ኖኅ ሪል ስቴት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ለገሐር አካባቢ ባለ 36 ወለል ለቢሮ ተቋማት የሚሆን ሕንፃ ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ይህ የተገለጸው በተለምዶ ፊጋ እየተባለ በሚጠራውና ሰሚት አካባቢ በሚገኘው መንደር ‹‹ኖኅ ጋርደን የመኖሪያ አፓርትመንቶች›› እሑድ ግንቦት 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ለቤት ገዥዎች በተላለፉት ወቅት ነው፡፡
የኖኅ ሪል ስቴት ኩባንያ አስተዳደር አባል አቶ ዓብይ ኃይለ ማርያም እንደገለጹት፣ በቢሮ አገልግሎት ለሚሰጡ ተቋማት የሚውል ሕንፃ ለገሐር አካባቢ የሚገነባ ሲሆን 2,800 ካሬ ሜትር ላይ አርፏል፡፡ በአጠቃላይ፣ ሕንፃውን ለመንባትም 1.5 ቢሊዮን ብር እንደሚጠይቅ አቶ ዓብይ ገልጸዋል፡፡
የሕንፃው ግንባታ ከተጀመረ አንድ ወር ሲሆነው፣ አዲስ አበባ ላይ በተፈጠሩት ድርጅቶች እንዲሁም የባቡር መንገድ ከግምት በመክተት የተጀመረ ፕሮጀክት እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በተያያዘም የኖኅ ሪል ስቴት ኩባንያ የመሬት አቅርቦት ከየት እንደሆነ ከጋዜጠኞች ለቀረበው ጥያቄ ‹‹በከተማው የመሬት አቅርቦት እኛ በምንፈልገው መጠን የለም፡፡ ስለዚህ በአብዛኛው መሬት ከግለሰብ፣ ከጅርጅቶች እንዲሁም ከነባር ባለይዞታዎች ብዙ ገንዘብ ከፍለን ነው የምንገዛው፤›› በማለት በመንግሥት በኩል ሪል ስቴት መሬት አቅርቦት እንደሌለ በመግለጽ፣ ‹‹ይሁን እንጂ የሊዝ በተሻለ መንገድና በተሻለ ዋጋ የሚቀርብበት ሁኔታ ካለ መገንባት እንችላለን፡፡ የምንሸጥበትንም ዋጋ ቀንሰን ተጠቃሚ ማብዛት እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡
እሑድ ግንቦት 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ያስረከባቸው ቤቶች የተጨማሪ እሴት ታክስና ሊዝን ጨምሮ ከ1.1 ሚሊዮን እስከ 2.5 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ለቤት ባለቤቶች አስረክቧል፡፡