Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በባንክ ሥራ እንዲሳተፉ እንደተፈቀደው ሁሉ በኢንሹራንስ ዘርፍም ተግባራዊ ይደረጋል የሚል እምነት አለን››

አቶ ያሬድ ሞላ፣ የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት

የአገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪን ሊያራምዱ ይችላሉ የተባሉ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውም በዚህ ሪፎርም ውስጥ እንደሚያልፍ ይጠበቃል፡፡ በዘርፉ መስተካከል አለባቸው የተባሉ ጉዳዮች ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየቀረቡ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የመድን ሰጪዎች ማኅበር አሉኝ ያላቸውን ጥያቄዎች አቅርቧል፡፡ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃና የኢንዱስትሪውን ወቅታዊ ጉዳዮች፣ እንዲሁም የማኅበሩን ዓላማና እንቅስቃሴ በተመለከተ ዳዊት ታዬ የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የኒያላ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ ሞላን አነጋግሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ ዋና ዋና ዓላማዎች ምንድናቸው? ተግባራዊ አደርጋቸዋለሁ ብሎ የሚያከናውናቸው ሥራዎች እንዴት ይገለጻሉ?

አቶ ያሬድ፡- ማኅበሩ ሲቋቋም ሊያከናውናቸው የሚገቡ ተግባራትን ነድፎ አስቀምጧል፡፡

ከተግባሮቹ መካከል የመጀመርያው የፖሊሲ ቀረፃ ነው፡፡ ይህም ማለት አባል ድርጅቶች ሊኖራቸው በሚፈልጉት፣ በጋራ አቋም ሊጓዙበት በሚፈልጉት አቅጣጫና ሒደት ላይ ፖሊሲ ቀርፆ ማስፈጸም ነው፡፡ አባላቱን በመወከል የሚከናወነው የጥቅም ማስጠበቅ ሥራ ዋነኛው ሲሆን፣ ይህም በሥሩ ብዙ ዘርፎች አሉት፡፡ ከእነዚህም መሀል ኢንሹራንስን በተለየ በሚመለከቱ አዋጆችና ድንጋጌዎች ዝግጅት ላይ አስተዋጽኦ ማበርከትን ጭምር ያጠቃልላል፡፡ በአጠቃላይ የንግዱን ማኅበረሰብ ወይም የንግዱን ሥራ፣ በተለይም ኢንሹራንስን በሚመለከት የሚወጡ አዋጆች፣ ድንጋጌዎች፣ ደንቦችና የመሳሰሉት ዝግጅት ላይ የማኅበሩ ጥቅሞች እንዲንፀባረቁ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው በኢንሹራንስ ሱፐርቪዥን፣ በገበያ ሥነ ምግባር ጉዳዮችና በመሳሰሉት ላይ የማኅበሩን ጥቅም ማስጠበቅ የሚለውም ሌላው ተግባሩ ነው፡፡ የውል አሰጣጥና የካሳ ክፍያ አገልግሎት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ፣ እንዲሁም በጠለፋ ዋስትና አገዛዝና የፋይናንስ ሪፖርት ጉዳዮች የማኅበሩን ጥቅሞች ማስጠበቅ የሚልም ይገኝበታል፡፡ የማኅበሩ ዓበይ ተግባር ነው ብለን የምናምነው፣ የኢንዱስትሪውን የገበያ ውድድር አስመልክቶ በተወዳዳሪ ኩባንያዎች መካከል የተሻለ መረዳትና መግባባት እንዲኖር፣ የመረጃ ውልልጥ እንዲኖር ማገዝና የመሳሰሉትን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ የባለሙያ እጥረት ችግርን ለመፍታት የሚደረገው የሥልጠናና የሰው ሀብት ግንባታ ሥራ፣ የኢንሹራንስ አገልግሎት ለሚገዙ ተጠቃሚዎች፣ ለኅብረተሰቡ፣ ለሚዲያና በኢንሹራንስ አገልግሎት ውስጥ ለሚመለከታቸው ሁሉ የኢንሹራንስ አገልግሎት ሚና በሚገባ እንዲታወቅ ማገዝ ከማኅበሩ ተግባራት ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን የገለጹልኝን ምን ያህል ሠርታችሁበታል? ኢንዱስትሪውን በተመለከተ የሚወጡ ሕጎች ላይ እናንተ ምን ያህል አስተዋጽኦ ነበራችሁ? በአጠቃላይ ማኅበራችሁ በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለው አበርክቶ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ያሬድ፡- አንድ ማኅበር ከዕለታት አንድ ቀን በአባላቱ በጎ ፈቃድ ስለተመሠረተና ልደቱን እያከበረ ስለሄደ ብቻ አበርክቶ አይኖረውም፡፡ መዋቅራዊ ቁመናው ምን ይመስላል? የሰው ኃይልና የንብረት ዝግጅቱ፣ ብቃቱ፣ ተሞክሮውና የማስፈጸም ብቃቱ የት ደርሷል? የሚለው መታየት አለበት፡፡ ከዚህ አኳያ ስንመለከተው ማኅበሩ ራሱ በሚገባ የተገነባና የተደራጀ ባለመሆኑ አበርክቶቱ እጅግ አናሳ መሆኑን አባላቱም ይስማሙበታል፡፡ እንደ አበርክቶት እንጥቀስ ካልን የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያ በመመሥረት ረገድ፣ ማኅበሩ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ሊጠቀስ የሚገባው ነው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ የመጀመርያው የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኋላ ልመልስዎት ነው፡፡ ኢንዱስትሪውን በሚመለከቱ የሚወጡ ሕጎች ላይ አስተዋጽኦዋችሁ ምን ያህል ነው? ለምሳሌ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለው የዋጋ ሰበራ ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ለጉዳዩ አንድ መፍትሔ ለመስጠት ከብሔራዊ ባንክ ጋር እየመከራችሁ ነበር፡፡ ጉዳዩ ምን ደረጃ ላይ ደረሰ? በሌላ በኩልም በሌሎች መመርያዎች ላይ የእናንተ ሐሳብ ምን ያህል ሕግጋቱ ላይ ታይቷል?

አቶ ያሬድ፡- እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ የማስፈጸም አቅሙ ጠንካራ ነው ማለት አይቻልም፡፡ በበቂ ሁኔታ እየተሠራ ነው የሚል እምነት የለም፡፡ ግን ማኅበሩን ለማጠናከር እየተሠራ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ከብሔራዊ ባንክ ጋር አዋጆችንና ደንቦችን በተመለከተ በተጋበዝንበትና በተጠራንበት ቦታ ሁሉ ተገቢ ውይይት በማድረግ አቋማችንን ለማንፀባረቅ እየሞከርን ነው፡፡ ግን እውነት ለመናገር ማኅበሩ ከሚጋበዝበት የማይጋበዝበት ይበልጣል፡፡ ብንሳተፍ ግን አስተዋጽኦው ከፍ ይል ነበር፡፡ ለምሳሌ የትራንስፖርት አዋጆች ሲወጡ አሁንም የተሰጡ የሪፎርም ሐሳቦች ሲታሰቡ ማኅበሩ ቢጋበዝ ብዙ ጠቃሚ ሐሳቦችን ያቀርባል፡፡ ስንጋበዝ ግን እናቀርባለን፡፡ የዓረቦን ተመንን በሚመለከት ገበያው አሁን ሙሉ ለሙሉ እያነጣጠረ ያለው በዋጋ ሰበራ ላይ ነው፡፡ ለምን እንደዚህ ሆነ የሚለውን እንመልከተው፡፡ የመጀመርያው ውስጣዊ ችግሮች ልንላቸው የምንችለው ኩባንያዎች እርስ በርስ ተናንቀው ለመጠፋፋት የሚሄዱበት፣ ከአገልግሎት ጥራትና የሥራ ቅልጥፍና ይልቅ በዋጋ ሰበራ ላይ ብቻ ያተኮረው አካሄድ ነው፡፡ ዛሬ በአገራችን ውስጥ ፈጽሞ ዋጋ ጨምሮ የማይገኘው አገልግሎት ኢንሹራንስ ነው፡፡ ከዓመት ወደ ዓመት ዋጋው እየቀነሰ የሚገኘው ብቸኛ አገልግሎት ኢንሹራንስ መሆኑን በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያን የኢንሹራንስ ገበያ የሚከታተሉ የውጭ ኢንሹራንስ ባለሙያዎች የእናንተ የአገልግሎት ክፍያ ‹‹ፕሪሚየም›› ሳይሆን ‹‹ፍሪሚየም›› ነው እያሉን ነው፡፡ እንዲያውም የዓለም አቀፍ አማካሪዎች የኢትዮጵያን የኢንሹራንስ ገበያ በፍርኃት መመልከት ጀምረዋል፡፡ ጠንቀቅ ብላችሁ ልታስቡበት ይገባል እያሉ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በእርግጠኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ የአገልግሎትም ሆነ የሌሎች ምርቶች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲሄድ፣ ዋጋው እየቀነሰ የመጣው ኢንሹራንስ ብቻ ነው ብሎ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የመድን ሽፋን ዋጋ በተለየ ሊቀንስ የቻለበት ምክንያቱ ምንድነው? ኢኮኖሚው እያደገ ሲሄድ በዚያው ልክ የአገልግሎት ዋጋው ሊጨምር ይችላል ተብሎ ይታሰባልና በተቃራኒው የኢንሹራንስ ዘርፉ በተለየ የዋጋ ማሽቆልቆል አጋጥሞታል የሚባለው ለምንድነው? ምክንያቱስ ምንድነው?

አቶ ያሬድ፡- ፊት ለፊት እንድንነጋገርበት የማንፈልገው አንድ ሀቅ አለ፡፡ አንድ ኢንሹራንስ ኩባንያን ከምሥረታው ጀምሮ ብናየው የመመሥረቻ ካፒታሉ እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ ኩባንያ ስትመሠርት በጠንካራ መሠረት ላይ መሆን አለበት፡፡ በባለሙያዎች የታገዘና ሌሎች የደረሱበት ለመድረስ የሚያስችል ዝግጅት መደረግ አለበት፡፡ አሁን እዚህ እየሆነ ያለው ይህ አይደለም፡፡ እንደ ምንም ካፒታል ይሰበሰባል፣ ካፒታሉ ከተሰበሰበ በኋላ የሰው ኃይል ፍለጋ ውስጥ ስትገባ የሌሎች ኩባንያዎች ሠራተኞች ላይ ነው ዓይንህን የምትጥለው፡፡ ሠራተኞችን በማማለል ማስኮብለል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ገበያ ተብሎ የሚወጣው፣ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር የተመሠረተ ደንበኝነት ያላቸውን ኩባንያዎች እየሄዱ በዋጋ ሰበራ ማማለል ይሠራል፡፡ እነዚህ ነገሮች ውጤታቸው ምንድነው ስንል አሁን በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ በሰፊው እየተንሰራፋ ያለው የአጭር ጊዜ ውጤትን አጉልቶ የማሳየት ጉጉት ወይም ፈረንጆቹ እንደሚሉት ‹‹ሾርት ተርሚዝም›› የሚሉትን ዓይነት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከሼር ሆልደርስ ተፅዕኖና ጉጉት ጀምሮ የሚታየው ትርፍ፣ ትርፍ የሚል ነው፡፡ ትርፉን ለማምጣት የረዥም ጊዜ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ የሰው ኃይል ግንባታና ሌሎች ብዙ ነገሮች ይጠይቃል፡፡ አንድ ኩባንያ እዚህ ላይ ምን ብቃት አለው? ምን ዝግጅት አለው? ጠንካራ ኩባንያ ተገንብቷል ወይ? የሚለው ላይ አያተኩርም፡፡ ጥያቄው ሁሉ ዘንድሮ ትርፉ ስንት መጣ ነው የሚለው፡፡ ለምሳሌ የአንድ ኩባንያን የሒሳብ መዝገብ የሚያይ ሰው የለም፡፡ ሁሉም ሰው ትርፉና ኪሳራውን ነው የሚያየው፡፡ እንዲህ ባሉት ግፊቶች ማኔጅመንቱም ሆነ ቦርዱ ጉጉት ያድርበታል፡፡ ባለአክሲዮኖችን ለማስደሰት የመሄድ ነገር አለ፡፡ የትርፉ ቁመና ምን ይመስላል የሚለውን በደንብ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ እናንተንም ስታዘብ ትርፉ ላይ ነው የምታተኩሩት፡፡ በትክክል ዕዳው ምን ይመስላል? የሚለውንም ማየት አለባችሁ፡፡ በረዥም ጊዜ ዕቅዱና ሊያስገኝ የሚችለውን ጠቀሜታ መፈተሽ አለባችሁ፡፡ ዘመናዊ አይሲቲ ላይ ኢንቨስት አድርጓል ወይ? ተተኪ የሰው ኃይል በማፍራት ምን ያህል ተጉዟል? የሚሉትን መመልከት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው አሁን ባለው ደረጃ በአገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ያለው አስተዋጽኦ እጅግ አነስተኛ እንደሆነ በተለያዩ ሪፖርቶች ይገለጻል፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ኢኮኖሚው ላይ ያለው አስተዋጽኦስ እንዴት ይታያል? እያደገ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ ያሬድ፡- የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን በአገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን አስተዋጽኦና የሚገኝበትን ደረጃ የምንመለከትባቸው ሁለት ዋና ዋና መንገዶች አሉ፡፡ የመጀመርያው የአገሪቱ የነፍስ ወከፍ የዓረቦን ክፍያ የምንለው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የኢንዱስትሪው አጠቃላይ የዓረቦን ገቢ ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት (GDP) ያለው ድርሻ ወይም ‹‹ኢንሹራንስ ፔኔትሬሽን ሬት›› የምንለው ነው፡፡ ይህንን ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ስናወዳድረው እጅግ ገና መሆናችንን ያሳያል፡፡ ለምሳሌ ጎረቤት ኬንያን ብንወስድ የነፍስ ወከፍ የዓረቦን ክፍያ 40 ዶላር ነው፡፡ እንደ ሞሮኮ ያሉ አገሮች 104 ዶላር ደርሰዋል፡፡ በአፍሪካ ከፍተኛ የሚባለው የደቡብ አፍሪካ ነፍስ ወከፍ ድርሻ 842 ዶላር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ግን ሦስት ዶላር አልሞላችም፡፡ የኢንዱስትሪው አጠቃላይ የዓረቦን ገቢ ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት አንፃር ሲታይም የኢንሹራንስ ድርሻ 0.4 በመቶ ነው፡፡ የኬንያን ኢንሹራንስ ካየኸው ግን 2.6 በመቶ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚው አስተዋጽኦ የሚያደርገው 13.8 በመቶ ነው፡፡ እንግዲህ በእነዚህ በሁለቱ ዋና ዋና መሥፈርቶች ስናየው የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ የነፍስ ወከፍ ገቢም ሆነ ከአገሪቱ ከአጠቃላይ ምርት አኳያ ድርሻው እጅግ አነስተኛ የሚባል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ለምን ሆነ?

አቶ ያሬድ፡-  ይህ ለምን ሆነ ለሚለው ጥያቄ የመጀመርያው መልስ ኢንዱስትሪው ያለበት የመዋቅር ቅርፅ ሁኔታ ነው፡፡ ይህም አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ ተመሥርቶ በገበያ ተወዳዳሪነት አልፎ የሚጓዝበት መንገድ፣ ወይም አስተዳደራዊ መዋቅሩ ምን ይመስላል ለሚለው መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ኢንሹራንስ በብሔራዊ ባንክ በአንድ ዲፓርትመንት ቁጥጥር ውስጥ ነው የሚያልፈው፡፡ የዛሬ 45 ዓመት ወደ ኋላ ሄደን ብናየው እጅግ በጣም የተሻለ የኢንሹራንስ አስተዳደርና መዋቅር ነበረው ማለት ይቻላል፡፡ ራሱን ችሎ የሚሠራበት ሁኔታ ነበር፡፡ ኢንሹራንስ እንዲያድግና እንዲጎለብት ከተፈለገ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ወይም ራሱን የቻለ ኮሚሽን ያስፈልገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወጥቶ ለብቻው በሚዋቀር ተቋም መመራት አለበት ለማለት ነው?

አቶ ያሬድ፡- አዎ፡፡ ለብቻው ወጥቶ በኢንሹራንስ ጉዳዮች ላይ በጥልቅ የሚሠራ ኮሚሽን ያስፈልገዋል፡፡ የዕለት ተዕለት የኦፕሬሽን ችግሮችን ከመፍታትም ሆነ ኩባንያዎችን በማገዝ አዳዲስ ፖሊሲዎችን እንዲያመነጭ፣ እንዲሁም አሁን ያለውን ዝቅተኛ አፈጻጸም ለመቀየር ከተፈለገ ራሱን በቻለ ኮሚሽን መመራት አለበት፡፡ በቶሎ ለገበያ ከማቅረብ አልፎ የረዥም ጊዜ ስትራቴጂያቸውን እንዲነድፉ ይህ ኮሚሽን ከፍተኛ ዕገዛ ይኖረዋል፡፡ የኮሚሽኑ አወቃቀርም ምርጥ አዕምሮ ባላቸው የኢንሹራንስ ባለሙያዎች በመሆኑ ለለውጥ ወሳኝ ነው፡፡ የኮሚሽኑን ቦርድ ግን መንግሥት ሊሰይም ይችላል፡፡ የቦርድ ሰብሳቢም ብሔራዊ ባንክ ሆኖ ሊሠራበት ይቻላል፡፡ ግን በቦርዱ ውስጥ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ተወካይ ይኖራሉ፡፡ የኢንሹራንስ ተጠቃሚዎች ተወካዮችም ይኖሩታል፡፡ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በቦርዱ ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ፡፡ የኢንሹራንስ ኮሚሽን ከዚህ አልፎ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ ቅሬታ ተቀብሎ ጣልቃ ገብቶ የመፍታት ጉልበትና አቅም ያለው በመሆኑ፣ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቁጥጥር ሥር ወጥቶ በኮሚሽን ደረጃ መዋቀር አለበት፡፡  

ሪፖርተር፡- የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ራሱን ችሎ በኮሚሽን ሥር መሆን አለበት የሚለው አመለካከት በተደጋጋሚ ሲቀነቀን ቆይቷል፡፡ አሁንም የግድ ነው እያሉኝ ነው? የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው እንዲያድግ ከተፈለገ የዚህ ኮሚሽን መቋቋም ወሳኝ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? የሌሎች አገሮችስ ልምድ ምን ይመስላል? በኮሚሽን ሥር የሚተዳደሩ ውጤታማ መሆን ችለዋል?

አቶ ያሬድ፡- አሁንም ኬንያን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ የኬንያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በኢንሹራንስ ኮሚሽን ነው የሚተዳደሩት፡፡ የኬንያ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ኃላፊ በኢንሹራንስ ነው የሚሾመው፡፡ ኮሚሽኑ እንደ ተቋም የሚዋቀረው ግን በጣም በሠለጠኑ የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ነው፡፡ ሰፊ ነው፡፡ ሁሉንም ኩባንያዎች ካልሆነ በስተቀር ኢንዱስትሪው በደንብ እንዲያድግ ከተፈለገ በተቆለፈለት ቦይ ብቻ እንዲሄድና እንዲፈስ ከማድረግ ይልቅ፣ ሰፋ ብሎ እንዲያድግ የማገዝ ሥራ መከናወን አለበት፡፡  ይህንንም ለማድረግ የኮሚሽኑ መቋቋም ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡

ሪፖርተር፡- የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣኑ ከብሔራዊ ባንክ ሥር ወጥቶ ራሱን ችሎ በኮሚሽን ደረጃ መዋቀሩ መፍትሔ መሆኑ ከታመነበት፣ ይህንን ሐሳብ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረባችሁ ይነገራልና ምን ምላሽ ይሰጣል ብላችሁ ትጠብቃላችሁ? ደግሞስ እናንተ ምን ያህል ገፍታችኋል?

አቶ ያሬድ፡- አዎ የማኅበሩ አመራሮች ከክቡር ገዥው ዶ/ር ይናገር ደሴ ጋር ቀጠሮ ይዘን በጉዳዩ ላይ ጥሩ ውይይት አድርገናል፡፡ በዚህ ነገር በጣም ደስተኞች ነን፡፡ ጅምሩ መልካም መሆኑን ዓይተናል፡፡ ክቡር ገዥውም አሁን ባለው አካሄድና ይዞታ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ለውጥ እንደማያመጣና የተለየ የዕድገት ደረጃ ላይ ይደርሳል ብለው እንደሚያምኑ ጭምር ገልጸውልናል፡፡ አሁን እየተኬደበት ባለው መንገድ ኢንዱስትሪውን ማሳደግ እንደማይቻልና ራሳቸውም እንደማያምኑ በግልጽ ነግረውናል፡፡ እኛም እንደ መፍትሔ የአጭርና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ክንውን ብለን ከያዝናቸው ዕቅዶቻችን ውስጥ አንዱ ይኼ መዋቅራዊ ጉዳይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን ጉዳይ ብሔራዊ ባንክ ጭምር ያምንበታል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢንሹራንስ ዘርፉ ከብሔራዊ ባንክ ወጥቶ ራሱን መቻል እንዳለበት ማለት ነው?

አቶ ያሬድ፡- አዎ፡፡ ብሔራዊ ባንክ ያምንበታል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ በመከርንበት ስብሰባ ላይም ተነስቷል፡፡ ስለዚህ መንግሥት አሁን በተጀመረው ሪፎርም ይህንን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶት ዛሬ ነገ ሳይል ሥራውን ይጀምራል ብለን እናስባለን፡፡ እኛ ለውይይቱም ሆነ ለጥናቱ ይጋብዙናል ብለን እየጠበቅን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ከታመነ ጉዳዩን በቶሎ ለመፈጸም የእናንተ ግፊት ምን ያህል ነው?

አቶ ያሬድ፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት ይኼ መዋቅራዊ ችግር ቢኖርም፣ በግል የውስጥ ችግር የለንም ማለት አይደለም፡፡ ለራሳችን ዕድገት ችግር የፈጠሩብን ውስጣዊ ችግሮች አሉብን፡፡ ከምሥረታው ጀምሮ ከአቅማችን ጋር የተያያዙ፣ የምንዘረጋቸው ኦፕሬሽናልና የስትራቴጂ ጉዳዮች ምን ላይ ነው የሚያተኩሩት?  የዛሬን ትርፍ ነው ወይስ በዘላቂነት ኩባንያ እንዲያድግ የማድረግ ነው? ባለሀብቶችም ይህንን ቢጠይቁ ደስ ይለናል፡፡ የኩባንያውን እውነተኛ ጥንካሬ ከአንድ ኩባንያ ላይ ሥራ ነጥቆ አምጥቶ ትርፋማ ነኝ ስላለ ነው? ዘላቂ ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርቷል ወይ? ዘለቄታዊ ዕድገት አለው ወይ? የሚሉና የመሳሰሉት ላይ ችግሮች አሉ፡፡ ግልጽ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ከተነሳ የአገልግሎቱ ዓይነት ውስን መሆን ራሱ እንደ ችግር የሚታይ ነው፡፡ ኢንዱስትሪ ውስጥ አዳዲስ የኢንሹራንስ አገልግሎቶች የሉም፡፡ ጊዜውን ያገናዘቡ አዳዲስ የመድን ሽፋኖች አይሰጡም፡፡ ፈጠራ የለም፡፡ ኅብረተሰቡም ስለኢንሹራንስ ጠቀሜታ ብዙ ግንዛቤ የለውም፡፡ ስለዚህ ተደራሽነቱ ተገድቧል፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለው የኢንሹራንስ ሥራ ከመኪናና ከመሰል የኢንሹራንስ ሽፋን አገልግሎቶች ጋር ብቻ የተያያዘ ሆኖ የመቆየቱ ምክንያት ምንድነው ብለው ያምናሉ?

አቶ ያሬድ፡- አንዱ ትልቁ ችግር ግንዛቤ ነው፡፡ ኢንሹራንስ በኅብረተሰቡ ዘንድ ጠቀሜታው በደንብ መታወቅ አለበት፡፡ በደንብ በጥልቀት እንዲታወቅ ካለመሥራት የመጣ ነው፡፡ በኢንሹራንስ ላይ ግንዛቤ እንዲፈጠር በደንብ አልተሠራም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ማድረግ ግን የማን ድርሻ ነበር?

አቶ ያሬድ፡- ይኼ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ከእኛ መጀመር ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ እኛ መሥራት አለብን፡፡ በጋራ በማኅበራችን በኩል መሥራት አለብን፡፡ በነገራችን ላይ አሁንም አጀንዳ ነድፈን አንዱ እየተንቀሳቀስንበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ኢንሹራንስ በግልጽ በኅብረተሰቡ ዘንድ ጠቀሜታው በድንብ መታወቅ አለበት፡፡ ለምሳሌ የሞተር ኢንሹራንስ ለምንድነው በጣም የጨመረው ብትል አስገዳጅ በመሆኑ ነው የሚለው ይበዛል፡፡ በአዋጅ አስገዳጅ በመሆኑ ነው፡፡ ማሪን ኢንሹራንስንም ብናየው ለኤክስፖርት ሌተር ኦፍ ክሬዲት ለመክፈት ወይም ዕቃ ለማስገባት ግዴታ የማሪን ኢንሹራንስ መገዛት ስላለበት ነው፡፡ የሠራተኛ ጉዳት ዋስትናም እንዲሁ ነው፡፡ ስለዚህ ብዙዎቹ እንዲያውም 80 በመቶ አካባቢ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ገቢ የሚያመጡት አስገዳጅ መድኖች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ማለት እንግዲህ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በአስገዳጅ መድኖች ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን ያሳያልና ጤናማ ነው ሊባል ይችላል?

አቶ ያሬድ፡- ጤናማ አይደለም፡፡ ኢንሹራንስ በፍላጎትና በምርጫ እንዲሆን መሥራት አለብን፡፡ ለምሳሌ ከሁሉም የመድን ሽፋኖች በፍላጎት እየተገዛ የሚኖረው የሕይወት ኢንሹራንስን እናንሳ፡፡ ለሕይወት ኢንሹራንስ ደንበኛ ገበያ ለመፍጠር በጣም ጥሩ ሁኔታ ነው የምንለው፣ መካከለኛ ገቢ ላይ የደረሱ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖር አስፈላጊ ነው፡፡ እንደምታውቀው ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ኑሮ ላይ የሕይወት መድን ብለህ ላታስብ ትችላለህ፡፡ ብዙ የለም፡፡ በሚገርም ሁኔታ ግን ባለፉት አሥር ዓመታት ያለው ባለ መካከለኛ ገቢ እያደገ መጥቷል፡፡ ይህ ማለት ለሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን መክፈል የሚችል ኅብረተሰብ አለ፡፡ የሕይወት ኢንሹራንስን ለመሸጥ ግን ፕሮጀክቶቻችንን ስንመለከታቸው ሃያና ሰላሳ ዓመታት በሼልፍ ላይ የቆዩ ናቸው፡፡ አዲስ በተለይ ወጣቱን ትውልድ ሊስቡ የሚችሉና ጠቀሜታቸውም ጎልቶ የሚታይ ለምሳሌ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎቶችን እያቀረብን አይደለንም፡፡ እንደሚታወቀው አዲሱ ትውልድ ወደ ባንክና ኢንሹራንስ ቅርንጫፎች መሄድን ብዙም የሚደግፈው አይደለም፡፡ በአንፃሩ ያለን ፕላን ደግሞ ቅርንጫፎች ማብዛት ነው ተብሎ በስትራቴጂና በዕቅድ ተቀምጧል፡፡ ግን ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ ግብዓቶችንና አገልግሎቶችን በሚገባ አልፈጠርንም፡፡ ሰው የሚፈልገው ቀለል ያለ ብዙ የወረቀት ሥራዎች ያልበዙበት አገልግሎትን ነው፡፡ የካሳ ክፍያን በቀላሉ ማግኘት ይፈልጋል፡፡ እውነት ለመናገር እዚህም እዚያ በየኩባንያዎቹ ሙከራዎች ቢኖሩም ገና ነው፡፡ የተባበረ ጥረት የለም፡፡ ተቆጣጣሪውም ቢሆን እነዚህን አገልግሎቶች የማበረታታት፣ ወይም እንዲህ ያሉ አገልግሎቶች ሲቀርቡ አገልግሎቶችን አፅድቆ በፍጥነት ወደ ገበያ እንዲገቡ የማድረግ አቅሙ ገና ነው፡፡

አሁንም ኬንያን ብጠቅስልህ፣ የኬንያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወረቀት አልባ እየሆኑ ነው፡፡ ብዙ ኢንሹራንስ ኩባንያዎቻቸው ሙሉ በሙሉ ወደ ወረቀት አልባ አገልግሎት ተሸጋግረዋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው አላደገም፣ ግንዛቤ አልተፈጠረም ስንል የእኛ አቅም ደካማነት ተነስቶ እንደገና ምን ያህል አገልግሎቶችን ፈጥረን አቅርበናል ካልን ገና ነን፡፡ አሁንም ደንበኞቻችንን የምንጨቀጭቀው ያንኑ የድሮውን 30 ዓመት የቆየውን አገልግሎት ይዘን ነው፡፡ ብዙ አዳዲስ አሠራሮችን መሞከርና መጀመር አለብን፡፡ በዚህ ረገድ አንዳንድ የተጀመሩ ጥናቶች አሉ፡፡ ኅብረተሰቡም ግንዛቤው እየጨመረ ከመጣ እነዚህ ችግሮች ሊፈቱ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያለው የኢንዱስትሪው ችግር እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ ነው ብለው ያስባሉ? ምክንያቱም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ፣ እያለ የኢኮኖሚውን ዕድገት የመጠነ የኢንሹራንስ አገልግሎት ለመስጠት አልተቻለምና በታሰበው ልክ እንዴት ለውጥ ይመጣል? ደግሞስ ኢኮኖሚውን የመጠነ የመድን አገልግሎት ያለመኖርስ ውሎ አድሮ ችግር አይፈጥርም?

አቶ ያሬድ፡- እንግዲህ ኢኮኖሚው ላይ ያለውን አስተዋጽኦ ስንመለከት የመንግሥትም ሆነ የግል ዋና ዋና የኢኮኖሚ አውታሮች (እኛ ሪስኮች የምንላቸው) ሁሉም የተሸፈኑ ናቸው፡፡ ምናልባት የሚከፍሉት ዓረቦን ከዓመት ወደ ዓመት እያነሰና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን እያቀጨጨ ይምጣ እንጂ አደጋው ሽፋን ማግኘቱ አልቀረም፡፡

ሪፖርተር፡- መሉ ለሙሉ የኢንሹራንስ ሽፋን አላቸው ማለት ይቻላል?

አቶ ያሬድ፡- የተሸፈኑ ናቸው፡፡ ከተሽከርካሪ ኢንሹራንስ ጀምሮ እስከ እርሻ ድረስ ዋና ዋና ሜካናይዝድ የሚባሉ እርሻዎች ጭምር ሙሉ ለሙሉ የመድን ሽፋን አላቸው፡፡ የሚበዙት ማለቴ ነው፡፡ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ኢኮኖሚውን ደግፏል ወይ ከተባለ አዎ ከሚችለው በላይ ወገቡ እስኪተረተር ደግፎ ተሸክሞታል፡፡ ለዚያውም የሚገባውን የዓረቦን ገቢ ሳያገኝ ማለት ነው፡፡ ግን የታወቀ ነው የሚሰበረው የኢንሹራንስ ኩባንያ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ያሬድ፡- ለምሳሌ በተሽከርካሪዎች የሚደርሱትን የአደጋዎች መጠን ስናይ የተሽከርካሪ ኢንሹራንስ አክሳሪ እየሆነ እየመጣ ነው፡፡ ግን እንዲህም ሆኖ ዋጋውን እየቀነሰ ዓረቦኑን ከመሰብሰብ የተገታ የለም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁንም ከሚሰበሰበው አጠቃላይ ዓረቦን ትልቁን ድርሻ የያዘው ይኸው የሞተር ኢንሹራንስ መሆኑስ?

አቶ ያሬድ፡- አዎ፡፡ ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው እሱ ነው፡፡ እዚህ ላይ የተቆጣጣሪውን ጣልቃ መግባት ይጠይቃል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን? በምን ዓይነት መልክ?

አቶ ያሬድ፡- አሁን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እርስ በርሳቸው ተናንቀው ሊጠፉ ደርሰዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- ምክንያቱን ሊያብራሩልኝ ይችላሉ? በምን ምክንያት ነው ተናንቀው ሊጠፉ ነው የሚባለው?

አቶ ያሬድ፡- በዋጋ ሰበራ ነው፡፡ ፈጽሞ ያልተገባ ዋጋ እየተሰጠ ኢንዱስትሪውን አደጋ ላይ እየጣለው ነው፡፡ አንድ ምሳሌ ልስጥህ፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ የአንድ የንግድ የጭነት ተሽከርካሪ የዓረቦን ክፍያ የተሽከርካሪውን ዋጋ ከስድስት እስከ ሰባት በመቶ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን ከአንድ በመቶ በታች ነው፡፡ የቤት መኪኖችንና የመሳሰሉትን ብትወሰድ ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ ለዓረቦን የሚከፈለው የተሽከርካሪውን ዋጋ በአማካይ ከ2.5 እስከ ሦስት በመቶ የሚሆነው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስትመጣ ግን ከ0.75 በመቶ በታች ነው፡፡ እንዲያውም በብዛት 0.5 በመቶ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢንዱስትሪው ተያይዞ ሊጠፋፋ የደረሰበትን ደረጃ ነው፡፡ ይህ መስተካከል አለበት፡፡ ምናልባት ግን በሌሎች አገሮችም እንደተደረገ ነው፡፡ ይህንን የዋጋ ሰበራ ለማስቀረት መከናወን የሚኖርበት ሥራ አለ፡፡ ይህም አነስተኛ ወይም የወለል ዋጋ ማስቀመጥ ነው፡፡ ይህን ዓይነት አሠራር ለመተግበር ከብሔራዊ ባንክ ጋር በተደረገ ውይይት፣ ብሔራዊ ባንክ ጉዳዩን የሠለጠነ ኢንሹራንስ አስሊ በምንላቸው ተጠንቶ ይቅረብልኝ ብሏል፡፡ በዚሁ መሠረት ማኅበሩም ባለሙያ ቀጥሮ እያስጠና ይገኛል፡፡ ይህ ማለት በአማካይ የመጨረሻው ዋጋ ምን መሆን አለበት የሚለውን ይለያል፡፡ ይህ ዋጋ ገዥ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ከተገለጸው ዋጋ በታች መውረድ አይቻልም፡፡ በሌሎች ታሪፎች ላይ ለምሳሌ በንግድ መርከብና በአየር መንገድ ላይ የሚወጡ ታሪፎች እንዳሉ ሁሉ፣ በኢንሹራንስ አገልግሎትም ይኼ ቢወጣ ይጠቅማል፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጠነከሩ ማለት ተመልሰው ለኅብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ያድጋል፡፡ አሁን ያለው የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የዋጋ ሰበራ አደጋ እየሆነ ነው፡፡ ችግሩ ሁሉም አገልግሎቱን መመልከት አይፈልግም፡፡ ዋጋውን ብቻ እየተመለከትክ ከሄድክ አስቸጋሪ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህም ሆነው የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ እያተረፉ ነው፡፡ አሁንም ትርፍ ትርፉን አትይ ካላሉኝ አትራፊ ሆነናል እያሉ ሪፖርት እያደረጉ ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ይህ የዋጋ ሰበራ እያቀጨጫቸው ነው የሚባል ከሆነ ሁለቱን ነገሮች እንዴት ያስታርቁልኛል?

አቶ ያሬድ፡- አትራፊ ስንል ምን ማለታችን ነው? ቀደም ብዬ እንዳልኩህ አንድ ኩባንያ በጣም ትርፋማ ነኝ ሲል ውስጣዊ ብቃቱ፣ ለነገ ያደረገው አስተዋጽኦና የዕዳው ሁኔታ በደንብ መታየት አለበት፡፡ የሒሳብ ሪፖርቱ ላይ ያለው ትርፍና ኪሳራ ብቻ አይደለም፡፡ ሁለተኛ ግን ተገኘ የሚባለው ትርፍ በቂ ትርፍ ነው ወይ? እንዲያውም ለመሠረተ ልማት ትልቅ በጀት መድበህ እንዳታተርፍ የሚያደርግህ የትርፍ መጠን ማነስ ነው፡፡ በኢንሹራንስ ትርፍ የመጨረሻው ዝቅተኛ ነው ከተባለ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትርፍ ነው፡፡ ኢንሹራንስ በጣም ትርፋማ እንዲሆን አደጋ ቁጥጥር ላይ በነፃ ኢንቨስት የሚያደርግባቸው ነገሮች አሉ፡፡ ብዙ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ነው፡፡ ነገር ግን ኩባንያዎች የሚያገኙት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ትርፍ በረዥም ርቀት እንዳይሄዱ አድርጓቸዋል፡፡ አደጋ ቀነሰ ማለት ትርፋማነታቸው ጨመረ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንዴ ከአገልግሎት ሰጪዎች ከሚመጣው ግፊት የተነሳ ባዶ ሳጥን መሸጥ የሚባል ነገር አለ፡፡ ትልቅ ፓኬት በስጦታ ወረቀት ጠቅልለህ መሸጥ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢንሹራንስ አገልግሎት የምታገኘው በከፈልከው ልክ ነው፡፡ ሁሉም ኢንሹራንስ የሚገዙ ሰዎች የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መድን ሰጪ ሳይሆን፣ እንደ ሥጋት አመራር አማካሪ አድርገው ቢመለከቱዋቸው ደስ ይለኛል፡፡ የአደጋ ሥጋቶች ምንድናቸው? ይህንን በምን መንገድ ልቀንስ? ብሎ በኋላ መተላለፍ ያለባቸው አደጋዎች ብቻ ተመርጠው ነው ኢንሹራንስ የሚገባላቸው፡፡ እዚህ ላይ ብንሠራ ብዙ ነገሮችን እንቀይራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ እንዳያድግ ምክንያት ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱት ውስጥ የኢንሹራንስ ሽፋን ውሎች ግልጽ ያለመሆንና ውስብስብነት ነው፡፡ ፖሊሲዎቹ በሙሉ በውጭ ቋንቋዎች መቅረባቸው ችግር ነው፡፡ ስለዚህ አንድ አገልግሎት ለማግኘት የመጣ ደንበኛ የፖሊሲው አተገባበር በሚገባው ቋንቋ አለመዘጋጀቱ እንደ ችግር ይታያል፡፡ ይህ ችግር እንዴት ይፈታል?

አቶ ያሬድ፡- እውነት ነው፡፡ ችግሩ ይታያል፡፡ በተለይ የውሉ ድንጋጌዎችና መንፈሱ በሚተረጎምበት ወይም በካሳ ክፍያ ወቅት አንዳንድ ነገሮች ላይ የሚነሳ ጥያቄ አለ፡፡ ለምሳሌ ይኼ ነገር አልገባኝም፣ አልተረዳሁትም ነበር የሚሉ ነገሮች ይመጣሉ፡፡ ግን መሠረታዊው ነገር መነሻውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ የመድን ውሉ ምንጩ የት ነው? ብለን ከጠየቅን ምንጩ ከኢትዮጵያ ውጭ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ ሰዎች የሚያስቡት የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አቅማቸው አነስተኛ ከመሆኑ የተነሳ ሥጋት ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ የመክፈል አቅማቸውና የመሳሰሉትን ገምተው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይ የጠለፋ መድን ጽንሰ ሐሳብን በደንብ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እንደ ህዳሴ ግድብ ባሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶች አደጋ ቢደርስ ያንን መልሶ የመተካት አቅሙ ያለው የአገር ውስጥ የኢንሹራንስ ኩባንያ የለውም፣ አይኖረውም፡፡ ስለዚህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ የጠለፋ ዋስትና የሚሰጡ ኩባንያዎች የጠለፋ ዋስትና ይገዛሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ብሔራዊ ባንክም በሚያደርገው ቁጥጥር የጠለፋ ዋስትና የገዙት በጣም ምርጥ ከሚባሉት ነው፡፡ ይኼ ለኅብረተሰቡም ትልቅ ጠቀሜታ ያለው፣ ግን ብዙ ጊዜ የሚዘነጋ ነው፡፡ ለማንኛውም የውሎቹ መሠረት ከጠለፋ መድን ሰጪዎች የሚመነጭ ነው፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በሙሉ የሚሸፈኑ፣ እነዚህ ደግሞ የማይሸፈኑ ናቸው ብለው ኢንሹራንስ ከተወለደበት ከ400 ዓመታት በላይ ቋንቋዎቹ ብዙም አልተቀየሩም፡፡ ጠንከር ያሉ የሕግ ቃላት በመጠቀማቸው ነው፡፡ እርግጥ በአንዳንድ ኩባንያዎች ቀለል ባለ ትርጓሜ ለማድረግ ሙከራዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ይህንን ጉዳይ በተጠናከረ ተሠርቶበታል ማለት አይቻልም፡፡ ይህ ማለት ግን ሽፋን የለውም ማለት አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኞቹ ንብረቶች ከተማ ውስጥ የምታያቸው ሕንፃዎችና ፕሮጀክቶች በዓለም ላይ ታዋቂ በሆኑ የጠለፋ መድን ሰጪ ኩባንያዎች ዋስትና አላቸው፡፡ ይኼ ጥሩ ነው፡፡ ሌላው ነገር ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንሹራንስ ያለበት ደረጃ አነስተኛ ነው ስትል፣ እንግሊዝ አገርም ሆነ በሌላው አገር የተሽከርካሪ ዋስትና ውልን ብንመለከት አንድ ዓይነት ነው፡፡ ጥቂት ከሆኑ ማጣፈጫዎችና ማሻሻጫዎች ካልሆኑ በቀር መሠረታዊ የውሉ መንፈስና ይዘት አንድ ዓይነት ነው፡፡ ስለዚህ ዋስትና ገቢዎች ይኼ ደስ ሊላቸው የሚገባ ነገር ነው፡፡ ኢንሹራንስ በዓለም ላይ አንድ ዓይነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የጠለፋ መድን የሚገባላቸውን ትተን የጤና ኢንሹራንስ ወይም የሕይወት ኢንሹራንስን ብንወስድ ግን፣ የውጭ ኢንሹራንስ ፖሊሲዎችን መሠረት የሚያደርግ መሆን አለበት ተብሎ አይታመንም፡፡ ፖሊሲውን በግልጽ ቋንቋ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ አሁን እንደምናየው ለሕይወት ኢንሹራንስ ሰዎች የማይገቡት ፖሊሲው ስለማይገባቸው ጭምር ነው ብለን ልንወስድ እንችላለን፡፡ እነዚህ የአገልግሎት ዓይነቶች እዚህ የተዘጋጁ ስላልሆኑ ነው ለሚለው ጥያቄ ምላሽዎ ምንድነው?

አቶ ያሬድ፡- እውነት ነው፡፡ ቅድም እንዳነሳነው አንዳንዴ የመንግሥት ተቆጣጣሪ አካሉ አስገዳጅ ሁኔታዎች መኖር ኢንሹራንስን የበለጠ እንዲታወቅ ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ያሬድ፡- ለምሳሌ ያነሳኸውን የጤና ኢንሹራንስ በሚመለከት የደመወዝ አቅሙ ከዚህ በላይ የሆነ ሰው የጤና ኢንሹራንስ መግዛት አለበት የሚል ነገር ቢቀመጥ፣ ለኅብረተሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብዬ አስባለሁ፡፡ የአንድ ቤተሰብን ውጤታማ ጉዞ ለማስቀጠል ጤንነት ወሳኝ ነው፡፡ ጤንነት ግን ምርጫ አድርገህ ብቻ የምትተወው ከሆነ አስቸጋሪ ነው፡፡ ኅብረተሰባችን እየተለማመደው ያለ ጉዳይ አይደለምና ከዚህ በላይ ደመወዝ ያለው ሠራተኛ የጤና ኢንሹራንስ መግዛት አለበት ቢባል ሁኔታዎች ይለወጣሉ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ የኢንሹራንስ ውሎችና ዝግጅቶች ለገዥው በሚገባው ቋንቋና መልክ እንዲቀርቡ የሚል አስገዳጅ ሁኔታ ቢመጣ ሁሉም ሰው የሚሠራበት ነው፡፡ የሬጉሌሽንና የኮሚሽን መኖርና የማስገደድ ሁኔታዎች ጥቅማቸው የሚለካው እዚህ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም በሠለጠኑት አገሮች የሚተገበርና የሚሠራበት ስለሆነ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላው ኢንዱስትሪውን ሊያጎለብት የሚችል የትምህርት ተቋም የለም፡፡ ኩባንያዎች ባለሙያዎችን እየተነጣጠቁ የቀጠሉበት አንዱ ምክንያት ኢንዱስትሪውን የሚመጥን የሠለጠነ ኃይል ለማፍራት ካለመቻል ጋር ይያያዛል፡፡ እንደ ችግር የሚነሳው ደግሞ የባንክና የኢንሹራንስ ባለሙያዎችን ያሠለጥን የነበረው ተቋም መክሰም ነው፡፡ አሁን በባለሙያ እጥረት ምክንያት በየራሳችሁ ማሠልጠን የጀመራችሁ አላችሁ? ኢንዲስትሪውን ለማሳደግ ሲታሰብ የትምህርት ተቋም ያለመኖሩስ ችግር አይደለም?

አቶ ያሬድ፡- እንደምታስታውሰው የባንክና መድን ማሠልጠኛ ተቋም ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበረው ነው፡፡ ለእኛም ግልጽ ባልሆነልን ምክንያት እንዲቆም ተደርጓል፡፡ በወቅቱ መንግሥት በወሰደው አቅጣጫ የሆነ ነው፡፡ ግን በአሁኑ ጊዜ ያንን አጠናክሮ መልሶ የመጀመር ሁኔታዎች በብሔራዊ ባንክ በኩል ያሉ ይመስለናል፡፡ እንዲያውም ማሠልጠኛው ድሮ እንደሚታወቀው በዲፕሎማ ደረጃ ነበር የሚያሠለጥነው፡፡ እውነተኛውን ፍላጎት ስንፈትሽ ግን በዲፕሎማ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲያውም ተጠናክሮ በዲግሪና ከዚያም ባሻገር ባሉ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞችና መርሐ ግብሮች ባለሙያዎችን ለማፍራት መዘጋጀት አለበት፡፡ በነገራችን ላይ ማኅበሩም በዚህ ጉዳይ ላይ በጥልቀት እየሠራ ነው፡፡ ለምሳሌ በኢንዱስትሪ ውስጥ ያለው የስኬል ክፍተት ምንድነው? ፈትሸን ለዚህ የሚሆኑትን የአጭር ጊዜ ሥልጠና ለመካከለኛና የረዥም ጊዜ ትምህርት የሚለውን ለይተናል፡፡ እዚህ ላይ ሌሎች ባለድርሻዎችም እንዳሉ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፋይናንስ ዘርፍ ቅበላው አነስተኛ ቢሆንም አዲስ የሞከረው ጅማሮ አለ፡፡ 25 ተማሪዎችን በድኅረ ምረቃ ይወስዳል፡፡ ግን አብዛኛው የባንክ ዘርፍ ነው፡፡ የኢንሹራንስ ተማሪዎችን ስናያቸው በየአንዳንዱ ባች አነስተኛ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች በኢንሹራንስ ዘርፉ ካሪኩለም ቀርፀው ባለሙያዎችን ቢያፈሩ ይደገፋል፡፡ በዚህ ረገድ ፕላን ያላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካሉ ማኅበሩ ማናቸውንም ዕገዛ ለማድረግና አብሮ ለመሥራት ዝግጁ ነው፡፡ አንዳንድ ኩባንያዎች በራሳቸው መንገድ መጓዝ ጀምረዋል፡፡ ለምሳሌ ኒያላ ኢንሹራንስ ኩባንያ ላለፉት ዓመታት ከየኮሌጁ በተለያዩ ዘርፍ የተመረቁ ተማሪዎችን በመመልመል፣ በዘርፉ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎች ቀጥሮ ከብሔራዊ ባንክ ጋር በመሆን ሥልጠና ይሰጣል፡፡ እስካሁን 75 ባለሙያዎችን አፍርቷል፡፡ በየዓመቱ 25 ባለሙያዎችን የማፍራት ሥራ ጀምሯል፡፡ ሌሎችም እንዲሁ እያደረጉ ነው፡፡ ውጤታማ የሚሆነው ግን በጋራ ተተኪ ባለሙያዎችን እንዴት እናፍራ በሚለው ላይ በመሥራት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርብ ከተጀመረው የፋይናንስ ተቋማት ሪፎርም ጋር ተያይዞ ባንኮች ይሻሻላል ብለው ያቀረቧቸው አንዳንድ መመርያዎች እንዲሻሻሉላቸው እየተደረጉ ነው፡፡ አሁንም ሊፈጸምልን ይገባል ያሉትንም ምላሽ እየጠበቁ ነው፡፡ በእናንተ ረገድ አላሠራ ያሉ መመርያዎች እንዳሉ ይታመናል፡፡ በዚህ ረገድ እናንተ መስተካከል ይገባቸዋል ብላችሁ ያሰባችኋቸውን መመርያዎች እንዲስተካከሉ እያደረጋችሁት ያለው እንቅስቃሴ ምንድነው? የምትጠብቁት ነገር አለ? የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን በተመለከተ መሻሻል አለባቸው ብላችሁ ያቀረባችኋቸው ጥያቄዎችስ? በየትኞቹ ጉዳዮች?

አቶ ያሬድ፡- በነገራችን ላይ ብሔራዊ ባንክ ለእኛም ግብዣውን አቅርቦልናል፡፡ እንዲሻሻል በምትፈልጉት ጉዳዮች ላይ አዋጁን ጨምሮ ሐሳብ አቅርቡ ተብሏል፡፡ እኛ በዚህ መሠረት ሐሳቦች አቅርበናል፡፡ ለምሳሌ በስፋት እየተነሳ ያለው የውጭ ዜግነት ያላቸውን ባለአክሲዮኖች በተመለከተ እኛም ጥያቄ አቅርበናል፡፡ በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ኢትጵያውያን ባለአክሲዮን ሆነው ቢገቡ የበለጠ ጠንካራ መሆንና ትርፋማ መሆን ይቻላል የሚል ጠንካራ አቋም አለን፡፡ ማኅበሩም ይህንን በደንብ ተወያይቶበት ጉዳዩ እንዲሻሻል አቅርበናል፡፡ ትውልደ ኢትጵያውያን በባንክ ሥራ እንዲሳተፉ እንደተፈቀደው ሁሉ በኢንሹራንስ ዘርፉም ተግባራዊ ይደረጋል የሚል እምነት አለን፡፡ ሌላው ለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ዕድገት መሠረት የሚሆነው ኢንቨስትመንት ከመሆኑ አንፃር፣ በዚህ ረገድ ያለው አሠራር እንዲሻሻል ጠይቀናል፡፡ በሌላው አገርም ውጤታማ መሆን የሚቻለው በኢንሹራንስ ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ነው፡፡ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ ፈጽሞ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ውጤታማ በሚሆን ኢንቨስትመንት ላይ እንደ ፍላጎታቸው የሚያንቀሳቀስና የሚያስኬድ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ማለት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ኢንቨስትመንት ላይ የሚያውሉት የገንዘብ መጠን አነስተኛ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው?

አቶ ያሬድ፡- አዎ! አሁን ባለው መመርያ አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ 65 በመቶው የሚሆነውን ገንዘቡን መያዝ አለበት፡፡ ኢንቨስትመንት ላይ ማዋል አይችልም፡፡ ኢንቨስት ማድረግ የሚችለው 35 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥም በባንክ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ የምትችሉት ከአምስት በመቶ መብለጥ የለበትም የሚል ነው፡፡ በሪል ስቴትና በመሳሰሉት ኢንቨስትመንቶች ደግሞ መሳተፍ ያለባቸው ከአሥር በመቶ ባልበለጠ ብቻ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር እንዲህ ያለው መመርያ በምን መሥፈርት የወጣ እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ እንዲህ ያለው መመርያ ካሳ የመክፈል አቅምን ለመጠበቅ ነው ከተባለ የጠለፋ ዋስትና አለ፡፡ አስተማማኝ የጠለፋ ዋስትና ከገዛህ ሥጋት የለም፡፡ በመሠረቱ በኢንሹራንስ አሠራር ዓረቦን ትሰበስባለህ፣ የካሳ ክፍያው እስኪደርስ ችግሩ ምንድነው? በሌላው ዓለም ገንዘብ እጅህ ላይ የሚቆይ በመሆኑ ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያ የሚያደርገው በኢንቨስትመንት ላይ ማዋል ነው፡፡ ያንን ኢንቨስትመንት ግን እኔ በፈቀድኩልህ መንገድ ብቻ ያውም ይህችን ያህል ብቻ ብለህ መገደብ ራሱ ተገቢ አይሆንም፡፡ ይህ ማለት ዕድገትህንም እኔ በፈቀድኩልህ መጠን ብቻ ነው ማድረግ ያለብህ እንደ ማለት ነው፡፡ ይህ መመርያ ኢንዲስተካከል ለብሔራዊ ባንክ በግልጽ አቅርበናል፡፡ ሊሻሻሉ ይችላሉ ብለን ከምናስባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ይህ መመርያ ቢስተካከል ብዙ ነገር ይቀየራል፡፡ እንደ ኒያላ ኢንሹራንስ ብትጠይቀኝ የዚህ መመርያ መሻሻል ዕድገታችንን በእጥፍ ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የተሰበሰበው ዓረቦን በሙሉ ለኢንቨስትመንት ሊውል ቢችል ተብሎ መሠጋቱ ግን አግባብ አይደለም? በእርግጥስ እንዲህ ዓይነት ሥጋቶች መኖራቸው ትክክል ሊሆን የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም?

አቶ ያሬድ፡- ወደ ቴክኒካዊ የሆኑ ጉዳዮች ይወስደናል እንጂ ብዙ ነገር መናገር ይቻል ነበር፡፡ ለምሳሌ የካሳ ክፍያ ሲመጣ ከጠለፋ መድን ኩባንያዎች ቅድሚያ ክፍያ የመጠየቅ መብቶች ሁሉ አለን፡፡ ‹‹ካሽ ኮል›› እንለዋለን፡፡ ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ ኒያላ ኢንሹራንስ ለዳንጎቴ ወደ 11 ሚሊዮን ብር የሚሆን የካሳ ክፍያ ከፍሏል፡፡ ከመክፈሉ በፊት 80 በመቶ የሚሆነውን በካሽ ኮል አስቀድሞ ነው የከፈለው፡፡ ይኼ ከጠለፋ ኩባንያዎች ጋር ስትደራደር እንዲህ ዓይነቱ አሠራር የተለመደ ነው፡፡ ስለዚህ የገንዘብ እጥረት እንኳን ቢኖርብህ አስቀድመህ መውሰድ የምትችልበት ዕድል ሁሉ አለ፡፡ ደግሞ የራስህንም ገንዘብ ቢሆን አሟጥህ እጅህን አጨብጭበህ አይደለም የምትቀመጠው፡፡ እዚያ ድረስ መሄድ ይቻላል፡፡ ያን ያህል የሚያስበረግግ አይደለም፡፡ ኩባንያዎችን የሚመራው ማኔጅመንት በጥናት ላይ የተመሠረተ እስከሆነ ድረስ ያን ያህል ገንዘቡን አጥፍተውት ይቀመጣሉ ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ያ የቁጥቁጥ መንገድ ዕድገቱን ራሱ ይገድባል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የኢንቨስትመንት መጠን ይገድባል በተባለው መመርያ የተቀመጠው አንቀጽ ሙሉ ለሙሉ ይነሳ ነው ያላችሁት? ወይስ በ35 በመቶ ተገድቦ የቆየው የኢንቨስትመንት መጠን ከፍ ይበል ነው?

አቶ ያሬድ፡- ለጊዜው ለኢንቨስትመንት የምናውለው መጠን ከፍ እንዲል ነው የጠየቅነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ጥያቄ ካነሳችሁትና ብዙ ሲያከራክር የነበረው ሌላው ጉዳይ የባለአክሲዮኖችን የባለቤትነት ድርሻ መጠን የሚገድበውን መመርያ በተመለከተ ያነሳችሁት ጥያቄ አለ?

አቶ ያሬድ፡- አዎ! የባለ አክሲዮኖች የድርሻ መጠንን የሚመለከተው መስተካከል አለበት ብለን ጠይቀናል፡፡ በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ አንድ ባለአክሲዮን ለይዝ የሚችለው ከአምስት በመቶ መብለጥ የለበትም ተብሎ ተገድቧል፡፡ ግን ሲሚንቶ ፋብሪካና ዘይት ፋብሪካ ስታቋቁም እንዲህ ያለው ገደብ የለም፡፡ በእነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ ድርሻ መሆን ያለበት አምስት በመቶ ብቻ ነው የሚል የለም፡፡ ፍላጎት አለኝ፣ ኢንቨስት ማድረግ እችላለሁ፣ ገንዘቤን ወጪ አድርጌ በኢንሹራንስ ኢንቨስት አደርጋለሁ ብሎ የሚመጣን ሰው ይህንን ማድረግ አትችልም ብለህ ለምን ትከለክለዋለህ? ይህ ፈጽሞ ሊገባን የሚችል ነገር አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም በኢንሹራንስ ኩባንያው ውስጥ አንድ ሰው 20 በመቶ ድረስ ድርሻ ሊኖር ይችል ነበር፡፡ ይህንን ወደ አምስት በመቶ አወረዱት፡፡ ስለዚህ የቻለውን ያህል ኢንቨስት አደርጋለሁ ካለ መከልከል የለበትም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ተፅዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች በሚል በተለየ ብዙ መሥፈርቶች የማያልፉበት መመርያም አለ፡፡ ይኼ ባለሀብቶች ወደ ኢንሹራንስ ዘርፉ እንዳይሳቡ የሚያደርግ ነው፡፡ ለምሳሌ ኢንዱስትሪውን ለዳያስፖራው ክፍት አድርገናል ብለን፣ በዚህ በኩል ደግሞ አንድ ባለሀብት ሊይዝ የሚችለው የአክሲዮን ድርሻ ይህ ብቻ ነው ማለት አያስኬድም፡፡ ምናልባት የኮሙዩኒዝም ሐሳብ ሊሆን ይችላል፡፡ ኅብረተሰቡን በስፋት ለማቀፍ ታስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ይኼ ግን የባለሀብቱ የኢንቨስትመንት ፕሮግራም ስለሆነ መደገፍ አለበት፡፡ በፈቀደው መጠን መሳተፍ መቻል አለበት፡፡ መስተካከል አለበት ብለን የጠየቅነው ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የቦርድ ስብስብን በሚመለከት የቀረበ ጥያቄ አለ፡፡ አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ በንግድ ሕጉ ከሦስት ጀምሮ የቦርድ አባላት ሊሆኑ እንደሚችሉ ተቀምጧል፡፡ ብሔራዊ ባንክ የንግድ ሕጉንም በመተው በትንሹ ዘጠኝ የቦርድ አባላት ሊኖሩት ይገባል በሚል ደንግጓል፡፡ ተግባራዊም እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ራሱን የቻለ ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ አዳዲስ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የቦርድ ብቃቱ የሚለካው ቁጥሩ በማነሱ ነው የሚል ነው፡፡ አሁን ውጤታማ የሚባለው የቦርድ አባላት ቁጥር አምስት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን እያካሄደ ባለው ሪፎርሙ ይህንን እየተገበረ ነው፡፡ የሚኒስትሮችን ቁጥር ማሳነሱ ጥሩና የሚመሠገን ሥራ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ በተለይ ከብሔራዊ ባንክ እንደ መከራከሪያ የሚቀርበው አንድ ቦርድ ቢያንስ ሦስት ንዑስ ኮሚቴዎች ሊኖሩት ይገባል የሚል ነው፡፡ ስለዚህ የቦርድ አባላቱ ከዘጠኝ በላይ መሆን አለባቸው ይላል፡፡ እኛ ዓለም እየሄደበት ካለው መንገድ ተገንጥለን የትም መድረስ አንችልም፡፡ በነገራችን ላይ የቦርድ አባላት ስትመርጥ የተቀመጡ መሥፈርቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ የትምህርት ደረጃ ነው፡፡ ዲግሪ ያለው ይላል፡፡ አንድ ሰው ዲግሪ ይዤ ነው ኢንቨስት የማደርገው ሊል አይችልም፡፡ ስለዚህ የቦርድ ቁጥር ስብጥር ምን መሆን አለበት የሚለውን ብሔራዊ ባንክና መንግሥት በፅኑ ያስቡበታል ብለን እናምናለን፡፡ እኛ ግን ጥያቄያችንን አቅርበናል፡፡

ሪፖርተር፡- ለቦርድ አባላት የሚከፈለውን ክፍያ በተመለከተ የተደነገገው ድንጋጌ መስተካከል ይኖርበታል ብላችሁ ታምናላችሁ፡፡

አቶ ያሬድ፡- በጣም ከሚገርሙ ድንጋጌዎች አንዱ ይህ ነው፡፡ እኛም ጥያቄውን አንስተናል፡፡ አንድ የቦርድ አባል የሚከፈልህ ይህን ያህል ነው ብሎ መወሰን አግባብነቱ አይታየንም፡፡ በሚሊዮኖች በሚያተርፍ ኩባንያ የቀን ተቀን ሥራዎችን የሚመለከቱ የቦርድ አባላት፣ በሥራቸው ልክ ባለቤትም እንደ መሆናቸው ጥሩ ክፍያ ቢኖራቸውና የሚያድጉበት መንገድ ለምን ይዘጋል?

ሪፖርተር፡- ባለአክሲዮኖች ከፈቀዱ ለቦርድ የሚከፈለውን  ክፍያ መገደብ ላይ አሁንም ጥያቄ የሚያነሱ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን ቀደም ብለው እንደጠቀሱልን የአንድ ባለአክሲዮን የባለቤትነት ደረጃ መገደቡ ላይ አንዳንድ ወገኖች ትክክል ነው ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ያለ መገደብና ትልቅ ደረጃ መያዙ በኩባንያው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚል አስተያየትም አለ፡፡ የፋይናንስ ተቋማትን ከእነሱ ፍላጎት አንፃር ተፅዕኖ ፈጥረው ውሳኔዎች ሊያሳልፉ ይችላሉ የሚለውስ ሥጋት እንዴት ይታያል?

አቶ ያሬድ፡- እዚህ ላይ እንደ ዕድል ሆኖ በኢንሹራንስ ላይ የሚወጡትን መመርያዎች ስታይ የተለየ ነገር ትመለከታለህ፡፡ ለባንኩ ዘርፍ የወጣ መመርያ ኮፒ ሆኖ ለኢንሹራንሱም ይመጣል፡፡ አሁን የምትለኝ የባለድርሻ አክሲዮኖች ስብጥር ተፅዕኖ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ግፊት አለው ብትለኝ እስማማለሁ፡፡ በኢንሹራንስ ላይ ግን ተፅዕኖ አይኖረውም፡፡ ለምንስ ይኖረዋል? የኢንሹራንስ ኩባንያ የሚያበድረው ነገር የለውም፡፡ ውል ነው የሚሰጠው፣ ግዴታዎች አሉ፡፡ የውሉ ተፈጻሚነት አለ፡፡ አንዳንዴ ለባንክ ኢንዱስትሪው የሚወጡ መመርያዎች፣ በእውነት በኢንሹራንሱ ላይ ውጤታቸው ምንድነው? አስፈላጊ ናቸው ወይ? በሚል በደንብ የታዩ አይመስለኝም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪን ለመጫን የወጡ የሚመስሉ አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምሳሌ?

አቶ ያሬድ፡- የአንድ የኢንሹራንስ ማኔጅመንት አባል በሌላ የፋይናንስ ተቋም በተመሳሳይ ወቅት በቦርድ አባልነት መሥራት አይችልም የሚል ድንጋጌ አለ፡፡ በአንፃሩ ግን የባንክ ከሆነ ይፈቀዳል፡፡ ይህንን ስናየው ኢንሹራንስን አሳንሶ የማየት የሚመስሉ አሉ፡፡ ምንም ማብራሪያ ያላገኘንለት ነገር ነው፡፡ እንዲስተካከል ከጠየቅናቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ ይኼ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ተቀባይነት ያገኘ ይመስለኛል፡፡ በብዙዎች ላይ ውይይት አድርገናል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ተቀብሏቸው የወሰዳቸው አሉ፣ ያልተቀበላቸውም አሉ፡፡ ውጤቱን የምናየው ግን መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ኢንዱስትሪው በዚህ ሪፎርም ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ብለን እናምናለን፡፡ ወይ የምናድግበት ወይ የምንሞትበት ነው ብለን የምናስበው፡፡  በነገራችን ላይ እስካሁን በመጣንበት ከሄድን ከፍተኛ የቁልቁለት መንገድ ውስጥ ገብተናል፡፡ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ከተጋረጠበት አደገኛ ውድቀት መታደግ አለብን፡፡ በእኛ በኩል በቂ ዝግጅት አለን፡፡ ለውይይት ቢጠሩን ዝግጁ ነን፡፡ ከመፍትሔ ሐሳቦች ጋር መቅረብ እንችላለን፡፡ የጠለፋ መድን ሰጪዎቻችንም ቢሆኑ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን እንዴት እናሳድግ በሚለው ላይ መፍትሔ የሚሆን ነገር ሊሰነዝሩ ይችላሉ፡፡ እነሱም ፈቃደኞች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ኩባንያዎች ይግቡ በሚለው ነጥብ ላይ ብዙ ጊዜ ሐሳብ ሲነሳ ባንኮችን ነጥለን ነው የምናየው፡፡ የውጭ ባንኮች ይግቡ አይግቡ በሚል ጥያቄ ይነሳል እንጂ፣ በኢንሹራንሱ ዘርፍ የውጭ ኩባንያዎች ቢገቡስ የሚለው ሐሳብ ብዙ ጊዜ አይነሳም፡፡ በኢንሹራንስ ዘርፍ የውጭ ኩባንያዎች ይግቡ የሚለው የማይነሳው ለምንድነው? በአንፃሩ የውጭ የጠለፋ መድን ሰጪዎች ከኢትዮጵያውያን ጋር እየሠሩ መሆኑ ቢታወቅም፣ በመደበኛ የኢንሹራንስ ቢዝነስ የውጭ ኩባንያዎች መግባት እንዴት ይታያል?

አቶ ያሬድ፡- በመጀመርያ ደረጃ በአሁኑ ወቅት ከ60 ከመቶ በላይ የውጭ የጠለፋ መድን ሰጪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ እየሠሩ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ይህም የሆነው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የአገሪቱ አደጋ የመሸከም አፕታይት ለምንለው የግዴታ የውጭ መሆን አለብን፡፡ ለምሳሌ ከፍተኛ አደጋዎች ቢመጡ ሁላችንም ተያይዘን ነው የምንከስረው፡፡ ስለዚህ ውጭ አገር ካሉ የጠለፋ መድን ሰጪዎች ጋር መሥራት አለባቸው፡፡ ኢንሹራንስ ድንበር ዘለል በሆኑ ውሎች አማይነት በአንድ አገር ኢኮኖሚ ላይ የፀና ጉዳት እንዳያመጣ ነው፡፡ ይህን ከማድረግ አልተቆጠብንም፡፡ አሁንም እያደረግን ነው፡፡ ነገር ግን ቀጥታ ፈቃድ አውጥተው ኢትዮጵያ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆነው ቢገቡና ቢሠሩ ይጠቅማሉ፡፡ እንዲያውም በግሌ እኔ የማምነው የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው በአጠቃላይም የፋይናንስ ዘርፉ በአጠቃላይ ተዘግቶ ሊቆይ አይችልም፣ መከፈት አለበት፡፡ ሲከፈት ግን የውጭ ኩባንያዎች በሚገቡበት ሁኔታ ላይ ፈጽሞ አግበስብሶ የመቆጣጠር ፍላጎት በመከላከል ቢገቡና እንዲወዳደሩ ቢደረግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ የውጭ ኩባንያዎች ይግቡ ከተባለ ጠቀሜታቸው እንዴት ይገለጻል?

አቶ ያሬድ፡- ለምሳሌ ቅድም ያነሳነውን የሕይወት ኢንሹራንስ ለማሳደግ እጅግ ይጠቅማል፡፡ አሁን እኛ በያዝነው መንገድ በፖሊሲያችንና በተሞክሯችን ብዙ ልናንፏቅቀው አንችልም፡፡ በጣም የተዘጋጁ ብቃት ያላቸው የውጭ ኩባንያዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በአፍሪካ ውስጥ ወደ 20 አገሮች የሚሠራ ኩባንያ አለ፡፡ ይህ ኩባንያ የሚመጣው እንደ ባለአክሲዮን ሆኖ ነው፡፡ ሼር ይገባል፡፡ በሕይወት ኢንሹራንስ ላይ ባለሙያዎችን የተለየ ሥልጠና ሰጥቶ ሠራተኞች አቅምን ይገነባል፡፡ የሕይወት ኢንሹራንስ ያሳድጋል፡፡ ዛሬ ወይም ነገ መከፈቱ ስለማይቀር እንደ ኒያላ ኢንሹራንስ እየተዘጋጀን ነው፡፡፡ ኅብረተሰቡም እንዲመለከት ያደርገዋል፡፡ እኛም ውስጣችንን እንድንመለከት ያደርጋል፡፡ ራሳችንን ሞርደን እንድንተጋ ያደርጋል፡፡ ትክክለኛ በሆነ ውድድር ላይ እንድንሳተፍ ያደርገናል፡፡ አሁን እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረተው አጠቃላይ ዓረቦን ኬንያ ውስጥ ያለ አንድ ወይም ሁለት ኩባንያ የሚያመርተው ነው፡፡ የውጭ ኩባንያዎችም የራሳቸውን አገልግሎት አምጥተው እየሠሩ ነው፡፡ ስለዚህ ሳይዘገይ ይምጡ፡፡ ቀጭጨን ከምንሞት ራሳችንን ተወዳዳሪ አድርገን እንድንሠራ መግባት አለባቸው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...