Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

 ከኪሳቸው በላይ የሚያስቡ ባለሀብቶች ያስፈልጉናል

ከአንድ ወር በፊት ሪፖርተር ጋዜጣ የፊት ለፊት ገጽ ላይ አንድ ትኩረቴን የሳበውን ርዕስ ለዛሬው ጽሑፌ መንደርደርያ አድርጌዋለሁ፡፡

የዜና ዘገባው ርዕስ ‹‹መንግሥት የሚደጉመው ፓልም ዘይት በሌሎች ፈሳሽ ዘይቶች እንዲቀየር ጤና ሚኒስቴር ጠየቀ›› የሚል ነበር፡፡ የዘገባው አንኳር መልዕክትም የፓልም ዘይት ከጤና አንፃር የሚያስከትለውን ተፅዕኖ በመገንዘብ ጤና ሚኒስቴር መንግሥት ለእንዲህ ያለው ዘይት የሚያደርገውን ድጎማ እንዲያቋርጥ የሚጠይቅ ነው፡፡

ይህ የዜና ርዕስ ምናልባት ለአንዳንዶች ‹‹እና ምን ይጠበስ?›› ሊያስብል የሚችል ቢሆንም፣ እንደ እኔ ግን ለውጥ አለ ከተባለ መንግሥታዊ ተቋሞቻችን በየሚመሩት ዘርፍ ዜጎችን የመታደግ ሥራ መሥራት እንደሚችሉ የሚጠቁመን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማቅረብና ማስፈጸም ቢችሉ አገር ልትለወጥ ትችላለች በሚል ነው፡፡

በጠቀስኩት ርዕስ የተዘገበው ዜና ከሞላ ጎደል መልዕክቱ የፓልም ዘይት ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ተረድቶ በዚህ ዘይት ላይ የተደረጉ ጥናቶችና ጥናቶችን ተንተርሶ መደረግ የሚኖርበትን ምክረ ሐሳብ በመያዝ ችግሩ ይህ ከሆነማ በመንግሥት ድጎማ የሚገባው ዘይት በፈሳሽ ዘይት መለወጥ አለበት የሚል ነው፡፡

ነገሩን ጠለቅ ብለን ስንመረምረው ደግሞ ይህ የፓልም ዘይት በመንግሥት ድጎማ ገብቶ አገሩን አጥለቅልቆ በእያንዳንዳችን ኩሽና የዕለት ጉርሳችን ማጣፈጫ ከሆነ ውሎ ያደረ ሲሆን፣ ተፅዕኖ እንዳለው መስማት ከጀመርንም ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን ነገሩን ነገሬ ብሎ በጊዜ ብዛት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በመረዳት መላ ለመፈለግ አልተሞከረም፡፡ የፓልም ዘይት የጤና ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ከተባለ ደግሞ ጉዳቱ በተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ላይ ብቻ የሚገደብ አይደለም፡፡ እንደው አቅም ኖሮ ፈሳሽ ዘይት በቤቱ ውስጥ ለማብሰያ የሚጠቀም ቢሆን እንኳን፣ ከቤት ወጣ ብሎ በየትኛውም ምግብ ቤት ጎራ ሲል ‹‹ከማሙሽ›› የሚያመልጥ የለም፡፡

ትልቁም ትንሹም ሆቴልና ምግብ ቤቶች የሚጠቀሙት ይህንኑ ዘይት ነውና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የፓልም ዘይትና እኛ ሳንገናኝበት የምንውልበት ቀን ያለመኖሩን ያስገነዝበናል፡፡ ስለዚህ ችግሩ የሁሉም ዜጋ ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ችግር ሆኖ እንጂ ይህ ዘይት መዘዙ የበዛ ነው የሚለው አዲስ ነገር ባይሆንም፣ ውሎ አድሮ የሚያመጣውን ችግር ተገንዝቦ መሠራት ይገባው ነበር፡፡

ስለዚህ ምርቱ በዘለቄታነት የምንጠቀምበት አይደለም የሚለውን ያመለክተናል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ እንዲህ የሚወራበት ዘይት በመንግሥት ተፈቅዶ እንደውም ተደጉሞ ኅብረተሰቡ እንዲጠቀም የመደረጉ ጉዳይ ብዙ ሊያነጋግር ቢችልም፣ ሊያመጣ የሚችለው ተፅዕኖ እየታወቀ እየተጠቀምንበት ነው፡፡

ዛሬ ደግሞ ጤና ሚኒስቴር ይህ ጉዳይ በዚሁ መቀጠል የለበትም ብሎ መነሳቱና መንግሥት ቆራጥ ውሳኔ እንዲያሳልፍ መጠየቁን መስማታችን ከቀደመው ጊዜ የተሻለ አሳቢ የጤና ሚኒስቴር ባለሙያዎችና አመራሮች አግኝተናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ለውጥ ስለመኖሩ ያሳየናል፡፡ የለውጥ አንዱ መገለጫ ስለኅብረተሰቡ ደኅንነት የሚጨነቅ ማግኘት ነው፡፡ ‹‹ለውጥ አለ›› የሚለው ነጥብ የሚያሳየውም እዚህ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የሕዝባቸውን ጤና አጠባበቅ ተከታተሉ የተባሉ የሥራ መሪዎች የዚህን ዘይት ችግር ጠንቅቀው የሚያውቁ ቢሆንም፣ ምንም ያለማለታቸው ያስተዛዝባል፡፡

በዚህ ዘገባ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን እንድመለከት አድርጎኛል፡፡ አንዱ የጤና ሚኒስቴር የጉዳዩን አሳሳቢነት በመገንዘብ ኃላፊነቱን ለመወጣት ድፍረት የተሞላበት ውሳኔ መውሰዱ አንዱ ነው፡፡ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ የሚባለውን አነጋገር መተግባር የነገ ትውልድንም ለማዳን የወሰደው ጤናማ ውሳኔ በመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ጉዳይ ይህ ለጤና አደጋ ሊሆን ይችላል የተባለውን ዘይት ለመተካት ምን ይደረግ የሚለውንም መጠይቅ ይዞ የሚመጣ ስለሚሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ ለጤና አደጋ የሚሆን ዘይት በገፍ ማስገባት ከመጀመርዋ ቀደም ብሎ በተትረፈረፈው የቅባት እህል ምርቶች ዘይት ጨምቀው የሚሸጡ የበዙ ዘይት ፋብሪካዎች ነበሩበት፡፡ ሸማቾችም ይህንን ዘይት በቀላሉ ከየሰፈሩ መደብሮች ያገኛሉ፡፡ አማርጠው የአገር ውስጡን ዘይት አጣፍጠውበት ይጠቀሙ ነበር፡፡

እንዲህ ያለው የአገር ውስጥ የዘይት ምርት አመራረቱ ኃላፊነት የተሞላበት፣ ስግብግስነት የሌለበት በመሆኑ አምራቹም በሚገባ አምርቶ ሸማቹም ያለ ሥጋት ይጠቀምበት ነበር፡፡

ቆይቶ ግን የዘይት ምርት ሸፍጥ የሚሠራበት መሆን ሲጀምር ነገሮች ተበላሽተዋል፡፡ ቆይቶም በአገር ውስጥ የቅባት እህሎችን ተጠቅመው የሚያመርቱ በአቅራቢያችን የሚገኙ የዘይት አምራቾች እየተዳከሙ ሄዱ፡፡ በአገር ውስጥ መመረቱ ቀረና ከውጭ ይገባ ጀመር፡፡ ይህ ከምናዝንባቸው ታሪኮቻችን አንዱ ሆነ፡፡

የአገር ውስጥ ፍላጎትን በመሙላት ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው ከትናንሽ እስከ ትላልቅ የዘይት ማምረቻዎች ጉልበት አጥተው ከውጭ በሚመጡ ያውም ለጤና ጠንቅ በሆኑ የውጭ ዘይቶች ተጥለቀለቅን፡፡ እነሆ አሁን በቅባት እህሎች አምራችነት የምትታወቀው አገር በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመት የውጭ ምንዛሪ እያወጣች የምግብ ዘይት ታስገባለች፡፡

ጤናማውን ምርትን ትታ በሽታ ታስገባለች ቢባል ማጋነን ይሆን? ለማንኛውም የአገር ውስጥ የዘይት ምርት መዳከም ብቻ ሳይሆን እንዲጠፉ የተፈረደባቸው እንደ ጥሬ ዕቃ የሚጠቀሙበት ምርት አጥተው አይደለም፡፡ ብዙ ሺዎችን የሥራ ዕድል ያስገኙ የነበሩት የዘይት ፋብሪካዎች የተዘጉትና አዳዲሶችም እንዳይፈጠሩ የተደረገው ዘይት ማምረት ትልቅ ጥበብ ሆኖባቸው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ማሳደግ የምትችለው የዘይት ማምረት ሥራ የሰጣቸው ያለ ብዙ ድካም ከውጭ ሸቀጥ አስመጥቶ መቸርቸር የለመደው የአገራችን የግብይት ሥርዓት ተዋንያኖች ጡንቻ በመፈርጠሙ ጭምር ስለመሆኑ መረሳት የለበትም፡፡

አገር ለምግብ ዘይት እያወጣች ያለው የውጭ ምንዛሪ ቆጭቶት ዘይቱን እዚህ ማምረት አለብኝ ብሎ በወኔ የሚነሳ ጨዋ አስመጪ ማጣታችን ያሳዝናል፡፡ ዜጎች ለበሽታ የሚዳርግ ዘይት ከማስመጣት እዚሁ ላምርት ብሎ በቅን ልቦና አለመሥራት ያመጣው ጣጣ ነው፡፡ እዚህ ላይ ባለሀብቶች ለጤና የሚጠቅም ዘይት አምጥተው ሸማቾች በጤና ኖረው ለረዥም ዓመታት ዘይት እንዲገዟቸው ከማድረግ ይልቅ፣ ስንጥቅ ትርፍ የሚያተርፉበትና ለጤና ጠንቅ የሆነውን ዘይት የማስገባታቸው ነገር በጣም ያስተዛዝባል፡፡ ከራሳቸው ውጪ ሌላውን ማየት የማይችሉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ ሳይቀር ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡

በቅርቡ በአማራ ክልል አንድ የኅብረት ሥራ ማኅበር በድፍረት የዘይት ማምረቻ ከፍቶ እየሠራ መሆኑንና ሥራው መስመር እየያዘለት መሆኑን የሚገልጽ ዜና ስሰማ፣ እንዲህ ያሉ ብርቱዎችን ካበዛን ለዘይት የሚወጣ የውጭ ምንዛሪ ሊቀር የሚችልበት ዕድል ሰፊ ሲሆን፣ እነዚህን አምራቾች ልንጠብቃቸው ካልቻልን ግን እጅ ረዥሞቹ ይቆጫቸዋልና የምግብ ዘይትን ለማምረት የሚደረገውን ጥረት እንዳያደናቅፉት መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህን ኢንቨስትመንቶች በተለየ መንገድ ማበረታታት ይጠይቃልና ይህንንም ማሰብ ተገቢ ይሆናል፡፡

እነሆ ዛሬ በገፍ የገባው ዘይት ከዚህ በኋላ መግባት የለበትም እየተባለ እንኳን የተነሳሳ የለም፡፡ በጥቅሉ ሲታይ ዘይት በአገር ውስጥ እንዳይመረት ብዙ ምክንያቶች ሊደረደሩ ቢችሉ እንደ አንድ ዋነኛ ምክንያት ሊቀመጥ የሚችለው ሸፍጥ ያለበት መሆኑ ነው፡፡

ዘይት የሚያመርቱ የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ ልከን ከእነዚህ ምርቶች ተገኘ ከሚባለው የውጭ ምንዛሪ ያልተናነሰ ወጪ አውጥተን ዘይት እናስገባለን፡፡ ከዚህ በኋላ ሸፍጥና ጅልነት እንዴት ይኖራል?

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት