ዐምደ ብርሃን ከሦስት አሠርታት በፊት ከሚኖርበት ጎንደር ዙሪያ በልጅነቱ ከቤተሰቡ እንዲኮበልል ያደረገው አጋጣሚ የተፈጠረበት በእረኝነቱ መጠበቅ የሚገባውን የቤት እንስሳ ባለመጠበቁ ነበር፡፡ ‹‹የፍየል ዓይን ወደ ቅጠል፣ የነብር ዓይን ወደ ፍየል . . ›› የሚለው ብሂል የደረሰበት፣ ይጠብቃት የነበረው ፍየል በነብር መነጠቁ፣ መበላቷ ነበር፡፡ ‹‹እናትና አባቴ ይደበድቡኛል፣ እንዴት ዓይናቸውን አያለሁ፤›› ብሎ ወደ ቤት ከመመለስ ይልቅ የሁለት ቀን መንገድ ተጓዘ፡፡ ያላሰበው ሥፍራ ራሱን አገኘው፡፡ ከጎንደር ከተማ ዳርቻ በምትገኘው ቁስቋም ማርያም፡፡ ድምፅ ወደ ሰማበት አካባቢ ሲዘልቅ በርካቶች ተሰባስበው ሲያነበንቡ፣ ሲያነቡ፣ ሲያዜሙ ይሰማል፡፡ ቀልቡን ይገዛዋል፣ ይነሽጠዋል፡፡ አዲስ ዓለም ውስጥ ይገባል፡፡
በጎንደር ዘመነ መንግሥት እቴጌ ምንትዋብ ባሠሯት ቁስቋም ማርያም ገዳም የሚገኝ የአብነት ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን የሚከታተሉትን አይቶ እርሱም በዘመን ጉዞ ዘለቀበት፡፡
እረኛ እያለ በ15 ዓመቱ የኮበለለው ዐምደ ብርሃን አሁን ላይ በዘመናዊ ሕንፃ ላይ በመምህር ጳውሎስ አስተማሪነት በሚካሄደው የቅኔ ትምህርት ቤት ረዳት መምህር፣ አስነጋሪና ዘራፊ ከመሆኑ ባሻገር ሐዲሳትን ይማራል፡፡
በጎንደር ከተማ ሰሜናዊ ምዕራብ (ባሕር) አቅጣጫ የምትገኘው የደብረ ፀሐይ ቁስቋም ማርያም ገዳም የተመሠረተችው በ18ኛው ምዕት ዓመት በአፄ በከፋ ባለቤት በእቴጌ ምንትዋብ አማካይነት ነው፡፡ አዝማናትን ያሳለፈችው ገዳሟ በጥንታዊ ዕቃ ቤቷ ውስጥ ዘመናዊ ሙዚየም በመገንባት ብቻ አልተወሰነችም፡፡ ቅርስን ከመጠበቅ ባሻገር ጥንታዊው የቤተ ክርስቲያን የጉባዔ ትምህርትንም እየሰጠች ትገኛለች፡፡ ከአብነት የትምህርት ቤቶቿ አንዱ የቅኔ ትምህርት ቤት ሲሆን፣ ለዘመናት በጎጆ ቤት፣ በዛፍ ጥላ ሥርና በመለስተኛ ቤቶች ይሰጥ የነበረው የቅኔ ትምህርት ዘንድሮ በዘመናዊ ሕንፃ ባለአንድ ፎቅ ከእነ ሠገነቱ በሆነ ውስጥ እየተሰጠበት ይገኛል፡፡
ከልሒቅ እስከ ደቂቅ ሦስት መቶ ተማሪዎች የቅኔውን ትምህርት ይከታተላሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች የቅዳሴና የሌሎች መምህራንም ቅኔን ለመቀፀል ከየአካባቢ የመጡ ይገኙባቸዋል፡፡ የግዕዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ባለሙያ ዓባይነህ አስፋው እንደሚገልጹት፣ ከተማሪዎቹ መካከል ከኤርትራ የመጡ የቅዳሴ መምህር ኀቤከ የሚባሉ አሉበት፡፡
ከተማሪነቱ ተሻግሮ በአሁኑ ወቅት አስነጋሪና ዘራፊ የመምህሩ ጴጥሮስ ረዳት ሆኖ እያገለገለ ያለው ዐምደ ብርሃን፣ በእረኝነቱ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ማስቀደሱና ከቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር መተዋወቁ የፍየሏ በነብር መበላት ሰበብ ወደ ጉባዔ ቤት መዝለቁ ሕይወቱን ለውጦታል፡፡
‹‹የሁሉ ነገር መክፈቻ ቅኔ ነው፣ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ሁለንተና ነገርን የሚፈታና የሚገጥም እንደሆነ ቅኔም እንዲሁ ነው፣ አንድ ሰው ቅኔ ከተማረ የሐዲሱንም ብሉዩንም፣ ሊቃውንቱን፣ መነኮሳቱን መጻሕፍት ይተረጉማል፡፡
በብሕትውና ያሉት የኤርትራ ተወላጁ የቅዳሴ መምህር ኀቤከ ለዓባይነህ እንደነገሩት፣ ‹‹በዓለም ከመኖር ገዳም መኖር ይሻላል፡፡ በገዳም ከመኖር ተማሪ ቤት መኖር ይሻላል፡፡ እዚህ የመጣሁት የቀለም ፍቅር፣ የመጽሐፍ ፍቅር ስቦኝ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ቃለ እግዚአብሔር አይጠገብም፡፡››
እንደ አቶ ዓባይነህ አገላለጽ፣ የተማሪዎች ዕድሜ ስብጥር ከአሥር እስከ 80 ዓመት ያሉ የሚኖሩትም፣ የሚማሩትም በአንድነት ነው፡፡ ከሚማሩት ውስጥ መምህራን አሉበት፡፡
እንደ መምህሩ ዓይነ ሥውር ከሆኑ ተማሪዎችም አንዱ፣ ‹‹ለምን ትማራለህ?›› ሲሏቸው፣ ‹‹መኖሪያዬ ስለሆነ ዕውቀት ለመካፈል፤›› ሲሉ ነው የመለሱት፡፡
የአብነት ትምህርት ቤት ዓይነ ሥውር ሆኖ ጥሩ ዜጋ እንዲሆን ማድረጊያ አንዱ መሣሪያ ነው፡፡ ሳይማር ማን ነው የሚቀበለው? አይደለም ሥውር ሙሉ አካል ያለውን የሚቀበል የለም ይላሉ ባለሙያው፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት በጎጆና በዛፉ ሥር ይከታተሉ የነበሩ የቅኔ ተማሪዎች ዘንድሮ ፀሐይ ወጥቶላቸው በአዲስ ሕንፃ ሠገነት ላይ እየተማሩ ይገኛሉ፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ይቀድሱ፣ ያገለግሉ ለነበሩት ለሊቀ ጠበብት ጎላ መታሰቢያ እንዲሆን ቤተሰቦቻቸው ባሠሩት ሕንፃ ላይ ነው ትምህርቱ የሚሰጠው፡፡ ‹‹የሕንፃው አሠራር ትዕምርታዊ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ትውፊትን የጠበቀ፣ ኪነ ሕንፃው በመቋሚያ፣ በፀናፅል፣ በከበሮ የተጌጠ የፋሲልን ግንብንም የሚመስል ሆኖ መታነፁን አቶ ዓባይነህ ያወሳሉ፡፡
በከፍታማዋ ቁስቋም ላይ የተገነባው የቤተ ቅኔ ሕንፃ ከፍ ማለቱ ተማሪዎች ለማሰቢያ፣ ለማሰላሰያ፣ ለአመስጥሮ ይረዳቸዋል፡፡ ሠገነቱ ላይ የሚማሩት በበጋ ሲሆን፣ ክረምት ሲመጣ ግን ከቤት ውስጥ ነው፡፡ የቁስቋሙ ቤተ ቅኔ ተማሪዎች በትርፍ ጊዜያቸው መጻሕፍትን የሚመረምሩበት ቤተ መጻሕፍት ማደራጀቱ ትምህርት ቤቱን ልዩ ያደርገዋል፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ የሚታወቀው የቤተ ክርስቲያን ዕቃ ቤት ነው፡፡ መጻሕፍቱን ማየት የሚፈቀድላቸው ትልልቅ መምህራን ካልሆኑ ለተማሪዎች የተመቸ አይደለም፡፡
‹‹አንድ ሺሕ ብር አንድ ፌስታል አይገዛም››
በተለያዩ የቅኔ ተማሪ ቤቶች በአማካይ የሚኖረው ተማሪ በ20 እና 50 መካከል ነው፡፡ ቁስቋም 300 ተማሪ ይደርሳል፡፡ ብሒልን ከባህል እያዛመዱ ከዘመኑም ሳይነጠሉ ትምህርቱን እያስኬዱት ነው፡፡ ተማሪዎቹ ከመኖሪያ ጎጆ በስተቀር የዕለት ጉርስ፣ የዓመት ልብስ የሚያገኙት ቀፍፈው ነው፡፡ በልመና ሕይወት ውስጥ ነው ያሉት፡፡
የገቢ ምንጭ እንዲሆናቸው የዳቦ መጋገሪያ አዘጋጅቶ ዳቦ ቤት በሟቋቋም ቢያስቡም መንገድ ላይ ነው ያለው፡፡ ተማሪዎቹን ሊረዳ፣ ሊደግፍ እንደሚችል እምነት አላቸው፡፡
ከዋልድባ ቅኔ ለመማር የመጡ የቅዳሴ መምህር ለአቶ ዓባይነህ እንዳወጓቸው፣ ጉባዔ ቤቱን በየጊዜው ከለንደን ገንዘብ በመላክ የሚደግፉ ሁለት የኤርትራ ተወላጅ ሴቶች ናቸው፡፡ ‹‹በሃይማኖት አንድ ነን፣ በአገር ብንከፋፍልም፤›› በማለት ይረዳሉ፡፡ ‹‹የቅኔ መምህሩ የሚከፈላቸው 1,000 ብር ነው፡፡ ሦስት መቶ ተማሪ ያስተምራሉ፡፡ አንድ ሺሕ ብር አንድ ፌስታል አይገዛም፣ ሃይማኖት አስገድዷቸው ነው እንጂ፣ አይዟችሁ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ተማሪዎች ከልመናው ከቀፈፋው ይልቅ የሚረዱበት ዳቦ ቤት ቢቆምላቸው ተስፋ እንዳይቆርጡ ያደርጋል፡፡
ተማሪዎች ተስፋ የሚቆርጡበት ረዳት ከማጣት ነው፡፡ ተከታይ ከሌለ አባቶቻችን ሲያረጁ ማን ይተካል? ልጆቻችን ከተዉት ቤተ ክርስቲያንም ሁሉም ነገር ይዘጋል፡፡ እኛን የሚቀብረን እናጣለን፡፡ በመንፈስ አይዟችሁ ማለት ራሱ ምፀዋት ነው ይላሉ፡፡ ምዕመናንና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሁሉ የቅኔ ትምህርት ቤቱን ቢረዱልን ደስተኛ ነኝ ይላሉ፡፡
ቅኔ ሲፈታ
ቅኔ ካሉት ፍቺዎች አንዱ ቀነየ ገዛ የሚለው ነው፡፡ ለዚህም ነው የውስጥና የውጭ ህዋሳትን ለህሊና አስገዝቶ በሰከነ መንፈስና በተመስጦ፣ በተወሰነ ወይም ቁርጥ ባለ ሐሳብ ላይ የሚታሰብ ስለሆነ ቅኔ የሚለውን ስያሜ ሊያገኝ ችሏል ብለው መጋቤ ምሥጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሒ የሚገልጹት፡፡ ‹‹የቅኔ ሥነ ጥበብ በኢትዮጵያ›› በሚለው ሐተታቸው ነው፡፡
ይህም ይታወቅ ዘንድ በተመስጦ ቅኔ በመቁጠር ላይ ያለና በቅኔ ምሥጢር ልቡ የተሰወረ ሰው ቅኔ በሚቆጥርበት ወይም በሚያስብበት ጊዜ በአጠገቡ ወይም በፊቱ የሚደርሰውን ወይም የሚደረገውን ነገር እያየ አያይም፣ አይሰማም፣ አይሰማም፡፡
. . . በጎንደር ዘመነ መንግሥት ጊዜ የጎንደር ደብረ ቁስቋም አለቃ በእልፍኛቸው ውስጥ ምንጣፋቸውን አስነጥፈው፣ መጻሕፍታቸውን በፊታቸው ደርድረው፣ ለበዓለ ቁስቋም የሚቀኙትን ቅኔ ሲያስቡና ሲቆጥሩ፣ ሲያወጡና ሲያወርዱ ንጉሡ ዘው ብለው ሲገቡ ልባቸው ተመስጦ ሊያዩዋቸው ባለመቻላቸው ቀና ብለው ሳያዩዋቸው ቁጭ እንዳሉ ቀሩ፡፡ ንጉሡም ገርሟቸውና ደንቋቸው በእሳቸው አጠገብ አልፈው ከአልጋ ላይ ተቀምጠው ፍፃሜውን ለማየት ሁኔታቸውን ይመለከቱ ጀመር፡፡ በዚህ ረገድ ንጉሡ ብዙ ጊዜ ካጠፉ በኋላ፣ የደብረ ቁስቋሙ አለቃ አዕምሯቸውን ሲመለስ ንጉሡ ተቀምጠው ቢያዩ ደንግጠው በመነሳት ንጉሡን እጅ ነሱ፣ ንጉሡም፣ ‹‹ምነው? ምን ሆነህ ነው? ብለው ቢጠይቋቸው ‹‹ጃንሆይ ቁስቋምን ያህል ደብር አምነው ሹመውኛል፣ ለበዓል የተሰበሰበው ሰው አለቃው ምን ይናገር ይሆን እያለ ዓይን ዓይኔን ሲያየኝ ያልሆነ ነገር ቢሰማ ደብሩን አዋርዳለሁ፣ ጃንሆይን አሳማለሁ፣ እኔም አፍራለሁ ብዬ ቅኔ እቆጥር ነበር፤›› አሉ ይባላል፡፡
በሌላ አተረጓጎም ቅኔ ማለት (ቀነየ) ተቀኜ፣ ሙሾ አወጣ፣ ግጥም ገጠመ፣ አራቆ ተናገረ፣ አዜመ፣ አንጎራጎረ፣ መራ ተብሎ ከሚተረጎመው ግስ የተገኘ ጥሬ ዘር እንደሆነ የቅኔ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡
ሺነዋ
በአንድ ወቅት እቴጌ ምንትዋብ በግብር ቤታቸው ካህናቱንና ቀሳውስቱን ጋብዘው ያስቀረቡት ምግብና መጠጥ ታዳሚዎቹ እንደ ጠበቁት ባለመሆኑ እቴጌን በቅኔ ሊነግሯቸው ፈለጉና ግብር ቤቱ ከተሠራበት እንጨት አንዱን መረጡና፣ ‹‹እቴጌ ይኼ እንጨት ምን ይባላል?›› ይሏቸዋል፡፡ እቴጌም ‹‹ይህማ ግማርዳ›› ይባላል ይሉና ይመልሳሉ፡፡ ነገሩ ቆይቶ የገባቸው እቴጌ በሌላ ቀን የሞቀ ድግስ ይደግሱና ካህናቱና ቀሳውስቱ ግብዣ ጠርተው፣ ‹‹በልቶ ጠጥቶ መውጣትና መመለስ ክልክል ነው›› ብለው በጠጅና በጮማ ያጠግቧቸዋል:: ከጠጁ ብዙ ለመጠጣት ለሽንት መውጣት ባለመቻላቸው ከቀሳውስቱ መካከል አንዱ በመነሳት እቴጌን ‹‹እንወጥሮት አምስት መቶና አምስት መቶ ስንት ነው?›› ይሏቸውና እቴጌም መልሱ የቀለላቸው መስሏቸው፣ ‹‹አምስት መቶና አምስት መቶማ ሺነዋ›› ብለው ይመልሳሉ:: ይኼን መልስ የፈለጉት ተጋባዥ ‹‹ኧረ እቴጌ ሺናው ብለዋል፤›› ብለው እቴጌን እንዳሸነፏቸው ይነገራል።