Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቃሉን ባለመጠበቁ የሪል ስቴት ኩባንያው ደንበኞቼ ተጉላሉብኝ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኃይሌ ዓለም ኢንተርናሽናል ኩባንያ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 አካባቢ ለገነባቸው ሪል ስቴት ቤቶች የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲገባለት ከዓመት በፊት ክፍያ ፈጽሞ ቢጠባበቅም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቃሉን መጠበቅ ባለመቻሉ ደንበኞቹ እየተጉላሉበት መሆኑን አስታወቀ፡፡

በሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴና ባለቤቱ የተመሠረተው ኩባንያ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በ40 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ፣ በ300 ሚሊዮን ብር ወጪ ስምንት አፓርታማዎችንና 38 ቪላ ቤቶችን ገንብቶ ለደንበኞቹ ማስረከቡን ያስረዳል፡፡

ነገር ግን ደንበኞቹ በገዟቸው ቤቶች ኑሮአቸውን ለመቀጠል ቢወስኑም፣ ትራንስፎርመርም ሆነ የኤሌክትሪክ መስመር ባለመዘርጋቱ ችግር እንደገጠማቸው አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና ኃይሌ ዓለም ኢንተርናሽናል ኩባንያ ሚያዝያ 2010 ዓ.ም. ውል መፈጸማቸውን፣ ለሥራው 4.4 ሚሊዮን ብር ክፍያ መፈጸሙ ተገልጿል፡፡

በወቅቱ በ15 ቀናት ውስጥ መስመር እንደሚዘረጋ ቃል የተገባ ቢሆንም፣ ሥራው ሳይጀመር ዓመት መቆጠሩን የኃይሌ ዓለም ኩባንያ የሪል ስቴት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታደሰ ከበደ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹በቅርቡ ወደ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅንተን ኃላፊዎችን አነጋግረን ነበር፡፡ የተሰጠን ምላሽ በአሁኑ ወቅት የተቋሙ ትኩረት ከተለያዩ ቦታዎች ለተፈናቀሉ ዜጎችና ለጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ድርጅቶች እንጂ ለሪል ስቴት ኩባንያዎች አይደለም የሚል ነው፤›› ሲሉ አቶ ታደሰ የገጠማቸውን ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን በችግር ውስጥም ቢሆን የተወሰኑ ነዋሪዎች ቤታቸውን ተረክበው ኑሮ ጀምረዋል፡፡ ከእነዚህ ደንበኞች መካከል የሕክምና ባለሙያው ፕሮፌሰር ይግዛው ከበደና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

ፕሮፌሰር ይግዛው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አብዛኛው ዕድሜያቸውን በመንግሥት ቤት (በዩኒቨርሲቲ የሕክምና መምህር) ሲሠሩ ነው የቆዩት፡፡ ‹‹በረዥም ጊዜ በመከራ በተጠራቀመ ገንዘብ የሪል ስቴት ቤት ብገዛም፣ ቤቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ስላልገባለት ኑሮዬ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ከዚህ በኋላ ለኪራይ የማወጣው ገንዘብ ስለሌለም ያለ መብራት ቤቱ ውስጥ ገብቼ እየኖርኩ ነው፤›› ሲሉ ችግሩን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ችግሩን አጢኖ በፍጥነት መፍትሔ እንዲሰጣቸው ፕሮፌሰሩ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአዲስ አበባ ሪጅን ሥራ አስኪያጅ አቶ ብዙወርቅ ደምሴ፣ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች