Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሙሉ በሙሉ ክፍያ ለፈጸሙ 198 የ40/60 ተመዝጋቢዎች ዕግድ ተሰጠ

ሙሉ በሙሉ ክፍያ ለፈጸሙ 198 የ40/60 ተመዝጋቢዎች ዕግድ ተሰጠ

ቀን:

መንግሥት አዳዲስ የቤት ግንባታ ፓኬጆችን በመጨመር በ2005 ዓ.ም. መጠናቀቂያ ወር ላይ ባደረገው ድጋሚ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምዝገባ በወቅቱ ተሠልቶ የነበረውን ጠቅላላ ዋጋ መቶ በመቶ ከከፈሉ ነዋሪዎች መካከል፣ 198 ተመዝጋቢዎች ባቀረቡት ክስ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በከሳሾች ቁጥር ልክ እንዲታገዱ ትዕዛዝ ተሰጠ፡፡

ዕግዱን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ፍትሐ ብሔር ስምንተኛ ምድብ ችሎት ሲሆን፣ ዕግዱን የሰጠው በእነ ራሔል ዘወንጌል የክስ መዝገብ ለተካተቱ 198 ተመዝጋቢዎች ሐሙስ ግንቦት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ዕግዱን የሰጠው በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 80/93 እና 222/228 መሠረት 626,004 ብር የዳኝነት መክፈላቸው ተረጋግጦ ነው፡፡  

ተመዝጋቢዎቹ ክስ የመሠረቱት በዋናነት በኢትዮጵያን ንግድ ባንክ ላይ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራዝና በኮንስትራክሽን ከተማ ልማት ሚኒስቴር ላይ ነው፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ እነሱ ሙሉ በሙሉ በመክፈላቸው ቤቶቹ ተጠናቀው በዕጣ ሲከፋፈሉ ቅድሚያ ለእነሱ እንደሚሰጣቸው የገቡት ሕጋዊ ውል ታልፎ፣ የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ከ40 በመቶ በላይ የቆጠቡ በዕጣው እንዲካተቱ ተደርጎ ዕጣው እንዲወጣ መደረጉን በመቃወም መሆኑ ይታወቃል፡፡

የዕጣውን መውጣት በቅድሚያ በመቃወም 98 ሰዎች ክስ በመመሥረታቸው፣ ዕጣ የወጣባቸው ከ18 ሺሕ በላይና ወደፊት ዕጣ የሚወጣባቸው ቁጥራቸው ያልታወቁ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በፍርድ ቤቱ እንዲታገዱ ያደረጉ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ በከሳሾቹ ቁጥር ልክ ቤቶቹ ከየሳይቱ ታግደው እንዲቆዩ ትዕዛዝ በመስጠት የሌሎቹ ቤቶች ዕግድ እንዲነሳ አድርጎ ነበር፡፡

ከ98 ቤቶች በስተቀር ቀሪዎቹ ዕጣ የወጣባቸውም ሆነ ወደፊት ዕጣ የሚወጣባቸው ቤቶች ዕግድ በመነሳቱ፣ 198 ተመዝጋቢዎች ‹‹ዕጣ ለወጣላቸው ነዋሪዎች ለማዘዋወር በሒደት ላይ እንደሆነ ደርሰንበታል፤›› በማለት በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 205 እና 154 ድንጋጌ መሠረት የዕግድ አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡

ተመዝጋቢዎቹ በአቤቱታቸው እንደገለጹት፣ ቤቶቹ ቢዘዋወሩ የማይተካ ጉዳት እንደሚደርስባቸው እርግጠኞች ናቸው፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ በቁጥራቸው ልክ 101 ባለሦስት መኝታ ቤት፣ 86 ባለሁለት መኝታ ቤትና 11 ባለአንድ መኝታ ቤት በየሳይቱ ከሚገኙ፣ ቢቻል ዕጣ ካልወጣባቸው ቤቶች ላይ ቀንሶ ሳይተላለፉ እንዲቆዩ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም አቤቱታቸውን ከተመለከተ በኋላ በጠየቁት አቤቱታ መሠረት ቤቶቹ ታግደው እንዲቆዩ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ተከሳሾች ለሰኔ 21 ቀን ምላሽ እንዲሰጡ በማለት ለክርክር ለሰኔ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምን ያህል አመልካቾች እንደተሰባሰቡ ቁጥራቸውን ማወቅ ባይቻልም፣ በርካታ ተመዝጋቢዎች (መቶ በመቶ የከፈሉ) አንድ ላይ በመሆን የክስ ፋይል ለመክፈት እየተዘጋጁ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