‹‹የፓንክረስት ስም በ20ኛው ክፍለ ዘመን በተለያዩ ዝግጅቶችና ሁነቶች በግንባር ቀደምትነት ተነስቷል፡፡ የሴቶች የመምረጥ መብት፣ የሠራተኛው መደብ መብት የማስከበርና የፀረ ፋሺስት ንቅናቄዎች፣ እንዲሁም በፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ስሙ ይታወሳል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የፓንክረስት ቤተሰብ እናት ሲልቪያ፣ ልጅ ሪቻርድና የልጅ ሚስት ሪታ ኢትዮጵያ በፋሺስት ጣሊያን ላይ በነበራት አይበገሬነት ተሳትፏል፡፡ ድኅረ ጦርነትም ኢትዮጵያና ኤርትራ አብረው እንዲሆኑ ብዙ ጥሯል፡፡››
የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትና የዩኔስኮ ለሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ ወንበር አንድርያስ እሸቴ (ፕሮፌሰር)፣ ለፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስትና ለባለቤታቸው ሪታ ፓንክረስት መታሰቢያ ከዓመታት በፊት ለክብራቸው ሲባል በተዘጋጀ መጽሔት ላይ ያሰፈሩት ቀዳሚ ቃል ነው፡፡
ሃቻምና ያረፉት በኢትዮጵያ የታሪክና ማኅበራዊ ጥናት ሁነኛ ሥፍራ የነበራቸው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ጎን የነበሩት የትዳር አጋራቸው ሪታ ፓንክረስት በሙያም አጋራቸው ከመሆን ባሻገር፣ በኢትዮጵያ ቤተ መጻሕፍት ህንፀት ታሪክ ውስጥ ከብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር እስከ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አብያተ መጻሕፍት አሻራ መጣላቸው ይወሳል፡፡
የሪታ አብዛኛው የሥራ ዘመናቸው በአካዴሚያዊ ቤተ መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ላይብረሪያን በመሆን ለአሥር ዓመት ሠርተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ኦብዘርቨር የተሰኘ መጽሔት ያዘጋጁ ነበር፡፡ የ1966 ዓ.ም. የየካቲት አብዮት ተከትሎ ዘውዳዊ ሥርዓቱ ሲያከትም፣ ለፓንክረስት ቤተሰብም ለልጆች ትምህርት ምቹ ሁኔታ ባለመፈጠሩ በ1968 ዓ.ም. ወደ ለንደን ተመልሰዋል፡፡ በዚያም ሪታ በለንደን ፖሊ ቴክኒክ በቤተ መጻሕፍት አገልግሎት ኃላፊነት ለ11 ዓመታት ከሠሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ከባለቤታቸው ሪቻርድ ጋር በ1979 ዓ.ም. በመመለስ የቤተ መጻሕፍት አማካሪ፣ የአካዴሚያ መጻሕፍትንና የተለያዩ ጥናቶች አርታኢ በመሆን ሠርተዋል፡፡ በሌሎች የበጎ ፈቃድ ተግባራትና ኃላፊነቶችም የኢትዮጵያ ጥናት ወዳጆች ማኅበር (ሶፊ) የኢትዮጵያ ገሚኒ ትረስትን ጨምሮ ላቅ ያለ አገልግሎት መስጠታቸው ገጸ ታሪካቸው ያሳያል፡፡
ከኅትመትና አርትኦት ውጤቶቻቸው መካከል ስለአማቻቸው ሲሊቪያ ሥራዎች፣ ለኢትዮጵያ ሴቶች በአርአያነት ስለሚጠቀሱት ስንዱ ገብሩ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ስለተረሱ ሴቶች የሚያወሱ ይገኙባቸዋል፡፡ ከባለቤታቸው ሪቻርድ ጋር ያዘጋጁት ኢትዮጵያ ሬሚነሰንስ (Ethiopian Reminiscences) መጽሐፍ በኢትዮጵያና በውጭው ዓለም በ1950 እና 1960ዎቹ የነበሩ ትልልቅ ኩነቶችን የሚተነትን ነው፡፡
በ1919 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ በ1927) በሩማንያ የተወለዱት ሪታ በአሥራ አንድ ዓመታቸው ከወላጆቻቸው ጋር ወደ እንግሊዝ ሄደዋል፡፡ በካምብሪጅ ፐርሴ በሚባለው የልጃገረዶች ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ከተከታሉ በኋላ በኦክስፎርድ ፈረንሣይኛና ሩሲያኛ በማጥናት የማስትሬት ዲግሪያቸውን እ.ኤ.አ. በ1948 አግኝተዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በ1956 ከመምጣታቸው በፊት በፓሪስ ጥናትና ሥራ ላይ ነበሩ፡፡
ሪታ አዲስ አበባ በመጡበት ዓመት እናትና ልጁን ሲልቪያና ሪቻርድ ፓንክረስት በማግኘት ወደ ሥራው ዓለም የተቀላቀሉት ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር በመቀጠር ነው፡፡ የቤተ መጻሕፍት ትምህርትንም በተልዕኮ ተከታትለዋል፡፡ ኢትዮጵያ በመጡ በዓመታቸው ለስድሳ ዓመት የትዳር አጋራቸው ሆነው ከዘለቁት ሪቻርድ ፓንክረስት ጋር ጎጆ መሥርተው፣ ሁለት ልጆችን አሉላ አንድሪውና ሔለን ሲልቪያን አፍርተዋል፡፡ የልጅ ልጆችንም ዓይተዋል፡፡
ሪታ ፓንክረስት ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በተወለዱ በ92 ዓመታቸው ያረፉት ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. መሆኑ ታውቋል፡፡