Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በጊዜው ይካሄድና በይራዘም መሀል የሚዋልለው ቀጣዩ ምርጫ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በትረ ሥልጣኑን በጨበጡ ማግሥት ወደ ሰሜን አሜሪካ አቅንተው በዚያው ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ካደረጓቸው ንግግሮች መካከል ተጠቃሹ በኢትዮጵያ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ ዋነኛ ዓላማቸው መሆኑን መግለጻቸው ነበር፡፡

ባለፉት 28 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) የሥልጣን ዓመታት ምንም እንኳን አገሪቱ አምስት ዙር አጠቃላይ ምርጫዎች ያካሄደች ቢሆንም፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ምርጫ መሠረታዊ መሥፈርቶችን የማያሟላ፣ በማጭበርበሮች የታጀበ፣ እንዲሁም ወከባና እንግልት የማያጡት ነው በማለት ትችታቸውን ሲሰነዝሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

በተለይ በምርጫ 97 በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ተነቃቅቶ የነበረውን የፖለቲካ ፍላጎትና በምርጫ ካርድ ሥርዓትን መለወጥ ይቻላል የሚለውን አስተሳሰብ፣ ምርጫውን ተከትሎ በተፈጠረው አላስፈላጊ አምባጓሮና አታካራ ቀዝቃዛ ውኃ ቸልሶበት አልፏል፡፡

በዚህም የተነሳ በ1997 ዓ.ም. የነበረው የዜጎች በፖለቲካና በተለይም ደግሞ በምርጫ የመሳተፍና እምነት ማሳደር ከነበረበት ወርዶ፣ ከዚያ በኋላ የተከናወኑ ምርጫዎች የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባሎቻቸው እንዲሁም የተወሰኑ ተስፋ ያልቆረጡ ዜጎች ጉዳይ ወደ መሆን ወርዶ ነበር፡፡

ገዥው ፓርቲም ድኅረ ምርጫ 97 ባወጣቸው አፋኝ ሕጎች በመታገዝ የተለየና የተቃውሞ ሐሳብ ያላቸውን ግለሰቦች፣ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞችን ወደ እስር ቤት ሲያግዝ መክረሙ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

በዚህም ምክንያት አብዛኛው ሕዝብ ፖለቲካ ለምኔ በማለት ወደ የዕለት ተዕለት ጉዳዩ አተኩሮ ከ97 ወዲህ ሁለት ምርጫዎች ተከናውነው ውጤታቸውም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ሙሉ በሙሉ በአንድ ፓርቲ የበላይነት ሥር እንዲውል አደረገው፡፡

ከእነዚህ የምርጫ ውጤቶች በኋላ ሕዝቡ በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞውንና ጉምጉምታውን ሲገልጽ የሰነበተ ሲሆን በተለይ ግን ከምርጫ 2007 ማግሥት ጀምሮ ተቃውሞዎቹ ሥር እየሰደዱ መንግሥትን ወደ ማስጨነቅ ተሸጋግረው ነበር፡፡

በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተለይ ደግሞ በኦሮሚያ ከተሞች ሲካሄዱ የነበሩ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች አይለው፣ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ውስጥም ያለው ልዩነት እየጎላ መጥቶ በሥራ ላይ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መልቀቂያ አስጠይቆ፣ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከ ማሾም ደርሷል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ማራቶን አከል ስብሰባ ያደረገው ኢሕአዴግ በስብሰባው መጠናቀቅ በፓርቲው ባህል ባልተለመደ መንገድ ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሥልጣናቸው ለቀው በምትካቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን መጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በርካታ የማሻሻያ ሥራዎችን እንደሚከናወኑ የገለጹ ሲሆን፣ ኅብረተሰቡም በከፍተኛ ደስታና ተስፋ ነበር የተቀበላቸው፡፡

ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን የመጡ ሰሞን ያገኙት ቅቡልነት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ አለመረጋጋቶች፣ መፈናቀሎችና ግጭቶች ሳቢያ አሁን እንደ ቀድሞ ባይሆንም አሁንም በእሳቸው ተስፋ የሚያደርጉ በርካቶች ናቸው፡፡

በተቃራኒው ደግሞ ተስፋቸውና ደስታው በኖ ወደ ተስፋ መቁረጥና መቆዘም የተሸጋገሩና ድጋፋቸውን ወደ ተቃውሞ የቀየሩም እንዲሁ ይገኛሉ፡፡

ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ካከወኗቸው ዓበይት ተግባራት መካከል የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ማደስ መቻላቸውና ጦርነትም ሰላምም ያልነበረበትን ሁኔታ ወደ ሰላም መለወጣቸው፣ አፋኝ የሚባሉ የአገሪቱን ሕጎች ለማሻሻል የተለያዩ ቡድኖች ተቋቁመው የማሻሻያ ሥራዎች መከናወናታቸው ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በአገሪቱ የሚገኙ ሕጎችን ከማሻሻል አንፃር ምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች ሲመሩባቸው የነበሩና ከዚህ በፊት ቅሬታ ይቀርብባቸው የነበሩት ሦስት ዋና ዋና ሕጎችን ለማሻሻል የተጀመረው ሥራ አንዱ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን መልሶ የሚያቋቁም አዋጅ ተረቅቆ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት በሥራ ላይ የነበረው የቦርዱ ማቋቋሚያ አዋጅ 532/1999 በአዲሱ አዋጅ 1133/2011 እንዲተካ ተደርጓል፡፡

በአዲሱ አዋጅ መሠረት የቦርዱ አባላት ቁጥር ከዘጠኝ ወደ አምስት ዝቅ እንዲል የተደረገ ሲሆን፣ የሚሾሙት አምስት የቦርድ አባላት ከዚህ በፊት ከነበረው አሠራር በተለየ የሙሉ ጊዜ ሠራተኞች እንዲሆኑ ይደነግጋጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው በፓርላማው ሳይሆን በቦርዱ አማካይነት የሚደራጅ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡

የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ለማስፋትና ሁሉንም አሳታፊ ማድረግ እንዲቻል እንደሚሠራ በተደጋጋሚ ቃል የሚገባው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳደር፣ ዕቅዶቹን ተፈጻሚ ለማድረግ በርካታ ተግዳሮቶች ከፊቱ እንደተጋረጡበት የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡ በተለይም በአገሪቱ የተለያዩ ሥፍራዎች የተከሰቱ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች ዓበይት የፖለቲካና ማኅበራዊ ጉዳዮችን ለመከወን እንቅፋት ከመሆናቸው ባሻገር፣ መንግሥትም ሙሉ በሙሉ ወደ ምርጫ ጉዳዮች እንዳይገባና እዚህም እዚያም ለሚቀሰቀሱ ግጭቶት ምላሽ መስጠት ላይ እንዲያተኩር መገደዱን የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡

ከዚህ ባለፈም መንግሥት በየሥፍራው የሚከሰቱ ግጭቶችን፣ መፈናቀሎችንና የዜጎች ሕይወት መጥፋትን ለመቆጣጠርና ለማረጋጋት መለሳለስ አሳይቷል በማለት የሚተቹትም በርካቶች ናቸው፡፡

የቀጣዩ ምርጫ ነገር

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሆነ እየገለጹ የሚገኙ ሲሆን፣ በርካታ ፓርቲዎችም በውህደት፣ በጥምረትና በቅንጅት ለመሥራት ስምምነቶችን እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡

ከሁሉም በላይ የአገሪቱን የፖለቲካ ከባቢ ሰቅዞ የያዘው ጉዳይ ቀጣዩ አጠቃላይ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ይካሄዳል ወይስ ይራዘማል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ቁርጥ ያለ ምላሽ የሚጠበቅበት ቢሆንም፣ ከመንግሥትም ሆነ እንደ አዲስ ከተዋቀረው የምርጫ ቦርድ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይካሄዳል ወይም ደግሞ ይራዘማል የሚል ምላሽ አልተገኘም፡፡ ምርጫ ቦርድ በአንድ መግለጫው ግን የሚያካሂደው ሪፎርም የምርጫ ጊዜውን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን መግለጹ አይዘነጋም፡፡

ምንም እንኳን በአገሪቱ ፖለቲካ ተሳታፊ ከሆኑ የተለያዩ ቡድኖች መካሄድ አለበት የለም መራዘም ነው ያለበት የሚል ክርክር የሚደመጥ ቢሆንም፣ ጉዳዮን በበላይነት የሚመራው ምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሊሰጥና ሊወስን ቀርቶ የቦርድ አባላቱ እንኳን እንዳልተሟላለት በመጥቀስ፣ ምርጫው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ መከናወኑ የማይታሰብ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ የደረሱ በርካቶች የተቃውሞ ጎራው አባላትና የፖለቲካ ተንታኞች አሉ፡፡

እነዚህ አካላት ለመከራከሪያነት የሚያቀርቡት ሐሳብ በዋነኛነት የሚያጠነጥነው ደግሞ፣ ከአገሪቱ አጠቃላይ የሰላምና ደኅንነት ሁኔታ እንዲሁም እነዚህን የሰላምና ደኅንነት መደፍረስን ተከትሎ የተከሰቱት መፈናቀሎች ዙሪያ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ፣ ‹‹አገሪቱ አሁን ካለችበት የፀጥታ አለመኖር አንፃር ስለ ምርጫ ማሰብ በመራጩ ሕዝብ ላይ ማፌዝ ነው፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን ይገልጻሉ፡፡

በማከልም፣ ‹‹ፓርቲያችን የምርጫ ፓርቲ ነው፡፡ ነገር ግን ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተፈናቅሎ በጎዳና እየዋለና እያደረ፣ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ባልተካሄደበት ሁኔታ፣ እንዲሁም በአገሪቱ በጠፋው መረጋጋት ሳቢያ ተዟዙረው መቀስቀስና ሐሳብ መሸጥ በማይቻልበት ሁኔታ ስለምርጫ መካሄድ አለመካሄድ ማውራት እናገለግለዋን በሚሉት ሕዝብ ላይ መቀለድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በርካታ ተፈናቃዮች ያሉበት የምርጫ ክልል ተጉዞ ምረጡኝ ለማለት የሚያስችልና የሚያስደፍር አስቻይ ሁኔታ የለም የሚሉት አቶ አበበ፣ ‹‹አሁን ሁሉም የፖለቲካ ኃይል ገዥውን ጨምሮ በቅድሚያ አገሪቱንና ሕዝቡን የማረጋጋት፣ ሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ደኅንነትን የመመለስ አጀንዳ ላይ ቅድሚያ ተሰጥቶ መሠራት አለበት፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ያክላሉ፡፡

እንደ እሳቸው አረዳድ አሁን በአገሪቱ የሚገኙት ምስቅልቅሎች የተረጋጋ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ምርጫ ለማከናወን የሚያስችሉ አይደለም፡፡ ‹‹ስለዚህ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ይካሄድ ወይስ ይራዘም የሚለውን ቀልድ ትተን፣ መሠረታዊ ወደ ሆነው አገርና ሕዝብን የማረጋጋት ሥራ መረባረብ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት እንስጥ፤›› ብለዋል፡፡

ከምርጫ ማከናወን ጋር በተያያዘ የተጻፉ በርካታ መጣጥፎች እንደሚያሳዩትም፣ የፖለቲካ አስተዳደር ለውጥ በማድረግ ላይ ባሉ አገሮች የሚደረጉ ምርጫዎች አብዛኛውን ጊዜ ለነውጥና ላለመረጋጋት ምክንያት መሆናቸውን ያትታሉ፡፡

በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና የፖለቲካ ቡድኖች ባለቡት አገር፣ ውሉ ባለየ የለውጥ እንቅስቃሴ ሰሞን ምርጫ ማከናወን ከፍተኛ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ አለመረጋጋቶችንና ምስቅልቅሎችን እንደሚያስከትል በስፋት ይገልጻሉ፡፡ ይህንን አተያይ በመጋራት በርካቶች ምርጫ ለማድረግ ከመቸኮል ይልቅ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋትና የሚያግባቡ የጨዋታ ደንቦች ማዘጋጀት፣ እንዲሁም ተቋማትን ማጠናከር ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

ምንም እንኳን እንዲህ ያሉ አተያዮች በስፋት የሚሰሙ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ፖለቲካ ተዋናይ የሆኑ ኃይሎች ቀጣዩ ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መካሄድ አለበት የሚል አስተያየታቸውን አስረግጠው ይሰነዝራሉ፡፡

ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መካሄድ አለበት ብለው ከሚሞግቱ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የሚጠቀሰው ደግሞ፣ ከኢሕአዴግ መሥራች ፓርቲዎች አንዱ የሆነው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አንዱ ነው፡፡

የሕወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በክልል ደረጃ በአክሱም ከተማ የተከበረውን የግንቦት 20 በዓል አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር፣ የፓርቲውን አቋም በድጋሚ አስረግጠው አስታውቀዋል፡፡

‹‹በቀጣዩ ዓመት የሚደረገውን ምርጫ በወቅቱና በአግባቡ አለማድረግ ሕገ መንግሥቱንና ፌዴራላዊ ሥርዓቱ እንዲፈርስ መፍቀድ ማለት በመሆኑ፣ የሚፈለገውን ሁሉ በማድረግ ሁሉን ያሳተፈና ያማከለ በማድረግ ማካሄድ ለአገር ያለው ትርጉም ከፍተኛ በመሆኑ ሁሉም ሊታገልለት ይገባል፤›› ሲሉ የፓርቲያቸውን አቋም ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ምርጫ ለማከናወን አስቻይ ነው ወይ የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ነው፡፡ በተለይ ከታኅሳስ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋማዊ ለውጥ ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ የሚገልጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አባላቱ እንኳን ገና ያልተሟሉለት ከመሆኑና በቀረው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ይቻላል ወይ ከሚሉ ጥያቄዎች አንፃር ምርጫው ካልተካሄደ፣ ሕገ መንግሥቱና ፌዴራላዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ይወድቃል በሚል አመለካከት ብቻ ድኅረ ምርጫ የሚያመጣውን ችግር ለመጋፈጥ መዘጋጀት ጀብደኝነት ነው በማለት የሚኮንኑ ድምፆች ተበራክተዋል፡፡

ቦርዱ ከሚኖሩት አምስት አባላት መካከል እስካሁን አራቱ ያልተሾሙ ሲሆን፣ አራቱን የመመልመል እንቅስቃሴ እንኳን የተጀመረው ገና በቅርቡ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማ ሹመታቸው ፀድቆላቸው በሥራ ላይ የሚገኙት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ለማነፃፀሪያነት አምስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ ቢወሰድ እንኳን፣ ምርጫው አንድ ዓመት ሲቀረው በርካታ የዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸው የሚታወስ ነው፡፡

በምርጫ 2007 ወቅት ቦርዱ ምርጫውን ከማስፈጸም ጋር የተያያዙ 30 ያህል ዓበይት ክንውኖችን አቅዶ በጥቅምት ወር 2007 ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ እነዚህን ጉዳዮች በዝርዝር በጊዜ ሰሌዳው ከማካተቱ በፊት የተደረጉ ሥራዎች ወራት መውሰዳቸውንም በወቅቱ በሒልተን ሆቴል ተሰጥቶ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተጠቅሶ ነበር፡፡

በዚህ ሥሌት መሠረት ቀጣዩ ምርጫ በተያለዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማድረግ ቢያንስ ቢያንስ አሁን ዝግጅቶች መጀመር የሚኖርባቸው ቢሆንም፣ ምርጫውን በበላይነት የሚያከናውነው የምርጫ ቦርድ አባላት እንኳን ገና አልተሟሉም፡፡ ይህም ካለው የፖለቲካ መካረር ጋር ተደምሮ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያስመስለዋል፡፡

ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ምርጫውን ለማድረግ ካለው ፍላጎት አንፃር፣ ‹‹ከአንድ ዓመት በኋላ ምርጫ ለማድረግ የምንዘጋጅ አይመስልም፤›› በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት የአረና ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አረና) ሊቀመንበር አቶ አብርሃ ደስታ ናቸው፡፡

‹‹በእኛ ፓርቲ አረዳድ ምርጫ የአንድ ቀን ሥራ ስላልሆነ፣ አሁን ምርጫው መካሄደ አለበት ወይም መራዘም አለበት ብሎ መከራከር አስፈላጊ አይደለም፡፡ ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ ከምርጫው ጋር የተያያዙ ዝግጅቶችና እንቅስቃሴዎች አሁን መጀመር አለባቸው፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ እየተመለከትን አይደለም፡፡ ስለዚህ በሌላ አባባል ምርጫው ተራዝሟል ወይም ይራዘማል የሚል ትርጉም ነው ያለው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲካሄድ ነው የምንፈልገው፣ ካልተደረገም አይገርመንም፡፡ ምርጫን የተመለከቱ ዝግጅቶች ካልተጀመሩ ምርጫው ይራዘም አይራዘም የሚለው ጉዳይ አላስፈላጊ ክርክር ነው፤›› በማለት የአስቻይ ሁኔታዎች መቅደምን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለመከናወን አንድ ዓመት ብቻ የሚቀረው ጠቅላላ ምርጫ በጊዜው ይካሄዳል ወይስ ይራዘማል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ቢሆንም፣ በርካቶች ግን በቅድሚያ የአገሪቱን ሰላም፣ ፀጥታና ደኅንነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው በማለት ይሟገታሉ፡፡ ለዚህም የሚያነሱት መከራከሪያ ደግሞ እነዚህ ነገሮች በሌሉበት ሁኔታ ምርጫ ማከናወን ሥርዓትን ብቻ ሳይሆን አገርን ያከስራል የሚል ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች