Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቅዳሜና እሑድ የተቀናነሱበት ወጣትነት!

ጆሮ የሚሰነጥቅ ሙዚቃ ተከፍቷል፡፡ ሾፌሩም ከሙዚቃው ድምፅ እኩል ጮክ ብሎ እያቀነቀነ ነው፡፡ ‹‹ሀፒ በርዝ ዴይ ቱ ዩ፣ ሀፒ በርዝ ዴይ ቱ . . .›› እያለ ሲጮህ የተወሰኑ ተሳፋሪዎችን ሥጋት ውስጥ ጨመረ፡፡ በተለይ በሞባይል ስልክ ለመነጋገር የፈለገች ወጣት፣ ‹‹ኧረ እባክህ ቀንሰው፤›› ብትልም ሰሚ አላገኘችም፡፡ እንደ ተሳፋሪው ሁሉ ግራ የተጋባው ወያላ፣ ‹‹ምን እየሆንክ ነው?›› አለው፡፡ ሾፌሩ በከፍተኛ ድምፅ ጮክ ብሎ፣ ‹‹ዛሬ’ኮ ልደቴ ነው!›› አለ፡፡ ወያላውም እንደ ምንም የሙዚቃውን ድምፅ አስቀንሶት ስለልደቱ መነጋገር ጀመሩ፡፡ ጥያቄም አቀረበለት፤ ‹‹ለመሆኑ ስንተኛ ዓመትህን ነው የምታከብረው?›› አለው፡፡ ሾፌሩ ዕድሜውን መናገር አልፈለገም፡፡ ወያላው ግን ወጥሮ ስለያዘው ዝም ማለት አልቻለም፡፡ ፀጉሩ ላይ ሽበት ጣል ጣል አድርጐበታል፡፡ ከዚያም በላይ ፊቱ ላይ የተጣጠፉት ቆዳዎች ረጃጅም መስመር ሠርተው፣ ረጅም የሕይወት መንገድ መጓዙን ያሳብቁበታል፡፡ ‹‹37 ዓመቴ ነው!›› ሲል ወያላው መሳቅ ጀመረ፡፡ ምክንያቱ ከሁላችንም የተሰወረ አልነበረም፡፡ ዕድሜያችንን ስንጠየቅ ቁጥሩን መጥራት ይከብደናል አይደል?

ሾፌሩ ግን በወያላው ሳቅ እንደ መናደድ እያለ፣ ‹‹ምን ያስቅሀል?›› አለው፡፡ ወያላውም፣ ‹‹አባባልህ እኮ ነው የሚያስቀኝ፣ ዕድሜዬ 37 ነው አልከኝ!›› አለ አሁንም እየተገረመ፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹እና ታዲያ ስንት ነበር የገመትከው?›› ሲለው፣ ወያላው መልሶ፣ ‹‹ለመሆኑ 37 ዓመት የሆነህ የታክሲ ሾፌርነት ከጀመርክ ነው? ወይስ አዲስ አበባ ከመጣህ?›› ሲለው፣ ሾፌሩ በጣም ተናደደ፡፡ ‹‹በቃህ ዝም በለኝ፣ በልደቴ ቀን አትነጅሰኝ፤›› ብሎ ድጋሚ ‘ሀፒ በርዝ ዴይ ቱ ዩ. . .›› እያለ መጮሁን ቀጠለ፡፡ አሽሙረኛው ወያላ በነገር ወጋ ስላደረገው ያንን ለማካካስ ሳይሆን አይቀርም ድምፁ በጣም ጨምሯል፡፡ የዕድሜ ነገር ሲነሳ የሳቀው ሁሉ ያኮርፋል፡፡ ሁሉም ፈጣሪ የሰጠውን ዕድሜ ጨምርልኝ ብሎ ከመለመን ይልቅ፣ በሩብ ወይም በግማሽ ቀንሶ ከእኩያው በታች መዋል ይፈልጋል፡፡ ዕድሜና መልክ አልናበብ እያሉ ግን ችግር ይፈጥራሉ፡፡

ወያላው ሒሳብ መሰብሰብ ሲጀምር፣ ‹‹ሰው ግን ለምንድነው ዕድሜውን የሚደብቀው?›› በማለት ለተሳፋሪው በሙሉ ማለት ይቻላል ጥያቄ አቀረበ፡፡ ይህን ጥያቄ ልሞክረው አልሞክረው እያልኩኝ ሳሰላስል አንድ አዛውንት ቀድመውኝ መናገር ጀመሩ፡፡ ጆሮ ተሰጣቸው፡፡ ‹‹ምን የሚያስደብቅ ነገር አለ? ዕድሜ እንደሆን ፀጋ ነው፡፡ እንዲያውም የኖርንባቸውን ዘመናት እያሰብን ፈጣሪን ለማመስገኛ ምክንያት ይሆነናል፤›› ብለው ረዘም ያለ ማብራሪያ ሰጡ፡፡ ወያላውም፣ ‹‹ለመሆኑ አባት የእርስዎስ ዕድሜ ስንት ነው?›› ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ ምንም ዓይነት መልስ መስጠት አልፈለጉም፡፡ ፀጥ፣ እረጭ፣ ጭጭ ብለው በታክሲው መስኮት አሻግረው በመስኮት አሻግረው ማየት ጀመሩ፡፡ ወያላው ሊተነኩሳቸው የፈለገ ይመስላል፡፡ ‹‹ሃምሳ ይሞላዎታል?›› ሲላቸው አዛውንቱም፣ ‹‹በሚቀጥለው ዓመት ሃምሳኛ ዓመቴን እደፍናለሁ፤›› አሉ፡፡ ወያላው የለበጣ ሳቀ፡፡ ሌሎች ተሳፋሪዎች ግን የራሳቸውን ዕድሜ ማስላት የጀመሩ ይመስል በሐሳብ ተውጠው ዝም ብለዋል፡፡

ወያላው አሁንም አግራሞት በተቀላቀለበት ስሜት፣ ‹‹በተለይ ሴቶች! በተለይ ሴቶች! ዕድሜያቸውን ከሚጠይቋቸው ሌላ ነገር ቢጠይቋቸው ይቀላቸዋል፤›› ሲል፣ አንዲት በንግግሩ ብግን ያለች የምትመስል ወጣት፤ ‹‹ምን ለማለት ፈልገህ ነው አንተ?›› አለችው በሻከረ ድምፅ፡፡ ወያላውም በቀጥታ፣ ‹‹አአይ እናቱ ዕድሜሽ ስንት ነው ለማለት ፈልጌ ነው?›› ሲላት ለመልስ አፍታ አልፈጀባትም፣ ‹‹ማን የሰየመህ ዕድሜ ተቆጣጣሪ ነህ?›› አለችው፡፡ ‹‹ለመሆኑ ከሒሳብ ተቀባይነት ውጪ ማን ነው የእኛን ዕድሜ መርማሪነት የሾመህ? የሚጫነውንና የሚወርደውን ሰው አስተናብር እንጂ ምን ቆርጦህ ነው የእኔን ዕድሜ የምትጠይቀው?›› በማለት ተንጣጣችበት፡፡ ወያላው መልሶ፣ ‹‹አላልኳችሁም ሴቶች ዕድሜያቸውን የሚጠይቃቸው ወንድ ጠላታቸው ነው፡፡ ይኼው ዕድሜሽ ስንት ነው ስላት እንደ ኔቶ የጦር አውሮፕላኖች በቦምብ ልትደበድበኝ ነው፤›› እያለ በልጅቷ ላይ ትንሽ አላገጠባት፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹ሰው ዕድሜውን እየቀነሰ ባንክ ማስቀመጥ ሳይጀምር አይቀርም፤›› አለ፡፡ ‹‹አንተ ምናምንቴ ያንተን የት ደብቀህ በሰው ዕድሜ የምትፈላሰፈው፣ ንገሩኝ ባይ… ›› ስትለው ፀጥታ ነገሠ፡፡

‹‹አብዛኛው ሰው ሁሌም ወጣት መስሎ ለመታየት ካለው ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ዕድሜውን ይቀሽባል፡፡ በተቻለው መጠን ዝቅ አድርጐ መናገር ያስደስተዋል፡፡ ‹‹እሱኮ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነው፤›› ሲባሉ ደስ የሚላቸው ጎልማሶችና አረጋውያን አሉ፡፡ አርሰን ቬንገር ተጫዋቾች ሲመለምሉ ከተጨዋቹ ብቃትና ተክለ ሰውነት በላይ ዕድሜ በጣም ይማርካቸዋል ይባል እንደነበር ድፍን የእኛ ሰው ስለመስማቱ ጥርጣሬ ያለ አይመስልም፡፡ ታዲያ እሳቸው ይመጣሉ የተባለ ይመስል አዳሜ ዕድሜውን የመደበቁ ሚስጥር ምንድነው? ይኼ ዕድሜ የዓባይን ልማት ለማሳካት ሲባል ለቦንድ ግዢ ቢውል ኖሮ ስንቶቻችን በአራትና በአምስት እጥፍ እናባዛው ነበር?›› የሚለው አጠገቤ የተቀመጠ ቆምጫጫ ጎልማሳ ነው፡፡ ‹‹አንተስ ስንት ይሆንሃል?›› ስለው እየተቅለሰለሰ፣ ‹‹ሰላሳ የምሞላው በሚቀጥለው ዓመት ነው…›› ሲለኝ ከመሳቀቄ የተነሳ አንገቴን ደፍቼ ቀረሁ፡፡ እናንተ 15 ዓመታትን ቅርጥፍ አድርጎ ካደኝ፡፡

‹‹በውጪው ዓለም ብዙ ጊዜ ወጣቶች ዕድሜያቸውን ጨምረው መናገር ይቀናቸዋል፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ መዝናኛዎች ውስጥ ተገብቶ ለመዝናናት የሚያስፈልገው ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ዕድሜም ጭምር ነው፡፡ ስለዚህ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ልጆች በእነዚያ መዝናኛ ሥፍራዎች ውስጥ ገብተው ለመዝናናት ዕድሜያቸውን ጨምረው መናገር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከኑሮዋቸው ሁኔታ አንፃር ሰውነታቸው በጣም ስለሚገዝፍና ትልልቆች ስለሚመስሉ ፊታቸውን ወይም ሰውነታቸውን ዓይቶ ዕድሜያቸውን መገመት ያዳግታል፡፡ አንዳንዴ የ14 ዓመት ልጅ የሰላሳ ዓመት ሰው መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ እዚህ በተገላቢጦሽ በሃምሳ ዓመታቸው የ20 ዓመት ወጣት ካልመሰልን እያሉ መከራቸውን የሚያዩ በዝተዋል፡፡ ፀጉር ሲሸብት በቀለም ይጠፋል፣ ፊት ሲጨማደድ እንዴት ይደረጋል?›› የሚሉ አሿፊዎች በበዙበት አገር ትዝብቱ በርክቷል . . .›› እያለ አንዱ ከኋላ በኩል ሲናገር የዕድሜ ዩኒቨርሲቲ መምህር መሰለኝ፡፡

‹‹እናትና ልጅ ናቸው አሉ ትንሽ የጤና እክል አጋጠሟቸው ሆስፒታል ሄደው ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ የመጀመሪያው ምርመራ እየተደረገላቸው ሳለ የወጣቷ ዕድሜ ሲጠየቅ፣ 27 ብላ ከዕድሜዋ ላይ ሳትጨምር ሳትቀንስ ለመርማሪዋ ነርስ የእውነት ቃሏን ትሰጣለች፡፡ የዕድሜዋን ቁጥር በትክክል የተናገረች የመጀመሪያዋ ሳትሆን አትቀርም ተብሎላታል አሉ፡፡ እናትም ተራቸው ደርሶ እየተመረመሩ ዕድሜያቸውን ሲጠየቁ ትንሽ ካሰላሰሉ በኋላ ‹‹37›› ብለው ሲመልሱ፣ ነርሷ በድንጋጤ ወደቀች፣ ከዚያም ወደ ድንገተኛ ክፍል ተላከች መባሉም ተሰምቷል፡፡ 

‹‹በእናቷ ሁኔታ የተገረመችው ወጣት፣ ‹እማዬ እኔ ደረስኩብሽ ማለት ነው፡፡ ትክክለኛውን ዕድሜ ለምን አትናገሪም? ይኼው ነርሷ በአንቺ ዕድሜ ደንግጣ ፌንት አደረገች› አለቻቸው፡፡ ቀጥላም የትልቁ ወንድሟን ስም ትጠራና ‹እሱ እንኳን 40 ዓመት ሞልቶታል› ስትላቸው እናትየው በጣም ተገርመው፣ ‹ሞላው እንዴ?› በማለት ትንሽ ካሰላሰሉ በኋላ ‹‹ለነገሩ . . .› ብለው ወሬያቸውን ቀጠሉ፡፡ ‹ለነገሩ ጃንሆይ ከሥልጣናቸው ሲወርዱ ዕድሜዬ 37 ነበር› ብለው አረፉት፡፡ ልጃቸው ይበልጥ እየገረማት፣ ‹ታዲያ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አልጨመረም ማለት ነው?› በማለት ስትጠይቃቸው ፈገግ እንደ ማለት ብለው፣ ‹አዬ ልጄ በዚህ ዘመን ምን ያልጨመረ ነገር አለ ብለሽ ነው? ጨምሯል፣ ኧረ በጣም ጨምሯል በቃ 57 በያቸው› ይላሉ፡፡ ወጣቷ ‹ኧረ ማዘር አታሹፊ ተጨማሪ እሴት ታክስ እኮ የለውም› ብትላቸው፣ ‹በቃ 60 በያቸው› ሲሏት፣ የእናቷ ሁኔታ በጣም እያሳቃት 37 የነበረውን ገልብጣ 73 አደረገችው ይባላል . . .›› የሚለው ደግሞ ከመጨረሻው መቀመጫ የተሰየመ ወጣት ነው፡፡ 

‹‹ምናልባት በአግባቡ በሥራና በቁምነገር ያሳለፉትን ዕድሜ ብቻ አስበው ይሆናል የተናገሩት፡፡ ብዙ ጊዜ እዚህ አገር መቃብር ላይ የሞቱ ሰዎች ዕድሜ ሲጻፍ ከተወለዱበት ቀን ጀምሮ እስከ ሞቱበት ድረስ ያለው ነው የሚታሰበው፡፡ ፈረንጆቹ ዘንድ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ ይልቁንም አንድ ሰው በሥራ አገሩን ያገለገለበት ወይም ቁምነገር የሠራበት ወቅት ብቻ ተቆጥሮ መቃብሩ ላይ ይጻፍለታል፡፡ ስለዚህ ወደ ፈረንጅ መቃብር ጐራ ብለው የዕድሜያቸውን ሁኔታ የማየት ዕድል ያጋጠማቸው የአገራችን ሰዎች ሃያ፣ ሰላሳ፣ አርባ የሚሉ በርከት ያሉ መቃብሮችን ሲመለከቱ ‘እኔን፣ እኔን በወጣትነታቸው ተቀጩ’ ማለታቸው አይቀርም፡፡ ነገሩ ግን ሌላ ነው፡፡

‹‹አንዳንዴ የማቱሳላን ዕድሜ ያህል ኖረው (ለሺሕ በጣም ጥቂት የጐደለው) ምንም ነገር ሳይሠሩና ሳይፈጥሩ መሞት አለ፡፡ ማቱሳላም 958 ዓመት ነበር በምድር የኖረው፡፡ ኖረና ሞተ የሚለው ሕይወት በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ከኖርን አይቀር፣ ዕድሜ ከተቆጠረብን አይቀር፣ ምድር ላይ የዘመኑ ሰዎች ተብለን ከተመላለስን አይቀር ለሕዝባችንና ለምድራችን አንድ ጠብታ ማበርከት ይጠበቅብናል፡፡ ብዙ ዘመን አንኖርም፣ ብዙ ዘመን መኖር በራሱ ቁምነገር አይሆንም፡፡ ነገር ግን እንደ ጤዛ ታይቶ በሚጠፋው በዚህ ጥቂት ዘመን መካከል ስንኖር አንድ ነገር ለመሥራት እንነሳ፡፡ ቆይ ቆይ ዕድሜያችንን የምንደብቀው ከታክስ ለመሸሽ ነው? ወይስ ዕድሜ ሲጨምር ወጣትነት ይናፍቃል?›› የሚሉት በፀጥታ ተውጠው የነበሩ አንዲት የተማሩ የሚመስሉ እናት ናቸው፡፡

ወያላው ሾፌሩን እንደገና ይጎነትል ጀመር፡፡ ‹‹መልክህና ዕድሜህ አይቀራረቡም፤›› አለው፡፡ ሾፌር ክፍት ብሎት፣ ‹‹ከጧት እስከ ምሽት ቁርና ፀሐይ እየተፈራረቁብኝ እንዴት እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ትጠይቀኛለህ?›› አለ፡፡ ነገረኛው ወያላ ፈገግ እያለ፣ ‹‹እውነትህን ነው ሺሻና በርጫው ሲጨመርበት ደግሞ ዕድሜን አለማሰቡ ይሻላል፤›› ሲለው አንድ ጎልማሳ ‹‹ወደው አይስቁም፤›› ሲል ተሰማ፡፡ ወያላው ለራሱ፣ ‹‹ዘንድሮ ታክስ መሥሪያ ቤት የተደበቀና የተጭበረበረ ገንዘብ ያሳድዳል፣ በየሥርቻው የተከማቸውን ዕድሜ ማሳደድ የጀመረ እንደሆነ እኔ የለሁበትም፤›› ሲል ያቺ ወያላውን የተረበች ወጣት፣ ‹‹የአንተም ወጣትነት ስንትና ስንት ቅዳሜና እሑዶች የተቀናነሱበት እንደሆነ እኮ ግንባርህ ይናገራል . . .› ስትለው፣ ጉዞአችን አልቆ ‹‹መጨረሻ›› ተብለን ወርደን ወደ ጉዳያችን ተበታተንን፡፡ አንዳንዴ ያንን የመነቸከ ፖለቲካ ትተን ማኅበራዊ ጉዳዮቻችን ላይ ማተኮር ለጤና ጥሩ ነው፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት