‹‹ገለልተኛ ሜዳ›› የሚለውን የፌዴሬሽኑን ውሳኔ አልተቀበለውም
የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ በ‹‹ፀጥታ ችግር›› ሳቢያ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተሰረዘበትን ጨዋታ በተለዋጭ ዝግ ስታዲየም ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር በአዳማ እንዲያካሂድ የተላለፈበትን ውሳኔ በመቃወም ጨዋታውን እንደማያካሂድ ይፋ አድርጓል፡፡ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሊግ ኮሚቴ በበኩሉ፣ ፕሪሚየር ሊጉ በወጣለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ይጠናቀቅ ዘንድ የተቋረጠው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ግንቦት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ ስታዲየም እንዲካሄድ ወስኗል፡፡
ሁለቱ ክለቦች ባለፈው እሑድ ግንቦት 25 በአዲስ አበባ ስታዲየም ሊያካሂዱት የነበረው 27ኛ ሳምንት ጨዋታ፣ በፀጥታ ሥጋት ሰበብ የተሰረዘው ጨዋታ አስተናጋጁ ቡድን በሜዳውና በደጋፊው ፊት የሚያከናውነው የደርሶ መልስ መርሐ ግብር ነበር፡፡ ይህ ጨዋታ በ34 ነጥብ በወራጅ ቀጣና አካባቢ ለሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ወሳኝ ከመሆኑ ባሻገር በሜዳ ገቢ ተጎጂ የሚያደርገው እንደሆነም እየተነገረ ይገኛል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለኢትዮጵያ ቡና ግንቦት 26 ቀን በጻፈው ደብዳቤ ‹‹የፕሪሚየር ሊጉ መርሐ ግብር በወጣው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ይህ ውድድር ግንቦት 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀኑ 9.00 በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታው ተመልካች በሌለበት በዝግ እንዲደረግ የተወሰነ በመሆኑ የኢትዮጵያ ቡናና የመቐለ 70 እንደርታ እግር ኳስ ክለቦች በወጣው ፕሮግራም መሠረት በዕለቱና በሰዓቱ በቦታው በመገኘት ውድድራችሁን እንድታከናውኑ የሊግ ኮሚቴ ያስታውቃል፤›› በማለት ለሁለቱ ቡድኖች በአድራሻቸው አሳውቋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለዚህ ውሳኔ የበቃው፣ ከሁለቱ ቡድኖች ውድድር ጋር ተያይዞ ጨዋታው በአዲስ አበባ ስታዲየም ቢደረግ ሊከሰት የሚችለው የፀጥታ ሥጋት ከፌዴራል ፖሊስና ጉዳዩ በአንድም ሆነ በሌላ ከሚመለከታቸው አካላት በደረሰው መመርያ መሠረት እንደሆነ የፌዴሬሽን ምንጮች ለሪፖርተር ይገልጻሉ፡፡ ይሁንና ውሳኔው በተለይ ለባለሜዳው ቡድን ኢትዮጵያ ቡና ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ጎን ከግምት ማስገባት ሲኖርበት ያንን አለማድረጉ፣ ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ ቡና የሚደርስበትን ፍትሐዊ ያልሆኑ አካሄዶችን ለፌዴሬሽኑ በቃልና በጽሑፍ ገልጾ ምላሽ አለማግኘቱ እየተነገረ ይገኛል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ቡና የፌዴሬሽኑ ውሳኔ በደረሰው ቅጽበት ማለትም ግንቦት 26 ቀን በጻፈው ደብዳቤ፣ ‹‹ክለባችን በ25/09/2011 ዓ.ም. ከመቐለ 70 እንደርታ ቡድን ጋር በሊጉ 27ኛ ሳምንት ጨዋታ ለውድድር መቅረቡ ይታወሳል፡፡ ሆኖም በእኛ በኩል ምንም ዓይነት ጥፋት ሳንፈጽም በዕለቱ ውድድር ሳይጀመር መሰረዙ ተገልጾልናል፡፡ በማግሥቱ ጨዋታውን በወጣው ፕሮግራም በአስተናጋጅነታችን፣ በሜዳችን የሚካሄድበት ፕሮግራም ይላካልናል ብለን ስንጠብቅ፣ በ26/09/2011 ዓ.ም. ውድድሩ በ27/09/2011 ዓ.ም. በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በዝግ እንደሚካሄድ የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰን፡፡
‹‹ከፍተኛ ወጪ አውጥተን ወደ መቐለ በመጓዝ በከተማችንም ቡድናችንን በማዘጋጀት ያወጣነው ወጪ ከግምንት ሳይገባ የዚህ ዓይነቱ ውሳኔ መሰጠቱ በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡
‹‹በሌላ በኩል እኛ መቐለ ለውድድር ሄደን የደረሰብንን በደል በቃልና በተጨማሪም በጽሑፍ ሦስት ጊዜ ውሳኔ እንዲሰጠን ስንጠይቅ ምንም ሳይወሰን ዛሬ በእኛ ላይ በምሽት ስብሰባ ተደርጎ የተሰጠው ውሳኔ በእጅጉ ያሳዘነን ከመሆኑ በላይ ክለባችን ከሜዳው የሚያገኘውን ገቢ በማቋረጥና ለአዳማ ጉዞ የምናወጣው ወጪ የከተማዋን ነዋሪና ደጋፊ ሞራል የሚነካ፣ ሁኔታን በመፍጠር ተጫዋቾቻችንን ለአስፈላጊ እንግልት የሚዳርግ ከመሆኑ ባሻገር የሞራልና የአካል ድክመት የሚፈጥር በመሆኑ ክለባችን አይቀበለውም፡፡
‹‹በጋራ ያቋቋምነው ፌዴሬሽን ለሊግ ኮሚቴ ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ የዝግ ስታዲየም ጨዋታ ውሳኔ መስጠት የፌዴሬሽኑ የፍትሕ አካል መሆኑ እየታወቀ ሊግ ኮሚቴ ያሳለፈው ውሳኔ ሕገወጥ ስለሆነ ውሳኔው ተሸሮ በሜዳችን ለተመልካቾች ክፍት በሆነ ስታዲየማችን እንድንጫወት ይደረግ ዘንድ እየጠየቅን ከዚህ ውጪ ያለ አማራጭ ክለባችንን የሚጎዳ ስለሆነ የማንቀበለው መሆኑን እንገልጻለን፤›› በማለት ኢትዮጵያ ቡና ለፌዴሬሽኑ ውሳኔ ያለውን አቋም ግልጽ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና የመቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ እንዲቋረጥ ፀጥታውን በተመለከተ የሚመለከተው አካል ውሳኔ ተገቢነቱ ባያከራክርም፣ ፌዴሬሽኑ ባስተላለፈው ውሳኔ ግን ብዙዎቹ የስፖርት ቤተሰቦች ተከፍተዋል፡፡ በበዛ መልኩ ትችት እያስተናገደ ይገኛል፡፡
ከመነሻው የፀጥታ ችግር ቢኖር እንኳን ስታዲየም የታደመውንና የጨዋታውን መጀመር በመጠባበቅ ላይ የነበረውን ደጋፊ ከስታዲየሙ በኃይል ለቅቆ እንዲወጣ ማስደረጉ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ ይህም ሳያንስ የክለቡ ደጋፊዎችም ሆኑ ሌሎች የማይመለከታቸው ወገኖች በየመንገዱ በፀጥታ ኃይሎችና ሠራተኞች ወከባና ድብደባ ሲፈጸምባቸው መታየቱ ጉዳዩ እንዲካረር አድርጓል፡፡
በሌላ በኩል በዕለቱ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተለይ ከፀጥታው ጋር ተያይዞ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ የበዛ እንደሚሆን መረጃው ከደረሳቸው ስታዲየሙ ክፍት ተደርጎ ትኬት እንዲቆረጥ ማድረግ ትክክል እንዳልነበረ የሚናገሩ አሉ፡፡