Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉዝግመተ ለውጥና ብሔርተኝነት

ዝግመተ ለውጥና ብሔርተኝነት

ቀን:

በሺፈራው ሉሉና በእንግዳሸት ቡናሬ

የ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ዓለምን ያናወጡ የሳይንስና የፖለቲካ  ፍልስፍናዎች የተከሰቱበት ነው፡፡ ማርክስና ፍሬድሪክ ኤንግልስ እ.ኤ.አ. በ1848 የኮሙዩኒስት ማኒፌስቶ (The Communist Manifesto) የተባለውን በእንግሊዝ ለንደን ከተማ አወጡ፡፡ በ1859 የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ፍልስፍና The Origin of Species” (ዘ ኦሪጂን ኦፍ ሰፒሺስ) ታትም የወጣ ሲሆን፣ ከስምንት ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ. በ1867 የማርክስና የኤንግልስ የማርክሲዝም ፍልስፍናን የያዘው ካፒታል የተባለው መጽሐፍ ታትሞ ወጣ፡፡ በመቀጠልም ሀርበርት ስፔንሰር (Herbert Spencer, እ.ኤ.አ. 1874) ሶሻል ዳርዊኒዝም (Social Darwinism) የተባለውን የፖለቲካ ፍልስፍና እ.ኤ.አ. በ1952 አቅርቦት ከነበረው ተስማሚው/አሸናፊው ይኖራል/ይቀጥላል (The Survival of the Fittest) የሚለውን አስተሳሰብ ከዳርዊን ፍልስፍና ጋር በማያያዝ አቅርቧል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1863 ኤርነስት ሬነን (Ernest Renan) የእየሱስ ሕይወት (The Life of Jesus) የተባለውን መጽሐፍ አሳተመ፡፡ ይህ መጽሐፍ የክርሰቶስን መለኮታዊነት የሚክድና/የሚቃወም መጽሐፍ በመሆኑ ለዳርዊነስቶች፣ ለማርክሲስቶች፣ ለሶሻል ዳርዊኒስቶችና ተከታዮቻቸው እግዚአብሔር የለም ለሚለው አስተሳሰባቸው ተጨማሪ ኃይል ሊሆናቸው ችሏል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም እስካሁን በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ሰዎች በእግዚአብሔር እንዳያምኑና እምነት የለሽ ከሃዲያን እንዲሆኑ ምክንያት ሆኗል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሶሻል ዳርዊኒዝም አስተሳሰብ የዝግመተ ለውጥ ፍልስፍናን ለማኅበራዊ ዕድገትም መሠረታዊ መርህ አድርጎ የሚወስድ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ሌላው የተነሳው የፖለቲካ አስተሳሰብ ሶሻል ዴሞክራሲ (Social Democracy) የተባለው ነው፡፡ የዚህ የፖለቲካ አስተሳሰብ መነሻው ማርክሲዝም ሲሆን፣ የሶሻሊስት የፖለቲካ ማኅበረሰብ በአብዮት ሳይሆን በሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ (Reform) ማምጣት ይቻላል በሚሉ ፖለቲከኞች የተጀመረ ሲሆን፣ በመጨረሻም የሶሻሊስት አስተሳሳብ በሒደት ጠፍቶ  ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍትሕን በሊበራል ዴሞክራሲና  በካፒታሊስት ኢኮኖሚ ውስጥ ማምጣት ይቻላል ወደሚለው ያደገ ነው፡፡ ይህንንም ለማምጣት ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ኢኮኖሚውን በመቆጣጠር ካፒታሊዝም በራሱ ወደተሻለ ዴሞክራሲ እንዲያድግ ማድረግ ነው የሚል ነው፡፡ 

የሶሻል ዳርዊኒዝም (Social Darwinism) አስተሳሰብ መሠረቱ የዝግመተ ለውጥ ፍልስፍና ሲሆን፣ የኅብረተሰብ ዕድገት በማያቋርጥ ትግል ውስጥ ነው፡፡ ሁልጊዜ አሸናፊው ወደላቀ የኅብረተሰብ ዕድገትና ወደላቀ የሰው ዘር ሲያድግ (The Survival of the Fittest) ደካማውና የማያስፈልገው ይጠፋል፡፡ ለማኅበረሰብ ዕድገት አሸናፊው ወደላቀ የኅብረተሰብ ክፍል እንዲያድግ ጦርነት አስፈላጊ መሆኑን ያምናል፡፡

በዚህ ፍልስፍና መሠረት ጥቁሮች፣ በእስያና በላቲን አሜሪካ የሚገኙ ማኅበረሰቦች ዝቅተኛ የዝግመተ ለውጥ ሒደት ላይ ያሉና ዝቅተኛ የሰው ክፍል እንደሆኑ ይሰብካል፡፡ የሶሻል ዳርዊኒዝም ፍልስፍናን የአውሮፓ አገሮች በወቅቱ ሌሎች ያልሠለጠኑ የተባሉ አገሮችን አፍሪካን፣ እስያንና ላቲን አሜሪካን በቅኝ ግዛት ለመግዛት ጉልበት ሆኗቸዋል፡፡ በቅኝ ግዛት ሥር የወደቁ አገሮች ሕዝቦች የዝቅተኛ የሰው ክፍል ተደርገው ተቆጥረዋል፣ ብዙዎች ተገድለዋል፣ ከነጭ ተለይተው በተመደበላቸው ቦታ ብቻ እንዲኖሩ፣ ነጭ የገባበት እንዳይገቡ፣ ከነጭ ጋር እንዳይጋቡ ተደርገውና ተገልለው እንደ እንስሳ ተቆጥረው እንዲኖሩ ተደርገዋል፡፡ የጣሊያን መንግሥትም ኢትዮጵያን ለመውረር የሞከረውና በ1888 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1896) በዓድዋ ጦርነት ተሸንፎ የወጣው በዚህ ወቅት ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ቢሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ የዚህ ፍልስፍና ሰለባ በሆነ ነበር፡፡ የዚህን ፍልስፍና ገፈት የቀመሱት ጣሊያን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ በያዛት በኤርትራ የሚገኙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ናቸው፡፡ የአስመራ ከተማ የዚህ አስከፊ ታሪክ ምስክር ናት፡፡ ሌሎች የአፍሪካ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዚህ ፍልስፍና ምክንያት ታላቅ መከራን ተቀብለዋል፡፡

የ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽና የ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በእነዚህ አስተሳሰቦች ዓለም የተወጠረችበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የአንደኛው ዓለም ጦርነት በስላቭ ብሔረተኞች (Extreme Slave Nationalists) ምክንያት፣ የሩሲያ አብዮት እንዲሁም የናዚ ጀርመን መነሳት፣ የጣሊያን ፋሺዝምና የሁለተኛው ዓለም ጦርነት መነሳት ምክንያት ሆኗል፡፡

