Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በቦይንግ ማክስ አውሮፕላን ላይ የተቀናጀና ግልጽ የብቃት ማረጋገጫ ሥራ እንዲከናወን ተጠየቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር የበረራ ደኅንነት ጥያቄ በተነሳበት የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላን ላይ፣ ግልጽና የተቀናጀ የብቃት ማረጋገጫ ሥራ እንዲከናወን ጥሪውን አቀረበ፡፡

ከሰኞ ግንቦት 26 እስከ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በደቡብ ኮሪያ መዲና ሶል ዓመታዊ ጉባዔውን ያካሄደው የአየር መንገዶች ኅብረት በማክስ አውሮፕላኖች በደረሱት አደጋዎች ምክንያት በተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ላይ ያለው እምነት መሸርሸሩን ገልጾ፣ የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ግልጽና የተቀናጀ አሠራር እንዲከተሉ ጠይቋል፡፡

የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ሚስተር አሌክሳንደር ዡኒያክ በማክስ አውሮፕላኖች በደረሱት  ሁለት አደጋዎች ምክንያት ኅብረተሰቡ በተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ላይ ያለው እምነት መናዱን ገልጸው፣ ሁሉም ዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ወጥ የሆነ የተቀናጀ የብቃት ፍተሻ እንዲያከናውኑ አሳስበዋል፡፡ አውሮፕላኑን መልሶ ወደ ሥራ ለማስገባት የሚደረገው እንቅስቃሴም ወጥነት ያለው፣ ከአየር መንገዶችና ከተለያዩ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት ጋር በመተባበር መሆን እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡

ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የሦስተኛ ዓለም አገሮች አብራሪዎችን ዝቅ አድርጎ የመመልከት አባዜ በምዕራባዊያን አካባቢ ይታያል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አሌክሳንደር ዡኒያክ፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ አውሮፕላኑ እንጂ አብራሪዎቹ ሲወቀሱ እንዳልሰሙ ተናግረዋል፡፡

በጉባዔው ላይ በተካሄው የፓናል ውይይት ላይ የሉፍታንዛና የሲንጋፖር አየር መንገዶች ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ማክስ አውሮፕላንን ወደ ሥራ ለማስመለስ የተለያዩ ተቆጣጣሪ ተቋማት በተናጠል የሚከተሉት አሠራር ሥጋት እንደጫረባቸው ገልጸዋል፡፡ የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን የማክስ አውሮፕላን እንዲበር ፈቃድ ሰጥቶ፣ የአውሮፓ አቪዬሽን ሴፍቲ ኤጀንሲ ፈቃድ ለመስጠት የተራዘመ ጊዜ የሚወስድ ከሆነ ለኢንዱስትሪው ፈተና እንደሚሆን ዋና ሥራ አስፈጻሚዎቹ ገልጸዋል፡፡

በጉባዔው ላይ የተሳተፉትን የቦይንግ ኩባንያ ተወካዮችን ሪፖርተር ለማነገጋገር ጥረት ቢያደርግም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

በጉባዔው ላይ የታደሙት የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ቦርድ አባልና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማክስ አውሮፕላንን በቀዳሚነት ወደ ሥራ እንደማይመልስ አስታውቀዋል፡፡

የአሜሪካ ፌዴራል አቪዬሽን አድሚኒስትሬሽን የሚያካሂደውን የብቃት ፍተሻ ሥራ አየር መንገዱ እንደሚያጤነው ገልጸው፣ ሌሎች እንደ አውሮፓ አቪዬሽን ሴፍቲ ኤጀንሲ ያሉ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣናት የብቃት ማረጋገጫውን እንዴት ይቀበሉታል የሚለውን እንደሚከታተል ተናግረዋል፡፡ ‹‹እኛ በአደጋው በቀጥታ ተጎጂ በመሆናችን አውሮፕላኑን ለማብረር የመጨረሻዎቹ እንጂ የመጀመርያው አንሆንም፤›› ሲሉ አቶ ተወልደ የአየር መንገዱን አቋም አረጋግጠዋል፡፡ 

አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ስም የገነባ በመሆኑ የደረሰበትን አደጋ ተቋቁሞ፣ የጀመራቸውን የማስፋፊያ ሥራዎቹን አጠናክሮ መቀጠሉን አክለው ገልጸዋል፡፡  

አንድ መቶ ያህል ማክስ አውሮፕላኖችን ከሥራ ውጪ ያደረገችው ቻይና 580 ሚሊዮን ዶላር ኪሣራ እንደደረሰባት ያሳወቀች ሲሆን፣ አራት ማክስ አውሮፕላኖችን ያቆመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የደረሰበትን የገንዘብ ጉዳት ገና እንዳላሰላ አቶ ተወልደ ጠቁመዋል፡፡

የቦይንግ ኩባንያ ከፍተኛ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር በርናርድ ቾይ፣ ኩባንያቸው ከማክስ አውሮፕላን ባለቤት ከሆኑ አየር መንገዶች ጋር በመወያየት ላይ እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች