የቡና ማቀነባበሪያና የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ለመገንባት ተስማምቷል
በ10 ዓመት አራት ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝና ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንቨስት እንዲያደርግ አስውቆ ነበር
የቻይናው ጫማ አምራች ኋጂዬን ግሩፕ፣ 61 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገበት የሚነገርለትን የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሙሉ በሙሉ በመረከብ በፓርኩ ለማምረትና ፓርኩን ለማስተዳደር የመግባቢያ ስምምነት ፈረመ፡፡
ኩባንያው ባለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ጫማ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጉልህ ድርሻ በመያዝ ዘርፉን እየመራ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የዱከም ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ያለውን ጨምሮ የራሱን ማምረቻ ኢንዱስትሪ ማዕከል በመገንባት በሁለት ፋብሪካዎቹ እያመረተና ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገርም በአዲስ አበባ ከተማ ለቡ አካባቢም ሌዘር ሲቲ በማለት የሰየመውን የማምረቻ ተቋም ለመገንባት እንቅስቃሴ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡
ይህ ባለበት፣ የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክን በመረከብና በፓርኩ ለማምረት ብሎም የቻይናም ሆነ የሌሎች አገሮችን ኢንቨስቶች በማሳመን ወደ ፓርኩ እንዲመጡ እንደሚሠራ ስምምነቱን ባደረገበት ወቅት የኩባንያው ፕሬዚዳንት ዣንግ ሁዋሮንግ ገልጸዋል፡፡
ሐሙስ፣ ግንቦት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አዳራሽ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ ከኩባንያው ተጠሪ የመግባቢያ ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡ በአራት ወራት ውስጥ ፓርኩ ሥራ ሊጀምር እንደሚችል ይጠበቃል።
ከኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ጋር ከታካሄዱ ረጅም ድርድሮች በኋላ የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክን መረከብ እንደቻሉ የገለጹት፣ የኋጂዬን ግሩፕ ፕሬዚዳንት፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ በፓርኩ የጫማ፣ የአልባሳትና ጨረቃጨርቅ፣ የግንባታ ቁሳቁሶችና ሌሎችም ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ምርቶች እንደሚመረቱበት አስታውቀዋል፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም እንዲህ ያሉ ምርቶች ከፓርኩ ለገበያ እንደሚቀርቡ ገልጸዋል፡፡
ከ30 ሔክታር በላይ ስፋት ባለው ይዞታ ላይ የተገነባው ጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በምዕራፍ ሁለት ግንባታው 40 ሔክታር በሚሸፍን ቦታ የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ጨምሮ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከል ለመገንባት ስምምነት መፈረሙንም ወይዘሪት ሌሊሴና ሚስተር ሁዋሮንግ ገልጸዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ በስምምነቱ ወቅት እንዳሉት፣ የኩባንያው ወደ ጅማ ኡንዱስትሪ ፓርክ መግባት በተለይ በአካባቢው ለሚገኘው የቡና ሀብት ትልቅ ፋይዳ አለው። ይህ ዕቅድ በሁለተኛው የኋጂዬን የኢንቨስትመንት ምዕራፍ እንደሚተገበር የገለጹት የኩባንያው ፕሬዚዳንት፣ የቡና ማቀነባበሪያ በመገንባት ለቻይናና ለሌሎችም ዓለምአቀፍ ገበያዎቹ የቡና ምርቱን ሙሉ በሙሉ እንደሚያቀርብ አስታውቀዋል፡፡
በጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚካሄዱ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ከ12 ሺሕ እስከ 15 ሺሕ ለሚደርሱ ወጣቶች የሥራ ዕድል በጅማ ፓርክ እንደሚፈጠር ወይዘሪት ሌሊሴ ሲገልጹ፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ በበኩላቸው ኩባንያው ከሰባት ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ልምድ ያለው በመሆኑ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፓርኩን ወደ ሥራ እንደሚያስገባው እምነታቸውን ገልጸዋል።
ላለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ጫማ ሲያመርት የቆየው ኋጂዬን ግሩፕ ወደ ኢትዮጵያ በገባበት ወቅት ሲገልጽ የነበረው በ10 ዓመታት ውስጥ ዓመታዊ የወጪ ንግድ ገቢው አራት ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስና ኢንቨስትመንቱም ወደ ሁለት ቢሊዮን ዶላር እንደሚያሻቅብ ነበር፡፡ ይሁንና በሰባተኛ ዓመቱ ላይ እያስገኘ ያለው ዓመታዊ ገቢ ከ30 ሚሊዮን ዶላር ብዙም ፈቅ አላለም፡፡ ኢንቨስትመንቱም ቢሆን ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ አልተሻገረም፡፡
ይህም ሆኖ የኩባንያው ፕሬዚዳንት ስለኩባንያቸው መርሆዎች ሲናገሩ፣ የአገሪቱን ሕግጋት ማክበር፣ በሙስናና ጉቦ በመስጠትና በመሳሰሉት ተግባራት ብሎም በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ አለመሳተፍ ኩባንያቸው የሚመራባቸው መርሆዎች ናቸው ብለዋል፡፡