የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የቀድሞ ሥራ አስኪያጁን ፍቃዱ ኃይሌን (ኢንጂነር)፣ ትድሃር ኤክስካቬሽን ኤንድ ኸርዝ ሙቪንግ ሊትድና ናይል ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበርን ጨምሮ 19 ግለሰቦችን በ145.9 ሚሊዮን ብር ዕዳ ከሰሰ፡፡
ባለሥልጣኑ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት ባቀረበው ክስ፣ በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙትን የቀድሞ የባለሥልጣኑ ሥራ አስኪያጅ ፍቃዱ (ኢንጂነር)፣ ሙሉጌታ አብርሃም (ኢንጂነር)፣ አቶ አህመዲን ቡሴር፣ ዋስይሁን ሽፈራው (ኢንጂነር) በማካተትና ምክትል ሥራ አስኪያጅ የነበሩትን አቶ ግደይ ህሽ ጨምሮ በወቅቱ የባለሥልጣኑ ሥራ አመራር (ፕሮሰስ ካውንስል) አባላት የነበሩ 13 ግለሰቦች ናቸው፡፡
ባለሥልጣኑ ባቀረበው ክስ እንዳብራራው፣ ከመገናኛ እስከ ጦር ኃይሎች ያለውን መንገድ ለማሠራት ያወጣውን ውስን ጨረታ ትድሃር ኤክስካቬሽን የተባለው የእስራኤል ኩባንያ ያሸንፋል፡፡ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ዋጋ 1.1 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ በሁለት ሎቶች ተከፍሎ ሲሠራ መቆየቱን ጠቁሞ ሎት አንድ ከማዕድን ሚኒስቴር እስከ መገናኛ አደባባይ ሲሆን፣ ዋጋውም 635,344,860 ብር እንደነበር ጠቅሷል፡፡ 127,069,172 ብርም ቅድሚያ ክፍያ መክፈሉንም አክሏል፡፡
ለዚህም ናይል ኢንሹራንስ ለ730 ቀናት ፀንቶ የሚቆይ ዋስትና ማቅረቡንም ጠቁሟል፡፡ ከለም ሆቴል እስከ ውኃ ልማት ድረስ ያለው መንገድ ግንባታም ደግሞ 528,660,658 ብር ሲሆን፣ 105,732,332 ብር ቅድሚያ ክፍያ ሲከፈለው ናይል ኢንሹራንስ በተመሳሳይ ለ730 ቀናት ዋስትና ሰጥቶት እንደነበርም በክሱ ገልጿል፡፡
ኮንትራክተሩ በውሉ መሠረት ወደ ሥራ ገብቶ እየሠራ ቢሆንም፣ ባሳየው ደካማ የሥራ አፈጻጸም አማካሪ መሐንዲሱ በተለያዩ ጊዜያት ችግሩን እንዲያስወግድ በባለሥልጣኑ በኩል ማስጠንቀቂያ ሲሰጠው መቆየቱን ገልጿል፡፡ ኮንትራክተሩ ያለበትን የአፈጻጸም ችግር ሊያርም ባለመቻሉ፣ አማካሪ መሐንዲሱ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሲሰጠው ኮንትራክተሩ ምላሽ መስጠቱን ጠቁሟል፡፡
ትድሃር ኤክስካቬሽን በሰጠው ምላሽ እንዳስረዳው፣ በሁሉም የድርጅቱ ክፍያዎች ላይ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዕግድ እንደጣለባቸውና በውሉ መሠረት ሥራውን ለመቀጠል በማያስችል ደረጃ ላይ መሆኑን ገልጾ፣ ባለሥልጣኑ ፕሮጀክቶቹን እንዲረከበው ማስታወቁን በክሱ ገልጿል፡፡
ባለሥልጣኑም በውሉ መሠረት ኮንትራቱ እንዲቋረጥ ቢያደርግም፣ ትድሃር ግን ከወሰደው ቅድሚያ ክፍያ ውስጥ 145,936,838 ብር ሳይከፍል ውሉን በማቋረጡ በሕግ አስገዳጅነት የወሰደው ገንዘብ እንዲመለስለት ክስ መመሥረቱንም በክሱ አስታውቋል፡፡ ናይል ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ለኮንትራክተሩ በገባው ውል መሠረት እንዲከፍል ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም፣ የተለያዩ ምክንያቶች በመፍጠር ለመክፈል ፈቃደኛ አለመሆኑንም አክሏል፡፡ በመሆኑም እሱም በሕግ አስገዳጅነት የገባውን ዋስትና ተፈጻሚ እንዲያደርግለት ባለሥልጣኑ ፍርድ ቤቱን በክሱ ጠይቋል፡፡
ስማቸው ከላይ የተጠቀሱ ስድስት ተከሳሾችና ሌሎቹም ተከሳሾች ከሕግና መመርያ ውጪ ውስን ጨረታ በማዘጋጀት፣ ውሉን በመፈረም፣ የግዥ አዋጅ ቁጥር 496/2001 አንቀጽ 48 እና የአስተዳደሩን የግዥ አፈጻጸም መመርያ ቁጥር 3/2002 አንቀጽ 15.26.2 በመተላለፍ፣ የተጠቀሰው ገንዘብ ጉዳት እንዲደርስ በማድረጋቸው ባልተነጣጠለ ኃላፊነት ተጠያቂነት እንዳለባቸው መግለጽ ክሱን አቅርቧል፡፡