Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርልማታዊ መንግሥት ሸሸ ወይስ አፈገፈገ?

ልማታዊ መንግሥት ሸሸ ወይስ አፈገፈገ?

ቀን:

በሔኖክ ጥላሁን

በታኅሳስ 2010 ዓ.ም. ታትሞ የወጣው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) የንድፈ ሐሳብ መጽሔት ‹‹ኒዮ ሊበራሊዝም ሸሸ ወይስ አፈገፈገ?›› በሚል ርዕስ ሰፊ ርዕዮተ ዓለማዊና ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ትንታኔ በመስጠት፣ ኒዮ ሊበራሊዝም የገጠሙትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ በእርግጥ ጽሑፉ የወጣበት ወቅት ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጠንካራ ተቃውሞ በገጠመው ወቅት መሆኑ ምክንያታዊ ትንታኔ ሳይሆን፣ ከነበረበት ጫና በመነሳት ትኩረት ማስቀየሪያ ነው ብለው ያሰቡ በርካቶች ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በገጠመው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት የሚከተላቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍልስፍናዎች ጊዜ ያለፈባቸውና የአተገባበር ችግር ያለባቸው መሆናቸውን በማንሳት ‹‹የአገሪቷ መፃኢ ዕድል ምን ይሆን?›› የሚል ሥጋት በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ በዚህ የለውጥ ወቅትም አገሪቱ ላለፉት ከሃያ ላላነሱ ዓመታት ስትከተለው የነበረውን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም ተገቢነትና አስፈላጊነት በማንሳት ከመወያየትና ከመከራከር በላይ፣ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሌለ ብዙዎችን ሊያግባባ ይችላል፡፡ በዚህ መሠረት ልማታዊ መንግሥት በኢትዮጵያ የመጣበት መንገድ ያስገኘውን ውጤትና ቀጣይ ዕጣ ፈንታውን ዝርዝር ሐሳቦችን በማንሳት፣ ውይይት ማድረግና ትንታኔ መስጠት ተገቢና ወቅታዊ ይሆናል፡፡

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የምሥራቅ እስያ አንዳንድ አገሮች በተለይም ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ያስመዘገቡት ፈጣንና አስገራሚ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ዓለም ተጨማሪ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም እንድታይ አስገድዷታል፡፡ በጃፓን የተጀመረው በመንግሥት ፊት አውራሪነት (State-led) የሚመራ የልማት ጉዞ ኮሪያን፣ ታይዋንን፣ ሲንጋፖርንና በእዚያን ጊዜ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር ትገኝ የነበረችውን ሆንግ ኮንግን አቋርጦ ቻይናን በማዳረስ በሰው ልጆች ታሪክ ባልታየ ሁኔታ  አገሮቹን ወደ ታላቅነት ሕዝቦቻቸውንም ወደ ብልፅግና ማማ አውጥቷቸዋል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማግሥት ጀምሮ ብቅ ያለው የልማታዊ መንግሥት (Developmental State) አስተሳሰብ በሦስተኛው ሚሊንየም መጀመርያ ከግማሽ ደርዘን የሚልቁ አገሮችን ሥር ከሰደደ ድህነት ወደ ኢንዱስትሪ ማዕከልነት አሸጋግሯል፡፡ በተለይም በ1950ዎቹ (እ.ኤ.አ.) መጀመርያ በጦርነት ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረውና ከፍተኛ የጦርነት ሥጋት አንዣቦባቸው የነበረባቸውን ደቡብ ኮሪያና ታይዋንን በዚሁ ርዕዮተ ዓለም ታሪካቸው እስከ መጨረሻው ተቀይሯል፡፡ በኋላም ከ1978 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ ኢኮኖሚዋን በጎረቤቶቿ አምሳያ የቀረፀችው ቻይናም ከ40 ዓመታት በላይ ሳይፈጅባት አሜሪካን ተከትላ የምድራችን ባለ ሁለተኛ ደረጃ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆን ችላለች፡፡

በርካታ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ምሁራን በልማታዊ መንግሥት ምንነት ላይ የተለያዩ ትርጉሞችን ያስቀምጣሉ፡፡ እዚህ ላይ ሮስቶው የሚባለውን ጸሐፊ ማንሳቱ ግድ ይላል፡፡ አሁን በኢኮኖሚ አደጉ የሚባሉ አገሮች ዕድገታቸውን ሲጀምሩ ዛሬ እንደሚሰጡን የተሳሳተ ምክር ሳይሆን፣ መንግሥት በኢኮኖሚ ውስጥ መሠረታዊና ወሳኝ ሚና እንደነበረው በ15ኛው ክፍለ ዘመን ሆላንድን፣ በ17ኛውና በ18ኛው ክፍለ ዘመን እንግሊዝና ፈረንሣይን በምሳሌነት ያነሳል፡፡ በዚሁ ዙሪያ ጥልቅ ምርምር በማድረግ የሚታወቀው ሌላው ምሁር ቻልመርስ ጆንሰን “MITI and the Japanese Miracles›› በሚለው መጽሐፉ የልማታዊ መንግሥት መጀመርያ በቢስማርክ ዘመን ወደነበረችው ፕሩሲያና በሜይጅ ዘመን ወደነበረችው ጃፓን በመውሰድ፣ ‹‹ይህ አስተሳሰብ ከአሜሪካና ከሩሲያ የርዕዮተ ዓለም ግጭት በላይ የሆነ ‘Capitalist Developmental State የፖለቲካና ኢኮኖሚ ሥርዓት ነው፤›› ይላል፡፡ ከላይ ከተሰጡት አብነቶችና ማብራሪያዎች  በመነሳት ልማታዊ መንግሥትን ስንረዳው፣ መንግሥት በተመረጠና ጉድለት በታየበት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ የሚፈቅድና በካፒታሊስት የኢኮኖሚ ክልል ውስጥ የሚገኝ ልማትን እንደ ዋንኛ አጀንዳ አድርጎ የሚወስድ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አስተሳሰብ ነው ብለን ልንረዳው እንችላለን፡፡

በአፍሪካ ከቅኝ አገዛዝ በኋላ በ1960ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ያስመዘገበችው ከ2.5 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ዕድገት በልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ የተቃኘ እንደነበር፣ በኋላም በምዕራቡ ዓለምና እነሱ በመሠረቷቸው ዓለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት አስገዳጅነት “Structural Adjustment Program (SAP) ያደረጉት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ፖሊሲዎች ማሻሻያ በሚል የጫኑት ፕሮግራም፣ አስቀድሞ ተስፋ ታይቶበት የነበረውን ዕድገት እንደቀለበሰው ይከራከራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከሁለት አሥርት ዓመታት በኋላ በርካታ የአፍሪካ መንግሥታት በገጠማቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ አማራጭ እንዲያዩ በመገደዳቸው፣ በእስያ ውጤታማ የሆነውን የልማታዊ መንግሥት አንደ መፍትሔ እንዲወስዱ እንዳደረጋቸው የቅርብ ጊዜ ሀቅ ነው፡፡ ቦትስዋና፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሪሺየስ፣ ሩዋንዳና ኢትዮጵያን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡ በአሁኑ ወቅት በርከት ያሉ የአፍሪካ አገሮች የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብን በፖሊሲዎቻቸው በማካተት ተነፃፃሪ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ላለፉት 17 ዓመታት የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለምን በመከተል ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የምዕራብ አገሮች ተቋማት ሳይቀር በአድናቆት የሚያወሱት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከ2000ዎቹ (ዓ.ም.) አጋማሽ ጀምሮ ባሉት ጥቂት ዓመታት ርዕዮተ ዓለሙን በአግባቡ ባለመተግበርና በቅርቡ ደግሞ፣ በአገሪቱ በመጣው የፖለቲካ ለውጥ ምክንያት ‘ልማታዊ መንግሥቱ ወዴት አለህ?’ የሚሉ ጥያቄዎች እንዲነሱ በር ከፍቷል፡፡

ልማታዊ መንግሥት በኢትዮጵያ

በ1924. . . . አፄ ኃይለ ሥላሴ የንግሥና መንበሩን ከተቆናጠጡ ጥቂት ዓመታት በኋላ አገሪቷን ወደተሻለ የልማትና የቴክኖሎጂ ዕድገት ለመውሰድ በነበራቸው ጉጉትና ፍላጎት የተነሳ፣ ጥቅምት 1924 .ም. የኢትዮጵያ በሥልጣናትና ምሁራንን ያቀፈ የልዑካን ቡድን ወደ ጃፓን ላኩ፡፡ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደ ሥላሴከበደ ሚካኤልና ሌሎች አባላትን የያዘው ይኼ ቡድን በወቅቱ “Japanizers” በመባል ይታወቃል፡፡ ይህ ቡድን ከጃፓን አስገራሚ የልማት ጉዞ ልምድ ለመቅሰም አልሞ ወደዚያው ተጓዘ፡፡ የኢትዮጵያና የልማታዊ መንግሥት ትውውቅም አንድ ብሎ ጀመረ፡፡ ጌዲዮን ጃለታ በ2012 (እ.ኤ.አ.) ባሳተመው ጽሑፍ እንደገለጸው የተላከው የልዑካን ቡድን በጃፓን የሥልጣኔ ጉዞየቴክኖሎጂ ግኝትሌሎች የዕድገት ምክንያቶችን በተመስጦ ለማጥናት ጥረት እንዳደረገ ጠቅሷል፡፡ የከበደ ሚካኤል ጃፓን እንደ ምን ሠለጠነች? የሚለው መጽሐፍም የዚህ ጉዞና ጥናት ውጤት እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡ ይሁን እንጂ የጃፓን የዕድገት ሞዴል በኢትዮጵያ በሚፈለገው መንገድ ተተግብሮ ውጤት እንዳላመጣ ታሪካችን ያስረዳል፡፡ ለዚህም እንደ ዋነኛ ምክንያት ከሚጠቀሱት መካከል ወደ ጃፓን የተጓዘው ቡድን ጥልቅና በቂ ጥናት አለማድረጉ፣ በወቅቱ የነበረው መንግሥት ለልማታዊ መንግሥት ሞዴል ተገቢ ትኩረት አለመስጠቱና በኋላም አገሪቷ ወደ ጦርነት መግባቷ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ የጃፓን ሞዴል (የልማታዊ መንግሥት) ፅንሰ ሐሳብም በኢትዮጵያ ከጥቂት ግለሰቦች የዘለለ ዕውቅናው ሳይስፋፋ ለዘመናት ተረስቶ ኖረ፡፡

1983 .ም. . .  ኢትዮጵያን ለአሥራ ሰባት ዓመታት ሲያስተዳድር የነበረው ወታደራዊና ሶሻሊስት መንግሥት መጨረሻ ዓለምን ለሁለት ወጥረው ሲፋተጉ የነበሩት የምዕራቡ ዓለም ካፒታሊዝምና ሩሲያ መራሹ ሶሻሊዝም ፍትጊያ ማብቂያና የአንድ አስተሳሰብ ልዕልና መጀመርያ፣ በ1960ዎቹ የማርክሳዊ አስተሳሰብ አራማጅ ወጣቶች የተደረገ ትግል ማክተሚያና የአዲስ መንግሥት መጀመሪያ፣ የምዕራቡ ዓለም ከቀዝቃዛ የዓለም ጦርነት በኋላ ያገኘውን ድል በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት ለማጠናከር ተፅዕኖውን ያበረታበት ወቅት አዲሱ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የተረከበውን ባዶ ካዝና ከምዕራቡ ዓለም በሚገኝ ምፅዋት ለመሙላት ደጅ የጠናበት ወቅት ነበር፡፡ የማርክሳዊ ሌኒናዊ አስተሳሰብ አቀንቃኝ በሆኑ የ1960ዎቹ ወጣቶች የሚመራው አዲሱ መንግሥት አገሪቱን ከገባችበት የኢኮኖሚ ችግር ለማውጣት ሲከተል የነበረውንና ሲታገልለት የኖረውን ርዕዮተ ዓለም ከጠረጴዛው ሥር ማስቀመጥ ግድ የሆነበት ጊዜም ነበር፡፡ በተለይም በ1970ዎቹ መጀመሪያ በአሜሪካ የሬገንበታላቋ ብሪታንያ የታቸር በኒዮ ሊበራሊዝም የፖለቲካ ጽንሰ ሐሳብ ፍቅር የከነፉበትና ዓለም አቀፍ የገንዘብና የንግድ ተቋማትን ጭምር ለጉዳይ አስፈጻሚነት ሥምሪት የሰጡበት ወቅትም ነበር፡፡

ከቅኝ አገዛዝ ተላቀው በተስፋ አዲሱን ጊዜ የጀመሩ የአፍሪካ አገሮች ለብድርና ለዕርዳታ ወደ ምዕራባውያን መንግሥታትና የፋይናንስ ተቋማት በስፋት ያመሩበት ጊዜ ሲሆን፣ ኢሕአዴግም ከትግል ሜዳ ይዞ የመጣውን የማርክሳዊ ሌኒናዊ ፍልስፍና በይፋ ለመጣልም ለማንሳትም አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት ሁኔታ መፈጠሩን ያስተዋሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ የምዕራቡን ዓለም ይሁንታ ላለማጣት መንግሥታቸው ነጭ ካፒታሊዝምን እንደሚከተል በአንድ ስብሰባ እንደተናገሩ በቅርቡ በሞት የተለዩት የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ‘ዳንዲ’ በተባለው መጽሐፋቸው ጠቅሰዋል። እዚህ ላይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የረጅም ጊዜ ወዳጅ አሌክስ ደዋል በአንድ ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረው ውይይት እሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ባሉት የመጀመሪያ አሥርት ዓመታት፣ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ለውጥ ግራ ተጋብተው እንደነበር እንዳጨወቱት በማንሳት በወቅቱ ኢትዮጵያ ‘ይኼ ነው’ የሚባል ርዕዮተ ዓለም ትከተል እንዳልነበር ያወሳል፡፡

1993 .. . .  ዓለምን ያስደነገጠ በርካታ ወጣቶችን ሕይወት ያስገበረ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ማብቂያ፣ በበርካታ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮች አለመግባባት ውስጥ የከረመው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የውስጥ ፍትጊያውን በአንድ ቡድን የበላይነት ያጠናቀቀበት ዋዜማ፣ በአገሪቱ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም መጀመሪያ፣ ዓለም ከምዕራባውያን የገበያ መር ፋታ የሚነሳው ትወታ ጋብ ያለችበትና አዳዲስ ተዋንያን ወደ መድረኩ ብቅ ያሉበት ጊዜ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከ1993 ዓ.ም. ተሀድሶ በኋላ ያወጣቸው ፖሊሲዎች ከሞላ ጎደል የልማታዊ መንግሥትን አስተሳሰብ መሠረት ያደረጉና ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በፖሊሲ ማዕቀፍ ጭምር በተግባር የልማታዊ መንግሥት (Developmental State) የኢኮኖሚ ሥርዓትን ተግባራዊ አድርጓል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ተመራማሪዎች በዚህ ወቅት መንግሥት የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ለመቀበሉ፣ በርካታ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ፡፡ በተለይም በፓርቲው ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባትዋነኛ ችግሩ የፖለቲካ አመራሩ መበስበስ (Bonapartism) ነው’ በሚል መጠናቀቁና አገሪቱ ለበርካታ ዓመታት ከአምስት በመቶ በላይ ዕድገት አለማስመዝገቧ እንደ ማንቂያ ደውል እንደተጠቀመው ይጠቅሳሉ፡፡ በዓለም አቀፍ የፖለቲካና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴም የቻይና፣ የህንድ፣ የቱርክና ሌሎች ምዕራባዊ ያልሆኑ አገሮች ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና የፋይናንስ አማራጭ ሆኖ መምጣት ለመንግሥት ተጨማሪ ድፍረትን እንደሰጠ የሚከራከሩ በርካቶች ናቸው፡፡