ሶሻል ዳርዊኒዝም አስተሳሰብ አውሮፓን በማመሱ በሕዝቦች መካከል ፍርኃትንና አለመተማመንን ስለፈጠረ የዘውግ (National) ጥያቄ እየጎላ መምጣት ጀመረ፡፡ በወቅቱ አውሮፓ በኢንዱስትሪ አብዮት ውስጥ የነበረች ሲሆን፣ በኢንዱስትሪው ዕድገት ምክንያት ከፍተኛ የሰው ፍልሰት ከገጠር ወደ ከተማ የነበረበትና በአንድ በኩል የዘውግ የበላይነትና የበታችነት ውጥረት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፍልሰትና የተለያዩ ዘውጎች የተደባለቁበት/ውህደት የፈጠሩበት ጊዜ ነበር፡፡  በአንፃሩ ደግሞ የሶሻል ዳርዊኒዝም  የፖለቲካ አስተሳሰብ የሰውን የበላይና የበታችነት የሚሰብክበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ውጥንቅጥ ወቅት የተለያዩ ማኅበረሰብ ራስን የመጠበቅና መከላከል ወይም አሸንፎ ወደ ላቀ ደረጃ መድረስ አንገብጋቢ ጥያቄ ነበር፡፡ በመሆኑም አንዱን ዘውግ ከሌላው መለየት ደግሞ ሌላ ችግር ነበር፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ዘውግ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለማስረዳትና ለመለየት እንዲመች ከሞከሩት አንዱ እ.ኤ.አ. በ1881 በኦስትሪያ (Austria Viena) የተወለደው ኦቶ ባወር (Otto Bauer) የተባለው እ.ኤ.አ. በ1907 የዘውግ ጥያቄና ሶሻል ዴሞክራሲ (The Question of Nationalities and Social Democracy) የተባለውን ጽሑፍ አወጣ፡፡ ይህንን ተከትሎ ጆሴፍ ስታሊን (Joseph Stalin) የኦቶ ባወርን ሐሳብ መሠረት በማድረግ በ1913 እ.ኤ.አ ማርኪስዝምና የዘውግ ጥያቄ (Marxism and the National Question) የተባለውን ጽሑፍ አወጣ፡፡

ዘውግ (Nationalities) የሚለውን ትርጉም ለመስጠት ባዎርና ስታሊን ብዙ ደክመው ነበር፡፡ ይኼንንም ያስገደዳቸው በወቅቱ በአውሮፓ የነበረው ውጥንቅጥ ሁኔታ በሕዝብ መካከል እያስነሳ ያለውን ችግር በፍልስፍና በማስደገፍ መፍትሔ ሊመጣ ይችላል በሚል ነበር፡፡ ስታሊን ማርክሲስት ሲሆን ባወር ግን ሶሻል ዴሞክራት ነው፡፡ የአውሮፓ ሁኔታ የሁለቱንም የፖለቲካ አስተሳሰብ ያሳሰበ ነበር፡፡

ጆሴፍ ስታሊን የኦቶ ባወርን የዘውግ ፍልስፍና በመተቸት የራሱን ፍልስፍና አቀረበ፡፡ የስታሊንንም ሆነ የኦቶ ባወርን የዘውግ ፍልስፍና በአውሮፓ ለመተግበር የተደረገው ሙከራ ያመጣው ነገር መተላለቅ በመሆኑ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፡፡ በአጠቃላይ የዘውግ ፍልስፍና መሠረቱ በዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ፍልስፍናና  በሶሻል ዳርዊኒዝም ፍልስፍና ምክንያት በአውሮፓ የተፈጠረውን ቀውስ ይፈታል በሚል ነበር፡፡ ነገር ግን ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖ በዘውግ መካከል የበለጠ ችግር ከመፍጠር በስተቀር ያመጣው መፍትሔ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም የዘውግ ፍልስፍና  መሠረቱ ሰዎችን ከፋፍሎ ለመግዛት በሶሻል ዳርዊኒዝም ፖለቲካ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ እንጂ አቶ ስብስቤ ዓለምነህ እንደሚያስገነዝበው የሌለና የአዕምሮ ቅዠት በመሆኑ ችግር ሊፈታ አይችልም፡፡

ይህ ፍልስፍና ከኢትዮጵያ ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ የሶሻል ዳርዊኒዝም  ፍልስፍና ነበር ወይ ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በወቅቱ ይህ ዓይነት ፍልስፍና ለመኖሩ እንኳን በኢትየጵያዊያን ዘንድ የሚታወቅ አይመስለኝም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳች የሚያገናኛቸው ታሪካዊም ሆነ ማኅበራዊ መሠረት በሌለበት ሁኔታ የጆሴፍ ስታሊን ፍልስፍናን አምጥተን ሕዝብ ያልሆነውን ሆነሀል፣ እኛ እናውቅልሀለን ወይም ወክለንሀል ብሎ ሕዝብን ማስጨነቅ አዕምሮ ላለውና ከሚያስብ ትወልድ የሚጠበቅ አልነበረም፡፡ እንዲያው ችግሩ እንኳን ነበር ብለን ብናስብ ለእኛ መፍትሔ የሚሆነው የአውሮፓው የጆሴፍ ስታሊን ፍልስፍና ነው ወይ? እኛ በአፍሪካ የምንኖር የራሳችን ታሪክ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴትና ግንኙነት፣ የራሳችን የሆነ ፍልስፍናና የኑሮ ዘይቤ ያለን ነን፡፡ እኛ በአውሮፓ በሽታ አልታመምንም፣ ከታመምንም በሽታችን የምሥራቅ አፍሪካ በሽታ ነው የሚሆነው፡፡ ማነው የጆሴፍ ስታሊን ፍልስፍና ለኢትዮጵያ ያውም ላልታመመው ማኅበረሰብ መድኃኒት አድርጎ የማዘዝ ሥልጣን ያለው? ላልታመመ መድኃኒት መስጠት ደግሞ መርዝ እንደ መስጠት ይቆጠራል፡፡

ከ1928 ዓ.ም. እስከ 1933 ዓ.ም ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በተቆጣጠረችበት ወቅት፣ በሶሻል ዳርዊኒዝም የዘውግ ፖለቲካ አገሪቱን ከፋፍላ ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ጥረት አድርጋ ነበር፡፡ ሆኖም በአገሪቱ በነበረው ጠንካራ ታሪካዊና ማኅበራዊ ትስስር ምክንያት ሳይሳካ ቢቀርም፣ አሁንም ቢሆን ያን ጊዜ የተዘራው መርዝ ወጣቶች በ1960ዎቹ ባለማወቅ ካመጡት የዘውግ አስተሳሰብ ውስጥ ነፍስ በመዝራት አሁን አገሪቱን በማመስ ላይ ይገኛል፡፡ የብሔር ፖለቲከኞችና የብሔር ሊሂቃን ተብዬዎች ይህንን ፋሽስታዊ የሶሻል ዳርዊኒዝም ፍልስፍና በመሸከም በሕዝብ ላይ በመጫን ልክ ፋሽስት ጣሊያን ከ1928 ዓ.ም. እስከ 1933 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተገበረችውን በከፋ ሁኔታ በአሁኑ ዘመን በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡

እኛ የአቶ እንዳለው ልጆች የእነሱ ፍልስፍና ተገዢ በመሆን ይኼው ለአራት አሥርተ ዓመታት ስንታመስ እንኖራለን፡፡ ማነው የባወር ወይም የስታሊን ሐሳብ ትክክል ነውና ዓለም ሁሉ ለዚህ እንዲገዛ አዋጅ ያወጣው?

ብሔረተኞች/ዘውገኞች ለጥቅማቸው ሲሉ ዋለልኝ መኮንን ከስታሊን ፍልስፍና ገልብጦ ያቀረበውን ጽሑፍ ወይም ሌላ ሰው የጻፈለትን/አንዳንድ ሰዎች ስለሚገምቱ ነው/ይጠቅሳሉ፡፡ ለመሆኑ ዋለልኝ በወቅቱ ስለኢትዮጵያ ወይም ስለአፍሪካ ታሪክ በቂ እውቀት፣ የሥራና የሕይወት ተሞክሮ ነበረው ወይ? የኢትዮጵያን ሕዝብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በቅጡ ሊረዳበት የሚችልበት የዕድሜ፣ የሕይወትና የሥራ ተሞክሮ ነበረው ወይ? መልሱ አልነበረውም ነው፡፡ አንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ወጣት የሌላ አገር ችግር ፍልስፍና ያውም የአውሮፓ/የአፍሪካ እንኳን ቢሆን ጥሩ/ገልብጦ ስለጻፈ የኢትዮጵያ ችግር ባልሆነበት ችግር መፍቻ ብሎ በመውሰድ (ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንደሚባለው) የዘውግ ፖለቲከኞች የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የተጠቀሙበት ነበር እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ አይደለም፡፡

ለዚህም እንደ ማስረጃ ከሆኑት አንዱ የኮሌጅ ቀን ግጥሞችና ሕያው ድምፆች፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የወርቅ ኢዩቤልዩ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዲን ጽሕፈት ቤት የተዘጋጀ መጻሕፍት የወቅቱ የብስለት መገለጫ ነበርና! አንድም ቦታ የዋለልኝ መኮንን አሻራን የሚያሳይ ጽሑፍ አልታየም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዋለልኝ መኮንን ከስታሊን ፍልስፍና ገልብጦ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሳያገናዝብ ያቀረበውን የብሔር ጥያቄ  (The National Question) ጽሑፍ  ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በልደት አዳራሽ ለጀማሪ ተማሪዎች የገለጻ መስጫ ፕሮግራም ላይ ያለ ስምምነትና ብቃት ያነበበው እንደነበርና የዘውግ ፖለቲከኞች መጠቀሚያ እንዳደረጉት የታሪክ ጸሐፍት ይመሰክራሉ (ገጽ 198 ባህሩ ዘውዴ)፡፡ የብሔርን ጥያቄ አመጡ ተብዬዎችና አቅራቢዎች ትክክለኛውን ትርጉም ያኔም የገለጸም፣ የጠየቀም  የለም፡፡ አሁንም ድረስ ትርጉም አልባ ግን የአንድነት ችግር መንስኤ ሆኗል! የሕጎች ሁሉ የበላይና መሠረት በሆነው በሕገ መንግሥታችንም (የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት) ውስጥ ብሔሮች/ብሔረሰቦች/ሕዝቦች የሚሉ ትርጉም የሌላቸው ቃላት ወይም በትርጓሜ አንቀጽ ውስጥ እንኳን ያልተተረጎሙ ትርጉም አልባ በሆኑ ሐሳቦች አገር ለመምራት እንፍጨረጨራለን፡፡

የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት (ትሕነአድ/ተሓህት) በ1968 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ብሔራዊ ተፅዕኖ በሚለው ርዕስ ይህንን የተሳሳተ ትምህርት በመውሰድ፣ አንዱ ሕዝብ የሌላው ጨቋኝ እንደሆነና መፍትሔው መገነጣጠል እንደሆነ ጽፎት እናገኛለን፡፡ ለዚህም ሐሳብ ብዙ ሰዎች ባለማወቅ ደማቸውን አፍሰውበታል፡፡ እዚህ ላይ ልንገነዘበው የሚገባው ነገር ቢኖር፣ አንድን ነገር ከመደገፍም ወይም ከመቃወም በፊት ከሥረ መሠረቱ የመመርመር ባህል ሊኖረን ይገባል፡፡ ፖለቲከኞች ይህንን ፋሽስታዊ አስተሳሰብ አሁንም ቢሆን እየተጠቀሙ ያሉት፣ ይህንን ነገሮችን የመጠየቅና የመመርመር ድክመታችንና አለማወቃችንን ነው፡፡

ሌላው ችግር ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትውልዱን ለማስተማር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ በሬዲዮ የቀረቡ ንግግሮች በመጽሐፍ መልክ በታተመው ጽሑፋቸው በዘመናዊት ኢትዮጵያ ስለትምህርት በተለይ ያሰቡና በሥራም ያለመጠን የደከሙ ታላቁ ንጉሠ ነገሥታችን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡ በንጉሠ ነገሥት ክብርና በቤተሰብ ደስታ ለ30 ዓመት ያህል የኖሩበትን ቤተ መንግሥት ለከፍተኛ ትምህርት መደብር ይሆን ዘንድ ወስነው የመጀመሪያውን ዩኒቨርሲቲ መሠረቱ፡፡ ይህ ጽሑፍ ለዚህ ንጉሣዊ ቸርነት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ የተዘጋጀ ነው ይሉናል፡፡ በተጨማሪም ትልቁ ፈላስፋ ፕላቶን እንዳለው ሰው ትክክለኛውን ትምህርት ያገኘ እንደሆነ ለስላሳና (ኖብል) እግዜርን የሚመስል ፍጥረት ነው፡፡ ትምህርት ያላገኘ እንደሆነ ግን በምድር ላይ ካሉት አራዊት ሁሉ የባሰ ነው፡፡ ጥርጥር የሌለው ነገር ነው፡፡

ዘውገኛ የሆነው ትውልድም በዚህ ዘመን የመነጨ ነው፡፡ ትውልዱ እንዲማር ንጉሡ ሕዝቡን በከፍተኛ ደረጃ በተለያየ መንገድ ቀስቅሰዋል፡፡ አንጀሎ ዴል ቦካ ባዘጋጀው የንጉሡ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ላይ ያለው የስታትስቲክስ መረጃ እንደሚያሳየው የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥርን እ.ኤ.አ. በ1948 ከ100,000 እ.ኤ.አ. በ1960  ወደ 400,000፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥርን እ.ኤ.አ. በ1948 ከ4,000  እ.ኤ.አ. በ1960 ወደ 33,000፣ በዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ቁጥርን እ.ኤ.አ. 1950 ከ72 እ.ኤ.አ. በ1960 ወደ 940 እ.ኤ.አ. በ1968 ወደ 4,250 ማደጉንና ንጉሡ ትምህርትን በአገሪቱ ለማስፋፋት ያደረጉትን ከፍተኛ ጥረት ይገልጻል (ዘ ንጉሥ ገጽ 250) ፡፡

ንጉሡ የተማረ ሰው በኅብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታን እንዲያገኝ አድርገዋል፡፡ በዘመኑ ኅብረተሰቡ ለተማረ ሰው የነበረው ከበሬታና አድናቆት ከፍተኛ ነበር፡፡ የተማረ ሰው የተናገረውን ሁሉ ሳይመረምሩ እንደ እውነት አድርጎ የመቀበል ባህል ዳብሮ ነበር፡፡ ከዚያም አልፎ የተማረ ይግደለኝ የሚል አባባል ዳብሮ ነበር፡፡ ጎን ለጎን የተማረው ክፍል ራሱን ወደ ከፍታ የሰቀለበት ወቅት ነበር፡፡ ትንሽ እውቀት አደገኛ መሆኑን የተገነዘበ አልነበረም፡፡ እውቀት ማለት ደግሞ የቀለም እውቀት ብቻ አይደለም፡፡ ከአካባቢ፣ ከማኅበረሰቡ፣ ከታሪክ፣ ከሥራ፣ ከዕድሜ ተሞክሮና ነገሮችን የመመርመር ባህል ካልታከለበት በቀለም እውቀት ብቻ ሙሉ ሰው መሆን አይቻልም፡፡ በወቅቱ የነበረው ተማረ የተባለው ክፍል የቀለም እውቀትን ብቻ የሁሉ ነገር አዋቂ እንዳደረገው ያስብ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የትምህርት ሥርዓቱ በዋነኛነት የተቀረፀው በምዕራባዊያን መሆኑና የመጀመሪያዎቹ መምህራን በከፊል ከእነዚህ አገሮች በመሆናቸው የራሳችንን ባህል፣ ታሪክና እሴት ላይ ከማተኮር ይልቅ በምዕራባዊያን ባህልና ሥልጣኔ ላይ ትኩረት ያደረገ፣ ይህንንም የሚመኝና ራሱን ከዜጎቹ ከፍ አድርጎ የሚመለከት ተማሪ ማፍራቱና ኅብረተሰቡም ለተማረው ክፍል የሰጠው የከፍታ ሥፍራ ተሰሚነት ስላገኘለት የአውሮፓን ፋሽስታዊ ፍልስፍና አምጥቶ በአገሪቱ ላይ ሲጭን አጨብጭበን ተቀበልን እንጂ አይሆንም ያሉ ጥቂቶች ነበሩ፡፡ እነሱንም የተለያየ ስያሜ እየለጠፍን አጠፋናቸው፡፡ ይህ ታዲያ ለዘውገኞች ታላቅ የመፈልፈያ መሠረት ፈጠረላቸው፡፡

በመጀመሪያ መረዳት የሚኖርብን የዘውግ/ብሔርተኝነት/ዘረኝነት አስተሳሰብ መሠረቱ የዝግመተ ለውጥ አስተሳሰብ መሆኑን ነው፡፡ የዝግመተ ለውጥ አስተሳሰብን ወደ ማኅበረሰብ ዕድገት በማምጣት ሶሻል ዳርዊኒዝም የተባለው የፖለቲካ አስተሳሰብ ፍልስፍና እንዲከሰት ሆኗል፡፡ በሶሻል ዳርዊኒዝም ፍልስፍና የማኅበረሰብ ዕድገት (ልክ እንደ ዳርዊን የተፈጥሮ ዝግመተ ለውጥ) ጫካ ከሚኖር ሰው፣ የጋሪዮሽ፣ የባሪያ፣ የፊውዳል፣ ካፒታሊዝም ሥርዓት ድረስ የሚያድግ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ በሚኖረው የመኖር ትግል፣ ኃይለኛው ወይም ብቃት ያለው የሰው ክፍል እያሸነፈ ደካማው እየጠፋ፣ በእጅጉ የላቀ የሰው ክፍልና የዚህ ማኅበረሰብ እየተፈጠረ እንደሚመጣ ያምናል፡፡ ስለዚህ ነው በእስያ፣ በአፍሪካና፣ በላቲን አሜሪካ የሚገኙ ሕዝቦች እንደ ዝቅተኛ የሰው ክፍል፣ ወይም ዝግመተ ለውጣቸው ከፍተኛ ደረጃ ያልደረሰ ተብለው ሲፈረጁ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ እንደ ከፍተኛ የሰው ክፍል የተፈረጁት፡፡ ይህ አስተሳሰብ ለቅኝ ገዥዎች ጉልበትን የሰጠ ሲሆን፣ በተግባርም በአፍሪካና በእስያ ፈጽመውታል፡፡

ይህ አስተሳሰብ አውሮፓንም ያመሰ ነበር፡፡ በአውሮፓ በተለያዩ ዘውጎች/ብሔር/ጎሳ መካከል የላቀ የሰው ክፍልን ለማረጋገጥ ትግል ውስጥ እንዲገቡ ያደረገ ሲሆን፣ በኋላም የናዚ ጀርመን ሂትለር የአሪያን ዘውግ/ብሔር/ጎሳ ከሁሉ የላቀ ስለሆነ ሌሎች ለዚህ ዘውግ/ብሔር/ጎሳ መገዛት አለባቸው፣ ወይም መጥፋት አለባቸው በማለት በመነሳቱ ለብዙ ሚሊዮን ሕዝብ ሞትና ስደት ምክንያት ሆኗል፡፡ በሰው ልጅ ላይ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ሰቆቃ ተፈጽሞበታል፡፡ የፋሽስት ኢጣሊያም ይህንን ፍልስፍና በመደገፍ ከናዚ ጀርመን ጋር ባደረገው ኅብረት ከ1928 ዓ.ም. እስከ 1933 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1935-1941) ኢትዮጵያን በመውረር ከፍተኛ ዘግናኝ ጭፍጨፋዎችን ያካሄደው፡፡ ፋሽስት ኢጣሊያም የዘውግ/የጎሳ አስተሳሰብን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግና ሕዝቡን ከፋፍሎ ለመግዛት ያደረገው ሙከራ በሕዝቡ ዘንድ በነበረው ጠንካራ የአንድነት መሠረት ሊሳካለት አልቻለም፡፡

የዘውግ/ብሔር/ጎሳ አስተሳሰብ

  1. የዘውግ/ብሔር/ጎሳ አስተሳሰብ በአውሮፓ የሶሻል ዳርዊኒዝም የፖለቲካ ፍልስፍና ተከትሎ የመጣና ዘውግን/ብሔር/ጎሳ ለመከፋፈልና ትርጉም ለመስጠት ሲባል የተጀመረ ነው፣
  2. የዘውግ ፍልስፍና ባመጣው ልዩነት፣ ፍጥጫና የእርስ በርስ መተላለቅ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፡፡

ይህንን የከሰረ የክፋት ትምህርት ወደ አገራችን በማምጣት ማኅበራዊ መዋቅሩ ጠንካራና፣ በሺዎች ዘመናት የተገነባውን የእርስ በርስ ግንኙነት በማፍረስ ላይ እንገኛለን፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የዘውግ/ብሔር/ጎሳ አስተሳሰብ መሠረቱ ዝግመተ ለውጥ ነው፡፡ ይህም መጨረሻው አንዱ ዘውግ ከሌላው የተሻለ መሆኑን ወይም የላቀ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓት የተጠቀመው ይኼንኑ የሶሻል ዳርዊኒዝም የፖለቲካ ፍልስፍና ተግባራዊ በማድረግ ነው፡፡ የኢትዮጵያም የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲከኞች ሊያረጋግጡልን የሚፈልጉት የሶሻል ዳርዊኒዝም የፖለቲካ ፍልስፍና ነው፡፡ አንዳንዶች የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲከኞች ከወርቅ ሕዝብ ተፈጠርን ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ኢትዮጵያን የፈጠሩ ራሳቸውን ሲያደርጉ ሌሎች ደግሞ የኢትዮጵያ መሠረት ሲሆኑ፣ ሌሎች ደግሞ እንደ ዝቀተኛ ተቆጠርን ሲሉ ይሰማል፡፡ ይኼ ሁሉ የሚሆነው ካለማወቅ ወይም አውቆ ፍልስፍናውን ለግል ጥቅም ከማዋል አኳያ ነው፡፡

የተሻለ ዘውገኛ ብሔረተኝነት

በአገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት (2011 ዓ.ም) ወደ 107 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የዘውግ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ አስተሳሰባቸው በሰው ልጅ እኩልነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲከኞች ትልቁ ችግራቸውና የጋራ አስተሳሰባቸው ራሳቸውን ያልወከላቸውን ሕዝብ ተወካይ አድርገው መሾማቸውና የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ማኅበረሰቡን በተለያዩ የበላይነት ወይም የዝቅተኝነት አስተሳሰብ መቀስቀሳቸው ነው፡፡

 በዘጠኙም ክልል ከአንድ በላይ የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲከኞች አሉ፡፡ ሁሉም ልክ ከ1966 እስከ 1972 ዓ.ም. በአብዮቱ መጀመሪያ እንደነበሩት ፓርቲዎች በወዛደር ተወካይነት እንደተላለቁት፣ አሁንም የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ተወካይ እኔ ነኝ በሚል የእርስ በርስ ሽኩቻና በሴራ ፖለቲካ በመጠላለፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ ዋነኛ ዓላማው የላቀ የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ክፍል ማረጋገጥ ነው፡፡ ማለትም አንዱ ዘውግ ከሌላው በኢኮኖሚ የበለፀገ፣ በአስተሳሰብ የነጠረ፣ ኃይለኛና አስፈሪ፣ የነጠረ ደም ያለው፣ ወዘተ… ማረጋገጥ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ የራሴ ዘውግ/ብሔር/ጎሳ ብሎ ከሚቆጠረው ውጭ ያለውን ኅብረተሰብ እንደ ሰው የማይቆጥር ዜጋ ይፈጥራል፡፡ አገር የሚባል ነገር ለዘውግ አስተሳሰብ ሥጋት ይሆንበታል፡፡ ምክንያቱም ከአሱ የተሻለ ወይም እኩል የሆነ ሌላ ዘውግ ማየት ስለማይፈልግ ከዚህም የተነሳ ጨካኝ፣ ለሰው ፍቅር የሌለው ለእምነቱ የማይገዛ ማኅበረሰብ ይገነባል፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የዝግመተ ለውጥ ሐሳብ የዲያብሎስ ስለሆነ በዚህ መሠረት ላይ የተገነባው የሶሻል ዳርዊኒዝም የፖለቲካ ፍልስፍናና የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ ጨካኝ፣ ነፍስ ገዳይ፣ ፍቅር የሌለው የራሱን ብቻ የሚያስብ ትውልድ የሚፈጥረው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሁሉ የክፉው ሐሳቦች ናቸው፡፡

‹‹እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አዕምሮ አሳልፎ ሰጣቸው፣ ዓመፃ ሁሉ ግፍ መመኘት ክፋት ሞላባቸው፣ ቅናትን፣ ነፍስ መግደልን፣ ክርክርን፣ ተንኰልን፣ ክፉ ጠባይን ተሞሉ፣ የሚያሾከሹኩ፣ ሐሜተኞች፣ አምላክን የሚጠሉ፣ የሚያንገላቱ፣ ትዕቢተኞች፣ ትምክህተኞች፣ ክፋትን የሚፈላለጉ፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያስተውሉ፣ ውል የሚያፈርሱ፣ ፍቅር የሌላቸው፣ ምሕረት ያጡ ናቸው፤›› (ሮሜ፣ ም፣ 1 ፤ ቁ፣ 28-31)።

በቅርቡ በኢትዮጵያ የተደረጉ የጭካኔ ሥራዎችን አንዳንድ ሰዎች፣ “ሰይጣንም ይኼንን የሚሠራ አይመስለንም፣ እኛ የተለያዩ የጭካኔ ድርጊቶችን ለሰይጣን እያስተማርን የምንገኝ ይመስላል፤” በማለት ሲገልጹ ይሰማል፡፡ ይህ አባባል ጥልቅ መልዕክትን የያዘ ነው፡፡ የሶሻል ዳርዊኒዝም የፖለቲካ ፍልስፍናና የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ ምን ያህል ክፉ እንድንሠራ እንደሚያደርገን ያስረዳል፡፡

ከላይ እንደተገለጸው በአገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት (2011 ዓ.ም) ወደ 107 የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉ ይነገራል፡፡ ከዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ በመሆኑም በአማካይ በአንድ ክልል አሥር የሚሆኑ የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች አሉ ማለት ይቻላል፡፡

በአንድ ክልል አሥር የሚሆኑ የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ቢኖሩ ሁሉም ለዚያ ወከልን ለሚሉት ዘውግ የተሻለ ዘውገኛ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ስለዚህ በዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የሚኖረው ውድድር የተሻለ ዘውገኝነትን ማረጋገጥ ነው፡፡ በመሆኑም የሚኖረው መወዳደሪያ ወከልን ለሚሉት ዘውግ፣ የሱን ከሌላው ዘውግ የበለጠ መሆኑን በኢኮኖሚ የተሻለ፣ በአስተሳሰቡ የላቀ፣ በጀግንነቱ የላቀ፣ የነጠረ ደም፣ የላቀ የሰው ክፍል መሆኑን የማረጋገጥ ፉክክር ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ሌላውን ዘውግ/ብሔር/ጎሳ በመጥላት ከተፎካካሪው የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች የበለጠ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ በአንድ ክልል የሚገኝ የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች የተሻለ ሶሻል ዳርዊኒስት/አፓርታይድስት መሆኑን ማረጋገጥ የግድ ይሆናል፡፡ የተሻለ የዘውግ ወኪል ለመሆን ከሌላው የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች የተሻለ ዘውገኛ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡

በዚህ ዓይነት ከሁሉም የዘውግ/ክልል 9 የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ተመረጡ እንበል፡፡ የሁሉም አላማ ወከልን የሚሉትን ዘውግ የበላይነት ማረጋገጥ ይሆናል፡፡ በመሆኑም አገሪቱ በዘውግ የበላይነት (ሶሻል ዳርዊኒስት/አፓርታይዲስት) ሽኩቻ ትናጣለች ማለት ነው፡፡ በአሁኑ አካሄዳችን በአገሪቱ ወደ 86 የሚጠጉ  ዘውግ/ብሔር/ጎሳ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሁሉ የዘውግ ክልል/አስተዳደር እየጠየቁ እንደሆነ ይነገራል፡፡ 86 የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ከ86 የዘውግ/ብሔር/ጎሳ አካባቢ ቢመረጡ እያንዳንዱ ድርጅት የራሱን ዘውግ የበላይነት ለማረጋገጥ በሚያደርገው ንትርክ የሚፈጠረውን ጥፋት መገመት ያዳግታል፡፡

የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ የአዕምሮ በሽታ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ እንደ አቶ ሰብስቤ ዓለምነህ የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ በነቀርሳ አዕምሮ ቅዠት የሚመደብ ሲሆን፣ የሰውን የማገናዘብና የማስተዋል ክህሎት ሙሉ በሙሉ የሚዘጋና ከእንስሳዊ ባህሪም የሚያሳንስ ነው፡፡ በትክክልም ነው፡፡ ዋናው መገንዘብ ያለብን ነገር የበሽታው መንስዔ ምን እንደሆነ ነው፡፡ የአዕምሮ በሽታ መንስዔው በዋናነት ሁለት ነው፡፡ አንደኛው መንፈሳዊ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በአንጎል ላይ በተለያየ ሁኔታ በሚደርስ ጫና፣ ጉዳትና መዛባት ነው፡፡  የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ በሽታ በአንጎል ላይ በሚደርስ ጉዳት የሚከሰት አይደለም፡፡ የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ በሽታ ከመንፈሳዊው ዓለም ነው፡፡ የሰው አዕምሮ ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር የሚገናኝበት ረቂቅ የሆነ የመንፈስ አካል አለው፡፡ ይህ የመንፈስ አካል ከእግዚአብሔር ወይም ከዲያብሎስ መልዕክቶችን/መገለጥን ይቀበላል፡፡ በአዕምሮ ተተርጉሞም ወደ ተግባር ይቀየራል፡፡ መንፈሳችን ለእግዚአብሔር ከተገዛ ከእግዚአብሔር መልካሙን የፍቅር ሐሳብ ይቀበላል፡፡ መንፈሳችንን ለዲያብሎስ ካስገዛን የዲያብሎስን ክፉ ሐሳብ ይቀበላል፡፡ የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ ሐሳብ መሠረቱ ዳርዊኒዝም እንደሆነ ተረድተናል፡፡ ይህ አስተሳሰብ መሠረቱ እግዚአብሔርን መካድ ነው፡፡ ሰው እግዚአብሔርን ሲክድ መንፈሱ ለዲያብሎስ ተገዥ ይሆናል፡፡ ሰው የዲያብሎስን ፍልስፍና ሲከተል መንፈሱ የዲያብሎስን ሐሳብ ለአዕምሮው ማቀበል ይጀምራል፡፡ ስለሆነም ሰይጣናዊ የሆኑትን የክፋት ሐሳብ ከመተግበር የሚያግደው ነገር የለም፡፡

 የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች የየትኛውም እምነት አካል ነን ቢሉም እንኳን የሚፈጽሙት ድርጊት ተመሳሳይ ሲሆን የትኛውንም የእምነት ክፍል አይወክሉም፡፡ ምክንያቱም እምነቶች ሁሉ መልካምነትን፣ ፍቅርን፣ አንድነትንና መተሳሰብን የሚያስተምሩ ስለሆኑ ነው፡፡ ጥላቻና ነፍሰ ገዳይነት ግን ከዲያብሎስ ነው፡፡

የዘውግ/ብሔር/ጎሳ ፖለቲካ ከመንፈሳዊው ዓለም የሚመነጭ የአዕምሮ በሽታ በመሆኑ፣ በሕክምና መድኃኒት የለውም፡፡ መድኃኒቱ መልካም ወደ ሆነው ፈጣሪ በንስሐ መመለስ ብቻ ነው፡፡  ሁሉን መንፈሳዊ በሽታ መፈወስ የሚችል የፈጣሪ ኃይል ስለሆነ፡፡

ዘውገኛ/ብሔርተኛና የትወልድ ውርስ

‹‹አባቱን የሚረግም፣ እናቱንም የማይባርክ ትውልድ አለ። ለራሱ ንፁህ የሆነ የሚመስለው ከርኩሰቱ ያልጠራ ትውልድ አለ። ከፍ ከፍ ያሉ ዓይኖች ያሉት፣ ሽፋሽፍቶቹም ወደ ላይ የሚያዩ ትውልድ አለ። ድሆችን ከምድር ላይ ችግረኞችንም ከሰው መካከል ያጠፋና ይጨርስ ዘንድ ጥርሶቹ ሰይፍ መንጋጎቹም ካራ የሆኑ ትውልድ አለ፤›› (መጽሐፈ ምሳሌ፣ ም፣ 30 ቁ፣ 11 – 14) ‹‹ዘመናችን በምድር ላይ እንደ ጥላ ነውና እኛ የትናንት ብቻ ነን፣ ምንም አናውቅም፣ ስለዚህ የቀደመውን ትውልድ ጠይቅ፣ አባቶቻቸውም ለመረመሩት ነገር ትጋ፤›› (መጽሐፈ ኢዮብ፣ ም፣8 ፣ ቁ፣ 8-9)

የአገራችንን በመተው የሌላውን እውቀት፣ ባህል፣ ጥበብ፣ ፍልስፍናና አስተሳሰብ በመመኘት ወደማንወጣበት አዘቅት ከገባንና የተጣመመ አስተሳሰብ ካጎለበትን 50 ዓመታት (ግማሽ ምዕተ ዓመት) ሊሆነን ነው፡፡ ይህም በሁሉ ዘርፍ፣ በፖለቲካው፣ በባህል፣ በትምህርት፣ በሥነ ምግባር፣ ወዘተ አገራችንን ችግር ውስጥ አስገብተናታል፡፡ በዚህ ክፍል እንደተመለከትነው መሠረታዊው ችግር ባለማወቅ የዝገመተ ለውጥ ውላጅ የሆነውን የሶሻል ዳርዊኒዝም የፖለቲካ አስተሳሰብ አምጥተን በሕዝባችን ላይ በመጫናችን ነው፡፡ አሁን ያለው አዲስ ትውልድ መልካም እንዳያስብ፣ እንዳይመራመር፣ ክፉውን ከመልካሙ ለይቶ እንዳይመራ የአቶ እንዳለው ልጅ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

አንድ ማኅበረሰብ በሒደት ያካበተውን እውቀት፣ ጥበብና ማኅበራዊ መስተጋብር መሠረት ያደረገ አስተሳሰብና ዕድገት ካልገነባ፣ እንዲሁም ከሌላው መልካም የሆኑትን ለይቶ በመውሰድ ከራሱ ማኅበራዊ እሴቶች ጋር በማቀናጀት ካልተጓዘ ወደ ቀውስ ውስጥ እንደሚገባ ኢትዮጵያ ዓይነተኛ ምሳሌ ናት፡፡

የተቃወሰ የፖለቲካ ሊሂቅ (ምሁር ተብዬ) የበዛበት አገር ውስጥ መሠረታዊ ችግሮችን ነቅሶ አውጥቶ ችግርን መፍታት አስቸጋሪ ነው፡፡ የተማረ ይግደለኝ ብሎ ለተማረ ከፍተኛ ግምትና ክብር በሚሰጥበት አገር ውስጥ የተቃወሰ ምሁር አገርን ወደ ገደል ይዞ ሲነጉድ አለማወቁን ደፍሮ የሚያጋልጥና ለማስተካከል የሚሞክር እንዳላዋቂ ወይም እንደጠላት ይቆጠራል፡፡ አብዛኛው በተማረ ይግደለኝ አብሮ ወደ ገደል ሲነጉድ ይታያል፡፡ ገደልም ውስጥ ሆነን ከገደሉ ለመውጣት ሳይሆን ወደ ባሰው ገደል ለመውረድ ጥረት እናደርጋለን፡፡

በኢትዮጵያ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ የነበረው ተማረ የሚባለው ክፍል የተጣመመ የክፉውን ፍልስፍና በአገሪቱ ማስረፁ ሳያንስ፣ አሁንም በፖለቲካው ዘርፍ በደጋፊም ሆነ በተቃዋሚው በኩል ሆኖ እንዲሁም ባሰረፀውና በመለመለው አዳዲስ  የአቶ እንዳለው ልጆች አገሪቱን ወደ ገደል እየመራ ይገኛል፡፡ ይህ ምሁር ተብዬ የአባቶቹን መልካም ሐሳብና ራዕይ ጥሎ በሌሎች አስተሳሰብ ውስጥ ለመኖር የሞከረ፣ ነገር ግን መኖር ሳይችል ቀርቶ አቅጣጫ የጠፋበትና የተጠፋፋ፣ አዲሱንም ትውልድ በዚህ ክፉ የሶሻል ዳርዊኒዝም አስተሳሰብ አቅጣጫ ለማሠለፍ እየሠራ ይገኛል፡፡ ነገርን ከመሠረቱ፣ ውኃን ከምንጩ፣ እንደሚባለው ትውልድ ሊመረምርና የቀደመውን ትውልድ መጠየቅ፣ አባቶቻቸውም ለመረመሩት ነገር መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ያለፈውን 45 ዓመታት የተመራነው አባቶቻችን በመረመሩት ሳይሆን በእነ አቶ እንዳለው ልጆች ፍልስፍና ነው፡፡

በእርግጥ በመጀመሪያዎቹ አካባቢ ተማረ የሚባለው ክፍል መልካም የሠራ መስሎት ባለማወቅ አገሪቱን ችግር ውስጥ እንደከተተ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ሰው በልጅነቱ እንደ ልጅ ያስባል እንደ ልጅም ይተገብራል፣ በመሆኑም ከእውቀትና ከተሞክሮ ማነስ የተነሳ ስህተት ሊፈጽም ይችላል፡፡ ነገር ግን መልካም መንፈስ ያለው ከታላላቆቹና ከአባቶች በመማር ያስተካክላል፡፡ ኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርጋት የተሳሳተው ወጣት ታላላቆቹንና አባቶቹን ለመስማት ባለመፈለጉ፣ ከዚያም አልፎ ከእነ መልካም አስተሳሰባቸው ሰሚ አጥተው እንዲጠፉ መድረጉ ነው፡፡ የሳተው ትውልድ ሲሰማ የነበረው የራሱን የተሳሳተ አስተሳሰብ ብቻ በመሆኑ መልካሙን መንገድ ለማየት ተስኖት ኖሯል፡፡ አሁንም ትውልድን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እየመሩ በትውልድ መካከል ጥላቻንና መለያየትን እየዘሩ ያሉት አብዛኛው ከ55 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው፣ በጥላቻና ከእኔ ብቻ በላይ የለም በሚሉ ሰዎች መሆኑ ያስገርማል፡፡

ዕድሜ መስተዋት ነው የሚባል አባባል አለ፡፡ ይህ ማለት ዕድሜ ብዙ ነገርን ያስተምራል፣ የሳተው ስህተቱን እንዲያውቅ ይረዳል፣ ያላወቀውንና ያልተረዳውን እንዲረዳ ይረዳል፣ ከስህተቱ ተምሮ መልካሙን እንዲያደርግ ይረዳል፡፡ ነገር ግን በእኛ አገር ዕድሜ መስተዋት ሳይሆን ዕድሜ ጨለማ ነው የሚያሰኝ ነው፡፡ ትውልድ ከታላላቆቹና፣ በዕድሜ ከበለፀጉት ጥላቻን፣ ዘረኝነትን፣ ነፍሰ ገዳይነትን፣ ተንኮልን፣ ሴራን፣ ስግብግነትን፣ ሌብነትን እንዲሁም እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀልን የሚማርባት አገር ሁናለች፡፡

ያንተ መኖር ለኔ ታላቅ በረከት ነው፣

እግዚአብሔርም ያለው በዚህ መካከል ነው፡፡

ፍቅርን እንገንባ አብረን እንኑር፣

ለትውልድ እንዲሆን የኛ ትብብር፣

መምጫውም እንድንሆን በረከተ እግዚአብሔር፡፡

ሳይሆን የሚያስተምሩን፣ የሚያስተምሩን እኔነትን ብቻ ነው፡፡

እንዲታወቅልኝ ከፍጥረት የላቅኩኝ ልዩ ቋንቋ ያለኝ ታላቅ አሲዳም፣

ያንተ ይፍረስና የኔ ብቻ ይሁን ምድሩም ሰማዩም፣

ያንተ መኖር ለኔ በረከት ሳይሆን፣ ስለሚሆን መርገም፡፡

እግዚአብሔርም ይወቅ የፈጠረው ፍጥረት ለኔ መሆኑን፣

ሌላውም ይገንዘብ ቢኖር የማይጠቅም ሬሳ መሆኑን፣

ለኔ ብቻ ትቶ መምረጥ እንዳለበት የስደት ቤትን፡፡

በዕድሜ የበለፀገው ትውልድ ከስሕተቱ ንስሐ ገብቶ መልካሙን ከላስተማረ፣ ያሳሳተውንም አዲስ ትውልድ ወደ መልካም መንገድ መምራት ካልቻለ፣ ከ45 ዓመታት በፊት የተደረገውን ስህተት አሁን ያለው ትውልድ በባሰ ሁኔታ የማይደግምበት ምንም ምክንያት የለም፣ እያየንም ያለነው ይኼንኑ ነው፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ታላላቆቹንና አባቶቹን የማይሰማና ጠራርጎ አጥፍቶ ራሱን ብቻ የሚሰማ እንዳይሆን ያሠጋል፡፡

የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በአብዛኛው ሃይማኖተኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ከዝግመተ ለውጥ እያደገ የመጣው የዘውግ የፖለቲካ ፍልስፍና ባመጣው ቀውስ ምክንያት፣ ከእምነቱ በላይ ጥላቻንና ዘረኝነትን ሲሰብክ እየዋለ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወይም መስጊድ ሄዶ አምላኩን ሲጣራ ይታያል፡፡ እግዚአብሔርንም የክፋት ተባባሪ ልናደርገው እንሞክራለን፡፡ ግብዝ አማኝ ውስጡ በጥላቻ ተሞልቶ ቤተ ክርስቲያን ወይም መስጊድ ሄዶ ወንድሜ/እህቴ ሲባባል ይሰማል፡፡ ለመሆኑ በኢትዮጵያ ያለው አምላክ የተለየ ይሆንን? ለክፋት የሚተባበር፣ የክፉዎችን ጸሎት የሚሰማ?

‹‹በብርሃን አለሁ የሚል ወንድሙንም የሚጠላ እስከ አሁን በጨለማ አለ፤›› (1ኛ የዮሐንስ መልዕክት ምዕራፍ 2፣ ቁጥር 9)። ‹‹ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፣ በጨለማም ይመላለሳል፣ የሚሄድበትንም አያውቅም፣ ጨለማው ዓይኖቹን አሳውሮታልና፤›› (1ኛ የዮሐንስ መልዕክት ምዕራፍ 2፣ ቁጥር 11)። ‹‹ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፡፡ ነፍሰ ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ፤›› (1ኛ የዮሐንስ መልእክት ምዕራፍ 3፣ ቁጥር 15)።

እንዴት ነው የኦሮሞው ክርስቲያን ወይም እስላም፣ የአማራውን ክርስቲያን ወይም እስላም የሚጠላው? እንዴት ነው የአማራውን ክርስቲያን ወይም እስላም የትግሬው ክርስቲያን ወይም እስላም ሊጠላ የሚችለው? በየትኛው ሃይማኖታዊ መመዘኛ/ቃል ነው ሊጠላ የሚችለው? በአሁኑ ጊዜ ከዝግመተ ለውጥ እያደገ የመጣው የዘውግ የፖለቲካ ፍልስፍና ያመጣብን ክፉ ትምህርት ቋንቋችን ከእግዚአብሔር በላይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ እግዚአብሔር ፈጣሪነቱን ትቶ የኛን ቋንቋ እንዲናገርና ሌላውን እንዲጠላ ለማድረግ እየሞከርን ነው፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለው ተጽፏል፣‹‹አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፣ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፣ ወንድም ሴትም የለም፣ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና፤›› (ወደ ገላትያ ሰዎች ምዕራፍ 3፣ ቁጥር 28)። ‹‹አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል፤›› (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች ምዕራፍ 12፣ ቁጥር 13)። በዚያም ‹‹የግሪክ ሰው አይሁዳዊም የተገረዘም ያልተገረዘም አረማዊም እስኩቴስም ባሪያም ጨዋ ሰውም መሆን አልተቻለም፣ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉ ነው፣ በሁሉም ነው›› (ወደ ቆላስይስ ሰዎች ምዕራፍ 3፣ ቁጥር፣ 11)።

‹‹አንተም በፍፁም ልብህ፣ በፍፁምም ነፍስህ፣ በፍፁምም አሳብህና በፍፁምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትዕዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትዕዛዝ የለች፤›› (የማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 12፣ ከቁጥር 30 እስከ 31)

ታዲያ አንድ ክርስቲያን በምን መሠረት ላይ ነው ዘርና ቋንቋን እየጠቀሰ መለያየትንና ጥላቻን የሚያስተምረው? መለያየትን የሚያስተምር የእግዚአብሔር ሊሆን አይችልም፡፡ በጣም የሚገርመው በቋንቋ መስመር አስምረን ከዚህ መስመር ወዲህና ወዲያ ያለው የዚህኛው ወይም የዚያኛው ቋንቋ መሬት ነው ተባብለናል፡፡ መሬቱን እንኳን ቋንቋ ተናጋሪ ልናደርገው ሞክረናል፡፡ አየሩንስ ምን ልናደርገው ይሆን? ምናልባት ወደፊት ከዚህ መለስ ያለው አየር ይህንን ቋንቋ ስለሚናገር መተንፈስ አትችልም መባባላችን ላይቀር ይችላል፡፡ ወንዞችንስ ምን ልናደርጋቸው ነው? ከሌላው ቋንቋ ክልል ስለመጡ ልንጠላቸው ይሆንን? ወይስ ወደኛ ቋንቋ ክልል እንዳይገቡ ግድብ ያስፈልገን ይሆን? ለእንስሳትስ አጥር አጥረን ገደብ ማበጀት ሳይኖርብን ይቀራል፡፡ መዘዙ ብዙ ነው፡፡

የአፋሩን ፍየል/በግ/በሬ አማራው ወይም ኦሮሞው ላይመገብ ነው? ምክንያቱም የአፋሪኛ ቋንቋ ክልል ስለሆኑ፡፡ ከአማራው ክልል የመጣን ፍየል/በግ/በሬ ትግሬው ወይም ኦሮሞው ላይመገብ ነው? ምክንያቱም የአማርኛ ቋንቋ ክልል ስለሆኑ፡፡ ወፎችንስ ምን ልናደርጋቸው ነው? በሰማዩ ላይ አጥር ማጠር ሊያስፈልገን ይሆን? ወይስ እንደለመድነው እግዚአብሔር የክፋት ትምህርታችን ተካፋይ እንዲሆንና ሰማዩን እንዲያጥርልን ቤተ ክርስቲያንና መስጊድ በመሄድ ልናሳስበው ይሆንን? ጉዳችንኮ ብዙ ነው፡፡

ቋንቋ ሰውን በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ኑሮው እርስ በርሱ በማግባባትና በማስተሳሰር ችግሩን በተሻለ እውቀት በመፍታትና በማሳደግ፣ የተሻለ ኑሮ ለመኖር የሚያስችለው መሣሪያ ነው፡፡ ቋንቋ በመሠረቱ የሰዎች መግባቢያ ነው እንጂ መለያያ አይደለም፡፡ በምንም መሥፈርት ቋንቋ መለያያ ከቶ ሊሆን አይችልም፡፡ ቋንቋ ከሌለ ሰዎች መግባባት አይችሉም፡፡ እንዴትና በምን መለኪያ ነው መግባቢያው ተገልብጦ መለያያ ሊሆን የሚችለው? ሰዎች ምነው ማስተዋልና ማገናዘብ ተሳነን?

‹‹ሕዝቤ ሰንፈዋልና አላወቁኝም ሰነፎች ልጆች ናቸው፣ ማስተዋልም የላቸውም ክፉ ነገርን ለማድረግ ብልኃተኞች ናቸው፣ በጎ ነገርን ማድረግ ግን አያውቁም፤›› (ትንቢተ ኤርምያስ ምዕራፍ 4፣ ቁጥር 22)።

ወደፊት ትዳር እንዴት ሊመሠረት ነው? ሴቷና ወንዱ ቋንቋቸውን ካልገለጹ ዘውጉ እንዴት ይለያል? በዲኤንኤ አይለይ ነገር ቋንቋ በዘር/በደም አይተላለፍም፡፡ የክፋት ፍልስፍና ሲያድግ የማያደርገው ስለሌለ፣ ምናልባት ለወደፊቱ የብሔር/ዘውግ ልሂቃን (ተማርን ተብዬዎች) አንዱ የምርምር አቅጣጫቸው የሚሆነው ከደም ቋንቋን የመለየት ምርምር ሊሆን ይችላል፡፡ የትዳር መሠረቱ እግዚአብሔር ነው፣ መሥፈርቱም ሰው መሆን እንጂ ቋንቋ ወይም ዘውግ አይደለም፡፡ ሰው ከቋንቋ ወይም ከዘውግ ሳይሆን አንድ ሥጋ የሚሆነው ከባልና ከሚስት ጋር ነው፡፡

‹‹ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ በሚስቱም ይጣበቃል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤›› (ዘፍጥረት ምዕራፍ 2፣ ቁጥር 24)። ‹‹ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፣ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፣ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ የሚለውን ቃል አላነበባችሁምን?›› (የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 19፣ ቁጥር 5) ‹‹ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል ከሚስቱም ጋር ይተባበራል ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ፤›› (ወደ ኤፌሶን ሰዎች ምዕራፍ 5፣ ቁጥር 31)።

ከተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ የሚወለዱ ዕድል ፈንታቸው ምንድነው? ዘውግን/ብሔርን የሚወስነው ማነው፣ እናት፣ አባት ወይስ የጎሳ አለቃ ወይስ ክልል? ወይስ ቀበሌ? የመንግሥት መሥሪያ ቤት? ሥልጣኑ የማነው? የዘውግን/ብሔርን ፍልስፍና የማይቀበሉ የት ሄደው ሊኖሩ ነው? ከዚህ በፊት እንደተደረገው የመንግሥት መሥሪያ ቤትና ቀበሌ ስም እያየ ዘውግ እየለጠፈ ከክልል ሊያሳድድ ይሆን?

በዘውግ የፖለቲካ ፍልስፍና በክልሎች ታጥረን እንዴት አድርገን ነው በዓለም ደረጃ ብቁ ዲፕሎማትና ተመራማሪ ማፍራት የሚቻለው? አንድ ዲፕሎማት የዓለምን ታሪክ፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ ፍልስፍና፣ ወዘተ… ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ አጠገቡ ያለውን ወንድሙን የጠላ እንዴት አድርጎ ነው ስለዓለም የሚያውቅ ትውልድ ማፍራት የሚቻለው? በዓለም ደረጃስ ማንን ነው የሚወክለው? የማንንስ ጥቅም ነው የሚያስከብረው? ዲፕሎማት አፈራን እንኳን ብንል በወጭ አገር የሚገኘውን ጥቅም ምክንያት ያደረገ ግብዝ ዲፕሎማት እንጂ እውነተኛ ዲፕሎማት ማፍራት አይቻልም፡፡

ታዲያ ዘውገኛ/ብሔርተኛ ለትውልድ ምን ያወርሳል?

ጥላቻ፣ መለያየት፣ ዘረኝነት፣ ስግብግብነት፣ ሌብነት፣ ለወላጆች አለመታዘዝ፣ የበላይነት/የበታችነት ስሜት፣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል፣ ወዘተ. . . ወይስ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ አገራዊነትን፣ ሰጪነትን፣ ሠራተኝነትን፣ ለወላጆች መታዘዝን፣ የእኩልነት ስሜት፣ እኔ ከሞትኩ ወርቅ ይብቀል? መልሱን ለዘውገኛ/ብሔረተኛ እንተወዋለን፡፡

‹‹አፍህ ክፋትን አበዛ፣ አንደበትህም ሽንገላን ተበተበ። ተቀምጠህ ወንድምህን አማኸው፣ ለእናትህም ልጅ ዕንቅፋት አኖርህ። ይህን አድርገህ ዝም አልሁህ እኔ እንደ አንተ እሆን ዘንድ ጠረጠርህ እዘልፍሃለሁ በፊትህም እቆማለሁ። እግዚአብሔርን የምትረሱ እናንተ፣ ይህን አስተውሉ አለዚያ ግን ይነጥቃል የሚያድንም የለም፤›› (መዝሙር ምዕራፍ 50፣ ከቁጥር 19 እስከ 20)። (ይጥቀላል)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...