Saturday, September 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ቢገባደድም ጥሬ ምርት ማግኘታቸው ሥጋት አሳድሯል

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአራት ክልሎች ግንባታቸው እየተካሄደ የሚገኙት የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ለማቀነባበር የሚያስፈልጓቸው የግብርና ውጤቶች ባለመድረሳቸው ሥጋት አሳድረዋል ተባለ፡፡

ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከተማ በተካሄደው የግብርና ዘርፉ ተዋናዮች ስብሰባ ወቅት ነበር ይህ ሥጋት ለመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተነሳው፡፡ በውይይቱ ወቅት በተለይ ከኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቀረበው ጥያቄ ይህንኑ ሥጋት አመላክቷል፡፡ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራና በደቡብ ክልሎች ግንባታቸው እየተከናወነ የሚገኙት የግብርና ማቀነባበሪያ ፓርኮች ከአራት ወራት እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት ዝግጁ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ ይሁን እንጂ ፓርኮቹ ለማቀነባበር የሚያስፈልጋቸው ምርት አቅርቦት ላይ እየተሠራ አይደለም ተብሏል፡፡

ፓርኮቹ ለሥራ ዝግጁ በሆኑበት ወቅት ለማቀነባበር የሚጠቀሙበት ምርት ማጣታቸው ሊታሰብበት ይገባል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሑሴን ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸው፣ በትብብር ከተሠራ ግን ለግብርና ኢንዱስትሪዎች የሚውል ምርት ማቅረብ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከሪፖርተር ተጠይቀው እንደገለጹት፣ አራቱ የተቀናጀ ግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሙከራ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ የክልሉን የግብርና ሥራዎች በሥራቸው የሚመሩት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ በኦሮሚያ ክልል ግንባታው እየተጠናቀቀ ለሚገኘው የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታና አብረው መጎልበት ስላለባቸው የጥሬ ምርት አቅርቦት ሥራዎች ዕቅድ በማውጣትና በመከታተል የሚሠራ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ኮሚቴው ባወጣው ዕቅድ መሠረት በየሩብ ዓመቱ አፈጻጸሙ እየተገመገመ እንደቆየ የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንት ግርማ (ዶ/ር)፣ ዋና ሥራውም የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ የግንባታ ሥራ ከመጠናቀቁ በፊት የሚቀነባበሩትን ግብዓቶች በበቂ መጠን ማዘጋጀት እንዲቻል ማድረግ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ለኢንዱስትሪው ብቃት ያላቸው ባለሀብቶች ተመልምለው የሚያመርቱት ምርትና ዓይነት ከወዲሁ መታወቅና መለየት እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡ የምርት ዝርያ ዱበባለኢንዲስትሪው ከተመረጠና ከተለየ በኋላ ገበሬው የሚፈለገውን ዓይነት ዝርያ እንዲያመርት የሚደረግበት አካሄድ መቀየሱንም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ኦሮሚያ፣ ቡልቡላ በተባለ ቦታ እየተገነባ በሚገኘው አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ለመሳተፍ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶችና የገበሬ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየኖች ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡

የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገብንቶ መጨረስ ሳይሆን፣ ጎን ለጎን ለማቀነባበር የሚያስፈልጉትን ጥሬ ምርቶች ማቅረብ መቻል ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንት ግርማ (ዶ/ር)፣ የሚፈለጉትን ግብዓቶች በዝናብ ላይ ጥገኛ በሆነ እርሻ ኢንዱስትሪን መመገብ አስቸጋሪ በመሆኑ የቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሚገኝበት አካባቢ ያሉትን ተፋሰሶች በመጠቀም የመስኖ እርሻ እንደሚካሄድ አብራርተዋል፡፡

ፈንታሌና ነቲብላ የተባሉትን ጨምሮ ሌሎችም ነባር የመስኖ ፕሮጀክቶች የሚገኙበት አካባቢ ላይ የተተከለው የቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ እንደ አዳኣ በቾ ያሉ የከርሰ ምድር ውኃ ፕሮጀክቶችም ለፓርኩ ምቹ ግብዓቶችን በማመቻቸት ላይ የሚገኙ የሥራ ሒደቶች ስለመሆናቸው ተብራርቷል፡፡

ለመጀመሪያ ምዕራፍ የሚያስፈልጉ ማምረቻ ሼዶች፣ የቢሮ አገልግሎት የሚሰጡ ግንባታዎችን ጨምሮ፣ መብራት የማስገባት ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንት ግርማ (ዶ/ር)፣ የፍሳሽ ማጣሪያና የውኃ መስመር መዘርጋት ሥራዎች እንደሚቀሩ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም የጥሬ ምርት ማሰባሰቢያና ማቆያ ጣቢያዎች ዝግጅትም እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም በሻሸመኔ የምርት ማሰባሰቢያና ማቆያ ጣቢያ ግንባታ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡

የቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ማስተር ፕላን እንደሚያሳየው በመጀመሪያው ምዕራፍ ከ72 ሚሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ወጪ የሚደረግበት፣ 263 ሔክታር የሚያካልል ፕሮጀክት ነው፡፡ ለዚሁ ፓርክ ግብዓት ማቅረብ የሚቻልበት ከ335 ሺሕ ሔክታር በላይ የእርሻ ሥራ የሚካሄድበት ሰፊ መሬትም ለግብዓት መጋቢ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በአራት ዓመታት ውስጥ እስከ 180 ሚሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ወጪ እንደሚጠይቅ፣ በተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ያወጣው የማስተር ፕላን ሰነድ ይጠቁማል፡፡

ከቡልቡላ አግሮ ፓርክ በተጨማሪ በምዕራብ ትግራይ የቤይከር አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በደቡብ ምዕራብ አማራ የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁም በምሥራቃዊ ደቡብ ክልል የይርጋለም አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ 150 ሔክታር ይዞታ ለሚኖረው የቤይከር አግሮ ፓርክ የሚውለውን 73 ሚሊዮን ዶላር የመነሻ ኢንቨስትመንት ካፒታል ባሻገር፣ ለይርጋለምና ለቡሬ ፓርኮች የመጀመሪያ ምዕራፍ ልማት ከ120 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግና የሁለቱ ፓርኮች ይዞታም በጠቅላላው ከ263 ሔክታር በላይ እንደሆነ ዩኒዶ ያወጣው የማስተር ፕላን ሰነድ ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች