Saturday, June 15, 2024

ውስብስቡን የኢትዮጵያ ችግር ለመፍታት ጥልቀት ያለው ዕይታ ያስፈልጋል!

ተደጋግሞ እንደሚነገረው የኢትዮጵያ ችግር ለዓመታት ሲንከባለል የመጣ ሲሆን፣ በጣም ውስብስብና አታካች ነው፡፡ ነገር ግን ይኼንን የዘመናት ውስብስብ ችግር ለመፍታት የሚያስፈልገው በተለያዩ መስኮች ዕውቀት፣ ብስለት፣ ቅንነትና ጥልቀት ያለው ዕይታ ነው፡፡ አሁን በስፋት እንደሚታየው በስሜታዊነትና በግብታዊነት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች፣ ጊዜያዊ እርካታ ከማስገኘትና ቆይቶ ደግሞ ከመሰልቸት ያለፈ ፋይዳ የላቸውም፡፡ በተለይ ለውጥ በሚካሄድባት አገር ውስጥ ከጊዜያዊ ሆይ ሆይታና ግርግር ውስጥ በፍጥነት በመውጣት የተቋማት ግንባታና የሕግ ማዕቀፎች ላይ በፍጥነት ካልተሠራ፣ የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ የእምቧይ ካብ ከመሆን አያልፉም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ከሚጠበቁበት ተግባራት መካከል አንዱ፣ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት በማስፈን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያግዙ መደላድሎችን ማመቻቸት ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ሕግ ማስከበር፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ያለ ምንም መስተጓጎል እንዲከበሩ ማድረግ፣ የፍርድ ቤቶችን ነፃነት ማረጋገጥ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን መክፈትና መጪው ምርጫ ዓለም አቀፍ ደረጃን ጠብቆ እንዲካሄድ የሚረዱ ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ችግርን መፍታት የሚጀመረው እንዲህ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊያን መብቶቻቸው በሙሉ ተከብረውላቸው በፈለጉበት ሥፍራ መዘዋወር፣ መኖር፣ መሥራትና ሀብት ማፍራት የሚችሉበት ዕድል በሥርዓተ አልበኞች እንዳይደናቀፍ ተግቶ መሥራት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው በተግባር ተረጋግጦ መታየትም ይኖርበታል፡፡ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንበት ብልሹ አሠራር ተወግዶ በኢትዮጵያ ምድር ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት መናኘት አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ከመብታቸው እኩል ግዴታቸውን መረዳት ይኖርባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያን ውስብስብ ችግር ለመፍታት በቅንነት መንፈስ በመቀራረብ አብሮ መሥራት እንጂ፣ ትከሻ ለትከሻ እየተለካኩ መናናቅ ያስገኘው ቢኖር ውድቀት ብቻ ነው፡፡ ድህነት ከመጠን በላይ በሚያናጥርባት አገር ውስጥ በትዕቢት ተሞልቶ መገፈታተርም ሆነ፣ በቂም በቀልና በጥላቻ ተሞልቶ አገር ማመስ ያተረፈው ቢኖር ፀፀት ብቻ ነው፡፡ በስሜት እየተነዱ ፀብ መቆስቆስና ማኅበረሰቦችን ማጋጨት፣ የንፁኃንን ደም ከማፍሰስና አቅመ ደካሞችን ከማንገላታት ውጪ የፈየደው የለም፡፡ ይልቁንም ለዘመናት በተቆለለ ችግር ላይ ተጨማሪ ችግር በመፍጠር የሕዝብ አንገትን ነው እያስደፋ ያለው፡፡ ይህ ደግሞ አይፈለግም፡፡

ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ካልተጨነቁ ማን ይጨነቅላቸዋል? ኢትዮጵያዊያን ካልተከባበሩ ማን ያከብራቸዋል? ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መሥራት ካልቻሉ ዕድገትና ብልፅግና ከየት ይመጣል? ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አብረው ካልማሰኑ የሚመኙትን እንዴት ያገኛሉ? በፖለቲካ አቋም ልዩነት ምክንያት የሚፈጠሩ ቅራኔዎችን በማጦዝ እርስ በርስ መሻኮት ትርፉ ተያይዞ መጥፋት ነው፡፡ ባዕዳንን ገላጋይ እያደረጉ እነሱን ደጅ መጥናት የአገር ሚስጥርን አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ባለፉት ዓመታት የተለመደ ተግባር በመሆኑ ወደፊት ተፅዕኖው በስፋት መታየቱ አይቀርም፡፡ የውጭ ኃይሎችን ገላጋይና ሸምጋይ ከማድረግ ይልቅ፣ ባህላዊውን የግጭት አፈታት ዘዴ መጠቀም ቢቻል ወደ ቀውስ ከመንደርደር ይታደጋል፡፡ ጥልቀት ያለው ዕይታ ያላቸውና ምራቃቸውን የዋጡ ጎምቱዎች ባሉባት አገር፣ እየተንደረደሩ ከውጭ ኃይሎች ጋር መላላስ ውጤቱ ለፀፀት ይዳርጋል፡፡ ውስብስቡ የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው እርስ በርስ በሚደረግ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መስተጋብር መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው ትዕግሥት አልባ ሩጫ ፋይዳ ቢስ እንደሆነ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ችግር መፍታት ስላልቻለም አገሪቱን የማያባራ መነታረኪያ አድርጓል፡፡

ምሁራንና ልሂቃን ከስሜታዊነትና ከግብታዊነት የተላቀቁ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ፣ የውይይትና የክርክር ባህል እንዲለመድ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እነሱም በማኅበራዊ ሚዲያ ከሚያደርጉት አላስፈላጊ ድርጊት ታቅበው፣ በተለይ የወጣቶች ንቃተ ህሊና እንዲጎለምስና ምክንያታዊ ሞጋች እንዲሆኑ በኃላፊነት ስሜት የመሥራት ግዴታ እንዳለባቸው ቢረዱ መልካም ይሆናል፡፡ ወጣቶችን ማንም እየተነሳ በፈለገው መንገድ እንዲነዳቸው መፈቀድ የለበትም፡፡ ማንም እንደ መንጋ እያሰማራቸው በገዛ ወገናቸው ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ የሚደረጉት፣ ስሜታቸውን መግራት ባለመቻላቸው እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ወጣቶች በዕውቀት ሲጎለምሱና አካባቢያቸውን መረዳት ሲጀምሩ ጥያቄዎችን ከማቅረብ አልፈው፣ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ ማፍለቅ እንደሚችሉ የታወቀ ነው፡፡ የወጣቶች ዕይታ ሲሰፋ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያግዙ ሥራዎች በቀላሉ ይከናወናሉ፡፡ በጨዋነትና በሥርዓት መመራት ባህል ይሆናል፡፡ አምባገነንነት የሚራባበት ሥፍራ አይኖረውም፡፡ ሕገወጥነት በሕግ አደብ ይገዛል፡፡ ለሁሉም እኩል የሆነች አገር እንድትኖር ያግዛል፡፡ የሚያዋጣው ይኼ ነው፡፡

ጨዋውና አስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው በሥርዓት መመራት እንደሆነ፣ በተለያዩ ሥፍራዎች ከተደረጉ ውይይቶችና ከሚቀርቡ አስተያየቶች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይኼንን አርቆ አሳቢና አስተዋይ ሕዝብ ጥልቀት ባለው ዕይታ በሚመራ አስተሳሰብ ፍላጎቶቹን መረዳት የግድ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያን ውስብስብ ችግር ለመፍታት የሕዝቡን መሠረታዊ ፍላጎቶች ማጤን ብቻ ሳይሆን፣ የጉዳዩ ባለቤትም ስለሆነ ተሳትፎውን በስፋት ማግኘት ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም ምሁራን፣ ልሂቃን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የትምህርት ተቋማት፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የመሳሰሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች አገራዊ ተሳትፎ ችግርን ለመፍታት ብቻ ሳይሆን፣ መፍትሔ ለማመንጨትም ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ አገር በቀል ዕውቀት የታከለበት ሥልጣኔ ማስፈን ከተቻለ የአገር ተስፋ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ አስተዋይና ጨዋ ሕዝብ ይዞ ዕይታን በመጋረድ አላስፈላጊ ድርጊቶች ውስጥ መርመጥመጥ ያስንቃል፡፡ በተለይ ፖለቲከኞችና የመብት ተሟጋቾች ነን የሚሉ ወገኖች ከሚያስንቁ ድርጊቶች ራሳቸውን ማላቀቅ አለባቸው፡፡ የተከበረች አገር ውስጥ የሚያስንቁ ድርጊቶች ውስጥ መገኘት የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ፣ ዘለቄታ ያለው ክብርና ዝና አያስገኝም፡፡ ይልቁንም ትውልድና ዘመን ተሻጋሪ ለሆነው ቁምነገር ራስን ማዘጋጀት ይመረጣል፡፡ የኢትዮጵያ ውስብስብ ችግር የሚፈታው ጥልቀት ባለው ዕይታ ነው የሚባለው ለዚህ ነው!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...

የ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

በንጉሥ ወዳጅነው ‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ...