የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን እንይ ጄኔራል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርንና የቀድሞ ሥራ አስኪያጁን አቶ ፍቃዱ ኃይሌ (ኢንጂነር) ጨምሮ፣ ስድስት ግለሰቦችን በ3,799,503 ብር ዕዳ ከሰሰ፡፡
ባለሥልጣኑ ክስ የመሠረተው እንይ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ከዓለም ባንክ እስከ የሺ ደበሌና ከሾላ የረር በር ድረስ ያለውን የመንገድ ፕሮጀክት ቀሪ የአስፋልት ሥራ ለማጠናቀቅ፣ 400 ቶን ሬንጅ በሁለት ወራት ውስጥ ለመመለስ ከባለሥልጣኑ ተበድሮ ሳይመለስ በመቅረቱ እንደሆነ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረበው የፍትሐ ብሔር ክስ ያስረዳል፡፡
ኮንትራክተሩ የገጠመውን የሬንጅ እጥረት ጠቅሶ ለባለሥልጣኑ የጻፈውን የብድር መጠየቂያ ደብዳቤ፣ የቀድሞ የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ እንዲወስድ እንደፈቀዱለትና 399.85 ቶን ሬንጅ መውሰዱንም ባለሥልጣኑ በክሱ ጠቁሟል፡፡ ነገር ግን ኩባንያው በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ እንደሚመልስ ተስማምቶ የወሰደውን የሬንጅ ብድር ሊመልስ ባለመቻሉ፣ በተደጋጋሚ ደብዳቤ እንደተጻፈለትም አክሏል፡፡
ይኼንንም ሊያደርግ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሁሉም ተከሳሾች ባልተነጣጠለ ኃላፊነት የጠቀሰውን ገንዘብ እንዲከፍሉት ዳኝነት ጠይቋል፡፡ እንይ ኩባንያ የወሰደውን የአስፋልት ሬንጅ በዓይነት ከመመለስ ወይም በወቅቱ የገበያ ዋጋ ተመላሽ ከማድረግ ይልቅ፣ ከአራት ዓመት በኋላ በቶን 24,703 ብር መሆን ሲገባው የተገዛበትን ዋጋ (የስቶክ ዋጋ) መሠረት በማድረግ 3.5 ሚሊዮን ብር ብቻ የመለሰ መሆኑን ገልጿል፡፡ በሁለተኛ ዙር በብድር የወሰደውን የአስፋልት ሬንጅ በተገዛበት ዋጋ ሲመልስ በወቅቱ የነበረው የአንድ ቶን ሬንጅ የገበያ ዋጋ 17,532 ብር ሲሆን፣ ተመላሽ ማድረግ የነበረበት የ128.64 ቶን ሬንጅ ዋጋ 2,255,433 ብር መሆን እንደነበረበትም ባለሥልጣኑ በክሱ አብራርቷል፡፡
ነገር ግን የተገዛበትን የስቶክ ዋጋ መሠረት በማድረግ፣ ከክፍያው ተቆርጦ 1,667,211 ብር ብቻ መሆኑንም አክሏል፡፡ እንይ በአጠቃላይ ተመላሽ ማድረግ የነበረበት 3,797,503 ብር መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ በወቅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ፍቃዱ (ኢንጂነር) ከአሠራር፣ ከደንብና ከሥርዓት ውጪ ሬንጁ ለተቋራጩ በብድር እንዲሰጥ በመፍቀዳቸው የተጠቀሰውን ያህል የገንዘብ ጉዳት እንዲደርስ በማድረጋቸው ክስ መመሥረቱን አስረድቷል፡፡
የባለሥልጣኑ የቀድሞ የፋይናንስ ደጋፊ የሥራ ሒደት መሪ የነበሩት አቶ አብደላ ረዲም፣ እንይ ኩባንያ በወሰደው አግባብ በዓይነት ወይም በወቅቱ በነበረው የሬንጅ ዋጋ ገንዘቡን እንዲመልስ ባለማድረጋቸው፣ በተቋሙ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ገልጿል፡፡ የግዥ ንብረትና ጠቅላላ አገልግሎት ደጋፊ የሥራ ሒደት መሪ የነበሩ አቶ ወንድምነህ ካሳ፣ እንይ የወሰደውን የሬንጅ ብድር በገባው ቃል መሠረት በወቅቱ ባለው ዋጋ ተሠልቶ 9,211,597 ብር እንዲመልስ ጽፈውት የነበረውን ደብዳቤ በመተውና አቋማቸውን በመቀየር፣ ሲበደር በነበረበት ዋጋ እንዲከፍል በመስማማትና ጉዳቱ እንዲደርስ በማድረጋቸው መከሰሳቸውን ገልጿል፡፡
የተቋሙ የኮንትራት መንገድ ግንባታ ክትትልና ቁጥጥር የሒደት ሱፐርቪዥንና የኮንትራት ፕሮጀክት ፋይናንስ አስተዳደር ኬዝቲም አስተባሪ የነበሩት አህመዲን ቡሴር (ኢንጂነር) እና አቶ ዓብይ ተክሌ፣ እንይ የወሰደውን ሬንጅ በዓይነት መመለስ ወይም በወቅቱ ዋጋ ተመላሽ እንዲያደርግ ከማድረግ ይልቅ ከአራት ዓመታት በኋላ በተገዛበት ዋጋ (ወጪ በተደረገበት) በመስማማታቸው በተቋሙ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ገልጿል፡፡ ሁሉም ተከሳሾች ያልተነጣጠለ ኃላፊነት ያለባቸው በመሆኑ ክሱን እንደመሠረተባቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በክሱ በዝርዝር ገልጾ ዳኝነት ጠይቋል፡፡