Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበዋና ኦዲተር ሪፖርት መነሻ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች ልዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ...

በዋና ኦዲተር ሪፖርት መነሻ ጠቅላይ ሚኒስትሩና የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች ልዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠየቀ

ቀን:

4.2 ቢሊዮን ብር ያላግባብ ወጪ መደረጉ ተገልጿል

ዓቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሠረት ተጠይቋል

በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት በተደጋጋሚ የፌዴራል በጀት ተቀባይ የመንግሥት ተቋማት የሕዝብ ገንዘብ ብክነትና ሕገወጥ አጠቃቀም ከዓመት ዓመት አልተሻሻለም በመባሉ የተማረሩ የፓርላማ አባላት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የተቋማት ኃላፊዎች በምክር ቤት ቀርበው ልዩ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠየቁ፡፡

- Advertisement -

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በ174 ባለበጀት የመንግሥት ተቋማት ላይ በ2010 የበጀት ዓመት ያከናወነውን የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት፣ ሐሙስ ግንቦት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፓርላማው አቅርቧል፡፡

ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በተከታታይ ለአሥር ዓመታት ተመሳሳይ የሚመስል ሪፖርት ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ የምክር ቤቱ አባላት የሕዝብ ገንዘብ እስከ መቼ ተመዝብሮ ይዘለቃል የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡ 

ዋና ኦዲተሩ ባቀረቡት ሪፖርት በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ አለመሰብሰቡን፣ የበጀት ጉድለት የተገኘባቸውንና ትክክለኛ የወጪ ማስረጃ ያልቀረበባቸውን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ እንዲሁም ከዚህ በፊት እንዲያስተካክሉ መመርያ ከተሰጣቸው የመንግሥት ተቋማት አብዛኞቹ ምንም ዓይነት ዕርምጃ አለመውሰዳቸውን አስታውቀዋል፡፡

የገንዘብ ብክነትና የአሠራር ጥሰት በሰፊው የተዳሰሰበት የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት እንዳመለከተው፣ በ129 መሥሪያ ቤቶች ላይ በተደረገ ምርመራ 4.2 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ያላግባብ ወጪ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ያልተወራረደ ጥቅል ገንዘብ ውስጥ ከ763 ሚሊዮን ብር ሳይወራረድ እስከ አንድ ዓመት የቆየ መሆኑን አቶ ገመቹ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም 2.5 ቢሊዮን ብር ማስረጃ ሳይቀርብለት ከአምስት ዓመት በላይ ማስቆጠሩን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ከ432 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ እንዴትና መቼ እንደወጣ እንኳን አይታወቅም ብለዋል፡፡

በጥሬ ገንዘብ ረገድም ከ950 ሺሕ ብር በላይ ጉድለት መገኘቱን ያስታወቁት አቶ ገመቹ፣ ጉድለቱ ከተገኘባቸው ተቋማት መካከል በዋናነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሆኑን አመልክተዋል፡፡ የሰመራና የጂግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎችም ተከታዩን ደረጃ መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዕለቱ ከቀረበው ሪፖርት በተጨማሪ የምክር ቤት አባላቱን ያስቆጣው ከ2010 በጀት ዓመት በተጨማሪ በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም. በምክር ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በተገኙበት ከበጀት ተቀባይ መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ጋር ተደርጎ በነበረው ውይይት፣ ለተቋማቱ የተላለፈው መመርያ ተግባራዊ አለመሆኑ አንደኛው ነው፡፡

በመጋቢት ወር የጋራ ውይይት ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ያላግባብ ወጪ የተደረጉ ሒሳቦችን እንዲመልሱ ለተቋማቱ መመርያ ቢሰጣቸውም፣ መመርያውን ያከበሩት ከአምስት በመቶ እንደማይበልጡ ዋና ኦዲተሩ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ ገንዘቡን በሁለት ወራት ውስጥ እንዲመልሱ ተነግሯቸው የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን የሚጠበቀውን ዕርምጃ እየወሰዱ አለመሆናቸውን አቶ ገመቹ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በወቅቱ ስንሰበሰብ ይህ አዳራሽ ሙሉ ነበር፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ያላግባብ ያወጡትን ወጪ በሁለት ወር ውስጥ እንዲመልሱ ነበር የተነገራቸው፡፡ ሁሉም ተቋማት ገንዘቡን እንዲመልሱና ሪፖርት እንዲልኩ ታዘው የነበረ ቢሆንም፣ 26 መሥሪያ ቤቶች መርሐ ግብራቸውን ብቻ ነው የላኩት፤›› ብለዋል ዋና ኦዲተሩ፡፡

መሥሪያ ቤቶቹ በላኩት መርሐ ግብር በመጪው ዓመት ገንዘቡን እንደሚመልሱ መግለጻቸው ተጠቁሟል፡፡ በተመሳሳይ በ2009 ዓ.ም. ሪፖርታቸው ሕግ ጥሰው 228.7 ሚሊዮን ብር  ወጪ ያደረጉ ተቋማት ገንዘቡን እንዲመልሱ ተነግሯቸው እንደነበር አቶ ገመቹ አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን በተነገራቸው መሠረት ገንዘቡን የመለሱት ከአምስት መቶ እንደማይበልጡ፣ የተመለሰውም 12 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

‹‹ለሚቀጥለው ዓመት ይደረጋል የሚለው ጉዳይ በፍጹም ተቀባይነት የለውም፡፡ እሺ ቢባሉ እንኳን ምንም ዓይነት ዕርምጃ ይወስዳሉ ብዬ አላስብም፡፡ ሊሆንም አይችልም፡፡ በየዓመቱ የሕዝብ ገንዘብ እየባከነ፣ ያላግባብ ወጪ እያወጡ፣ ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረበን ነጋዴ ትተው ከሌላ ነጋዴ በጭማሪ ዋጋ እየገዙ፣ እንደፈለጉ የአገር ሀብት እያባከኑ መሄድና ሁሌም ተመሳሳይ ሪፖርት መስማታችን እዚህ ላይ ሊቆም ይገባል፤›› ሲሉ አንድ የምክር ቤት አባል ከረር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

እኚሁ የምክር ቤት አባል፣ ‹‹ይህ ጉዳይ እዚህ ላይ መቆም ካለበት ዛሬውኑ ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡ አሁን ልናደርግ የሚገባው ብዬ የማምነው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በሥራቸው ያሉት ተቋማትና ኃላፊዎች እዚህ መጥተው በልዩ ጉባዔ የእያንዳንዱን መሥሪያ ቤት ወጪ ልንጠይቃቸውና ማብራሪያ ሊሰጡ ይገባል፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ሌላ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው የሕዝብ ተወካይ ሆነው በምክር ቤቱ በቆዩባቸው ስምንት ዓመታት፣ ተመሳሳይ ሪፖርትና ተመሳሳይ የፋይናንስ ብክነት መስማት እንደሰለቻቸው በምሬት ገልጸዋል፡፡

በምክር ቤቱ አባላትም ሆነ በዋና ኦዲተሩ የቀረቡትን አስተያየቶች የደገፉት አፈ ጉባዔው ተመሳሳይ አቋም አንፀባርቀዋል፡፡

አፈ ጉባዔው ባለፈው መጋቢት ወር ራሳቸው በመሩት የጋራ መድረክ የተላለፈውን መመርያ በማስታወስ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ ተቋማቱን በተመሳሳይ መንገድ የማሻሻያ ዕርምጃ እንዲወስዱ በማሳሰብ ብቻ አናልፍም፤›› ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አሁን በቀረበው ሪፖርት መሠረት ክስ እንዲመሠርት አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...