Saturday, September 30, 2023

በመንግሥት ተቋማት የሚስተዋለው የሀብት አጠቃቀምና ብክነት እያስነሳ ያለው ጥያቄ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአገር አስተዳደር ወይም በፖለቲካዊ አስተዳደር የሕግ ተገዥነትና የሕግ አስከባሪነት ሚና ቁልፍ ሚና እንዳለው ይታወቃል፡፡ በተለይ በሠለጠነው ዓለም የሕግ ተገዥነት ለአገር ኢኮኖሚ፣ ሥልጣኔ፣ ደኅንነትና እኩልነት ያለው አስተዋጽኦ ትልቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ላለው ግንኙነት ሕግ እንደ ዋነኛ ውል ወይም ኮንትራት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

ሕገ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ እንደ ገዥ ማሰሪያ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ሕዝብ ለማንኛውም ሕግ ተገዥ ይሆናል፣ መንግሥትም ሕግን በማስከበር የሕዝቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደኅንነት ያረጋግጣል፡፡ ይህ ሲባል መንግሥትም ለሕግ ተገዥነት ራሱን ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡

ሌላው አገላለጽ ሕግ በሁለቱም ላይ የገዥነት ሚና ይኖረዋል፡፡ ሕዝብ ለሕግ እንደሚገዛ ሁሉ መንግሥትም ለሚወስደው ኃላፊነት ሁሉ በሕግ ይገዛል፡፡ ይህ ሲሆን ነው በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን የሚፈጠረው፡፡ ሕግ በሚባለው ሥርዓት መንግሥትና ሕዝብ በርካታ ውሎችን ይገባሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ለአብነትም ያህል የሀብት አጠቃቀም ውል ይገኝበታል፡፡

በዚህም ሥርዓት መንግሥት ከሕዝብ ሀብት ያሰባስባል፡፡ ሕዝብ መንግሥት ለሚያደርግለት የደኅንነት ጥበቃ፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦትና የተለያዩ አገልግሎቶች  የሰበሰበውን ግብር ሌሎች የገቢ ዓይነቶች በሕግና ሥርዓት ለተገቢው ዓላማ በማዋል፣ ለሕዝብና አገር ጠቃሚ ለሆነ ነገሮች የማዋል ኃላፊነት አለበት፡፡ ይኼንንም ኃላፊነት ለመወጣት በተጣለበት የሕግ ድንጋጌ ተገዥ በመሆን ለሕዝብ ዓመኔታ መብቃት ይጠበቅበታል፡፡

የመንግሥት ታማኝነት ልኬት

መንግሥት ለሕዝብ የሚያሳየው ኃላፊነትና ታማኝነት ከሚልኩባቸው መንገዶች አንዱና ዋናው የሀብት አጠቃቀሙ ነው፡፡ ይህ የሀብት አጠቃቀሙም ሊመሠገን ወይም ሊወገዝ የሚችለው ኦዲት ከተደረገ በኋላ በሚገኘው ውጤት ወይም ግኝት ነው፡፡ የሒሳብ ሥራ ማወራረዱ (ኦዲት) ደግሞ በመንግሥትና በሕዝብ (ግብር ከፋዩ) መካከል የተገባው ውል በሥርዓት መተግበሩንና አለመተግበሩን የሚያሳይ መስታወት ነው፡፡ ይህ የመንግሥትና የሕዝብ ውል በበርካታ አገሮች እንደሚደረገው ሁሉ በኢትዮጵያ ሲተገበር ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ግብርና ሌሎች ገቢዎችን መሰብሰብ ጠንከር እያለ ሲሆን፣ መንግሥትም ሕግ የማስከበሩን (ግብር የመሰብሰብ ተግባሩን) እያጠናከረ መጥቷል፡፡ እንዲሁም በተመሳሳይ በግብር ሰብሳቢውና በተጠቃሚው መንግሥት ላይ የሚደረገው ቁጥጥር እየጠነከረ መሄዱን፣ በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሚካሄደውን የኦዲት ክዋኔ መመልከት ይቻላል፡፡

ከስህተት ነቃሽነት ባለፈ

የኦዲት ሥራ መንግሥት የሚሰበሰበው ሀብት በአግባቡ ለሕዝብና ለመንግሥት አገልግሎት መዋሉንና አለመዋሉን በመለካት በሕዝብ የሚመዘንበት መንገድ ሲሆን፣ በሌላ በኩል መንግሥት ራሱ ባሉት ሦስት አካላት የሥልጣን ክፍፍልና ቁጥጥር የሚያደርግበት (Check and Balance) መሣሪያ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተለይ ሕግ አውጪ የሚባለው አካል ሕግ አስፈጻሚውን ከሚቆጣጠርባቸው ዋና ዋና መንገዶች አንዱ የኦዲት ሥራ ወይም ቁጥጥር ነው፡፡

በዚህም ነው በሕገ መንግሥቱ መሠረት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ተጠሪነቱ ለሕግ አውጪው አካል ሆኖ እንዲቋቋም የተደረገው፡፡ ዋና ኦዲተርም በባለ በጀት የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ላይ ኦዲት በማከናወን ለሕግ አውጪው ሪፖርት ያደርጋል፡፡ ሕግ አውጪውም በሚቀርብለት ሪፖርት መሠረት ሥራ አስፈጻሚውን ይቆጣጠራል፡፡ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ይህን ሥርዓት ሲተገብር ቆይቷል፡፡

በየዓመቱ በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሚደረገው የኦዲት ሥራ እየተጠናከረና እየሰፋ መጥቷል፡፡ በተከታታይ ዓመታትም ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት በርካታና አጀብ የሚያሰኙ ሪፖርቶችን በማውጣት፣ የመንግሥትን ሰፊ ቀዳዳና እንከኖች ይዞ ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡

ይሁን እንጂ በርካታ ታዛቢዎች የዋና ኦዲተርን ሥራ በጠንካራ ጎኑ እያዩት ቢሆንም፣ ከኦዲት ግኝቶች በኋላ በሚወሰድ የአሠራርና ሕግ የማስከበር ጎዳና ላይ ግን ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ይህ የታዛቢዎቹ ጥያቄ ደግሞ አሁን አሁን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ጭምር ጎልቶ እየተሰማ ይገኛል፡፡ ካለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ጀምሮ በፓርላማው የሚቀርቡ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርቶችን በተመለከተ፣ የፓርላማው አባላት በመንግሥት ተቋማት የሚታየው ሥርዓት ያጣ የሀብት አጠቃቀምና ብክነት በመተቸት እየጠየቁ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ ዱቢሶ በተከታታይ ለዘጠነኛ ጊዜ ዓመታዊ ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ጊዜ፣ የፓርላማ አባላት በምሬትና በቁጣ ጭምር የመንግሥትን የበጀት አጠቃቀምና የሥራ ክንዋኔ አብጠልጥለዋል፡፡ ዋና ኦዲተሩ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የበጀት አጠቃቀምና በርካታ ስህተቶችን መንቀሱ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ፣ ዕርምጃ ካልተወሰደ ስህተት መንቀሱ ብቻ የት ያደርሳል ብለው ሞግተዋል፡፡

ባለፉት 28 ዓመታት የተለያዩ የዋና ኦዲተር ኃላፊዎች የተሾሙለት ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት፣ በየዓመቱ ከመንግሥት የበጀት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ብዙ እንከኖችንና ጥፋቶች አጋልጧል፡፡

ከማንም በላይ ግን በአቶ ገመቹ ዱቢሶ የሚመራው ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ብዙ ጉዶችን አጋልጧል፡፡ በእያንዳንዱ ዓመት በርካታ ቢሊዮን ብሮች ያላግባብ ውጪ ተደርገዋል፣ በርካታ ቢሊዮን ብሮች የሚያወጡ ግዥዎች ሕግን ሳይከተሉ ተፈጽመዋል፣ በበርካታ ቢሊዮን ብሮች የሚገመት የሕዝብ ሀብት ባክኗል በማለት ጥራት ያለው የኦዲት ግኝት ይፋ እያደረገ ነው፡፡

የአገሪቱን ኢኮኖሚ ያግዛሉ የተባሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችና የመሠረተ ልማት አውታሮች መጠናቀቅ ከሚገባቸው ጊዜ ለዓመታት በመዘግየታቸው ተጨማሪ በጀት በመውሰዳቸው የአገሪቱን ካዝና ማሟጠጣቸው፣ ይባስ ብለው በከፍተኛ የውጭ ብድር እተገነቡ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ከመጓተታቸው ባለፈም በጅምር ሲቋረጡ መታየታቸው፣ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች ከመጓተታቸው በላይ ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ የብድር መክፈያና የዕፎይታ ጊዜያቸው ሲጠናቀቅ መስተዋሉ ብዙ የተባለበት ነው፡፡

እነዚህ ሰፊና ሥር የሰደዱ ችግሮችን ዋና ኦዲተሩ በተከታታይ ሲያጋልጡና የመፍትሔ ያለህ ሲሉም ቆይተዋል፡፡ እነዚህን ችግሮች ደግሞ የፓርላማ አባላት የግንቦት ወር በመጣ ቁጥር ሪፖርት ሲቀርብላቸው ሪፖርቱን ሲያስተጋቡና መንግሥት ዕርምጃ እንዲወስድ በግል ሲያሳስቡ፣ እንዲሁም በፓርላማው የውሳኔ ሐሳቦችን ሲያሳልፉ ቆይተዋል፡፡

ነገር ግን መንግሥት በተደጋጋሚ የእርምትና የተጠያቂነት ዕርምጃ ለመውሰድ ሲምልና ሲገዘት ከመስማት ውጪ፣ ይህ ነው የሚባል ዕርምጃ ሲወስድ እምብዛም አይታይም፡፡ ምናልባት አልፎ አልፎ ከሙስና ጋር በማያያዝ በመካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሹማምንት ከማሰር ያለፈ፣ ይህ ነው የሚባልለት ዕርምጃ ወስዶ ለሕዝብ ተጠያቂነትን ሲያረጋገጥ  ዓይታይም፡፡

በአንፃሩ በተደጋሚ የሕዝብ ሀብት ብክነትና ምዝበራ ጉዳይ ሪፖርት ቀርቦ፣ በሚዲያውም በኩል የዜና ግብዓትነቱ ወይም ቁም ነገርነቱ ወርዶ እንደ መደበኛ ክስተት እስከ መታየት መድረሱ ይስተዋላል፡፡

ሐሙስ ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በቀረበው የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት በ174 የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2010 በጀት ዓመት የፋይናንስ አጠቃቀምና ሕጋዊነትን አስመልክቶ፣ የኦዲት ግኝታቸው ተጠቃሎ ቀርቧል፡፡ በኦዲት ግኝቱም መሠረት በርካታ የሒሳብ አያያዝ ግድፈቶች፣ የውስጥ ቁጥጥር ድክመቶችና ሕገወጥ አሠራሮች በቀረበው ሪፖርት የተገለጹ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የጥሬ ገንዘብ ሒሳብ ኦዲት ሲደረግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በሰመራና በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲዎች በድምሩ ከ960 ሺሕ ብር በላይ ጉድለት መገኘቱን ምክር ቤቱ መገንዘብ ችሏል፡፡

በተመሳሳይም ውዝፍ ተሰብሳቢ ሒሳብን አስመልክቶ በተደረገው ማጣራት ሥራ ከትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በ129 መሥሪያ ቤቶችና በአሥር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ላይ በወቅቱ ያልተወራረደ 4.2 ቢሊየን ብር መገኘቱ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ እንዲሁም 77 መሥሪያ ቤቶችና ሰባት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ደግሞ ደንብና መመርያን ሳይከተሉ ያላግባብ 145.6 ሚሊየን ብር ክፍያ መፈጸማቸውን፣ በቀረበው የኦዲት ሪፖርት ምክር ቤቱ አረጋግጧል፡፡

በሌላ በኩል የግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመርያን ሳይከተሉ ግዥ የፈጸሙ 100 መሥሪያ ቤቶችና ስምንት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መሆናቸውን፣ እነሱም 956.8 ሚሊዮን ብር በኦዲት ግኝት እንደተደረሰባቸው ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ አስረድተዋል፡፡

የ11 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች የግንባታ ፕሮጀክት ግዥ አስመልክቶ ደግሞ፣ ተቋማቱ ሥራ ለመጀመር የሚያስፈልጓቸውን ኮምፒዩተር፣ ጄኔሬተርና መሰል ቁሳቁሶችን ለመግዛት ቢታቀድም ምንም ዓይነት የዕቃ ግዥ ሳይፈጸም ከ67 እስከ 85 በመቶ ግዥ እንደተፈጸመ ተደርጎ የውሸት ሪፖርት የቀረበ መሆኑን ነው አቶ ገመቹ ለምክር ቤቱ የገለጹት፡፡

በዘንድሮው የዋና ኦዲተር ሪፖርት ለፓርላማ አባላቱ ከቀደሙት ዓመታት የተለየ ሪፖርት አልቀረበላቸውም፡፡ ነገር ግን ስሜታቸውን የቀሰቀሰውና ለቁጣ የዳረጋቸው በመጋቢት 2011 ዓ.ም. የፓርላማው አባላት (አፈ ጉባዔውን) ጨምሮ፣ ዋና ኦዲተር፣ ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በተገኙበት ከባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ጋር ተደርጎ በነበረው ውይይት የተላለፉ መመርያዎች አለመተግበራቸው ነበር፡፡ ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ያላግባብ ወጪ ያደረጓቸው በጠቅላላው ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በሁለት ወራት ውስጥ ተመላሽ እንዲያደርጉ የተላለፈላቸውን መመርያ ተግባራዊ አለማድረጋቸው ቁጣ ቀስቅሷል፡፡ እንደ ዋና ኦዲተሩ ገለጻ በመመርያው መሠረት ወጪያቸውን የመለሱት አምስት በመቶ የሚሆኑት ብቻ ሲሆኑ፣ እነሱም ከጠቅላላው ተመላሽ ገንዘብ ውስጥ 12.5 ሚሊዮን ብሩን የድርሻቸውን አስመልክተዋል፡፡ ሌሎቹ ተቋማት ግን በቀጣይ ዓመት ለማስመለስ ማቀዳቸውን የሚያሳይ የትግበራ ዕቅድ ሪፖርት ማድረጋቸውን አቶ ገመቹ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

ትናንት ያልታመነ ነገ እንዴት ይታመናል?

በየዓመቱ የኦዲት ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ ምክር ቤቱ በሚያደርጋቸው መደበኛ ስብሰባዎች ጨምሮ፣ በቋሚ ኮሚቴዎች አማካይነት ሥራ አስፈጻሚውን አካልና በሥሩ የሚገኙ ተቋማትን ሲጠይቅና የእርምት ዕርምጃ እንዲወስዱ ያሳስባል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሁሉንም የተቋማት ኃላፊዎችና አመራሮች በማነጋገር፣ የውሳኔ ሐሳብና የመፍትሔ ዕርምጃ እንዲወስዱም ያሳስባል፡፡ ሕግ እንዲከበርም መመርያ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን የፓርላማ አባላት ይህ ሁሉ የቁጥጥር ሥራና የውሳኔ ሐሳብ ብዙም ፍሬ እያፈራ አላገኙትም፡፡ ይልቁንም ‹እዚህ ቁጭ ብለን የማይሻሻለውን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ችግር በሪፖርት መልክ ማዳመጥም ሆነ፣ ያወጣነው ሕግ ሲከበር የማታይና የሕዝብ ሀብት በየዓመቱ በዘፈቀደ ሲባክን የምናይ ብቻ ከሆነ  የእኛ እዚህ መቀመጥ ምን ፋይዳ አለው?› እያስባላቸው ነው፡፡

ለዚህም ነው ባለፈው ሳምንት መደበኛ ስብሰባ ላይ ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶቹ በተሰጣቸው መመርያ መሠረት ተመላሽ እንዲያደርጉ የተነገራቸውን ከመፈጸም ይልቅ፣ የድርጊት መርሐ ግብራቸውን ማስገባታቸው የፓርላማ አባላትን ያስቆጣው፡፡

‹‹በየዓመቱ የማስተካከያ ዕርምጃ እንወስዳለን ሲሉ ይሰማሉ፡፡ ነገር ግን ከዓመት ዓመት ተመሳሳይ የሕግ ጥሰትና ብክነት ነው የሚታይባቸው፡፡ በመሆኑም ለሚቀጥለው ዓመት የድርጊት መርሐ ግብራቸውን ስለመፈጸማቸው በምን እርግጠኛ እንሆናለን?›› ሲሉ አንድ የምክር ቤቱ አባል ጠይቀዋል፡፡ እኚሁ አባል ለተቋማቱ በድጋሚ ጊዜ መስጠት እንደማያስፈልግ ገልጸው፣ በሕግ ይጠየቁ ብለዋል፡፡

አባላቱ ከዚህ በፊት በነበረው አሠራርና ልምድ ማሳሰቢያ ከመስጠት ይልቅ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በአስፈጻሚው አካል ሥር የሚገኙ የተቋማት አመራሮች ተጠርተው ችግሩን በተመለከተ ካልተጠየቁ የሚል ሐሳብ ነው ያቀረቡት፡፡

ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር የተባሉት የምክር ቤቱ አባል፣ ‹‹ዋና ኦዲተሩ ለዘጠኝ ዓመታት ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ እኔ ደግሞ ለስምንት ዓመታት የምክር ቤቱ አባል ሆኜ ሰምቼያቸዋለሁ፡፡ ነገር ግን በኦዲት ግኝቱ መሠረት ዕርምጃ ካልተወሰደና የሕግ የበላይነት ካልተረጋገጠ እስከ መቼ የሕዝብ ሀብት እየባከነ እናያለን?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በተመሳሳይ በርካታ አባላት በየዓመቱ የሚሰሙት የኦዲት ሪፖርት ተመሳሳይ ይዘት ማንፀባረቁንና ሕጋዊ ዕርምጃ ሲወስድ ባለማየታቸው፣ ‹የእኛ እዚህ ተቀምጦ ሕግ ማውጣታችንም ሆነ የሕዝብ ወኪልነታችን ምን ፋይዳ አለው?› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

‹‹በ2010 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ውጤት መሠረት የፌዴራል መሥሪያ ቤት ባለ በጀት መሥሪያ ቤቶች ባለፉት ዓመታት የታዩትን ግድፈቶች በማረምና የተዘረጋውን የመንግሥት የፋይናንስ፣ ግዥ፣ እንዲሁም የንብረት አስተዳደርና አጠቃቀም ሥርዓት ተከትለው በመሥራት ረገድ አሁንም አብዛኞቹ በሚጠበቀው ልክ ለውጥ እያሳዩ አይደለም፤›› በማለት የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት ይገልጻል፡፡ ‹ለነኚህ ግኝቶች ትኩረት ተገኝቷል ዕርምጃ ተወስዶ ሊስተካከሉና ሊታረሙ ይገባል፤›› ሲሉም ዋና ኦዲተሩ  አሳስበዋል፡፡

እንደ ዋና ኦዲተሩ ማብራሪያ ዝርዝር የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት ዝርዝር ሪፖርት አጠቃላይ በሁለት ዘገባ፣ በሁለት ጥራዝ፣ እንዲሁም የእያንዳንዱ ክዋኔ ኦዲት ዝርዝር ሪፖርት ደግሞ በ28 ጥራዝ፣ አስተያየት ሲሰጥባቸው የሚገቡ የ11 መሥሪያ ቤቶች ኦዲት ሪፖርቶች ለየብቻ ተዘጋጅተው ለአፈ ጉባዔ መላካቸውን ዋና ኦዲተሩ ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ሪፖርቶቹንም የምክር ቤቱ የመንግሥት የወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎችም በጥልቀት መርምረው፣ ተገቢ ዕርምጃ እንዲወስዱና ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ ዋና ኦዲተሩ በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡

በዘንድሮው ሪፖርት የዋና ኦዲተሩ የሒሳብ አያያዝ፣ ሕጋዊነት፣ የወጪና ገቢ አያያዝ፣ ሕግ የጣሰ ክፍያና ግዥ በበርካታ ተቋሞች ተሰተውሏል፡፡ ምንም እንኳን እንከን የተገኘባቸው ተቋማት በርካታ ቢሆኑም በዩኒቨርሲቲዎች የታየውን ለአብነት መመልከት ይቻላል፡፡

የቦታ ርክክብ ሳይደረግ ለ11 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ በሚል ለኮንትራክተሮች የተከፈለው ገንዘብ ቅደም ተከተሉን ያልያዘና አግባብነት የሌለው እንደነበር በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ የእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች ጉዳይም በድጋሚ በማግሥቱ በምክር ቤቱ የመንግሥት የወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጠራው ስብሰባም በድጋሚ ተነስቶ ነበር፡፡ በዚህ ውይይት ላይ ቋሚ ኮሚቴው የቀድሞ ትምህርት ሚኒስቴርና የአሁኑ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርን የ2009 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት አስመልክቶ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊዎች፣ የፌደራል ዋና ኦዲተር፣ እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስቴር የበላይ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው ነበር፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን የ2009 ዓ.ም. የኦዲት ግኝት አስመልክቶ ካነሳቸው ጥያቄዎች ለአብነት የቦታ ርክክብ ሳይደረግ ለ11 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ በሚል ለዘጠኝ ኮንትራክተሮች የተከፈለው 72,037,164.75 ብር ቅደም ተከተሉን ያልጠበቀና አግባብነት የሌለው ክፍያ መፈጸሙ፣ ያላግባብ በወጪ የተመዘገቡ ተሰብሳቢ ሒሳቦች ተመላሽ እንዲሆኑ ማድረግን፣ መመርያን ሳይከተል የተፈጸመ ግዥን በሚመለከት፣ እንዲሁም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ካለው የሥራ ስፋት አንፃር የተመደበለትን በጀት ከመሥሪያ ቤቱ ዕቅድና ክንውን ጋር በማጣጣም ባለመሥራቱ፣ ተመላሽ የሆነውን 274,540,750 ብር አስመልክቶ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የበላይ የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ተጠይቀዋል፡፡

የሥራ ኃላፊዎቹ በሰጡት ምላሽ የኮንትራክተሮችን ክፍያ አስመልክቶ የመንግሥትን መመርያ ተከትለው መፈጸማቸውን፣ ችግሩ የተፈጠረው መጀመርያ ስምምነት ማድረጋቸው ላይ መሆኑን፣ በመሆኑም ከዚህ ቀደም የነበሩትን የአሠራር ክፍተቶችና የነበሩ ስህተቶችን በማረም የተሻለ የአሠራር ሥርዓት ዘርግተው እየሠሩና ለውጥም እያዩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ምላሽ ተከትሎ የፌደራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ የተሰጠው ምላሽ አግባብነት የሌለውና ጉዳዩ ተደባብሶ ማለፍ የሌለበት እንደሆነ በማስታወስ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በበጀት ዓመቱ ካልተፈቀደለት የሚተካ በሚል የተጠቀመጠው ትክክል አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ መሥሪያ ቤቱ በመመርያውና በገባው ውል መሠረት ግዥ ባለመፈጸሙ በክትትልና በአሠራር ችግር ምክንያት በቅጣት 484,197.68 ብር መንግሥት ያላግባብ እንዲያወጣ ተደርጓል በማለት፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ትምህርት እንዲወስድና በቀጣይ መታረም እንዲችል ዕርምጃ ተወስዶ ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትና ለምክር ቤቱም ሊገለጽ ይገባል ሲሉ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ የመንግሥትን መመርያ ሳይከተል የተደረገ ግዥ አግባብነት የሌለው መሆኑን ጠቅሶ፣ ሰነዶች በወቅቱና በአግባቡ ሳይቀርቡ የተፈጸሙ ክፍያዎች ስህተት መሆናቸውን በማመላከት በቀጣይ የአሠራር ሥርዓት ሊዘረጋለት ይገባል ብሏል፡፡ ለ11 ዩኒቨርሲቲዎች ግንባታ የሚውል የቦታ ርክክብ ሳይፈጸም የተደረገው ቅድመ ክፍያ አግባብነት የሌለው መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ከፍተኛ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ያላግባብ እየባከነ በመሆኑ፣ ከፍተኛ የኦዲት ግኝት በታየባቸው መሥሪያ ቤቶች ላይ ተገቢነት ያለው ዕርምጃ ሳይወሰድ በየጊዜው ሪፖርት ብቻ እያዳመጡ መሄድ የመፍትሔ አካል እንደማይሆን አስታውቋል፡፡ ለዚህም ይመስላል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ  አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው፣ ከፍተኛ የኦዲት ግኝት የታየባቸው የመንግሥት ተቋማት ተጠያቂ እንደሚሆኑና መንግሥት አስፈላጊውን ዕርምጃ እንደሚወስድ አስረድተዋል፡፡

‹‹ምክር ቤቱ በምንም ምክንያት በዚህ መንገድ ተመሳሳይ ሪፖርት እየዳመጠ ሊሄድ አይገባም፡፡ ሁላችሁም (የምክር ቤቱ አባላቱን) እንዳነሳችሁትት የዚህ ዓይነት የፋይናንስ ብክነትና ሕግ የጣሰ የበጀት አጠቃቀም እዚህ ላይ መቆም ስላለበት፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በአስቸኳይ በሕጋዊ መንገድ የተጠያቂነት ዕርምጃ መውሰድ አለበት፤›› ሲሉ አፈ ጉባዔው አሳስበዋል፡፡

ከፓርላማው ውጪ ሌላ ማን ይጩህ?

በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠውና ለፓርማው በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት ፓርላማው ሕገ ያወጣል፣ ያወጣውን ሕግ በአስፈጻሚው በኩል መተግበሩንና አለመተግበሩን የመከታተል ኃላፊነት አለበት፡፡ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥትን በጀት ማፅደቅ ለፓርላማው ከተሰጡት ኃላፊነቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ይኼንኑ ፓርላማው ያፀደቀውን የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች በጀት ተግባራዊነትና ክንዋኔ የቀኝ እጁ በሆነው የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አማካይነት ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ የበጀት አጠቃቀምና የሥራ ክንዋኔዎች ግድፈት ሲገኝ እንዲታረም ከማድረግ ባሻገር ዕርምጃ እንዲወሰድ ያደርጋል፡፡ ይህ ዓይነቱ የፓርላማው ሥልጣንና ኃላፊነት ለሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች የሚያወጣቸው ጉዳዮች አፈጻጸማቸውን በተመለከተ ተመሳሳይ ሚና አለው፡፡ ለአብነትም በሰብዓዊ መብት ጥበቃና አከባበር፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና የሕግ አከባበር ጉዳዮች ተመሳሳይ ሚናዎች እንዳሉት ይታወቃል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ተግባር ከሕግ አውጪ ሚናና ከአስፈጻሚው አካል የሕግ አስከባሪነት ባሻገር፣ የመንግሥትን ሀብት የመቆጣጠር ሚዛናዊነት ማረጋገጥን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

ይሁን እንጂ በመንግሥት በኩል ለሚኖረው የሕግ አስከባሪነት ሚና ሕግ አውጪው በዋነኝነት ቢጠቀስም፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሚዲያዎች የራሳቸውን ሚና እንዳላቸው ይታመናል፡፡ ይህንንም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነውም ቢሆን መንግሥትን በመከታተል የቁጥጥር አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡

በዓለም ዙሪያ በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች የሚሠሩ በርካታ የሲቪል ማኅበረሰቦች ይገኛሉ፡፡ እንደ መብት አቀንቃኝነት ሁሉ በአካባቢ ጉዳዮች፣ በፍትሕ ዘርፍ፣ እንዲሁም በተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች በመንግሥት በኩል የሰብዓዊ ወይም የሌሎችን ጉዳዮችን በተመለከተ የሕግ ጥሰት ሲኖር ይሟገታሉ፡፡ ለሕጋዊ መብቶች፣ ፍላጎቶች ጥቅሞች ይከራከራሉ፡፡ ሚዲያዎችም መንግሥት በመከታተል እንዲሁ የራሳቸውን የቁጥጥር ሚና ያከናውናሉ፡፡ የተለያዩ የሙያ ማኅበራትም በመደራጀትና እንደ ዘርፋቸው የራሳቸውን ሚና ሲያደርጉ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ አገሮች እንደሚታየው በሀብትና በአስተዳዳር ረገድ፣ በተለይም ከኦዲት ጋር በቀጥታ በተዛመደ የሲቪል ማኅበረሰብም ሆኑ የሙያ ማኅበራት የኢትዮጵያን መንግሥት ሲቆጣጠሩ አይታይም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ጋሬጣ ለዓመታት መንግሥት ምኅዳሩን በመዘጋጋት ተጠያቂነትን በማጥፋቱ እንደሆነ ይተቻል፡፡

አንዳንድ ባለሙያዎች የኦዲትና የፋይናንስ አጠቃቀምን በሕግ አውጪው ብቻ መቆጣጠር አዳጋች እንደሆነ በመግለጽ፣ የሲቪል ማኅበረሰቦችና አቀንቃኞች ሊኖሩ ይገባል ይላሉ፡፡ ምንም እንኳ ከሙስናና ከመልካም አስተዳደር ጋር በተገናኘ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች እንዳሉ ቢታወቅም፣ ከመንግሥት ሒሳብ አያያዝና በጀት አጠቃቀም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት፣ ያላቸው አንዳችም የሉም፡፡ በዚህ ረገድ ፓርላማውን በቁጥጥር ሥራ የሚደግፈው አጋዥ እንደሌለ ለማየት ይቻላል፡፡

የጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈተና

የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ጉዳይ በሚከታተሉ ባለሙያዎች አካባቢ በመላ አገሪቱ የተንሰራፋውን ብክነት በተመለከተ፣ በኢሕአዴግ አስተዳዳር ሙስናን ለመዋጋት እውነተኛ ቁርጠኝነት ቢኖር አደጋው ለገዥው ፓርቲ ለራሱ እንደሆነ ሲገልጹ ይሰማል፡፡ ይህ ደግሞ የሙስና ኔትወርኩ ወይም ትስስሩ በዋነኝነት በከፍተኛ አመራሩ ዘንድ ምን ያህል እንደሆነ ለማሳየት ነው፡፡ ለዚህም ይሆናል በተለይ ፓርላማው ቁጥጥር እያደረገ ነው ቢባልም ውጤት አልባ አድርጎ ያስቀረው ሲሉም ያክላሉ፡፡

ከሙስና ጋርም ሆነ ከኦዲት ግድፈቶች ጋር በተያያዘ ፓርላማው የሚያስተላልፈው ውሳኔ በመንግሥት በኩል ዕርምጃ አለመውሰድ ሁልጊዜም በመንግሥት ላይ የተዓማኒነትና የተጠያቂነት ጉዳይ ጥያቄ የሚነሳበት፣ የመንግሥትን ሕግ የማስከበርና የሕግ ተገዥነት ካለፉት ዓመት በጠነከረ ሁኔታ ከዚህ ዓመት በኋላ በድጋሚ የሚነሳ ዋና ጉዳይ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡

በዚህ ጉዳይ ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬም ሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከማንም በላይ የሚፈተኑበት እንደሚሆን ይነገራል፡፡

ምንም እንኳ ባለፈው ሳምንት የቀረበው የዋና ኦዲተሩ ሪፖርት የ2010 በጀት ዓመት ቢሆንምና ከዓመቱ የተወሰነውን ጊዜ ዶ/ር ዓብይ ያስተዳደሩበት ቢሆንም፣ በቀጣይ ግን ሪፖርቱን ተንተርሰው የሚወሰዱት ዕርምጃዎች ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ ዋና ዓቃቤ ሕጉ የሚመዘኑበት መሆኑ አይቀርም የሚሉ አሉ፡፡

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወደ ሥልጣን በመጡበት ጊዜም ሆነ በዚህ ዓመት በምክር ቤቱ አዳዲስ ካቢኔያቸውን ባሾሙባቸው ጊዜያት፣ ሙስናን መዋጋትና የመንግሥትንና የሕዝብን ሀብት አጠቃቀም ሕጋዊነት ማስተካከል ከቀዳሚ አጀንዳዎቻቸው ውስጥ መሆናቸው አመላክተው ነበር፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉንም በተመለከተ በተመሳሳይ ትልቅ ኃላፊነት እንደሚጠበቅባቸው እየተነገረ ነው፡፡

ባለፈው መጋቢት ወር መድረክም ቢሆን ከኦዲት ጋር በተገናኘ ችግር ያለባቸው ተቋማትም ሆነ አመራሮች በአስቸኳይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲጀምሩ ስምምነት ላይ መደረሱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ባለፈው የምክር ቤቱ ስብሰባዎች ከዋና ኦዲተሩ ሪፖርት በኋላ በምክር ቤቱ አባላቱም ሆነ በአፈ ጉባዔው አቶ ታገሰ ጫፎ ዕርምጃ በመውሰድ ረገድ፣ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉም ሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠንከር ያለ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

ፓርላማው የመጨረሻ ዕርምጃውን ይጠቀም ይሆን?

በቀጣይ ከሚጠበቁ ጉዳዮች አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦዲትና በሕዝብ ሀብት አጠቃቀም የገቡትን ቃል ስለማስከበራቸው ለጊዜው ምንም ማለት ባይቻልም፣ በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አማካይነት የመንግሥት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ በቅርቡ የታዩ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል፡፡ ለዚህም ባለፉት 14 ወራት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ከተለያዩ ግለሰቦች በመመሳጠር የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በተባሉ ተጠርጣሪ አመራሮች ላይ የእስር ዕርምጃ ወስደዋል፡፡ ጉዳያቸውም በፍርድ ቤት የተያዘ ሲሆን፣ ተመሳሳይ ዕርምጃ እንደሚቀጥል ከዚህ በፊት ለሕዝብ ፍንጭ ተሰጥቷል፡፡ ከኦዲት ግኝት ጋር በተያያዘና ከፓርላማው ማሳሰቢያ ጋር በተገናኘም መንግሥት የሚወስደው ዕርምጃ በሒደት የሚታይ ይሆናል፡፡

ነገር ግን በመንግሥት በኩል እንደ ቀደሙት ዓመታት በቸልተኝነት ቢቀጥልስ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ይህ ደግሞ በፓርላማ አባላትም ጭምር እየተነሳ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት በሚወስደው ዕርምጃ፣ ቀድሞውንም የተዓማኒነት ጥያቄ የሚቀርብበትን የኢሕአዴግ አስተዳደር በሕዝብ ተዓማኒነት መልሶ እንዲያገኝ ይረዳዋል? ወይስ በዚያው ይቀጥላል? የሚለውም በቀጣይ ይታያል፡፡

በሌላ በኩል የፓርላማው የቁጥጥር ሥልጣን እስከ ምን ይደርሳል የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ነገር ግን በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ፓርላማው ከዚህ በላይ ሊሄድ ይችላል፡፡ ይኸውም ሥልጣን ሕግ አውጪው ከአስፈጻሚው ላይ ሊወስደው የሚችለው የመጨረሻ ኃይል ነው፡፡ እሱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የመተማመኛ ድምፅ እንዲሰጥ ማድረግና በአባላቱ ድምፅ በሥልጣን እንዲቆይም ሆነ እንዲወገድ ማድረግ ነው፡፡ የዚህ የመተማመኛ ድምፅን በተመለከተ በአፈ ጉባዔውም ሆነ በአባላት ጥያቄ መሠረት በ1/3 ድምፅ ሊከናወን ይችላል፡፡

ምንም እንኳን አሁን ባለው አስተዳደር ፓርላማው እዚህ ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል የሚያሳይ ፍንጭ ባይኖርም፣ ሕግ ማስከበር አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ ያን ያህል ርቀት መሄድ እንደሚቻል የአገሪቱ ሕግ ያስቀምጣል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -