Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉስለ ‹‹የፍትሕ አካላት›› ወዴት አቤት ይባላል?

ስለ ‹‹የፍትሕ አካላት›› ወዴት አቤት ይባላል?

ቀን:

በሪያድ አብዱል ወኪል

እንደ መንደርደሪያ. . .

እውነትም ‹‹አንዳንድ ነገሮች›› ብዙ ያስገርማሉ፡፡ በተለይ በተደጋጋሚ አቤቱታ ቀርቦባቸው መንግሥታዊ ጆሮ ሲነፈጉና ትኩረትም ሆነ ተግባራዊ ምላሽ ሲያጡ ያበሳጫሉ፡፡ ይህ አቤቱታ ከመሠረታዊው የሰው ልጆች ሁሉ በእኩልነት የመታየት መብት ጋር የተያያዘ ሲሆንና እየተሠራ ያለው ሥራ ከሕግም ሆነ ከህሊና ጥያቄ (Moral) አኳያ ስሁት ሆኖ ሲስተዋል ደግሞ፣ ከማበሳጨትም በላይ ይሆንና ወደ ማስቆጣት ይሻገራል፡፡

- Advertisement -

ይህ ብልሹና አግላይ አሠራር እንዲሻሻል፣ ዜጎችንም በእኩልነት አካታች እንዲሆን ደጋግማችሁ እየጠየቃችሁ ሁኔታው ግን ከዓመት ዓመት ባለበት ሲረግጥና ተቋማትን እየቀያየረ ሲጠብቃችሁ መጠየቅ ይደክማችኋል፡፡ ‹‹ለውጥማ አለ!›› ብላችሁ ትሩፋቱን እየጠበቃችሁ ሳለ ተስፋችሁ ላይ ቀዝቀዝ ያለ ውኃ የሚቸልስ ተመሳሳይ መገፋት ሲጠብቃችሁ፣ ‹‹አንዳንድ ነገሮች ብዙ ያስደንቁኛል. . .›› እያላችሁ ከጥላሁን ገሠሠ ጋር መደነቃችሁ አይቀርም፡፡

አቤቱታችሁ የቀረበውና ምላሽ የተነፈጋችሁት ዜጎችን በእኩል ዓይን ተመልክቶ ለማስተናገድና ሌሎች የመንግሥት አካላትም ይህንኑ አርዓያ እንዲያደርጉ የማቀናጀት ኃላፊነትና ግዴታ፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 13(1) ከተጣለባቸው ‹‹የፍትሕ ተቋማት›› ሲሆንና የተቋማቱ አውራ ከሆነው ቤተ ፍትሕ ሲሆን ደግሞ ጉዳዩ ግራ የገባው ግራነቱ ከማስገረምም፣ ከማስደነቅም፣ ከማስቆጣትም ከፍቶ ተስፋ አስቆራጭ ይሆንባችኋልና ወደ ውስጥ እህህ ትላላችሁ፡፡

‹‹አምናና ካቻምና፣ ታምሜ ነበረ

ዘንድሮ ባሰብኝ፣ ሳይሻለኝ ቀረ፡፡››

የይግባኙ ምክንያት በአጭሩ!

ዕለተ ዓርብ ግንቦት 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ንጋት ላይ የሸገር ሬዲዮ የማለዳ ወሬዎችን እያደመጥኩ ነው፡፡ ሬዲዮ ጣቢያው አንድ ጥሩ ልምድ ጀምሯል፡፡ የከራስ ተነሳሽነት ጥየቃው ትይዩ አድማጮቹ በተለያዩ ተቋማት አሠራሮች ላይ የሚያነሷቸውን ቅሬታዎች ‹‹ማንን ምን እንጠይቅልዎ?›› ብሎ በሰየመው መሰናዶ ይቀበላል፡፡ ቅሬታው ለተነሳበት አካልም ጥያቄውን በቀጥታ በማቅረብ ምላሹን በስልከኛው ጋዜጠኛ ግርማ ፍሰሐ በኩል እንካችሁ ይላል፡፡ ይህ የብዙኃን መገናኛ ሚና የሆነውና በብዙ ሲተገበር ግን የማላስተውለው በጎ ጅምር ወደ ሌሎች የብዙኃን መገናኛዎች፣ በተለይም ወደ ሕዝባዊዎቹ እንዲጋባና ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያስመኛል፡፡

በእርግጥ በንግግሯ ካከበርኳት ከአንዲት ምሥጉን የመንግሥት ተቋም ኃላፊ በቀር የተገልጋይ ቅሬታ ቀርቦበት ምላሽ የመስጠት፣ ሕዝባዊ ግዴታውንና መንግሥታዊ ኃላፊነቱንም የመወጣት ፍላጎት ሲያልፍም የማይነካው ሹመኛ ዛሬም ከወንበሩ ተደላድሏል፡፡ በእርግጥም ‹‹ቅሬታው ትክክል ነው፣ ችግሩን ለመፍታት እንሠራለን፣ ተገልጋያችንም ስለተፈጠረባቸው መጉላላት ይቅርታ እንጠይቃለን!›› ሲል ያደመጥኩት ኃላፊም ሆነ ተወካይ አላጋጠመኝም፡፡ ቅሬታዎቹን አምኖ በመቀበል ለመፍታት ከመጣጣር የግማሽ መፍትሔነት ጎዳና ይልቅ፣ ልማዳዊውን የማስተባበል መንገድ አሁንም እየሄድንበት እንደሆነም አስተውያለሁ፡፡

በዕለቱ ጋዜጠኛው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ከሆኑ አራት ያህል ወራት ያስቆጠሩትን አቶ ተስፋዬ መለሰን አነጋግሮ ነበር፡፡ ቅሬታውን በተወካያቸው በኩል ወደ ሸገር ሬዲዮ በቀጭኑ ሽቦ ያደረሱት ሰዎችም ለአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች በቅርቡ በዕጩ ዳኝነት በተደረገው ምልመላ ላይ ነበር ቅሬታቸው፡፡ ሆኖም ዋነኞቹ ባለቅሬታዎች የሆኑትና አሁን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በረዳት ዳኝነት እየሠሩ ያሉት ግለሰቦች፣ ለጋዜጠኛው ሙሉ ሥዕሉን እንዳልሰጡትና ጋዜጠኛውም በጉዳዩ ላይ በተለይም በአዲስ አበቤዎቹ የሕግ ተማሪና ባለሙያዎች ነባር ቅሬታ ላይ የተሟላ መረጃ እንዳልነበረው ቃለ ጭውውታቸው አስረድቶኛል፡፡

አቶ ተስፋዬ የፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት እንደመሆናቸው መጠነኛም ቢሆን ‹‹ፖለቲካዊ ቁመና›› እንደሚኖራቸው፣ በአገራችን የፍትሕ ዘርፍ ላይ ከነበረው የፍትሕ ጽሕፈት ቤቶችና የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች አሰያየም እረዳለሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲ የሕግ ተማሪዎችን ለድርጅት አባልነት ከመመልመል ጀምሮ የሚስተዋለው ይህ ችግር ዳኞችን ለፌዴራልም ሆነ ለሌሎች ፍርድ ቤቶች ሹመት በማጨቱ ረገድም ሲቀጥል ይታያልና ነው ይህንን ማለቴ፡፡ ለዳኞች ሹመት በፌዴራል ‹‹ለሕገ መንግሥቱ›› ለከተማዋ ፍርድ ቤቶች ሲሆን ደግሞ፣ ‹‹ለሕገ መንግሥቱና ለከተማዋ ቻርተር ታማኝ የሆነ/ች›› የሚለው መሥፈርት በራሱ ችግር ባይሆንም፣ ወደ ሥራ ሲመነዘር ‹‹ለገዥው ፓርቲ ታማኝ የሆኑ›› ተብሎ እንዲተረጎም መሆኑም አንዱ ‹‹የማይፈለጉ ሰዎችን›› ከዳኝነቱ ዘርፍ የማንጓለያ ወንፊት እንደነበርና እንደሆነ አይዘነጋም፡፡

‹‹መሥፈርት አላሟሉም›› ሲባል?

በሪፖርተር ጋዜጣ የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ዕትም ‹‹የሥራ ማስታወቂያ›› ገጽ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት ለከተማዋ ፍርድ ቤቶች ዳኞችን መልምሎ ለማሾም ባስነገረው ማስታወቂያ ሥር፣ ከ‹‹ታማኝነት›› እና ከአራት ዓመት የሥራ ልምድ ባሻገር ‹‹የቅድመ ዳኝነት ሥልጠና የወሰዱ›› የሚል ‹‹እንዳያማህ ጥራው. . .!›› ለከንቱ እንዳልተተረተ የሚያሳብቅ መሥፈርትን ነበር አንዱ የማጣሪያ መሥፈርት አድርጎ ያቀረበው፡፡ በዚህ ገፊ መሥፈርት የሸገር ልጆች ከፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቢሮና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተባረንበታል፡፡ ይህንን አግላይ መሥፈርት አዲስ አበቤዎች ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች ችሎት ደጃፍም ተንጓለውበታል፡፡ በዚሁ መሥፈርት ሳቢያ አዲስ አበባውያኑ የሕግ ተማሪዎች፣ ምሩቃንና በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተበታተኑ የሕግ ባለሙያዎች ለፌዴራል ፍርድ ቤቶችና ለፌዴራሉ ዓቃቤ ሕግነት ብቻ ሳይሆን፣ እነሆ አሁን ደግሞ ተወልደው ያደጉባትን ከተማ ፍርድ ቤቶች እንኳን በዳኝነት እንዳያገለግሉ እየተደረጉ ነው፡፡

በሌላ አነጋገር የዳኝነትና የዓቃቤ ሕግነትን ልምድ እንደ አስገዳጅ የሥራ ልምድ በመሥፈርትነት ለሚያቀርቡ ሌሎች የሕግ ባለሙያ ሥራዎችና የሥራ ማስታወቂያዎች ሁሉ፣ አዲስ አበባውያኑ ‹‹ብቁ!›› ተወዳዳሪ አይሆኑምና ውድድሩ ሳይጀመር ይወድቃሉ ማለትም ነው፡፡ ታዲያ የዜግነት ክብሩ ከወዴት አለ? አዲስ አበባውያኑ የሕግ ተማሪዎች፣ ምሩቃንና ባለሙያዎችስ በማጥለያው ሾልከው ከመንጠባጠብ በቀር ይህንን ወረቀት ከየት ሊያገኙት ይችላሉ? አቶ ተስፋዬ ስለቅሬታው ምንጭ ሲናገሩ የአዲስ አበባ ወይም የክልል ሳይባል ሁሉም በእኩልነት ተወዳድሮ የሚሾምበት ስለመሆኑ በመጥቀስ፣ ‹‹መሥፈርቱን ካሟላ ብቻ ነው ዳኛ መሆን የሚችለው፡፡ ቅሬታም ሲነሳ ‹መሥፈርቱን አሟላ ነበር ነገር ግን መሥፈርቱን አሟልቼ እንዳልወዳደር ተደርጌያለሁ› የሚል ሰው ካለ፣ ማስረጃው ከቀረበና ትክክል ከሆነ እሱ ያስኬዳል፡፡ ማስረጃው ሳይቀርብ እንዲሁ ተገለልኩ የሚል ሰው ካለ ካላሟላ መገለል ሳይሆን መሥፈርት አላሟላም ነው የሚሆነው ምላሹ፤›› ብለዋል፡፡

በየወቅቱ ተሿሚ የሚቀያየሩለት ከለጋሽ ተቋማት ሚሊዮኖች የሚለገሰው የፌዴራሉ የፍትሕ አካላት ባለሙያዎች ሥልጠናና የሕግ ምርምር ኢንስቲትዩት ሥራውን በአግባቡ ሠርቶ በማይመሠገንበት ሁኔታ፣ በፌዴራሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች ለሚወጡ የሥራ ውድድርና ዕድሎች ተገቢ (Eligible) የሆኑ አመልካቾች የሚመጡት ከክልል ብቻ ይሆናልና የአዱ ገነት ልጆች እንደተለመደው (Business as Usual) እንዲሉ፣ የበይ ተመልካች ሆነን ቀረን ማለትም አይደል? አቶ ተስፋዬ በምላሻቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ‹‹ግለሰቦች ‹የተበላሸ አሠራር ተስተውሏል› ሳይሆን ‹መሥፈርቱን አላሟላንም› ማለት ነው ያለባቸው፤›› ሲሉ አድምጫለሁ፡፡ አቶ ተስፋዬ የሕግ ባለሙያ ያውም በዳኝነቱ ምድብ ውስጥ ያሉ ናቸውና በሕግ ቋንቋ እንግባባለን ብዬ አምናለሁ፡፡ በእኩልነት ስለመስተናገድ መብት ሲወሳ በሕግ ትምህርት፣ በተለይም በመሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች የሕግ ዘርፍ ትንታኔ ውስጥ አርስቶትል ይደጋገማል፡፡

በኢመደበኛ መርህነትም “Equality Consists in the Same Treatment of Similar Persons… the Worst Form of Inequality is to try to Make Unequals Equal. . . የሚሉት የአርስቶትል አባባሎች ይወሳሉ፡፡ እኩል የመወዳደሪያ ሁኔታ (Equal Opportunity) ውስጥ እንዲሆኑ ዕድሉን ያልሰጠናቸውንና ሁኔታውን ያላመቻቸንላቸው በሁለት የተለያየ መስተንግዶ ውስጥ ያሉ ሰዎችን መምህሩ እንዳለው፣ በአንድ ዓይነት ሚዛነ ልኬት (In the Same Treatment) መስፈሩ ‹‹Treating Unequals Equally is Against the Principle of Equality›› ይሆናልና የአቶ ተስፋዬም ሆነ በዚህ አቋም ላይ ያሉ ሌሎች ግለሰቦች መከራከሪያ በሕግም ሆነ በህሊና የዳኝነት ሸንጎ መሠረት የሌለው ይሆናል፡፡

ልክ እንደ ‹‹ታማኝነቱ›› ሁሉ ይህንን የሥልጠና ዕድል ለማግኝትም ያለው ‹‹የፖለቲካ ውጣ ውረድ›› ቀላል አልነበረም፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በአዲስ አበቤነቴ ከማዕዱ ብገፋም በከባድ ትግል ውስጥ አልፌ ወረቀቱን ይዣለሁ፡፡ በዓቃቤ ሕግነትም አገልግያለሁ፡፡ ይህንን ሁሉ የምጽፈው ስለፍትሐዊነትና እኩልነት ካለኝ መቆርቆር ነው፡፡ ምሥጋና ለሪፖርተር ጋዜጣ አዘጋጆች ይሁንና በጉዳዩ ላይ ከአንድም ሁለት ሦስት ጊዜ ጽፌበታለሁ፡፡ ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም. የተለያዩ ወቅቶች በስሜም በብዕር ስምም ‹‹ይድረስ ለሪፖርተር›› ስል በሪፖርተርም ‹‹ይድረስ ‹ለሚመለከታችሁ› የፍትሕ አካላት›› በማለት ተመሳሳይ ጭብጥ ያላቸው ስሞታዎች ተስተናግደዋል፡፡

ለመሆኑ ሥራ ፈላጊው ከየአቅጣጫው በርክቶባት ከአቅሟ በላይ የሆነባትን መናገሻ ከተማ ‹‹የሚያስተዳድሩ›› ሰዎች ለኢጆሌ ፊንፊኔ ቅድሚያ የሚሰጡበት የሥራ ዘርፍ ይኖር ይሆን? የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔስ ዝርዝሩን ሲመለከት ምን ብሎ ይሆን? የከተማዋ ምክር ቤት አባላትስ ዳኞቹ ለሹመት ሲቀርቡላቸው እንደ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሁሉ (በ2009 ዓ.ም.) ተደጋጋሚ የአዲስ አበቤዎች አቤቱታና የረዳት ዳኞች ውትወታ አልደረሳቸው ነበር ይሆን? አዱ ገነት ምንም እንኳን የፌዴራሉ መንግሥት ማዕከል ብትሆንም ለእኛ ለሸገሬዎቹ እንደ ክልል ናትና ሌሎች ክልሎች ለተወላጆቻቸው የሚሰጡትን ዓይነት የቅድሚያ መብት ብንጠይቅ ከጠባብነት ይቆጠርብን ይሆን. . ?

‹‹ያልተጠየቀ ዳኝነት›› ይሏል ይህ ነው!

እኔ እስከማውቀው ድረስ አዲስ አበባውያኑ የሕግ ተማሪዎችና ባለሙያዎች ይህንን የእኩል ባለመብትነት ጥያቄ በሚያበሳጨን ልክ አላጮህነውም፡፡ በሕግ ትምህርት ቤት ከተጎዳኝናቸው የየክልሉ ወንድሞቻችን ኢትዮጵያውያንም ሆነ የሙያ እኩዮቻችን የሕግ ባለሙያዎች ጋር ችግር የለብንም፡፡ ማንም ስለአዲስ አበቤዎች ይህንን መመስከር ይችላል፡፡ ዝንጋኤውን የፈጠረው ችግሩ ከዓመት ዓመት ይቀረፋል እያልን ለውጥን በተስፋ በመጠበቃችን ብቻ ነው፡፡ አቶ ተስፋዬ ይህንን እውነታ ቢረዱትም ከጋዜጠኛው ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ያሉትን ሲሰጡ በስጨት ብለው ነበር፡፡ ‹‹እዚህ ጋ ከክልል መጡ የሚለው ነገር ማስተካከያ ቢደረግበት ጥሩ ነው፡፡ ከክልል ሳይሆን ከአዲስ አበባም ጭምር የመጡ አሉ. . . ዋናው ነገር ምንድነው ክልል ክልል ክልል ሲባል ዋናው መስተካከል ያለበት ጉዳይ ሆን ተብሎ ከክልል ብቻ ሰው ለማምጣት ተደረገ ሳይሆን፣ ነገርዬው ለከተማው ማኅበረሰብ ብቁ የዳኝነት አገልግሎት መስጠት የሚችል ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሕግ ባለሙያ የሆነ እንዲወዳደር ነው የተደረገው፤›› የሚለውን ‹‹እውነት የሚመስል›› አገላለጽ የተጠቀሙት፡፡

ውድድሩ በኢትዮጵያውያን መካከል የሚደረግ ነውና ኤርትራውያን ወገኖቻችን በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ችሎት አዳራሾች ተገኝተው እንደማይዳኙን የታመነ ነው፡፡ በኢትዮጵያውያን መካከልም ማንም ከማንም ያነሰ ወይም የበለጠ ኢትዮጵያዊነት የለውምና አቶ ተስፋዬ መቆርቆራቸው ስለኢትዮጵያውያን ሁሉ ሊሆን በተገባ ነበር፡፡ ቁርቋሬው ለአዲስ አበባውያንም ሊተርፍ ያልተጠየቀ ዳኝነትን ከመስጠትም መቆጠብ ይጠበቅባቸው ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ እዚህ ግድም አንባቢያን ስለአዲስ አበቤዎች መሠረታዊ በእኩልነት የመስተናገድ መብት ሳነሳ፣ ጉዳዩን ከተጋጋለው የከተማዋ ፖለቲካ አንፃር እንዳይመነዝሩብኝ ለማስታወስ እገደዳለሁ፡፡ የከተማ አስተዳደሩን በተመለከተ ከሦስቱም ‹‹የጥግ ፖለቲከኞች›› የተለየ ትርክት ያለኝ በመሆኑ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ያስቀመጠውን ‹‹የልዩ ጥቅም›› አስታራቂ ሐሳብ እቀበላለሁ፡፡ ይህ አማካይ (Golden Mean) ከዜጎች የእኩልነት መብት ጋር አይቃረንም ብዬም አምናለሁ፡፡ በዚህ ጽሑፍ የአዲስ አበባውያኑን ጉዳይ እያነሳሁ ያለሁት ስለዜጎች የእኩልነት መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ለማውሳት እንጂ፣ ስለከተማዋ ባለቤትነት አጀንዳ ለማስያዝ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ጉዳዩን የበለጠ ‹‹ፖለቲሳይዝ›› ላለማድረግ ተብሎ እንጂ፣ ‹‹ሥልጠናውን የወሰደ/ች›› የምትለውን መሥፈርት በደንብ ለመመርመር ‹‹የትኛውን ሥልጠና?›› ብለን ብንጠይቅ ነገሮች የበለጠ ይገልጹልናል፡፡ የመሥፈርቱ ችግር የከፋው ሥልጠና ብሎ ብቻ ባለመቆሙ ነው፡፡ ሥልጠናው የግድ ‹‹አንድ ዓመትና ከዚያ በላይ›› እንዲሆን ነው የተፈለገው፡፡

በሕግ ሙያ በዋነኝነትም ለዓቃብያነ ሕግና ለዳኞች የሚሰጠው ሥልጠና አንደኛው ለአዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሚሰጠው ‹‹የቅድመ ሥራ ሥልጠና›› ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ክህሎትን ለማዳበር በየወቅቱ የሚሰጠውና ‹‹የሥራ ላይ ሥልጠና›› የሚባለው ነው፡፡ ይኸውም አሁን ላይ እንደ ሠልጣኞቹ፣ እንደ ክልሉና እንደ ማሠልጠኛ ማዕከሉ አጠቃላይ ሁኔታ ከሦስት ወራት ጀምሮ ስድስትና ዘጠኝ ወርን ይዞ አንድ ዓመትና ዓመት ከመንፈቅ ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ መሥፈርቱ ‹‹ሥልጠና›› ያለው የትኛውን ሥልጠና ይሆን? ከምን መነሾ? ለምን ዓላማ? አሁን ባለው ሁኔታ የአንድ ዓመትና የዓመት ከመንፈቁን ሥልጠና የሚሰጡት የኦሮሚያና የትግራይ ክልል ማዕከላት ሲሆኑ፣ የአማራና የደቡብ ክልሎች የቅድመ ሥራ ሥልጠና ቆይታ ዘጠኝ ወራት ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት በወጣው የዳኝነት ማስታወቂያ ላይ የተወዳደሩ ቅርቦቼ የወሰዱት ሥልጠና ከአንድ ዓመት ያነሰ በመሆኑ ብቻ፣ ከውድድሩ መቀነሳቸው በ‹‹ሰው ሀብቱ›› በኩል እንደተነገራቸው ግርምት ውስጥ ሆነው ነግረውኛል፡፡

ኧረ በሕገ መንግሥቱ!

በተግባር ነፍስ ዘርቶ ካለመታየቱና የጥቂት ድንጋጌዎቹን መሻሻል ከመሻቴ በቀር፣ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትን ከመግቢያው ጀምሮ በሙሉ ልቤ እቀበለዋለሁ፡፡ ይኸው ሰነድ በአንቀጽ 41 ‹‹የኢኮኖሚ የማኅበራዊና የባህል መብቶች›› በሚለው ርዕስ ሥር ‹‹ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በአገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው፤›› ካለ በኋላ፣ በአንቀጹ ንዑስ ሁለት ሥር ‹‹ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተዳደሪያውን፣ ሥራውንና ሙያውን የመምረጥ መብት አለው፤›› በማለት ይደነግጋል፡፡

በሕገ መንግሥታችን አዲስ አበባ የፌዴራል መንግሥቱ ርዕሰ ከተማ ስለመሆኗ በሚደነግግበት አንቀጽ 49፣ እንዲሁም አንቀፅ 43 እና 39 ሥር ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከራስ በራስ ውድድር በተጓዳኝ በፌዴራል አስተዳደር ውስጥ ‹‹ሚዛናዊ›› ውክልና የማግኘት መብት እንዳለው ተደንግጎም እናገኛለን፡፡ አዲስ አበባ በቂ ሊባል የሚችል ወንበር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተያዘላት ቢሆንም፣ ተወካዮቿ የነዋሪዎቿን መብትና ጥቅም ከማስከበር ይልቅ በየጊዜው ከተፈራረቁ ሹማምንት ጋር በመሞዳሞድ ሲሽኮረመሙ መኖራቸውን መጻፍ አያሻኝም፡፡ ከሁሉም በከፋ ሁኔታ የተሸረሸረው ድንጋጌ ደግሞ በአንቀጽ 25 ውስጥ የሰፈረው የዜጎች በእኩልነት የመታየት መብትን የሚመለከተው ነው፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ሰነዶች ሁሉ መነሻ (Umbrella Principle) የሆነው የእኩልነት መብት በሕገ መንግሥታችን ሰፍሯል ቢባልም፣ አዲስ አበቤዎች ከሌላው እኩል በሆነ ሜዳ ላይ እንዳይወዳደሩና ዘርፉን እንዳይቀላቀሉ የፍትሕ አካላቱ ክልላዊ በራቸውን ከልለዋል፡፡

ዘለግ ላለ ጊዜ ይፋዊ ሥራውን ያቆመው የፌዴራሉ የፍትሕ አካላት ባለሙያዎች ሥልጠና ማዕከልም ቢሆን በትግራይ፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ መሰል ማዕከላት ያሉት ሲሆን፣ በእነዚህ ቅርንጫፎቹ በኩል እንጂ በመሀል አገር መሥሪያ ቤቱ በኩል መሥራት ካቆመ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አዲስ አበባውያኑ የሕግ ምሩቃን ይህንን ‹‹ማዕከል›› የመቀላቀል ተስፋቸው ማዕከሉ በሥራ ላይ በነበረበት ወቅትም አልነበረም፣ አሁንም ያው ነው፡፡ ተጠሪነቱ ለፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሆነውና የጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ‹‹ሪፎርም›› ያልደረሰውን ይህንን ተቋም በተመለከተ የሸገሩ ግርማ ፍሰሐ በዚሁ ‹‹ማንን ምን እንጠይቅልዎ?›› መሰናዶው ላይ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑትን ወ/ሮ ደሚቱ አምቢሳን አናግሮ ነበር፡፡ ሚኒስትሯ ሸፋፍነው ቢያልፉትም የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች መንግሥት እጅግ በጣም ችላ ያለውና ከመዋቅር ጀምሮ በችግር የታጠረ ተቋም ስለመሆኑ ገልጸው ቅሬታቸውን አቅርበውበታል፡፡

ለአዲስ አበባውያኑ የሕግ ተማሪዎች፣ ምሩቃንና የሕግ ባለሙያዎች በፌዴራል ደረጃ ዓቃቤ ሕግና ዳኛ የመሆን ሙያዊ መረጣን ያከበረላቸውና የሚያከብርላቸው የሕግ ተቋም አልነበረም፣ አሁንም የለም፡፡ ይህ መገፋት ሲገርመንና በተለያዩ መድረኮች ‹‹አቤት!›› ስንል ቆይተን ተግባራዊ ምላሽ እየጠበቅን ሳለ ደግሞ፣ እንኳንስና በፌዴራሉ በከተማዋ ፍርድ ቤት ችሎቶች አካባቢም እንዳትታዩ እየተባልን ነው፡፡ እዚህ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊዎችንም መተቸቱ አግባብ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ እኔ የቅድመ ዳኝነትና ዓቃቤ ሕግነት ሥልጠናውን ያገኘሁበት የደቡብ ክልል ሥልጠና ማዕከል ከሐዋሳ ከተማ ለሚላኩለት ሠልጣኞችም ኮታ በየዓመቱ ይይዛል፡፡ የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ግን አዲስ አበቤዎቹ የሕግ ባለሙያዎች (በተለይም የከተማዋ ዓቃቤ ሕጎች) በፌዴራሉ ሥልጠና ማዕከል እንዲስተናገዱ አላደረገም፣ የራሱን ሥልጠና ማዕከልም አላዘጋጀም፡፡

ማንም ሕገ መንግሥቱን ያነበበ ሰው እንደሚረዳው የእኩልነት መብት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንኳ ከማይነኩት መብቶች ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባውያኑ የሕግ ባለሙያዎች በግልጽ ባልታወጀ አዋጅ፣ በይፋ ባልተደነባ ደንብና መመርያ አሰናካይነት መገፋታችን ይበቃል፡፡ ተገፍተን ተገፍተን የደረስንበት ጥግ የፈጠረብን ሕመም ገና አልጠገገም፡፡

‹‹ዳኞቹ›› እንዴት ተገመገሙ? እንዴትስ ተሾሙ?

ጋዜጠኛ ግርማ ፍሰሐ ሲቀጥል፣ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማ ከክልል የመጡ ዳኞችን በምን ዓይነት መሥፈርት ነው የሚገመግመው? የማያውቃቸውን ዳኞች በምን ዓይነት ሁኔታ ነው የሚገመገሙት? ዳኞች ዳኛ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በኅብረተሰቡ ይገመገማሉ ስለሚባል ኅብረተሰቡ የማያውቀውን ዕጩ ዳኛ እንዴት ይገመግማል?›› የሚል ጥያቄ አንስቷል፡፡

የከተማዋ ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በራሱ መንገድ ማጣራትን እንደሚያደርግ በመግለጽ ምላሻቸውን መስጠት የጀመሩት አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹የሥነ ምግባር ማስረጃ ከሚሠራበት ቦታ ያመጣል. . . የሚሠራበት ተቋም ደግሞ የመንግሥትም ይሁን የግል መረጃ በሚሰጥበት ጊዜ መረጃው ተዓማኒነት አለው ተብሎ ግምት ይኖራል፡፡ ምክንያቱም ተቋም ሆኖ የውሸት መረጃ ይሰጣል ብለን አናምንም፣ ይኼ አንደኛው ነው፡፡ ሁለተኛው ስልክ በመደወልም ሆነ  በተለያየ አቅጣጫ መረጃ እናሰባስባለን. . .›› ብለዋል፡፡ በቃ ዳኛ የሚገመገመው እንዲህ ነው አለቀ፡፡ ጋዜጠኛ ግርማ ጥያቄውን አስከተለ፣ ‹‹አቶ ተስፋዬ አሁንም ላቋርጥዎት እናንተ የምትፈልጉዋቸውን ዳኞች በየትኛውም መለኪያ ልትገመግሙት ትችላላችሁ፡፡ ጥያቄው ግን የኅብረተሰቡ መለኪያ፣ የኅብረተሰቡ መስፈሪያ ምንን መነሻ አድርጎ ነው? ምክንያቱም ከክልል የመጡ ዳኞች ኅብረተሰቡን አያውቁትም. . .››

አቶ ተስፋዬ ‹‹የማኅበረሰቡን ግምገማ በተመለከተ. . . ያው መገምገም ያለበት እዚያው የሠራበት ቦታ ስለሆነ የሠራበትን አካባቢ ደግሞ በተለያየ መልኩ ኢንፎርሜሽን በማሰባሰብ ማጣራት የሚደረግ በመሆኑ፣ የዚያን ያህል ሳይጣራ ይመጣል የሚለው አስተሳሰብ ትክክል አይሆንም፤›› በማለት መልስ ያሉትን አስተዛዛቢ መልስ ሰጥተዋል፡፡

እውነታው ግን ዳኞች መገምገም ያለባቸው በሠሩበት አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሚኖሩበት አካባቢና በሚኗኗሩት ኅብረተሰብ ውስጥም ነው፡፡ የሕዝብ አስተያትና የግልጽ አሠራሮች አስፈላጊነትም ታሳቢ የሚያደርገው አብረውት የሚኖሩትን ሰው ሰብዕናና ባህሪ እንደሚያውቁ ቅድመ ግምት ተይዞ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ሕዝብ አዲስ አበባ ውስጥ ስላልኖረና ስላልሠራ ሰው እንዴት ሊያውቅ? እንዴትስ አስተያየት ለመስጠት ሊደፍር ይችላል? ይህ ሥርዓት እኮ ሕዝቡ የሚጮህለት የዳኝነት ነፃነትን ማጎናፀፊያ አንዱ መንገድም ነው፡፡ አሁን ላይ እንደ ችግር እየተነሱ ያሉት የዳኞች ቁጥር ማነስ በራሱ የሚፈጥረው ችግር እንዳለ ሆኖ የፍትሕ ጥራትና መሰል ችግሮች (Personality of the Judges) በዳኝነቱ ዘርፍ ላይ በነበሩትና አሁን ድረስ በዘለቁት ብቃትን ሳይሆን፣ መተካከክን መነሾ ያደረጉ ምልመላዎች ያስከተሏቸው ችግሮችም ናቸው፡፡ እንኳንስና በአቅምና በርቀት የሚገደበው የከተማው አስተዳደር አገራዊ የዳኝነት ሥልጣንና የተሻለ በጀት ያለው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም የሠለጠነ የሚባል አመዛዘን ‹‹Background Screening System›› አልዘረጋም፡፡

ሆኖም የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ላይ በዳኞች አመላመል ላይ የሚታዩ ችግሮች ቢኖሩም የዕጩ ዳኞችን ሙሉ ስም ዝርዝር በፌስቡክ ገጹ ሳይቀር ለሕዝብ አስተያየት አቅርቦ እንደሚያስተች ሳስብ፣ የከተማዋ ፍርድ ቤት ላይ የግልጽነት ችግር መስፈኑን በግልጽ እረዳለሁ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት ላይ የሚሾም አንድ ሰው የግድ አዲስ አበባ ተወልዶ ማደግ ባይጠበቅበትም፣ ኅብረተሰቡ በደንብ የሚያውቀውና ኅብረተሰቡንም በደንብ የሚያውቅ ቢሆን እንደሚመረጥ ለአቶ ተስፋዬ ይጠፋቸዋል ብዬ አላምንም፡፡ አቶ ተስፋዬ ለጋዜጠኛው እንደነገሩት ዓይነት የድጋፍ ደብዳቤ አመዛዘን ብቻ ዳኛ አይመዘንም፡፡

የምንጠይቀው ዳኝነት!

የአዲስ አበባውያኑ የሕግ ባለሙያዎች ጥያቄ ላድበስብስህ ቢሉት እንኳ ለማድበስበስ የማይመች ግልጽ ጥያቄ ነው፡፡ መሠረታዊ የእኩልነት ሰብዓዊ መብታችን ይከበር ከክልል ወንድሞቻችን ጋር በእኩል ሜዳ ላይ እንወዳደር ነው፡፡ አዲስ አበባውያኑ የሕግ ምሩቃን ሥልጠናውን የሚያገኙበት፣ የምስክር ወረቀቱን የሚሰጣቸውና የእኔ የሚላቸው ስለሌለ ብቻ ከዳኝነትና ዓቃቤ ሕግነት ውድድሮች እንዲገለሉ የሚደረግ ከሆነ፣ ጥያቄው ወደ ፖለቲካ እንደሚመነዘር አይጠረጠርም፡፡

የምንጠይቀው ዳኝነት ሁለት ነው፡፡ ይኸውም የፍትሕ ዘርፉን ለመቀላቀል በሕግ ትምህርት መመረቅ ብቻውን በቂ ያልሆነበት አስገዳጅ ሁኔታ ከተፈጠረ፣ ከክልል የፍትሕ አካላት ማሠልጠኛ ማዕከላት የሚወጡ ባለሙያዎችን በፌዴራል ደረጃ በዳኝነትና በዓቃቤ ሕግነትም ሆነ አሁን እንደተስተዋለው በአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች ላይ በዳኝነት የሚመደቡ ከሆነ፣ እንደ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ በየክልሉ የሚሰጡ የሥልጠና መርሐ ግብሮች ላይ አዲስ አበባውያኑ ተመራቂ የሕግ ተማሪዎች የሚካተቱበት የሕግና የፖለቲካ አግባብ መኖር አለበት፡፡

በፖለቲካዊ የበጀት ሁኔታዎች ይህ የማይቻል መስሎ ከታየ ደግሞ የፌዴራሉ የፍትሕ አካላት ባለሙያዎች ሥልጠና ማዕከልን በብቁ የሰው ኃይል አደርጅቶ፣ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን በእኩል የሚበቃና እኩልም የሚያበቃ አገራዊ የሕግ ባለሙያዎች ማዕከል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ሲባል ታዲያ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮና ፍርድ ቤቶችም የተለየ ኮታ እንዲይዝ በማድረግ፣ የእስካሁኑን የመገፋት በደል በሥራ ላይ ሥልጠና በማካካስም ነው፡፡ ሥልጠና የገፊነት መሥፈርት ሆኖ በዜጎች መካከል የሞራልም ሆነ የኢኮኖሚ ልዩነት መፍጠሪያ መሆን የለበትም፡፡ አዲስ አበቤዎቹ የሕግ ተማሪዎችም ዓቃቤ ሕግና ዳኛ የመሆንን ህልም ይሰንቃሉና ከዚህ የሙያ ምርጫ ማዕድ ተገፍተው ሲወድቁ ማየትን አንሻም፡፡ ከዚህ በላይ ያቀረብኩት የይግባኝ አቤቱታ በእውነትና ስለእውነት የቀረበ መሆኑን በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ-92 መሠረት በቃለ መሃላ እያረጋገጥኩ፣ የቅሬታውን መፈቻ ቀን በናፍቆት እጠብቃለሁ፣ አይራቅ፡፡ ሰላም ለእናንተ ይሁን!

ከአዘጋጁ-፡ ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...