በተለይም በ1993 ዓ.ም. . .  ለውጡ ከተጀመረበት ማግሥት ጀምሮ በገጠር ምርታማነት በከፍተኛ ደረጃ ማደግ በወቅቱ የወጣው የግብርና መርህ ፖሊሲ መሠረት እንደሆነ መጥቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡ በተቃራኒው በከተሞች የተንሰራፋው ሥራ አጥነትየኑሮ ውድነትና የመሠረት ልማት ግንባታ ችግር በ1997 ዓ.ም. አገር አቀፍ ምርጫ ለገዥው ፓርቲ ትልቅ ችግር ሆነው ታይተዋል፡፡ ለዚህም ፓርቲው በሚያሳትማቸው ፖለቲካ ሰነዶች ከ1993 ዓ.ም. ለውጥ በኋላ በከተማ እየመጣ የነበረው ለውጥ ዘገምተኛ እንደነበር አመላክቷል፡፡ በከተሞች ከፍተኛ ሽንፈት የገጠመው ኢሕአዴግ እንደገጠሩ ሁሉ፣ በከተሞችም የልማት ተግባራትን ለማከናወን ቃል በመግባት በተለይም በአዲስ አበባበ 2000 .ም. ከተማዋን ከባለ አደራ አስተዳደር ተረክቦ ሰፋፊ የልማት ፕሮጀክቶችን አከናውኗል፡፡ በዚህም በተወሰነ ሁኔታም ቢሆን በከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራየቤቶች ግንባታና ሰፋፊ የመንገድ ዝርጋታዎችን በማከናወን፣ በከተማም የልማታዊ መንግሥት ትሩፋት የሚላቸውን የልማት ውጤቶች ለሕዝቡ አቅርቧል፡፡ ከ1990 ዓ.ም. መጨረሻ እስከ 2005 ዓ.ም. መጀመሪያአገሪቱ በልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም በመጠቀም በተነፃፃሪ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታም እንዲፈጠር አስችሏል፡፡

2005 .ም. . . . በኢትዮጵያ በተከታታይ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት ብዙዎችን እያነጋገረ እያለ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድንገት ከዚህ ዓለም በሞት መለየት፣ በእሳቸው እግር ሊተካ የሚችል ብቁ አመራር ያለ መኖርና በእሳቸውም ጊዜ ቢሆን፣ በእጅጉ ተስፋፍቶ የነበረው ሌብነትና እርስ በርስ መጠራጠር በርካቶችን አገሪቱ መንታ መንገድ ላይ እንደሆነች እንዲያስቡ ያስገደደ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ በተለይም በየአካባቢው ያለው የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ዕጦት ሥር እየሰደደ የመጣበት ወቅት ቢሆንም፣ በተቃራኒው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በብዙ ኢትዮጵያውያንና ዓለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ ተስፋ እንዲሰነቅ ያደረገ በመሆኑ የምዕራቡን ዓለም ጨምሮ ሌሎች ብዙኃ አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት በአፍሪካ የታዩ የኢኮኖሚ ዕድገቶች ውጤታማ እንደሆኑ የመሰከሩበትና በተለያዩ አጋጣሚዎች የአገሪቱ ዕድገት ተምሳሌቶች በተሞክሮነት የቀረቡበት ጊዜም ነበር፡፡

የሥርዓቱ መሐንዲስ ተደርገው ከሚወሰዱት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ፣ በአገሪቱ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ‘ይህ ነው’ የሚባል ለውጥ ሳይደረግ በነበረበት እንዲቀጥል ተደርጓል፡፡ የአገሪቱን ከፍተኛ የሥልጣን መንበር የያዙት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የቀደመውን ሒደት ለማስቀጠል ያላቸውን ታማኝነት በተደጋጋሚ በመግለጽ፣ የመለስን ሌጋሲ ማስቀጥል ለአገሪቱ የሞት ሽረት ጉዳይ እንደሆነ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የሥልጣን ዘመን የጀመረው የልማታዊ መንግሥት ሥርዓት የአተገባበር ችግር ምንም ማስተካከያ ሳይደረግበት በመቅረቱና በፓርቲው ውስጥ በመሪነት ወንበር የተቀመጡትና የአንጋፋነት ሚና የሚወስዱት ጥቂት ግለሰቦች እርስ በርስ አለመናበብና አለመከባበር ጋር ተዳምሮ ችግሩ እየተባባሰ አንዲመጣ አድርጎታል፡፡ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮም ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞ መልኩን በመቀየርና መጠኑን በማስፋት፣ በበርካታ የአገራችን ክፍሎች በመዛመት በ2010 ዓ.ም. ለመጣው የፖለቲካ ለውጥም አንድ ምክንያት ሆኗል፡፡

የመጨረሻው መጀመሪያ

ኢትዮጵያ ራሷን የእስያ ሞዴል ልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ አራማጅ አድርጋ ከገለጸችበት ከ1993 .ም. በኋላ ባሉት ጥቂት ዓመታት በተለይም በገጠሩ የአገራችን ክፍል ተነፃፃሪ የምርት ዕድገት የተገኘ ሲሆን፣ በከተሞች ግን ዘገምተኛ ለውጥ የታየበት ሁኔታ ነበር፡፡ ከ1997 ዓ.ም. አገር አቀፍ የምርጫ ቀውስ በኋላ በከተሞች ተንሰራፍተው የነበሩትን ሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነትና የመሠረተ ልማት ችግር ለመፍታት የተሠሩ ሥራዎች ለገዥው ፓርቲ የልማታዊ መንግሥት ቅርፁን የሰጡ ሲሆን፣ አገሪቱም ከፍተኛ የተባለለትን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለተከታታይ ዓመታት አስመዝግባለች፡፡ ይሁን እንጂ ከልማታዊ መንግሥታት ባህርይ የሚመነጩ ችግችን አስቀድሞ ለመከላከል ተቋማዊ አሠራሮች በሚያስፈልገው ጥራትና ፍጥነት ባለመዘርጋታቸው ምክንያት፣ ሥርዓቱ ራሱን እንዲያጠፋ በር ከፍቷል፡፡ በኢትዮጵያ የልማታዊ መንግሥት ውድቀት ምክንያቶች በርካታ ነጥቦችን ማስቀመጥ ቢቻልም፣ ለሥርዓቱ መድከም ዋና ዋና የተባሉትን ምክንያቶች ነጥብ በነጥብ መመልከት ተገቢ ይሆናል፡፡

የቢሮክራሲው ብቃት መጓደል

በልማታዊ መንግሥት ኢኮኖሚ ሥርዓት ላይ ሰፊ ጥናት ካደረጉ ምሁራን መካከል ኢቫንስ 1995 ዓ.ም. ባሳተመው ጽሑፍ ‹‹ቢሮክራሲና ማኅበራዊ መዋቅር (Social Structure) መካከል ያለ የጠበቀ ግንኙነት ለልማታዊ መንግሥት ስኬት መሠረት ነው፤›› ይላል፡፡ ልማታዊ መንግሥት በመሠረታዊነት በቢሮክራሲው ልሂቃን የሚመራና ጥብቅ ሙያዊ ብቃትና ሥነ ምግባር የሚሻ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሥርዓት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ልማታዊ መንግሥት ቢሮክራሲ ምንም ዓይነት ማሻሻያ (Reform) ያላደረገና ከሞላ ጎደል የቀደመው ሥርዓት ውጤት ነው፡፡ ከዚህ በላይ ቢሮክራሲው የልማታዊ መንግሥት መሠረት ሆኖ እንዳይወጣ ያደረገው ገዥው ፓርቲ የተከተለው የፖለቲካ ሥርዓት ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚገኘው የሰው ኃይል ከፓርቲው መዋቅር ጋር የተደበላለቀበትና ተቋማት የሰው ኃይላቸውን በሥራ አፈጻጸም ሳይሆን፣ ለፓርቲው ባለታማኝነት እንዲያደራጁ በመደረጋቸው በሒደት የመንግሥት የማስፈጸም አቅም ችግር ውስጥ እንዲገባ አስገድዶታል፡፡ ቻልመርስ ጆሃንሰን እንዳስቀመጠው የልማታዊ መንግሥት ቢሮክራሲ ከፓርቲ ተፅዕኖ ነፃ (Autonomous)፣ የማስፈጸም አቅም ያለው (Capable) መሆን አለበት ሲል ይከራከራል፡፡ የመንግሥት በኢኮኖሚ ውስጥ ጣልቃ ገብነትን የሚፈልገው የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ከፍተኛ የማስፈጸም አቅምና ከብልሹ አሠራርና ሌብነት የፀዳ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚን (Civil Service) ይፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ በተለይም ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ ሀብት መፍጠር ከጀመረችበት 1990ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የፓርቲ መዋቅር በመንግሥት ተቋማት (በትምህርት ተቋማት ሳይቀር) የመዘርጋት ሥራ በስፋት ሲከናወን በመቆየቱ ምክንያት፣ በሒደት ሲቪል ሰርቪሱ ከማይወጣበት የማስፈጸም አቅም ማነስ ችግር ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡

በልማታዊ መንግሥት ሥርዓት ኪራይ ማደል (Rent Allocation) የመንግሥት ዋነኛ ተግባር ነው፡፡ በተለይም የግሉ ዘርፍ በልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ያለውን ሚና ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገው ይህ ተግባር፣ መንግሥት ፍትሐዊና ሕግን የተከተለ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ እንዲያድግ ያስገድዳል፡፡ ብዙዎቹ የልማታዊ መንግሥታት ይህን ተግባር የአገሪቱን ዕድገት ባረጋገጠ መልኩና ውጤታማ እንዲሆን ቢሮክራሲውን ብቃትን መሠረት ያደረገ የሲቪል ሰርቪስ አደረጃጀት (Meritocracy) ዘዴን ይከተላሉ፡፡ ለዚህም ፈጻሚውን አካል ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ማድረግና የሥራ ነፃነትን መስጠት የማስፈጸም አቅም በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ያስችላል፡፡ ሲንጋፖር፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ (በተለይም በጤና ዘርፍ) ያደረጉት ማሻሻያ (Reform) እንደ አብነትይወሰዳል፡፡

ነገር ግን በኢትዮጵያ የሆነው ሁሉ የዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤት በስፋት በተከናወነው የፓርቲ መዋቅርም ልመላና የአንድ አስተሳሰብን የማስፋት ሥራ በብዙ የኃላፊነት ቦታዎች ለሥራው በትምህርትና በልምድ ብቁ የሆኑ ሠራተኞች ሳይሆን የፖለቲካ ካድሬዎች በብዛት የኃላፊነት ቦታዎችን በመያዛቸው፣ ሲቪል ሰርቪሱ ልማትን ማቀላጠፉን ትቶ እንዲያሸልብ አድርጎታል፡፡ ለዓመታት በሌብነትና በከፍተኛ አቅም ማነስ ችግር ውስጥ የገባው ሲቪል ሰርቪስ መጨረሻምፓርቲ ረጃጅም ግምገማዎች የመልካም አስተዳደር፣ የሙስና ችግሮችና የተበላሸ የሥልጣን አተያይ ዋነኛ የሥርዓቱ ችግሮች እንደሆኑ አስቀምጧል፡፡ ስለሆነም የአንድ ፓለቲካ አስተሳሰብ ጥገኛና መሠረታዊ የማስፈጸም አቅም ማነስ መገለጫው የሆነው ሲቪል ሰርቪስ የሥርዓቱ ማክተሚያ ምክንያት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አገር ተወዳዳሪ ሆኖ የመገኘት ትልቅ ሥጋት እንደሆነ ታየ፡፡ ይህም በአገሪቱ እየታዩ ላሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ምንጭ እንዲሁም የሥርዓቱ መጨረሻ መጀመሪያ እንደሆነ ያስገነዝባል፡፡

ልማታዊነትና ኢፍትሐዊነት

ፍሬዴሪክ ሃይክ “The Road to Serfdom” በሚለው መጽሐፉ የትኛውም ርዕዮተ ዓለም የንድፈ ሐሳብ (Theory) እና የተግባር (Action) ውጤት ነው ይላል፡፡ በዚህ ምክንያት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም ውጤታማ ነው የሚባለው ንድፈ ሐሳብና ትግበራው ተጣጥመው ሲተገበሩ ነው፡፡ ያለወቅቱ አልያም ያለመጠኑ በተዛባ መንገድ የሚተገበር የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ልክ ተዛብቶ (ያለመጠኑ) እንደተወሰደ መድኃኒት ነው ብሎ ያምናል፡፡ ውጤቱ በተቃራኒው ጎጂ ነው ብሎ ያስቀምጣል፡፡ ይህን ሐሳብ በአግባቡ መረዳት የኢትዮጵያን የልማታዊ መንግሥት የተዛባ የኢኮኖሚ አተገባበር ላስተዋለ ሰው ሐሳቡ ምን ያህል ልክ እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ኢትዮጵያ በሞዴልነት የወሰደቻቸው የምሥራቅ እስያ አገሮችን የፖሊሲ አተገባበር ስንመለከት ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄና የሕግ ማዕቀፍ በማውጣት እንደተገበሩት ያሳያል፡፡ በአንድ ወቅት አሌክስ ደዋል “The Theory and Practice of Melese Zenawi” በሚል ርዕስ ያሳተመው ጽሑፍ ላይ ጠቅላይ ሚኒስተሩ በኮሪያና ታይዋን የልማታዊ አስተሳሰብ ልዕልናን ያረጋገጡ (Hegemony of Developmental Discourse) እንዴት እንደሚያደንቁ ሲያስቀምጥ፣ በታይዋን እንደ ሙሰኛ የሆነ የጉምሩክ ባለሙያን እንደ አብነት እንደሚያነሱ ይገልጻል፡፡ ባለሙያው ወደ አገር ውስጥ ከሚገባ የፍጆታ ዕቃ 12 በመቶ ዋጋ ያለው ሙስና እንደሚቀበል በተቃራኒው ወደ ውጭ ከሚሄድ (Export) ንግድ ላይ ግን፣ አገሪቱ የምትልከው ምርት ጥራትና ዋጋ ላይ እንደማይደራደር በምሳሌነት እንደሚያነሱ ጽፏል፡፡ ይህ እንግዲህ ልማታዊ መንግሥት በኢኮኖሚ ውስጥ ባለው ድርሻና የአገሪቱ አንጡራ ሀብት ለላቀ ጥቅም ሲል እንደሚያድል (Rent Allocation) በመገደዱ፣ ሀብቱን በፍትሐዊነትና ከአድሎ በፀዳ ሁኔታ መጠቀሙ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በኢትዮጵያ በተለይም ከ2000 .ም. ጀምሮ ከፍተኛ ሀብት መፍጠር መጀመሩን ምክንያት በማድረግ እያደገ የመጣው ሀብትን በፍትሐዊነትና በአግባቡ ያለ መጠቀም (Rent Seeking) ሥርዓቱ ችግር ውስጥ እንዲገባ አስገድዶታል፡፡

በተለይም በልማታዊ መንግሥት የመንግሥት ዋነኛው ተግባር ተደርጎ የሚወሰደው ለብዙኃኑ ጥቅም ሲባል መንግሥት የሚሰጠው የግብር፣ የመሬትና የሌሎች ድጋፎች (Rent Allocation) አንድ በኩል በአስፈጻሚ አካል ብቃት ማነስ በሌላ በኩል፣ የመንግሥት አካላትና በልማታዊነት ስም የሚንቀሳቀሰው ባለ ሀብት የብዙኃኑን ሀብት ለግል ጥቅም በማዋሉ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ኢፍትሐዊነት እንዲከሰት አድርጓል፡፡ የኖቤል የኢኮኖሚ ተሸላሚውና የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ የቅርብ ወዳጅ የነበረው ጆሴፍ ኢ. ስቲግሊትዝ “The Price of Inequality” በሚለው መጽሐፉ የገቢ ኢፍትሐዊነት መጨረሻ የዕጣ ፈንታ ያለ መመጣጠን (Inequality of Opportunity) እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በኢትዮጵያም የመንግሥት የተዛባ የፖሊሲ አፈጻጸም ለብዙኃኑ የአገሪቱ ሕዝቦች ልማቱ ዕድል ሳይሆን እርግማን እንደሆነ እንዲያስቡ አድርጓል፡፡ በዚህ ርዕስ መነሻ እንደተቀመጠው ትክክለኛ የርዕዮተ ዓለም አተገባበር (Implementation) እና የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ልዕልና (Hegemony)፣ በተለይም ልማታዊ መንግሥት ምን ያህል ወሳኝ እንደሆኑ ዓይተናል፡፡ በኢትዮጵያ የሁለቱ ሐሳቦች ብልሽት የልማታዊ መንግሥቱ መጨረሻ መጀመሪያ አንድ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ማሰብ ከባድ አይደለም፡፡

ያልተጣጣሙት ልማትና ዴሞክራሲ

ልማት ወይስ ዴሞክራሲ? የሚሉ ሐሳቦች በበርካታ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ምሁራን ዘንድ ዛሬም አንድ የመከራከሪያ ሐሳብ ነው፡፡ ይህ ክርክር ይበልጥ ትኩረት የሚያገኘው በልማታዊ መንግሥት ጽንሰ ሐሳብ ውስጥ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ የልማትና የዴሞክራሲ አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን፣ የቱ መቅደም አለበት የሚለው ተጨማሪ የመከራከሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ቻልመርስ ጆንሰን ስለልማትና ዴሞክራሲ የሚያነሳውን መከራከሪያ መዋሱ አስፈላጊ ነው፡፡ እሱ እንደሚለው በልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ኢኮኖሚያቸውን የለወጡ አገሮች  በተለይም ደቡብ ኮሪያ፣ ታይዋን፣ ሲንጋፖርና በኋላም ቻይና መጀመርያ አምባገነናዊ የፖለቲካ ሥርዓት እንደተከተሉና ዴሞክራሲያዊ ነበረች የምትባለው ጃፓንም ቢሆን ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የሚኮን አምባገነናዊነት (“Soft Authoritarian” ወይም “Benevolent Dictatorship”) የሚባለውን ዓይነት ሥርዓት እንደነበራት በማስቀመጥ፣ በልማታዊ መንግሥት ውስጥ ልማትና ዴሞክራሲን በተመሳሳይ ጊዜ መተግበር እንደሚያስቸግር  ያነሳል፡፡ ኤዲግሄጂ የተባለው ጸሐፊ ይህን ሐሳብ ሲያጠናክር ‹‹የልማታዊ መንግሥት ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች ቦታ ሊኖራቸው አይችልም፣ ምክንያቱም የመንግሥታቱ አምባገነናዊ ባህሪይ ነው ልማቱን ሊያረጋግጥ የሚችለው፤›› ብሎ ይከራከራል። በዚህም ምክንያት የልማታዊ መንግሥት ቅቡልነት (Legitimacy) የሚመጣው ከሚያስመዘግቡት የኢኮኖሚ ዕድገት እንጂ፣ ከሥርዓቱ ዴሞክሪሲያዊ ባህሪይ ሊሆን እንደማይችል ይገልጻል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ በሌላኛው ወገን የሚገኙ ፖለቲከኞችና ምሁራን፣ ልማትና ዴሞክራሲ ተነጣጥለው ሊታዩ እንደሚገባ ይሞግታሉ፡፡ ሁለቱንም በተነጣጠለ ሁኔታም ሆነ በአንድነት ማስኬድ እንደሚቻል ያስቀምጣሉ፡፡ በተለይም መለስ ዜናዊ ልማታዊ መንግሥት ውስጥ ዴሞክራሲያዊ የመሆን ጉዳይ ከልማቱ ተነጥሎ ሊታይ የሚገባው እንደሆነ፣ ዴሞክራሲያዊ የመሆንና ያለመሆን አማራጭ በመንግሥት ሊወሰን እንደሚችል ያስቀምጣሉ፡፡ እዚህ ላይ ክርክሩን ጋብ አድርገን ኢትዮጵያ በተከተለችው የልማታዊ መንግሥት የዴሞክራሲ አተገባበር ችግሮችን መመልከቱ ተገቢ ይሆናል፡፡

በ1993 ዓ.ም. ገዥው ፓርቲ ለሁለት ከተከፈለ በኋላ አቶ መለስ ዜናዊ አዲስ ባዘጋጁዋቸው ፖሊሲዎች ዙሪያ በሰጡት ሥልጠና ላይ፣ ዴሞክራሲ ለኢትዮጵያ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና መሠረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት ያወጣቸው የመሬትና ሌሎች ፖሊሲዎች ከዴሞክራሲያዊ ሴቶች ጋር ሲጋጩ ታይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ማግሥት የወጡ የፍትሕ፣ የመገናኛ ብዙኃንና የሲቪል ማኅበራት ሕጎችና መመርያዎች አሳሪና ከዴሞክራሲ መርሆች ያፈነገጡ እንደሆኑ ብዙዎች ይሞግታሉ፡፡ አምባገነን ሆነው ልማትን የጀመሩት የምሥራቅ እስያ አገሮች በተነፃፃሪ ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ የብሔርናና የቋንቋ ብዙኃነት የሌለባቸው መሆኑ በተጨማሪም፣ አገሮቹ የነበሩበት አካባቢያዊ ሁኔታ አስቸጋሪ የነበረ መሆኑ አምባገነናዊነት በሕዝቡ ይኼ ነው የሚባል ተቃውሞ እንዳይገጥመው እንዳደረገው ይነሳል፡፡ ደቡብ ኮሪያ ሰሜን ኮሪያን ለጦርነት ያፋጠጠች አገር አድርጋ ስለምትቆጥር፣ ታይዋን ቻይናን ልትውጣት የተዘጋጀች ጠላት አድርጋ ስለምታስብ፣ ጃፓን ከቻይና ጋር ያላትን ታሪካዊ ግጭት ስለምታስብ፣ ቻይና አሜሪካ በታይዋን በኩል ልታጠቃኝ ትችላለች የሚለው አስተሳሰባቸው መንግሥታቱ እነዚህን እንደ ምክንያት በመጠቀም አምባገነናዊነትን በሕዝቡ ላይ ሲጭኑ ጠንካራ ተቃውሞ እንዳይገጥማቸው ሆኗል። ነገር ግን በኢትዮጵያ ከዚህ ፍፁም የተለየ ነባራዊ ሁኔታ መኖሩና ከወረቀት የዘለለ የዴሞክራሲ መርሆች አለመተግበር፣ አገሪቱን ወደ ከፋ ችግር ልማታዊ መንግሥቱንም ወደ ፈተና እንደከተተው ታይቷል፡፡

በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የታየው ሥር የሰደደ የሰብዓዊ መብት ገፈፋ የፍትሕ ተቋማት ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ያለመሆን ሚዲያው በአንድ ወገን ቁጥጥር ሥር መውደቁና የሚደረጉ ምርጫዎች ተዓማኒነት ማጣት ብዙኃኑን ሕዝብ ወደ ተስፋ መቁረጥ ገፉት። በተለይም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ ለአንድ ወገን ያደላ ነው የሚሉ ልሂቃንና ተሟጋቾች እየተበራከቱ መሄድ፣ በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ቅሬታ ውስጥ ከተተ። በብሔርና በቋንቋ ላይ መሠረቱን ባደረገው የፌዴራል ሥርዓት የተነሳ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የአካባቢያዊ መስተዳድሮች የተቀየሱላቸው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በብሔራችንና በቋንቋችን የተነሳ ተገልለናል (Marginalize) የሚሉ ቡድኖች በየአካባቢው እንዲነሱ ምክንያት በመሆን፣ የልማታዊ መንግሥት መሠረት (Pillar) የሆነው አገራዊ መግባባት በመናድ ችግር ውስጥ እንዲገባ አደረገው፡፡

ሽሽት ወይስ ማፈግፈግ?

የልማታዊ ርዕዮተ ዓለም ታሪክ በምሥራቅ እስያ ነብሮች (Asian Tigers) የኢኮኖሚ ዕድገት አንዱ ገጽታው ሲሆን፣ በዚሁ ፍልስፍና ካለሙበት ያልደረሱ የደቡብ አሜሪካና የአፍሪካ አገሮች ውድቀት ሌላኛው ገጽታው እንደሆነ የፖለቲካ መዛግብት ያወሳሉ፡፡ የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ስኬታማ ያልሆነባቸው አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየው ከፍተኛ የሆነ የአመራር ጉድለት፣ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳያከናውን በማድረግ ሥርዓቱን ለውድቀት አገሪቱን ለከፍተኛ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ እንደሚዳርግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ በስኬትና በውድቀት መንታ መንገድ ላይ ትገኛለች፡፡ ከላይ በዝርዝር እንዳየነው በኢትዮጵያ የልማታዊ መንግሥት ጉዞ መደነቃቀፍ የጀመረው ቀደም ባሉት ዓመታት መንግሥት አዛብቶ በተገበራቸው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እንደሆነ መረዳት አያስቸግርም፡፡

የዘርፉ ምሁራን እንደሚያስቀምጡት የልማታዊ መንግሥት አራት ቅድመ ሁኔታዎችን በአንድ ላይ መተግበር ካልቻለ፣ ማለትም መንግሥት ለልማት ያለው ቁርጠኝነት፣ ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ቢሮክራሲ፣ ከሙስና የፀዳ የመንግሥት መዋቅርና ከባለ ሀብት ተፅዕኖ ተነፃፃሪ ነፃነት ያለው መዋቅር መዘርጋት እንዳለበት በመግለጽ፣ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ሲጎድል መንግሥቱ ልማታዊ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ ይገባል ይላሉ፡፡ በእነዚህና ከላይ በዚህ ጽሑፍ ላይ በዝርዘር በተነሱ ምክንያቶች በኢትዮጵያ ልማታዊ መንግሥቱ ችግር ውስጥ እንደገባ መከራከር ይቻላል፡፡ በቅርቡም በኢትዮጵያ የመጣው የፖለቲካ ለውጥ የልማታዊ መንግሥቱ ዕጣ ፈንታ “በሽሽትና በማፈግፈግ” መሀል እንዲገኝ አድርጎታል፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና አባል ድርጀቶቹ በሚሰጧቸው መግለጫዎችና በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች የልማታዊ መንግሥቱን ዕጣ ፈንታ ለጥያቄ እንዳቀረቡት ተመልክተናል፡፡ መንግሥት በአገሪቱ ለሚተገበሩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ፖሊሲዎች ምክንያታያዊና አዋጭ ከሆነ የፖሊሲ አማራጭ በማውጣት በፍጥነት መተግበሩ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው፡፡ በቀጣይ የአገሪቱ ዕድል ፈንታ የሚወሰነው መንግሥት በሚከተለው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ርዕዮተ ዓለም መሆኑ ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም፡፡ የትኛውም የፖለቲካ ይሁን የኢኮኖሚ አስተሳሰብ የሰው ልጅ የአስተሳሰብ ውጤት እንጂ፣ የማይቀየር ወይም የማይሻሻል ባለመሆኑ አገሮች ለአተገባበሩ በሚከፍሉት ዋጋ ነው ውጤቱን የሚያዩት፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም ከጀመረችው ተስፋ ሰጪ የኢኮኖሚ ዕድገት የተገኙ ውጤቶችን በመለየትና በፖለቲካና በማኅበራዊ ዘርፎች የታዩ ጉድለቶችን በማረም ካሰብንበት ለመድረስ ልማታዊ መንግሥቱ ‹‹ሸሸ ወይስ አፈገፈገ››? ለሚለው ጥያቄ ተገቢ ምላሽ በመስጠት ለቀጣይ ጉዞ ራስን ማዘጋጀቱ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...