በታደሰ ሻንቆ
ከአምባገነንነትና ከትርምስ መላቀቅ፣ ሻል ያለና የሚሻሻል ሕይወት ውስጥ መግባት የሁሉም ሕዝብ ፍላጎት መሆኑ ብዙም አያከራክርም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዴሞክራሲ በላይ ብዙ የሚያስማሙ ፍላጎቶች አሉት፡፡ ሆኖም የፖለቲካ ልሂቃን በሚባሉት ‹‹ለውጥ ፈላጊዎች›› አካባቢ ከዴሞክራሲ በቀር የጋራ መግባባት ገና የለም፡፡ ዴሞክራሲ ከየትኛውም ፓርቲ ወገናዊነት ነፃ የሆነ የተቋማት ግንባታ የሚል አቋም ድረስ ብዙዎቹ፣ ካንጀትም ይሁን የለውጡ አየር የግድ ብሏቸው አብረው የሚሄዱ ይመስላሉ፡፡
በተቀረ ፍላጎቶቻቸው ለየቅል ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ በሥልጣን የነበሩና ገና ሥልጣን ያልቀመሱ ብሔርተኞች ሕገ መንግሥቱና ብሔር/ቋንቋን መሠረት ያደረገ አወቃቀርና የፓርቲ አደረጃጀት እንዳለ እንዲቀጥል የሚሹ ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተቃራኒ ደግሞ ሕገ መንግሥቱና የፌዴራል አወቃቀሩ ካስማ እንዲቀየርና የብሔር ፓርቲ አግላይ ገዥነት እንዲቀር የሚሹ ናቸው፡፡ በእነዚህ በሁለቱ የፖለቲካ ፍላጎቶች መሀል አማካይ መንገድ የያዙ ወገኖችም አሉ፡፡ የብሔር ብሔረሰብ መብቶችን መረጋገጥ ከዜግነት መብቶች መረጋገጥ ጋር አንድ ላይ ይዘው ፖለቲካውና የፓርቲ አደረጃጀቱ ከየብሔረሰባዊ ጎሬ እየወጣ ሕዝብን ከሕዝብ ያስተቃቀፈ እንዲሆን፣ ከዚህም አኳያ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል የሚሹ ወገኖችም አሉ፡፡ ከእነዚህ ልዩነቶች ጎን የምርጫ ጊዜም መከራከሪያ ሆኗል፡፡
ሀ) ያለው ሕገ መንግሥትና የፓርቲ አደረጃጀት እንዲቀጥል የሚሹት፣ ብሔርተኛ ፖለቲካ የፈለፈላቸው ጣጣዎች መከራከሪያ አሳጥቷቸውም ይመስላል፣ በፍሬ ነጥብ ከመከራከር ይልቅ የማጭበርበር ትግል ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡ አባይ (ዋሾ/ቀጣፊ) ክርክራቸውም በጎራቸው ውስጥ አስቂኝ መፈናከር ፈጥሮባቸዋል፡፡ የሕወሓት ወግ አጥባቂዎች በሚመሩት ክርክር ሕገ መንግሥቱና ፌዴራላዊነቱ እየተጣሰ ያለው አሁን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ለማፍረስና አሀዳዊነትን ለመመለስም እየተሠራ ነው፡፡ ጂኦግራፊያዊ አወቃቀርና የዜግነት ፖለቲካም ‹‹የአሀዳዊነት የክርስትና ስሞች›› ናቸው ይባላል፡፡ የሕወሓት ኢሕአዴግ ገዥነት ተቃዋሚ ሆነው በቆዩት ብሔርተኞች አካባቢ ደግሞ ብሔርተኛ ፖለቲካን ሕገ መንግሥቱንና አወቃቀሩን ለማዝለቅ ብልጠቴ ያሉት መከራከሪያ፣ እስከ ዛሬ ሕገ መንግሥቱና ፌዴራላዊ ግንኙነቱ መቼ ተግባራዊ ሆኖ ያውቅና? የነበረው እኮ ከላይ እስከ ታች የአንድ የሕወሓት ኢሕአዴግ አምባገነንነት ነበር፡፡ ያ ማለት የነበረው ሥርዓት አሀዳዊነት ነበርና አሁን የተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ የአሀዳዊነት ውጤት ናቸው፡፡ ሕገ መንግሥትና ፌዴራላዊ ሥርዓቱ በዴሞክራሲ ተግባራዊ ሲሆኑ ዛሬ ያሉት ችግሮች ይወገዳሉ ባዮች ናቸው፡፡
