Tuesday, March 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያን ከውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ጥገኝነት ለማላቀቅ ታዳሽ ኃይል ላይ ትኩረት ተደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን ከውኃ ኃይል ማመንጫዎች ጥገኝነት ለማላቀቅ ትኩረት ቢያደርግም፣ በዕቅዱ መሠረት ያልሄደለት የፌዴራል መንግሥት በድጋሚ ትኩረቱን አማራጭ የኃይል አቅርቦት ላይ አደረገ፡፡

በዚህ መሠረት በአጠቃላይ ከፀሐይ ኃይል 800 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን የጀመረ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ከዴንማርክ መንግሥት በተገኘ የኮንሴሽን ፋይናንስ በኦሮሚያ ክልል አሰላ አካባቢ 100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ 12 አነስተኛ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ግንባታ የሙከራ ፕሮጀክት ለማስጀመር ዓርብ ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. የፊርማ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡ የእነዚህ ፕሮጀክቶች ወጪ በኢትዮጵያና በዓለም ባንክ የሚሸፈን መሆኑ በዕለቱ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት ፕሮጀክቶቹ በ296.3 ሚሊዮን ብር በጀት ብሔራዊ የኃይል መረብ በማይደርስባቸው ቦታዎች እንደሚገነቡና ለ67,700 ቤቶች የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያዳርሱ ታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ በአጠቃላይ 50 ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አላት፡፡ ከዚህ ውስጥ 45 ሺሕ ሜጋ ዋት ከውኃ፣ ቀሪውን ከንፋስ፣ ከፀሐይና ከእንፋሎት ማመንጨት እንደሚቻል ይነገራል፡፡

አገሪቱ ባለፉት ዓመታት ከውኃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችሉ በርካታ ፕሮጀክቶች የተካሄዱ ሲሆን፣ በታሰበላቸው መንገድ ባይጓዙም ከንፋስና ከእንፋሎት የተወሰኑ ፕሮጀክቶች ተጀምረዋል፡፡ ነገር ግን የአዳማና የአሸጎዳ ንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ተጠቃሽ ቢሆኑም፣ አሸጎዳ የቴክኒክ ችግር እንዳጋጠመው ተጠቁሟል፡፡

በተለይ ግድቦች ውኃ መያዝ በማይችሉበት ወቅት ታዳሽ የኃይል አቅርቦቶች ወሳኝ ቢሆኑም፣ አማራጭ ፕሮጀክቶቹ ግን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦቱን እምብዛም መደገፍ በማይችሉበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ይገለጻል፡፡

የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በቅርብ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ እየተካሄዱ ያሉ የውኃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ህዳሴ፣ ኮይሻና ገናሌ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ሆነው ይጠናቀቃሉ፡፡

‹‹ከዚህ በኋላ አገሪቱን በገጠማት የካፒታል እጥረት ምክንያት የኃይል ማመንጫ ግንባታዎች የሚካሄዱት በግልና በመንግሥት አጋርነት ይሆናል፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅሟ 4,300 ሜጋ ዋት ቢሆንም፣ ግድቦች ውስጥ በቂ ውኃ ባለመግባቱ የሚያመነጩት ኃይል ወደ 1,400 ሜጋ ዋት ቀንሷል፡፡ በዚህ ምክንያት የፈረቃ ፕሮግራም ውስጥ የተገባ ሲሆን፣ ፈረቃውም እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም. ይዘልቃል፡፡

ነገር ግን ከውኃ ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን በዕቅድ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ ቢሠራ ይህ ችግር ሊቀረፍ ይችል እንደነበር ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች