Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ አበባ ሆቴል ስያሜውን እንዳይጠቀም የተላለፈው ውሳኔ ታገደ

ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ አበባ ሆቴል ስያሜውን እንዳይጠቀም የተላለፈው ውሳኔ ታገደ

ቀን:

የተላለፈው ውሳኔ ነጋዴዎችን ሥጋት ላይ የሚጥል ነው ተብሏል

በአዲስ አበባ ከተማ ካዛንቺስ የሚገኘውና ጥቅምት 7 ቀን 1999 ዓ.ም. በተወሰደ የንግድ ፈቃድ ከጥር 17 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ ‹‹ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ አበባ ሆቴል›› በሚል ስያሜ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ አበባ ሆቴል፣ ስያሜውን እንዳይጠቀም በፍርድ ቤት የተላለፈበት ውሳኔ በይግባኝ ታገደ፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የንግድ ምልክቱና ስያሜው ባለቤት ‹‹ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴልስ ኮርፖሬሽን›› መሆኑ ተጠቅሶ በቀረበ ክስ፣ ጄኤች ሲሜክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ድርጅት የሆነው ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ አበባ ሆቴል የሚለው ስያሜ፣ ተመሳሳይ ስም በየትኛውም ቦታ ሆነ ዕቃዎች ላይ የለጠፋቸውን ማስታወቂያዎች እንዲያነሳና የተከፈተ ድረ ገጽ እንዲዘጋ፣ እንዲሁም ለከሳሽ 750,000 ብር ከወለድ፣ ወጪና ኪሳራ ጋር እንዲከፍል የካቲት 20 ቀን 2011 ዓ.ም. ውሳኔ ማስተላለፉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመቃወም ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር ችሎት ይግባኝ ያለው ጄኤች ሲሜክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ አበባ ሆቴል የንግድ ምልክት ሳይሆን የንግድ ስም መሆኑን ጠቁሟል፡፡ የንግድ ስያሜውን በንግድ፣ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም ቢሮ አስመዝግቦ ጥቅምት 7 ቀን 1999 ዓ.ም. ከወሰደ በኋላ በ2001 ዓ.ም. የሆቴል አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑንም አክሏል፡፡

ከሳሽ ሆኖ የቀረበው ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴልስ ኮርፖሬሽን ‹‹መብቴን ይጎዳዋል›› የሚል ከሆነ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2143 (1) መሠረት ክሱን ማቅረብ የነበረበት አገልግሎቱን መስጠት በጀመረበት ሁለት ዓመት ውስጥ መሆን ሲገባው፣ ከአምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ይህንንም የሕጉን ድንጋጌ በመጥቀስ ለሥር ፍርድ ቤት ‹‹በይርጋ ሊታገድ ይገባል›› በማለት በመከራከሪያነት ማቅረቡንም አስታውቋል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት ግን ምክንያቱን እንኳን ሳይገልጽ፣ ‹‹በተከራካሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት ከውል ውጪ የሆነ ግንኙነት አይደለም፤›› በማለት ያላግባብ ሕጋዊ መከራከሪያ ሐሳቡን ውድቅ እንዳደረገበት በይግባኙ ገልጿል፡፡ ነገር ግን ራሱ የሥር ፍርድ ቤት ካሳን አስመልክቶ በሰጠው ውሳኔ ላይ የጠቀሰው የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2101 የተከራካሪዎች ግንኙነት ከውል ውጪ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ይግባኝ ባይ ጠቁሟል፡፡  

የሥር ፍርድ ቤት የይርጋ ክርክሩን ውድቅ ለማድረግ የጠቀሰው ማቋረጫ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 1851 የይርጋ ማቋረጫ ምክንያቶች ጋር የተጣጣመ አለመሆኑን፣ ጄኤጅ ሲሜክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በይግባኙ ገልጿል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎትም በመዝገብ ቁጥር 90361 አስገዳጅ ትርጉም መስጠቱንም አስታውሷል፡፡

ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴልስ ኮርፖሬሽን የንግድ ምልክትና የንግድ ስያሜን በሚመለከት የተሰጠን አስተዳደራዊ ውሳኔን በሚመለከት፣ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 320 እና በአዋጅ ቁጥር 25/88 ድንጋጌ መሠረት ሥልጣን ላለው የፌዴራል ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለት ሲገባው ቀጥታ ማኅበሩን መክሰሱ አግባብ እንዳልሆነም በይግባኙ አመልክቷል፡፡ የሰበር ሰሚ ችሎትም በመዝገብ ቁጥሮች 69603፣ 63454 እና 59025 አስገዳጅ ትርጉም እንደሰጠበትም አክሏል፡፡ የሥር ፍርድ ቤት በራሱ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 231 (1) ድንጋጌ መሠረትም ውድቅ ሊያደርገው ይገባ እንደነበርም ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም በፍትሐ ብሔር ሕግ ድንጋጌዎችና ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ውሳኔዎች በመታለፋቸው ሊታረም እንደሚገባም ገልጿል፡፡

የሥር ፍርድ ቤት ከሳሽ፣ ‹‹ባለቤት ነኝ›› ያለበት የንግድ ምልክት በውስጡ “INTER CONTINENTAL” ወይም “INTER.CONTINENTAL” የሚል የተጻፈበት አራት ማዕዘን መሆኑን የገለጸው ይግባኝ ባይ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው የኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴልስ ኮርፖሬሽን የንግድ ምልክት ደግሞ በሞላላ ቅርፅ ውስጥ “INTER CONTINENTAL HOTELS & RESORTS የሚል የተጻፈበት መሆኑንም ጠቅሷል፡፡ ይግባኝ ባይ ጄኤች ሲሜክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚጠቀምበት ደግሞ የሚነበብ ጽሑፍ የሌለበት ሎጎ ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም ከከሳሹ ጋር የማይመሳሰል መሆኑንም አክሏል፡፡ በመሆኑም የሥር ፍርድ ቤት በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 244 (2መ) ድንጋጌ መሠረት፣ በፍሬ ጉዳይ ክርክር ሊያየው እየተገባ ውድቅ ማድረጉ ተገቢ አለመሆኑን ይግባኝ ባይ ጠቁሟል፡፡

የሥር ፍርድ ቤት ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ አበባ ሆቴል በመዝጋቢ መሥሪያ ቤት ሕግን ተመሥርቶ የተሰጠ የሆቴል ስም መሆኑን የተቀበለው ቢሆንም፣ ማኅበሩ የንግድ ስያሜ እንጂ የንግድ ምልክት አለመሆኑን እየገለጸ እያለ አዋጅ ቁጥር 501/98 አንቀጽ 26 (2) ድንጋጌን በመተላለፍ የሰጠው ውሳኔ መታረም ያለበት መሆኑን ገልጿል፡፡ ማኅበሩ በንግድ ስያሜነት ያስመዘገበው በአዋጅ ቁጥር 686/2002 አንቀጽ 26 (1) እና (28) ድንጋጌን መሠረት መሆኑንም አክሏል፡፡ ስያሜውም በአዋጅ ቁጥር 67/89 እና በተሻሻለው 686/2002 የተፈቀደለት መሆኑን ለሥር ፍርድ ቤት ተጨማሪ ማስረጃ ጭምር ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም፣ ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ በመስጠት በማለፉ ሊታረምለት እንደሚገባ በአቤቱታ ገልጿል፡፡

በአጠቃላይ የሥር ፍርድ ቤት “INTER CONTINENTAL” ወይም “INTER.CONTINENTAL” የሚለው የንግድ ምልክት ብቻ መሆኑን ከሳሹ አምኖ እያለ፣ ‹‹በዚህ ምልክት ሊሰጥ ያሰበው አገልግሎት መቼም ያው የሆቴል አገልግሎት ነው፤›› የሚል መደምደሚያ ላይ መድረሱ ተገቢ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ በግምት እንጂ በሕግና በማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ባለመሆኑ፣ የፍርድ አሰጣጡ ይግባኝ ባይን ብቻ ሳይሆን በሕጋዊ መንገድ የንግድ ስምና ምልክት መዝገባቸውን አግኝተው ሥራቸውን በማከናወን ላይ የሚገኙ ነጋዴዎችን ሳይቀር ሥጋት ላይ የሚጥል በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባው በይግባኙ ጠይቋል፡፡

በመሆኑም የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2143 (1) ድንጋጌ መሠረት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ክሱ ስላልቀረበ በይርጋ እንዲታገድ፣ ከሳሽ ይግባኝ ማቅረብ እንደ ቀጥታ ክስ ማቅረብ እንደሌለበት፣ ከሳሽ ባለቤት ነኝ ያለበት የንግድ ምልክት ከይግባኝ ባይ ጋርም ሆነ ዓለም አቀፍ ከሚታወቀው ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴልስ ኮርፖሬሽን ጋር እንደማይመሳሰልና ማኅበሩ ስያሜውን በማንኛውም ቦታ የለጠፋቸው ማስታወቂያዎችንና የከፈተውን ድረ ገጽ እንዳይጠቀም የሚለው የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሻርለት ያቀረበው የዳኝነት ይግባኝ አቤቱታ ተቀባይነት አግኝቶ ለክርክር ተቀጥሯል፡፡

የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ታግዶ ለክርክር ለሰኔ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡          

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...