ከእነሱ በተቃራኒ ሕገ መንግሥቱና አወቃቀሩና ከብሔር ፓርቲነት ጋር እንዲቀየር የሚሹት ወገኖች በበኩላቸው፣ ፌዴራሊዝም አያስፈልግምና አሀዳዊነት ይመለስ ማን አለና! የፌዴራላዊነት አቀነባበራችን ሥልት ይቀየር ተባለ እንጂ እያሉ ከማስተባበል ዘለው ህሊና የሚረታና የወግ አጥባቂዎቹን ማጭበርበሪያ መና የሚያስቀር (የብሔረሰቦች መብትና የራስ አስተዳደር ገደል እንደማይገባ የሚያሳምን) መከራከሪያና ትልም የላቸውም፡፡ ተቀናቃኞቻቸው ያልተባለውን ተባለ የሚሉት አሀዳዊነት የምር ይመጣብናል ብለው ጠርጥረው እንዳልሆነ (ያልወደዱትን አቋም የጠለፋ ስም በመስጠት ከሕዝብ መነጠያና ማስጠመጃ ታክቲክም እንደሆነ) ያልተረዱም ሳይኖሩ አይቀሩም፡፡ እንዲህ ያለው የጠለፋ/የስም ልጠፋ ሥልት ድፍን 28 ዓመታት የበለፀግንበት ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹ሕገ መንግሥቱ የተጻፈበትን ወረቀት ያህል ተግባራዊ ዋጋ አጥቷል›› ሲባል ‹‹ሕገ መንግሥቱ ወረቀት ተባለ››፡፡ በአፈና ላይ ቅዋሜ ሲደረግና ለመብት ሲጮህ ‹‹ሕገ መንግሥታዊውን ሥርዓት ሊያፈርሱ ነው››፡፡ ሕወሓት ሲነቀፍ ‹‹በትግራይ ሕዝብ ላይ ዘመቻ ተከፈተ››፡፡ ደርግ በእንቅልፍ ልቡ እንዲገዛ ያስቻለና የሕዝብ መስዋዕትነትን ያበዛ የሕወሓት ስህተተኛ ፖለቲካና የትግል ሥልት ሲተች፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ በብዙ ሺዎች የከፈለውን መስዋዕትነት ዋጋ ለማሳጣት ተሞከረ››፣ ወዘተ፣ ወዘተ ይባላል፡፡ የሥልቱ መገለጫዎች ብዙ ናቸው፡፡
እንዲህ ያለውን በግድ አልክ ባይ፣ ‹‹አላልኩም›› በማለት መርታት አይቻልም፡፡ በአሳማኝ መከራከሪያ የበለፀገ ፖለቲካ ይዞ በሰፊው እየተረተሩ ማሳጣትን ይጠይቃል፡፡ ክፍልፋይ ብሔርተኝነትን ተቃውመው በግል መብት ጥግ የሚቆሙት ፖለቲከኞች ግን ትናንትናም ዛሬም የሚያቀርቡት መከራከሪያ እመኑኝ ልማልላችሁ ከማለት የማይሻል፣ ‹‹የግል/የዜግነት መብት ሲረጋገጥ የቡድን መብት ይረጋገጣል›› ባይነት ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ፣ የ27 ዓመታት ልምድ የብሔርተኛ ፖለቲካንና አገዛዝን ክስርስሩን አውጥቶ ብዙ የሚተረክ መረጃ አንበሽብሿልና ያለው ሕገ መንግሥትና አወቃቀር እንዲቀጥል የሚሹ ብሔርተኞች ይፈሯቸዋል፡፡ በየአካባቢው ገብተው የመቀስቀስ ሙከራቸውን በኃይልና በፀብ እስከ መመለስ ድረስ ያሳዩት ባህሪ የዚሁ መገለጫ ነው፡፡
በተረፈ በተግባር የከሰሩት ግትር ብሔርተኞችም ሆኑ፣ የሕገ መንግሥቱና የፌዴሬሽኑ ብሔርተኛ ትርታ እንዲቀየር የሚሹት ወገኖች የዴሞክራሲን ለውጥ የማሳካት ትግል ሕዝባዊ መሠረት ይዞ እንዳይቀለበስ የማድረግ ርብርብ ውስጥ በጥቅሉ የሉበትም ማለት ይቻላል፡፡ ብሔርተኞቹ ምን ዓይነት የጓዳ ባህሪ እንዳላቸው መናገር ባይቻልም፣ በፊት ለፊት ከምናየውና ከምንሰማው የዓብይ መንግሥትን እየሸረደዱና ሕግና ሥርዓት ማስከበር ያልቻለ መንግሥት ተብሎ በድጋፍ ‹‹መክሰሩ››ን የእነሱ ትርፍ አድርገው እያሰቡ፣ ምርጫው ቶሎ ደርሶ የምርጫ አትራፊ ለመሆን ሲያደቡ ይታያሉ፡፡ ያለው ብሔርተኛ ሥርዓት ከእነ ሕገ መንግሥቱ እንዲቀየር የሚሹት ወገኖች በበኩላቸው፣ አላባራ ያለውን ግጭትና መፈናቀል፣ እንዲሁም ከየግለሰብ ፀብ የሚነሳ የብሔር ጥቃት እያባዘቱ ከምርጫ በፊት ሕገ መንግሥቱና አወቃቀሩ እንዲቀየር ይወተውታሉ፡፡ የዓብይ መንግሥት ይህንን እንዲያደርግ በላይ በታች እያሉ ይቁለጨለጫሉ፡፡ በዚች በሽግግር ወቅት ሕገ መንግሥቱ ካልተቀየረና ያ ሳይሆን ወደ ምርጫ ከተኬደ ልፋታቸውና ምኞታቸው ውኃ እንደበላው አድርገው የሚያሰቡም አሉ፡፡ መንቆራጠጡ የበረታባቸው እንዲያውም፣ የዓብይ መንግሥት ሕገ መንግሥት ወደ መሻሻል እንዲገባና ብሔርተኛ ፖለቲካን በሕግ እንዲያግድ እስከ መጠየቅ ደርሰዋል፡፡
በሕገ መንግሥት መሻሻል ጉዳይ በተፋጠጡት ሁለት አቋሞች በኩል ሁለት አስገራሚ መከራከሪያዎች ብቅ ብለዋል፡፡
ሕገ መንግሥቱ ከምርጫ በፊት ይሻሻል በሚሉት ወገኖች በኩል ጠንከር ብሎ የታየው መከራሪያ እስከ ዛሬ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ እንደ ዓብይ መንግሥት ሰፊ አገራዊ ድጋፍ ያገኘ መንግሥት ታይቶ አይታወቅም፣ በዚህ ብሔረ ብዙ ድጋፍን ባፈሰ ሁኔታ ውስጥ ሕገ መንግሥት ያልተሻሻለ መቼ ሊሻሻል ነው!? የድጋፍ ሰፊነት ራሱ ሕገ መንግሥት ማሻሻልን ተገቢና ወቅታዊ ያደርገዋል የሚል ነው፡፡
በወግ አጥባቂዎቹ ብሔርተኞች በኩል ደግሞ ሕገ መንግሥቱ መሻሻል ካለበት የሚሻሻለው ሕገ መንግሥቱ ውስጥ በተቀመጡ መንገዶች ነው፡፡ ምርጫውንም ከጊዜ ገደቡ ማሳለፍ አለማሳለፍ ሕገ መንግሥት የማክበርና ያለማክበር ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹መከበር አለበት የሚባለው ሕገ መንግሥት እኮ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሕገ መንግሥት ሳይሆን፣ ሕወሓት ድርጅታዊ ሥራውን ሕዝባዊ ልባስ የሰጠበት ሕገ መንግሥት ነው፤›› የሚለውን ትችት ለመመከትም ያቀርቡት የነበረው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር ዳር ተወያይቶበት፣ በፍላጎቶቹ ያዳበረው ነው፤›› የሚለው አታላይ መከራከሪያ ሰሚ ካጣ በኋላ ሌላ ቋንቋ ደግሞ መጥቷል፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥት በማርቀቅና በማፅደቅ ክንዋኔው ጠባብ አካሄድ ሊኖረው ይችላል፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት አረቃቀቅና አፀዳደቅ ጠባብ ነበር፡፡ ለጃፓኖችም ሕገ መንግሥት የሰጧቸው አሜሪካኖቹ ነበሩ. . . ወዘተ›› የሚል፡፡
ሁለቱም ወገኖች ማዕዘናቸው ያላደረጉት ቁልፍ ነጥብ፣ ያለውን ሕገ መንግሥት አጠበቅንም አዲስም ጻፍን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የእኛ የሚሉትና የሚሳሱለት ሕገ መንግሥት ሆኖ የመገኘቱን ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ይህን ዓይነቱን ተቀባይነት የተቀዳጀ ነው? በፀደቀ የ24 ዓመት ዕድሜ ውስጥ ይህን ተቀባይነት መቀዳጀት አልቻለም፣ በልሂቃኑም ሆነ በሕዝቦች ዘንድ ይህ ችግሩ እስከ ባንዲራ ድረስ የዘለቀ ነው፡፡ ሁለቱም ወገኖች ይህን ዓይን የሚዋጋ እውነት ያውቁታል፡፡ ግትሮቹ ብሔርተኞች ሕገ መንግሥቱ መሻሻል ካለበት መሻሻል ያለበት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ነው ሲሉ የሕዝቡን ፍላጎት እያሰቡ ሳይሆን፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያለውን አንድ ክልላዊ ምክር ቤት እንኳ እንቢ ካለ ማሻሻያ ውድቅ የሚሆንበትን በተለይም የአንቀጽ 105/1/ለ አይበገሬ ቁልፍ ለብሔርተኛ ፍላጎታቸው መቀጠል መተማመኛ በማድረግ ነው፡፡ በዚህ የሽግግር ወቅት ሕገ መንግሥት ካልተሻሻለ እያሉ የሚወተውቱትና ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ሕገ መንግሥት ማሻሻል ህልም ሆኖ እንደሚቀር የሚሰብኩትም ወገኖች የመቅበጥበጣቸው ሚስጥር፣ ያንን ኢሕአዴግ ያስቀመጠውን ቁልፍ በአቋራጭ ማምለጥና የእነሱን ፍላጎት ሕገ መንግሥት አድርጎ ማፀደቅ ነው፡፡
ሕገ መንግሥት ማሻሻል በአቋራጭ መንገድ ሲባል፣ አሁን አለ የሚባለውን ሕገ መንግሥት የሌለ/የከሸፈ ያህል ቆጥሮ ማለት ነው፡፡ አሁን በምንገኝበት የአገሪቱ እውነታ፣ እዚህ አካሄድ ውስጥ ብንገባ፣ እግዜሩም ታክሎበት ልናገኝ የምንችለው ደግ ውጤት ቢኖር፣ የኢትዮጵያን ኅብረተሰብ ከፋፍሎ የሚያነታርክ እንደ ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት የፈጭቶ ጥሬ ውጤት ነው፡፡ ይኸውም እንኳ በህልም ያለሙትን እንደ ማግኘት ያህል ዕድሉ ኢምንት ነው፡፡ የመሆን ሰፊ ዕድል ያለው የ1987 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት ከመሸወዳችን ወደ መበታተን መጓዛችን ነው፡፡ በአሁኑ ደረጃ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያለውን ሥርዓት ተከትለን ከምርጫ በፊት እናሻሽላለን ቢባል ደግሞ፣ ግትር ብሔርተኞች የምክር ቤት ወንበር የተቆጣጠሩበት ክልል አይታጣምና በአንድ ክልላዊ ምክር ቤት እንቢታ የማሻሻል ሙከራው መና ሊቀር የሚችልበት ዕድል በእጅ ያለ ነው፡፡ ሲከሰት እናንገራግራለን ቢባል፣ የሕገ መንግሥት መረገጥን ማመካኛ አድርጎ ከፌዴሬሽኑ የመለየትን አማራጭ መጋበዝ ይሆናል፡፡ ይህች ቀን እንድትመጣ የሚሹና በዚህ አቅጣጫ ሕዝብን ለማሸፈት የሚሠሩም እንዳሉ ዕውቅ ነው፡፡
የሕገ መንግሥት መሻሻል የተፈለገው፣ የጥቂቶችን ፍላጎት ሕዝብ ላይ የመጫን ታሪክ ተዘግቶ መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከሞላ ጎደል ይሁን ያሉት ሕገ መንግሥት እንዲመጣ ከሆነ፣ አቋራጭ መንገድ ፍለጋና መቅበጥበጥ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ያለው ሕገ መንግሥት ውስጥ የተቀመጠውም ቁልፍ አስፈሪ አይሆንም፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያው የሚመነጨው ከኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ለውጥ ከሆነ፣ ለውጡም የአገሪቱን እውነታና የሕዝብን ፍላጎት የተቆናጠጠ ከሆነ፣ ይህንኑ ሐዲድ ተከትሎ ለውጡ በድርጊቶች፣ በውይይቶች በክርክሮችና በድርድሮች የመግባባትና የኅብረተሰብ ንቃት የመሆን ብርታት እያጎለበተ ከሄደ አወላካፊ ጓሎችን መፈረካከሱ አይቀርም፡፡ ይህ ሒደት የዴሞክራሲ ለውጡን ድርጊታዊና አስተሳሰባዊ ሥር የማያስያዝ ሒደት ነው፡፡ የአዕምሮ ሙሽትን (አዕምሮን) የመቀየር ሒደት ነው፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻል የሚሻው የአዕምሮ ለውጥ ከተገኘ፣ ሕገ መንግሥቱ ሳይጻፍ የተረቀቀ ያህል ተሠርቷል ማለት ነው፡፡ የጥቂቶች ሴራና ውስወሳ ሕዝብን ሊያደናግር ወይም በመነጠል ዕርምጃ ሊያስፈራራ የሚችልበት አቅም አይኖረውም፡፡ መላው ሕዝብ ሰፊ ፍላጎቱን በሕገ መንግሥት መልክ ለመቅረፅ ሲነሳም ከፊቱ ተገትሮ የሚገታው አንዳችም መዝጊያና ቁልፍ አይኖርም፡፡
ይህ ስኬት ሊደረስበት የሚችል ነው? እዚህ ስኬት ላይ መድረስ ይቻላል? ያለ አንዳች ጥርጥር! ዴሞክራቶችና የዴሞክራሲ ወገኖች ለውጡ ምን ምን እንደሚሻ በቅጡ እስከገባንና ንቁ ርብርብ እስካደረግን ድረስ፣ ስኬቱ ቤታችንን እያንኳኳ ነው ሊባልም የሚችል ነው፡፡ እንደምን ቢባል፣ አሁን የምንገኝበት እውነታ የ27 ዓመታት አገዛዝ ልምዳችን ያደረሰብንን ስብራቶች እየዘከዘከ እዩልኝ ስሙልኝ እያለ ነው፡፡ ምን እንደሚያሻን፣ ምን ማረም እንዳለብን ከሕዝብ ሰቆቃ አንብቡ እያለን ነው፡፡ የመከራ ምክሩ፣ መጽሐፍ አንብቦ ዕውቀት የመገንዘብ ያህል የለውጡን ይዘት አበጥሮታል፡፡ የሚቀረው የመከራ ምክሩን በውይይትና በክርክር እየሰለቁ የመስማትና የማሰማቱ የእኛ ፋንታ ነው፡፡ በዚህ መልክ የሚካሄደው የአዕምሮ ለውጥ ለመጪው ምርጫ ይድረስም፣ አምስትና ከዚያ የዘለለ ዓመታት ይውሰድም፣ ሳይታክቱ መትጋት የሚያስገኘው አጠቃላይ መግባባት የሚያመጣው የሕገ መንግሥት ለውጥ ምንም ዓይነት ቡድን በሴራ የማያናጋው ይሆናል (ይህንን ውጤት የማሳካት ጉዳይ ፖለቲካዊ መታመስ ሳይፈጥሩ መጪውን ምርጫና የዴሞክራሲ ግንባታችንን የሚጠቅሙ የሕገ መንግሥት አንቀጽ ማሻሻያዎችን አሁን ባለንበት ሁኔታ ውስጥ ከማካሄድ ጋር አይጣላም)፡፡
ለ) በተረፈ ሕገ መንግሥቱን በአጠቃላይ የመከለሱ ሥራ፣ የግድ መጪውን ምርጫ መቅደም እንደሌለበት ከተግባባን፣ ሌላ ተከታይ ጥያቄ እናንሳ፡፡ መጪውስ ምርጫ ለሕገ መንግሥታዊው የጊዜ ገደብ የግድ መገዛት አለበት ወይ? በፍፁም፡፡ ለጊዜ ገደቡ መገዛትን ግድ የማናደርገው ግን፣ ቁጥረ ብዙ ቁንጥርጣሪ የፖለቲካ ቡድኖች ገና ዝግጅታቸውን ስላላሟሉ አይደለም፡፡ ይህ ከምርጫው ኃላፊነት ውጪ ነው፡፡ የምርጫው ክንዋኔያዊ ኃላፊነት በብልሽት ያልተጨመላለቀ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎችንና ሥርዓቶችን ማሟላት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ምርጫውን በታወቀ ወቅት ለማካሄድ መሠራት ያለበትን ሁሉ የመሥራቱ ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሚደረስበት መሰናዶ ደካማ ከሆነ ጊዜውን ገፍቶ መሰናዶውን ማሟላት አግባብ ነው፡፡ ለምን ቢባል? ለሕገ መንግሥቱ በመታመን ረገድ ጊዜ ገደቡን ለጊዜ ገደብነቱ ከማክበር ይልቅ፣ ጊዜውን ጥሶ ያልተልኮሰኮሰ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ የማካሄድን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ማክበር በእጅጉ ስለሚበልጥ ነው፡፡ ለዚሁ ሲባል የምርጫው ጊዜ ሲደርስ ከአካባቢ አካባቢ ያለውን የነፃ ዝውውር፣ የእንቅስቃሴና ሕግ የማስከበር አስተማማኝነት ፌዴራላዊና አካባቢያዊ ምክር ቤቶች ከፓርቲዎች ጋር የተገናዘበ ግምገማ አድርገው፣ የጊዜ ገደቡን የማለፍ ውሳኔ ቢያደርጉ አድራጎታቸው ሕገ መንግሥታዊ የመሆን ያህል ትርጉም የሚሰጥ ነው፡፡
ስለምርጫ ስናወራ ተመዝግቦ ሳጥን ውስጥ ካርድ ስለመክተትና የዚህ ዓይነቱ ክንዋኔ ሳይጭበርበር ስለመካሄዱ ብቻ አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ ሲባል ምርጫ ብቻ የሚታሰበን ከሆነ ጉዟችን ወዴት እንደሆነ ስተናል ማለት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የአስተሳሰብና የኑሮ ግንኙነት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የሐሳቦች፣ የፈጠራዎችና የሥራዎች ውድድር የሞላበት ነው፡፡ ገና በኑሮነት የማንዋኝበትን ሥርዓት አናውቀውም ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን መታፈንንና ተሸማቆ ኑሮን እስከተመራንበት ድረስ፣ ሳይፈሩ ጥፋትንና በደልን ማጋለጫ፣ መታገያ፣ ታግሎ መርቻ ሕጋዊ መንገዶችን እስከናፈቅን ድረስ በዴሞክራሲዎች ውስጥ አነሰም በዛ የሚንፀባረቀው የእኩልነት ስሜትና በሥርዓቱ እምነት አሳድሮ ለመብት የመከራከርና ጥቃትን የመፋረድ ድፍረት የሚያስቀናን እስከ ሆነ ድረስ፣ የምንሻውን ዴሞክራሲ ገና ባናጣጥመው በተወሰነ ደረጃ እናውቀዋለን፡፡
የመብትና የእኩልነት ስሜት ሽርፍራፊዎችን እስካሁን በሞካከርናቸው የለውጥ ጉዞዎቻችን መቆነጣጠራችንም አይካድም፡፡ የ1966 ዓ.ም. አብዮት ይዞት በመጣው የለውጥ ሙከራ ውስጥ ባለፍነውም ሆነ በወሬ በምናውቀው ሰዎች ዘንድ ብዙ ጊዜ የሚነገረው፣ በተውሶ ርዕዮተ ዓለም ምክንያት ስለደረሰ አሳቻ ጉዞና ጥፋት ነው፡፡ የገባር ሥርዓቱ ምን ያህል መንኳሰስና እብሪት የተሞላበት እንደነበር፣ ለመኳንቶችና ለባለርስቶች እንዴት ይደገደግ/እጅ ይነሳ እንደነበር፣ እንዴትስ ያለ መስተንግዶ ይሰጣቸው እንደነበር፣ ወጉ ቢጓደል ምን ይደርስ እንደነበር የሚያውቅ፣ ‹‹ዘመናዊ›› በሚባለው የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሠራዊት ውስጥ (በ1960ዎች ውስጥ ሳይቀር) የሎሌና የጌታ ግንኙነት እንደነበር (ወታደሮች ለከፍተኛ መኮንኖች የቤት አገልጋይና የግል ቤት ገንቢ እስከ መሆን ድረስ ይሰማሩ እንደነበር)፣ የአማላጅነቱና የደጅ ጥናቱ ባህል ምን ያህል የተንሰራፋ እንደነበር የተገነዘበና ያስታወሰ፣ የ1966 ዓ.ም. ለውጥ የቱን ያህል የጠነዛ ግንኙነትና ዘልማድ ለመሻገር እንደረዳ መገንዘብ አይገደውም፡፡ የ1966 ዓ.ም. አብዮት ጭቆናንና ብዝበዛን እንቢ ያለ አብዮታዊ ንቃትንና ትግልን ይዞ ቢመጣም፣ ብዙ ነገሩ በተቀየረ ሥርዓት ውስጥ ጓድ እየተባባሉ መረገጥ፣ መመዝበሩን፣ መስገድና በጥፊ መወልወሉን እንደገና ከመኖር አላወጣንም፡፡ የደርግ አምባገነንነት በፊት የነበረንን ደግ ነገር ጨምሮ ማኅበራዊ ውቅራታችንን ሃይማኖታዊ ስለትን ማጭበርበሪያ እስከ ማድረግ ድረስ በልሽቀት አፈራርሶብናል፡፡ ደርግ ወድቆ የነገሠው ብሔርተኝነትም፣ በብሔረሰባዊ ማንነት መኩራትንና በአፍ መፍቻ ቋንቋ መሥራትን ቢያጎለብትምና ራስ በራስ አስተዳደርን ተከልኩ ቢልም፣ ተማክሎ የቆየውን ገዥነት ብሔርተኛዊ ፌዴራላዊ መልክ እንዲይዝ ከማድረግ አላለፈም፡፡ ልማታዊ ለውጡና ተሃድሶውም ልሽቀትንና ተባይነትን ከላይ እስከ ታች ለማሸነፍም፣ ከመስፋፋት ለማቆምም አልቻለም፡፡ የብሔረሰብ መብቶችን የማረጋገጥ ሸንካፋ ክንዋኔዎቹ የዕይታን መከታተፍን፣ የብሔርተኛ አንጓላይ ገዥነትን፣ ከዚህም የተፈለፈለ መሸካከርና ጥላቻን አሳቅፎናል፡፡
ዛሬ ዴሞክራሲ የምንሻው እስካሁን ከመጣንባቸው ሥርዓቶችና ከለውጥ ሙከራዎቻችን ያገኘናቸውን በጎ ነገሮች ይዘን፣ ከደረሱብን የድቀት ኪሳራዎች ለመውጣት ነው፡፡ ለዚህ ጉዞ፣ የዴሞክራሲ ለውጡ ወደ ኅብረተሰብ እንቅስቃሴነት ማለፉ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል መንግሥት ደረጃ የተቀመጡ ሰዎች ‹‹ሕዝብ ሊያግዘን ይገባል. . . ከለውጡና ከሰላም ጎን ሕዝብ ሊቆም ይገባል፤›› ማለታቸው ምንም አያመጣም፡፡ በመንግሥትም በኩል፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችም በኩል ያሉ የዴሞክራሲ ኃይሎች ዴሞክራሲን የሕዝብ እንቅስቃሴ የማድረግ መሐንዲስነቱን፣ አነቃቂነቱንና ቀስቃሽነቱን ካልሠሩ ማን ሊመጣና ሊሠራው ነው!? ለውጡ ያለ መቀልበስ ዋስትና የሚያገኘው ብዙኃን አቀፍ እንቅስቃሴ ሲሆን ነው፡፡ ሰላም የመበጥበጥና ሕዝብ የማጋጨት ሸሮች፣ የዝርፊያና የኮንትሮባንድ መረቦች፣ የበደል ድርጊቶች እየተጋለጡ ለውጡ የሚራመደው፣ ዜጎች በዳዮቻቸውን መልሶ ደጀ ጠኝ ከመሆን የተለየ አዲስ ሕይወትን መለማመድ የሚጀምሩት በለውጡ አጥለቅላቂነት ውስጥ ነው፡፡
በጭርታ ውስጥ ፓርቲዎች ወደቢሯው መጥቶ አባል አድርጉኝ ያላቸውን ሁሉ እያጋበሱና የምርጫ ዕጩ እያደረጉ ስላቀረቡ፣ ለውጡ ለሕዝብ የረባ ፍሬ የሚሰጥ አይሆንም፡፡ የኅብረተሰቡ ምርጥ የዴሞክራሲ ታጋዮች ከወጣቱም ከጎልማሳውም በተግባር እየተፈለቀቁ የሚወጡት፣ እነዚህን ፍልቃቂዎች የመንግሥት አውታራት፣ ተሃድሶውም ሆነ የዴሞክራሲ ፓርቲዎች እየዘገኑ ለውጡን ማበልፀግ የሚችሉት ሕዝብ አቀፍ በሆነው እንቅስቃሴ ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ሰፊ እንቅስቃሴ ውስጥ ነፃ የብዙኃን ማኅበራት በየአቅጣጫው ይገማሸራሉ፡፡ ሐሳቦች፣ ክርክሮችና ውይይቶች ይፍለቀለቃሉ፡፡ ነፃ ፍትሐዊ ምርጫ ማካሄድ መሠረታዊ ጥቅሜ የሚል ማኅበራዊ ግንዛቤ ይዳብራል፤ ለዚያ የሚሆን ሰፊ የሰው ኃይል ስንቅ ይፈጠራል፡፡
የሐሳቦች መፋጨትና መንሸራሸር ፓርቲዎችን ማብጠልጠልና መፈተጉ አይቀርምና፣ አንጓላይ የሆኑና የማያንጓልሉ (የሚበጁና የማይበጁ) ፓርቲዎችን የመመዘን የሕዝብ አቅም ያድጋል፡፡ ብሔረሰብ/ብሔረሰባትን በለየ አባልነት ላይ የቆሙና አግላይ ገዥነትን ለማዝለቅ የሚሹ ፓርቲዎች ፈተና ይሆንባቸዋል፡፡ ‹‹ክልላዊ›› ኅብረተሰባቸውን ሁሉ ሕዝቤ ብለው የሚያዩ፣ አባልነትን በብሔረሰብ ማንነት የማይመርጡ ኅብረ ብሔራዊ የአካባቢ ፓርቲዎች መበራከታቸው ይጨምራል፡፡ በአግላይ የብሔር ፓርቲና በኅብረ ብሔራዊ የአካባቢ ፓርቲ መሀል ምን ያህል ልዩነት እንዳለ፣ አግላይ የብሔር ስብስብንና የዓላማ ትኩረትን እንደያዙ እንደ ከዚህ በፊቱ ኢሕአዴግ በግንባርነት መግጠምና የአካባቢያዊ ኅብረ ብሔራዊነት ድምር መሆን ምን ያህል የአመለካከት ልዩነት እንዳለው፣ በፌዴራል ሥልጣን ላይ ለመውጣትም የትኛው አግባብነት እንደሚኖረው ጥርት ብሎ ይወጣል፡፡ ለየብሔር በመቆምም ሆነ ለኢትዮጵያ በመቆም ስም ከሚነግዱ ጠባብ ፓርቲዎች ባሻገር፣ በወጥ ፓርቲነትም ሆነ በዓላማ የተገናኙ አካታች የአካባቢ ፓርቲዎችን ባሰባሰበ ግንባርነት መልክ ኅብረ ብሔራዊነታቸው የደረጀ ፓርቲዎችን የማግኘት ዕድል ይበረክታል፡፡ አማራጮች ሲሟሉና ውድድሩ እውነታዊ መረጃ ለሕዝብ የማቅረብ አቅሙ ሲተባ፣ መራጮችም ፓርቲዎችን ባላቸው አተያይ፣ ባላቸው ዓላማና ተግባራዊ ፖለቲካ ምን ያህል ሕዝብን አስተቃቅፎ ግስጋሴን ለመምራት እንደ ተዘጋጁ በደንብ መመዘንና ውሳኔ ማድረግ ይችላሉ፡፡
እነዚህ ውጤቶች ደህና ሊባል ከሚችል የአገራዊ ‹‹ክልልላዊ›› የመንግሥት ዓምዶች ኢወገናዊ መሻሻል ጋር፣ በምርጫ ያሸነፈ ፓርቲም ፖሊሲውንና አስፈጻሚዎቹን ሾሞ መንግሥትን ከመምራት በቀር፣ የሙያና የሕዝብ አገልግሎት አገራዊ ‹‹ክልላዊ›› አውታራትን ሰንሰለት ተከትሎ ፓርቲያዊ መረብ የማይሠራበትን (በመረቡም አማካይነት ቅጥርን፣ ምደባን፣ ዕድገትን፣ ዝውውርንና የሥራ ስንብትን ሁሉ ለማቡካት የማይችልበትን) ድንበር በደንብ ከለየ መሰናዶ ጋር ሲገናኙ፣ የሚገኘው የምርጫ ውጤት ፍሬያማ ይሆናል፡፡ ከዚህ አኳያ አንዱ ጋ ሐሳቦች፣ ክርክሮችና ውይይቶች ሲናኙ፣ ብዙኃን ማኅበራትና ፓርቲዎች ሲላወሱ ሌላው አካባቢ ፆም አዳሪ ከሆነ ለውጡም የአካባቢው ሕዝብም ተጎዳ ማለት ነው፡፡ ፆም ያደረንና በዴሞክራሲ ልምምድ የተንበሸበሸን አንድ ላይ እንደ ፍጥርጥራቸው ምርጫ ያካሂዱ ማለትም ትክክል እንደማይሆን ከወዲሁ መታወቅ አለበት፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