Thursday, February 29, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት ካለበት የውጭ ብድር በዚህ ዓመት 9.4 ቢሊዮን ብር ከፈልኩ አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ካለባት የ27 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ብድር ዕዳ በበጀት ዓመቱ አሥር ወራት ውስጥ 14.2 ቢሊዮን ብር ለመክፈል ቢታቀድም፣ እስካሁን 9.4 ቢሊዮን ብር መከፈሉን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ረቡዕ ግንቦት 28 ቀን 2011 በፓርላማ የመሥሪያ ቤታቸውንና የተጠሪ ተቋማት የአሥር ወራት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት፣ በማክሮ ኢኮኖሚና በፊስካል ፖሊሲ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው እንደገለጹት፣ አገሪቱ ከውጭ አገሮች በብድር ካገኘችው 27 ሚሊዮን ዶላር ዕዳ የፌዴራል መንግሥቱ ድርሻ 15.8 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ቀሪው 11.2 ቢሊዮን ዶላር የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ድርሻ ነው፡፡

በ2011 ዓ.ም. መንግሥት የውጭ ዕዳ ለመክፈል 14.2 ቢሊዮን ብር ለመክፈል ቢያቅድም፣ እስካሁን ማሳካት የቻለው 9.4 ቢሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 66 በመቶ መሆኑን ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በበኩላቸው ምን ያህል መጠን ያለው ዕዳ እንደከፈሉ ያሉት ነገር የለም፡፡

በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ ‹‹በመልሶ›› ማበደር ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ከተሰጡ ብድሮች ውስጥ 243.84 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ በአሥር ወራት ውስጥ ከዕቅዱ በላይ ወደ 432.78 ሚሊዮን  ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

ከውጭ ዕዳ በተጨማሪ አገሪቱ ባለፉት አሥር ወራት ከውጭ መንግሥታትና ከአጋር ድርጅቶች በብድርና በዕርዳታ ያገኘችውንም ገቢ በተመለከተ በሪፖርታቸው ተዳሷል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ በ2011 ዓ.ም. ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት፣ ከዓለም አቀፍ የልማት ድርጅቶችና ከተለያዩ መንግሥታት በብድርና በዕርዳታ 5.7 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢታቀድም የተገኘው ግን 4.7 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡

ከአጠቃላይ የብድርና የዕርዳታ ገቢ ውስጥ ሁለት ቢሊዮን ዶላሩ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የተገኘ መሆኑን፣ 1.3 ቢሊዮን ዶላርና ተጨማሪ አንድ ቢሊዮን ዶላር የተገኘው በቅደም ተከተል ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማትና ከአየር ንብረት ለውጥ ድጋፍ ሰጪ መንግሥታት መሆኑን አቶ አህመድ አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም 223 ሚሊዮን ዶላር ከአውሮፓ ኅብረት ሲገኝ፣ ከኢትዮ ቻይና ትብብር ደግሞ 65 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አክለዋል፡፡

የአገሪቱ የዕዳ ክምችት ከኤክስፖርት አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር አሳሳቢ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

የኤክስፖርት አፈጻጸምን ውስንነት በዘላቂነት ለመፍታት የግል ሴክተሩን በከፍተኛ ደረጃ በማሳተፍና አላሠራ ያሉ ማነቆዎችን ለይቶ በመንቀሳቀስ፣ ኤክስፖርት ተኮር ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባም አቶ አህመድ ገልጸዋል፡፡ የኤክስፖርት ገቢ አፈጻጸም ከዓመት ዓመት ማሽቆልቆል የማክሮ ኢኮኖሚው ጤናማ አለመሆን መገለጫ መሆኑን ያወሱት አቶ አህመድ፣ የኢኮኖሚ ሚዛን ክፍተቶችን ለመሸፈን በከፍተኛ ሁኔታ እየተሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ በ2011 በጀት ዓመት አሥር ወራት ውስጥ ከኤክስፖርት 2.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ቢገኝም፣ ከ2010 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 2.3 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ187.1 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱን አስታውቀዋል፡፡

በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት በሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም. የአሥራ ሁለት ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ አጠቃላይ የፍጆታ ዋጋ ዕድገት 12.6 በመቶ መሆኑንም አቶ አህመድ ጠቁመዋል፡፡ የዋጋ ንረቱ በአንድ አኃዝ እንዲገደብ ለማድረግ ያልተቻለ ቢሆንም፣ በዝቅተኛው ሁለት አኃዝ እንዲረጋጋ ለማድረግ እንደተቻለም አብራርተዋል፡፡

በዋናነት  ለዋጋ ንረቱ የአቅርቦት ችግር፣ ውስጣዊ የፖለቲካ አለመረጋጋትና የሕግ የበላይነትን አለማክበር ምክንያቶች እንደሆኑ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ የውጭ ክፍያ ሚዛን መዛባት ለማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት ከሚጠቁሙ የኢኮኖሚ መሣሪያዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አህመድ፣ ለአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችንም ሆነ የካፒታል ዕቃዎችን በአገር ውስጥ ማሟላት እንዳልተቻለና ከውጭ ማስገባት ግዴታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት አስተማማኝ ምንጭ የሆነው የሸቀጦች የወጪ ንግድ አፈጻጸም ችግር እንደገጠመው ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

የኢኮኖሚ ሚዛን በመጠበቅ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለመፍጠር በተደረገው ጥረት፣ ባለፉት አሥር ወራት የመንግሥት ወጪ በገቢ እንዲሸፈን፣ እንዲሁም የዕዳ ጫናን ለማቃለል የሚያስችሉ ተግባራት እንደተከናወኑ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ ዕድገት ቢኖርም የዕድገት ፍጥነቱ ግን እየቀነሰ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በ2011 በጀት ዓመት ይሰባሰባል ብሎ ካቀደው 235.7 ቢሊዮን ብር ውስጥ 160.4 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ እንደተቻለም ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡ ሚኒስትሩ የመጪው በጀት ዓመት የአገሪቱ ረቂቅ በጀት ዝግጅት መጠናቀቁን፣ በዚህ ሳምንት መጨረሻም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚላክ ጠቁመዋል፡፡

በረቂቅ በጀት የሚጠየቀው ምን ያህል እንደሚሆን ሚኒስትሩ ባይገልጹም፣ በ2012 ዓ.ም. ከፍተኛ በጀት በልዩ ሁኔታ የሚመደብላቸው የመስኖ ሥራና የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡

በተለይ ለመስኖ ልማት ፕሮጀክቶቸ ቀደም ሲል የነበረው 8.5 ቢሊዮን ብር ለ2012 በጀት ዓመት ወደ 14.5 ቢሊዮን ብር ከፍ እንደሚል አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡ በመጪው ዓመት ለክልሎች የሚመደበው ረቂቅ የበጀት ድጋፍ ጠቋሚ ጣሪያ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በተሰጠው የበጀት ማከፋፈያ ቀመር መሠረት ተዘጋጅቶ፣ ለክልል መንግሥታት ከመንግሥት ግምጃ ቤትና ከውጭ ብድርና ዕርዳታ ምንጮች የሚያገኙትን የፋይናንስ መጠን በመወሰን ሁሉም ክልሎች እንዲያውቁ መደረጉንም ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች