር ሁሉንም ነገር ማለት ይቻላል እንደ ትናንቱ እንዳስቀመጥከው መቼ ታገኘውና?›› ሲለኝ ነበር። ‹‹እንዴት?›› ብዬ ማብራሪያ መጠየቅ በእውነቱ ድካም ሆነብኝ። እያወቅኩት? እያወቅነው? እየተዋወቅን? ከአቋም እስከ ጥራጥሬ በነበረበትና በትናንትና ሥፍራው ዋጋው አልገኝ ማለቱን እያየሁ ለምን ብዬ ላድክመው? ዕድሜ ለጊዜ መንገዱም ብዙ ይናገራል፡፡
እናንተዬ ዘመኑና ሰው ትናንት እንደምናውቀው አልገኝ ብሎ አሻፈረኝ እንዳለ ምን አስረጂ ያስፈልገዋል ትላላችሁ? ሰው ብትሉት እንደ ቃሉ፣ እንዳለባበሱ፣ እንደተቀመጠበት ወንበር (ሹመት) ክብደት የመገኘቱ ነገር በተጠያቂነትና በግልጽነት አሠራር ብቻ የሚመለስ እንቆቅልሽ አልሆነም። ታማኝነት፣ ቀናነት፣ ሰው አክባሪነት፣ ሰብዓዊነት . . . የሚባለሉ እሴቶች ምን እንደዋጣቸው የታወቀ ነገር የለም። እኔስ አፋልጉን ብለን አደባባይ እንውጣ ይሆን እላለሁ የምለው ሳጣ። ‘የጨነቀው እርጉዝ ያገባል’ ቢሆንብኝም፣ አሁን አሁን ሆን ብሎ አስረግዞ የሚያገባው በዛ እንጂ። ተመልከቱ ተረትና አባባሉም ለትናንት እንጂ ለዛሬ አልሠራም እያለ መጥቷል። ‹‹ወይ ጊዜ!›› አሉ አዛውንቱ ባሻዬ፣ በስንት ልመናና ምልጃ የቀጠሉት ዕድሜ ጉድ እያሳየ ቢያስቸግራቸው!
ስለዘመን ካነሳን አይቀር ማለቂያ ባይኖረውም አንዳንድ እንበል እስኪ። እንግዲህ የዘንድሮ ነገር ከአዋቂውም ጭምት አይደል የባሰብን? ታዲያ እንጫወታ። በረባ ባረባው በሚያልቀው ዘመናችን ዘመንን ማማት እንደሆነ ሲወርድ ሲዋረድ የተቀበልነው የአያት የቅድም አያቶቻችን ወግ ነው። በተለይ የአሁኑ ትውልድ ባይኖረውም ይትበሃሉን ለመጠበቅ ደፋ ቀና ሲል እታዘበዋለሁ። ታዲያ ሰሞኑን ነው አየሩም ጠዋት እንዳረፈደው በማያመሽበት ግንቦት አንድ ጎልማሳ ወዳጄ መጥቶ፣ ‹‹አንበርብር! ያን ሰሞን ካስተዋወቅኩህ የከንፈር ወዳጄ ጋር ልንጋባ ቆርጠናል፤›› ሲለኝ ‹‹ማለፊያ! እንኳን ደስ አለህ!›› ብዬ አቀፍኩና የወዳጅነት ደስታዬን ገለጽኩለት። ‹‹እና ምን ልርዳህ?›› ስለው፣ ‹‹ቤተሰቦቿ ዘንድ ሽማግሌ አድርጌ ልልክህ ነው፤›› አለኝ። ‹‹በቃ እንጋባ ብላችሁ ራሳችሁ ቆርጣችሁ ስታበቁ የምን ድራማ ነው?›› ልለው አሰብኩና ከአፌ መለስኩት። በወግና በልማዱ ውስጥ ጣልቃ ገብቼ ባልፈተፍትስ?
‹‹አሁን እኔ እንደ ዘመኑ አሽሙረኛ ምን ብዬ ነው ባለቀ ጉዳይ ሄጄ ‘ልጃችሁን ለልጃችን’ የምለው?›› ልበለው እያልኩ ከራሴ ጋር ስሟገት ቆየሁ። እንዲህ ያለውን ድፍረትና ወኔ ስለማላውቀው በጣም ተጨነቅኩ። በኋላ ማንጠግቦሽን፣ ‹‹እንዲያው ምን ይሻለኛል?›› ብላት፣ ‹‹ነገር ማጥበቅ ስትወድ? ደረስ ብለህ ብትመጣ ምን እንዳይቀርብህ ነው? እንዲያው ያንተስ ነገር . . .›› ብላ አታማርርብኝ መሰላችሁ? እኔ እሷን ሳገባ በሽማግሌ መላክ ምክንያት ያየሁትን አሳር ትናንት ዋጋ ሰጥታ ስታሞጋግሰኝ እንዳልነበር፣ አሁን ለይስሙላ የሚሠራው ሥራና ዕቅድ ሁላ ደጋፊ ሆናልኝ ቁጭ። እንዲህ እውነትን በአደባባይ ‘ዓይንሽን ላፈር’ ብሎ ሕይወትን ቴአትር ያደረገበት ዘመን ይሁን ግን? ‘የምንኖረው አርቴፊሻል’ አለች ያቺ ድምፀ መረዋ! ወይ ዘመናዊነት በስንቱ ገባበት!
እንደምታውቁት እዚህ አገር ሥራ ላይ ብቻ አተኩሮ መኖር ከባድ ነው። ማኅበራዊ ሕይወቱ ራሱ ራሱን የቻለ ሥራ በሉት። መቼስ ምን ይደረግ በዚህ ቀውጢ ጊዜ የኑሮ ማዕበል በራስ ላይ ድራማ ለመሥራት ሥራ አልፈታም ብዬ ሰላሜን አላጣ እያልኩ፣ እየተነጫነጭኩ ወደ ሙሽሪት ቤተሰቦች አመራሁ። በሩቅ የማውቃቸው ሦስት ጎልማሶችም አሉበት። ‹‹ሲጋቡ ሸምግለን ሲጣሉ ሸምግለን. . .›› እያለ ከመካከላችን አንዱ አንዲት ቀልድ አወጋን። ‹‹ሚስት ‘እንዲህ በጠጅ የምትጨርሰውን ገንዘብ ብትቆጥበው ዓለምን ትዞርበት ነበር፤’ ትለዋለች ባልን። ባል ሲመልስ ምን ቢል ጥሩ ነው? ‘አምስት ብርሌ ጠጅ ስጠጣ ራሷ ትዞር የለም ወይ? እኔ ምን አደከመኝ?’ አላት፤›› ሲለን ሳቅ በሳቅ። ነገ ፍቅር እንደ ጫጉላና የእጮኝነት ጊዜ አልሆን ሲል ሥራ ፈተን ‘ተው!’ ‘ተይ!’ ስንል የምንውለ ራሱ . . . ተውት ማሟረት ይሆንብናል። ብቻ በተቀመጠበትና በተተከለበት ሥፍራ የሚገኝ ነገር እየጠፋ ነው። እንደተዋችሁት የምታገኙት ሰው አለ ከተባለ ግን ምናልባት ታክሲ ጥበቃ የተሠለፈ ሰው ብቻ መሆን ይገባዋል። እውነቴን አይደል? ‘ካልተሳፈሩበት ቶሎ ተሽቀዳድሞ፣ ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ’ እንዳልተባለ ዛሬ ተለውጦ ታክሲ ቆሞ እንዳልጠበቀን ቆመን ጠባቂዎቹ እኛ ሆንን። ‹‹ዘ ይገርም ሻሸመኔ!›› ያለው ማን ይሆን?!
ስለታክሲ ጥበቃ ሳነሳ ባለፈው ሰሞን አንድ ወዳጄ፣ ‹‹እነሱ ተመችቷቸው በ‘ቪ8’ ይንፈላሰሳሉ እኛ እዚህ እንደ ድንጋይ ተገትረን እንውላለን፤›› ሲል ብሰማው፣ ‘ጓደኞችህ ተመችቷቸው በመርሰዲስ ይንፈላሰሳሉ አንተ እዚህ ቆመህ ቀረህ! ድንጋይ!’ እያለ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሥር ቆሞ ይሳደብ ስለነበረው ‘ጀብራሬ’ አንድ መጽሐፍ ውስጥ ያነበብኩት ትዝ ሲለኝ ነበር። የእኛ ኑሮ በትዝታ ሆኗል። ‹‹ማርጀታችን የሚታወቀው በተስፋ መኖር ትተን በትዝታ መኖር ስንጀምር ነው፤›› ያለው ሰው እንዴት ያለ ሊቅ ነበር? የሕዝቡ የትራንስፖርት ችግር ፈጽሞ የማይገባቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ምን መፍትሔ እያሰቡልን እንደሆነ፣ በእውነቱ እኛም አላወቅንም ቃል አቀባዮችም አልነገሩንም። ድሎትና ቅምጥል ኑሮ አሳዳጅ የሆኑ አንዳንድ ባለሥልጣኖቻችንንና እኛን ላነፃፀረ ግን ወዳጄ ለማለት የፈለገው ነገር በደንብ የሚገለጽለት ይመስለኛል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሕዝብና ለእውነት፣ ለማህተባቸው ብለው መስዋዕትነት የከፈሉትንና በሕዝብ ሀብት እንቁላል መስለው የሚንፈላሰሱብንን ስታስቡ እንዴት ያለ ህሊና እንዳላቸው ማወቅ አያሰኛችሁም? ዘረፋ የአገር የበኩር ልጅ ይመስል የዘራነውን ሁሉ እየወረሰን እስከ መቼ እንደምንኖር እንጃ! እስከ መቼስ በራስ ላይ መቀለድ ተቀናቃኝ የሌለው ሀብታችን ሆኖ ይቀራል?
ታክሲ ጥበቃ በተሠለፍንበት ነው ብያችኋለሁ። አንዱ ‘ወይ ሐረር ወይ ሸገር ነይና አጫውችኝ’ በሚለው ዜማ ማፏጨቱን ገታ አድርጎ፣ ‹‹ኤድያ ፍቅር ድሮ ቀረ ታክሲ በሽ በነበረበት ዘመን፡፡ አሁን ነይ ቢሏት እሷስ ልምጣ ብትል በምን ትመጣለች?›› ሲል ፈገግ ያሰኘዋል ሰውን። ሌላው ይቀበልና፣ ‹‹ኧረ እውነትህን ነው! ‘ከትልቁ ሾላ ከሥሩ ደርሼ፣ ያለ ዕድል አይበሉ መጣሁ ተመልሼ’ አይደል የሚለው የአገሬ ሰው። ስም በተረፈብን ዘመን ባዶ ኪስን ማን ይጠጋል?›› ይላል። ‹‹እንዲህ የትራንስፖርት ፖለቲካ ከራሳችን አልወርድ ብሎ እንዴት አድርገን ነው መካከለኛ ገቢ ካላቸው ተርታ የመሠለፍን ዕቅድ የምናሳካው?›› ይለዋል ሌላው። ‹‹መልስ የለም! እስቲ በፊት ረሃባችንን እናስታግስ ሌላው ቀልድ ነው . . .›› እየሳቀ ይመልሳል ሦስተኛው። ‹‹ውይ ፈጣሪ ሲወዳቸው እኮ!›› ትላለች ደግሞ አንዷ ቀዘባ ሠልፈኛ። ‹‹ማንን?›› ይጠይቃታል (ወዳጇ ነው መሰል አብረው ናቸው) ‹‹ውዱን ጠቅላይ ሚኒስትር ነዋ። እንኳን እንዲህ ስንሆን አላዩን . . .›› አለች የአንጀቷን መንሰፍሰፍ ፊቷን ፈገግ አድርጋ ለመግለጽ እየሞከረች። ‹‹ቢያዩን ዝም የሚሉ ይመስልሻል?›› ከማለቱ ሦስተኛው ሠልፈኛ፣ ‹‹እንዴት ዝም ይላሉ? ‘መንግሥት ለእያንዳንዱ ዜጋ መኪና ማደል ባይችልም ኑ ልጠጋላችሁ ግቡ’ ይላሉ እንጂ፣ እንዴት ዝም ይላሉ?›› ብሎ ፈገግ አለ። ‹‹እንዴት?! መቼ ለእያንዳንዳችን መኪና ይሰጠን አልን?›› ሲለው ሌላው ሠልፈኛ ተናዶ የጎረምሳው መልስ ከአንጀት መሳቅ ነበር። ቅኔው ገባኝ ያለ አብሮት ይስቃል! ባይገባውስ ይተውን እንጂ!
የማለዳውን ቅዝቃዜውን ችዬ በታክሲ ዕጦት እየተንገላታሁ ሥራ መፈለጌን መቼም አልተውኩትም። ቆይቼ አንድ ሥራ አግኝቻለሁ። ‘የማታ ማታ’ እንዲሉ! ሥራው በጣም ዘመናዊና ጥራት ያላቸው የቤት ዕቃዎችን ማሻሻጥ ነው። ከባህር ማዶ ወደዚህ ጠቅልሎ ለመኖር ያሰበ ‘ዳያስፖራ’ ነው። የቤቱን ዕቃ በኮንቴይነር ጭኖ የመጣው የዛሬ ሁለት ዓመት ቢሆንም፣ ዕቃው በቀላሉ ከጉምሩክ ሊያልፍለት ሳይችል በመቅረቱ ተማሮ ቆይቶ። አሁን ከሁለት ዓመት በኋላ ‘ዕቃህን ውሰድ’ ቢሉት ደወለልኝና ‹‹የሚገዙ ሰዎች ፈልግ እንጂ እኔ እንደሆንኩ ቤቴን ከሞላሁ ቆይቻለሁ፤›› አለኝ። ታዲያ በአካል ሳገኘው፣ ‹‹እንኳን ደስ አለህ!›› አልኩት። ‹‹ኧረ ተወኝ እባክህ? ‘ኑ አገራችሁ’ ይላሉ ይኼው ስንመጣ የሚሠሩትን ሥራ። እኔ የምለው መሰደድ እንዴት አይብስብን? እንዴት ስደት አያምረን? ሰው በአገሩ እንደ ዜጋ መከበር ካልቻለ መብቱ ያላግባብ የማንም መጠቀሚያ የሚሆን ከሆነ አገር ምንድነው?›› ብሎ በምሬት የልቡን አጫወተኝ። የጉምሩክ ጉዳይ ፍርድ ቤት ተይዞ ምንም ልለው ስላልፈለግኩ ዝም አልኩ። የሕግ የበላይነት ከተረጋገጠ እኮ እንዲህ ብዙ መናገር አይጠበቅብንም ነበር። በለስ ቀንቶኝ ዕቃዎቹን አሻሽጬ ስጨርስ ድርሻዬን ሰጥቶኝ ተለያየን።
በሉ እስኪ እንሰነባበት። የእኔ ነገር ለካ የሽምግልናውን ጨዋታ አልጨረስኩትም? አሁን እኔ ሰው ነኝ? ምን ሆነ መሰላችሁ ‘አሁን ማን ነው የሚጀምረው? ምን ብሎ ነው የሚናገረው?’ ስንባባል ሳለን የሙሽሪት እናት በቤት ሠራተኞቻቸው ታጅበው ጠጁን፣ ጠላውን፣ ቢራውን፣ ውስኪውን፣ ሽንጡን፣ ዳቢቱን፣ ሻኛውን ከፊታችን አስቀረቡና ‘በሉ!’ ይሉን ጀመር። አባወራው ደግሞ ‘አሞራው በሰማይ ሲያይሽ ዋለን’ ከፍተው ጆሯችንን አደነቆሩት። ‹‹እንዲያው ትንሽ እንኳ ሳንጫወት?›› ሲላቸው ከመሀላችን አንደኛው ሁለቱም የፌዝ ሳቅ ስቀው፣ ‹‹ብሉና ይደርሳል። ምን የሚያስቸኩል ነገር ኖረና ለወሬው?›› ብለው በነገር ወጉን። ኃፍረት ቢያሽመደምደንም የመብሉ አጋጣሚ የሚታለፍ አልነበረም። ‹‹ይታይህ እንግዲህ የእኛ ሰው? ወይ አልሠለጠነ ወይ አንደኛውን ወደ ኋላ አልቀረ?›› ብዬ ግሮሰሪ ስንገናኝ የባሻዬን ልጅ አጫወትኩት። ‹‹እናንተስ ስንት ሽማግሌ የሚያስፈልግበት ሥፍራ እያለ . . .›› ብሎ በእንጥልጥል ተወው። ‹‹ማለት?›› ስለው ‹‹ጊዜው ነዋ። በዚህ ጊዜ ሽማግሌ የሚያስፈልገው እኮ ጊዜ ነው። ሰው የሚሠራውና የሚያስበው መልካም ነገር እንዳለ ሆኖ፣ ጊዜ አልፈታቸው ያሉ ችግሮች ከዕለት ወደ ዕለት በዝተዋል። ቢነገር ቢዘከር አልሰማ ብሏል። ‘ለችግሮቻችን መፍትሔ ፈልግልኝ’ ብለን ጊዜን በሽማግሌዎች ደጅ መጥናት አለብን። በዴሞክራሲ ካልሆነ በሽምግልና መሞከር አለብን!›› ብሎኝ ‹‹ድገመኝ!›› አለው ወደ አሳላፊው ዞሮ። ቢራውን በአንድ ትንፋሽ ጨልጦ፣ ‹‹እንዴት ነው ነገሩ? ዕድሜ ለጊዜ እንደ ዘመኑ ሰው የትዳር ጥያቄያችንንም እንደ መብት ጥያቄ ጎዳና ላይ እናድርገው እንዴ? የሆነስ ሆነና ከሰላማዊ ሠልፍ ወደ ጎዳና ላይ የጋብቻ ጥያቄ እንዴት ይሆን ‘ትራንስፎርም’ ያደረግነው? ኧረ ለመሆኑ ከጎዳና ሠልፍ እንዴት ወጥተን ነው ወደ ጎዳና ጋብቻ ጥያቄ ለመሸጋገር አቅም ያገኘነው? መልሱን ብትፈልግ ጊዜን ጠይቅ፤›› ሲለኝ፣ እስኪ ቸር ያሰንብተን ብዬ እኔም ፊቴን ወደ ቢራዬ አዞርኩ። ማን ይሞኛል ታዲያ? መልካም ሰንበት!